Print this page

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፡- ሰላምን፣ ፍቅርን፣ አንድነትን በቃልም በተግባርም አስተምረው ያለፉ ታሪክ ሁሌም የሚዘክራቸው መንፈሳዊ አባት!

Wednesday, 01 June 2016 12:27

 

በተረፈ ወርቁ

ክፋትና ጥላቻ፣ ዓመፃና እርኩሰት፣ የእርስ በርስ ጦርነትና እልቂት ክፉ ዜና በሚንጣት በዚህች ሁላችንም በምንኖርባት ዓለማችን ፍቅርን የሕይወታቸው መመሪያና ሕግ አድርገው የኖሩ፣ ደግሞም የሚኖሩ፣ ለምድራችን ሰላምን፣ ፍቅርን፣ አንድነትን፣ ይቅርታንና ምሕረትን የሰበኩ የሃይማኖት አባቶችና መንፈሳዊ መሪዎች ትናንትና ነበሩን፣ ዛሬም እንዳሉን በብዙ ተስፋ እናደርጋለን።

የክፋትን፣ የእርስ በርስ መበላላትን የጥላቻ ዘርን ፈጽመው ያመከኑ፣ ለጥፋትና ለሞት የተመዘዙ የቃየል ሰይፎችን በሰላምና በዕርቅ ቃል ወደ ሰገባቸው እንዲመለሱ ያደረጉ፣ ለእልቂት የተዘረጉ እጆችን፣ የተራራቁና የተለያዩ ብኩን ልቦችን በፍቅር ቃል ያጣመሩና አንድ ያደረጉ፣ አንዳንች የጥፋትና የእልቂት ደመና ፅልመት ለጋረደው ሕዝባቸው ሰላምን ያወጁ፤ ታሪክን የቀየሩ፣ የዘር፣ የብሔር፣ የሃይማኖት፣ የቋንቋ ድንበር ሳያግዳቸው- በፍቅር ልብ፣ በእንባቸው ለሰው ፍጥረት ሁሉ በጸሎት የተጋደሉ፣ በብርቱ መቃተትና ምልጃ፤ የሃይማኖትን፣ የፍቅርን መልካም ገድል የተጋደሉ ከፍ ያለ የመንፈስ ልእልና ላይ የተቀዳጁ የሃይማኖት አባቶችን፣ መንፈሳዊ መሪዎችን ታሪካቸውን፣ ገድላቸውን አንብበናል።

እንዲህ ዓይነት አባቶች፣ ጀግኖች ታሪክ፣ መንፈሳዊ ተጋድሎአቸው፣ ፍቅራቸው፣ ትዕግሥታቸው- የጽናት፣ የተስፋ፣ የብርታት ምንጭ ናውና ታሪካቸው፣ ገድላቸው ተደጋግሞ ሊነገር፣ ሊዘከር ይገባዋል። በዛሬው አጭር ጽሑፌ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ፫ ፓትርያርክ ለነበሩት ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቅጥር ግቢ ውስጥ ለመታሰቢያነት ቆመላቸው የነበረው ሐውልት በዕድሜ ብዛት በማርጀቱና በመፈራረሱ ምክንያት የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች በኾኑ በጎ አድራጊው በአቶ ቁምላቸው ገ/ሥላሴና ቤተሰቦቻቸው የእኚህን ታላቅ አባት ሐውልት ፩.፭ ሚሊዮን ብር በፈጀ ወጪ ባማረ ሁኔታ ዳግመኛ እንዲሠራ አድርገው ባሳለፍነው ዕለተ ሰንበት፣ እሑድ ለምርቃት በበቃው የቅዱስነታቸው ሐውልት መነሻነት ጥቂት ነገሮችን ለማለት ወደድኹ።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያሪክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ብፁዓን አባቶች፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮችና ምእመናን፣ አባት አርበኞች፣ የመገናኛ ብዙኃንና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ነበር የቅዱስነታቸው ሐውልት ምረቃ ሥነ-ሥርዓት የተካሄደው። በዚሁ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ላይ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣

‹‹ተዘከሩ መኳንንቲክሙ ዘነገርክሙ ቃለ እግዚአብሔር ወእንዘ ትሬእዩ ሠናየ ግዕዞሙ ተመሰሉ በሃይማኖቶሙ፤ የእግዚአብሔርን ቃል የነገሩአችኹን መምህራኖቻችሁን አስቡ፤ መልካም ሥራቸውን አይታችኹ በሃይማኖት ምሰሉአቸው።›› በሚል መነሻ የመጽሐፍ ቃል ቅዱስነታቸው የትናንትናዎቹን ባለውለታዎቹን፣ የአባቶቹን የእምነት ጽናትና ተጋድሎ አስቦ፣ ለአባቶቹ ታሪክና ቅርስ የሚቆረቆር፣ ይህ ታሪክና ቅርስም ተጠብቆ ለትውልድ ትውልድ እንዲተላለፍ የሚተጋ ትውልድ ለቤተ ክርስቲያን፣ ለአገር፣ ለዛሬውና ለመጪው ትውልድም መልካም ተምሳሌት እንደሆነ ነበር የተናገሩት።

ቅዱስነታቸው እንዳስታወሱትም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ፫ ፓትርያርክ የነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተ/ሃይማኖት ‹‹እግዚአብሔር የለም›› የሚለውን የደርግን ኮሚኒስታዊ ሥርዓት ብርቱ ፈተና፣ መከራ በጽናት ተቋቁመው፣ የቤተ ክርስቲያኒቷን ህልውና፣ አንድነት ያስጠበቁ አባት ነበሩ። በበርካታ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶችና ምእመናን ዘንድም ‹‹የሁሉም ሰው አባት›› በሚል ቅጽል የሚታወቁት አባ ተ/ሃይማኖት አንድ ቀንም እንኳን ስለ ትውልድ ስፍራቸው፣ ስለተገኙበት ብሔርና ጎሳ ተናግረው የማያውቁ፣ በዚህ ምድር ላይ እንግዳና መፃተኛ ሆነው በጾምና በጸሎት፣ በተጋድሎ የኖሩ ፍጹም ባህታዊ አባት እንደነበሩ ብዙዎች በመንፈሳዊ ቅናትና አድናቆት ይመሰክሩላቸዋል።

በስብከተ ወንጌል፣ በበጎ አድራጎት፣ በልማት ሥራ ስማቸው አብዝቶ የሚነሣው እኚህ መንፈሳዊ አባት፣ ስለ ሥራቸው እንዲነገርላቸው የማይፈልጉና ‹‹እናት ከፍቅር የተነሣ ለልጆችዋ የምታደርገውን ነገር ሰው ኹሉ ይወቅልኝ ትላለች እንዴ!? በማለት ለሚያከናውኗቸው ሥራዎቻቸው ከማንም ዕውቅናም ሆነ ምስጋና የማይፈልጉ አባት ነበሩ። አቡነ ተ/ሃይማኖት የራሴ የሚሉት ሀብትና ንብረት ያልነበራቸው፣ የወር አበላቸውን በሙሉ ለበጎ አድራጎት ሥራ የሚያውሉ፣ በጾምና በጸሎት የተጠመዱ፣ መቼም ቢሆን አልጋ ላይ ተኝተው የማያውቁ አባት እንደነበሩ በቅርብ የሚያውቋቸው አባቶች ይመስክሩላቸዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም አንድ በብዙዎች ዘንድ የሚነገር ታሪክ አላቸው። በአንድ ወቅት ቅዱስነታቸው ጉብኝት ለማድረግ ሌሎችን ብፁዓን አባቶች አስከትለው ወደ ሀገረ ፖላንድ ይጓዛሉ። በዚያም ያረፉት በካርዲናሉ መኖሪያ ቤት ነበር። አቡነ ተ/ሃይማኖት ለእረፍት ለማረፊያ በተዘጋጀላቸው ክፍላቸው ውስጥ ይግቡ እንጂ አልጋ ላይ አይተኙም ነበር። ጠዋት ግን አልጋውን የተኙበት ለማስመሰል የተነጠፈውን ብርድ ልብስም ሆነ አንሶላ ያመሳቅሉት ነበር።

ታዲያ አንድ ቀን ምሽት ላይ የካርዲናሉ ሠራተኛ ዕቃ ለማውጣት ወደ ቅዱስነታቸው ክፍል ስትገባ አልጋው እንደተነጠፈ አቡነ ተ/ሃይማኖት ግን መሬት ላይ ምንጣፋቸውን ዘርግተው ተኝተው ታያቸውና ደንግጣና ተገርማ ያየችውን ነገር ለካርዲናሉ ትነግራቸዋለች። ካርዲናሉም የአቡነ ተ/ሃይማኖት ቅድስና፣ ትሕትና፣ ትኅርምት አስደንቆት ቅዱስነት ጉብኝታቸውን እስኪያጠናቅቁ ድረስ በራሱ መኪና ከቦታ ቦታ በመውሰድ በትጋት ሲያገለግሉአቸው እንደነበር በሰፊው ይተረካል። ቅዱስነታቸው በአመጋገብም በኩል በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ከበሶ፣ ከተተቀለ ድንችና ጥቂት ፍራፍሬ በስተቀር ሌላ ምግብ በልተው እንደማያውቁ በቅርብ የሚያውቋቸው ሰዎች ይናገራሉ። 

ከአሥራ ኹለት ዓመታት የፓትርያሪክነት አገልግሎት በኋላ ግንቦት ፳፰ ቀን ፲፱፻፹ ዓ.ም. በተወለዱ በ፸ ዕድሜያቸው ዓመታቸው በእረፍተ ሞት ከዚህ ዓለም የተለዩት አቡነ ተ/ሃይማኖት መላ ዘመናቸውን በጸሎት፣ በጾም፣ በሰጊድ ያሳለፉ ከመሆናቸው ጋር ከዚህ ዓለም በሞት በተለዩ ጊዜ የሰውነታቸው ክብደት ፳፭ ኪሎ ግራም ደርሶ ነበር። የቅዱስነታቸው አስክሬን ባረፈበት በቅድስት ሥላሴ በመንበረ ጠቅላይ ቤተ ክህነትም የመታሰቢያ ሐውልት ቆሞላቸው ነበር። ግና ይህ ሐውልት ለ፳፰ ዓመታት አገልግሎት ሰጥቶ በዕድሜ ብዛት በማርጀቱና በመፈራረሱ ምክንያት የቤ/ን ተቆርቋሪ፣ አገር ወዳድ በሆኑ ኢትዮጵያዊ በጎ አድራጊ በአቶ ቁምላቸውና ቤተሰቦቻቸው ዳግመኛ ተሠርቶላቸዋል።

 አቶ ቁምላቸው በዕድሜ ብዛት ያረጀው የእኚህ ቅዱስ አባት ሐውልት ባዩት ቁጥር ውስጣቸውን እረፍት ይነሣው ስለነበር ከቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ አባቶችና የሥራ ሓላፊዎች ጋር ተመካክረው ባገኙት መልካም ፈቃድና ክትትል ይህን ሐውልት እንዳሠሩ ይናገራሉ። አቶ ቁምላቸው በሐውልቱ ምረቃ ወቅትም እንደተናገሩት- በፍቅራቸው፣ በእምነት ተጋድሎአቸው፣ በበዛ ትዕግሥታቸውና ጽናታቸው ለቤተ ክርስቲያን፣ ለአገርና ለትውልድ ተምሳሌት፣ ሕያው ቅርስ የኾኑ አባቶቻችንን ማክብር፣ ሥራቸውንም መዘከር ቅዱስ ተግባር ከመሆኑም ባሻገር ከሁሉም ታሪኩን ከሚወድና ከሚያክብር ኢትዮጵያዊ የሚጠብቅ ታሪካዊ ሓላፊነትና ግዴታ እንደሆነ ነው አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት።

በመንበረ ፓትርያሪክ ቅርስ ጥበቃ፣ ቤተ መጻሕፍትና ወመዘክር መምሪያ ሓላፊ የኾኑት መምህር ሰለሞን ቶልቻ ለቅዱስነታቸው ስለተሠራው ሐውልት የተናገሩት አንድ ዐቢይ ቁም ነገር እዚህ ጋር ሊነሣ የሚገባው ይመስለኛል። ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክና ቅርስ ለአገራችን ብቻ ሣይሆን ለአፍሪካና ለመላው ዓለም ኩራትና ቅርስ መሆናቸውን በማስመር፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት /በዩኔስኮ መዝገብ በዓለም አቀፍ ቅርስነት ያስመዘገበቻቸው ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀሱ ቅርሶች/ Tangible and Intangible Heritagesለአገራችን የቱሪዝም ኢኮኖሚ ያላቸውን ዘርፈ ብዙ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳና ጠቀሜታ እግረ መንገዳቸውን ገልጸውታል።

መምህር ሰለሞን አክለውም በሌላው ዓለም የታዋቂ ሰዎች መካነ መቃብር በጥሩ ኹኔታ ተጠብቆ እንደሚጎበኝ በመግለጽ፣ ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ለኢትዮጵያ ነጻነት፣ አንድነት በዱር በገደሉ የተጋደሉ ኢትዮጵያውያን አርበኞች፣ ጀግኖች፣ ከውጭ አገራትም ዕድሜያቸውን ሙሉ ስለ ኢትዮጵያ ነጻነት ሲጋደሉ የኖሩ፣ ስለ ሕዝቦቿ አኩሪ ታሪክ፣ ባህል፣ ቅርስ በሰፊው የጻፉና ለዓለም ያስተዋወቁ እንግሊዛዊቷ ዕውቅ የሰብአዊ መብት ታጋይ የእነ ሲሊቪያ ፓንክረስት፣ እንዲሁም በተለያዩ ሙያና ሥራ አገራችንን በአፍሪካና በመዓለም መድረክ ያስከበሩ የቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ፣ የሌሎች ታላላቅ ኢትዮጵያውያን መካነ መቃብር ያለበት በመሆኑ በአገር ውስጥና በውጭ አገር ጎብኚዎች የሚዘወተር አንድ የቱሪስት መዳረሻ ቅዱስ መካን መሆኑን ሙያዊ የሆነ መንገድ አብራርተዋል።

ስለሆነም አሉ በማጠቃለያቸው ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም ሆነ ለአገራችንና ለትውልድ ሁሉ ሕያው ታሪካቸው ይዘከር ዘንድ በማሰብ በበጎ አድራጊው በአቶ ቁምላቸውና ቤተሰቦቻቸው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ፫ ፓትርያሪክ ለነበሩት ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተ/ሃይማኖት ዳግመኛ የተሠራው ሐውልት የሁላችንም ኢትዮጵውያን የታሪክ ምስክርና ሕያው ቅርስ እንደሆነ ነው ያስረገጡት።

ዕውቁ የታሪክ ምሁርና ተመራማሪ ፕ/ር ላፒሶ ጌዴልቦ፣ ‹‹ታሪክ ለአገር ዕድገት ቁልፍ መሳሪያ ነው!›› እንዲሉ በእውነትም የትናንትና ባለውለታዎቻችን ታሪካቸው በሚገባ ተጠብቆ በሕያው ቅርስነት እንዲተለላፍ ማድረግ ለአገር ዕድገትና ብልጽግና ጉዞ ቁልፍ መሳሪያና ዋስትና ከመሆኑም በላይ ለታሪክና ለቅርስ የሚቆረቆሩ ሰዎች ነገ ለአገሩ፣ ለወገኑ ፍቅር ያለውና የሚቆረቆር ትውልድና መልካም ዜጋ እንዲኖረን የሚያደርግ ክቡር ሥራ እንደሆነ ምስክር አያሻውም።

ሰላም!

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
970 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin