ጀግኖቹን ያከበረው ደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ

Wednesday, 15 June 2016 12:49

ከሄኖክ ስዩም

መንቆረር ነን። የቀደመ ስሟ ይሄ ነበር። ታሪክ በቀደመው ራስ ኃይሉ ገና በኋለኛው ራስ ኃይሉ ፈዘዘች ይላታል። ደብረ ማርቆስ የአሁኑ መጠሪያዋ ነው። ንጉሥ ተክለኃይማኖት ናቸው የአዲሱ ስያሜዋ ባለቤት። በንጉሡ በተክለኃይማኖት ዘመን ስሟ ገናና፣ ክብሯ ታላቅ ነበር። ይህንን ታሪኳን ከነበር ለማውጣትና ትናንትናዋን ለማደስ ብዙ የምትደክም ከተማ ናት። ስኬቷም ውበቷም የዚኽ ማሳያ ነው።

ከከተማዋ ስያሜ ስሙን የወረሰው ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ እገኛለሁ። ከየአቅጣጫው እንደኔ እኔን ላመጣኝ ጉዳይ የመጡ እንግዶች ብዙ ናቸው። ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ከአዲሶቹ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አንዱ ነው። ፈጣንና ቀልጣፋ ተግባሩ ግን መነጋገሪያ አድርጎታል። ህዝብ ህዝብ የሚሸት ዩኒቨርሲቲ ነው። በዙሪያው ለሚገኘው ማህበረሰብ ለውጥ ይተጋል። ከዚያም ሲያልፍ እንዲህ ባለው ተግባሩ ሀገራዊ ሚና ይጫወታል።

አዳራሹ ሞልቷል። ሊያውም ግዙፍና ሺውን የሚውጥ ሰፊ አዳራሽ ሆኖ ነው። መድረኩ ላይ የጎዣም ኪነት ቡድን ባህላዊ ጨዋታዎችን እያቀረበ ነው። የመድረኩ ስር ባነር ተለጥፎበታል። ባነሩ "ኪነ ጥበብ ለማኅበረ ምጣኔ ሀብታዊ ልማት" የሚል ጽሑፍ ከላይ ሰፍሮበታል። ከስሩ "፬ኛው የሐዲስ ዓለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም ዓመታዊ ዐውደ ጥናት" ይላል።

ዕለቱ ግንቦት 27 ነበር። ጉባኤው ከግንቦት 27-28 ቀን 2008 ዓ.ም. ለሁለት ተከታታይ ቀናት የሚካሄድ ሲሆን ለአራተኛ ጊዜ የተዘጋጀ ነው። ዩኒቨርሲቲው የአካባቢ ጥናት ማእከሉን በታላቁ ጮቄ ተራራ ስም ሰይሟል። የባህል ጥናቱ ማእከል ደግሞ በደራሲ፣ አርበኛ፣ ዲፕሎማትና መምህር በሆኑት ሁለገቡ የጥበብ አባት በሐዲስ ዓለማየሁ ስም የተሰየመ ነው።

ሐዲስ ዓለማየሁ “የእልም እዣት”፣ “ወንጀለኛው ዳኛ” እና “ትዝታን” የመሳሰሉ መጽሐፍት ደራሲ ናቸው። በሀገራችን ህዝብ ዘንድ በፍቅር እስከ መቃብር ድርሰታቸው ገነው ይታወቃሉ። ፍቅር እስከ መቃብር አንድ መጽሐፍ ብቻ አይደለም። ግማሽ ምዕተ ዓመት እያነጋገረ፣ እያመራመረ፣ እየተወደደ፣ እየተነበበ የኖረ ነው። ዘንድሮው 50ኛ ዓመት እዩቤልዩውን እያከበርንለት ነው።

የጎዣም ኪነት ቡድን ተከታታይ ጨዋታዎችን አቅርቦ ከመድረኩ ወረደ። መደበኛው መርሐ ግብር ጀመረ። የባህል ማዕከሉ ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው አንዳርጌ እንኳን ደህና መጣችሁ ብለው፤ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲን የምርምርና ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ወደ መድረኩ ጋበዙ። ምክትል ፕሬዝዳንቱ ዶክተር ስማቸው ጋሻዬ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አቀፍ ስራዎችን ጥረት እና የሀዲስ ዓለማየሁ የባህል ጥናት ማዕከልን እንቅስቃሴዎች በአጭሩ አስተዋውቀው ታዳሚውን አመስግነው። ከእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው በኋላ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት የዕለቱን የክብር እንግዳ እንዲጋብዙና ንግግር እንዲያደርጉ ጋበዙ። ዶክተር ንጉሴ ምትኩ ወደ መድረኩ ወጡ። በዩኒቨርሲቲው ስም ጉባኤው ለመታደም የተገኙ አንጋፋና ወጣት የሀገራችንን ደራሲያንና የጥበብ ሰዎች እንዲሁም ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲ የተገኙ እንግዶችን አመስግነው። የዕለቱን የክብር እንግዳ ለንግግር ጋበዙ። ጉባኤው በአቶ አወቀ እንየው የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ የመክፈቻ ንግግር መከፈቱ ተበሰረ።

በርካታ ደራሲያን ታድመዋል። አንጋፋዎቹም ወጣቶቹም አሉ። የባህል ጥናት ማዕከሉን ተቋም እንደ ተቋም በሚዳስሰው የዶክተር መርሻ አለኽኝ የጥናት ጽሑፍ ተጀመረ። ዶክተር ታዬ አሰፋ የፍቅር እስከ መቃብርን መጽሐፍ በ50 ዓመት ጉዞ ያበረከተውን ሁለንተናዊ አስተዋጽኦ የተመለከተ የጥናት ጽሑፋቸውን አቀረቡ። አቶ ስማቸው ንጋቱ ደግሞ የቅኔ ታሪካዊ አመጣጥን የሚዳስሰውንና የጉባኤ ቤቶቹን ልዩነት የተመለከተ የጥናት ጽሑፋቸውን ለውይይት አቀረቡ።

ውይይቱ ቀጠለ። አያሰለችም። የፍቅር እስከ መቃብር የሬዲዮ ትረካን ትዝታ አድርጎ ያስቀረው ባለዋሽንት መድረኩን እያዋዛው ነው። የዩሐንስ አፈወርቅ የዋሽንት ዜማ ከውይይቱ ጭብጥ ጋር ተዳምሮ ሳይሰለች የሚመሽ ቀን አደረገው። የአጫብር ዜማ ትምህርት አሰጣጥ ትናንትና እና ዛሬ በአራቱ አድባራት በአቶ ተግባሩ አዳነ፣ የያሬድ የዜማ መጽሐፍ ምልክቶች ተመሳሳይ ለሚመስሉ ድምጾች መደበኛ አጠቃቀም ያላቸው አስተዋጽኦ፤ በዶክተር ሙሉቀን አንዱዓለም፣ የአማርኛ ቋንቋ አጠቃቀም ችግር በደብረ ማርቆስ ከተማ ተተኳሪነት በዶክተር አለማየሁ ተመስገን ቀርበው ውይይት ተደረገባቸው። ቅዳሜ መሸ። እሁድ ዳግመኛ ሊገናኝ ተሰብሳቢው ተለያየ።

እሁድ ግንቦት 28 ቀን 2008 ዓ.ም. ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ አዲሱ አዳራሽ ውስጥ ነን። ሁለተኛው ቀን አራተኛው ዓመታዊ የሀዲስ ዓለማየሁ የባህል ጥናት ጉባኤ ሊጀምር ነው። የጎዣም ጣፋጭ ባህላዊ ዜማዎችን የጎጃም ኪነት ቡድን እያቀረበ ነው። ትናንት ውይይቱን ያልጠገበው ተሰብሳቢ ቀድሞ ከአዳራሹ ክትት ብሏል።

የመድረኩን ውይይት ለመምራት አቶ ተስፋዬ አራጊ ወደ መድረኩ መጡ። የመጀመሪያው ጽሑፍ የዶክተር ሰለጠነ ስዩም ነበር። የደጃዝማች በላይ ዘለቀ የአርበኝነት ታሪክ ዙሪያ ያጠነጥናል። ለዚህ ጀግና ዩኒቨርሲቲው በስሙ አንድ ካምፓስ ሰይሟል። ታላቁን ኢትዮጵያዊ አርበኛ የሚዘክርውን ዩኒቨርሲቲ ጥሪ አክብረው የጀግናው በላይ ዘለቀ ቤተሰቦች በጉባኤው ተግኝተዋል።

 

 

 

የጥናቱ ጽሑፍ ቀርቦ እንደአለቀ ደራሲና ጋዜጠኛ አበረ አዳሙ ወደ መድረክ ወጣ። በላይ ዘለቀን የሚዘክር ግጥም ማቅረብ ሲጀምር ያ ባለዋሽንት በዋሽንቱ ድምጽ አጀበው። አዳረሹ በአንዳች ደስ በሚል መንፈስ ተወረረ። የደጃዝማች በላይ ዘለቀ የልጅ ልጆች ወደ መድረኩ ወጡ። ቤተሰቦቻቸው አጀቧቸው። ይኽ ቅጽበት ልዩና አስደሳች ነበር።  

በዚኽ መንፈስ የእሁዱ ጉባኤም እንደ ደመቀ ቀጠለ። ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ የሀዲስ ዓለማየሁን ትዝታ መጽሐፍ መነሻ አድርገው መድረኩን የያዘ ንግግር አደረጉ። የሌፎ ሌፎ ጭፈራ የአጨፋፈር ስልት ላይ አቶ ጥላሁን ታዬ፣ አጼ ዘርዓያቆብና የኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ እድገት በአቶ ዳዊት ግርማ የመነሻ ጥናት ጽሑፎች ቀርበው ደማቅ ውይይት ተካሄደባቸው። የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ለባለዋሽንቱ ከያኒ ለዩሐንስ አፈወርቅ የህይወት ታሪኩን የሚያትት ዘጋቢ ፊልም አዘጋጅቶ በሺዎች በሚቆጠር ኮፒ አሳትሞ ገበያ ላይ እንዲውል ስጦታ አበረከተ።

ብዙዎች ጉባኤው ሀገራዊ ፋይዳ ያለው እንደሆነ ምስክርነታቸውን ሰጡ። ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲም ያለ እድሜው ያደገ ፋና ወጊ ነው ሲሉ ያወደሱም ነበሩ። የፍቅር እስከ መቃብርን ታሪክ ከመነሻ እስከ መድረሻ በድንቅ ቡርሹ በስዕል ያዘጋጀውና ያቀረበው አቶ ነጋልኝ ሉሌም ስራዎቹን አስጎበኘ።

ሁለት ቀናት ከአስር በላይ የመነሻ የጥናት ጽሑፎች፣ ሰዓት የገደበው የሞቀ ውይይት፣ በትንፋሽ የተፈወሰ ድካምና ዋሽንት ያጀበው አይረሴ ጊዜ ነበር። ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲን የዓመት ሰው ይበለን ብያለሁ።         

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1810 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1012 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us