ቻይና የታሸገ አየር እየገዛች እኛ አየር አማቂዎቻችንን እናጠፋለን

Wednesday, 20 April 2016 13:19

 

ወሰንሰገድ መሸሻ በላቸው/ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

በተለያዩ የአለማችን ክፍል ሰዎች የቢዝነስ ፕሮጀክቶቻቸውን፣ የቴክኖሎጅ ሥራ ፈጠራቸውን፣ የምርምር ውጤቶቻቸውንና አዳዲስ ግኝቶቻቸውን እንዲሁም የቢዝነስ ሥራ ፈጠራቸውን ዝርዝር ሃሳብ በተለያዩ መድረኮች ላይ ከሽነው በማቅረብ ለሚፈልጉት ግብ ለመድረስ ሲሰሩ ኖረዋል፣ በፕሮጀክቶችና በምርምር ፅንሰሃሳቦች ላይ በተመሰረቱ ውድድሮችም በመሳተፍ ጥምር ጥቅም ሲያገኙም ቆይተዋል።

 

ከአመታት በፊት በዚህ መልኩ የመድረክ ውድድር ተሳታፊ የነበረችው ራቼል ሲኪያና ባቀረበችው አንድ ዓለም አቀፍ ፕረዘንቴሽን/ጥናታዊ የምርምር ፅሑፏ አየርን አሽጎ ለእንስሳት፣ ለእፅዋትና ለሰው ልጆች እንዲያገለግል እንደሚቻል በመግለጧ ምሁራኖች ተሳልቀውባት፣ እጅግ አውግዘዋትና እብድ ብለው ፈርጀዋት እንደነበር ይታወሳል።

 

 

አምና በዲሰምበር 2015 በብሪታንያ ገጠር ነዋሪ የነበረው ተማሪ ከሮኪ ተራራ ባመረተው ንፁህ አየር በ4000 ጠርሙሶች አሽጎ ለቻይና ተጠቃሚዎች የላከ መሆኑንና አየር ገቢ ማስገኛ አዋጭና አትራፊ ቢዝነስ ሊሆን መቻሉን ያዩትና የሰሙት አውጋዥ፣ ተሳላቂና በእብደትነት ፈራጅ ለሆኑት ምሁራን አስደንጋጭ ዜና ሆኖ እንደነበርም ይታወሳል።

 

 

እዚያው ብሪቲሽ ውስጥ ሊዎ ዲ ዋትስ የተባለ እንግሊዛዊ የሥራ ፈጣሪ ይህንን ንግድ በማሳደግና በማስፋፋት በፌበርዋሪ 5/2016 ብዙ ሺህ የታሸጉ የአየር ምርቶችን ወደ ቻይና በመላክ አንዱን እሽግ በ80 ፓውንድ/በ115 ዶላር /400 ዩያን በቻይና/ መቸብቸቡንና በቅርቡ በቻይና  የጠቆረና አፋኝ የሆነ ጉምና ጭጋግ ሳቢያ በተፈጠረ የአየር መዛባትና በተከሰተው የንፁህ አየር እጥረት ለተጎዱት ቻይናውያን በፌበርዋሪ 8/2016 ከካናዳ ምእራባዊ ከተማ ከኤድሞንተን የተመረቱ የታሸጉ የንፁህ አየር ምርቶች የቻይናውያኑን ሕይወት መታደጋቸውንና እጅግ አዋጭ ገበያ መፈጠሩን በወቅቱ ዴይሊ ሜይል፣  ቢቢሲና ሚረር ዘግበውት አለምን ጉድ አሰኝተውት የነበረበት ትልቅ ዜና ሆኖ ነበር።

 

የአየር ንብረት መዛባት የሰው ልጅ በራስ ተነሳሽነት እየፈጠረው ያለው አደጋ መሆኑን በዚህ ፅሑፍ ለመግለፅ ገጹ የሚገድበን ቢሆንም በሐገራችን የአለማያ ሐይቅ ሙሉ ለሙሉ ደርቆና ውሃው ጠፍቶ የእርሻ መሬት ወደ መሆን መቀየሩን፣ በዋና ዋና መንገዶቻችን አቅራቢያ ይታዩ የነበሩ ሐይቆችና የተንጣለሉ ሰፋፊ ኩሬዎች ዛሬ ላይ መጥፋታቸውን ማንሳቱ ግን ግድ ብሎናል።

 

የሰው ልጅና እንስሳት ከእፅዋት ከሚለዩባቸው አበይት ምክንያቶች አንዱ እፅዋት የራሳቸውን ምግብ በቀጥታ ከተፈጥሮ ማዘጋጀት በመቻላቸው ነው። የስነፍጥረት ተመራማሪዎች ባስቀመጡት መረጃ መሰረት በምድራችን ላይ 285ሺህ የሚጠጉ የአበባ እፅዋትና 148 ሺህ የሚጠጉ አበባ የሌላቸው እፅዋት ይገኛሉ ብለው አስፍረዋል።

ከዛፍ እድገት መረጃዎች አንዱና አስደናቂው ነገር ዛፎች ወደ ላይ እያደጉና እየረዘሙ ሲሄዱ ከመሬት ወደ ላይ ለክተው ምልክት ያደረጉበት ቦታ /ቢስማር ቢመቱበት/ ለሚሊ ሜትር ያህል ለውጥ ሳያሳይ ካልተቆረጠ በስተቀር በዚያው በለኩት ከፍታ ቦታ ላይ ሆኖ ያገኙታል።

 

የዛፎች እድገት የሚጨምረው በግንድና በቅርንጫፋቸው ላይ የሚገኙ ህዋሳት አዳዲስ የተክሉን ክፍል እንደ ብሎኬት ባናት ባናታቸው ባላቸው ላይ እየከመሩ በመሄድ በመሆኑ ለክተው ምልክት ያደረጉበት ቦታ በነበረበት ሆኖ እድገቱ ከበላዩ እንደብሎኬቶቹ በሚቀጥሉ ታዳጊ አካሎቹ ሳቢያ እያደገና እየረዘመ ስለሚሄድ ቢወፍርም፣ ቢረዝምም በስረኛዎቹ ግንዶች ላይ ከመሬት የነበራቸው እርቀት በነበረበት ይቆያል።

 

ልብ ይበሉ የሰው ልጅ እድገት እንደዛፎቹ አስተዳደግ ቢሆን ኖሮ ሲወለድ የጨቅላው ልጅ ፀጉሩ ከምድር የነበረው እርቀት ካደገም በኋላ እዛው ያኔ ጨቅላ በነበረበት ከፍታ ላይ ተቀምጦ ቁመቱ ግን እረዝሞ፣ ወፍሮ ባገኜነው ነበር።

ሰዎችና ሕይወት ያላቸው ፍጡራን የሚተነፍሱትን ኦክስጅን አየር ከሚለግሱት የእፅዋት ዝርያዎች አንዱ ከሆኑት ዛፎች ውስጥ አንድ መካከለኛ ቁመት ያለው ዛፍ በአመት ወደ ከባቢ አየር የሚለቀው ኦክስጅን አራት አባላት ላሉት ቤተሰብ በእስተማማኝ ሁኔታ የሚበቃ ነው።

 

ዛፎች በቅጠላቸው ላይ የውሃ ትነትን እየለቀቁ አካባቢን ያቀዘቅዛሉ። ግዙፍ ዛፍ አዲስ ከተተከለ እፅዋት ይልቅ ከ 70 በመቶ በበለጠ የአካባቢ ብክለትን ያስወግዳል። በየምክንያቱ ወደ አየር እየተለቀቁ ያሉትን መርዛማ ጋዞችን በማመቅ ወደ ከባቢያችን ከመሰራጨት ይታደጉናል። እኛ ደግሞ ከችግኝነታቸው -ጀምረን ደፍጥጠን እናጠፋቸዋለን፣ በከብቶች ልቅ ግጦሽ እናስበላቸዋለን፣ ዛፍ ሆነው በዘፈቀደ የሚለቀቁብንን ካርበኖችን እንዳይመጡልንና መርዛማ ጋዞችን እንዳያምቁልን በማድረግ አካባቢያችንን በአየር ንብረት መዛባት በድርቅ እናስጎዳዋለን። ሰዎች በኮንስትራክሽን፣ በእርሻም ሆነ ለኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ሲሉ ከ40 ዓመት በላይ የኖሩ አገር በቀል ዛፎችን በጅምላ ይመነጥራሉ። 100 ሜትር ለሚሆን በጥቂት ሚልየን ብር ወጪ የሚሸፈን መንገድን ለመስራት  በመንገዱ አቅጣጫ የሚገኝን የዘመናት እድሜ ያለውን ዛፍ በመቁረጥ ቀጥተኛ መንገድ በማድረግ ብርን ለማዳንና ለመቆጠብ  መንገዱ ጠመዝማዛ እንዳይሆን በሚል ብቻ ዛፉን በጭካኔ ይገነድሱታል።

 

በሕግ አንፃርም እስከ 40 ዓመት የኖሩ ትልልቅ ዛፎችን መንጥሮ ለግል ጥቅም ማዋል አንዲት አህያ በመኪና ገጭቶ ከመገኘት እጅግ የቀለለ መሆኑን በተግባር ካየሁት አንድ ምሳሌ ማንሳቱን ወደድኩ ሼፌሩ መንገድ ላይ አንዲት ሴት አህያ ገጭቶ በመግደሉ አህያዋ እራሷ ለባለቤቱ የምትሰጠው የቀን ጥቅም ተሰልቶ አህያዋ በአማካይ ከ25 አመት በላይ ኖራ ይህንኑ የቀን ስሌት ለጌታዋ እንደምትሰጥ፣ ወልዳ እስከ 6 አህዮች እንደምታስገኝለትና እኒህ አህዮች ቢያንስ ለ35 አመት ገቢ ሊያስገኙለት እንደሚችሉ በመግለፅ ገጪው በብዙ አስር ሽህ ብሮች ለባለአህያው እንዲክስ ሲወሰንበት ገጭው ይች አህያ 1 አመት እንኳን ለመኖር መቻሏ ባልተረጋገጠበት አርግዛ ወልዳ ማሳደግ መቻሏ በማይታወቅበት ሁኔታ እንዴት ይህን ያህል እንድክስ ይፈረድብኛል ብሎ መከራከሩን ስናስብ ዛፍ ከአህያይቱ በበለጠ ለማኅበረሰቡ ባጠቃላይ ለሐገር፣ ለአህጉር ብሎም ለመላው ዓለም ከሚሰጠው የማይለካ ጥቅም አንፃር እጅግ የከፋ ቅጣትና ካሳ የሚያስከፍል ሆኖ አለመዘጋጀቱ ሊታሰብበት የሚገባ ትልቅ አጀንዳ ይመስለኛል።

 

እፅዋት ቅጠላቸው፣ ሥራሥራቸው፣ ግንዳቸው፣ ፍሬያቸው፣ ቅርፊታቸው ባጠቃላይ ሁለመናቸው እጅግ የሚጠቅሙን ንጥረነገሮችን በብዛት የያዙ ናቸው። የሚወድቅና የሚጣል ነገር የለባቸውም። በየመንደሩና በየስርቻው የሚበቅሉ እፅዋቶች ሳይቀሩ ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚሰጡና ከፍተኛ የኢኮኖሚ ገቢ የሚያስገኙ ከመሆናቸው ባሻገር አካባቢን ከድርቅና ከበርሃማነት ይታደጋሉ። ለብዙ ሰዎች የሥራ እድል በመክፈት ረገድም ዘርፉ አስተማማኝ ነው።

 

 

ብዙ ፋብሪካዎች በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እያስመጡ የሚጠቀሟቸው አርቲፊሻል ኬሚካሎች በጤናም ሆነ በሐገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሱት ችግር በቀላሉ የማይታይ አደጋ ነው። ከተፈጥሮ እፅዋት እነዚህን አርቲፊሻል ኬሚካሎች እዚሁ በማምረት መተካት ይቻላል። ዛፉ ሳይቆረጥና ሳይጨፈጨፍ ጥምር ጥቅም እንዲሰጥ ያደርጋል።

በቤት ውስጥ ለምግብ ማብሰያነትና ለሙቀት ተብለው ከሚቃጠሉ ማገዶዎች በሚወጡ መርዘኛ ኬሚካል አዘል ጭስ በየአመቱ 2.4 ሚልዮን የሚጠጉ ሰዎች ሕይወታቸው እንደሚያልፍ በዓለም ጤና ድርጅት የቀረበ አንድ ጥናታዊ መረጃ አመልክቷል።

 

መረጃው እንደሚያብራራው በማገዶ ጭስ የሚገኙ መርዘኛ ንጥረነገሮች ውስጥ ካርበንሞኖኦክሳይድ፣  ካርበንዳይኦክሳይድ፣ ሰልፈርዳይኦክሳይድና አሞኒያ ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ በነዚህ መርዘኛ ጋዞች በቤት ውስጥ በሚከሰት የአየር ብክለት የአይን ህመም፣ የመተንፈሻ አካል ህመም፣ አስም፣ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ሳል፣ የልብ ደም ዝውውር መታወክ፣ የቆዳ በሽታ ከማስከተላቸውም በላይ 2.4 ሚልዮን ህዝብ በየአመቱ እንደሚሞትና አብዝሃኞቹ ሴቶች ህፃናትና አረጋውያን እንደሆኑ መረጃው አክሎ ገልጧል።

 

የእንጨት ዘሮችን ለማገዶ ማዋል በአካባቢ ጥበቃው ላይ ራስ የሚያዞር ታላቅ ችግርን ይፈጥራል። የመሬት መራቆትን፣ የእፅዋት ሽፋን መሳሳትን፣ የመሬት መጎሳቆልን፣ ምድረበዳነትንና ከፍተኛ ድርቅን ብሎም እረሃብን ያስከትላል። ባጠቃላይ ተፈጥሮን ያዛባል። እነዚህ የጤናና አጠቃላይ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ማስወገድና ያለብንን የውሃ እጥረት በማሟለት ሴቶች በውሃ መቅዳት ያለባቸውን ከፍተኛ ሸክም መቅረፍ ከፍተኛ ትኩረትን የሚሻ ቢሆንም ዛፎችን መንከባከብ ይህንን ድርሻ ይወጣል።

 

እፅዋት በብዛት ያሉበት ደናማ መሬት አፈሩ በእርጥበት ውስጣዊ ከርሱ በውሃ የመሞላት ባሕሪው ጎልብቶ ወደ ለምነት በቀላሉ ይቀየራል። በጥቂት ጥልቀት የጉድጓድ ውሃ ማግኘትንና የተደበቁ ምንጮችንም ማፍለቅና አዳዲሶች እንዲመነጩም ያደርጋል።

 

የካርበን ልቀትን መጥጦ በመከላከል ደረጃ የእፅዋት ክምችት /ደኖች 25 በመቶውን ድርሻ ይወጣሉ። ዘርፈ ብዙ አገልግሎት የሚሰጡ እፅዋት ላይ በማተኮር የተፋሰስ ልማቱን በዋናነት በማገዝ እየተባባሰ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ በመቋቋም ለአፈር ለምነትና የአፈር መሸርሸርን በመንከባከብ ድርቅን የሚቋቋሙ እፅዋትን በማብቀል የካርበን ልቀትን መቀነስ፣ ለአይን እይታ የሚስቡና የሚማርኩ ለመዝናኛነት የሚያገለግሉ እፅዋት በማልማት ለአካባቢውና ለነዋሪዎቹ ማኅበረሰብ የገቢ ምንጭ መፍጠር፣ ነዳጅ ባዮ ፊዩል በማምረት ማገዶንና ኃይልን መቆጠብ፣ የተበከለ ውሃን በማጥራትና ለመስኖ ልማቱ ማገዝ፣ በካይ ጋዞችን በመቀነስ ከካርበን ኢኮኖሚ ተጋሪ መሆንና ለኢንዱስትሪው ሽግግር የጥሬ እቃ አቅርቦትና አርቲፊሻል ኬሚካሎችን በተፈጥሮ በመተካት ደንን፣ እርሻንና ኢንዱስትሪን የሚያስተሳስር ሥራ ላይ በመመርኮዝ መንቀሳቀሱ እንደ ቻይና የታሸገ አየር ለመግዛት አቅም ለለላት ሐገራችን ደኖቻችን የተበከሉ ካርበንና መርዘኛ ጋዞችን መጥጠው በማመቅ ንፁህ አየር እንዳናጣ የመታደግ ኃላፊነታቸውን እንዳይወጡ ማድረግ በእራስ ላይ የሞት ፍርድ መፍረድና ራስን ማጥፋት መሆኑን በማስታወስ እያንንዷን ተክል/ዛፍ እንደህልውናችንና ልጆቻችን አይተን ልንንከባከብ ግድ ይለናል።

 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
592 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us