ዶናልድ ትረምፕ ሰኞ ማለዳ በኦቫል ኦፊስ…

Wednesday, 25 January 2017 13:20

 

ግሩም ተበጀ

 

ለቁርስ የቀረበላቸውን እንቁላል ፍርፍር እንደነገሩ ከበሉ በኋላ (ስልጣን ከያዙ ወዲህ የምግብ ፍላጎታቸው እምብዛም ሆኗል) አንድ ፍንጃል የይርጋ ጨፌ ቡና በላዩ ላይ ከለሱና ከሲ አይ ኤ ወደመጣው ሰው ዞር ብለው “አይስስን ዛሬውኑ ድራሹኑ ማጥፋት አለብን። አሁኑኑ…” አሉት…
ሲ አይ ኤ፡- እሱን ማድረግ አንችልም ሚስተር ፕሬዝዳንት። አይስስን ራሳችኑ ነን ከቱርክ፣ ሳዑዲ፣ ኳታር እና ሌሎች ጋር ተባብረን የፈጠረነው… እንዲሁ ከመሬት ተነስተን ልናጠፋው አንችልም።


ትረምፕ፡- ይህቺን ይወዳልና! እኔ ምን አገባኝ ታዲያ… ዲሞክራቶች ናቸው የፈጠሩት አይስስን!
ሲ አይ ኤ፡- ዲሞክራት፣ ሪፐብሊካን እዚህጋ ምንም አይሰራም ሚስተር ፕሬዝዳንት። በዚህም ሆነ በዚያ እኛው ነን የፈጠርናቸው። አይይ ካሉ ሚስተር ፕሬዝዳንት ከተፈጥሮ ጋዝ ሎቢ ግሩፕ የሚያገኙት ገቢ ይነጥፋል…


ትረምፕ፡- እሺ እነዚህን ሰይጣኖች ተዋቸው… ለፓኪስታን የምናደርገውን ድጋፍ አሁኑኑ እንድናቆም እፈልጋለሁ። ሕንድ ራሷ ትቻላት … እኛ ምን አገባን።
ሲ አይ ኤ፡- ይህን ማድረግ አንችልም ሚስተር ፕሬዝዳንት…


ትረምፕ፡- እኮ ለምን?


ሲ አይ ኤ:- ፓኪስታንን ካልደገፍናት ሕንድ ባሎቺስታንን ከፓኪስታን ትነጥቃታለቻ…
ትረምፕ፡- ትንጠቃታ። እኛ እዚህ ውስጥ ምን ጥልቅ አደረገን…


ሲ አይ ኤ፡- ይሄ ከሆነማ ሕንድ ካሽሚር ውስጥ ሰላም አገኘች ማለት ነው። እንዲያ ከሆነ ደግሞ ማነው መሳሪያዎቻችንን የሚገዛን። ሕንድና ፓኪስታን ካልተጣሉ ደግሞ ሁለቱም ልዐለ ኃያል መሆናቸው ነው። ፓኪስታንን እያስታጠቅን ሕንድን ካሽሚር ውስጥ ሰላም ካልነሳናት እንዴት ይሆናል...


ትረምፕ፡- እሺ ሌላው ይቅር ታሊባን ግን መጥፋት አለበት…


ሲ አይ ኤ፡- ትልቁ ዳቦ ሊጥ ሆነ (ይሄ የሲ አይ ኤ አባል አዲስ አበባ፣ ሽሮ ሜዳ ከራርሞ ስለነበር በተረትና ምሳሌ ሁሉ ነው አሉ የሚያወራው) ይሄን ፈፅሞ ማድረግ አንችልም ሚስተር ፕሬዝዳንት… በ1980ዎቹ ሶቭየት ራሺያን ልክ እንዲያስገባልን ብለን ታሊባንን የፈጠርነው እኛው ራሳችን ነን። አሁን ደግሞ በፋንታው ታሊባን ፓኪስታንን እረፍት እየነሳልን ነው...


ትረምፕ፡- ምን አይነት እዳ ውስጥ ነው የገባሁት! እሺ በቃ ታሊባንንም ተዉት… ግን ከዛሬ ጀምሮ ደቡብ ኮርያን ከሰሜን ኮርያ ጥቃት መጠበቅ እናቆማለን። ወይ ለጥበቃችን ትክፈል አለበለዚያም እኛ እሷን ለመጠበቅ ዶላር አንከሰክስም… ወስኜያለሁ በቃ!!


ሲ አይ ኤ፡- ሚስተር ፕሬዝዳንት ይህንማ ማድረግ አንችልም… ከደቡብ ኮርያ አጠገብ ገሸሽ ካልን ደቡብና ሰሜን ኮርያ ሊዋሃዱ ይችላሉ። በኢኮኖሚ የበለፀገችው ደቡብ ኮርያ እስከ አፍንጫዋ ከታጠቀችው ባለኒውክሌር ሰሜን ጋር ተዋሀደች ማለት ለአሜሪካ የአካባቢው ሀያልነት አደጋ የሆነ ልዕለ ሃያል ሀገር ተፈጠረ ማለት እኮ ነው። የእኛ ከደቡብ ኮርያ መውጣትማ አይታሰብም…


ትረምፕ፡- በቃ ይሄንንም ተዉት… ሽብርን የሚደግፉ የመካከለኛው ምስራቅ መንግሥታትን ማጥፋት አለበን። አዎ… እንዲያውም ከሳዑዲ እንጀምር…


ሲ አይ ኤ፡- ይሄ የማይታሰብ ነው ሚስተር ፕሬዝዳንት፣ እነዚህን መንግስታት ፈጥረን፣ ደግፈን እዚህ ያደረስናቸው እኛው ራሳችኑ ነን - ምክንያቱም ነዳጅ ዘይታቸው ያስፈልገናላ!! እዚያ አካባቢ ዲሞክራሲ ድርሽ ማለት የለበትም። አለበለዚያ ሕዝቡ የሚፈልገውን መርጦ ነዳጃቸው አካባቢ ድርሽ እንዳንል ቢያደርገንስ…


ትረምፕ፡- ይህቺን ይወዳል ትረምፕ፣


ያቺን ይወዳል ትረምፕ…


ሁሉን ይወዳል ትረምፕ…


እንዴት ባንዷ ታሰረ ጋሽ ትረምፕ!! (በነገራችን ላይ ትረምፕ ልጅ ያሬድን ሲወደው ለጉድ ነው። …

.
በቃ አሁኑኑ ኢራንን እንውረር … አሁኑኑ።


ፔንታጎን፡- ከይቅርታ ጋር ይህን ማድረግ አንችልም ሚስተር ፕሬዝዳንት…


ትረምፕ፡- እኮ ለምን እናንተ ቦቅቧቆች…


ፔንታጎን፡- ምክንያቱም ኢራን ውስጥ የወደቀብንን ስቲልዝ ሰው አልባ አውሮፕላናችንን ለማስመለስ ከኢራን ጋር ድርድር እያደረግን ነው። ከዚህም በተጨማሪ የኢራን በአካባቢው መኖር ለእስራኤል እንደማብረጃ ነው።


ትረምፕ፡- እሺ በቃ ኢራቅን እንውረር!


ሲ አይ ኤ፡- እንደገና?


ትረምፕ፡- ወረናታል እንዴ? … አዎ ልክ ነህ … ለካንስ ወረናታል … ግን ምን ችግር አለው … ይህቺን ወስላታ ሐገር ለምን ደግመንስ ቢሆን አንወራትም…


ሲ አይ ኤ፡- ግን እኮ ወዳጃችን አይስስ 1/3ኛውን ኢራቅ ቀድሞውኑ ተቆጣጥሮ የለ…


ትረምፕ፡- እሺ የተቀረውንስ ቢሆን እንውረራ… እዚሁ ተቀምጠን ምን እንሰራለን ታዲያ… እናንተ ሰዎች ምንድነው እንደዚህ የሚያንቦቀቡቃችሁ - እኔ ሄጄ ልዋጋላችሁ እንዴ…


ሲ አይ ኤ፡- አስፈላጊ ስላልሆነ እኮ ነው ሚስተር ፕሬዝዳንት… አሁን ኢራቅ ላይ ያስቀመጥነው ሺአ መራሹ መንግሥት በራሱ አይስስን እየተዋጋ እኮ ነው…


ትረምፕ፡- በቃ እሺ ሙስሊሞች አሜሪካ ድርሽ እንዲሉ አልፈልግም…


ኤፍ ቢ አይ፡- የማይሆነውን!

 

ትረምፕ፡- እኮ ለምን…


ኤፍ ቢ አይ፡- እንዲያ ካደረግን ሕዝባችን ፍርሃት አልባ ይሆንብናላ… የሚፈራው ነገር ያጣ ሕዝብ ደግሞ ጥሩ አይደለም…


ትረምፕ፡- እሺ በቃ ሕገወጥ ስደተኛ የሚባል ማየት አልፈልግም … ሁሉንም መንጥራችሁ አስወጡልኝ...

 

የአሜሪካ የድንበር ጥበቃ ጓድ፡- ሚስተር ፕሬዝዳንት ይሄን ማድረግ አንችልም…


ትረምፕ፡- እኮ እንዴት…


የአሜሪካ የድንበር ጥበቃ ጓድ፡- ሕገወጥ ስደተኞቹን ካባረርን የድንበር ግድግዳውን ማን ይገነባል…


ትረምፕ፡- እናንተ ሰዎች ምንም ስራ የምታሰሩኝ አይመስለኝም… እንደውም በቃ እውነተኛ አሜሪካዊ ያልሆነ ሁሉ ይህቺን ሐገር ጥሎ እንዲወጣ እፈልጋለሁ…


ስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ፡- ሚስተር ፕሬዝዳንት… ለመሆኑ ወዴት ሐገር ለመሄድ አስበዋል…


ትረምፕ፡- እንዴት ማለት?


ስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ፡- ሚስተር ፕሬዝዳንት፣ ከሬድ ኢንዲያንስ በስተቀር ማንኛችንም ከሌላ አህጉር እኮ ነው የመጣነው…


ትረምፕ፡- እና ታዲያ እዚህ ተጎልቼ ምን ልሰራ ነው። ሐሳቤን ሁሉ ውድቅ እያደረጋችሁ…


ሲ አይ ኤ፡- ሚስተር ፕሬዝዳንት… አያስቡ እርስዎ ኋይት ሐውስን ይንደላቀቁበት፤ እኛ የሚሰራውን እንሰራለን…

 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
668 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 926 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us