ለተማሪዎች ተጨማሪ አጋዥ መጻሕፍት

Wednesday, 01 February 2017 14:04

 

መ.ተ

አንደኛ ደረጃ ትምህርቴን በተማርኩበት ጊዜ አንድ የተማሪ መጽሐፍ ለሁለትም ለሦሥትም አንዳንዴ ለአራት እና ለአምስትም ተሰጥቶናል። የተማሪ ለመማርያ መጽሐፍ ጥመርታው አሁን በእጅጉ ተሻሽሏል። ያኔ ተጨማሪ የጠቅላላ ዕውቀትም ሆነ ማጣቀሻ እንዲሁም የልቦለድ መጻሕፍት ማግኘት የማይታሰብ ነበር። በንጉሠ ነገሥታዊ አገዛዝ ዘመን የተሻለ የእንደዚህ ዓይነት የጠቅላላ ዕውቀት እና የልቦለድ መጻሕፍት እንደነበሩ ግን አሁን ድረስ የዘለቁትን መጻሕፍት ተንተርሶ መመስከር ይቻላል። ይህ  ከብዙ ዓመታት በፊት የሆነ ነው። አሁን በያዝነው የጥር ወር መጀመርያ አካባቢ ደግሞ ከሀገረ አሜሪካ የተሰማው ከተማሪዎች ንባብ ጋር የተሰማው ዜና ደግሞ ብዙዎችን ያስገረመ ነው ተብሎለታል።

የአራት ዓመቷ ሕፃን አንድ ሺህ መጻሕፍት አነበበች መባሉን በመገናኛ ብዙኀን ሰምተናል። የቅድመ ሙዋለ ሕፃናት ተማሪ የሆነችው ይህቺው በአሜሪካ የምትገኝ ሕፃን የንባብ ፍቅር እንዲያድርባት የቤተሰቦቿ ሚና አያጠያይቅም። ብዙዎች ይህን ዜና ያነበቡ ወይም የሰሙ እና ያዩ ሰዎች እኔ ምን ያህል መጻሕፍት አንብቤአለሁ ልጄስ ንባብ ላይ እንዴት ናት/ ነው ብለው መጠየቃቸውም የማይቀር ነው። መልሱንም ራሳቸው ያውቁታል። ከዛም አንፃር ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ ወይንም ያፈነግጣሉ።

ወደ ተነሳንበት ርዕሰ ጉዳይ  ስንመለስ ለልጆቻችን ማለትም ለተማሪዎች ተጨማሪ መጻሕፍት እንደሚያስፈልጉ የተረዳን ምን ያህሎቻችን እንደሆንን የእያንዳንዳችን ቤት ይቁጠረን። መጻሕፍቱ እንደሚያስፈልጉ ግን ምንም አያጠራጥርም። እንዲያውም በዚህ መስክ አንቱ የተባሉ ምሁራን ልጆች (ተማሪዎች) ተጨማሪ መጻሕፍት ቢያነቡ በመደበኛ ትምህርታቸው ውጤት ላይ ገንቢ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ይስማማሉ። የተማሪ መጽሐፍ ውስንነትን በመቀነስ ተማሪዎች አጠቃላይ ዕውቀታቸውን ከፍ እንዲያደርጉም ያግዛሉ። የተማሪዎችን የማንበብ ዝንባሌ በመጨመር አንባቢ ትውልድ በመፍጠሩ ሒደት ወሳኝ ሚናም ይጫወታሉ። በደንብ (በጣም) እንዲያነቡም ያነሳሳል። የኋላ ኋላ የራሳቸውን ሕይወት ራሳቸውን ችለው (ጥገኛ ሳይሆኑ) እንዲመሩም እንደሚያግዛቸው ነው የዘርፉ አጥኚዎች የሚናገሩት።

ተጨማሪ አጋዥ መጻሕፍቱ ተማሪዎቹ ከተማሪ መማርያ መጻሕፍት የዘለለ ዕውቀት እንዲኖራቸውም ያደርጋሉ። ሌሎች የተማሪዎች ሥራዎችን ማለትም ከመደበኛ ትምህርት ውጪ ያሉትን ሥራዎችንም ያበለጽጋሉ። ከዚህም ሌላ ተማሪዎች በግላቸው መረጃ የመሰብሰብ ዓቅማቸውንም ተጨማሪ መጻሕፍት በማንበብ ያጎለብቱበታል። ተጨማሪ መጻሕፍት ለተማሪዎቻችን ማቅረብ ሌሎችም በርካታ ጠቀሜታዎች ይኖሩታል። በሌላ በኩል የተማሪ መጽሐፍ በአንድ ርእሰ ጉዳይ ላይ ብቻ አጠንጥኖ የሚጻፍ ነው። ከመማርያ መጽሐፍ ውጪ ያሉ መጻሕፍት ግን በተለያየ ርእሰ ጉዳይ ላይ ስለሚጻፉ የተማሪውን የመረጠውን ርእሰ ጉዳይ የማንበብ አማራጩንም ያሰፋለታል። እርስዎም የሚያነበውን የመምረጥ ዕድሉን ለልጅዎ ቢተዉ ይመከራል። የተቻሎትን ያህል መጽሐፍ ማቅረቡን ግን አይዘንጉ።

በዚህ መልኩ ከመጻሕፍት ንባብ ጋር ቀድሞ መተዋወቅ  ከኋላ የንባብ እና የአጠቃላይ ትምህርት ስኬት እና ውድቀት እንደሚገናኝ በተደረገ ጥናት ተረጋግጧል።

ጥራት ያለው ትምህርት ያለ ተጨማሪ መጻሕፍት እውን መሆን አይችልም። ይህም ተራ ድምዳሜ ሳይሆን ከተማሪ መማርያ መጻሕፍት (Student Text Book) ውስንነቶች ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው። በማንኛውም ዘመናዊ ሥርዓተ ትምህርት  ተገቢ የሆኑ ተጨማሪ መጻሕፍትን ጨምሮ ሌሎች የንባብ ቁሳቁስ ማሟላት ወሳኝ ነው። ይህን ጥያቄ ወላጆች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላትም ጭምር መመለስ እንዳለባቸው እሙን ነው። ስለዚህ መጻሕፍቱን ወላጆችም ይሁኑ የአካባቢው ማኅበረሰብ ትምህርት ቤትም ሆነ መንግሥት እና የረድኤት ድርጅት ማሟላት ይኖርባቸዋል።

መጻሕፍቱ ከተሟሉ በኋላ ወይም በሒደት እየተሟሉ የሚመጣው ቀጣይ ጥያቄ መጻሕፍቱ የት ይቀመጡ የሚለው ይሆናል። በእርግጥ ይህ ቀላል ጥያቄ ሊመስል ይችላል። መልሱ ግን በተግባር የታገዘ ስለሚሆን ቀላል አይሆንም። ሁላችንም የምንስማማበት ግን ተማሪዎቻችን በቀላሉ ሊያገኙአቸው በሚችሏቸው ቦታዎች ተጨማሪ መጻሕፍቱ ይቀመጡ የሚል ይሆናል። እነዚህም ቦታዎች የተማሪዎቹ መኝታ ቤቶች፣ መጫወቻ ቦታዎች፣ አብያተ መጻሕፍት፣ የተማሪዎቹ ቦርሳ፣ የወላጆች መኪና እና የትምህርት ቤት መጓጓዣ መኪናዎች ወዘተ መቀመጥ ይችላሉ።

በየትኛውም ርእሰ ጉዳይ ላይ ይጻፍ የትም ይቀመጥ በቂ መጻሕፍት አዘጋጅተናል ወይ ብለው ወላጆች፣ መምህራን፣ ትምህርት ቤቶችም ሆኑ መንግሥት ራሳቸው ጠይቀው ራሳቸው እና በወረቀት ያለ ሳይሆን በመሬት ያለ እውነታው የሚመልሱት ጥያቄ መጠየቅ ይኖርባቸዋል። እርስዎ እንደ ወላጅ ይህን እስካሁን አላደረጉ ከሆነ ቢያንስ ከአሁን በኋላ ማድረግ ይችላሉ። ለልጅዎ ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ውጪ በየወሩ አንድ ተጨማሪ መጽሐፍ ለመግዛት በወር የአንድ ሳምንት የልጅዎን የምሳ ወጪ ወይም የመዝኛኛ ማዕከል ወጪን አያክልም። የመዝናኛ ማዕከል ከተነሳ ማዕከላቱ ከነዥዋዥዌ፣ አምሳለ ፈረስ ግልቢያ፣ ሚዛን እና ክብደት… እኩል ለተዝናኚ ልጆች መጻሕፍት ቢያኖሩ ለነገው ትውልድ አንባቢ መሆን ማዕከላቱም አስተዋጽዖ አበረከቱ ማለት ነው።

ስለነዚህ መጻሕፍት በሕንድ በተደረገ ጥናት ከተጠየቁ ተማሪዎች መካከል 97% ለተጨማሪ ንባብ የተቀመጡላቸውን መጻሕፍት እንደወደዷቸው ተናግረዋል። በዚህ መልኩ እየወደዱ የሚያነቧቸው መጻሕፍት ለልጆቹ ዕውቀት መዳበር ብቻ ሳይሆን ለቃላት ሀብታቸው መዳበርም ይጠቅማሉ። የተቀሩት 3% ተማሪዎች ተጨማሪ መጻሕፍቱን ያልወደዱት ተጨማሪ አዲስ ነገር ስላላገኙባቸው መሆኑን ገልጸዋል። መጻሕፍቱ ለተማሪዎቹ በሚገባ ቀላል ቋንቋ መጻፍ እንዳለባቸው መታወቅ አለበት። ይህ በሌሎችም ሀገራት ያለ እውነታ ይመስላል።

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ብዙም ሳይራቅ የተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ፣ የትምህርት እና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) ስለመጻሕፍት አቅርቦቱ በመሠረታዊ የትምህርት ቁሳቁስ ኢኒሸቲቩ “የትምህርትን ጥራት ማሻሻል ተገቢና ደረጃቸውን የጠበቁ መጻሕፍት እና ሌሎች ቁሳቁስ ለተማሪዎቹ ለራሳቸው እና ለመምህራኑ በማቅረብ ላይ ይመሠረታል” ብሏል።

አቅርቦቱን አሻሽለን ተማሪዎቻችን ተጨማሪ መጻሕፍት ማግኘት ሲጀምሩ በመግቢያ ላይ እንደተጠቀሰችው የዐራት ዓመት ሕፃን አንድ ሺህ መጻሕፍት ባያነቡ እንኳ የተሻለ ማንበብ እንደሚችሉ ይታመናል። ልጆችዎ በዚህ መልኩ የንባብን ጎራ ተቀላለቅለው አንባቢ እንዲሆኑ  እርስዎ ምን አስበዋል? የልጆችዎን የነገ ተስፋ በንባብ እራሳቸው እንዲያለመልሙ ዛሬ የእርስዎ ሚና ሚዛን ያነሳል። እና አሁኑኑ ወደ ተግባር ይሒዱ።

(ይህ ጽሁፍ የቀረበዉ ሆሄ የሥነ ጽሁፍ ሽልማት ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር በመተባበር ነው። ሆሄ የሥነ ጽሁፍ ሽልማት የንባብ ባህል እና ሥነ ጽሑፍ በማበረታታት የንባብ ባህል በሀገሪቱ እንዲስፋፋ ለማድረግ፣ በየዓመቱ የላቀ ስራ ለሚያበረክቱ ደራሲያን እና ፀሀፍት ሽልማት እና እውቅና ለመስጠት፣ የልጆች የንባብ ክህሎት ለማዳበር የሚረዱ የተለያዩ ፕሮግራሞችን ለማካሄድ ኖርዝ ኢስት ኢቬንትስ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብት እና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲ በጋራ የሚያዘጋጁት ሽልማት ነው።)

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
641 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 189 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us