ከባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ እስከ ኬኒያ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ

Wednesday, 14 December 2016 13:55

ከሄኖክ ስዩም/ተጓዡ ጋዜጠኛ/

በኢትዮጵያ ከሚገኙ ብሔራዊ ፓርኮች አንዱ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ነው። ባሌን ብዙዎች የማይገለጽ ሲሉ በደፈናው ይገልጹታል። ከአናቱ የሚወርዱት ምንጮች ድንበር ለሚሻገሩ የሚሊዮኖች ህልውና መሰረት የሆኑ ወንዞች መነሻ ናቸው።

ከባሌ ተራሮች እስከ ኬኒያ ተራሮች የሚያስጉዘንም የዚህ ድንቅ ተፈጥሮ ጉዳይ ነው። ባሌ ከአዲስ አበባ 400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በኦሮሚያ ክልል የሚገኝ አዳባ፣ ዲንሾ፣ ጎባ፣ ደሎ መና እና ሀረና የተባሉ ወረዳዎች የሚያካልሉት 2150 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው የአፍሮአልፓይን ሥነ ምህዳር ነው።

የህገ ወጥ ግጦሽ፣ የጠራ የወሰን ክለላ አለመኖር፣ በተፈጥሮ ሀብቱ ላይ የሚደርስ ተደጋጋሚ አደጋ፣ የተቀናጀ የቱሪዝምና ተፈጥሮ ሀብት ልማት አለመኖር የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ችግሮች ከሚባሉት ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው። ለዚህም ነው በዓለም የቅርስ መዝገብ ለመመዝገብ በተጠባባቂነት ተይዞ ብዙ ጊዜ የቆየበት ምስጢር።

የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን ለመታደግ ከሚሰሩ ስራዎች መካከል በፍራንክፈርት ዙኦሎጂካል ሶሳይቲ የሚታገዘው ፕሮጀክት አንዱ ነው። ይህ ፕሮጀክት የጎረቤት ሀገር ልምድ ከተጀመረው ጉዞ ጋር ያለውን መጣጣም አጢኖ በኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን የተዘጋጀውን የልምድ ልውውጥ ደገፎ የባሌ ተራሮችን ይዘን ወደ ኬኒያ ተራሮች አናት ወጣን።

አንድ ሳምንት በኬኒያ ቆይታውን ያደረገው የኬኒያን ልምድ ፍለጋ የተጓዘ ልዑክ ከባሌ ተራሮች ህልውና ጋር ቁርኝት ይኖራቸዋል ተብሎ በሚታመኑ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች የተዋቀረ ነበር። የልዑካን ቡድኑ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የባህል ቱሪዝምና መገናኛ ብዙሃን ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ በክብርት ወይዘሮ ፈቲያ የሱፍ የተመራ አስራ አምስት አባላት ያሉት ሲሆን የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተርን ጨምሮ፣ ከፓርላማ አባላት፣ ከባሌ ዞን አመራሮች፣ ከባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ ከኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት፣ የኦሮሚያ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት፣ ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት፣ ከኦህዴድ ጽ/ቤት፣ ከመገናኛ ብዙሃን የተውጣጡ አካላትን ያቀፈ ነው።

በስምንት ቀናት የኬኒያ ቆይታ ከአምቦሴል እስከ ኬኒያ ተራሮች በተደረገ ጉዞ የኬኒያን ልቀት የእኛን ጉድለት እና የባሌን መፃኢ እድል የሚያሳዩ ልምዶች የተቀሰሙበት ጉብኝት ተደርጓል። ኬኒያ በዘርፉ ልቃ የሄደች ሀገር ናት። ከብሔራዊ ፓርኮቿ እኩል ሳፋሪዎቿ የዱር እንስሳቷን ህልውና ታድገዋል። በኬኒያ ኢንቨስትመንት ማለት ተፈጥሮን መጠበቅ እና ለተፈጥሮ ሀብቱ ልማት እኩል ድርሻን መወጣት ነው።

በጉብኝታችን መነሻ የኬኒያ ዱር እንስሳት አገልግሎት ናይሮቢ በሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት በክብር ተቀብሎ የዛሬዋ ኬኒያ እንዲህ በዱር እንስሳት ሀብቷ ገና የፓርኮቿ ህልውና አስተማማኝ ደረጃ ላይ የደረሰው ምን ታልፎ እንደነበር የውጣ ውረድ ጉዞውን የተቋሙ የስራ ኃላፊዎች አብራሩልን።

የኬኒያ ዱር እንስሳት አገልግሎት ዛሬ ተሳክቶለት እያንዳንዱ ኬኒያዊ የዱር እንስሳት ሀብቱ ጠበቃ ለመሆን በቅቷል። በየትኛውም ፓርክ እንደልብ የዱር እንስሳቱን መመልከት ይቻላል። የዱር እንስሳት ሀብቱን ወደ ኢኮኖሚ የቀየሩ ውድ እና ቅንጡ ሎጆች ከተፈጥሮ ተስማምተው በኬኒያ ፓርኮች እና ዱር እንስሳት መጠለያዎች ተሰግስገዋል።

የአፍሪካ ሁለተኛው ረዥም ተራራ የሚገኝበት እና በ1997 እ.ኤ.አ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ መዝገብ የተመዘገበው የኬኒያ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የባሌ እኩያ የሥነ ምህዳር ገጽታው በብዙ መልኩ ከባሌ ተራሮች ጋር የሚመሳሰል ነው። ከናይሮቢ ሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ 175 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የኬኒያ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክና በዙሪያው በሚገኙ የብዝሃ ህይወት ማዕቀፉ የተደረጉ ጉብኝቶች ሰፊ ልምድ የተገኘባቸው ናቸው።

የኬኒያ ደን አገልግሎት፣ የኬኒያ ዱር እንስሳት አግልግሎት እና ማህበረሰቡ እንዴት በቅንጅት እንደሚሰሩ በፓርኩ ኃላፊዎች የተደረገልን ገለጻ መሬት ላይ ወርደን ከተመለከትነው ጋር ተመሳሳይ ነው። እዚህ ጠንካራ ስልት፣ ለደቂቃም እፎይ የማይባልበት የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ እና ሀብትን ወደ ገንዘብ የመቀየር ዘዴ ተቀናጅተዋል።

በየፓርኮቹ ያደረግናቸው ውይይቶች፣ ከፓርክ ኃላፊዎች የተደረጉ ገለጻዎች ባሌን ለመታደግ የተደረገው ጉዞ በሀገራችን መተግበር ከቻለ ከእኛ በላይ እድለኛ አይኖርም። ባሌ በሥነ ምህዳር ስብጥሩ የታደለ መስህብ ነው። ባሌን በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ኢትዮጵያ ጥያቄ አቅርባ ጥያቄው ተቀባይነት አግኝቶ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ መዝገብ በተጠባባቂ መዝገብ ላይ የተመዘገበ ቢሆንም በየጊዜው የሚገጥሙት የተለያዩ ችግሮች የተፈጥሮ ሀብቱ ህልውና ጭምር አደጋ ሆነዋል። እንደ ጎረቤት ሀገር ፓርኮች ከሀብቱ ተጠቃሚ አለመሆናችን ብቻ ሳይሆን በዚሁ ከቀጠልን ብዝሃ ህይወቱን ለመጪው ትውልድ ላናስተላልፈውም እንችላለን። በኬኒያ የተመለከትነው ነገር የችግሩን ግማሽ ይፈታል የሚል እምነት አለኝ። ያ ከሆነ  ይሁን ምናልባትም ከኬኒያ ተወዳዳሪ ብቻ ሳይሆን በላጭ መሆናችንን ከሚያረጋግጡ ፓርኮች አንዱ ባሌ ተራሮች ይሆናል። አስቡት የኬኒያ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ አንድም በኬኒያ ብቻ የሚገኝ አጥቢ የዱር እንስሳት የማይገኝበት እና በውስጡ የሚገኙ የዱር እንስሳት በኢትዮጵያ ያሉ ሲሆን ባሌ በብርቅዬዎቹ አጥቢ የዱር እንስሳቶች መገኛነት ይታወቃል።

ለፓርክ ባለሙያዎች የሚደረገው ድጋፍ፣ የፖሊሲና ህግ ማዕቀፎች ጥንካሬ፣ የመንግስት ትኩረት እና ቁርጠኝነት፣ የግል ባለ ሀብቶች ተፈጥሮን ለመታደግ ያላቸው ሚና፣ የአደረጃጀት መዋቅሩና መሰል አሰራሮች እዚሁ ጎረቤት ሀገርን ሲለውጥ ከተመለከትን እኛስ የሚለውን ደጋግመን መጠየቅ ይኖርብናል። ጥያቄያችን መልሱ ከእኛው ብቻ የሚገኝ መሆኑንም ማሰብ አለብን።

ረዥም ርቀት ማሰብም ማየትም ይገባናል። ግማሽ ምዕተ ዓመት ያክል ልፋትና መከራ ብቻ የነበረው የኬኒያን ተፈጥሮ የመታደግ ጥረት ወደ አስደናቂ ኢኮኖሚ ከተቀየረ ዓመታት ተቆጥረዋል። ያም ሆኖ ግማሽ ሚሊተሪ የሆነውን የኬኒያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ኃይል የሚፈታተነው ችግር ከእኛ ጋር የሚወዳደር አይደለም። እንደ ልቡ የታጠቀው የፓርክ የጸጥታ ኃይል ከእሱ በላይ በታጠቀ ሽብርተኛ ቁም ስቅሉን ያያል። መሬት የግለሰብ መሆኑ ፓርኮችን ማስፋትና ማልማት ላይ ሌላው የኬኒያ ዱር እንስሳት አገልግሎት የገጠመው ፈተና እኛን የማያሰጋ ነው። በዚህም ውስጥ ግን ከኬኒያ ብዙ ልንማር የምንችለው ነገር አለ። 

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
1292 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 166 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us