“የሕይወቴ ምስጢር….” መፅሐፍን እንዳነበብኩት

Monday, 02 May 2016 16:09

የመጽሐፉ ርዕስ      “የሕይወቴ ምስጢር የተፈተነ ጋብቻ ኢዮበልዩ ግለ ታሪክ”

ደራሲ              አጥናፍ ሰገድ ይልማ

የገጽ ብዛት         304

ዋጋ               100 ብር

አታሚ                   AMT Printing PLC

አስተያየት አቅራቢ   ማዕረጉ በዛብህ

ግለ-ታሪክን መጻፍ በአገራችን ብዙ አልተለመደም። “ሕይወቴና የኢትዮጵያ ርምጃ” (1965) የተባለው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ‘ግለ-ታሪክ’ መሰል መጽሐፍ እንኳን በባለታሪኩ የተጻፈ ሆኖ እንዲታይ ቢሞከርም ጸሐፊዎቹ የንጉሡ ቅርብ ሰዎች እንደሆኑ ይወራል። ንጉሠ ነገሥቱ ያንን መጽሐፍ እኔው ራሴ ነኝ የምጽፈው ብለው ቁጭ ቢሉ አገሪትዋ ያለሳቸው አመራር ለረጅም ጊዜ እንድትጓዝ ግድ በሆነ ነበር። ስለዚህ በቅርብ ሰዎቻቸው መጻፉ ነውር የለውም። ከንጉሡ ቀጥሎ ግለ-ታሪካቸው ወይም የሕይወት ታሪካቸው ሊጻፍ የሚገባ ብዙ የተከበሩ ሰዎች ነበሩ። የብዙዎቹ አልተጻፈም። ከፊታውራሪ ተክለሐዋርያት በቀር በስነጽሁፍ የሚደነቁት ከበደ ሚካኤል (የክብር ዶክተር) እንዲሁም ሌላው (ባለ ክብር ዶክተር) የስነጽሁፍ ሰው ሀዲስ አለማየሁ እንኳን ግለ-ታሪካቸውን አልጻፉልንም። ብዙ ጠቃሚ የሕይወት ልምድና ታሪክ መረጃ አምልጦናል።

በተለያዩ ግለ-ታሪኮች ውስጥ የሚገኘው ፋይዳ ጠቃሚነት እንደ ባለታሪኮቹ የተለያየ ቢሆንም ቅሉ፤ ካለመጻፉ የመጻፉ ጥቅም የሚያመዝን ይመስለኛል። አንደኛ ከብዙ የግለ-ታሪክ ጽሁፎች የሚገኘው ልምድ ትምህርትና መረጃ ብዙ ነው። ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ዞሮ ዞሮ አንባቢ በመጨረሻ የራሱን ፍርድ ስለሚሰጥ መጻፋቸው ጉዳት የለውም።

 

ከላይ የተጠቀሰው “የሕይወቴ ምስጢር….” ደራሲ አቶ አጥናፍ ሰገድ ይልማ ግለ-ታሪክ መጻፍ አስቸጋሪ መሆኑን፣ ከራስ ጋር መከራከርን የሚጠይቅ መሆኑን ቢገልጽም፤ በመጨረሻ ክሳቸውን እንዳነሱ ነግረውናል። ግለ-ታሪካቸውን በመጻፋቸው ስለእሳቸው፣ ስለቤተሰባቸውና ከዚያም አልፎ በንጉሡና በደርግ ዘመን ስለነበሩት አንዳንድ ጠቃሚ ጉዳዮች መረጃዎች በማቅረብ የአንባቢ ጠቅላላ እውቀት እንዲዳብር ረዱ እንጂ አልጐዱንም። በተለይ ሁሉም ስለራሱ ብፁዕና ደግና አዋቂ አድርጎ በሚጽፍበት አንደኛ ባለ ኅብረተሰብ፣ አቶ አጥናፍ የሠሩዋቸውን ስህተቶች በማመንና በመፀፀት፣ በሥራቸውና በኑሮአቸው የነበሯቸውን ጠንካራና ደካማ ጐኖች በግልጽና በተዋበ ቋንቋ ያቀረቡት ይህ መጽሐፍ ብዙ የሚዳስሱ ጉዳዮችን የያዘ ነው። በመጠኑ እንመለከታቸዋለን።

 

ከመሐፉ ርዕስ ለመነሳት “የሕይወቴ ምስጢር የተፈተነ ጋብቻ ኢዮቤልዩ ግለ-ታሪክ” ነው የሚለው። ይህ ርዕስ ሦስት የተለያዩ ነገሮችን የያዘ ነው። እነርሱም የሕይወቴ ምስጢር፣ የተፈተነ ጋብቻ ኢዮቤልዩ እና ግለ-ታሪክ ናቸው። ሁሉም ነጥቦች በመጽሐፉ ውሰጥ በሚገባ የተዳሰሱ ቢሆኑም እንደ አርዕስት የመጽሐፉን መጠሪያ ስም አክብደውታል። ምንም እንኳን የመጽሐፉ ደራሲና የታሪኩ ዋናው ተዋናይ ራሳቸው አቶ አጥናፍሰገድ ቢሆኑም የባለቤታቸው የወ/ሮ አልማዝ ሥነጊዮርጊስ ግለ-ታሪክም ከደራሲው ግለ-ታሪክ ጋር የተጣመረና ያላነሰ በመሆኑ “የሕይወቴ ምስጢር” የሚለው ምናልባት የሕይወታችን ምስጢር ቢል ይበልጥ እውነታውን የሚያሳይ ይመስለኛል። “የተፈተነ ጋብቻ ኢዮቤልዩ” የሚለውም የደራሲው የብቻቸው ገጠመኝ ሳይሆን ባልና ሚስቱን የሚያጠቃልል ነው። በአጭሩ መጽሐፉ “የሕይወቴ ምስጢር” ቢባል በአንባቢ ላይ ትልቅ ጉጉት ሊያሳድር በቻለ ነበር። አለዚያም “የተፈተነ የጋብቻ ግለ-ታሪክ” ቢባል የተሻለ አይሆን ይሆን? ይህ አማራጭ ርዕስ ለስነጽሁፋዊ ምርምር ፋይዳነት ይኖረው እንደሆን ተነሣ እንጂ መጽሐፉ በርዕስ አሰጣጡ ምክንያት የምንባቡ ዋጋ ቀንሷል ለማለት አይደለም።

ወደዋናዎቹ የመጽሐፉ ዓበይት ጉዳዮች ሲገባ አከራካሪ የሚሆነው ዋናው ነገር የጠለፋው ጉዳይ ነው። ጠለፋ በአገራችን ማኅበራዊ ሕይወት ታሪክ ውስጥ የነበረ ነው። አንዳንድ ጊዜም ወንዱ ጠላፊ ፍቅሩን የሚገልጽበት ሲሆን ወይም ደግሞ “አላቻ ጋብቻ” ተብሎ ሲከለከል ተቃውሞውን በቁጣ የሚያሳይበት ልማድ ሆኖ እንደኖረ ብዙ ይተረካል። ታላቁ የስነጽሁፍ ሰው መንግሥቱ ለማም “ጠልፎ በኪሴ” የተባለ ቴአትር በመጻፍ የቀድሞ ባህላችን አካል እንደነበር ያስታውሰናል። ይህ ሁሉ ይባል እንጂ ጠለፋ በአሁኑ ዘመን (በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን) “እሰይ የኛ ጀግና” እየተባለ ከበሮ የሚደለቅለት፣ “ሎጋው ሽቦዬ” የሚጨፈርለት አይደለም። ደራሲው ይህንን ጉዳይ ከእኔ ይበልጥ አሳምረው እንደሚያውቁት አልጠራጠርም። እንደዚህ ከሆነ ታዲያ አቶ አጥናፍ ሰገድ ስለጠለፋው በሰፊው መጻፋቸው ለምንድን ነው የሚል ጥያቄ በአዕምሮአችን መነሳቱ አይቀርም። ጥያቄውን የሚያስነሱት አንዱ ምክንያት የዘመናት አስተሳሰብ መለዋወጥ ይመስለኛል። የዛሬ መቶና አምሳ ዓመታት ይወደዱና ይከበሩ የነበሩ ልማዶች ዛሬ በዘመነ ግሎባሊዝም ይወገዛሉ። አካሄዱ እንደዚህ ነው እንበል?

 

ደራሲው በሳቸውና በባለቤታቸው መካከል ስለተፈፀመው የጠለፋ ቴአትር ሲገልጹ “አልማዝ ሥነጊዮርጊስ ወልደአማኑኤል፣ በ16 ዓመቷ የዛሬ 50 መት በዚህ ወር ኅዳር 3 ቀን በዚህ ሰዓት ተጠለፈች። አጥናፍ ሰገድ ይልማ ተሰማ የአራት አመት እጮኛውን ጠልፎ በኪሱ አደረገ” ሲሉ ጽፈዋል። ከላይ እንደጠቀስኩት መጥለፍ ዛሬ የተነወረ ልማድ ሆኖ ቢታይም የዛሬ 50 ዓመትና ከዚያም በፊት እንደ “ጀግንነት” የሚቆጠር ድርጊት ነበር። ከዚያም በላይ ደራሲው እንደሚሉት ወይዘሮ አልማዝን (ያን ጊዜ ወይዘሪት) በስነስርዓት አጭተው አራት ዓመት ከቆዩ በኋላ የሠርጉ ቀን ተወስኖ እንዲነገራቸው ሽማግሌ ቢልኩ ከእጮኛቸው ቤተሰብ ያገኙት መልስ “ጋብቻው የሚፈጸመው ከአራት ዓመት በኋላ የኹለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ስታጠናቅቅ ይሆናል” የሚል ነበር። ከዚያም አልፎ እስከዚያ ጊዜ አልጠብቅም ካልክ “በማጨትህ ምክንያት ያወጣኸው ገንዘብ ካለ፣ በ10 እጥፍ ይመለስልኻል” ነበር የተባሉት። ሌሎች ለጠለፋው መከናወን አስተዋጽኦ ያደረጉ ጉዳዮች ደግሞ ነበሩ። ስለደራሲው ውቤ በረሃ ውስጥ ከምትገኝ ሴት ልጅ መውለድና ስለ አልማዝም ከአየር ኃይል መኰንኖች ጋር የጠበቀ ግንኙነት መመስረት ይናፈሱ የነበሩት አሉባልታዎችም የጠለፋውን ተግባር ያበረታቱና ያፋጠኑት ይመስላል። ደራሲው እነኝህ ሁሉ ነገሮች ተጣምረው የአራት ዓመት እጮኛዬን ጠልፌ በኪሴ አደረግሁ ነው የሚሉት። ዛሬ ላይ ሆኖ ጠለፋው ትክክል ነው አይደለም የሚል ክርክር መክፈቱ አስፈላጊ አይመስለኝም።

 

ስለ ጠለፋው የሞራሉን ውይይት ወደ ጐን ትተን የነበረውን የሽሽት፣ የድብብቆሽ፣ የመያዝና የመታሰር ፈተና፣ የተጠላፊዋን ድንጋጤና ለቅሶ፣ የራሳቸውን የጠላፊውን የሕሊና ሙግትና ጭንቀት ስዕላዊ በሆነ ድርሰት ነው ያቀረቡት። ድርጊቱ የተፈጸመበት ቦታ፣ ከቦታ ቦተ ለመደበቅ የተደረጉ ሽሽቶች፣ ከመያዝ ለማምለጥ የተሞከሩ የስለላ ስራዎች፣ ዋናዎቹ የድርጊት ተዋንያንና ረዳት ተዋንያን በእንቅስቃሴ ላይ እንዳሉ የነበረውን ሁኔታ ደራሲው ውብ በሆነው አማርኛቸውና የስነጽሁፍ ጥበባቸው ሲገልጹት ድርጊቱ ቁልጭ ብሎ እየተንቀሳቀሰ ለአንባቢ ይታያል - እንደፊልም። ምሳሌ ልጥቀስ ከመጽሐፉ፤ ደራሲው አንዱን ቅጽበታዊ ትርኢት ሲገልጹት እንደሚከተለው ነበር ያስቀመጡት፤

 

“ምንድን ነው ነገሩ? አለች አልማዝ፣ በኩኔታው ግራ ተጋብታ። ምንም አይደል ነይ እነግርሻለሁ ብዬ የመታቀፍ ያህል አባብዬና ደግፌ መኝታ ቤት ይዤያት ገባሁ። አልማዝ ጭብጥ ኩርትም ብላ አለቀሰች። ‘እባክህ ተወኝ። ሕይወቴን አታበላሸው’ አለች በሳግ ታፍኖ ቁርጥርጥ ባለ አንደበት። አሳዘነችኝ። በእንባ የታጀበው ጭንቀቷ፣ ከ’ሷ ባላነሰ እኔን አስጨነቀኝ። ስታለቅስ እኔም ለማልቀስ ዳድቶኝ ነበር። ከእጮኛነቷ እህትነቷ ተሰማኝ። …. እኔም ባባሁ። የፈታሁትን ሱሪ መልሼ ታጠቅኹ። ‘ለማንኛውም ማታ ያደርሰኛል’ አልኹና አልጋ ላይ እንዳለች ትቻት ከመኝታ ቤት ወጣሁ።”

 

አጥናፍ ሰገድ ቀደም ተብሎ በተጠቃቀሱት ምክንያቶችና በተቃጠለ የጉርምስና ፍቅር ስሜት ተነሳስተው ጠለፋውን ቢፈጽሙትም ተግባሩ ምን ያህል ያስጨንቃቸው እንደነበር ከላይ የቀረበው ከመጽሐፉ ቃል በቃል የተቀዳው አነጋገር በግልጽ ያሳያል። እንዳውም ተግባሩን አነውሮ በማየት “ትዳር ለመመሥረት ከልብ እመኝ ነበር። ይህን ምኞት ለማሳካት በፈጸምኩት ሕገ-ወጥ የጠለፋ ወንጀል፣ ያለ አንዳች ቅጣት በማምለጤና የተመኘሁትን ትዳር አራት ዓመት ሙሉ ከጠበቅኋት እጮኛዬ ጋር ከመፈጸም የበለጠ ምን ደስታ አለ?” ይላሉ።

 

ደራሲው የጠለፋውን ትረካ ከኅዳር 3 እስከ ኅዳር 13 ቀን በመዘርጋት በየዕለቱ በጠለፋው ላይ የሚያንዣብቡትን ስጋቶችና የጠለፋውን ሂደት ደህንነትና ዕድገት የጻፉት ከመጽሐፉ ጠቅላላ 304 ገጾች በ57ቱ ገጾች ነው። የጠለፋው ትረካ የመጽሐፉ አቢይ ጉዳይ ነው ማለት ይቻላል። እኔን ግን ሰፋ አድርጌ እንዳየው ያደረገኝ ርዝመቱ ሳይሆን የአጻጻፉ ኪነጥበባዊ እመርታው ነው - የሸርሎክ ሆምሰን ወይም የአጋታ ክርስቲን የስለላ ታሪክ ጽሁፎች አስታወሰኝ።

 

ደራሲው በግለ-ታሪክ መጽሐፋቸው ስለጠለፋው ብቻ ሳይሆን ከጋብቻ በኋላም ስላሳለፉት ሕይወት፣ በጋብቻቸው አልፎ አልፎ ስለገጠሙት ችግሮች፣ በሰፊው ቤተሰቦቻቸውና ልጆቻቸውም ስለተጫወቱዋቸው አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ አጋጣሚዎች ብዙ ብለዋል። ስለጋዜጠኝነት ህይወታቸው፣ ስለ ጓደኞቻቸው ቀጥሎም በከተማ አስተዳደር ሥራ ውስጥ ስላሳለፉት ጊዜ ያደረጉት ዳሰሳ በተለይ በእርሳቸው የአገልግሎት ዘመን ማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ ለነበርን ጋዜጠኞች ጥሩ ማስታወሻ ነው። ስለ አባታቸው ስለ አቶ ይልማና ስለአያታቸው ስለግራዝማች ተሰማ አባካንባው የነገሩን መረጃ፣ ዝክረ-ቤተሰብ ማስታወሻ ከመሆን አልፎ የዘመኑ የዜግነት ግዴታ ምን ያህል መስዋዕትነት የሚጠይቅ እንደነበረ ያስተምረናል። የደራሲው አያት ግራዝማች ተሰማ በአርሲ “መኻል ሠፋሪ” ነፍጠኛ ሠራዊት የነጭ ለባሽ መቶ አለቃ ሲሆኑ፣ ሠራዊቱ ከወራሪው የፋሺሰት ኢጣልያ ጦር ላይ ለመዝመት ወደ ኦጋዴን ሲንቀሳቀስ ተሰማ አባገንባውም በስራቸው ያሉትን ነፍጠኞች ጭፍሮቻቸውንና ልጃቸውን ይልማን አስከትለው ከሠራዊቱ ጋር እንደተጓዙ ከመጽሐፉ ይነበባል። በጠላት ላይ መደበኛ ውጊያ የማካሄዱ ጉዳይ በሰበብ አስባቡ እንዲዘገይ ሲደረግና ንጉሠ ነገሥቱም ሠራዊቱን ወደ ጦር ግምባር በመምራት ፈንታ ወደ ስደት ሲሄዱ፣ የአገራቸው ፍቅር ያቃጠላቸው ነፍጠኛው መቶ አለቃ ተሰማ አባካንባው ጠላቴን ሳላጠቃ ወደመንደሬ አልመለስም ብለውና ከጭፍሮቻቸው ጋር መክረው በጠላት ምሽግ ላይ በጣሉት አደጋ በተደረገ ውጊያ ላይ ሕይወታቸው አልፏል። የእኒህ ትልቅ አባት አሟሟት የጥንት አባቶቻችን ለአገራቸው የነበራቸውን ጽኑ ፍቅር የሚገልጽ ሲሆን፤ ሞታቸውም በአጋጣሚ የደረሰ ሳይሆን አስቀድመው የወሰኑት ነበር። ጦርነቱ ለጊዜው አይደረግም፤ ይህም የበላይ ትዕዛዝ ነው ሲሉ አለቃቸው ቀኛዝማች ወልደጻዲቅ ኃይሉ ቢነግሯቸውም አባገምባው ውሳኔያቸውን በሚከተሉት ቃላት ነበር የገለጹት፤

“እኔ ተሰማ አባገንባው የታጠቅሁት ጐራዴ ከሰገባው ሳይመዘዝ፣ የዝናሬ ጥይት ሳይጨረስ፣ ጠመንጃዬ ከአንገቴ ሳይወርድ፣ ሳይተኩስ፣ ሳይገድል፣ ማነኝ! ምንድን ነኝ ብዬ ነው አገር ቤት ተመልሼ የሚስቴ ባል፣ የጭሰኛዬ መልከኛ የምሆነው? እኔ አልመለስም።”

 

ነፍጠኛ የሚለው ቃል ነፍጥ/ መሣሪያ የያዘ ማለት ስለሆነ ጽንፈኞች እንደሚሉት የአማራው ብሔረሰብ የግል የመተዳደሪያ ሙያ ሳይሆን፤ የማንኛውም ብሔረሰብ ወታደራዊ ዝንባሌ ያለው ወንድ ልጅ የሚሰማራበት የሥራ ክፍል መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው። ነፍጠኛ የሚባለው በመደበኛ ሠራዊት ፈንታ በጦር መሪዎች እየተመለመለ ጠላት አገርን ሲወር የሚዘምት፣ ከአካሉ ክፋይ እስከ ሕይወቱ ያለውን እሱነቱን ለአገር መስዋዕት የሚያደርግ ባህላዊ ሠራዊት ነው። በጦርነት ጊዜ ለአገሩ እንደሚዋደቅ በሰላም ጊዜም የአገሩን ጸጥታና ዳር ድንበር የሚጠብቅና የሚያስከብር ነው። ደራሲው ይህንን እውነት በንጽፈ ሃሳብ ገለጻ ሳይሆን በአያታቸው ታሪክ በተጨባጭ አሳይተውናል። ለዚህ ነው መጽሐፉ በአጻጻፉ ጥበብ ልብ አንጠልጣይ ትረካ ብቻ ሳይሆን ትምህርታዊም የሚሆነው።

 

የመጽሐፉ ጠንካራ ጐኑ፣ የደራሲውን ውጣ-ውረድ የሞላበትን የሕይወት ታሪክ፣ ደራሲው ለባለቤታቸው ያላቸውን ፍቅርና ፈጸምኩ የሚሉዋቸውን ስህተቶች ቁልጭ ባለ የሐቅ አነጋገር ማቅረባቸው ሲሆን፤ ሌላው መጽሐፉን ተነባቢ የሚያደርገው ደግሞ የደራሲው ስዕላዊ ገለጻ ጥንካሬ ነው። አንድ ምሳሌ ልግለጽ። ተጠላፊዋ እጮኛቸው የጠለፋው ፕሮግራም ሙሉ በሙሉ ከመከናወኑ በፊት እጮኛዋን እንዲተዋት እንዴት እንደለመነችው ቀደም ብለን ያየን ሲሆን፤ ደራሲው ተጠላፊዋ እጮኛቸው የነበረችበትን ሁኔታ ስዕላዊ በሆኑ ቃላት ሲገልጹት “ከአልጋው ግርጌ ኩርምት ብላ፣ የባቄላ አበባ ከሚመስሉ ዓይኖቿ የሚፈሰውን የአልማዝን ዕንባ በመሐረብ አበስ አድርጌ ወደ የሺ ብቅ አልሁ” ይላሉ። የዚህ ገለጻ እውነታን ለማረጋገጥ ከመጽሐፉ በስተጀርባ ባለው የጥንዱ ፎቶግራፍ፣ የዚያን ጊዜይቱን አልማዝ ዓይኖች ማየት ይበቃል።n              

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
517 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us