የአየር ንብረት ለውጥ በኢትዮጵያ፤ ከ2 ዲ.ሴ የሙቀት መጠን ጭማሪ ጋር መኖር ምን ማለት ነው?

Thursday, 14 July 2016 15:37

በወልደአምላክ በውቀት (ፕሮፌሰር)

መግቢያ፡- ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የሚኖራት ተጋላጭነት

ባለፉት ጥቂት አመታት አገራችን ኢትዮጵያ ከኢኮኖሚ ዕድገት፣ ድህነት ቅነሣና ማህበራዊ ልማት አንፃር አሥደናቂ መሻሻሎችን አሳይታለች። ከ 1995/96 ዓ.ም ጀምሮ የአገሪቷ ኢኮኖሚ በየአመቱ በአማካይ ከ 10-11% እድገት እያሳየ ይገኛል። ይህም ከሠሃራ በታች ካሉ አገራት አማካይ እድገት አንፃር ሲታይ እጥፍ ሆኖ ይወሰዳል። በእንዲህ አይነቱ በጐ መሻሻልና መልካም ተሞክሮ ላይ በመመስረትም አገሪቷ በ2017.ዓ.ምመካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለመሠለፍ የሚያስችል ብሔራዊ ርዕይ ሰንቃለች። እንዲያም ሆኖ ግን መንስኤው ከአገሪቷ አቅም ባለፈ ለቁጥጥር አዳጋች የሆነው የአየር ንብረት ለውጥ ለዚህ ርዕይ ስኬት ዋነኛ ጋሬጣ ሊሆን ይችላል።

የአየር ንብረት ለውጥ ተከሰተ የሚባለው ለበርካታ (አስርና ከዚያ በላይ) ለሚሆኑ አመታት ነባራዊው የአየር ንብረት ሊለካ በሚችል መጠን በተከታታይ ልዩነት ሲያሳይ ወይንም ተለዋዋጭነቱ ሳያሰልስ መቀጠሉ ሲረጋገጥ ነው። ተለዋዋጭነት የአየር ንብረት ሥርዓት አይነተኛ ባህሪ ነው። በተወሰነ የጊዜ ገደብ (በወር፣ በወቅት፣ አመት)ውስጥ ተለክቶ የሚታወቅ የአየር ንብረት መረጃ ለረጅም ተከታታይ አመታት በተመሳሳይ የጊዜ ገደብ (በወር፣ በወቅት፣አመት) እየተለካ ከሚመዘገብ የአየር ንብረት መረጃ ጋር ሲነፃፀር የሚያሳየው ልዩነት የአየር ንብረት ተለዋዋጭነትን ለመግለፅ ያስችለናል። እነዚህ ተለዋዋጭነት የሚለካባቸው ልዩነቶች ያልተለመዱ የአየር ንብረት ሁኔታዎች ይባላሉ። በWMO አተያይ (IPCC የሚጠቀምበት) የአየር ንብረት ተለዋዋጭነት መንስኤዎች በአየር ንብረቱ ስርዓት ውስጥ ካለው ተፈጥሮአዊ ባህሪይ ውስጣዊ ሂደት የተነሳ ወይንም ተፈጥሮአዊ እና ሰው ሰራሽ የሆኑ ውጫዊ ከሆኑ ምክንያቶች ሊመነጩ ይችላሉ። በተመሣሣይ መልኩ የአየር ንብረት ለውጥ መንስኤዎችም ተፈጥሮአዊ ውስጣዊ ሂደቶችና ውጫዊ ግፊቶች ሊሆኑ ይችላሉ። UNFCCC በአየር ንብረት ለውጥ እና በአየር ንብረት ተለዋዋጭነት መካከል ያለውን ልዩነት ሲያስቀምጥ የአየር ንብረት ለውጥ ከሰው ልጆች ተግባር ጋር በተያያዘ ሲሆን የአየር ንብረት ተለዋዋጭነት ደግሞ ከተፈጥሮአዊ ምክንያቶች ጋር መያያዙን ይገልፃል። ሆኖም WMO ልዩነታቸው ከመንስኤያቸው ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ አይገልፅም።

በአሁኑ ጊዜ የሚታየው የአየር ንብረት ለውጥ መንስኤ በዋነኛነት ሰው ሰራሽ የሆነ ምክንያት ስለመሆኑ ግን ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ መግባባት ላይ ተደርሷል። በተለይም Fossil fuelን ጥቅም ላይ በማዋል የተነሳ የተከሰተው የአለም ሙቀት መጨመር ከቅድመ ኢንዱስትሪ ዘመን አንፃር ሲነፃፀር አለም አቀፍ አማካይ የሙቀት መጠን በ 0.85 ዲ.ሴ.ስለመጨመሩ በቅርብ የተጠናቀረው የIPCC መረጃ ሲያመለክትይህንኑ የሙቀት መጠን ወደ 2 ዲ.ሴ.ከፍ ለማድረግ የአለም መሪዎች ተስማምተዋል። በኢትዮጵያ ያለው አማካይ አመታዊ የሙቀት መጠን ከ 1960ዎቹ ጀምሮ በ 1.3 ዴ.ሴ. እንደጨመረ ተከታታይ ጥናቶች ያመለክታሉ። ይህም ከኢንዱስትሪ አብዮት ጀምሮ ከታየው አለም አቀፍ አማካይ የሙቀት ጭማሪ የላቀ ሆኖ ይገኛል።

   እዚህ ጋር የምናነሳቸው ወሳኝ ጥያቄዎች የሚከተሉት ናቸው።

1.   የአለም አቀፍ አማካይ የሙቀት መጠን በ 2 ዲ.ሴ በሚጨምርበት ጊዜ ኑሮ (አኗኗራችን) በኢትዮጵያ ውስጥ ምን መልክ ይይዛል?

2.   በአማካይ በ 2 ዲ.ሴ እየጨመረ የመጣውን አለም አቀፍ የሙቀት መጠን ለመላመድ (Adapt) ኢትዮጵያ ምን ልታደርግ ይገባል?

ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ ከሚሆኑ የአፍሪካ አገራት፣ ኢትዮጵያ ዋነኛ ተጋላጭ አገር ሆና ትጠቀሳለች። በዚህ ደረጃ የመሠቀሷ ምክንያት ግልፅ በመሆኑ አስገራሚ አይሆንብንም እነዚህም ምክንያቶች፣

·         አብዛኛው ህዝብ በአነስተኛና የዝናብ ጥገኛ በሆነ ግብርና ላይ የተሰማራ መሆን፣

·         የተቌማት ደካማነት

·         የመሠረተ ልማት ዕድገት አለመስፋፋት

·         የድህነት መንሰራፋት

·         የሰው ሀብት ልማት እድገት አናሳነት እና

·         አብዛኛው መሬት መጠነኛ የሆነ ሥነ-ምህዳራዊ ለውጥን ሊቌቌም የማይችል በመሆኑ ነው።

በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ የሆኑ ዘርፎች ተብለው የተለዩት ግብርናና የምግብ ዋስትና፣ ውሃና ኢነርጂ፣ መሠረተ ልማትና የህብረተሰብ ጤንነት ናቸው። በተመሳሳይ ከፍተኛ ተጋላጭነት የሚታይባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ሴቶች፣ ህፃናት፣ አረጋዊያን፣ የአካል ጉዳተኞች እና በሽተኞች በሚል ተለይተዋል።

ወደፊት ለሚከሰተው የአየር ንብረት ለውጥ፣ ኢትዮጵያ እንደምትጋለጥና እንደምትጠቃ ለማወቅ በቀላሉ በተለያዩ ጊዚያት በተከሰቱት ተፈጥሮአዊ የአየር ንብረት ተለዋዋጭነት የደረሰባትን ጉዳት ማስታወስ በቂ  ነው። በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያ ተፈጥሮአዊ የአየር ንብረት ተለዋዋጭነትንም ሆነ እየታየ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ መላመድ ግድ ይላታል።

 

  ከ2ዲ.ሴ. የሙቀት መጠን ጭማሪ ጋር ለመኖርወደ ልውጠታዊ (transformational) ማላመድ ተግባር መግባት

ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር መላመድ ማለት ወደፊት ሊመጣ ካለውም ሆነ አሁን ካለው የአየር ንብረት ሁኔታ ጋር ተጣጥሞ መጔዝ መቻል ነው። በተሻለ መንገድ ሲገለፅ መላመድ ማለት

 I.     ካልተለመደ የአየር ንብረት ጋር ተጣጥሞ መጔዝ፣

  II.     ተደጋጋሚና ኃይለኛ አስከፊ ክስተቶችን ለመቌቌም መቻል፣

III.     በአየር ንብረት ለውጥ መነሻ ለሚከሰቱ ድንገተኛ የአየር ንብረት ሁኔታዎች ዝግጁ መሆን ወይንም

IV.     እኒህ ከላይ የተጠቀሱትን ሦስቱን ጉዳዮች በማቀናጀት የሚተገበር ነው።

   V.     የማላመድ ስትራቴጂዎችን ለመቅረፅና ለመተግበር የሚከተሉትን መሠረታዊ ጉዳዮች ማስተዋል ያስፈልጋል።

 VI.     በአየር ንብረት ተለዋዋጭነትና አስከፊ ክስተቶች ዙሪያ ቀደም ሲል የታዩ ተሞክሮዎችን በመቀመር እና

VII.     የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ የሚወጡየወደፊት ሁኔታ አመላካች መረጃዎችን ጥቅም ላይ ማዋል ናቸው።

ቀደም ሲል ከታዩ የአየር ንብረት ተለዋዋጭነትና አስከፊ ክስተቶች የሚወሰዱ ተሞክሮዎች

የአየር ንብረት ተለዋዋጭነትና አስከፊ ክስተቶች በኢትዮጵያ ውስጥ ያስከተሉትን ተፅዕኖ ለመረዳት የሚያስችሉ ብዙ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል። ለምሳሌ በ1970ዎቹ የተከሰተው ድርቅ 7.8 ሚሊዮን ዜጐች ላይ ጉዳት ሲያደርስ ከ300,000 በላይ ሰዎችን ለሞት የዳረገ ነበር። በ1994 ዓ.ም የተከሰተው ድርቅ ደግሞ ምንም አይነት የሞት አደጋ ባያስከትልም 13.2 ሚሊዮን ዜጐች ላይ ጉዳት ያደረሰ ሆኖ አልፏል። በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለው ድርቅም እስካሁን ምንም የሞት ጉዳት እንዳላደረሰ ቢጠቀስም ከ10 ሚሊዮን በላይ የሆኑ ዜጐች ላይ ጉዳት እንዳስከተለ ይነገራል። ጥናቶች እንደሚጠቁሙትም በአብዛኞቹ የአገሪቷአካባቢዎች በየትኛውም አመት ድርቅ ሊከሰት የሚችልበት ዕድል ከ 40%በላይ እንደሆነ ነው።

በአገራችን የድርቁን ያህል ተሰልቶ ጉዳቱ ባይታወቅም፣ ሌላኛው አስከፊ የአየር ንብረት ክስተት ተፅዕኖ የሆነው የጐርፍ አደጋ ነው። ሆኖም ከጥቂት የተገኙ መረጃዎች አንፃር በ1953 ዓ.ም 10,000 የሚሆኑ ቤቶችን በከፊልና ሙሉ ለሙሉ በማውደም ከ15,000 በላይ የሚሆኑ ዜጎችን ቤት አልባ ያደረገ ጐርፍ ተከስቶ እንደነበር ይታወቃል። በ1986 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተከሰተው ጐርፍም 31.3 ሚሊዮን ብር የሚገመት የቤት ንብረት ውድመትንአስከትሏል። ሌላው አሰቃቂና በመራር ሀዘን የምናስታውሰው በድሬዳዋና ደቡብ ኦሞ እንዲሁም ሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ ተከስቶ የነበረውና በንብረትና የብዙ ሰው ህይወት ላይ የሞት አደጋ ያስከተለውን ጐርፍ መጥቀስ ይቻላል።

እንግዲህ እነዚህን ተለዋዋጭነቶች፣ አስከፊ የአየር ንብረት ክስተቶችና የሚያስከትሉትን ጉዳት ነው ካለፈው ጊዜ ክስተት ተምረን ለወደፊቱ መዘጋጀት ያለብን። ተለዋዋጭነት እየጨመረ፣ አስከፊ ክስተቶች በተደጋጋሚና በከፍተኛ መጠን እንዲጨምሩ የሚያደርግ የአየር ንብረት ለውጥ ይጠበቃል። በዚህም የተነሳ ከላይ የተጠቀሱት አይነት ጉዳቶች በላቀ መጠን መከሰታቸው አይቀሬ ይሆናል ማለት ነው።

 

 ከአየር ንብረት ለውጥ የወደፊት አመላካች መረጃዎች የሚወሰዱ ትምህርቶች

የአየር ንብረት ለውጥ አመላካች መረጃዎችን መጠቀም ሌላኛው የማላመድ ዘዴዎችን ለመወሰን የሚያስችል መሠረታዊ ግብአት ነው። የልቀት መጠን መለኪያ ሞዴሎች ላይ ተመርኩዞ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ በ2100 ዓ.ም ይታያል ተብሎ የሚጠበቀው የሙቀት መጠን ከ 2 እስከ 5 ዲ.ሴ. ይጨምራል ተብሎ ነው። በአንፃሩ አነስተኛ አመታዊ የዝናብ መጠን ጭማሪ እንደሚታይ ተመልክቷል። ይኸውም በአካባቢያዊና ወቅታዊ ሁኔታ ልዩነት ያሳያል። እርጥባማ አካባቢዎች እርጥባማ ሆነው ሲቀጥሉ፣ ደረቃማ አካባቢዎች የበለጠ ደረቃማ እንደሚሆኑ ይጠበቃል። ብዙ ጥናቶችም የበዛ ዝናብ የሚጥለው አስከፊ ክስተቶች በሚታዩበት ጊዜ እንደሆነ ይገልፃሉ። በተከታታይ የተደረጉ ጥናቶችም ወጥ ያልሆነ የዝናብ ስርጭት እንደሚታይ ሲያመለክቱ፣ ጥቂት ጥናቶች ደግሞ በበልግ ወቅት የስርጭት መጠን እየቀነሰ የሚሄድ መሆኑንና በክረምት ወቅት ደግሞ የተወሰነ መጠን እየጨመረ እንደሚሄድ ያመለክታሉ። ከዚህ ጋር ተያይዞ ሊታይ የሚገባው ደግሞ በተለያዩ አመታት መካከል ያለው የዝናብ ስርጭት መጠን ሲሆን ይህም በተለያዩ ጊዜና ቦታዎች የበለጠ በተወሳሰበ ሁኔታ እየተለወጠ የሚመጣ ሆኖ ይታያል።

በ2005 ዓ.ም በተደረገው ጥናት እንደተገመተው በ2042 ዓ.ም የአየር ንብረት ለውጥ በሚያስከትለው ጉዳት የGDP መጠን ከ 8-10% ሊቀንስ እንደሚችል ነው። ይህንን ጉዳት ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት ለማላመድ ዘዴዎች ትግበራ የሚያስወጣው ወጪ በአመት ከ 0.8 እስከ 2.8 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደሚሆን ይገመታል።

በቅርቡ ታህሳስ 2፣ 2008 ዓ.ም በ195 አገራት መካከል በተደረገው ታሪካዊው የፓሪስ ስምምነት በዚህ ምዕተ አመት ማገባደጃ የአለም አቀፍ የሙቀት መጠን ጭማሪን ከ 2 ዲ.ሴ.በታች ለማድረግ ተወስኗል። ለዚህም ከኢንዱስትሪ ዘመን ቀድሞ ከነበረው የሙቀት መጠን አንፃር በ 1.5 ዲ.ሴ.ብቻ ከፍ እንዲልም ጭማሪውን ወደ 1.5 ዲ.ሴ. መጠን ለመቀነስ ጥረቶች መደረግ እንዳለባቸው ስምምነት ተደርሷል። ይህም በአለም ከፍተኛ የፖለቲካ አመራሮች ደረጃ እንደ ታላቅ ስኬት ተቆጥሮ ምስጋና የተቸረው ጉዳይ ሆኗል።

ለምሳሌም የተባበሩት መንግስታት ሴክሬተሪ ጄኔራል ባንኪውን እንዲህ ብለዋል።

“ከመቼው ጊዜ በበለጠ ሁኔታ የሰው ዘር ላይ የተደቀነውን ውስብስብ አደጋ ለመጋፈጥ አለም አቀፋዊ ትብብር የምናደርግበት አዲስ ዘመን ላይ ገብተናል። በአለም ላይ የሚገኙ ሁሉም አገራት ለመጀመሪያ ጊዜ የልቀት መጠንን ለመግታት አደጋን ለመቌቌም እና የአየር ንብረት ሁኔታን በተመለከተ የጋራ መግባባት ላይ የተመሠረተ እንቅስቃሴ ለማድረግ ቃል ገብተዋል። ይህ በጋራ ለመስራት የሚያስችል ታላቅ ስኬት ነው።”

የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት የሆኑት ፍራንኮ ሆላንዴ ደግሞ

“ተሳክቶላችኋል፣ ሁሉንም የሚገዛ ታላቅ ስኬት ላይ የሚያደርስ አለም አቀፋዊ ስምምነት ላይ ደርሳችኋል። ከዚህ ጉባኤ በበለጠ ለሌላ ለማንኛውም ጉዳይ የላቀ ምስጋና ላቀርብ አይቻለኝም። በልጆቻችሁና በልጅ ልጆቻችሁ ፊት በኩራት ለመቆም የሚያስችላችሁ ተግባር ፈፅማችኋል።” በማለት አወድሰዋል።

የልቀት መጠንን በተመለከተ ካለፉ ልምዶችና ወደፊት ይታያሉ ተብለው ከተመለከቱት የልቀት መጠኖች አንፃር የአለም አቀፍ የሙቀት መጠንን ወደ 1.5 ዲ.ሴ.ወይንም ከ 2 ዲ.ሴ. በታች ለመቀነስ ዋነኛ በካይ ጋዝ ለቃቂ የሚባሉት አገራት መሠረታዊ በሚባል ደረጃ የልቀት መጠናቸውን የሚቀንሱበት እርምጃ ሊወሰድ ይገባል። ይህንንም በሆነ መልኩ ይተገብሩታል በሚል ተስፋ ማድረግ ብቻ ነው የምንችለው። ከዚህ ባለፈ ግን ሊነሱ የሚገቡ ወሳኝ ጉዳዮች አሉ እነዚህም፡-

 

 

$1   I.     ወደ 2 ዲ.ሴ. እየጨመረ ባለው የሙቀት መጠን ሁኔታ በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖረው ልዩነት እንዴት ይታያል

$1  II.     በ1.5 ዲ.ሴ. እና 2 ዲ.ሴ. መካከል ባለው የሙቀት መጠን መጨመር የተነሣ የሚፈጠረው ሙቀትና ተያያዥየአየር ንብረት ለውጦች በተለያዩ አካባቢዎች የሚያደርሱት የጉዳት መጠን ምን ያህል ይሆናል? በሌላ አባባል ምንም እንኳን በ2 ዲ.ሴ. ላይ የመግታት አላማ ስኬታማ ቢሆንም አንዳንድ የአለም አካባቢዎች ከ 2 ዲ.ሴ. የበለጠ የሙቀት መጠን ጭማሪ እንደሚኖራቸው የታወቀ ነው።

ለምሳሌ ያህልም፣ በ IPCC እና ሌሎች አጥኒዎች እንደተመለከተው በአርክቲክ አካባቢ ያለው የሙቀት መጠን ከአለም አቀፍ አማካይ የሙቀት መጠን በእጥፍ የጨመረ መሆኑ ሲሆን በአፍሪካም፣ የሙቀት መጠን ከአለም አቀፍ አመታዊ አማካይ የሙቀት መጠን አንፃር በሁሉም ወቅቶችና በአጠቃላይ በአህጉሩ በጠቅላላከፍ ያለ እንደሚሆን ይታወቃል። በዚህ የተነሳም በየትኛውም ደረጃ በሚከሰት የሙቀት መጨመር ምክንያት የሚመጣ ተፅዕኖ አካባቢያዊ ልዩነት እንደሚኖሩት ያስገነዝበናል።

የአየር ንብረት አመላካቾችና የተፅዕኖ ግምገማን በተመለከተ የሚወጡ መረጃዎች ያለባቸው ጉድለት፣እንዲሁም በጊዜና በቦታ አንፃር የሚኖረው ልዩነት እነዚህን አመላካች መረጃዎች ተጠቅመን ውሳኔ ላይ እንዳንደርስይገታናል። ሆኖም ግን ቀደም ባሉ ጊዜያት የታዩ የተለዋዋጭና አስከፊ ክስተቶች ተፅዕኖዎችንና ለወደፊት አደጋ አመላካች የሆኑ መረጃዎችን ስናስተውል አገራችን ኢትዮጵያ በፍጥነት የልውጠታዊ (transformational) ማላመድ ተግባር ውስጥ መግባት ይኖርባታል።

ወደ ልውጠታዊ ማላመድ ተግባር

የአየር ንብረት ለውጥን ለማላመድ የሚታቀድ ተግባር ‘ኢንክሪመንታል’ ማላመድን ወይንም ልውጠታዊ (transformational) ማላመድ ዘዴን ይከተላል። ‘ኢንክሪመንታል’የማላመድ ተግባር ጉዳትን ለመቀነስ የሚያስችሉ መጠነኛ ለውጦችን መተግበርን ሲያካትት  ልውጠታዊ (transformational) የማላመድ ተግባር ግን መሠረታዊ የሆነ ለውጥን የያዘና ይህም በተግባራዊ እንቅስቃሴ፣ በተቋማትና በመጠን ደረጃ የሚገለጥ ሆኖ ይገኛል።አንዳንድ ተመራማሪዎች የልውጠታዊ (transformational) ማላመድ ዘዴን በሚከተሉት ሦስት መንገዶች ይከፋፍሉታል።

1.  መጠነ ሰፊ በሆነ ደረጃ የሚተገበር

2.  ለተወሰነ አካባቢ ወይንም ሥነ-ምህዳር አዲስ የሚሆን

3.  ቦታዎችን መሰረታዊ በሆነ መልኩ የሚለውጥ

ከዚህ አመዳደብ እንደምንረዳው ልውጠታዊ የማላመድ ተግባር የሚከናወነው የማህበረ-ሥነምህዳራዊ ሥርዓታቸው ተጋላጭነት ከፍተኛ ለሆኑ ቦታዎችና የአየር ንብረት ለውጥ አደጋ ከ‘ኢንክሪመንታል’ ማላመድ ተግባር አቅም በላይ በሚሆንበት ጊዜ መሆኑን ነው። በኢትዮጵያ ቀደም ባሉት ጊዚያት የታዩት ተለዋዋጭነትና አስከፊ ክስተቶች፣ አገሪቷ ለክስተቶቹ የመጋለጥ ዕድሏ ከፍተኛ እንደሆነ አመላካቾች ናቸው። ሊያደርስ የሚችለው ተፅዕኖም የአገሪቷን GDP በ10% ያህል ሊያስቀንስ የሚችል መሆኑ ተገምቷል። ይህም ልውጠታዊ ማላመድን የመተግበር አስፈላጊነትን ያረጋግጥልናል።

አሁን ባለው ሁኔታ አገራችን ለልውጠታዊ ማላመድ ተግባር የሚበጅ ትክክለኛ ፖሊሲና ተቋማዊ ማዕቀፎችን አዘጋጅታለች። ከካርበን ነፃ የአየር ንብረት ተስማሚ አረንጔዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂን ለመገንባት ግልፅ የሆነ ብሔራዊ ርዕይና የፖሊሲ ማዕቀፍ ተቀርጿል። በቅርቡ በሚንስትር ደረጃ የተቋቋመው የአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ መስሪያ ቤትም የፖለቲካ ቁርጠኝነት እንዳለ የሚያሳይ ነው። የአየር ንብረት ተስማሚ የአረንጔዴ ልማት ስትራቴጂን ለመተግበር የሚያስችል በቅጡ የተደራጀ ተቋማዊ አወቃቀር ተፈጥሯል። በሚንስቴሮች የተዋቀረ ኮሚቴም ቁጥጥርና ማስተባበሩን በበላይነት ይመራል። ግብርናን በመሳሰሉ ቁልፍ ዘርፎችም፣ የአረንጔዴ ልማት ቡድኖችና ንዑስ ቡድኖች ተመስርተው ሥራውን እስከ ወረዳ ድረስ በማቀላጠፍ ያግዛሉ። ከመንግስታዊ አካላት ውጪ ያሉ ባለድርሻዎችም እንዳስፈላጊነቱ የሚሳተፉበት መንገድም ተበጅቷል። ከተለያዩ የአየር ንብረት ጥበቃ ተቆርቋሪዎች ከሚገኘው የገንዘብ ድጋፍ የአረንጔዴ ልማትን ወደሚተገብሩ አካላት በቀጥታ የሚደርስበት ዘዴም ተቀይሷል።

ከዚህም በተጨማሪ የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ፣ በአብዛኞቹ የአገሪቷ የልማት ፖሊሲዎችና ፕሮግራሞች ውስጥ ዋነኛ ትኩረት ተሰጥቶት እንዲካተት ሆኗል። ለምሳሌም- በግብርናና ውሃ ልማት ዘርፎች፣እንዲሁም በመጀመሪያውና በሁለተኛው የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ ተካቶ ይገኛል። እየተካሄዱ ያሉት የውሃ ሃብት፣ የግብርናና ምግብ ዘርፍ፣ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች እና ኢነርጂ ቆጣቢ ምድጃዎችን የማሰራጨት እንቅስቃሴዎች የአየር ንብረት ተስማሚ አረንጔዴ ልማት ፕሮጀክቶች እየተተገበሩ መሆኑን ያመለክታሉ። በተመሳሳይ መልኩ አገሪቷ የአረንጔዴ ልማት ስትራቴጂን እንዲሳካ ተቋማትን ለመቅረፅ፣ ዕቅዶችን ለመከታተል፣ የትግበራ ግብዓቶችን ለማሟላትና፣ ፕሮጀክቶችን ለማስጀመር እያደረገችው ያለው ትጋት ምስጋና የሚያስቸር ነው። ከዚህ ባለፈም፤ በመሠረተ ልማት፣ በትምህርትና በጤና ላይ የሚካሄዱ መደበኛ የልማት ሥራዎች ለማላመድ ትግበራ ግብዓት የሚሆኑ ናቸው። በእኔ አመለካከት፣ እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት በሙሉ ከልውጠታዊ የማላመድ ትግበራ ጋር የተቆራኙ ናቸው። እንዲያም ሆኖ ግን አንገብጋቢ የሆኑ የዕውቀት ክፍተቶች መኖራቸው አይካድም። ስለዚህም ለውሳኔ አሰጣጥ የሚያገለግሉ በጣም አስፈላጊ መረጃዎችን ለማግኘት ቅድሚያ ትኩረት በሚሰጥባቸው ጉዳዮች ላይ የምርምር ስራ መከናወን ይኖርበታል።

 

    ወደ 2 ዲ.ሴ. እያሻቀበ ከሚመጣው ሙቀት ጋር ተጣጥሞ ለመኖር ሲታሰብ ያለው የዕውቀት ክፍተትና የምርምር ስራ አስፈላጊነት

የአየር ንብረት ተስማሚ አረንጔዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት አገራችን እየጣለች ያለችው መሠረት መሻሻል የሚያሳይ ቢሆንምርዕዩን ወደተግባር ቀይሮ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተስማሚ ወደሆነ አረንጔዴ ልማት በማሳደግ ሂደት ግን ከፍተኛ ተግዳሮት ያጋጥማል። በዚያ ላይ የምርምር ሥራን የሚጠይቁ የዕውቀት ክፍተቶችም አሉ። በእኔ አስተሳሰብ ዋነኛ የዕውቀት ክፍተቶችንና የምርምር ሥራ አስፈላጊነትን እንደሚከተለው አቀርባለሁ።

 

የአየር ንብረት ተስማሚ አረንጔዴ ልማት በሚለው አሳብ ላይ ጥርት ያለ ዕውቀት መያዝ

ችግሩ የሚጀምረው የአየር ንብረት ተስማሚ አረንጔዴ ኢኮኖሚ የሚለውን አሳብ ጥርት አድርጎ ካለመረዳት ነው። የአየር ንብረት ተስማሚ ኢኮኖሚ ምን መምሰል አለበት? የአየር ንብረት ተስማሚ አርብቶአደርነት ምን ይመስላል? አየር ንብረት ተስማሚ ማሽላ ተኮር የእርሻ ስርዓት ምን መምሰል አለበት? የሚሉትን በአግባቡ መገንዘብ ያስፈልጋል። የአየር ንብረት ተስማሚነት ለሚለው ሃረግ በተለምዶ የሚሰጠው ትርጉም “ጫናን ተቋቁሞ መቀጠልን፣ መላመድንና ወደፊት የሚመጡ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖዎችን ለመቋቋም ወደሚያስችል አቋም በሂደት በመለወጥ ዝግጁ መሆን” የሚል ነው። እንዲህ አይነቱ ትርጔሜ በራሱ ሌላ ትርጉም የሚያስፈልገው ነው። የአረንጔዴ ልማት የሚለው አሳብ ደግሞ በባሰ ሁኔታ ነው የተተረጎመው። ብዙ ትርጉሞች ቢኖሩትም በብዛት የሚነገረው ግን“አረንጔዴ ኢኮኖሚ ማለት የሰዎችን ጤንነት የሚያሻሽል፣ማህበራዊ ፍትህን የሚያሰፍን፣ የአካባቢ ጉዳትንና ሥነምህዳራዊ ጉድለቶችን በተጨባጭ የሚቀንስ ሲሆን አነስተኛ የካርበን መጠን የሚጠቀም፣ ለሃብት ብክነት የማይዳርግ፣ ሁሉን አካታች ነው” የሚለው ነው። ይሄ ራሱ ጥርት ያለ አገላለፅ አይደለም። እንዲህ አይነቱ የሃሳብ ጥራት መጔደል ደግሞ በሥራው ላይ የሚታዩ መሻሻሎችንና ስኬቶችን በአግባቡ ለማወቅ፣ ቁጥጥርና ክትትል፣ ግምገማም ለማካሄድ አዳጋች ሁኔታን ይፈጥራል። በሌላ አነጋገር የአየር ንብረት ተስማሚነት አረንጔዴ ኢኮኖሚ ምንድን ነው? ምን ምንንስ ያካትታል? እነዚህስ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ምንድን ናቸው? የሚለውን በግልፅ ልናውቅ ይገባል። እንደዚያ በሚሆንበት ጊዜ ነው ወደ ልውጠታዊ ማላመድ የምናደርገውን ግስጋሴ  በልበሙሉነት ልናረጋግጥ የምንችለው።

 

ስለ አየር ንብረት ለውጥ የሚወጡ አመላካች መረጃዎችና ስለሚያስከትለው ተፅዕኖ የሚቀርቡ ጥቆማዎች አጠራጣሪነት

የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ በሚሠጡ መረጃዎች ላይ አመላካች የሚለው ቃል ትንበያ ከሚለው ቃል ይልቅ ጥቅም ላይ ይውላል። ይህም የአየር ንብረት ለውጥን ቁልጭ አድርጎ መተንበይ እንደማይቻልና መረጃዎቹ ውስጥ ጥርጣሬ እንደሚኖር አፅንዖት የሚሰጥ ነው።

የአየር ንብረት ለውጥ አመላካች መረጃዎች አጠራጣሪነት ከሦስት ዋነኛ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ የሚፈጠር ነው።

1.       ከተፈጥሮዓዊ የአየር ንብረት ተለዋዋጭነት ጋር

2.       ወደፊት ወደከባቢ ከሚለቀቁ ሙቀት አማቂ ጋዞች ጋር

3.       ለአየር ንብረት ጥናት ከሚያገለግሉ ሞዴሎች ጋር

የአየር ንብረት ለውጥ አመላካች መረጃዎች ላይ ግድፈት ካለ በተመሳሳይ ሁኔታ የተፅዕኖ ግምገማውም ትክክለኛነት አጠራጣሪ ይሆናል ማለት ነው። ከዚህ በተጨማሪም የተፅዕኖ መገምገሚያው ዘዴ (ሞዴል) ብቃት ላይም ሙሉእምነት ስለሌለ በየጊዜው እየተሻሻለ የሚሄድ ነው። የተለያዩ ቦታዎች ከሙቀት መጠን መጨመር ጋር በተያያዘ የሚያሳዩት መላመድ በተለያየ መንገድ (ሞቃታማ፣ ርጥባማ እና ደረቃማ በመሆን) ስለሆነ እንዲሁም በተለያዩ የጊዜ ገደቦች የተለያየ የአየር ንብረት ሊከሰት የሚችልበት ዕድል የሰፋ በመሆኑ፤ ልውጠታዊ የማላመድ ዘዴን ለመተግበር የሚደረገውን ጥረት እጅግ አዳጋች ያደርገዋል።

በአንዳንድ የምድር አካባቢዎች አዎንታዊ፣ በሌሎች ደግሞ አሉታዊ ተፅዕኖ በማድረስ በአማካይ የአለም ሙቀት መጠን ወደ 2 ዲ.ሴ. እያሻቀበ ባለበት በአሁኑ ጊዜ የአካባቢያችንንና በዙሪያችን ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ ገፅታ በተሻለ መንገድ ለመረዳት የሚያስችል የምርምር ሥራ አስፈላጊ ሆኖ ይገኛል። የዚህም ውጤትም ዕቅዳችንን የተሳለጠ ያደርገዋል።

 

የልውጠታዊ ማላመድ እንቅፋቶችና ውስንነቶች

በልውጠታዊ ማላመድ ዘዴ የአየር ንብረት ተስማሚ ኢኮኖሚ ለመገንባት የማላመድ ሥራዎች በስፋት ሊተገበሩ ይገባል። በንድፈ አሳብ ደረጃ የተለያዩ አማራጮች አሉ። እነዚህም፣ የቴክኖሎጂ፣ የፖሊሲና ተቋማዊ፣ ገበያ ተኮር፣ ወዘተ በማለት ሊዘረዘሩ ይችላሉ። እነዚህን አማራጮች በተግባር ለማዋል ግን እርስበርስ የተጠላለፉ ብዙ እንቅፋቶች አሉበት። እንቅፋቶች ናቸው የሚባሉት ጉዳዮች የማላመድ ተግባርን ለማቀድም ሆነ ለመተግበር እክል በመፍጠር አማራጮች እንዲጠቡ የሚያደርጉ ናቸው። እንቅፋቶቹ ከተቋም አሰራር፣ ከገንዘብ፣ ከቴክኖሎጂ፣ ከአቅም፣ ከተነሳሽነት እና ከመሳሰሉት ጋር የተያያዙ ናቸው። ከእንቅፋቶቹ በባሰ መልክ ደግሞ ማላመድ እንዳይተገበር የሚገቱ ውስንነቶች አሉ። ከሆነ ገደብ ባለፈ ማላመድን መተግበር የማይቻልበት ሁኔታ ይፈጠራል። ለአየር ንብረት ለውጥ የማላመድ ተግባርን ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ መተግበር ይቻላል ተብሎ የሚታሰበው ከልክ ያለፈ ተስፈኝነት በምርምር ውጤቶች የተደገፈ አይመስልም። ለምሳሌ፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በግብርና፣ በመሬት አጠቃቀምና ኢነርጂ ዘርፎች ላይ በስፋት ለመተግበር ስናስብ ምን አልመን ነው የሚለውን ማጤን ያስፈልጋል። ለዚህም ሲባል የአየር ንብረት ተስማሚ ኢኮኖሚ ስንገነባ የሚያጋጥሙ እንቅፋቶችንና ሊኖሩ የሚችሉ ውስንነቶችን ለመረዳት የሚያስችል የምርምር ሥራ አስፈላጊ ይሆናል።

   የተገኙ ውጤቶችን አንድ በአንድ በመዘገብ የመረጃ ቋት ማበጀት

የልውጠታዊ ማላመድ ዘዴ በሚተገበርበት ጊዜ የሚገኙ ውጤቶችን ተከታትሎ መዘገብና በመረጃ ቋት ውስጥ ማስፈር አስፈላጊ ነው።እንዲህ በማድረግም የትግበራውን ውጤታማነት መገምገም፣ ወደፊት ትኩረት ሊሰጥባቸው የሚገቡ ጉዳዮችን መለየት፣ በሁሉም ደረጃ ለሚገኙ የጉዳዩ ባለቤቶች ስለተገኙት ውጤቶችና ተሞክሮዎች ማጋራት፣ ሃብትን በአግባቡ መጠቀም እና ለህዝብም በግልፅ ማሳወቅ ይቻላል። የአየር ንብረት ተስማሚነትን ስናጎለብት ስኬትን መዘርዘርና መለካት በግልፅ የሚታይ ጉዳይ አይሆንም። ለምሳሌ የተጋላጭነት መጠንን ስንቀንስ  የሚገኙ ለውጦችን በቀላሉ ለመገንዘብ ያዳግታል ወይንም ከብዙ አመታት በኌላ የምንረዳው ይሆናል። ከዚህም በተጨማሪ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ የሚያደርጉ የማላመድ ስትራቴጂዎች በጊዜ ሂደት ጎጂ ሊሆኑ ወይንም ጥቅም ላይ ከዋሉበት ዘርፎች ባለፈ በሌሎች ዘርፎች፣ ማህበረሰቦችና ማህበራዊ ቡድኖች ላይ የተጋላጭነት መጠንን የሚያባብስ አሉታዊ ውጤት ሊኖራቸው ይችላል። ስለዚህ በዚህ መንገድም የምርምር ሥራ አስፈላጊ ሆኖ ይገኛል። ለምሳሌ፣ ስኬታማነትን በግልፅ ለመገንዘብ የሚረዱ አግባብነት ያላቸውን ዘዴዎች ለማዳበር የሚያስችል ምርምር መስራት ያስፈልጋል። በሌላ በኩል፣ ተገኘ የተባለው መልካም ውጤት በተለያዩ ጊዚያት፣ በተለያዩ ቦታዎች፣ በተለያዩ ዘርፎችና ማህበራዊ ቡድኖች ላይ ሊኖራቸው የሚችለውን ተፅዕኖ ሊገመግም የሚያስችል ዘዴን ለማዳበርም የምርምር ሥራ ያስፈልጋል።

 

  መደምደሚያ

ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ተለዋዋጭነት ሳቢያ ጉዳት እየደረሰባት ያለች አገር ነች። ድርቀት ከአየር ንብረት ተለዋዋጭነት፣ ድርቅና ጎርፍ ጋር በመጎዳኘት  ከአየር ንብረት ጋር ተያያዥ የሆኑ አስከፊ አደጋዎችን ያስከትላሉ። ወደፊትም በከፍተኛ ደረጃ መጠኑን በመጨመር በተደጋጋሚ ሁኔታ ይከሰታል ተብሎ ይጠበቃል። ይህንን ግምት ውስጥ በማስገባት የአገራችን መንግስት የአየር ንብረት ተስማሚነት አረንጔዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችል መሠረት በመጣል እመርታ አሳይቷል። ሆኖም ይህንን ርዕይ መሬት ላይ አውርዶ ለመተግበር የሚገቱ ብዙ ተግዳሮቶች አሉ። ይህንን ተግዳሮት ለማሸነፍ የሁላችንንም ጥረት ይጠይቃል። ከዚህ አንፃር፣ ይህ ህዝባዊ ገለፃና የውይይት መድረክም ጠቃሚ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው ተስፋ አለኝ።        

(ይህ ጹሑፍ በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ሳይንሳዊ ገለፃና ውይይት መድረክ የቀረበ ነው።)¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
558 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us