ተደጋግመው የሚነሱ ጡረታ ነክ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው

Wednesday, 28 December 2016 14:25

 


በጋዜጣው ሪፖርተር

 

ስለአገልግሎት ጡረታ አበል፣


በግል ድርጅት ሰራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 715/2003 መሠረት የአገልግሎት ጡረታ አበል (Retirement Pension) በሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች ይገኛል። አንደኛው ሠራተኛው መጦሪያ ዕድሜው 60 ዓመት ላይ ሲደርስ የሚወጣበት ሲሆን ሁለተኛው ሠራተኛው በሚሰራበት ወይም በሰራባቸው ድርጅቶች የ25 ዓመታት አገልግሎት ሲኖረውና ዕድሜው 55 ዓመት ሲሞላ በራሱ ጥያቄና ፈቃድ በጡረታ የሚገለልበት ነው። በዚህ መሰረት ያገለገሉ ባለመብቶች አበል ማስያ ስሌት ጡረታ ከመውጣታቸው አስቀድሞ ባሉት ሶስት ተከታታይ ዓመታት (36 ወራት) ሲከፈላቸው በነበረው ደመወዝ አማካይ መጠን ለመጀመሪያው 10 ዓመት አገልግሎት 30% በመውሰድ ከ10 ዓመት በላይ ለተፈጸመ ለእያንዳንዱ ዓመት አገልግሎት በ1.25 በመቶ (የጡረታ መዋጮ እየጨመረ በነበረበት ከ2004-2007 ድረስ ማባዣው 1.15፣ 1.19፣ 1.22፣ 1.25 ነበር) በማብዛትና ቀዳሚውን 30% በመደመር ነው። በዚህ መሰረት ረዥም አገልግሎት መስጠት እና ከፍተኛ ደመወዝ ተከፋይ መሆን ተጠቃሚነትን በጣም እንደሚያሳድጉ ልብ ይሏል። ለምሳሌ፡- አቶ አለምነህ የተባሉ አንድ ባለመብትን የጡረታ ፕሮፋይል እንመልከት።


· የአገልግሎት ዘመን 42 ዓመት፤
· ጡረታ በተወሰነላቸው ወቅት ይከፈላቸው የነበረ ጥቅል ደመወዝ (የስራ ገቢ ግብርና ጡረታ ሳይቀነሱ) ብር 7100.00፤
· ጡረታ ሲወጡ ይከፈላቸው የነበረ የተጣራ ደመወዝ (የስራ ገቢ ግብርና ጡረታ ተቀንሶ) ብር 4780.5፤
· ጡረታ ሲወጡ የተወሰነላቸው የአበል መጠን ብር 4970.00፤
· የተወሰነላቸው የጡረታ አበል ደሞዛቸውን የተካበት መጠን (Replacement rate) 103.9% ሊሆን ይችላል።
ከዚህ ስሌት በተጓዳኝነት መታየት ያለባቸው ሌሎች እውነታዎችም አሉ። የአክቹዋሪ ሳይንስ ምሁራን በስሌታቸው አቶ አለምነህ ለጡረታ ፈንዱ በስራ ዘመናቸው በሙሉ የቆጠቡት ገንዘብ እጅግ ቢበዛ ከ5 እስከ 7 ዓመታት ብቻ የሚዘልቅ ክፍያን የሚሸፍን መሆኑን በስሌታቸው ያሳያሉ። ይሁንና የማህበራዊ መድን አሰራር ስርዓቱ የመደጋገፍና የዐቅዱን ጥቅምና ኪሳራ የመጋራት (Principles of Solidarity and Risk Pooling & Benefit Sharing) መርህ የሚከተል በመሆኑ፡-
· ባለመብቱ የቱንም ያህል ዘመን ይኑሩ ምንም አይነት እገዳ ወይም ቅነሳ ሳይደረግባቸው በህይወት እስካሉ ከፈንዱ በየወቅቱ የሚደረጉ ጭማሬዎችን አክሎ ተጠቃሚ ይሆናሉ።
· የባለመብቱ ህይወት ቢያልፍ ደግሞ ተተኪዎቻቸው የባለመብቱን ጥቅም እንዲጋሩ ህጉ ይፈቅድላቸዋል። በዚህም መሰረት፡-
· የባለመብቱ ባለቤት (ወንድ ወይም ሴት ሊሆኑ ይችላሉ) የባለመብቱን አበል 50% በህይወት ዘመናቸው በሙሉ፣
· ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ የባለመብቱ ልጆች፣ ባለመብቱ አካል ጉዳተኛ ልጅ ያለው ከሆኑ ዕድሜው/ዋ 21 ዓመት እስኪሞላ የባለመብቱን አበል 20%፣
· በባለመብቱ ገቢ ሲተዳደሩ የነበሩ ወላጆች ካሉ ተረጋግጦ እናትም አባትም በህይወት ካሉ እያንዳንዳቸው የባለመብቱን አበል 15% ተጠቃሚዎች ይሆናሉ። ይህ የተተኪ የጡረታ አበል ለተተኪዎች እንደየመቶኛቸው ተከፋፍሎ የሚወሰነው ለዋናው ባለመብት የተወሰነው የጡረታ አበል 100% ድረስ ብቻ ነው። ከዚህ አንፃር ከያንዳንዱ ተተኪዎች አንድ አንድ ተጠቃሚዎች ብንወስድ እንኳን ጠቀሜታውን ማጤን ተገቢ ነው።
በአንዳንድ ሃገራት የማህበራዊ ዋስትና አሰራር መሰረት የተተኪዎች ጡረታ አበል የማይከፈል ወይም ባለመብቱ ለሚፈልጋቸው የተወሰኑ ተተኪዎች ብቻ በፈቃዱ ሽፋን የሚሰጥ ሲሆን (ምሳሌ፡- የላይቤሪያ የማህበራዊ ዋስትና ዐቅድ) በሀገራችን ይህ የተደረገበት ዋነኛው ምክንያት የማህበራዊ ዋስትና ዐቅዱ ማህበራዊ ቀውስንና የቤተሰብ ብተናን ሊታደግ በሚችል መልኩ የተቀየሰ በመሆኑ ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በሀገራችን የጡረታ አበል ክፍያ መጠን አነስተኛ ነው ወይም “በቂ አይደለም” የሚል አስተያየት ተደጋግሞ ይነሳል። ይህ የግንዛቤ ክፍተት የመጣውም አንድም ቀደም ብሎ የተገለፀውን “በበቂነት” ላይ ያለው አመለካከት መነሻው ስህተት በመሆኑ በሌላ በኩል ደግሞ ተተኪዎች የባለመብቶች ተተኪዎች መሆናቸውንና የባለመብቶችን አበል የሚጋሩ መሆናቸውን ባለማጤንና ባለመብቶች አድርጎ በመቁጠር ነው።
በብዙ ሀገራት የጡረታ አበል ደመወዝን የመተካት ድርሻ (Replacement rate) ከሠራተኞች ጥቅል ደሞዝ 80% የማይበልጥ ነው፤ ይህ የሀገራቱ የጡረታ ስሌት ለጋስ ከሆነና ሠራተኛው የብዙ አመታት አገልግሎት ካለው/ት የተጣራ ደመወዝን መቶ በመቶ እና ከዚያ በላይ ይተካል። በብዙ አዳጊ ሀገሮች ስሌቱ ከ55% እስከ 70% የሚደርስ ሲሆን በጡረታ አዋጁ ላይ ያለው የአበል ውሳኔ የስሌት ቀመር ደመወዝን የመተካት ድርሻ በጣም ጥሩ የሚባል እና የተጣራ ደመወዝን እስከ 100% እና ከዚያ በላይም የሚተካ ነው።

 

የጉዳትና የጤና ጉድለት ጡረታ


የስራ ላይ ጉዳትና የጤና ጉድለት ጡረታ አበል ጥቅሞች "በቂነት"
አዋጅ ቁጥር 715/2003 በአንቀፅ 27 ስር እንዳስቀመጠው አንድ የማህበራዊ ዋስትና ዐቅድ አባል መደበኛ ስራዉን በማከናወን ላይ እያለ ወይም ከስራው ጋር በተያያዘ ምክንያት በአካሉ ወይም በአካሉ የተፈጥሮ ተግባር ላይ በድንገት ጉዳት ሲደርስበት የጉዳት ጡረታ አበል ይወሰንለታል። የሚወሰነው የጡረታ አበል መጠንም በአባሉ ላይ አደጋው ከደረሰበት ወር በፊት ይከፈላቸው በነበረው ደመወዝ ላይ ተመስርቶ የሚሰላ ሲሆን መጠኑም አደጋው ከደረሰበት ወር በፊት ይከፈላቸው የነበረው የወር ደመወዝ 47% ይከፈለዋል።


ይህ አበል ለባለመብቱ እስከ ዕድሜ ልክ የሚከፈል ሲሆን ባለመብቱ ከዚህ አለም በሞት ቢለይ በጡረታ አዋጁ ላይ በተቀመጠው መቶኛ ድርሻ መሰረት ለተተኪዎች የሚተላለፍ ነው። ይህንን የማህበራዊ ዋስትና የጥቅም አይነት ልዩ የሚያደርገው በማህበራዊ መድን አሰራር ስርዐት ውስጥ የመደጋገፍ መርህ (Principle of Solidarity) በጉልህ የሚታይበትና የሚተገበርበት መሆኑ ነው። የአቅዱ አባል አደጋው በደረሰበት ወቅት ለጡረታ ፈንዱ ያዋጣው የመዋጮ መጠንና የፈጸመው የአገልግሎት ዘመን ከግምት ሳይገባ አባል በመሆኑ የአንድና የሁለት ወር አገልግሎት ብቻ ፈጽሞና ይህንኑ አገልግሎት ሲፈጽም በነበረበት ጊዜ የጡረታ መዋጮ ከፍሎ እስከ እድሜ ልክ ባለመብቱ/ የአቅዱ አባል ከዚህ አለም በሞት ቢለይ በጡረታ አዋጁ መሰረት ለተተኪዎች እንደየድርሻቸው የሚከፈል ነው።


ህጉ ይህንን መብት የሰጠበት ዋነኛው ምክንያት በደረሰባቸው የስራ ላይ ጉዳት ምክንያት የሚያጡትን ገቢ በሙሉ ወይም በከፊል እንዲተካና ለጉዳት/ችግር ተጋላጭ የሆኑትን የዐቅድ አባላት የሚደግፍ የአቅዱ አባላት ችግርን እና ጥቅምን እንዲጋሩ (risk pooling and benefit sharing) የተቀመጠውን አለም አቀፍ መርህን የሚከተል አሰራር ሆኖ የተቀየሰ በመሆኑ ገቢ የሚያስገኝ ስራ መስራት ያልቻሉት የሚጠቀሙበት ሰርተው ገቢ የሚያገኙት የዐቅድ አባላት ደግሞ ለዐቅዱ መዋጮ እየከፈሉ የሚቆዩበት በትውልድ መካከል የሚቆይበት ሂደት ነው። ይህም የሚከሰተውን ማህበራዊ ቀውስ እና የቤተሰብ ብተናን በመታደግ ያገኝ ከነበረው ገቢ ጋር ተመጣጣኝ በሆነ ገቢ ህይወትን ለመምራት የሚያስችል ነው።


ከዚህ የጡረታ አበል መብት ጋር ተደጋግሞ በአሰሪዎችና በሠራተኞች የሚነሳው ጥያቄ ግለሰቡ በአካሉ ላይ በደረሰው ጉዳት ምክንያት በጡረታ ከስራ ከተገለለ በኋላ በሌላ ስራ ተቀጥሮ ደመወዝ እየተከፈለው መስራት ይችላል? ከቻለስ ከሚከፈለው ደመወዝ ላይ የጡረታ መዋጮ ይቀነሳል? እድሜው የጡረታ መውጫ ዕድሜ ላይ ስላልደረሰ ወይም ስድሳ ዓመት ስላልሞላ እንዴት ይስተናገዳል? የሚል ነው። ጥያቄው መነሳቱ አግባብነት ያለው ሲሆን ግለሰቡ የደረሰበት የአካል ጉዳት ሳያግደው ተቀጥሮ መስራት የሚችል እስከሆነ ድረስ ምላሹ ግለሰቡ በመንግስት፣ በግል ወይም ራሱ ግለሰቡ በሚከፍተው የግል ድርጅት ውስጥ ተቀጥሮ ሊሰራ ይችላል የሚል ነው።


ለምሳሌ የፋብሪካ ሰራተኛ ሆኖ ሲያገለግል የነበረ ግለሰብ በደረሰበት (ለምሳሌ እጅ፣ እግር፣ አይን ወዘተ) የአካል ጉዳት ምክንያት መስራት ባለመቻሉ የስራ ውሉ ቢቋረጥና መስራት የማይችል መሆኑ በህክምና ቦርድ ቢረጋገጥ የጉዳት ጡረታ አበል ይወሰንለታል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ግለሰቡ በትምህርት መስክ፣ በሙያ ስልጠና፣ ቀድሞ በነበረው የስራ ልምድ ወ.ዘ.ተ ወይም ሌሎች ገቢ በሚያስገኙ ስራዎች ላይ በደመወዝ ተቀጥሮ ቀደም ብሎ የተወሰነለትን የጡረታ አበል አጣምሮ መጠቀም ይችላል። ይሁንና ቀደም ብሎ ግለሰቡ ከስራ የተገለለው መጦሪያ ዕድሜ ላይ ስለደረሰ ባለመሆኑ እድሜያው ለጡረታ እስኪደርስ ድረስ አዲስ ተቀጥሮ ከሚከፈለው ደመወዝ በአዋጁ ላይ በተቀመጠው የጡረታ መዋጮ መጠን መሰረት የሰራተኛውን መደበኛ የወር ደሞዝ መነሻ በማድረግ አሰሪ 11% ሠራተኛው ደግሞ 7% በጥቅሉ 18% የጡረታ መዋጮ ይከፍላሉ።


እድሜው 60 ዓመት ሲሞላም ወይም በመሀል ሌላ የስራ ላይ ጉዳት ወይም የጤና ጉድለት ቢደርስበት በአዋጅ ቁጥር 715/2007 መሰረት በስራ ላይ ጉዳት ምክንያት ይከፈለው የነበረውን የጡረታ አበል ተቋርጦ አዲሱን አገልግሎትና በመቀጠር ሲከፈለው የነበረውን ደመወዝ መሰረት በማድረግ እንደአግባቡ የአገልግሎት፣ የጤና ጉድለት ወይም የጉዳት ጡረታ አበል ይወሰንለታል።


ሌላው የጤና ጉድለት ጡረታ አበል ሲሆን ይህ የእክል አይነት የዐቅድ አባሉ ከ 10 አመት ያላነሰ አገልግሎት ኖሮት በስራ ላይ እያለ (የስራ ውሉ ሳይቋረጥ) በመሀል ስራውን ሊያሰራው የማያስችልና ሊድን የማይችል ህመም ሲያጋጥመውና ለዚህም የሀኪሞች ቦርድ ማረጋገጫ ሲሰጥበት የሚተገበር ነው። የሰራተኛው አገልግሎት ከ 10 አመት ያነሰ ከሆነ ጠቀም ያለ የዳረጎት አበል የሚያስገኝ ነው። የአበል ስሌት ቀመሩም ከአገልግሎት ጡረታ አበል ውሳኔ ቀመር ጋር ተመሳሳይ ነው።


(የዚህ ዘገባ ምንጫችን የግል ድርጅቶች ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ነው)

ይምረጡ
(11 ሰዎች መርጠዋል)
1607 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1014 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us