ኢትዮጵያ፡- ‘የእግዚአብሔር መንግሥት ምሥጢር ምድር!’

Wednesday, 20 July 2016 13:57

 

በፍቅር ለይኩን

 

‹‹ከዳዊት ከተማ … ከሳሌም፣ ከሰላም ከተማ ከኢየሩሳሌም … ንጉሥ ሰለሞን ንግሥተ ሳባን በክብር፣ በፍቅር … ከተቀበለባት ከቅድስት ከተማችን- ከኢየሩሳሌም ሰላምታን ይዤላችኹ መጥቼያለኹ …። ኢትዮጵያ በእስራኤል ልብ ውስጥ ናት፣ እስራኤልም በኢትዮጵያ ልብ ውስጥ ናት፤ ... እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ ... እግዚአብሔር አፍሪካን ይባርክ ... እግዚአብሔር የኢትዮጵያንና የእስራኤልን ወዳጅነት ይባርክ!!››


እነዚህ ጥልቅ በሆነ የወዳጅነት ፍቅር፣ ለሺህ ዘመናት በዘለቀ የሃይማኖት፣ የታሪክና የባህል ጥብቅ ቁርኝት፣ ትስስር በወለደው ልዩ ስሜት በአገራችን የተወካዮች ምክር ቤት መሰብሰቢያ የናኘ፣ ያስተጋባና ሞቅ- ደመቅ ባለ ጭብጨባ የታጀበ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር የቤኒአሚን ኔታናሁ ንግግር  ነው።


እንደሚታወቀው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር በአገራችን ባለፈው ሳምንት ለኹለት ቀናት ይፋዊ የሆነ ጉብኝት አድርገው በሰላም ወደ አገራቸው ተመልሰዋል። ይህ የኔታናሁ ጉብኝት ለኢትዮጵያ፣ ለአፍሪካ ቀንድና ለቀጣናው ያለውንና ወደፊትም ሊኖረው የሚችለውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ለፖለቲካል ኢኮኖሚስት ምሁራንና ተንታኞቻችን እንተወውና በዚህች አጠር ያለች ጽሑፌ በአገራችን በእስራኤልና በኢትዮጵያ መካከል ሺህ ዘመናትን ስላስቆጠረው ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ ግንኙነትና የባህል ትስስር ጥቂት የታሪክ እውነቶችን በመምዘዝ- ‹ሀገረ ኢትዮጵያ የእግዚአብሔር መንግሥት ምሥጢር ምድር› መኾኗን የሚያስረግጡ መለኮታዊ ትንቢቶችን በማንሣት አብረን እንቆይ ዘንድ ወደድኹ።


እግረ መንገድም በዚህ ከሰሞኑን የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚ/ር በአገራችን ባደረጉት ይፋዊ ጉብኝት ሳቢያ አንድ የታሪክ እውነት ደጋግመን ሰማን። ይኸውም፡- ‹‹ኢትዮጵያ የምትባል አገር ታሪኳ የ፻/የ፻፶ ነው።›› ብለው በአደባባይ የሚሟገቱና የሚሞግቱ የኢሕአዴግ ሹማምንት/ብሔርተኛ ፖለቲከኞቻችን ሳይቀሩ በኢትዮጵያና በእስራኤል መካከል ከሦስት ሺህ ዘመናት በላይ ስላስቆጠረው ግንኙነት በኩራት፣ በድፍረት ሲናገሩ በትዝብት ሰምተናቸዋል። ይህን እንደ የአመቺነቱ በታሪካችን ላይ የሚደረገውን ሸፍጥና መገለባበጥ ለጊዜው ወደጎን እንተወውና ወደቀድመው ቁም ነገራችን እንመለስ።


ጽሑፌን በአንድ ገጠመኜ ልጀመር። ከጥቂት ዓመታት በፊት የሥራ ባልደረባ በነበርኩበት በአንጋፋው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም እስራኤላውያኑ ፫ኛውን ዓለም አቀፍ የአይሁዳውያንን ኮንፈረስ አካሂደው ነበር። በዚህ ለሦስት ቀናት በዘለቀውና ከመላው ዓለም በመጡ ታላላቅ ምሁራንና ተመራማሪዎች የተለያዩ የጥናት ወረቀቶችን ባቀረቡበትና አስደናቂ በሆነ ዐውደ ርእይ በታጀበው የአይሁዳውያኑ ኮንፈረስ ማብቂያ ላይ ከእስራኤል አገር ከመጡ የኮንፈረንሱ ተሳታፊ ወጣቶችና ኢትዮጵያውያን ቤተ-እስራኤላውያን ጋር በመሆን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በቅጥር ግቢ ውስጥ ዞር ዞር እያልን የማስታወሻ ፎቶግራፎችን አብረን ተነሥተን ነበር።


ለፍቶ ግራፍ መነሻነት ከመረጥናቸው ሥፍራዎች መካከል ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የባህል ማእከል አንዱ ነበር። ታዲያ ስለ ባህል ማእከሉ ገለፃ ከተደረገልን በኋላ የማስታወሻ ፎቶ ለመነሳት ወደ ባህል ማዕከሉ መግቢያ በር አመራን። ወደ በሩ እያመራን ሳለንም እስራኤላውያኑ ወጣቶች በድንገት "the David Star" ብለው በታላቅ ድምፅ ጮኹ። ግር ብለውም በባህል ማእከሉ መግቢያ በር ላይ ተሰልፈውና ዓይናቸውን ተክለው በልዩ ስሜት ውስጥ ሆነው በበሩ ላይ የተቀረፀውን የዳዊትን ኮከብ በአንክሮት ያስተውሉት ጀመር። ፈጠን ብለው ሁሉም ካሜራቸውን አውጥተው ይህን የአባቶቻቸው የታሪክ መዘክር የሆነ ቅርስ በናፍቆት፣ በስስትና በጉጉት በካሜራቸው ለማስቀረት ይጣደፉ ገቡ።


በእስራኤላውያኑ ወጣቶች ፊት ላይ ይነበብ የነበረው ስሜት እጅግ ጥልቅና ልዩ፣ መደነቅንና አንዳች አግራሞትን የተመላ ነበር። በእርግጥም እንዲህ ዓይነቱ ስሜት ቢንጸባረቅባቸው አይፈረድባቸውም አልኩ ለራሴ። እንዲያ ዓለም ሁሉ ጠልቷቸውና ተጸየፏቸው፣ ዘራቸው እንደ ጨው ዘር በዓለም ሁሉ የተበተኑ፣ መድረሻና መጠጊያ ያልነበራቸው መፃተኛና ስደተኛ ሕዝቦች ነበሩና።


በሰው ልጅ ታሪክ ተፈጽሞ የማያውቅና ወደፊትም ይፈፀማል ተብሎ ለማሰብ በማይቻል ዘግናኝና አሰቃቂ በሆነ መንገድ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖቻቸው በናዚ ካምፕ በተፈጁበትና ባለቁበት፣ ቆዳቸው እየተገፈፈ፣ የሰውነታቸው ስብ እየወጣ ለሳሙና መስሪያ እንዲውል የተደረገበትን አስቃቂ የወገኖቻቸውን የታሪክ ስብራት በልባቸው ለተሸከሙ ለእነዚህ አይሁዳውያን ወጣቶች ይህን የጥንት የአባቶቻቸውን የክብር ታሪክና ቅርስ የሚዘክር ማስታወሻ ዓለም ‹‹የረሃብና የጦርነት ምድር›› በሚል ቅጽል በሚያውቃት በአገረ ኢትዮጵያ መገኘቱ ልዩ አግራሞትንና መደነቅን ቢያጭርባቸው የሚገርም አይሆንም።


"ኢየሩሳሌም ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ፣ ምላሴ ከትናጋዬ ጋር ይጣበቅ።" በሚል ፅኑ ቃል ኪዳን፣ ናፍቆትና ስስት በእያንዳንዱ አይሁዳዊ የልብ ጽላት ውስጥ የታተመችው እስራኤል- ባለ መታዘዝ ጠንቅ፣ በኃጢአቷና በዓመፃዋ የተነሣ በታሪኳ በተደጋጋሚ በአምላኳ የቅጣትና የመዓት በትር የተመታች አገር ናት። በዚህ ምድሪቱ ላይ ከኾነው መቅሰፍት መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው እስራኤላውያኑን ከ፩ ሺ ፰፻ ዓመታት በላይ አገር አልባ ያደረጋቸው የ፸ው ዓ.ም. ውድመት ነው።


ከአባቶቻቸው ከአብርሃም ጀምሮ እንደ አምላካቸው የሚወዱትና የሚያከብሩት መሪያቸው ሙሴ፣ ንጉሥ ዳዊትና አይሁዳውያኑ ነቢያት ትንቢት የተናገሩለትንና ተስፋ ያደረጉትን መሢሑን- የሕያው የእግዚአብሔርን ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስን በመግፋታቸው የተነሳ በ፸ ዓ.ም. የሚኮሩበት ቤተ መቅደሳቸው፣ ከተማቸው ኢየሩሳሌም በሮማውያን ወራሪዎች እንዳይኾኑ ኾና በአሰቃቂ ኹናቴ ወደሙ።


ይህ ጦርነት በአይሁዳውያኑ ላይ ያደረሰውን ሃይማኖታዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስ የጻፈው ዕውቁ አይሁዳዊው ታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስ- ታላቂቱ የዳዊት ከተማ፣ ኢየሩሳሌም የፍርስራሽ ክምር ኾነች። ነቢየ እግዚአብሔር ሚኪያስ አስቀድሞ በትንቢቱ፡- ‹‹ስለዚህ በእናንተ ምክንያት ጽዮን እንደ እርሻ ትታረሳለች፤ ኢየሩሳሌም የድንጋይ ክምር ትሆናለች። የቤቱም ተራራ እንደ ዱር ከፍታ ይኾናል።›› እንዳለው ቅድስቲቱ ከተማ የፍርስራሽ ክምር ሆነች። ከዚህ አሰቃቂ ጦርነትና ከረሃብ እልቂት የተረፉት አይሁዳውያን ወገኖች ደግሞ ተማረኩ፣ በባርነት ተሸጡ፣ ከአባቶቻቸው ምድር ተፈናቀሉ። ይለናል።


‹‹The Great Controversy›› በሚለው አነጋጋሪ መጽሐፏ የምትታወቀው የታሪክ ተመራማሪና ጸሐፊ የኾነችው እንግሊዛዊቷ ኤለን ጂ. ኋይት ይህን ዘግናኝ እልቂት በዚህ መጽሐፍዋ ውስጥ እንዲህ ተርከዋለች። በሮማውያን ሠራዊት ከበባ ሥር ወደቀችው እስራኤል ሕዝቦቿና ሠራዊቷ በረሃብና በውኃ ጥም እልቂት ይረፈረፉ ጀመር። በእነዛ ቀውጢ ቀናት በአካባቢያቸው የነበሩ ነገሮች ሁሉ ለምግብነት ዋሉ። ረሃቡ እየገፋ፣ እየባሰ ሲመጣ ደግሞ አይሁዳውያኑ እርስ በርሳቸው ሳይቀር ተበላሉ።


በሮማውያኑ ከበባ ሥር የወደቁትና በቤተ መቅደሱ የተተገኑት አይሁዳውያን ደግሞ በአሕዛብ እጅ አንሞትም በማለትም እርስ በርሳቸው በሰይፍ ተራራዱ፤ ያ ቅዱስ መቅደስ በደም አበላ ተመታ። የደም ጎርፍ የቤተ መቅደሱን በር አልፎ ወደ ውጪ ጎረፈ። በመጨረሻም ሮማውያኑ ወታደሮች በቤተ መቅደሱ ላይ እሳት ለቀቁበት፤ ያ አይሁዳውያኑ የሚኮሩበት አባቶቻቸው መቅደስ ለእግዚአብሔር ፍርድ ተተወ።


ሲቀርብም ከተማዋን አይቶ አለቀሰላት፤ እንዲህ እያለ፡- ለሰላምሽ የሚሆነውን በዚህ ቀን አንቺስ ስንኳ ብታውቂ፣ አሁን ግን ከዓይንሽ ተሰውሮአል። ወራት ይመጣብሻልና ጠላቶችሽም ቅጥር ይቀጥሩብሻል፣ ይከቡሻልም። በየበኩሉም ያስጨንቁሻል። አንቺንም በአንቺ ውሰጥ የሚኖሩትን ልጆችሽን ወደ ታች ይጥላሉ። በአንቺም ውስጥም ድንጋይ በድንጋይ ላይ አይተውም፣ የመጎብኘትሽን ዘመን አላወቅሽምና።›› ሉቃ. ፲፱፣፵፩-፵፬።


እንዳለ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኢየሩሳሌም የሰላሟን ጌታ በመግፋቷ የተነሣ ዛሬም ድረስ የጦርነትና የእልቂት ምድር ኾና ዘልቃለች። ለ፩ ሺህ ፰፻ ዓመታት በላይ አገር አልባ ሆነው እንደ ጨው ዘር ተበትነው የኖሩት አይሁዳውያን እ.ኤ.አ. በ1948 ዓ.ም. ዳግመኛ መንግሥት ኾነው ተቋቋሙ።


ይህች ደጋግማ በአምላኳ የቅጣት በትር የተመታች እስራኤል ከሀገራችን ጋር ያላት ታሪካዊ ትስስር ስንመለከት ውሉ የሚመዘዘው እንደ አምላካቸው በሚወዱትና በሚያከብሩት በነጻ አውጪያቸው በሊቀ ነቢያት፣ በትሑቱ ሙሴ ዘመን ነው። የሕዝበ እስራኤል መሪ ሙሴ የትዳር አጋሩ ትኾነው ዘንድ የመረጣት ሴት ኢትዮጵያዊቷ ነበረች። በዚህ ምርጫው ወገኖቹ አሮንና ማርያም ቢቃወሙትም ምርጫው የሙሴ ብቻ ሣይሆን የአምላክ ፈቃድ ነበረበትና ሙሴ ከአፍሪካ ምድር- የእግዚአብሔር የፍቅርና የጥበብ መዝገብ ተምሳሌት ከኾነችው ኢትዮጵያዊት ሴት ጋር በትዳር ሕይወት ተሳሰረ።


ይህ በፍቅርና በጥበብ ተሸምኖ በተዳወረ በቅዱስ ትዳር የተጀመረ የፍቅር ግንኙነት በኋለኛው ዘመንንም የጥበብ ፍቅር ልቧን ካሸፈተውና ነፍሷን ካስመነነው ኢትዮጵያዊቷ ንግሥት ሳባ/ማክዳ/አዜብ ዘመን ዳግመኛ ከንጉሥ ሰለሞን ጋር በሌላ የፍቅር ቃል ኪዳን ውል ታደሰ። ይህችን የጥበብ ርሃብተኛ የአክሱምን ንግሥት ሌትና ቀን እረፍት ነስቷትና ነፍሷን አስጨንቋት፣ ባሕር ተሻግራ፣ ድንበር አቋርጣ በጆሮ የሰማችውን በዓይኗ አይታ ለማረጋገጥ በመፈለግ ወደ ኢየሩሳሌም እንድትገሠግሥ ያደረጋት ምስጢር አንድና አንድ ነገር ብቻ ነበር። እርሱም ዓለም ሁሉ በአግራሞት የተመላበት፣ ተኣምር ነው የተሰኘበትንና የተደነቀበትን- ከእርሱም በፊት ከእርሱም በኋላ ያልሆነ የእስራኤል አምላክ ‹ያሕዌ› ለንጉሥ ሰለሞን የሰጠው ታላቅ ‹ጥበብና ማስተዋል› ነበር።


ጥበብን ሽታ፣ ጥበብን ተጠምታ፣ የልቧን ምስጢር ሁሉ ልታጫውተውና እንቆቅልሽዋንና የነፍሷን ጥያቄም ሁሉ ይፈታላት ዘንድ ከምድር ዳርቻ በብዙ ስጦታዎችና አጀብ ወደ ኢየሩሳሌም የተጓዘችው ንግሥተ ሳባ የኢትዮጵያ ንግሥት እንደነበረች የቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ ሊቃውንቶች ያስረዳሉ። እንግሊዛዊው ታሪክ ሊቅ ፕ/ር ዊልያም በጅ ‹The Histroy of Queen Sheba› በሚለው ዳጎስ ያለ መጽሐፋቸው ውስጥ ንግሥቲቱ ያስከተለቻችውን የአጃቢዎች ብዛትና የስጦታ መጠን በሚያስገርም ኹኔታ በዝርዝር ገልጸውታል። ንግሥተ ሳባ ለንጉሥ ሰለሞን የወርቅ፣ የከበሩ ማዕድናትና እንዲሁም በዓይነትና በቁሳቁስ ይዛ የሄደችው የስጦታ መጠን በገንዘብ ሲለካ ዛሬ አገራችን የምትመድበውን ዓመታዊ በጀት በብዙ እጥፍ የሚያስከነዳ መሆኑን ማወቅ ወይ ነዶ አያሰኝም ትላላችሁ …!?


ማንኛውም ይህን ዓለም ሁሉ ዕፁብ ድንቅ በማለት ዝናውን በአጥናፈ ዓለም ሁሉ የናኘለትን የሰለሞንን ጥበብ ከጆሮ ባለፈ በዓይኗ ልታየውና ልትደነቅበት አክሱማይቷ፣ የእኛይቷ የጥቁር ምድር ዕንቁ በልቧ ወሰነች። እናም ንግሥት በልቧ እንዲህ ያለች ይመስለኛል፡- ‹‹ይህ በዝና፣ ‹በስማ ብለው› ብቻ በሩቅ የሚሳለሙት ሣይሆን በአካል ተገኝቶ ጆሮ ሊሰማው፣ ዓይን ሊያየው የሚገባ ድንቅ ጥበብ ነው…።›› እናም የነፍሷን ናፍቆት፣ የጥበብ ረኻቧን መፍትሔ ለመስጠት ንግሥተ ሳባ ቅሌን ጨረቄን ሳትል ቆርጣ ተነሣች።


ኢትዮጵያዊቷን ከዚህ ውሳኔዋ ሊያስቆማት የሚችል አንዳች ምድራዊ ኃይል አልነበረምና። እናም የተመኘችውን አደረገችው። ውሳኔዋ ተግባራዊ ሊሆን ያን ቅዱስ ቀን መጣ፤ በጥበብ ፍቅር ልቧ የነደደ፣ ነፍሷ የተመኘችውን እስክታገኝ እረፍት እምቢ ያላት ያቺ ገናና ልዕልት የከበረ ቤተ-መንግሥቷን ጥላ፣ ከሠራዊቷና ከሕዝቧ ተነጥላ ትመንን ዘንድ የጥበብ ፍቅር ግድ አላት፣ እናም ጉዞ ጥበብን ፍለጋ … ጉዞ ጥበብን ሐሰሳ … ‹‹መንገዶች ሁሉ ወደ ኢሩሳሌም ያቀናሉ!›› ስትል ለነፍሷ ጮኻ ተናገረች።


ይህ ታላቅና ታሪካዊ የሆነ ጥበብን ፍለጋ፣ ጥበብን ሐሰሳ የንግሥት ሳባ ጉዞ፡- ተራ ጉዞ፣ አልባሌ መንገድ አልነበረም። የነፍስ ጩኸት፣ ጥልቅ የሆነ ከልብ የመነጨ፣ የዘመናት ናፍቆት የታከለበት የጥበብን ፍለጋ ጉዞ- የከበረና ከጉዞዎች ሁሉ የላቀ ልዩ ጉዞ ነበር እንጂ። እናም በኋለኛው ዘመን የእግዚአብሔር ጥበብ የሆነ፣ የአብ ክንዱና ኃይሉ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአክሱማይቷን የጥበብ ርኻብተኛ ተጓዥ እንዲህ ሲል አወደሳት፣ ዘከራትም። ‹‹ንግሥተ አዜብ ከዚህ ትውልድ ጋር ተነስታ ትፈርደበታለች፣ የሰለሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳርቻ ድረስ መጥታለችና።››


‹‹ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይሻል፤ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም። … ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ። … ንግሥተ ዓዜብ በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥታ ትፈርድበታለች፤ የሰለሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳር መጥታለችና፣ እነሆም ከሰለሞን የሚበልጥ ከዚህ አለ።›› ማቴ ፲፪ ፣ ፴፰-፵፪።


በእርግጥም የዚህች ኢትዮጵያዊት ንግሥት የጉዞዋ የመጨረሻ አድራሻ ለጊዜው ሰለሞን ቢሆንም፤ ፍጻሜው ግን- የሰለሞን የጥበብና የማስተዋል ምንጭ የእግዚአብሔር ጥበብ፣ የአብ ክንዱና ኃይሉ የሆነው እርሱ በነቢያት ትንቢት እንደተነገረለት፣ ሱባኤ እንደተቆጠረለት በዘመኑ መጨረሻ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ሰው ሊሆን የፈቀደው የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነበር። ኢየሱስም በመዋዕለ ስበከቱ ለተከታዮቹ፣ ለደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው እንዲህ ብሎአቸው ነበር፡-


‹‹የምታዩትን የሚያዩ ዓይኖች ብፁዓን ናቸው። እላችኋለሁና፣ እናንተ ዛሬ የምታዩትን ብዙዎች ነቢያትና ነገሥታት ሊያዩ ወደዱ አላዩም፣ የምትሰሙትን ሊሰሙ ወደዱ አልሰሙም አለ።›› (ሉቃ. ፲፣፳፫- ፳፬።) የእኛዋ ንግሥተ ሳባ ያን ታላቅ ጥበብ፣ ያን ዕፁብ ጥበብ፣ ያን ሕያው ጥበብ፣ ያን ዘላለማዊ ጥበብ … እንደቀደሙ የአይሁድ አባቶች- እንደእነ አብርሃምና ሙሴ በናፍቆት በዓይነ ኅሊናዋ አሻግራ እያየችው በሩቅ የተሳለመችው ይመስለኛል- ይህች የጥበብ ርኻብተኛ፣ ይህች የጥበብ ስደተኛ፣ የጥበብ ረኻብና ናፍቆት ልቧን ያጀገናት አፍሪካዊ፣ ኢትዮጵያዊ፣ ሳባዊ ታላቅ ንግሥት።


እናም የዚህች ኢትዮጵያዊት ታላቅ ንግሥት ይህ የከበረ ጉዞዋ በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል እንዲጻፍላት ሆነ። የልጅነትና ክብር፣ ኪዳንም የሕግም መሰጠት፣ የመቅደስም ሥርዓት፣ የተስፋውም ቃል ለእነርሱ የሆኑ አይሁዳውያኑ ግን ለዘመናት አባቶቻቸው ሊያዩ የተመኙትን፣ በሩቅ ሆነው የተሳለሙትን፣ ሱባኤ የቆጠሩለትን፣ በናፍቆትና በስስት የጠበቁትን- በሥጋ የተገለጠውን ያን ዕጹብና ታላቅ ጥበብ፣ የእግዚአብሔርን ሕያው ልጅ ክርስቶስን ሊቀበሉት አልወደዱም።


አባቶቻቸው በብዙ ናፍቆት የጠበቁትንና የጓጉለትን ይህን ጥበብ፣ እውነትና ሕይወት የኾነው፣ ይህ ዘላለማዊ ፍቅር በዓይናቸው ፊት ክብርና ሞገስን አላገኘም… እናም ሊያስወግዱት ወደዱ። ‹‹ወደገዛ ወገኖቹ መጣ ግን የገዛ ወገኖቹ አልተቀበሉትም።›› እንዲል ቅዱስ መጽሐፍ።


እነዚህ የጻድቁን መምጣት አስቀድመው ትንቢት የተናገሩትን አባቶቻቸውን ነቢያትን ያሳደዱና የገደሉ ‹‹አንገተ ደንዳና ሕዝቦች›› በኋለኛው ዘመንም ሊቀበሉት ያልወደዱትንና የገፉትን መሢሑን- እግዚአብሔርን ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስን ሀገራችን ኢትዮጵያ ገና ከዘመናት፣ ከትንቢቱ መፈጸም በፊት በንግሥተ ሳባ አማካኝንት በመንፈስ እጆቿን ወደ ላይ አንሥታ፣ ዘርግታ በክብር፣ በፍቅር ተቀበለችው። ልብ አምላክ ዳዊት፣ ‹‹ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች።›› እንዳለ በመዝሙሩ።


ንግስተ ሳባ/አዜብ አስቀድማ በሰለሞን ጥበብና ማስተዋል ውስጥ ገና በሩቅ አሻግራ ያየችውን የጥበብን ጌታ፣ የፍቅርን አምላክ -ለሰው ልጆች ኹሉ ቤዛ ሊኾን በሥጋ ሊገለጥ ያለውን የእግዚአብሔር ልጅ በእርሷ ልብና በልጅ ልጆቿ ልብ ውስጥ ለዘላለም በፍቅር ታተመ። በኋለኛው ዘመንንም ‹ሀገረ ኢትዮጵያ የእግዚአብሔር መንግሥት ምስጢር ምድር› የተሰኘችበት እውነት ፍጻሜውን እንዲህ አገኘ።


ንግሥተ ሳባ በንጉሥ ሰለሞን ልዩ ጥብበና ማስተዋል ውስጥ ያየችውንና የተሳለመችውን የእስራኤልን ቅዱስ፣ የፍቅርን አምላክ የጥበብን ጌታ- ኢየሱስ ክርስቶስን የአብራኳ ክፋይ፣ የጥቁር ምድሯ ትሩፋት- የንግሥት ህንደኬ ባለሟል የሆነው ኢትዮጵያዊው ጃንደረባው ባኮስ ያን ጥበብ፣ ያን ዘላለማዊ ፍቅር፣ በሥጋ የተገለጠውን የእግዚአብሔርን ልጅ፣ ‹ጥበብ› ኢየሱስ ክርስቶስን በሐዋርያው ፊሊጶስ አማካኝነት በታላቅ ሐሴትና ደስታ በጥምቀት፣ በፍጹም እምነት ተቀብሎ የእናት ምድሩን ጥበብን ፍለጋ ናፍቆትና ስስት- የዘመናት ጉዞ፣ የታሪክ ምዕራፍ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ዘጋው።


ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈላቸው መልእክቱ ንግሥተ ሳባ በሩቅ ኾና ስለተሳለመችው ጥበብም እንዲህ ይላል፣ ‹‹መቼም አይሁድ ምልክትን ይሻሉ፣ የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ፣ እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ ለአሕዛብም ሞኝነት ነው፣ ለተጠሩት ግን አይሁድ ቢሆኑ የግሪክም ሰዎች ቢሆኑ የእግዚአብሔር ኃይልና የእግዚአብሔር ጥብብ የሆነው ክርስቶስ ነው።›› ፩ቆሮ. ፩፣፳፬። ሐዋርያው በሌላም ስፍራ ይህን የእግዚአብሔር ጥበብ ሰዎች ሁሉ ያውቁት ዘንድ በጸሎቱ እንዲህ ይማጸናል፡- ‹‹የእግዚአብሔር ምስጢር ክርስቶስን እንዲያውቁ እጋደላለሁ፣ የተሰወረ የጥብበና የእውቀት መዝገብ ሁሉ በእርሱ ነውና።›› (ቆላ. ፪፣፫።) እንዲል።


የቤተክርስቲያናችን አባት የሆነው ቅዱስ ኤጲፋንዮስም በቅዳሴው የእግዚአብሔር ጥበብ የሆነውን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶሰን በጎላ፣ ባማረና በተረዳ ምስጢር እንዲህ ይገልጸዋል፡-


‹‹ጥበብሰ መድኃኒነ ውእቱ ዘቤዘወነ በጥብሐ ሥጋሁ ወተሣየጠነ በንዝኀተ ደሙ ወኀረየነ ለመንግሥቱ ለዓለም ዓለም።›› ጥበብ ግን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው በሥጋው መሥዋዕትነት ያዳነን፣ በደሙም ፈሳሽነት የተወዳጀን ለመንግሥቱም የመረጠን ለዘላለሙ።››


እንግዲህ ‹ሀገረ ኢትዮጵያ የእግዚአብሔር መንግሥት ምስጢር ምድር› የተሰኘችበት እውነት ይህ ነው!! ንግሥተ ሳባም በሩቅ ሆነና በሰሎሞን ውስጥ በናፍቆት ያየችውና የተሳለመችው፣ ወደ ሀገሯና ሕዝቧ ስለመጣው መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ- ታላቅ ማዳን፣ ሕያው ጥበብ ከሰማይ ሠራዊት ከቅዱሳን ከመላእክቱ ጋር በሰማይ በአንድነት ታላቅ ሐሴትንና ደስታን ያደረገች ይመስለኛል። ለምን ቢሉ የእርስዋ የዘመናት ናፍቆት የሕዝቧ፣ የኢትዮጵያም ናፍቆት ነበርና።


ንግሥት በሩቅ የተሳለመችውን ያን የእግዚአብሔርን ቅዱስ ልጅ፣ የዳዊትን ልጅ፣ የቅድስት ድንግል ማርያምን ልጅ፣ ‹የሰው ልጅ› ተብሎ የተጠራው ኢየሱስ ክርስቶስ በኢትዮያጵያዊው ጃንደረባ በእምነት መታዘዝ ምክንያት ምድራችንን ቀድሷታል፣ ባርኳታልና!! አስቀድሞም በእስራኤላዊው በንጉሥ ዳዊት የተተነበየው ‹‹ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር።›› የሚለው የመዝሙረኛው ትንቢትና የንግሥተ ሳባ የዘመናት የሩቅ ሕልምም በኢትዮጵያዊው ጃንደረባ እንዲህ ፍጻሜውን አገኘ።


በእውነትም ጥበብን የመሻትና የመጠማት የኢትዮጵውያን ብርቱ የነፍስ ጩኽትና ፍላጎት ዘመናትን የሚሻገር ታሪክ ያለው እንደሆነ ቅዱሳት መጻሕፍትም ሆነ ሌሎች በዓለማችን የሚገኙ ረጅም ዕድሜን ያስቆጠሩ የታሪክ፣ የጥበብና የፍልስፍና መጻሕፍቶች እማኝነታቸውን የሰጡበት እውነታ ነው። በተለምዶ ‹‹የታሪክ አባት›› ተብሎ የሚጠቀሰው ግሪካዊው ሄሮዱተስ የዓለምን ታላላቅ ሕዝቦችን የሥልጣኔ ታሪክ በጻፈበት መጽሐፉ፡- ‹‹ኢትዮጵያውያን ጥበብን የሚያፈቅሩ፣ የጥበብና የእውቀት ሰዎች፣ ምድራቸውም በተፈጥሮ ሀብት የበለጸገ፣ ለጤና ፈውስ በሆኑ የተፈጥሮ ምንጮችንና ወንዞችን የታደሉ ታላቅ ሕዝቦች ናቸው… ።›› ሲል በአድናቆት ጽፏል፣ መስክሯል።


እንግዲህ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚ/ር ቤኔአሚን ኔታናሁ በአገራችን የተወካዮች ምክር ቤት አዳራሽ ተገኝተው፤ ‹‹ኢትዮጵያ በእስራኤል ልብ ውስጥ ልዩ ስፍራ ያላት አገር ናት›› የሚለው በስሜት የተሞላ ንግግራቸው የሚዘክረውና የሚያጸናው እውነት ቢኖር ‹ሀገራችን ኢትዮጵያ የእግዚአብሔር መንግሥት ምስጢር ምድር› መኾኗን የሚያጎላና እውነቱን የሚመሰክር ንግግር ነው። ዛሬን አበቃሁ፤ በቀጣይ ስለ በዚሁ በመጀመርኩት ርዕሰ ጉዳይ ላይ አገራችን ኢትዮጵያ ‹የእግዚአብሔር መንግሥት ምስጢር ምድር› መኾኗን በሚያዘክረውና በንግሥተ ሳባና በንጉሥ ሰለሞን ግንኙነት አማካኝንት ወደ አገራችን በመጣው በቃል ኪዳኑ ታቦት አመጣጥና ምስጢር፣ የዘመናት የቃል ኪዳኑን ታቦት ፍለጋና በኢሩሳሌም የመቅደሱ መገንባት- የፍጻሜውን መጨረሻ በሚያትተው ጽሑፌ እስከ ምንነገናኝ … ይቆየን! ያቆየን!
ሰላም! ሻሎም!¾

ይምረጡ
(4 ሰዎች መርጠዋል)
1075 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 962 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us