“የድህነት ከበርቴዎች”

Wednesday, 11 May 2016 12:28

 

በማዕረጉ በዛብህ

ይህ ርዕስ የብሪታንያ ጋዜጠኛ እና ደራሲ የሆኑት ግራሐም ሐንኮክ Lords of Poverty በሚል ርዕስ የጻፉትን መጽሐፍ አንጋፋው ጋዜጠኛ ደረጀ ባልቻ ወደ አማርኛ ተርጉሞ በማሳተም የሰጠው ርዕስ ነው። አልፎ አልፎ ባየር ጠባይ ለውጥ ምክንያት በልማት ባልገፉት ሀገሮች የሚከሰተውን የረሀብ ሰቆቃ ለመታደግ ሀብታም ሀገሮች የሚለግሱትን ዕርዳታ እናደርሳለን፣ እናከፋፍላለን በማለት የሚሰለፉት የዕርዳታ አድራሽ ቢሮክራቶች እና የዕርዳታ ተቀባይ መንግሥታት መሪዎች (ከሚንስትሮች አንስቶ እስከ ፕሬዝደንቶች) እንዴት በተረጂዎቹ ሕዝቦች እልቂት እና ሰቆቃ እነሱ ከበርቴዎች እንደሚሆኑ የሚገልጸው መጽሐፍ ግራሐም ሐንኮክን አንድ ቁምነገረኛ የዓለም ድሐ ሕዝቦች ጠበቃ አድርጓቸዋል። ይህንን በዓለም ላይ እየተሠራ ያለውን ከፍተኛ ወንጀል ያጋለጠውን ዓቢይ መጽሐፍ ወደ አማርኛ በመተርጎም ደረጀ ባልቻም በጉዳዩ ላይ ለአገራችን አንባቢዎች የተሻለ ግንዛቤ ከመፍጠር አኳያ የሚመሰገን ሥራ ሠርቷል።

ግራሐም ሐንኮክ በዓለምአቀፍ የዕርዳታ አሰጣጥ ተግባር ላይ የሚካሄደውን የስልጣን፣ የክብርና የሙስና ወንጀል በከፍተኛ ጥናትና ምርምር በተደገፈ ሥራ መፅሐፍ ሲያቀርቡ፣ በራሳቸው አነጋገር እነዚህ የዕርዳታው አድራሽ፣ አከፋፋይና አጋፋሪ ለመሆን የሚሯሯጡትን ድርጅቶች “በጠራራ ፀሐይ” ከደሐው ተረጂ አፍ እየሰረቁ የሚበለጽጉ “የድህነት ከበርቴዎች” ናቸው ሲሉ ሰይመዋቸዋል። በመቀጠልም “በማንኛውም መልኩ የውጭ ዕርዳታ በጀት ባለበት ሁሉ ከግብር ከፋዩ እና ከደሐው ላይ መስረቅ ማለት ልክ ከሕፃን ከረሜላ እንደመስረቅ ነው” ሲሉ በፅናት ይኮንኑዋቸዋል። ይህ እጅግ አሳዛኝና አሳፋሪ ድርጊት በተለያዩ የዓለምአቀፍ ጉባኤዎች ሲነሳና ሲወገዝ የኖረ ጉዳይ ቢሆንም፤ ወንጀሉን ፍርጥርጥ አድርጎ በማጋለጥ ረገድ እንደ ግራሐም ሐንኮክ በበቂ ማስረጃና በጽናት ያቀረበ ሰው ያለ አይመስለኝም።

ደረጀ ባልቻ በብሪታንያ የስኮትላንድ  ተወላጅ ስለሆኑት የመጽሐፉ ደራሲ ስለግራሐም ሐንኮክ ጠባይ ጠለቅ ባለ መልኩ ሲገልጽልን “በባሕሪያቸው ነገሮችን በአሉበት ሁኔታ ከመቀበል ይልቅ በራሳቸው ግንዛቤ ላይ በመመርኮዝ በርካታ ጥያቄዎችን የሚያነሱ ናቸው” ይለናል። ሐንኮክ “በርካታ ጥያቄዎችን” ብቻ ሳይሆን የዓለማችንን ዓበይት ጥያቄዎች የማንሳት አቅም እንዳላቸው “የድህነት ከበርቴዎች” መጽሐፋቸው ጥሩ ምስክር ነው። ዓቢይ ጉዳይን በማንሣት ረገድ ደረጀ ባልቻም Lords of Povertyን ከመተርጎም አንጻር ለመጽሐፉ ደራሲ ከሚሰጣቸው ምስጋናና አድናቆት በመጠኑ ሊጋራ  ይገባዋል።

የትርጉም ሥራ የራስን ሃሳብ አውጥቶ አውርዶ እንደመጻፍ ነጻነት የማይሰጥ የሥነጽሑፍ ሙያ ነው። የመጀመሪያውን የተጻፈበትን ወይም የተነገረበትን ቋንቋ ከታሪካዊና ባሕላዊ አመጣጡ አንስቶ እስከ ሰዋሰዋዊ ሥርዓቶቹ ድረስ ያለውን ዕውቀት መካን ይጠይቃል። ከዚያም ባለፈ ስለሚተረጎመው ጉዳይ ከፍተኛ ዕውቀትና ግንዛቤ መጨበጥን፣ በተተርጓሚው ቋንቋ ባሉት ባሕላዊ ያነጋገር እና ያጻጻፍ ዘይቤ የተካኑ መሆን ከጥሩ የትርጉም ሥራ የሚጠበቅ ግዴታ ነው። ትርጉም ማለት አንድን የተጻፈ ወይንም የተነገረ ጉዳይ ዕውነቱን፣ ለዛውን እና ጥንካሬውን ሳይለቅ ፍፁም ተቀባይነት ባለው ደረጃ ከነበረበት ቋንቋ ወደ አዲሱ ወደሚተረጎምበት ቋንቋ ማሸጋገር ነው። ይርጉም ሥራ የተተረጎመውን አረፍተነገር፣ አንቀፅ ከምንጩ ቋንቋና ያባባል ልምድና ባሕል ማስተያየትንና ማረጋገጥን ይፈልጋል። ስለሆነም ከፍተኛ ዕውቀትን፣ የቋንቋ ተሰጥዎን እና ትዕግሥትን ይጠይቃል።

ሌላው የትርጉምን ሥራ አሳሳቢ የሚያደርገው በተተርጓሚው (በምንጩ) ቋንቋና በሚተረጎምበት በሌላው ቋንቋ ተጠቃሚ ሕዝቦች መካከል ያለው የቋንቋ፣ የሥነፅሑፍ ባጠቃላይ የባሕል፣ የኢኮኖሚ እና የቴክኖሎጂ ዕድገት ልዩነት ምክንያት በሚኖረው አለመመጣጠን የሚመጣው ችግር ነው።በሰፊ የትምህርት፣ የሳይንስ፣ የኢንደስትሪ፣ የሥነጽሑፍ ስልጣኔ ባሕል ውስጥ ባለፉት ባደጉ ቋንቋዎች የሚቀርቡ ንግግሮችንና ጽሑፎችን ዕድገታቸው ውሱን ወደሆኑ እንደ አማርኛ የበሰሉ ቋንቋዎች ለመተርጎም አንዳንድ ጊዜ የሚያስቸግሩ ሁኔታዎች ይታያሉ። ለምሳሌ አሜሪካኖችና እንግሊዞች አዘውትረው እንደ ቀልድ የሚሉዋቸውን  Hi, take care, take it easy, ወይም see you የሚባሉትን ያነጋገር ዘይቤዎች/ ብሂሎች እንዲተረጉሙላችሁ ጥቂት ሰዎችን ብትጠይቁ የሚሰጡዋችሁ መልሶች እንደተጠያቂዎቹ ብዛት የተለያዩ እንደሚሆኑ የሰማኛል። ቃል በቃል ቢተረጎሙ የሠመሩ መልእክቶችን አያስተላልፉም።

የትርጉም ሥራ የሚገመገመው በምንጩ መጽሐፍ፣ ሰነድ ወይም ንግግር የተካተተው ዋናው ሃሳብ ሳይለወጥ፣ ሳይቀነስ፣ ሳይባዛ በምንጩ ቋንቋ ያለውን ዕውነት ምን ያህል በጥንቃቄ ጠብቆ ገልጾታል በሚል መመዘኛ ነው ማለት ይቻላል። በነኝህ ከላይ በተነሱት መመዘኛዎች ሁሉ አንጻር “የድህነት ከበርቴዎች” Lords of Poverty የተባለውን የግራሐም ሐንኮክ መጽሐፍ በኔ ዕይታ ደረጀ ባልቻ ጥሩ አድርጎ ተርጉሞታል። ለምን እንዲህ ለማለት እንደደፈርኩ አንድ ሁለት ምሳሌዎች ከሁለቱ ሥራዎች ላቀርብ እወዳለሁ።

ግራሐም ሐንኮክ በLords of Poverty ገጽ 7 አንድ አፍሪካዊ ስደተኛ አለው ያሉትን “Why is it that every US dollar comes with twenty Americans attached to it?” የተባለውን ሕጸጻዊ ጥያቄ ደረጀ ወደ አማርኛ የተረጎመው “ለምንድነው እያንዳንዱ የአሜሪካን ዶላር ከ20 አሜሪካውያን ጋር እየተያያዘ የሚመጣው?” ሲል ነው። ይህ ትርጉም የአፍሪካዊውን ስደተኛ ንግግር እስከ ሕጸጻዊ ለዛው ቁልጭ አድርጎ ነው ያቀረበው። በጣም ጥሩ ትርጉም ነው።

የጽሐፉን ትርጉም ጥሩነት የሚያሳይ ሌላ ምሳሌ ልጨምር። ለዕርዳታ የሚፈሰው የገንዘብ ጎርፍ ለምስኪኑ ደሐ ተረጅ እስከምትደርሰው የምፅዋት ጠብታ ድረስ በለጋሹና በተረጅው መካከል ያለው የግንኙነት ገደል እጅግ የተራራቀ እንደመሆኑ መጠን፤ በጉዞው ውስጥ የሚያልፉ ብዙ የስርቆት እጆች እንዳሉ ለመግለጽ ሐንኮክ በእንግሊዝኛ በገጽ 190 “After the multi - billion dollar ‘financial flows’ involved have been shaken through the sieve of over - priced and irrelevant goods that must be bought in the donor countries, filtered again in the deep pockets of hundreds of thousands of foreign experts and aid agency staff, skimmed off by dishonest commission agents, and stolen by corrupt Ministers and Presidents, there is very little left to go around.” በማለት ግሩም አድርገው የገለጹትን ዕውነታ ደረጀ ባልቻም ባልተናነሰ የመግለጽ ችሎታ እንደሚከተለው ነው ያቀረበው።

“በብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚቆጠረው የዕርዳታ ፍሰት በለጋሽ አገሮች ውስጥ በሚገኙና ከፍተኛ ዋጋ በተጣለባቸው አግባብነትም በሌላቸው ሸቀጦች ላይ ከተራገፈና የቀረውም በመቶ ሺዎች በሚቆጠሩ የውጭ ኤክስፐርቶች እና የዕርዳታ ድርጅት ሠራተኞች ጥልቅ ኪሶች ውስጥ ከተጣራ፤ በአጭበርባሪ የኮሚሽን ኤጀንቶች ከላዩ ከተገፈፈ፣ በሙሰኛ ሚኒስትሮች እና ፕሬዚደንቶች ከተሰረቀ በኃላ፣ ሊከፈል የሚችለው ቀሪ እጅግ በጣም ትንሽ ነው።” (የድህነት ከበርቴዎች ገጽ 316)

ሚስተር ሐንኮክ ዕርዳታን በተመለከተ በሚደረጉ ስብሰባዎች እ.ኤ.አ. በ1986 የዓለም ባንክ ፕሬዚደንት የነበሩት ባርበር ኮናበል ያደረጉትን ንግግር ሲጠቅሱ “Our institution is mighty in resources and in experience but its labours will count for nothing if it cannot look at our world through the eyes of the most underprivileged, if we cannot share their hopes and their fears. We are here to serve their needs … to help them realize their strength their potential, their aspirations … Collective action against global poverty is the common purpose that brings us together today. Let us therefore re-dedicate ourselves to the pursuit of that great good.” ብለው ነው የገለጹት (ገጽ 38)። አስቲ ይህንን በደረጀ ባልቻ ትርጉም እንየው።

“ተቋማችን በሀብትና በልምድ ኃያል ነው። ነገር ግን፣ ዓለማችንን እጅግ በተጎሳቆሉት ዓይን ማየት ካልቻለ፤ ተስፋቸውንና ስጋታቸውን መካፈል ካቻለ፤ ድካማችን ውጤት-አልባ ነው። እዚህ ያለነው፣ ፍላጎታቸውን ለማሟላት፣ ጥንካሬያቸውን፣ እምቅ ችሎታቸውን፣ ፍላጎታቸውን … ዕውን ማድረግ እንዲችሉ ለመርዳት ነው። ዛሬ እዚህ ያሰባሰበን ዓለምአቀፍ ድህነትን በጋራ የመዋጋት ዓላማ ነው። ስለዚህ፣ ይህን ከፍተኛ በጎ ዓላማ ከግብ ለማድረስ ደግመን ቃል እንግባ።” (የድህነት ከበርቴዎች ገጽ 61-62)

ሐንኮክ እነኚህ ሁሉ ታላላቅ ቃላት ከተነገሩ በኋላ ጉባኤው የዓለምን ድሆች መርዳት ከሚል የሽንገላ ዲስኩር ወደምን ዓይነት ፈንጠዝያ እንደተሸጋገረ (እንግሊዝኛውን መጥቀስ ስለሚያስቸግር) ከሐንኮክ ሳይሆን ከደረጀ ትርጉም እንመልከት።

“በስብሰባው ላይ የተገኙት 10,000 ወንዶችና ሴቶች፣ ይህን ክቡር ዓላማ በፍፁም የሚያሳኩ አይመስሉም ነበር። በስብሰባው ወቅት የሚያዛጉ ወይም የሚያንቀላፉ ካልሆኑ፤ ማቋረጫ በሌላቸው ኮክቴሎች፣ የምሳ ግብዣዎች፣ የሰዓት በኋላ ሻይ፣ የእራት ግብዣዎችና የእኩለ ሌሊት መክሰሶች ይዝናኑ ነበር። ይህም እጅግ ሆዳምና የሆነ ስግብግብን እንኳን ቁንጣን ለማስያዝ የሚችልና የተትረፈረፈ ነበር። በዚያ አንድ ሳምንት ብቻ ለልዑካኑ የቀረቡት 700 ዝግጅቶች ጠቅላላ ወጪ 10 ሚሊዮን ዶላር ይገመታል። ይህን ያህል ገንዘብ፣ በሌላ መልክ ሥራ ላይ ውሎ ቢሆን፣ ምናልባት የችግረኞችን “ፍላጎቶች ሊያሟላ” በቻለ ነበር። ለምሳሌ፣ ዜሮፕታለሚያ የተባለው የቪታሚን ኤ እጥረት የሚያመጣው የዐይን ህመም፣ 500,000 የአፍሪካና የእስያ ሕፃናትን በየዓመቱ ለዐይነስውርነት ይዳርጋል። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሌሎችን ደግሞ የማየት ችሎታቸውን ያዳክማል። በ10 ሚሊዮን ዶላር፣ በታዳጊ አገሮች ለሚገኙ 47 ሚሊዮን ሕፃናት ለአንድ ዓመት ሙሉ የሚበቃ ቫይታሚን ኤ ማቅረብ ይቻል ነበር። በዚህም ያለጥርጥር፣ “እምቅ ችሎታቸውን ዕውን ማድረግ እንዲችሉ መርዳት ይቻል ነበር።” (የድህነት ከበርቴዎች ገጽ 62)

 

ድምዳሜ

ይህች አጭር የአስተያየት ጽሑፍ የተዘጋጀችው በሁለት ዓበይት ምክንያቶች ነው። አንደኛውና ዋናው ምክንያት፣ በታዳጊ አገሮች ችግር በደረሰ ቁጥር ኃብታም ሀገሮች ብዙ ጊዜ ከመርዳት ወደኋላ ባይሉም፣ በረጅዎችና በተረጅዎች መካከል ያለውን ሩቅ የግንኙነት ገደል በመድፈን ከመካከል ገብተው በድሆች ኪሳራ “የድህነት ከበርቴዎች” የሚባሉ ሌቦች እንደሚፈጠሩ ያለውን አሳዛኝ የዓለም ሁኔታ ግራሐም ሐንኮክ የተባሉት የብሪታንያ ጋዜጠኛና ደራሲ እንዴት ግሩም አድርገው እንደገለጹት ለማሳየት ነው። ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ በቋንቋው ምክንያትም ሆነ ወይም የሐንኮክን Lords of Poverty የተባለውን መጽሐፍ ያላገኙ ሰዎች ዛሬ መጽሐፉን በአማርኛ ቋንቋ ለማንበብ እንደሚችሉ ለማሳወቅ ነው። ጉዳዩ ሲጠቃለል የቀረበው አስተያየት የአማርኛው ትርጉም የእንግሊዝኛውን ጽሑፍ በጥንቃቄና በጥራት የሚያቀርብ መሆኑንም ለመግለጽ ነው።n

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
762 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1023 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us