የሕፃናት መጻሕፍት ምን አይነት ይሁኑ?

Wednesday, 15 February 2017 13:41

የሕፃናት መጻሕፍት ምን አይነት ይሁኑ?

መ.ተ

 

የሕጻናት (ልጆች) አመጋገብ እና አነባበብ በቅርጹ ተመሳሳይ ይመስላል። ጠንካራ ምግብ እንደማይቀርብላቸው፣ ቢቀርብላቸውም በአግባቡ እንደማይመገቡት ሁሉ ከዕድሜ ደረጃቸው በላይ የሆነ መጽሐፍ ቢቀርብላቸውም አንብበው ይረዱታል ወይም ይዝናኑበታል ማለትም ዘበት ነው። ሕፃናት ምግብን የሚጀምሩት ከወተት በተለይም ከእናት ጡት ወተት ነው። ከዚያ ለስላሳ ምግቦች በመመገብ ነው ጠንካራው ላይ የሚደርሱት ለማለት ሊቅነት አይጠይቅም።

አካልን የሚገነባው ምግብ ከእናት ጡት ወተት እንደሚጀመረው ሁሉ መንፈስን የሚገነባው የልጆች የንባብ ፍቅርም ከቤተሰብ በተለይም ከእናት መጀመር ያለበት ይመስለኛል። እናት ልጅዋን እያጠባች የምታነብ ከሆነ፣ ጨቅላ ልጅዋን በአራስ ቤት እና ከዚያ ቀጥሎ ባሉ ዓመታት እያነበበች የምትንከባከብ ከሆነ ለልጅዋ የወደፊት አንባቢነት መደላድል ትፈጥራለች። ሕፃኑ በቋንቋ ስሜቱን መግለጽ ሲጀምርም ለራስዋ ከምታነበው በተጨማሪ ለልጅዋም ብታነብለት ለአንባቢነቱ መንገድ እያሳየችው ነው። የእናትን አልን እንጂ አባትም ለሕፃን ልጁ ተመሳሳዩን ማድረግ ይችላል። እኩል ኃላፊነትም አለበት።

በዚህ መልኩ ወላጆች ለጨቅላ እና ታዳጊ ልጆቻቸው ያንብቡ እንጂ ወላጅን የመሠጠ መጽሐፍ ሁሉ ለልጅ ይነበባል ማለት እንዳልሆነም ግልጽ ነው። የሊዎቶልስቶይን “ጦርነት እና ሰላም” መጽሐፍ ለእንደዚህ አይነት ልጆች ከማንበብ ለልጆች ተብሎ በቀላል ቋንቋ በአጭሩ የተጻፈ የዚህኑ መጽሐፍ ቅጂ (simplified edition) ማንበቡ መጽሐፉን የልጆች መጽሐፍ ያሰኘዋል።ወይም ደግሞ “ጥንቸሉ ቡቡ” የሚል የተረት መጽሐፍ ልጆችን በቀላሉ ይማርካል።የልጆችን መጻሕፍት የልጆች መጻሕፍት የሚያሰኙ በርካታ የመምረጫ መስፈርቶች አሉ። ከእነዚህም አንዱ በዕድሜ ክልል መሰናዳታቸው ነው።

ከዐሥር እስከ ዐሥራ አምስት ዓመት ለሚሆኑ ልጆች የተጻፈ መጽሐፍን ከአምስት እስከ ሰባት ዓመት ላሉ ሕፃናት እንካችሁ አንብቡ ብለን ብንሰጣቸው በመነበቡ ሊመጣ የታሰበው ውጤት የመምጣቱ ዕድል እጅግ በጣም አናሳ ነው። ከአምስት እስከ ሰባት ዓመት ላሉ ሕፃናት የተጻፈ መጽሐፍም በተመሳሳይ መልኩ ከዐሥር እስከ ዐሥራ አምስት ዓመት ያሉ ልጆችን ላይስብ ይችላል።

በሌላ በኩል ለልጆች የሚጻፉ መጻሕፍት የተራቀቀ እውነታ ያልያዙ ከማስተማር ይልቅ ወደ ማዝናናት ያዘነበሉ ቢሆኑ እንደሚመረጥ ነው በዓለማችን የተለያዩ ክፍሎች በሕፃናት ንባብ እና መጻሕፍት ላይ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች የሚናገሩት።ባለሙያዎቹ ለጥናታቸው ራሳቸውን ሕፃናቱን፣ ወላጆቻቸውን፣ መምህራንን እና ከሕፃናት መጻሕፍት ጋር ተያያዥነት ያላቸው ተግባራት የሚያከናውኑ ሌሎችን በጥናታቸው አካትተዋል።

በተጠቀሰው ጥናት እና በሌሎችም ጥናቶች እንደተጠቀሰው ለሕፃናት የሚጻፉ መጻሕፍት በብዙ ማራኪ ሥዕሎች የተሞሉ እና ጥቂት ጎላ ጎላ ያሉ አጫጭር ጽሑፎች ያሉዋቸው መሆን ይኖርባቸዋል። የልጆቹ ዕድሜ በአነሰ ቁጥር በጽሑፍ የተያዙ ገጾች መጠንም ይቀንሳል። እድሜአቸው ሲጨምር ግን በአንጻሩ መጽሐፉ በገጽም በይዘትም እየጨመረ ይሔዳል። ይህን ከሚወስኑ ነገሮች አንዱ መጻሕፍቱ የተጻፉበትን ዓላማ መገንዘብ ነው።

የሕፃናት መጻሕፍት ዓላማ ማዝናናት ላይ ያተኩራል። ማሳወቅ ከዚያ በኋላ የሚመጣ ነው። ስለዚህም ነው ለሕፃናት የሚዘጋጁ መጻሕፍት ጥቅጥቅ ባለ ይዘት ብዙ ገጽ የሆነ መጽሐፍ በብዙ ርዕሰ ጉዳዮች ጋር የማይዘጋጀው። መጠነ ጽሑፉም ደቀቅ ያለ ሥዕሎቹም በተለያዩ ቀለማት ያሸበረቁ መሆናቸው በቀጥታ መጻሕፍቱ ከሚዘጋጁበት ዓላማ ጋር ይያያዛል።

ከዓላማ ጋር ተያይዞ ሊነሳ የሚችለው ሌላው ጥሩ የልጆች መጻሕፍት እንዴት አይነት ናቸው የሚለው ጥያቄ ነው። ጥሩ ሊባሉ የሚችሉ የልጆች መጻሕፍት ሊያሟሉ የሚችሏቸው በርካታ ነገሮች አሉ። ከእነዚህም አንዱ ማራኪ መሆን መቻላቸው ነው። ይህን ለማምጣት በተለይም ከንባብ ጋር ለመጀመርያ ጊዜ ለሚተዋወቁ ጨቅላ ሕጻናት የሚዘጋጁ መጻሕፍት ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው በሥዕል የተንቆጠቆጡ እንዲሆኑ ይመከራል። ይህም ብቻ ሳይሆን አጨራረሳቸው አስደሳች (happy Ending) ቢሆን የተሻለ እንደሚሆን ነው የሚመከረው። ከዚህ አንፃር አጨራረሳቸው አሳዛኝ የሆኑ መጻሕፍት ክፉ እና ደጉን መለየት ለማይችሉ ጀማሪ አንባቢዎች ማቅረቡ ብዙም ጠቀሜታ ላይኖረው ይችላል ነው የሚባለው። ለልጆች የሚጻፉ መጻሕፍት በብዛት የተረት ከመሆናቸውም አንጻር ማጠቃለያቸው ምክር በመሆኑ ለልጆቹ ስብዕና ግንባታ በጣም ያግዛል።

ከዚህም ጋር አብዛኞቹ የልጆች መጻሕፍት ገጸባሕርያት እንስሳት እና ጨረቃ፣ ጸሐይ እና እንጨትን የመሳሰሉ ግኡዛን አካላት እንደሆኑ ይታወቃል። ታሪኮቻቸውም በቀለማ ቀለም ከማማራቸውም ሌላ እንደተጠቀሰው ከሚያስቆጣ፣  ከሚሳዝን እና ደስ የማይል ስሜት ከማስከተል የፀዱ መሆን ይኖርባቸዋል።  ስለዚህም እርስዎ እንደወላጅ ለልጅዎ መጽሐፍ ሲገዙ እነዚህን ነገሮች ከግምት ውስጥ ማስገባትዎ የግድ ነው። እስካሁን ለልጅዎ መጽሐፍ ሲገዙ እንደዚህ አድርገው ያውቃሉ? አደረጉ ከሆነ መልካም። አላደረጉም ከሆነ አሁንም ጊዜው አልረፈደም ለልጅዎ የአዕምሮ ምግብ እነዚህን ማድረጉን ከወዲሁ ሊለምዱት ይገባል።

የሕፃናቱ መጽሐፍ ቋንቋም ቀለል ያለ እና ከአሻሚነት የፀዳ መሆን እንዳለበት ይመከራል። ርዝመታቸውም ለእያንዳንዱ የዕድሜ ክልል እንዲሆኑ ሆነው አጠር እና ረዘም ሊሉ ይችላሉ።  ይህ ማለትም ከሰባት እስከ ዐሥር ዓመት ዕድሜ ላላቸው ልጆች የሚጻፉት መጻሕፍት ከሰባት ዓመት በታች ላሉ ሕጻናት ከሚጻፉት ይበልጥ  ይረዝማሉ። ከሰባት እስከ ዐሥር ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሕጻናት ከነሱ በእድሜ ከሚያንሱ ሌሎች ሕፃናት የበለጠ ለረዥም ጊዜ ሊያነቡም ይችላሉ በሌላ በኩል። እርስዎ ለልጆችዎ መጽሐፍ ሲመርጡ በአካባቢዎ የሚገኝ የቤተመጻሕፍት ባለሙያ ማማከርም አይከፋም። ይህን አይነት ባለሙያ በቅርበት የማያገኙ ከሆነ የሚከተሉትን አምስት ወሳኝ ጥያቄዎች ጠይቀው መመለስዎ ወላጅ ለሆኑት ለእርስዎ አስፈላጊ ይመስላል።

 

መጽሐፉ ለልጄ ይሆናል?

ምርጫውን ለራሱ ለልጅዎት ተው፤ ለልጅዎ መጽሐፍ መምረጥ እንዳለ ሆኖ ከእርስዎ የተሻለ ማንም እንደማይገኝ እሙን ነው። ስለዚህ ልጅዎ የሚያነበውን መጽሐፍ እንዲመርጥ ዕድሉን ሰጥተው እርስዎም ተስማሚውን መጽሐፍ ለልጄ ይሆናል ወይ ብለው ይምረጡለት /ይምረጡላት። የልጅዎን ልዩ ፍላጎት እና ሥነልቦናም ስለሚያውቁ በምርጫዎ ብዙም የሚቸገሩ አይመስልም።

 

 

የመጽሐፉ ሥዕሎች በደንብ ተሥለዋል?

ሥዕሎቹ በተለይ ከ4 እስከ 8 ዓመት ላሉ ሕፃናት ለሚጻፉ መጻሕፍት ቁልጭ ብለው የሚታዩ ግልጽ መሆን አለባቸው። ከሚወክሏቸው ታሪኮችም ጋር መገጣጠም ይኖርባቸዋል። ቃል አልባ የሥዕል መጻሕፍትም የልጆቹን የቃላት ሀብት ለማዳበር ጥሩ ምንጭ ናቸው። ከነዚህም ሌላ ታሪኩ በደንብ ተጽፏል? ጽሑፉ ስመረጃ ሰጪ እና ጣዕም ያለው ነው? የሚሉ እና የመጽሐፉ ጭብጥስ ጊዜ አይሽሬ ነውወይ ብሎ መጠየቅም ይችላሉ።

ይህ ጽሑፍ በሆሄ የሥነፅሑፍ ሽልማት ፕሮግራም የቀረበ ነው። ሆሄ የሥነጽሑፍ ሽልማት የንባብ ባህል እና ሥነፅሑፍን በማበረታታት የንባብ ባህል በሀገሪቱ እንዲስፋፋ ለማድረግ፣ በየዓመቱ የላቀ ሥራ ለሚያበረክቱ ደራሲያን እና ፀሐፍት ሽልማት እና እውቅና ለመስጠት፣ የልጆች የንባብ ክህሎት ለማዳበር የሚረዱ የተለያዩ ፕሮግራሞችን ለማካሄድ ኖርዝ ኢስት ኢቨንትስ ከአ/አ ዩኒቨርሲቲና ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመፃሕፍት ኤጀንሲ ጋር በጋራ የሚያዘጋጁት ሽልማት ነው።¾

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
1045 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 191 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us