በጎጃም ባህል ያደገው ኦሮሞው ታሪክ ፀሀፊ

Wednesday, 25 May 2016 12:57

-    የኢትዮጵያ ታሪክ በአለቃ ተክለ ኢየሱስ ዋቅጅራ ዕይታ

 

በያዝነው ዓመት በርካታ መፃህፍት ለህትመት በቅተዋል። ከእነዚህ መፃህፍት መካከል አንዱ “የኢትዮጵያ ታሪክ በአለቃ ተክለ ኢየሱስ ዋቅጅራ” በሚል ርዕስ ሥርግው ገላው (ዶ/ር) ዝግጅትና አርትኦት ለአንባቢ የቀረበው መፅሀፍ ይገኝበታል። መፅሀፉ በ67 ምዕራፎች ተዋቅሮ 431 ገፆችን ያካተተ ነው። (የመጽሐፉ አዘጋጅ ሥርግው ገላው አለቃ ተክለ ኢየሱስን “እሳቸው” ከሚለው መጠሪያ ይልቅ “አንተ” በሚለው መጠሪያ ስለተጠቀሙ፤ ይህ ጽሁፍም ከአንቱታው ይልቅ የሥርግውን ሃሳብ በቀጥታ መጠቀምን መርጧል።)

የታሪኩ ፀሀፊ አለቃ ተክለ ኢየሱስ ዋቅጅራ የወለጋ ኦሮሞ ተወላጅ ነው። የትውልድ ዘመኑ የሚያሳየው በ1860 አካባቢ መወለዱን ነው። በ1871 ዓ.ም ራስ አዳል አቡናና አዋጦ ወደ ተባለ ቦታ በዘመቱበት ወቅት የራስ አዳል አጎት የሆኑት የሌምቱ ጎሹ የዚሁ ዘመቻ አካል እንደነበሩ የመፅሀፉ መግቢያ ያትታል።

 ከዘመቻው መልሱ የሌምቱ ጎሹ ስምንት ልጆችን ወደ አገሩ ምስራቅ ጎጃም ይዞ ሲመለስ ከስምንቱ ልጆች መካከል አንዱ ነገሮ  ነበር። ነገሮ በኋላ ተክለ ኢየሱስ በመባል የታወቀውና የመፅሀፉ  ፀሀፊ የሆነው ሊቅ ነው።

 

 የቀድሞው ነገሮ የኋለኛው ተክለ ኢየሱስ ልዩ ችሎታ የነበረው ሰው ነበር። የችሎታው መገለጫ ከሆኑት መካከል አንዱ የቋንቋ ችሎታው ነው። ከአፍ መፍቻ ቋንቋው በተጨማሪ አማርኛና ግዕዝ ቋንቋን በመማር በርካታ ለትውልድ የሚቀሩ የታሪክ የምርምር ስራዎችን መስራት ችሏል። አለቃ ተክለ ኢየሱስ ይህ ብቻ ሳይሆን፣ የመንፈሳዊ ትምህርት ሊቅ፣ ሰአሊና የትውልድ የዘር ሀረግ ጥናት (Genealogy) ባለሙያ ጭምርም ነው። የትውልድ ጥናት የሙያ ዘርፍ ወይንም በእንግሊዘኛው ጂኖሎጂ በማለት የሚጠራው ሙያ ዛሬም ቢሆን በሀገራችን ብዙም የማይታወቅና ያልዳበረ ዘርፍ ነው። ሆኖም ከዛሬ መቶ አመት በፊት ተክለ ኢየሱስ ይህንን ሙያ በግሉ አዳብሮ ከትውልድ ጋር በተያያዘ በወቅቱ በጎጃም አካባቢ ሲፈጠር የነበረውን ችግር ለመፍታት ሙከራ ሲያደርግ እንደነበር ይሄው በሥርግው ገላው አዘጋጅነት ለህትመት የበቃው መፅሀፍ ያብራራል

 በጊዜው በነበረው የርስት ውርስና ይገባኛል ጥያቄ ጋር በተያያዘ በዚያው በጎጃም በርካታ ውዝግቦች ይነሱ ነበር። የአካባቢው ተወላጅ የርስት ወራሽነቱን የሚያረጋግጠው የዘር ሀረጉን ወደኋላ በመቁጠር ሲሆን ይህንን የዘር ቆጠራ በሚገባ ማስረዳት ያልቻለ ሰው “በይገባኛል” ክርክር ጊዜውን ለማጥፋት ይገደዳል።

 ይህ ብቻ ሳይሆን ከርስት የመነቀል ሁኔታም ሊከሰት ይችላል። ይሄንን ክፍተት የተረዳው አለቃ ተክለ ኢየሱስ የዘር ሀረጉ የጠፋው ትውልድ ከመዝገብ እንዲመረምር በማሰብ የጎጃም ትውልድን የሚያሳይ የዘር ሀረግ መዝገብን በብዙ ድካም ማዘጋጀት ችሏል። ፀሀፊ አለቃ ተክለ ኢየሱስ ይህ የዘር ሀረግ ቆጠራ ልምዱ በታሪክ አፃፃፉም ላይ ተፅዕኖ ያሳረፈ ይመስላል። ታሪክን ሲፅፍ የዘር ቆጠራን በደንብ አጥርቶ ለማስቀመጥ ጥረት ሲያደርግ ይታያል። ይህም ተፅዕኖ በአብዛኛው ከመፅሀፍ ቅዱስ የአፃፃፍ ስልት ጋር በመያያዝ የመጣ ይመስላል። ለዚህ ማሳያ የሚሆነው በመፅሀፉ ገፅ 97 ላይ ያሰፈረው የሚከተለው ሀሳብ ነው።

 

“የቀደሙ ሰዎች በኦሪት በዜና መዋዕል፣ ትውልድ ፅፈው ነበር። በሀዲስም ወንጌላዊያን የጌታን ፅፈው ነበር። ነገር ግን የኢትዮጵያ ሊቃውንት ሀዲስና ብሉይ ሲያስተምሩ ትውልድ ማወቅ ጥቅም መሆኑን ሳይረዱ ጨምረው ሳያስተምሩ እየቀሩ ብዙ ሰው አስንፈው ይኖራሉ። የትውልድ ቁጥር አለማወቅ ጉዳት መሆኑ ብቻ በኢትዮጵያ አልታወቀም ቀድሞም በኢየሩሳሌም በኢኮኒያን መንግስት ናቡከደነፆር በማረካቻ 12 ነገደ እስራኤል ታውቋል።

ይሄውም በእዝራ መፅሀፍ ይገኛል። በተማረኩ በ72ኛው ዘመን ቂሮስ ንጉሰ ፋርስ ነግሶ እስራኤልን በአዋጅ ሰብስቦ ከምርኮ መልስ ዘሩባቤልን አለቃ አድርጎ እየርስታችሁ ግቡ ብሎ ሰደዳቸው። የዚህ ጊዜ ትውልዳቸውን ፅፈው የያዙ ሰዎች ዘለላቸውን ቆጥረው ነገዳቸውን አውቀው ከርስታቸው ገቡ። ሰነፎች ግን ሳይፅፉ ቀርተው ወገናቸው ነገዳቸው ጠፍቷቸው ከርስት ተነቀሉ። ተክህነትም ተነቀሉ።”

አለቃ ተክለ ኢየሱስ በዚህ የታሪክ አፃፃፍ ስልቱ ከመፅፍ ቅዱስ የዘር ግንድ አተናተን በመነሳት የአውሮፓ፣ የአፍሪካና የሌሎች የሰው ዝርያዎችን በዘር ግንድ ዛፍ ሲተነትንና ስርጭታቸውንም ለማሳየት ሲሞክር ይታያል። አብዛኛው የታሪክ ትንታኔውም የመፅሀፍ ቅዱስ ታሪኮችን መነሻና መሰረት አድርጎ የተፃፈ ለመሆኑ ፀሀፊው ራሱ እየደጋገመ የሚጠቅሳቸው ሀሳቦች ያስረዳሉ። ፀሀፊው የክርስትናንና የእስልምናን ሀይማኖቶችን አመጣጥ እንደዚሁም የኦሪት እምነትን አመጣጥ በስፋት ተንትኗል። የኢትዮጵያን ታሪክ ከጥንታዊው፣ ከመካከለኛውና ከዘመናዊው የጊዜ አከፋፈል አኳያም በስፋት ተንትኗል።

 

ጎጃምና አለቃ ተክለ ኢየሱስ

አለቃ ተክለ ኢየሱስ ትውልዱም ሆነ የዘር ሀረጉ የሚመዘዘው ከምስራቅ ወለጋ ኩታይ በተባለ አካባቢ ነው። ሆኖም እድገቱና ትምህርቱ ጎጃም በመሆኑ ሙሉ ማንነቱ የተቃኘው በጎጃም ባህልና ወግ ነው ማለት ይቻላል። ይህንን እውነታ በተመለከተ የመፅሀፉ አዘጋጅ በመግቢያቸው ገፅ 7 ላይ በሚከተለው መልኩ አስቀምጠውት እናገኘዋለን፡-

 

“ተክለ ኢየሱስ በደም ኦሮሞ ሆኖ ሳለ ባህሉ፣አስተሳሰቡና አጠቃላይ ማንነቱ ሁሉ ጎጃሜ ነበር። ይህም ማንነት የሚወሰነው በደም ሳይሆን ባደጉበት ማህበረሰብ ቋንቋ፣ባህልና አመለካከት መሆኑን  የሚያስገነዝብ መሆኑን የሚያመለክት ነው። የጎጃም አስተሳሰብ፣አባባል፣ሃይማኖት፣የኑሮ ዘይቤና አመለካከት ሙሉ በሙሉ በተክለ ኢየሱስ ላይ ይንፀባረቃል። ለጎጃሜ መጥፎ የሆነ ሁሉ ለተክለ ኢየሱስ መጥፎ ነው። ጥሩ የሆነው ሁሉ ለተክለ ኢየሱስ ጥሩ ነው። ይህም ተክለ ኢየሱስ  ገና ከህፃንነቱ ጀምሮ የጎጃምን ባህልና ወግ እየተጋተና እየተማረ ስላደገ ነው።”

 

አለቃ ተክለ ኢየሱስና የስዕል ስራዎቹ

አለቃ ተክለ ኢየሱስ የቋንቋ የጂኖሎጂና የስነፅሁፍ ባለሙያ ብቻ ሳይሆን የስዕል ባለሙያም ጭምር ነበር። በዚህ የስዕል ስራዎቹም የመኳንቱን ቤቶች አበያተ መንግስታትንና አበያተክርስቲያናት በተለያዩ ስዕሎች አስጊጧል። በዚህም ስራው በስዕሉ ካስጌጣቸው ስራዎች መካከል የዲማ፣የደብረ ማርቆስ፣የደብረ ዘይት የጥያሜ፣እና የአማኑኤል አበያተክርስቲያናት የሚገኙበት መሆኑን በመፅሀፉ ገፅ 2 ላይ ተመልክቷል።

 

ሥርግው ገላው ይህንን የአለቃ ተክለ ኢየሱስን መፅሀፍ ሲያዘጋጁ በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ የእሱን የእጅ ፅሁፎችና ቅጂዎች በማሰባሰብ መሆኑን አመልክተዋል። እነዚህ መረጃዎች ከተሰባሰበባቸው ምንጮች መካከልም እንጦጦ ማርያም ያለው የእጅ ፅሁፍ፣ የደጃዝማች ከበደ ተሰማ ቅጅና የብላታ መርስኤ ወልደ ቂርቆስ ቅጂ ይገኙበታል። እነዚህን ስራዎቹን ጠብቆ ለትውልድ በማስተላለፉ ረገድ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም የእጅ ፅሁፍ ቅጂዎቹን  በፎቶ ኮፒና በማይክሮ ፊልም አማካኝነት አዘጋጅቶ ዶክመንት በማድረግ ለህዝብ አገልግሎት ክፍት እንዲሆን ያደረገ መሆኑን የአዘጋጁ የመቅድም ማስታወሻ ያመለክታል።

አብዛኞቹ ቀደም ያሉ የታሪክ አፃፃፍ ስልቶች በአንድ መልኩ በውዳሴ በሌላ አቅጣጫ ደግሞ የመረጃ ምንጫቸው በትክክል ምን እንደሆነ የማይገልፁና የማይታቁ ናቸው።የአለቃ ተክለ ኢየሱስን ስራ በተመለከተ ከአዘጋጁ የመቅድም ማስታወሻ መረዳት እንደሚቻለው  የታሪክ አፃፃፍ ስልቱ ልክ እንደ ዘመናዊው ታሪክ አፃፃፍ የምርምር መንገዶችንና ዘዴዎችን የተከተለ ነው። በዚሁ መፅሃፍ ገፅ 12 ላይ የሰፈረው ሀሳብ ይሄንኑ እውነታ የሚያንፀባረቅ ሲሆን የሚከተለውን ይመስላል፡-

 

ተክለ ኢየሱስ ይሄንን ዜና መዋዕል ለማጠናቀር ቀጥለው የተመለከቱትን ምንጮች ተጠቅሟል። የኢትዮጵያን ታሪክ ከዴሰተ ዝዋይ፣ ከዘጌ ከናርጋና ከደቅ ከተገኙ የነገስታት ታሪኮች፣ የኦሮሞን አፈ ታሪክ ከአለቃ አፅሜ፣ ከአባ ባህሪ የዐፄ ቴዎድሮስን ታሪክ ከአለቃ ወልደ ማርያምና ከደብተራ ዘነብ የአፄ ዮሃንስን ታሪክ ከሊቀ መርዓዊ  የዓፄ ምኒልክን፣የክፉ ቀንን፣ የራስ መኮንን የጣሊያን ጉብኝትን እና የአደዋን ጦርነት ታሪክ ከአፈ ወርቅ ዘብሄረ ዘጌ እና በዘመኑ ከነበሩ ጋዜጦች እንደቀዳ መረዳት ተችሏል።”

ፀሀፊው ከዚህም በተጨማሪ በታሪክ አፃፃፉ ከግለሰቦች መወድስ ነፃ በሆነ  መልኩ ታሪኩን እንዳለ ያቀረበ መሆኑን ፀሀፊው እየደጋገመ ይገልፃል። ከዚህም በተጨማሪ የኦሮምን ታሪክ በስፋት ለመዳሰስ ሞክሯል። ለታሪክ ማስረጃነት ከተጠቀማቸው ሰነዶችና መጠይቆች በተጨማሪ ራሱ የአይን ምስክር የሆነባቸውንም ምንጮች በቀጥታ ተጠቅሟል።

 

 ቀሪውን የመፅሃፍ ምንባብ ለአንባቢያን በመተው በዚሁ ልሰናበት።

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
1201 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 165 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us