ማስታወቂያ ነክ ወጎች

Wednesday, 20 July 2016 13:54

 

 

በይርጋ አበበ

 

ማስታወቂያ ምንድን ነው? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ እንደ አብዛኞቹ የአገራችን ምሁራን “እንትን የተባሉት አሜሪካዊ ምሁር እንትን በሚለው መጽሐፋቸው እንደገለጹት” ብዬ ማስረዳት አልፈልግም። ማስታወቂያ ማለት መልዕክትን ለሚመለከተው አካለ በተገቢው መንገድ ማድረስ የሚረዳ የመገናኛ ዘዴ ነው። ነገር በምሳሌ ጠጅን በብርሌ እንዲሉ ይህንን ገለጻም በምሳሌ ለማስረዳት ልሞክር።


ለምሳሌ የአቡሽ እናት ወይዘሮ ማለፊያ ቡና አፍልተው ወይዘሮ ብርቄን ጠርተው አብረው መጠጣት ቢፈልጉ አቡሽን “ሂድና እማማ ብርቄን ቡና ፍልቷል ቶሎ ይምጡ ብለህ ንገራቸው” ብለው የላኩት አቡሽ ሲበር ሂዶ የታዘዘውን ይፈጽማል። መልዕክቱ በትክክል መድረሱ የሚታወቀው እማማ ብርቄ በሰዓቱ ከመጡ ነው፡፡ አለዚያ አቡሽ ማስታወቂያውን አየር ላይ አላዋለውም ይባላል። ወይም ደግሞ አቡሽ ማስታወቂያውን (መልዕክቱን) በትክክል አላደረሰም ማለት ነው።
ግን አቡሽ እየበረረ ሂዶ እማማ ብርቄን ቡና እንዲጠጡ እንዲህ ብሎ ቢናገርስ? “እማማ ብርቄ የኔ እናት የፈረስ ጭራ የመሰለ ቡና አፍልታ እየጠበቀችዎ ነው ያላት ቦታ ውስን ስለሆነ አሁኑኑ ይነሱና አብረውኝ ይሂዱ» ብሎ ቢናገር እማማ ብርቄ ሊያምኑት ይችላሉ?


ወደ ዋናው ርዕሰ ወጋችን እናምራና ማስታወቂያ ነክ ወጎቻችንን በክረምቱ በቆሎ እያዋዛን ብናወጋ ይበጀናል ያልኩትን ላውጋችሁ። ክረምት ሲመጣ ወይም ክረምቱ ሲጋመስ ተመልካቹን ከሚያሰለቹት የቴሌቭዥን ማስታወቂያዎች መካከል የትምህርት ቤት እና የትምህርት መሳሪያዎች ማስታወቂያዎች ግንባር ቀደሞቹ ናቸው። እነዚህ ድርጅቶች የሚያስነግሩት ተመሳሳይ ይዘት ያላቸውን መልዕክቶችን ሲሆን ሁሉም “ያለን ቦታ ውስን ስለሆነ ይምጡና ይመዝገቡ”፤ “ስለትምህርት ጥራታችን ተማሪዎቻችን ምስክሮቻችን ናቸው”..... ወዘተ... አይነት የቃላት ጋጋታ ናቸው።


አንዳንዶቹ ደግሞ እንዲህ ይላሉ “ለውድ ተማሪዎቻችንና የተማሪ ቤተሰቦች እንኳን ደስ አላችሁ ትምህርት ቤታችን ድሮ ከሚሰራበት ህንጻ ራሱ ወዳስገነባው እና ለትራንስፖርት አመች ወደሆነው እንትን አካባቢ መዛወራችንን ስንገልፅ በታላቅ ደስታ ነው። በዚህ አጋጣሚ የነባርና አዲስ ተማሪዎች ምዝገባ መጀመራችንን እናበስራለን...” እሺ ትምህርት ቤቱ ከኪራይ ቤት ወደ ግል ንብረቱ መዘዋወሩ ለወላጆች የሚሰጠው ደስታ ምንድን ነው?


ሳስበው ይህ መልዕክት ሊተላለፍ ታስቦ የነበረው “ለክቡራን የተማሪዎቻችን ወላጆች እናንተ ለልጆቻችሁ የትምህርት ክፍያ የከፈላችሁት ገንዘብ መሬት በልቶት አልቀረም። ይኸው የራሳችንን ህንጻ እንድንገነባ አስችሎናል። በዚህ አጋጣሚ አዲሱ ህንጻችን የመቀበል አቅሙን በምናምን እጥፍ ያሳደገ ስለሆነ ልጆቸሁን ሊያስመዘግቡ ሲመጡ ቢያንስ አንድ የሰፈር ልጅ ይዘው በመምጣት ይተባበሩን” እንደዚህ ሊባል የታሰበ ይመስለኛል።


ሌላ ደግሞ የበዓል ሰሞን ሲቀርብ ይኸው ቴሌቪዥናችንን የሚቆጣጠሩት ድርጅቶች አሉ። “በዚህ በዓል ከየትኛውም ክፍል በባንካችን ገንዘብ ሲላክልዎ ወደ ባንካችን ሲመጡ በፍጥነት ይረከባሉ። በታማኝነታችንም ይደሰታሉ” ይላሉ። የባንክ አገልግሎቱ ገንዘብን በታማኝነት አስቀምጦ ለማስረከብ መሆኑን ዘንግተው ልጅ ለናቷ ምጥ አስተማረች አይነት ማስታወቂያ ይደብራል፡፡ ደግሞም እኮ ዓለም ሉላዊነትን በተላበሰችበት በዚህ ዘመን ገንዘበዎን በፍጥነት እናስረክበወታለን ማለት ለምን አስፈለገ? በዚህ ዘመን ገንዘብን ባንኮች ቶሎ ማድረስ ካልቻሉ ታዲያ ሰውየው መጥቶ እንዲሰጠን ያስባሉ?

ለመሰናበቻ


የኢትዮጵያ ምሕዋረ ድምፅ መስሪያ ቤት/ ኢትዮ ቴሌኮም/ ደግሞ አለ። ይህ ግዙፍና ሃገራችንን በኔትዎርክ ተኮር ስራዎች በማገልገል ብቸኛ የሆነው ድርጅት የደንበኞቹን እርካታ ለማሟላት የተለያዩ አማራጮችን ይጠቀማል። ከነዚህ አማራጮቹ መካከል ደግሞ በዓላት ሲመጡ፣ አንዳንድ ክብረ በዓላት ሲከበሩና ካርድ ስንሞላ የጽሁፍ መልዕክት መላኩ ይጠቀሳል። የቴሌን ተደጋጋሚ የጽሁፍ መልዕክት ለደንበኞቹ መላክ የተመለከቱ የሰፈራችን ልጆች እንዲህ ሲሉ ቧለቱ “ካርድ ስንሞላ አሁን የሞሉትን ካርድ በትክክል ተቀብያለሁ አሁን በሞሉት ካርድ መሰረት የስልክዎ ሂሳብ ዜሮ የሚሆነው እንደ አውሮፓዊያኑ የዘመን ቀመር በምናምን ዓመት ነው፣ እንኳን ለእንትን በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ እና የመሳሰሉትን መልዕክቶች እየላከ ያስደሰተንን ያህል በቅርቡ ደግሞ ባትሪያችንን ቻርጅ ስናደርግ እንዲህ የሚል የጽሁፍ መልዕክት ይልክልናል። የስልከዎ ባትሪ ሊሞላ ትንሽ ይቀረዋል እባከዎ ትንሽ ይጥብቁና በደንብ ይሙላለዎት ምን ያስቸኩለዎታል? የት ይሄዳሉ? ይላል። የቴሌን ማሳሰቢያ ሰምተን ትንሽ ታግሰን ባትሪያችንን በደንብ እስኪሞላ ጠብቀን ስንከፍተው ደግሞ አሁን በደንብ ሞልቶለዎታል ሙዚቃ፣ ጌምና ኢንተርኔት ካልተጠቀሙበት በትንሹ ለሶስት ቀናት ሊገለገሉበት የሚያስችል የባትሪ ክምችት አለዎት። የዚህ የባትሪ መጠን አገልግሎት የሚጠናቀቀው እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ከሶስት ቀን በኋላ ነው»። ቢበቃንስ? መልካም ጊዜ እየተመኘሁ ልሰናበት።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
611 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 170 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us