የመሸጫ ዋጋ ያልተተመነለት ውዱ ፈሳሽ

Wednesday, 27 July 2016 14:14

 

  እያንዳንዱም ሰው ጥቂት ሊትር ፈሳሽ ይዟል

 ወሰንሰገድ መሸሻ በላቸው/ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. /

 

ፈቃደኛ ከሆኑ ሰብአዊ ፍጡር ሰውነት ውስጥ 11.25 ዩኒት የሚጠጋ ደም ሌሎችን ለመርዳት ሲባል ይወሰዳል፡፡ 1 ዩኒት ማለት ደግሞ 450 ሚሊ ሊትር ደም ማለት ነው፡፡

ደም በሰውነታችን ውስጥ 100 ሽኅ ኪሎ ሜትር በመጓጓዝ ጥሩም ሆነ ቆሻሻ ነገሮችን በደም ዝውውር ስነስርአት ደምን የሚያጣሩትንና በትክክል የሚሰሩትን ልብ፣ ኩላሊት፣ ጉበትና ሳንባን ጨምሮ በእያንዳንዱ የሰው ልጅ የአካል ክፍል ውስጥ በማለፍ እንደ ኦክስጂን፣ አልሚ ምግቦችና በሽታ ተከላካይ የሆኑ ጥሩ ነገሮችን ወደ ሰውነት ሕዋሳቶቻችን ያደርሳል፡፡ መርዛማ ካርቦንዳይ ኦክሳይድ፣ የተጎዱ እንዲሁም የሞቱ ሕዋሳትና ሌሎች ቆሻሻዎችን ከሕዋሳት ውስጥ ያስወግዳል፡፡

ደምን በአራት ዋና ዋና ክፍሎች ከፍለው ይገልፁታል፡፡ ከጠቅላላው ደም ውስጥ ከ52 እስከ 62 በመቶ የሚሆነው ፕላዝማ ነው፡፡ ከፕላዝማ ውስጥ 91.5 በመቶ የሚሆነው ውኃ ሲሆን፣ 7 በመቶው የተለያዩ ፕሮቲኖችና የፕላዝማ ክፍልፋዮችን አልቡሚን 4 በመቶ፣ 3 በመቶ ግሎቢንና ከ1 በመቶ ያነሰ መጠን ያለው ፋይብሪነጅንን ይዟል፡፡ 91.5+7= 98.5 በመቶ በጠቃቀስናቸው የተያዙ ሲሆን ቀሪው 1.5 በመቶ የሚሆነው ፕላዝማ የደም ክፍል የተሰራው አልሚምግቦች፣ ሆርሞኖች፣ የምንተነፍሳቸው ጋዞች፣ ኤሌክትሮላይቶች፣ ቫይታሚኖችና ናይትሮጅን ነክ ቆሻሻዎች ከሆኑ ሌሎች ንጥረ ነገሮች ነው፡፡

ነጭ የደም ሕዋሳት ከሙሉው ደም ውስጥ ከአንድ በመቶ ያነሱ ሲሆኑ ወደ ሰውነት ውስጥ ገብተው ሊጎዱ የሚችሉ አካላትን በማጥቃት ያጠፋሉ፡፡

ፕሌትሌቶች የሚባሉት ከሙሉው ደም ውስጥ ከአንድ በመቶ ያነሱና በቆሰለ ሰውነት በኩል ደም እንዳይፈስ ለማገድ ደምን በማርጋት ያግዛሉ፡፡

ቀይ የደም ሕዋሳት ከሙሉው ደም ውስጥ ከ38 በመቶ እስከ 48 በመቶ የሚሆኑና ሕብረህዋስ ውስጥ ኦክስጅንን ስለሚያስገቡ፣ ካርቦንዳይኦክሳይድን ስለሚያስወጡ ሕብረ ሕዋሱ በሕይወት እንዲቀጥል የሚያደርጉና ሄሞግሎቢን የሚባል የደም ክፋይንም ያካተተ ነው፡፡

ከላይ በመጠኑ ለመቃኘት የሞከርነው ሙሉውን ደም ወይም አራቱ ዋና ዋና የደም ክፍሎች ፕላዝማ፣  ነጭ የደም ሕዋስ፣ ፕላትሌትና ቀይ የደምሕዋስን ነበር፡፡

በእያንዳንዱ ቀይ የደም ሕዋስ ውስጥ ወደ 300 ሚልዮን የሚጠጉ የሄሞግሎቢን ሞለኪዩሎች ይገኛሉ፡፡ እድገቱን በጨረሰ ቀይ የደም ሕዋስ ውስጥ አንድ ሶስተኛው ሄሞግሎቢን ነው፡፡ እያንዳንዱ ሞለኪዩል ውስጥ ግሎቢን የሚባል ፕሮቲንና በውስጡ ብረት ያለው ሄም የሚባል ማቅለሚያ አለ፡፡ ቀይ የደም ሕዋስ በሳንባዎች ውስጥ ሲያልፍ የኦክስጂን ሞለኪዩሎች ሕዋሱ ውስጥ ይገቡና ከሄሞግሎቢን ሞለኪዩሎች ጋር ይጣበቃሉ፡፡ ከጥቂት ሰኮንዶች በኋላ ኦክስጂኑ ሕብረ ሕዋሳት ውስጥ በመግባት ሕዋሶቹ በሕይወት እንዲቆዩ ይረዳል፡፡

‹የሰው ልጅ በሙሉ የሕይወት ምንጩ ደም ነው፡፡ ደም ዘር፣ ቀለም ወይም ሐይማኖት ሳይለይ በሁሉም የሰው ልጆች ውስጥ የሚገኝ የሕይወት ኃይል ነው› ብሎ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ አስምሮበታል፡፡

ደም መለገስ መተኪያ የለለው ታላቅ ስጦታና ቸርነት ነው፡፡ የለገሱት ደም ደግሞ በተፈጥሮው በሰውነትዎ ተመልሶ ይተካል፡፡ ይህ ለግሰውት መልሶ በተፈጥሮ ሂደት በራሱ የሚተካልዎ ደም በተለያዩ ጉዳቶች በህክምና ላይ ለሚገኙ ወገኖች ህይወት መታደግ የሚያስችልና በእያንዳንዱ ሰው ውስጥ በትንሽ ሊትር የሚገኝ በዓለማችን የከበረ እጅግ በጣም ውዱ ፈሳሽ  ነው፡፡

ደም በአለማችን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እጅግ አስፈላጊና ውድ የሆነ ፈሳሽ ቢሆንም ዘመኑና ወቅቱ ከፈጠሩብን አደጋዎች መበራከት አንፃር ከሚደርሱት ዘግናኝ አደጋዎች አኳያ በደም አለመገኘትና እጥረት የተነሳ የሚሞተው ህዝብ ቁጥር በቀላሉ የሚገመት አልሆነም፡፡

በስህተት ከሌላ በሽተኛ የደም ናሙና በመውሰድ፣ ናሙናዎች ላይ የተሳሳተ ምልክት በመለጠፍና ሕመምተኛው ሳያስፈልገው ደም እንዲወስድ በመታዘዙ ለሞት የተዳረጉ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ስህተቶች በህክምናው ዓለም ተከስተዋል፡፡

በረቀቀ ሕክምና በምትሞካሸው አሜሪካ ከ1995 እስከ 2001 እ.ኤ.አ ባሉት ጊዜያት ውስጥ በዚህ መሰል የህክምናው ዓለም ስህተት ሳቢያ 441 ሰዎች ሕይዎት መቀጠፉን በወቅቱ በዜና ብዙኃኖቻቸው ገልፀውታል፡፡ በዚህ የተነሳም ሂማቶሎጂስቶች (ስለደም የሚያጠኑ ባለሙያዎች) ከባድ የመቁሰል አደጋ ካጋጠማቸው ታማሚዎች በስተቀር ደም መስጠቱን በብዙ አይመክሩም፡፡

አንዳንዶቹ በኒሞኒያ፣ በኢንፌክሽን፣ በልብ ድካምና በአንጎል ውስጥ ደም መፍሰስ ጉዳቱ ከፍተኛ መሆኑን አበክረው እያስጠነቀቁ ነው፡፡ እንደብዙ የሕክምና ባለሙያዎች መረጃ መሰረት በዓለም ዙሪያ 200 ሚሊየን ዩኒት ተጨማሪ ደም በየዓመቱ ሊለገስ እንደሚገባና ለዚህ ልገሳ የሚሆንም ደም አለመገኘቱንና ከፍተኛ እጥረት መኖሩን በመግለፅ ይወተውታሉ፡፡ 82 በመቶ የሚሆነው ህዝብ የሚኖረው ባልለሙትና ኋላ ቀር ተብለው በተፈረጁት ሐገሮች ውስጥ ነው፡፡

በእነዚህ ሐገሮች የሚለገሰው ደም በጠቅላላ ሰዎች ከሚሰጡት ደም 40 በመቶ የማይሞላ ነው፡፡ በእነዚህ ሐገሮች የሚገኙ ሆስፒታሎች ለህመምተኞች የሚሰጡት ደም እያጡ ደም ሳይሰጡ ሕክምና ለማድረግ ወይም ባጠቃላይ ሕክምናውን ለመሰረዝ እንደሚገደዱ በጥናት አስደግፈው ይገልጻሉ፡፡

በበለፀጉት ሐገሮችም ቢሆን የደም እጥረቱ ጎልቶ የሚታይ መሆኑንም ሳይደብቁ እየገለፁ ነው፡፡ የሰዎቹ እድሜ በተለቀ ቁጥር፣ የህክምና ዘዴዎች እየተራቀቁ በመምጣታቸው ቀዶ ሕክምና የሚደረግላቸው ህመምተኞች ቁጥርም እየጨመረ ነው፡፡ የሚለገሱት ደሞችም በተለያዩ ምክንያቶች ለበሽታ ወይም ለጥገኛ ሕዋሳት የተዳረጉ እንደሚሆኑ በማሰብ በሚያደርጉት ከፍተኛ ጥንቃቄ ሳቢያ የደም አቅርቦቱ እያጠረ መጣ፡፡  የደም ባንኮችም ስጋት ስላየለና በቂ ክምችትም እንደሌላቸውም በአፅንኦት አሳስበዋል፡፡

በአፍሪካም ስለጉዳዩ ከፍተኛ የሆነ የግንዛቤ እጥረት አለ፡፡ ደም መለገስ የራስን ደም ቀድቶ በማፍሰስ በራስ ላይ ጉዳት ማምጣት ነው ብለው ይሰጋሉ፡፡ እንደ ኤድስና መሰል ሌሎች በሽታዎች እንጋለጣለን ብለውም ስለሚፈሩ ሰጪዎቹም አይሰጡም ተቀባዮችም በፍላጎት አይቀበሉም፡፡

በኢትዮጵያ መንግስት ቱባ ቱባ ባለስልጣኖቻቸውን በቴሌቪዝን መስኮት እያቀረቡ ማሳየት፣ በማስታወቂያ ትልልቅ ቦርዶችም ላይ ደም እየለገሱ የሚመስሉ ምስሎቻቸውን በመለጠፍ ሰፊውን ሕዝብ ማነሳሳት፣ ታዋቂ ሰዎችን በአምባሳደርነትና ዝግጅቱን በስማቸው በመሰየም በዘመቻ ደም መሰብሰብ፣ ተማሪዎችና የመንግስት ሰራተኞች በዘመቻ ደም እንዲለግሱ መቀስቀስና ገንዘብ እየሰጡ ማትጋትን ስራቸው አድርገውታል፡፡ በቼክ ሪፑፕሊክ በተደረገ የደም ልገሳ ዘመቻ የተወሰነ ደም ለግሰው ቢራ እንዲጠጡ በመጋበዝ መንቀሳቀሳቸው፣ በሕንድ ፈቃደኛ ደም ለጋሾችን ለማግኘት ባለስልጣናት ቤት ለቤት እየሄዱ መቀስቀስ ጀምረዋል፡፡

በሰውነታችን ውስጥ የሚካሄዱት አብዝሃኞቹ ኬሚካላዊ ሂደቶች፣ መርዛማ የሆኑ ንጥረ ነገሮችና መወገድ ያለባቸው ሌሎች ነገሮች ወደ ደም ውስጥ ይገባሉ፡፡ እነዚህ ነገሮች ካልተወገዱ እጅግ የከፋ ችግር ሞትንም ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ከላይም ስለደም በገለፅነው ላይ ተመልክተናል፡፡ ስለዚህ እነዚህን ጎጂ ነገሮችን የማጣራቱንና የማስወገዱን ሥራ የሚያከናውነው ደግሞ ኩላሊታችን በመሆኑ ስለኩላሊት ጥቂት እንበላችሁ፡፡

በኩላሊት ውስጥ ዋነኛው የማጣሪያ ክፍል ኩሊቴ ይባላል፡፡ ኩላሊት ውስጥ ከ1 ሚሊዮን የሚበልጡ ኩሊቴዎች አሉ፡፡ በአንድ ነጠላ ኩሊቴ ውስጥ የሚገኘው እያንዳንዱ ቱቦ በአማካይ 3.05 ሴንቲሜትር ርዝመት ሲኖረው ስፋቱ ደግሞ 0.05 ሴንቲሜትር ብቻ ነው፡፡

ኩሊቴዎች 2 ሚሊየን የመሆኑ የቱቦ አይነት ቅርፅ ያላቸው ያለ አጉሊ መነፅር የማይታዩ ማጣሪያዎች ሲሆኑ ደምን የማጣራት ሥራን ይሰራሉ፡፡ በአንድ ኩላሊት ውስጥ ያሉትን ሁሉንም ቱቦዎች መዘርጋት ቢቻል 30 ኪሎሜትር የሚደርስ መሆኑን ጠበብቶች ይገልፃሉ፡፡ ደግነቱ ፈጣሪ በጥበቡ እዚያች ትንሿ  ኩላሊት ውስጥ በአግባቡ ሰትሯታል፡፡

ቦውማን ስርጉድ ኩሊቴ ውስጥ ባለው ጥምዝማዥ ቱቦ ጫፍ ላይ የሚገኝ ሲሆን ይህ ቱቦ ፀጉሮዎች ተብለው በሚጠሩ የተጠላለፉ እጅግ አነስተኛ የደም ስሮች የተከበበ ነው፡፡ ቱቦው በኩሊቴ ተጣርተው የተለዩትን ቆሻሻዎችና መርዛም የሆኑ ንጥረ ነገሮች ወደሚያስወግደው ኮሌክቲን ዳክት ወደተባለ ትልቅ ቱቦ ውስጥ ይገባል፡፡ ኩላ ገንዳ ሽንትን በማጠራቀም ወደ ቦየ ፊኛ የሚያሸጋግር ማስተላለፊያ ሲሆን ቦየ ፊኛ ደግሞ ሽንትን ከኩላሊት ወደ ፊኛ ይወስዳል፡፡ ኩላሊታዊ ደም መላሽ የተጣራ ደምን ወደ ሰውነት መልሶ ያስገባል፡፡ ኩላሊታዊ ደም ወሳጅ ደግሞ ያልተጣራ ደም ወደ ኩላሊት ይወስዳል፡፡ ኩላሊታዊ ትርሽሜ የሚባለው ሽንትን ወደ ኩላ ገንዳ የሚወስዱ ሾጣጣ መዋቅሮች ናቸው፡፡ ልህፅ(cortex} የእያንዳንዱን ኩሊቴ ችፍርግ የያዘ ነው፡፡

ሰዎች በጀርባቸው በኩል ከታች ከአከርካሪያቸው ግራና ቀኝ የተቀመጡ ሁለት ኩላሊቶች አሏቸው፡፡ እያንዳንዳቸው 10 ሴ.ሜ. እርዝመት፣ 5 ሳ.ሜ. ስፋት፣ 2.5 ሳ.ሜ ውፍረትና ከ110-170 ግራም ክብደት አላቸው፡፡

በደማችን ውስጥ ያሉ በርካታ ንጥረ ነገሮች በመላ ሰውነታችን ውስጥ መዘዋወር አለባቸው፡፡ ይህንን ሂደት በሚያከናውኑበት ወቅት ከሁሉም ኩላሊቶች ጋር በተገናኙ ኩላሊታዊ ደም ወሳጅ በሚባሉት የደምስሮች አማካይነት በተደጋጋሚ በኩላሊቶች ውስጥ ማለፍ አለባቸው፡፡

ኩላሊት ውስጥ ከገቡ በኋላ ኩላሊታዊ ደም ወሳጁ በኩላሊት የውስጥና የውጭ ንብሮች ላይ ወደ ሚገኙት ትንንሽ ደምስሮች ያሰራጫቸዋል፡፡ በደማችን ውስጥ የሚገኙት የተለያዩ ንጥረ ነገሮች በዚህ መንገድ ይበልጥ ሊስተናገዱ ወደ ሚችሉባቸው ቦታዎች እንዲተላለፉ ይደረጋል፡፡

በመጨረሻ ደሙ እያንዳንዳቸው 40 የሚሆኑ የተሳሰሩ ትንንሽ የደም ስሮች ወደ ሚገኙባቸው አነስተኛ የደም ስር ክምችቶች ጋር ይደርሳል፡፡ እያንዳንዱ ክምችት ችፍርግ (glomerulus) ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ቦውማን ስርጉድ ተብሎ በሚጠራ(ቦውማን ስርጉድ የሚለውን ስያሜ የተሰጠበት ምክንያት በ1840ዎቹ  እንግሊዛዊው የቀዶ ሕክምና ሂስቶሎጂስቱ ዊልያም ቦውማን ስርጉዱንና ተግባሩን ስለገለፀው ነው::) ባለ ሁለት ንብር ገለፈት የተከበበ ነው፡፡ ችፍርግና ቦውማን ስርጉድ አንድ ላይ ዋነኛ ማጣሪያ የሆነውን የጥበቃ በር ይፈጥራሉ፡፡

በደማችን ውስጥ ያሉት የደም ሕዋሳትና ፕሮቲኖች እጅግ አስፈላጊ ናቸው፡፡ ለሰውነታችን የኦክስጅን አቅርቦትን፣ መከላከያንና ጥገናን የመሳሰሉ ወሳኝ የሆኑ ግልጋሎቶችን ይሰጣሉ፡፡ የደም ሕዋሳትና ፕሮቲኖች ከሰውነት እንዳይወገዱ ለማድረግ የመጀመሪያው የማጣራት ሂደት ከሌሎቹ ንጥረ ነገሮች ሁሉ ቦውማን ስርጉድ ይለያቸዋል፡፡

ችፍርግ ውስጥ የገቡ የደም ስሮች ይከፈሉና በጣም ቀጫጭን ግድግዳዎች ያሏቸው ትንንሽ ፀጉሮዎች (capilaries) ይሆናሉ፡፡ ይህም በመሆኑ የደም ግፊት የተወሰነ ውኃና ሌሎች ትንንሽ ሞሊኩዩሎችን ከደም ውስጥ በማስወጣት ጥቃቅን በሆኑት የፀጉሮዎች ገለፈቶች በኩል ወደ ቦውማን ስርጉድና ከስርጉዱ ጋር ወደ ተያያዙት ጥቅል ቱቦዎች እንዲገቡ ያደርጋል፡፡ ይህ ቱቦ ጥምዝማዥ ቱቦ (convoluted tubule) በመባል ይታወቃል፡፡ ተለቅ ተለቅ ያሉት የፕሮቲን ሞለኩዪሎችና ሁሉም የደም ሴሎች እዚያው ደም ውስጥ መፍሰሳቸውን ይቀጥላሉ፡፡ የማጣራት ሂደቱም ይበልጥ ይጠናከራል፡፡

ኩላሊታችን ለሰውነታችን ጠቃሚ የሆነ ምንም ነገር እንዳይወጣ ይቆጣጠራል፡፡ በዚህ ወቅት በቱቦው ውስጥ የሚፈሰው ፈሳሽ ጠቃሚ የሆኑ የሟሙ ሞለኩዩሎችን እንዲሁም ቆሻሻዎችንና አስፈላጊ ያልሆኑ ንጥረ ነገሮችን የያዘ ውኃማ ድብልቅ ነው፡፡ በቱቦው የውስጠኛው ግድግዳ ላይ የሚገኙት በዚህ ተግባር የተካኑ ሕዋሳት እንደውሃ፣ ጨው፣ ስኳር፣ ማእድናት፣ ቪታሚኖች፣ ሆርሞኖችና አሚዶ አሲድ ያሉትን ጠቃሚ ሞለኩዩሎች ለይተው ያውቃሉ፡፡

እነዚህ ነገሮች እንደገና ወደ ቱቦው ግድግዳ ገብተው በዙሪያው ባሉት ፀጉሮዎች ያልፉና ዳግመኛ ወደ ደማችን ይገባሉ፡፡ ፀጉሮዎቹ ተጣምረው ትንንሽ ደም መላሽ የደም ስሮች ይሆኑና እነዚህ የደምስሮች ደግሞ ጥምረት ፈጥረው ኩላሊታዊ ደም መላሽ የተባለውን ትልቅ የደም ስር ያስገኛሉ፡፡ የተጣራው ደማችን በዚህ የደም ስር አማካይነት ከኩላሊታችን ይወጣና ሰውነታችን ሕያው ሆኖ እንዲንቀሳቀስ ማድረጉን ይቀጥላል፡፡

ከሶስት ሰዎች ሁለቱ በልብ ህመም ከመጠቃታቸው ጥቂት ቀናት ወይም ሳምንታት በፊት ቀስፎ የሚይዝ የደረት ውጋት፣ ደረት ላይ ምቾት የሚነሳ ስሜት መሰማት፣ ትንፋሽ ማጠርና የሰውነት መዛል/ከባድ ድካም ምልክቶችን ማየት ይቻላል፡፡

የደም ግፊት መጨመር፣ ደረት ላይ የመወጠር ስሜት፣ ሄደት መለስ የሚልና ለደቂቃዎች የሚቆይ ፍስስ የማለት ስሜት ይፈጠራል፡፡ ህመሙ ቀስ ብሎ ሊጀምር ወይም ወዲያውኑ ሊያጣድፍና ሊባባስ ይችላል፡፡ ሰውነትን የመጫጫን፣ የመፍዘዝ፣ የማላብ፣ ክብድ የማለት ወይም የመጨነቅ ስሜቶች ይታያሉ፡፡

የደረት ህመም ወደ ጉረሮ፣ አንገት ትከሻ መንጋጋ፣ ጀርባ ወይም ሁለቱ ክንዶች ላይ እንዲሁም እስከ እጅ መዳፍ ድረስ ሊሰራጭ ይችላል፡፡ ተደጋጋሚ የሆነ የመተንፈስ ችግር፣ የማስመለስ ስሜት ወይም ማስመለስ፣ ራስ የመሳት ስሜት ወይም ቀዝቃዛ ላብ የመሳሰሉት የልብ በሽታዎች ምልክቶች መሆናቸውንም የምርምር ውጤቶች ያሳያሉ፡፡

ለከፍተኛ የደም ግፊትና የልብ በሽታ ከሚዳርጉት ውስጥ ከመጠን በላይ የጨመረ ኮልስትሮል፣ የደም ቧንቧዎች ራሳቸውን የማደስ ብቃት ማጣት፣ የሲጋራ ሱስ፣ ከመጠን ያለፈ ክብደት፣ በቂ እንቅስቃሴ አለማድረግና ጭንቀት በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡ አንድ ሰው ካልተንቀሳቀሰ ወይም ሥራ ካልሰራ የደም ዝውውሩ ዘገምተኛ ይሆንና በደም ቧንቧዎች መዘጋትን/መደፈንን/ ያስከትላል፡፡

ጤናማ ያልሆነ ውፍረት እንደ ደም ግፊት፣ የልብ ህመምና የስኳር በሽታዎችን በማስከተልና በማባባስ የመኖር ተስፋን ያጨልማል፡፡ ኮሌስትሮል በደም ውስጥ የሚገኝ ጠቃሚ ቅባት ነው፡፡ በደም ውስጥ ኮሌስትሮል ከመጠን በላይ መጨመር የልብ ቧንቧዎች ውስጥ ሞራ መሰል እንዲፈጠርና ቧንቧዎቹ እንዲጠቡ ከዚያም የደም ዝውውር እንዲሰናከል ያደርጋሉ፡፡

ከፍተኛ የደም ግፊት በልብ ላይ ጫናን በመፍጠር የደም ቧንቧዎች ራሳቸውን የማደስ ብቃታቸውን በማሳጣት ቶሎ እንዲያረጁ በማድረግ የደም ዝውውር እንዲገታ ያደርጋል፡፡ በሲጋራ ውስጥ ያለው ኒኮቲን የተባለው ንጥረ ነገር የልብ ምትን ከመጨመር ባሻገር ደምን ወደ ልብ ይዘው የሚያጓጉዙ ጥቃቅን ስሮችን  ያጠብባል፡፡ ይህ ደግሞ በቂ ደም ወደ ልብ ህዋስ እንዳይደርስ ያደርጋል፡፡

ከፍተኛ የደም ግፊትና የልብ በሽታን ለመቀነስ የሚረዱትን የሚያገኙዋቸው ከሆነ በሳምንት 5 ቀን አትክልትና ፍራፍሬ በብዛት መመገብ፣ ኦሜጋ 3 የሚባለውን ጠቃሚ ቅባት ለማግኘት ዘይታማ አሳዎችን እንደሰርዲን/ቱና፣ ማካፌል ሳልመን በሳምንት 2 ወይም 3 ጊዜ መመገብ ይመከራል፡፡

የእንስሳት አስተዋፅኦ የሆኑትን እንደስጋ፣ ቅቤ፣ ወተት፣ የዶሮ ቆዳን በእጅጉ መቀነስ፣ የተልባ ዘይት እሳት ሲነካውና ብዙ ጊዜ ሲቆይ ጠቃሚነቱ ስለሚቀንስ ኦሜጋ 3 የተባለውን ቅባት ለማግኘት በትንሽ በትንሹ መፍጨትና ከምግብ ጋር ቀላቅሎ መብላት፣ ትራንስ የተባሉ በጣም ጎጂ ቅባቶችን ለመቀነስ በዘይት የተንጨረጨሩትን ምግቦች መቀነስና የአትክልት ቅቤ የሚባሉትን ማስወገድ ይገባል፡፡

የደም ብዛትን ኮልስትሮልንና ትራንስግሊስራይድን ለመቀነስ ስለሚረዳ ውድም ቢሆን የወይራ ዘይት መጠቀም፣ አንቲ ኦክሲዳንት በብዛት ያላቸውን አትክልትና ፍራፍሬዎችን መመገብ፣ አልኮል ቢያስፈልግ አንድ ወይም ሁለት መለኪያ ብቻ በየቀኑ መውሰድ፡፡ የተነጠረ ስኳር ያለባቸውን መጠጦችና ምግቦች እንደ ኬክ ብስኩትና ለስላሳ መጠጦች ያሉትን ማስወገድ ወይም መቀነስ፣ ሻይ መጠጣት በተለይም አረንጓዴ ሻይ ብዙ አንቲኦክሲዳንት ከመያዙም በላይ የደም መርጋትን ያስከትላል፡፡ በየቀኑ አንድ ወይም ሁለት ነጭ ሽንኩርት መውሰድ፣ ደም ብዛትን ለመቆጣጠር ጨው መቀነስና ካልሲየምና ፖታሲየም የያዙ ምግቦችን መመገብ ጥሩ መሆኑን የልብ ህሙማን ማኅበር ሰነድ ገልፆታል፡፡

የልብና ድንገተኛ የአንጎል ደም ስሮች መዘጋት የሚያስከትለው የልምሻ በሽታ /ኸርት ዲዝዝ ኤንድ ስትሮክ/ በዓለም አቀፍ ደረጃ በያመቱ 17 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን እየቀጠፈ ነው፡፡ ይህ በሽታ በዓለማችን ከሚከሰተው ጠቅላላ የሞት ብዛት 30 በመቶውን የሚወክለው ነው፡፡

የዓለም የልብ ፌዴሬሽን ከመላው አባላቱ ጋር በመሆን ለልብ በሽታዎችና ለድንገተኛ የአንጎል ደም ስሮች መዘጋት የሚያጋልጡ ነገሮችን ማለትም ጤናማ ያልሆነ አመጋገብን አለማዘውተር፣ የአካል እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ ሲጋራ ማጤስና ሌሎችንም የልብ ጠንቅ የሆኑ ምክንያቶችንና ችግሮችን ለመከላከል በዚህ የተነሳም የሚከሰተውን ሞት በ80 በመቶ ለመቀነስ የዓለም አቀፍ የልብ ቀን ሰይሞ መንቀሳቀስ የጀመረው እ.ኤ.አ.ከ 2000 ዓ.ም ጀምሮ ነው፡፡

የስኳር በሽታ የደም ስር የሚያጠብ በሽታ በመሆኑ ከመቶ ህመምተኞች ውስጥ 75ቱ በልብ ቧንቧ መዘጋት ይሞታሉ፡፡ አንዳንድ ሰዎች በጭንቀት ምክንያት የደም ግፊታቸው እንደሚጨምር የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ልብ ሲታወክ ልብ ደምን በሚገባው ኃይል መጠን መርጨት/መግፋት ያቅተውና ሰውነት ማግኘት የሚገባውን ኦክስጅንና ምግብ በበቂ ሁኔታ ማቅረብ ሲሳነው የልብ ድካም ይከሰታል፡፡ የልብ መታወክ የሚፈጠረው የልብ ጡንቻዎች ደም ለመግፋት የሚጠቀሙትን ኃይል ሲያጡ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት በእያንዳንዱ የልብ ምት ከልብ ወደ ሰውነት የሚረጨው የደም መጠን አነስተኛ ይሆናል፡፡ የልብ ጡንቻዎች ወደ ልብ የሚገባውን ደም ሁሉ በአግባቡ ወደ ሰውነት መልሰው ለመርጨት ሲያቅታቸው የልብ ደም ማጠራቀሚያ ክፍሎች ከመጠን በላይ በደም ይሞላሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ወደ ልብ ደም የሚያጓጉዙት |የደም መልስ ቧንቧዎች በተመሳሳይ ሁኔታ በደም ይሞላሉ፡፡ ይህም የደረሰበት ሰው የትንፋሽ ማነስ /አየር ማጠር/ የእግር ማበጥና ድካም ይሰማዋል፡፡

ቫይራልና ሜነንጃይቲስ በሽታ መከሰቻው የጀርባ ደም ስር መገተር፣ ከፍተኛ ትኩሳት፣ የፀኃይ ብርሃን የማየት ችግር፣ መጨነቅ፣ ራስምታትና ማስመለስ ናቸው፡፡ በሽታው ከተከሰተ በኋላ መደበኛ ህክምና ከጀመሩት ሰዎች ውስጥ ከ5-10 በመቶ የሚሆኑት ከ24-48 ሰዓት ውስጥ ለሞት ይዳርጋል፡፡ በተጨማሪም ህክምናውን ከወሰዱ በኋላ ዘላቂ ለሆነ የአእምሮ ጉዳት፣ የመስማት ችግር ትምህርት ለመቀበል የሚቸገሩት ከ10-20 በመቶ የሚጠጉ ተጠቂዎች ናቸው፡፡ ብዙ ጊዜ የሚያጋጥመውና በጣም አደገኛ በሆነው ሜንጎኮካል ሶፔቲሳይማ የተጠቃ ሰው ራሱን ትቶ በፍጥነት ለሞት የመዳረግ አጋጣሚው የጎላ ነው፡፡

የሰው ልጅ ትንፋሹ ከተቋረጠ ወይም ነፍሱ ከስጋው ከተነጠለ/ከሞተ በኋላ አእምሮው በውስጡ ያለውን ደም እየተመገበ በአማካይ ከ15-20 ሰከንድ ሥራውን ሳያቋርጥ ይሰራል፣ ማሰቡንም ይቀጥላል፡፡ ማንም ሰው ከተቀበረ በኋላ የሚፈርሰው ስጋው ከ9 ፓውንድ/ከ4 ኪሎ በታች ይሆናል፡፡ ምክንያቱም የሰው ልጅ ሰውነት የተገነባው 75 በመቶ በውሃ በመሆኑና ሲቀበር ስጋው ወደ ትነትነት ስለሚቀየር የሚኖረው ክብደት ይሟሽሽና አጥንቱ ብቻ ይቀራል፡፡

ሰውነታችን በየቀኑ የሚያስፈልገውን ምግብ ከማመንጨት በተጨማሪ በጉልምስና እድሜው በየቀኑ 300 ቢሊየን አዳዲስ ሴሎችን ያመርታል፡፡ የሰው አጥንት ከብረት የበለጠ ጥንካሬ የተላበሰ ነው፡፡ ለማነፃፀር ያህል የአጥንት ቴንሳይል ስትሬንግዝ 20 ሽህ ፒኤስ አይ ሲሆን የብረት ቴንሳይል ስትሬንግዝ ደግሞ 7 ሽህ ፒኤስ አይ መሆኑን ተመራማሪዎች ገልፀዋል፡፡ 

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
1092 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 950 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us