ፖለቲካችን የበላቸው ቤተሰቦች!!

Wednesday, 03 August 2016 14:52

 

/በሊሕ ላማ ከቤተመንግስት ጀርባ/

ማሊክ የባራክ ኦባማ ታላቅ ወንድም ናቸው፤ የአባታቸው ልጅ። ባራክ ሚሼልን ሲያገቡ አንደኛ ሚዜያቸውም ነበሩ። ሰሞኑን የብዙሃን መገናኛ ጉዳይ ሆነው ከርመዋል። “ዴሞክራቶችን አልወዳቸውም፤ ከመስራት ይልቅ ማውራት የሚቀናቸው ናቸው፤ እኔ የትራምፕ ደጋፊ ነኝ” በማለታቸው ነው-ማሊክ የመገናኛ ዘደዴዎች ትኩረት የሆኑት።

በርግጥ ማሊክ ይህንን ብለዋል። የወንድማቸው ፓርቲ የሆነውን ዴሞክራትን ‘አልወደውም፤ አልመርጠውምም’ ሲሉ ተደምጠዋል። ግን አንድ ጉዳይ ላይ አጽንኦት ሰጥተዋል። “ፓርቲውን አልወደውም ማለት ወንድሜን እጠላዋለሁ ማለት አይደለም” የሚለው የማሊክ አንክሮ ነው።

እንዲህ ያለውን ነገር የሰማ ኢትዮጵያዊ ብዙ ታሪኮችን አስቦ፣ ለሀገሩ ፖለቲከኞችም ፖለቲካንና ቤተሰብነትን የሚለይ ልብ ይሰጣቸው ዘንድ የህሊና ጸሎት ቢያደርግ አይገርምም። እዚህ አገር በፖለቲካ ምክንያት ስንቱ በወንድሙ ላይ ተነስቷል፤ ስንቱስ እህቱን አሳልፎ ሰጥቷል?! የሚታወቁትን ፖለቲከኞች ብቻ አንስተን እንመልከት!

ብንያም አዳነ፣ ዮሴፍ አዳነ፣ ንግስት አዳነና ዳንኤል ታደሰ፤እነዚህ ሰዎች ሙሉ የአንድ ቤተሰብ አባላት ነበሩ። ነሀሴ 1968 ከባህርዳር አውሮፕላን ጠልፈው በሱዳን ወደ አልጄሪያ ከተሻገረው ቡድን መካከል ብንያም አዳነ የተባለ ወጣት ይገኝበት ነበር። የትጥቅ ትግል ለማድረግ ከመካከለኛው ምስራቅተነስተው ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ በድካምና በአስም በሽታ ሱዳን በረሃ ውስጥ ሞተ።

እሱ ካለፈ በሁዋላ ቤተሰቦቹ እርስበርስ በፖለቲካ ምክንያት ኢሕአፓና መኢሶን ተባብለው ተገዳድለዋል። ይህንን እርሱ አልሰማም። እህቱ ዶክተር ነበረች-ንግስት አዳነ። ከሞስኮቭ በሕጻናት ሕክምና ተመርቃለች። ባሏ ደግሞ ዶክተር ዳንኤል ታደሰ ይባላል። ባልና ሚስቶቹ የመኢሶን አባል ናቸው። ለዚያውም የላይኛው የመኢሶን አመራሮች። የዶክተር ንግስት ወንድም ዮሴፍ ደግሞ የኢሕአፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ባልደረባና ከፓርቲው አንኳሮች አንዱ። ቆይቶ ፓርቲው በደርግ ቀይ ሽብርና በራሱ የውስጥ ችግር ተደመሰሰ። ዮሴፍ አዳነም ተገደለ።

እውነትነቱ ባይረጋገጥም ዮሴፍ አዳነን ያስገደለችው እራሷ ንግስት መሆኗን ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ለገነት አየለ በሰጡት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል። ጓድ ኮሎኔል እንዳሉት ‘ንግስት የወንድሟን መገኛ ለደርግ በመጠቆሟ...’ ዮሴፍ ሊገደል ችሏል። ኮሎኔል ፍስሀ ደስታም “በፖለቲካ አለመግባባት ምክንያት የአንድ እናት ልጆች ጎራ ለይተው እንዴት ይገዳደሉ እንደነበር…” በገለጹበት አንቀጽ፣ የኢሕአፓውን ዮሴፍ አዳነን እና መኢሶኗን እህቱን ዶክተር ንግስትን ጠቅሰዋል። ምናልባት አገላለጻቸው የአለቃቸውን የመንግስቱ ኃይለማርያምን ሃሳብ የሚያጎለብት ሳይሆን አይቀርም።

ዞሮም ተጠቅልሎም ዶክተር ንግስትንም የመንግስቱ ኃይለማርያም መንግስት ከነ ባሏ /ዶክተር ዳንኤል ታደሰ/ ገድሏታል። መኢሶንና ኢሕአፓ ያነበሩት የፖለቲካ አስተሳሰብ የአዳነን ልጆች ፈጃቸው። የአንድ እናት ልጆች አንድ ጡት ጠብተው ያደጉ ወንድማማቾችና እህታቸው፣ ከነአማቻቸው በሚከተሉት የፖለቲካ ድርጅት ስለተለያዩ ብቻ በሁለት ጎራ ተገዳደሉ።

የባራክ ኦባማ ወንድም ማሊክ ግን ‘ዴሞክራትን ጠላሁ ማለት ወንድሜን እጠላለሁ ማለት አይደለም’ አለ። ከ40 ዓመት በፊት የነበሩት የኛ ሰዎች ግን በፖለቲካ ልዩነታቸው የእናታቸውን ልጅ አሳልፈው ሰጡ።

እነ ንግስት ሲገዳደሉ የባራክ ኦባማ ወንድም ማሊክ 19 ዓመታቸው ነው። እነ ዮሴፍም እድሜያቸው በዚሁ አካባቢ ቢሆን ነው። ያኔ ግን የመቻቻል ልቡና ቸገረ። እንደ ማሊክ ማሰብ ጠፋ፤ መቋጫውም መጠፋፋት ሆነ።

የኅሩይ ልጆች

ዮሃንስ ኅሩይ የሕግ ምሁር ነበር። በደርግ መዋቅር ውስጥ በከፍተኛ 11 የቀበሌ 14 ሊቀመንበር ነበር። ቲቶ ኅሩይ ደግሞ የዮሃንስ ኅሩይ ታናሽ ወንድም ነው። ይሄኛው የኢሕአፓ ወጣት ክንፍ የሆነው ኢሕአወሊ ማዕከላዊ ኮሚቴ ሊቀመንበር ነበር። በዚህ ኮሚቴ አመራር ሰጪነት ብዙ የደርግና የመኢሶን ሰዎች ተገድለዋል። በአንዷ ቀንም ቲቶ ኅሩይ ያሰማራቸው ነፍሰ ገዳዮች፣ በ5ጥይት ደብድበው  ዮሃንስን ቢሮው ውስጥ ገደሉት። በመቻቻል ናፍቆት ዓመታትን የተሻገረው የአገራችን ፖለቲካ፣ የኅሩይን ልጆችም ደም አቃባ። የማሊክን ልብ ያጣው ፖለቲካችን ስራው እትብታቸው በአንድ ጉድጉዋድ የተቀበረን ወንድማማቾች ማጋደል ሆነ።

የገብረማርያም ልጆችና ተስፋዬ ደበሳይ

ፍቅርተ ገብረማርያም በ1964 ዓ.ም በአለም አቀፍ ሕግ ከሞስኮቭ ተመረቀች። ትምኅርቷን እንደጨረሰች ወደ ኢትዮጵያ መመለስ አልፈለገችም። ይልቁንም ወደ ፍሪቡርግ አውስትራሊያ አቀናች። እዚያ እንደሄደች ከታደለች ኃይለሚካኤል /የብርሃነመስቀል ረዳ ባለቤት/፣ ከአክሊሉ ኅሩይና ከተስፋዬ ደበሳይ ጋር መኖር ጀመረች። ወዲያው ከተስፋዬ ጋር በፍቅር ወደቁ። ተስፋዬ ደበሳይ ዶክተር ሲሆን የኢሕአፓ አድራጊ ፈጣሪ ነበር። ፍቅርተም የባሏን ፈለክ ተከተለች። ኢሕአፓ ሆነች። እነ ተስፋዬ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢሕአድ/ኢሕአፓን መሰረቱ። እርሷም ትግሉን ተቀላቀለች። ወንድሟ ጉልላት ገብረማርያም ደግሞ የወዝ ሊግ አባል ነው። ወዝ ሊግ በደርግ ዙሪያ በተኮለኮሉና “ሒሳዊ ድጋፍ እናድርግ” ባሉ ሰዎች የተመሰረተ መሆኑን ልብ ይሏል። ድርጅቱ የኢሕአፓ ሰዎችን ለደርግ እየጠቆመ ያስገደለ ነው።

ጉልላትና ፍቅርተ የተባሉ የአንድ አባት ልጆች ማዶ ለማዶ ተፋጠጡ። በዚህ መሀል ባልና ሚስቶቹ ፍቅርተና ተስፋዬ በ1968 ዓ.ም ሐምራዊትን ወለዱ። ከአንድ ዓመት በሁዋላ መጋቢት ላይ በተደረገ የደርግ አሰሳ የኢሕአፓው አንጎል ዶክተር ተስፋዬ ደበሳይ ሞተ። ሚስቱ ወደ አሲምባ /የኢሕአፓ ሰራዊት-ኢሕአሰ የጦር ቤዝ/ ተስደደች። ልጇን ለማን ጥላ?? ለሌላ ወንድሟ ለአቶ ተስፉ ገብረማርያም!! በወቅቱ ከኢሕአፓ አባላት መወለድም ‘ጸረ-አብዮተኛ’ ስለሚያሰኝ አቶ ተስፉ የእህቱን ልጅ የመኖሪያ አድራሻውን ቀይሮ አሳደገ። ይህ ቤተሰብ በዚህ መልኩ የኖረበት ፖለቲካ ለሞት፣ ለስደትና ለመበታተን ዳርጎታል።

ማሊክ ኦባማ ሆይ ለአንተ ይህንን ዓይነት ቅን ልቡና የሰጠህ አምላክ ስለምን ለአገሬ ሰዎች ነፈጋቸው ይሆን???

የወልዱ ልጆች፤ አውአሎም ወልዱና አባይ ወልዱ፤

ሁለቱም የሕወሃት አባል ሆነው አሰልቺውን ጦርነት አካሂደዋል። ሁለት አስርታት በተጠጋው ውጊያ ድርጅታቸው አሸንፎ ከተማ ሲገባ፣ አውአሎም የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆኖ አስመራ ሄደ። ታናሽ ወንድሙ አባይ ደግሞ በክልሉ ውስጥ የግብርና ቢሮ ኃላፊ ሆነ። አውአሎም ፓርቲውን እንደ ወንድሙ ይወድና ይሰራ የነበረ ታታሪ ሰው ስለመሆኑ ተደጋግሞ ተጽፎአል። አቶ ኢሳያስ የተባሉ የኤርትራ ፕሬዚዳንት ስለዚህ ሰው “አውአሎም ከቢሮው ሳይወጣ ተዓምር ሲሰራ የሚውል አምባሳደር ነው” ሲሉ መናገራቸው መጻሕፍት ላይ ሰፍሯል። በዚህ ሁኔታ አቶ አውአሎም እስከ 1990 አስመራ ከረሙ። ሆኖም በወዳጅ አገሮች መሀል ጦርነት ተቀሰቀሰ። አውአሎም ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ። ከዓመታት በሁዋላ ፓርቲው ‘ተሀድሶ አደረግሁ’ አለና ‘አስራ ሁለት ጎምቱ የሕወሃት አባላት ጉባኤ ረግጠው በመውጣት ከአባልነት ተሰናበቱ’ አለ። አቶ አውአሎምም ከአስራ ሁለቱ እንደ አንዱ ሆነ።

ያኔ ፓርቲው ሁለት ጎራ ይዞ ተሰነጣጠቀ። ወንድማማቾቹም ከወዲያና ከወዲህ ማዶ ሆኑ። በወቅቱ “አንጃ” የተባለውን የነ አውአሎምን ቡድን በማህበራዊ ጉዳዮችም ማግኘት፣ ለቅሶ መድረስ፣ ሰርግ መታደም፣ በሽተኛ መጠየቅ… ተወገዘ። ፖለቲካችን እስከ እድር ድንኳን፣ እስከ ህሙማን አልጋ የሚደርስ ክፉ በትሩን ዘረጋ። የወልዱ ልጆችም በፖለቲካ አቋማቸው ምክንያት ተቃረኑ፤ ተለያዩም። አንደኛው የአገሪቱ መንግስት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የክልሉ ፕሬዚዳንት ሆነ። ሌላኛው ደግሞ የራሱ ወንድም በአመራርነት አባል በሆነበት ፓርቲ፣ “አንጃ” የሚል ቅጣይ  ተለጠፈበትና ጎራው ወዲያ ማዶ ሆነ።

ማሊክ ኦባማ ሆይ ይህንን ብትሰማ ምን ትል ይሆን?! አንተ ያልከውን ቢሰሙስ እነዚህ ወንድማማቾች ምን ይሉ ይሆን?!¾

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
1155 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 953 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us