ጎቲም ሲሞንን በወፍ በረር

Wednesday, 20 April 2016 13:16

 

በይርጋ አበበ

ርዕስ              ጎቲም ሲሞን

ደራሲ              ያየሰው ሽመልስ

አሳታሚና አከፋፋይ ክብሩ መጽሀፍት መደብር

ይዘት              ፖለቲካና ስለላ ተኮር ወጥ ልቦለድ

የገጽ ብዛት         257

ዋጋ               60 ብር ከ90 ሳንቲም

በቅርቡ በአንድ እድሜ ጠገብና ወርደ ሰፊ መንግስታዊ ጋዜጣ ላይ አንድ ጽሁፍ አነበብኩ። ይህ መንግስታዊ ጋዜጣ (አዲስ ዘመን) “ህይወት እንዲህ ናት” በሚለው አምዱ ስር ወዳጄ ጥበቡ በለጠን እንግዳ አድርጎ ያቀረበበትን አርቲክል ነበር ያነበብኩት። የንባብ አምባሳደር የሆነው ወዳጄ ጥበቡ በለጠ “ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል” የሚለውን ዓለም አቀፍ እና ምሉዕ ኃይለ አባባል ሲያስረዳ ተመለከትኩ። የንባብ አምባሳደሩ አያይዞም ወጣቶች በንባብ ላይ ያላቸውን ለዘብተኝነት (ከማንበብ መሸሽ እለዋለሁ) አንስቶ ይተነትንና በአናቱም የጸሀፊያንን የጥበብ ስራ ከገበያ እየራቀ መሆኑን ሲናገር ተመለከትኩ።

ከላይ የጠቀስኩትን የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ሰፋ ያለ አርቲክል ባነበብኩ በሳምንቱ አንድ መጽሃፍ እጄ ላይ ገባ “ጎቲም ሲሞን” የሚል። ከይስማከ በስተቀር ከዴርቶጋዳ ውጭ ወጣት ጸሀፊ ያለ የማይመስለው ትውልድ እየተባለ በሚተችበት በዚህ ዘመን የጎቲም ሲሞን ደራሲ ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ ታሪካዊ ፖለቲካዊና ስለላን ማዕከል ያደረገ ወጥ ልብወለድ መጽሀፉን ለንባብ አበቃ። ይህ ወጣት ጋዜጠኛ በዚህ ወቅት በርካታ ገበያ ተኮርና ገበያ የሚፈልጋቸው ጸሀፊያን ስራዎቻቸውን ለህትመት ባበቁበት ወቅት መጽሀፉን ለገበያ ማቅረቡ የልጁን ድፍረት እንድገረምበት አድርጎኛል። ምክንያቱም እንደ ኮሎኔል ፍሰሃ ደስታ፣ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያም እና በዕውቀቱ ስዩም በቅርቡ ያሳተሟቸው መጽሃፍት የአንባቢውን ቀልብ እና ትኩረት ወጥረው በያዙበት ወቅት ያየሰው መጽሀፉን በማሳተሙ ነበር የተገረምኩት።

በእርግጥ በዚህ ዘመን ከያየሰው ሽመልስ በተጨማሪ ሌሎች በርካታ ወጣቶችም ከመጽሀፍ ስራዎቻቸው ጋር ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል። ለአብነት ያህል የሰንደቅ ጋዜጣው ጸጋው መላኩ “ሁለቱ ኢትዮጵያዎች” የሚል በጥንታዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ላይ የሚያተኩር መጽሀፉን ለንባብ ያበቃው በያዝነው ዓመት ነው። ሌሎች ጸሀፊያንም በዚህ ዓመት የመጀመሪያ ስራዎቻቸውን ያቀረቡበት ዓመት ነው ማለት ይቻላል። 

ለዛሬ በዚህ ዓምድ ልንመለከተው የወደድኩት በርዕሱ የገለጽኩትን የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋዜጠኛ የሆነው ያየሰው ሽመልስ ያሳተመውን ጎቲም ሲሞንን ወይም ዱልዱም ምላጭ መፅሐፍን ነው።

 

 

ጎቲም ሲሞን እንደ መጽሃፍ

ጎቲም ሲሞን ይዘቱን በምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ላይ ያደረገ ሲሆን መቼቱንም በ1980ዎቹ አጋማሽ ላይ ያደረገ ወጥ ልቦለድ መጽሃፍ ነው። ሰላም እንደ ሰማይ የራቀው፣ ብልጽግና እንደ ጠፈር ሳይንስ ብርቁ የሆነው፣ ርሃብ፣ ጦርነትና ድህነት ብቸኛ መገለጫዎቹ የሆኑት የምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካ የጎቲም ሲሞን መጽሀፍ ማጠንጠኛ ነው። በዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት በጦር ወንጀለኝነት ቢከሰሱም ከካርቱም አዲስ አበባ የሚመላለሱት ፊልድ ማርሻል ኡመር ሀሰን አልበሽር በፕሬዚዳንትነት የሚመሩትም ሆነ ከጦርነቱ በፊት ከሻዕቢያ ተፅዕኖ እንዳልተላቀቀ የሚነገርላት የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ጠብቀረሽ በዳቦ የሚባሉት ኢሳያስ አፈወርቂ የሚመሩት የኤርትራ መሬት ለጎቲም ሲሞን መጽሀፍ አስኳል እና መጠንጠኛ ሀሳብ ነው።

ለውጥ ማምጣት ባይችሉም በየዓመቱ አዲስ አበባ የሚሰባሰቡት የአፍሪካ አምባገነን ገዥዎች እንደተለመደው በአንዱ ዓመትም አዲስ አበባ ላይ ተገናኝተው ሊዶልቱ ሲሉ (ሊነጋገሩ እንዳልል ግብራቸው ስለማይገልጸው ነው) አረብ ቅጥረኛ ግብጻዊያን በመሪያቸው ሆስኒ ሙባረክ ላይ የግድያ ሙከራ ያደርጋሉ። ይህ የግድያ ሙከራ የአፍሪካ ገዥዎችን ለጭንቀትና ነግ በኔም ነው እንዲሉ ሲያስገድዳቸው የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንን ደግሞ የወሬ ጮማ አሸክሟቸው ነበር ያለፈው። በዚህ የግድያ ሙከራ የማቀነባበሩንና ትጥቅና ስንቅ የማቀበሉን ስራ የሰራቸው “ሱዳን” እንደሆነች ግብጽ ምላ ስትገዘት፣ ሱዳን በበኩሏ “ቤትሽን እየከፈትሽ ጅብን በደለኛ አትበይ። ጠላትሽን እዚያው ከጉያሽ ፈልጊ” ብላ የአጸፋ መልስ መስጠቷን የጎቲም ሲሞን ደራሲው ያየሰው ሽመልስ ይገልጽልናል። በዚህ መሃል ግን ለሆስኒ ሙባረክ የግድያ ሙከራ እንኳን ሊጠረጠር ቢታሰብ እንኳ ሃሳቡን ያሰበውን ‘እብድ’ ሊያስብል የሚችል አንድ ምስራቅ አፍሪካዊ መሪ እንደሆኑ ያየሰው ሽመልስ በታሪካዊ ልቦለዱ ምሎ ተገዝቶ እየነገረን ነው።

ጎቲም ሲሞን በገጽ ስምንት “…. እነዚህን መኪኖች በተኩስ እያጣደፉ ያሉት አራቱ ታጣቂዎችም ከአውቶሞቢሎቹ በአንዱ ውስጥ የሚፈለገው ዒላማ እንዳለ እርግጠኛ ሆነዋል። ኢላማው ለመኖሩ ደግሞ ከነበራቸው የመረጃ ሰንሰለት ባሻገር ከአውቶሞቢሎቹ መስታወት ግራና ቀኝ የተሰቀሉት ትናንሽ የግብጽ ሰንደቅ ዓላማዎች በቂ ምልክት ናቸው” ይላል። በአራት ታጣቂዎች የተኩስ እሩምታ የወረደባቸው ሆስኒ ሙባረክ ግን ምስጋና ለኢትዮጵያዊያን አጃቢዎቻቸው መስዋትነት እና ጥይት ለማይመታው አውቶሞቢላቸው ይግባና ከሞት ለጥቂት ተርፈዋል። ነገር ግን ሙባረክ ከሞት ቢተርፉም ተኩሱ ጥሎባቸው የሄደው ድንጋጤ ምን እንዳስመሰላቸው ጎቲም ሲሞን ላይ እንዲህ ይነበባል።

“ደንግጠዋል ቃል አይተነፍሱም። በትር እንደሳተው እባብ ‘እጥፍጥፍ’ ብለው ለተመለከታቸው የ75 ሚሊዮን ህዝብ መሪ መሆናቸውን ይጠራጠራል” ይላል። (ሆስኒ ሙባረክ አዲስ አበባ ላይ የግድያ ሙከራ ሲደረግባቸው የግብጽ ህዝብ ብዛት 75 ሚሊዮን ብቻ ነበር። በዚያ ወቅት የኢትዮጵያ ህዝብ 45 ሚሊዮን እንደነበር ልብ ይሏል)

ሆስኒ ሙባረክ አዲስ አበባ ላይ ለጥቂት ከመሞት መትረፋቸውን እንዳረጋገጡ በቀጥታ ወደመጡበት ካይሮ መመለሳቸውንና ካይሮ እንደገቡም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫቸው “ሱዳን ልታስገድለኝ ስትል አላህ አተረፈኝ። ሱዳን ግን የእጅሽን እንደምታገኝ አሳይሻለሁ” የሚል መግለጫ እንደሰጡ ደራሲው ይናገራል። ሱዳን በበኩሏ “ባልንጀራው ቢመታው ወደ ሚስቱ ሮጠ አሉ አበው። እዚያው ጠላትህን ፈልግ” ብላ ለግብጽ ክስ መልስ መስጠቷን የሚዘግበው ጎቲም ሲሞን ግብጽ ለምን ሱዳንን እንደጠረጠረች መጽሀፉ ላይ በቂ ማስረጃውን አቅርቧል።

የጥቃቱ ሰለባ ግብጽን ጨምሮ ኢራን እስራኤልና ሌሎች አገሮች ለሙባረክ የግድያ ሙከራ ከሱዳን በስተቀር ማንም አይሆንም ብለው ምለው በሚገዘቱበትና የአፍሪካ አገራት ገዥዎች በድርጊቱ ተሸማቅቀው በተቀመጡበት ሰዓት ግን አንድ አፍሪካዊ መሪ በሙባረክ አለመሞት አንጀታቸው እርር ድብን ሲል ጎቲም ሲሞን ያሳየናል። መሪው ማናቸው? ለምን እርር ድብን አሉ ለሚለው ጥያቄ መጽሀፉ መልስ ይሰጣል።

ከዚህ በተረፈ ደግሞ የኤርትራ መሪዎች ሻዕቢያዊያን እንደዛሬው ከቀድሞ ወዳጃቸው ህወሓት ጋር አይንና ናጫ ከመሆናቸው በፊት በኢትዮጵያ ህዝብ እና መሬት ላይ ያደርሱ የነበረውን ግፍና መከራ ይሄው ጎቲም ሲሞን ይተርካል። ኤርትራዊያኑ በኢትዮጵያ ላይ ሳይኮሎጂካልና ሁሉን አቀፍ ጉዳት እያደረሱ ባለበት ሰዓት ግን ህወሓት መራሹ የኢትዮጵያ መንግስት የእኛ ብቸኛ ጠላት ኦነግ እንጂ ማንም አይደለም ብሎ የኦሮሞ ነጻ አውጭ ግንባር (ኦነግ) ባልዋለበት ሲውል ባልሰራው ሲከሰስ መጽሃፉ ያስዳስሰናል።

ኢህአዴግ አገሪቱን መግዛት እንደጀመረ በርካታ ኤርትራዊያንና ትውልደ ኤርትራዊያን ታጋዮች በአቶ መለስ ዜናዊና በአቶ ታምራት ላይኔ ፊርማ በበርካታ የፌዴራል እና የክልል የመንግስት ኃላፊነት ቦታዎች ላይ መቀመጣቸውን የሚገልጸው ጎቲም ሲሞን ከዚህ ውስጥ በቀድሞው የፕሬስ መምሪያ (የአሁኑ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት) ኃላፊ የነበረውን ተስፋዬ ገብረዓብን በስም ሳይሆን በግብርና በገላጭ ቋንቋ ይጠቅሰዋል።

ሻዕቢያዎች በኢትዮጵያ መሬት ላይ ቆመው የራሳቸውን የስለላ ቡድን አቋቁመው አገሪቱን እና ህዝቧን ከመሰለልና ታላላቅ ባላስልጣናቱን እስከ መግደል የደረሰ እንቅስቃሴ ያደርጉ እንደነበርና ያን እንቅስቃሴም “በሊህ ላማ ወይም ስለታም ምላጭ” ብለው ሰይመውት እንደነበረም ጎቲም ሲሞን ይናገራል።

ይህ ሁሉ በሚሆንበት የጸሀፊው ድንቅ የጽሁፍ ችሎታ ላይ ግን ደራሲው ሆስኒ ሙባረክን ለመግደል ሙከራ ያደረጉትን ቅጥረኛ ግብጻዊያንን ማን እንደላካቸው በመጽሀፉ የመጀመሪያ ክፍል ላይ ማስቀመጡ ተገቢ ሆኖ አላገኘሁትም። በርካታ የቀድሞ ምሁራን የሚጠቀሙባቸውን ቃላት በጽሁፉ ላይ የሚጠቀመው ያየሰው ሽመልስ በተለይ አህጉራችንን “አፍሪካ” ብሎ ከመጥራት ይልቅ “አፍሪቃ” እያለ መጥራቱ “ቃ” የምትለዋን ፊደል ከየትኛው የውጭ ቋንቋ ላይ ተጽፎ እንዳገኘ እሱ ይወቅለት።

 

 

ጎቲም ሲሞን ከቋንቋና ስነ ጽሁፍ አንጻር

ደራሲ ያየሰው ሽመልስ በጎቲም ሲሞን ሲመጣ መረጃ ነግሮ ማለፍ ብቻ ሳይሆን የስነ ጽሁፍ ችሎታውንም ለማሳየት አቅም ያለው መሆኑን አስመስክሯል ማለት ይቻላል። የደራሲው የአጻጻፍ ስልት (ስታይል) በተለምዶ ይስማከ ወርቁ ይጠቀምበታል የሚባለው አይነት ሲሆን መጽሃፉ በማውጫ አልታጀበም። ያም ሆኖ ግን የመጽሃፉ ምዕራፎች በአጫጭር ገጾች የተወሰኑ በመሆኑ እና የተጠቀመው አማርኛ የከባድ ቀላል (ከባድ ቃላትን በቀላል አገላለጽ) በመሆኑ አንባቢን አይጎረብጥም።

ከቋንቋ እና ስነ ጽሁፍ አኳያ የደራሲው ድክመት ሆኖ ያገኘሁት ዲቃላ ፊደላትን የተጠቀመበት መንገድ ነው። ለአብነት ያህልም የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር አባት ሆነው የቀረቡትን ገጸ ባህሪ የኑሮ ደረጃ እና የቤተሰባቸውን ታሪክ በቃኘበት አንቀጹ “በተለይ በሕወሓት የትጥቅ ትግል ዘመን የቤተሰቡ አኗኗር ተጎሳቁሎ ነበር። ተስፋ የተጣለበት አምስተኛ ልጃቸውም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ትምህርቱን ትቶ ለበረሃ ትግል ወረደ። የልጆቻቸው ቁጥርና የቤተሰባቸው ገቢ ሊመጣጠን አልቻለም። ቢሆንም ከአድዋ መቐለና አክሱም እየተመላለሱ በአህያ እየነገዱ ኑሮን ተጋፈጡ። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የህክምና ትምህርቱን ትቶ ወደ በርሃ ወጥቶ የነበረው ልጃቸውም ከ17 ዓመታት ጦርነት በኋላ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነ። የልጃቸው የአገሪቱ ቁጥር አንድ ባለስልጣን መሆን ግን እሳቸውን ከንግድ ስራቸው የሚያሳርፋቸው አልሆነም። ይልቁንም ከአህያ ወደ መኪና ተሸጋግረው ከቸርቻሪነት ተነስተው አከፋፋይ ሆኑ” ይላል በመጽሃፉ ገጽ 149 ላይ።

ጎቲም ሲሞን ከቋንቋ እና ሰነ ጽሁፍ ልኬታው በተጨማሪ በታሪክ አወቃቀሩም ግጥም ሆኗል። መጽሃፉ ላይ የሰፈሩት ታሪኮች በሚገባ የተዋቀሩ ከመሆናቸውም በላይ ድፍረትን የተላበሰ ትንታኔም የታየበት ነበር።

 

ፖለቲካ በጎቲም ሲሞን

መጽሃፉ በምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ላይ ትኩረቱን እንደማድረጉ በተለይ በኢትዮ ኤርትራ ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያለ ትንታኔ ለመስጠት ሞክሯል። በመጽሃፉ ገጽ 20 ላይ የኤርትራው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆኖ የቀረበው ሰው ከቢሮው በአንደኛው መስኮት ሆኖ አስመራን ሲመለከት ያስቃኘናል። ሚኒስትሩ “ከሲኒማ አምፒር ተነስቶ ቀጥ ብሎ ሲያስተውል የፈንቅል ጎዳና ዓይኑ ገባ። ፈንቅል በሻዕቢያ የትግል ዘመን ውስጥ ዝነኛና ክብር የሚሰጠው ዘመቻ ነው። ደርግንና ምጽዋን የለያየ ዘመቻ። የኢትዮጵያ መተንፈሻ የነበረውን የምጽዋን ወደብ ከወንበዴ እየጠበቀ የነበረው የ606ኛ ኮር የካቲት 1982 ሲደመሰስ ሻዕቢያ ዘመቻውን ፈንቅል ብሎ ነበር የሰየመው። የፈንቅል ዘመቻም የምጽዋን ወደብ ከደርግ ወደ ሻዕቢያ ያዘዋወረ ሆነ። አብዮታዊ ሰራዊትም ስትራቴጂካዊ ቦታውን አጣ። ሻዕቢያም በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ጄኔራል መኮንኖችን ማረከ። ይህንን ስኬታማ ዘመቻ ለመዘከር ነው በአስመራ መሃል ለመሃል የሚሄደውን መንገድ ሻዕቢያዊያን ፈንቅል ጎዳና ሲሉ የሰየሙት” ሲል ይገልጻል።

በዚህ አንድ አንቀጽ ውስጥ የምንመለከታቸው አንደኛ የኢትዮጵያ መተንፈሻ የተባለው ምጽዋ በሻዕቢያ እጅ መውደቁ ሻዕቢያም ከተራ ሽፍታነት ጄኔራል መማረክ የቻለበት ዘመን መሆኑን እንዲሁም ሻዕቢያዎች ታሪክን አፍርሰው የራሳቸውን ታሪክ ለመጻፍ ያደረጉትን ችኮላ የተሞላበት የጎዳና ስያሜ ላይ እንመለከታለን።

ሌላው በጎቲም ሲሞን የተጠቀሰው ፖለቲካ የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬስ መምሪያ ኃላፊ ሆኖ የተሳለው ገጸ ባህሪ “እኔን ጨምሮ 16 ትውልደ ኤርትራዊያን በኢትዮጵያ መንግስት ኃላፊነት ላይ ተቀምጠናል” ብሎ የተናገረበት ክፍል ነው። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በተለያዩ ጊዜያት ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ ሊገቡ ሲሉ በሚያዙና በሚከፈተው መጠነኛ የተኩስ ልውውጥ የሚሞቱ ሰዎችን “የኦነግ አባላት” በሚል ኦነግን ባልዋለበት የሚያውለው ክፍል ነው። ህወሓት በተለይ ሻዕቢያን ከመወንጀል ይልቅ ኦነግን መወንጀል የመረጠበትን ምክንያት ደራሲው ያስቀመጠው የወቅቱ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ያራምዱ የነበረውን አቋም በማንሳት ነው። በአንድ ወቅት በኢህአዴግ ባለስልጣናት መካከል ኤርትራን በተመለከተ በተነሳ ክርክር አንድ ባለስልጣን “በ1972 ዓ.ም የተፈጸመብንን ክህደት ሁላችሁም ታስታውሱታላችሁ ብዬ አስባለሁ። የህወሃትን ጦር ለማስታጠቅና ቃል ገብቶ በሺህ የሚቆጠሩ ምልምሎችን ወሰደ። ይሁንና በጀብሃ መውጣት ምክንያት የተፈጠረበትን ክፍተት መሙያ አድርጓቸው ቀረ። በራሱ ወታደራዊ ፖለቲካ እዝ ስር አደረጋቸው። ከስንት ጭንቀትና ድካም በኋላ ነበር የለቀቃቸው” ብሎ መናገሩን በገጽ 37 ላይ ይገልጻል።

የኢህአዴጉ ባለስልጣን ከላይ የተጠቀሰውን ሃሳብ አቅርቦ ቢከራከርም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን “ከሻዕቢያ ጋር ተያይዞ የተነሳው ሃሳብ ትንሽ ማብራሪያ ያስፈልገዋል። በእርግጥ ሻዕቢያ ከማንም በላይ በእኛ ላይ ክህደት ፈጽሟል። ግን ያኔ ለህግና ለዓለም አቀፍ መርሆች የማይገዛ ታጣቂ ቡድን በመሆኑ የፈጸመው ነው። በወቅቱ በሁለታችን መካከል የሚኖረውን ግንኙነት የሚደነግግ ሰነድ አልነበረም። ያኔ በሺህ የሚቆጠር ታጋይ የምንመራ ድርጅቶች ነበርን። አሁን ግን አገር ነው  የምናስተዳድረው። ከእነዚህ ነጥቦች ባሻገር ሻዕቢያ ለእኛ የፀጥታ ስጋት የሚሆንበት ቁመና ላይ አይደለም። ካላበዱ በቀር ለእኛ የደህንነት ችግር አይሆኑም” ብለው ሲሞግቱት በመጽሃፉ ገጽ 39 ላይ እናገኛለን።

 

 

የጎቲም ሲሞን ድክመቶች

ጎቲም ሲሞን ማለት የትግርኛ እና እብራይስጥ ሲሆን ትርጓሜውም “ዱልዱም ምላጭ” እንደሆነ ደራሲው ይናገራል። ይህ መጽሃፍ ከላይ የተጠቀሱት ጠንካራ ጎኖቹ እንዳሉ ሆነው ሌሎች ያልተፈተሹ ክፍሎቹን ስንመለከት ደግሞ መጽሃፉ የተሰጠው ዋጋ ተገቢ ሆኖ አላገኘነውም። በተደጋጋሚ ከአዟሪዎች እጅ ላይ እንደተመለከትነው ዋጋው ከደራሲውና አሳታሚው እውቅና ውጭ ማስተካከያ ተደርጎበት 60.90 ብር የነበረው 90 ብር ተብሎ ተስተካክሎ አይተነዋል።

ከዚህ በተጓዳኝ ደግሞ የመጽሃፉ ሽፋን በቀላሉ በእጅ ንክኪ ቀለሙ የሚለቅ በመሆኑ ረጅም ጊዜ አንባቢ እጅ ላይ ከቆየ ሙሉ በሙሉ ቀለሙ ሊጠፋ ይችላል። እንደማንኛውም የአማርኛ መጽሃፍት ጎቲም ሲሞንም በአንዳንድ ክፍሎች ላይ የፊደላት ግድፈት አሉበት። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ መጽሃፉ ላይ የተሳሉት ገጸ ባህሪያት የሚያደርጉት ውይይት ሰፋ ያለ በመሆኑ አንባቢን በመጠኑም ቢሆን ሊያሰለች ይችላል ብዬ አስባለሁ።

እነዚህ ግድፈቶች ተስተካክለው በድጋሚ ህትመት እንደሚመጣ ተስፋ አደርጋለሁ።

ይምረጡ
(5 ሰዎች መርጠዋል)
1147 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us