የመስኖ ልማት በዴዴሳ ወንዝ

Wednesday, 01 March 2017 12:11

 

-    ለአንድ ኮንትራክተር ለምን ተሰጠ? ውጤቱስ ምን ይመስላል?

በሽመልስ ሙላቱ

መግቢያ

ኢትዮጵያ 1.13 ሚሊዮንስኩዌር ኪሎሜትር ስፋትያላትሰፊአገርናት።ከዚህውስጥ 74.3 ሚሊዮን ስኩዌር ኪሎ ሜትር (67%) መሬት ሊታረስ የሚችልና ለእርሻ ምቹ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ። በተመሳሳይ መልኩ ምቹ ነው ተብሎ ከሚገለፀው የሀገሪቱ የእርሻ መሬት 5.3 ሚሊዮን ሄክታሩ የገፀ ምድርና የከርሰ ምድር ውሃን በመጠቀም በመስኖ ሊለማ እንደሚችል ይገለፃል። የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው በኢትዮጵያ ለግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ ከዋለው አጠቃላይ መሬት 15 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በኋላቀርአስተራረስ ዘዴ የሚለማና ከዝናብ ጥገኝነት ያልተላቀቀ ነው። የዚሁ ሚነስቴር መስሪያ ቤት መረጃ እንደሚያመለክተው  በኢትዮጵያ በአነስተኛ የመስኖ ልማት እየለማ የሚገኘው መሬት 2.4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ነው።

የሀገራችን ኢኮኖሚ በየዓመቱ እመርታዊ ዕድገት እንዲያስመዘግብና ቀጣይነቱ እንዲረጋገጥ የግብርናው ዘርፍም ለኢኮኖሚው ማደግ የሚገባውን ሚና መወጣት እንዲችል የመስኖ ልማት ዋነኛ ምሰሶ ነው። የመስኖ ልማት ወቅትን ሳይጠብቁና ዝናብን ሳይጠብቁ ዓመቱን ሙሉ የሚያመርቱበት የግብርና ዘዴ እንደመሆኑ የሀገሪቱን አጠቃላይ ዓመታዊ የምርት መጠን በመጨመር የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ለተቀሩት የኢኮኖሚ ዘርፎች ማበብ የራሱን ሚና ይጫወታል።   

የመስኖ ዘርፍ በርካታ መዋዕለ ንዋይ የሚጠይቅና በውሃ ምህንድስና እውቀት ሰፊ የተማረ የሰው ሃይል የሚጠይቅ በመሆኑ ሀገርና ህዝብ የሚፈልገውን ያህል ብሎም መንግስት በሚያቅደው ልክ የተራመደ ዘርፍ ነው ለማለት አያሰደፍርም። ይህም ሆኖ መንግስት ለውሃ ሃብት ዘርፍ አስፈላጊውን የፖሊሲ ማዕቀፍ ከማርቀቅ አንስቶ እስከ ማፅደቅና ስትራቴጂ እሰከ መዘርጋት ብሎም ወደ ትግበራ በመግባት ግብርናውን ከተፈጥሮ ጥገኝነት በማላቀቅ የግብርና ምርት እና ምርታማነትን እንዲሁም ጥራትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን በቤተሰብና በአገር አቀፍ ደረጃ ለማረጋገጥ ባለፉት ዓመታት የበኩሉን ጥረት ማድረጉ ግን የማይካድ ሃቅ ነው። 

ሀገሪቱ እንደ እ.ኤ.አ በ 2025 ዓ.ም መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለማሰለፍም ራዕይ የሰነቀች ሲሆን በየዓመቱ በአማካኝ 10 በመቶ እድገት ማስመዝገብ ግቡን ለማሳካት እንደሚያስችላት የኢኮኖሚ ጠበብቶች ይናገራሉ። እንግዲህ  ‘ይህንን ትልቅ ራዕይ የሰነቀች ሀገር የመስኖ ልማቷን በምን መልኩ እያስኬደች ነው፣ በሀገሪቱ በመገንባት ላይ ያሉ የመስኖ ፕሮጀክቶች ምን ያህል ዓላማቸውን አሳክተዋል፣ ሀገሪቱ መካከለኛ ገቢ ሀገራት ድረስ ለመድረስ የምታደርገውን ጥረትና ወደ ኢንደስትሪ መር ኢኮኖሚ ለምታደርገው ሽግግርስ እነዚህ የመካከለኛና ሰፋፊ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ምን ያህል ድርሻ ይኖራቸዋል፣ ግቡን ለማሳካት በተቀመጠው እስከ እኤአ 2025 ድረስ ወይም ከዚያ በፊት ባሉት ጊዜያት እቅዱን ለማሳካት ከእያንዳንዱ ምን ይጠበቃል?’ የሚለው ጥያቄ አግባብ ይሆናል።

የአየር ንብረት ለውጥ፣ የህዝብ ቁጥር ማደግ ሰው ሰራሽና ተፈጥሮአዊ አደጋዎች ለማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች በአለም ላይ መፈልፈል ሁነኛ ምክንያት መሆናቸውን በየዕለት ዕለት እንቅስቃሴ የምናያቸውና የዜና አውታሮች የምንሰማቸው እንደ ረሀብ፣ ድርቅ፣ ቸነፈር፣ ስደትና ጦርነት ያሉ ክስተቶች በቂ ማስረጃዎች ናቸው። አለማችን  ተጋርጦባታል ከሚባለው ሽብርተኝነት ያልተናነሱም ስጋቶች ናቸው። ይህን ለሀገራትና ለህዝቦች ከባድ ፈተና የሚደቅኑ ችግሮችን ለመቋቋም ደግሞ መጪውን ጊዜ ታሳቢ ያደረገ የዘላቂ ልማት ዕቅድ በማቀድና የተቀናጀ አሰራር በመፍጠር መተግበር ወሳኝ ነው። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ለልማት ምቹ የሆነ የተፈጥሮ ሃብት ያላት በመሆኑ ሃብቱን በማልማት ያለውን ዕድል መጠቀም፣ ክፍተቱን በመሙላት የዜጎችን ህይወት መለወጥና ያለመችውን ራዕይ ማሳካት የምትችል ይሆናል።

አባይ ተፋሰስና የአርጆ ዴዴሳ ግድብ መስኖ ልማት ፕሮጀክት

የአባይ ተፋሰስ (Blue Nile) 199,812 ኪሎ ሜትር ስኩዌር ይሸፍናል። ተፋሰሱ ሦስት ክልሎችን አማራን፣ ኦሮሚያን እና የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልልን የሚሸፍንና ጥቁር አባይ የምንለውን ወንዝ ለመስራት በርካታ ወንዞችን ከበርካታ የመልከዓ ምድር አቀማመጦችና ህዝቦች ባህል ጋር አዋዶ ሰብስቦ የያዘ ተፈጥሮ ለኢትዮጵያ የለገሰው ገፀ በረከትና ምናልባት ፈጣሪ ኢትዮጵያን በሌሎች ሀገራት እንድትታወቅ (Branding) ለማድረግ የሞከረበት ሙከራ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።

በውሃ ሃብቱ መጠን ከሁሉም የላቀ ኢትዮጵያን ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር ከደም በሚቀጥነው ምናልባትም ከአለማችን ውድ በሆነው የተፈጥሮ በረከት በሆነው ውሃ ያስተሳሰረ፣ ከታላላቅ የአለማችን መፅሀፍቶች መፅሀፍ ቅዱስ አንስቶ እሰከ የታሪክ አባት በተባለው የግሪክ ፈላስፋ ሄሮደተስ ብዙ የተባለለት ነው አባይ ።

የአባይ ተፋሰስ ሲነሳ ብዙ ስላልተባለላቸውና ስላልተዘመረላቸው፣ ትልቁን አባይ ስለሚፈጥሩትና ለሀገራችንም ልማት የማይናቅ አስተዋፅኦ ስላላቸው ገባር ወንዞች ማንሳትና ማነሳሳት ግድ ይላል። ከዚህ አንፃር የዚህ ፅሁፍ ዓላማም ሀገሪቱ  በመስኖ ልማት ረገድ ምን ያህል ርቀት ተጉዛለች በሚል ተጠየቅ የዴዴሳ ወንዝ ላይ ስለሚገነባው የአርጆ ዴዴሳ ግድብና መስኖ ልማት ፕሮጀክት ግንባታን በወፍ በረር ማስቃኘት ነው።

የመስኖና የስኳር ልማት ትስስር ድሮና ዘንድሮ

ባለፉት መንግስታት ሀገሪቱ ያላትን የውሃ ሀብት በመጠቀም በመስኖ ለማልማት የተሞከረው በጣም ጥቂቱን ነው። ካሉት 12 ተፋሰሶች የአዋሽና የአባይ ተፋሰስን ጥቅም ላይ ለማዋል ተሞክሯል። ዛሬ የኢትዮጵያን ህዝብ የስኳር ልማት ፍላጎት በማሟላት ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ከሚገኙት የስኳር ፋብሪካዎች የመተሀራ፣ የወንጂ ሸዋና የፊንጫ ስኳር ፋብሪካዎች ግብዓት የሚውለውን የሸንኮራ አገዳ ለማልማት የተሞከረው በአዋሽና በአባይ ተፋሰስ ወንዞች አማካኝነት መሆኑን በዘርፉ ላይ የተፃፉ የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ።

ይሁንና 1984 .ም ወዲህ ለመስኖ ልማት ልዩ ትኩረት በመስጠት የሚመራበትን ፖሊሲና ስትራቴጂ በመቅረፅ ዘርፉን ይበልጥ ለማሳደግ ጥረት ተደርጓል፣ በመደረግም ላይ ይገኛል። 

ዘርፉ ምንም ዓይነት የመሠረተ ልማት አውታሮች ባልነበሩበት፣ ለዘርፉ ልማት የሚውል በቂ ፋይናንስ በሌለበትና የዘርፉ ልምድና የማስፈፀም አቅም ውስን በነበረበት ሁኔታ ሥራው የተጀመረ ከመሆኑ አኳያ ሲታይ አሁን የተደረሰበት ደረጃ አበረታችና ተስፋ ሰጪ ነው። ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው ባለፉት አስርት ዓመታት ከላይ የተገለፁት በኢትዮጵያ የስኳር ምርት ፋና ወጊ የነበሩት የመተሃራ፣ ወንጂ ሸዋና ፊንጫ ፋብሪካዎች የማሻሻያና የማስፋፊያ ስራዎችን ጨምሮ በርካታ ለስኳር ኢንደስትሪ መስፋፋትም ሆነ በአጠቃላይ ለግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ ማደግ መሠረት የሚሆኑ የመስኖ ግድቦች በሁሉም ክልሎች መገንባት የጀመርንባቸው ዘመናት ናቸው። በእነዚህ ታላላቅ ተግባራት ምንም እንኳን ከህዝባችን ቁጥር መጨመር የተነሳ የስኳር ፍላጎትን ሙሉ በሙሉ መመለስ ባይቻልም ሀገሪቱ ያላትን የውሃ ሃብት መጠቀም በመጀመር በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ጉልህ አስተዋፅኦ በማበርከት (እንደ ቆጋ ያሉ የተጠናቀቁ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶችን መጥቀስ ይቻላል) ለብዙ ዜጎችም የስራ እድል በመፍጠር እንዲሁም አገሪቱስኳርከውጭለማስመጣትታወጣየነበረውንከፍተኛየውጭምንዛሬማዳን ከፍተኛ ጥረት የተደረገበት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ጅማሮ ነው ማለት ይቻላል።

የዴዴሳ ወንዝና የአርጆ ዴዴሳ ግድብ መስኖ ልማት ፕሮጀክት

የግብርና ምርቶችን በዓይነትና በጥራት ለማሳደግ ብቻ ሣይሆን ከግብርና ወደ ኢንዱሰትሪ የሚደረገውን መዋቅራዊ ሽግግር የሚሰፋበትና የሚፋጠንበት ጭምር ነው። ይህን መዋቅራዊ ሽግግር ተግባራዊ ለማድረግ በዕድገትና በትራንስፎርሜሽን ዕቅድ (GTP-1 እና GTP-2 ያስተውሏል) ከተያዙ ዕቅዶች መካከል የስኳር ልማት ንዑስ ዘርፍ ዋንኛው ነው።

ለስኳር ልማት ኢንደስትሪ መስፋፋት ምቹ የአየር ንብረትና የተፈጥሮ ሃብት ያላት ኢትዮጵያ በዘርፉ ሙሉ እቅምን አሟጣ ለመጠቀም የፋይናንስ እጥረት ትልቅ ፈተና ቢሆንም መንግስት ዘርፉን በራሱ ለመገንባት ተነሳሽነት በመውሰድ በርካታ የመስኖ ግድቦችን በመገንባት ላይ ይገኛል። የአርጆ ዴዴሳ ግድብና የመስኖ ልማት ፕሮጀክትም በመንግስት ሙሉ ወጪ እየተገነቡ ከሚገኙት የመካከለኛና ሰፋፊ የፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ነው።

ዴዴሳ ወንዝ በአባይ ተፋሰስ ውስጥ ከሚገኙት 16 ንዑስ ተፋሰሶች አንዱና በሚሸፍነው የተፋሰስ ሽፋንም ትልቁ ነው። የዴዴሳ ወንዝ 19,630 ኪሎ ሜትር ስኩዌር የሚሸፍን ሲሆን አባይ ብለን ለምንጠራው ትልቁ ወንዝም 25 በመቶ የውሃ ድርሻ የሚያበረክትና የኦሮሚያ አራት ዞኖችን የጅማ፣ የኢሉ አባቦር፣ የምዕራብና የምሰራቅ ወለጋ ዞኖችን የሚያካልል ነው።

በርካታ የተለያዩ መፅሀፍትን መመልከትና የዘርፉን ባለሞያዎች ማነጋገር እንደተቻለው የዴዴሳ ወንዝ መነሻ ስፍራ ከዚህ ነው ብሎ መናገር የሚያስቸግር ቢሆንም ብዙዎቹ ለዚህ ፅሁፍ ግብዓት የተመለከትኳቸው መፅሀፍትና የጂኦ ሪሞት ሴንሲንግ መረጃዎች እንዲሁም ቃለ ምልልስ ያደረግኩላቸው ባለሞያዎች ከጅማ ዞን ሊሙ ሰቃ ወረዳ ከሚገኘው ጎማ ከሚባለው ስፍራ እንደሆነ ይስማማሉ። ዋና ዋና ገባር ወንዞቹም ዋማ እና አንገር (ግድቡ አሁን እየተገነባበት ከሚገኘው ከምስራቅ በኩል) እንዲሁም ዳበና እና ነጋዴ የተባሉት ወንዞች ደግሞ ከምዕራብ በኩል ናቸው። በነገራችን ላይ የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ከላይ ከጠቀስኳቸው ገባር ወንዞች በተለይም ስለ ዳበና በኦሮምኛ የተዘፈነ ዘፈን መኖሩንም ልብ ይሏል።

ዴዳሳ ከላይ የተገለፁትን ገባር ወንዞች ብቻ አይደለም የሚጠቀመው፣ ወደ 14 የሚጠጉ አነስተኛ ወንዞችንም ጭምር ጠራርጎ ከአባይ ጋር ወይም ከአባይ ሌላኛው ገባር ጋር ይገናኛል። ከአንድ የአካባቢው ነዋሪ ማረጋገጥ እንደቻልኩትም ዴዴሳ ከጅማ ዞን ጎማ ተነስቶ ወደ ሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ በመፍሰስ አባይን ከወደ ደቡብ ጫፍ ላይ ያገኘዋል። ከነቀምት ነጆ ያለውን መንገድ ተከትሎ መገንጠያው ላይ ወደ ቤንሻነጉል ክልል በሚወስደው መንገድ ዳቡስን ይዞ ነው አባይ የሚሆነው ሲሉ አጫውተውኛል። ውሃ የተጠማውን የሱዳንና የግብፅን በረሀንም በዚሁ መልኩ ህይወት ይዘራበታል ጋራ ሸንተረሩን፡ ሸለቆ ሜዳውን እየዞረ ብለውኛል። 

ጥናቶች እንደሚያሳዩት ዴዴሳ ወንዝ ላይ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክት የመጀመርያ ጥናት እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን የአባይን ወንዝ ለማጥናት በአሜሪካ መንግስት ድጋፍ USBR (United States Bureau of Reclamation) በተባለ ድርጅት አማካኝነት የጀመረ ሲሆን በኋላም ተቀማጭነቱ አሜሪካን ሀገር በሆነ ታምስ (TAMS) በተባለ አማካሪ ድርጅት አማካኝነት እ.ኤ.አ በ1975 ዓ.ም ተካሂዷል። በሁለቱም ጊዜ በተካሄዱት ሰፊ ጥናቶች የተገኙት ውጤቶች ያሳዩት በወንዙ የላይኛው ተፋሰስ በኩል ለሀይል ማመንጫና ለመስኖ ልማት ሊውል የሚችል በርካታ ግድቦችን መገንባት እንደሚቻል ሲሆን ጥናቶቹ በቀጣይም ለተካሄዱ ሌሎች ጥናቶች ፈር ቀዳጅ ነበሩ። ሳይጠቀስ መታለፍ የሌለበት ሌላኛው ጥናትም የኢትዮጵያን 12 ተፋሰሶች በአጠቃላይ ለማጥናት በተሰማራው WAPCOS (Water and Power Consultancy Service) በተባለ የህንድ አማካሪ ድርጅት አማካኝነት የተካሄደው ነው። በዚህ ጥናት የተለየ ነገር ቢኖር ለግድብ ግንባታ ሊውሉ ይችላሉ የተባሉ ሁለት የሃይድሮ ፓወርና የመስኖ ግድብ ስፍራዎችን ማመላከት ነበር።

በዚሁ መልክ የቀጠለው ቅድመ ጥናት በመጨረሻ በሀገር ውስጥ ተቋም በሆነው የፌዴራል የውሃ ስራዎችና ዲዛይን ቁጥጥር ድርጅት ተካሂዶ ሙሉ የዲዛይን ስራም ተከናውኖለት የአርጆ ዴዴሳ ግድብና መስኖ ልማት ፕሮጀክት በሚል 80 ሺህ ሄክታር ለማልማት በኦሮሚያ የውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት የስራ ተቋራጭነት  እንዲሁም እህት ድርጅት በሆነው የኦሮሚያ ውሃ ስራዎች ዲዛይንና ቁጥጥር አማካሪነት በውሃ መስኖና አሌክትሪክ ሚኒስቴር ባለቤትነት በ2003 ዓ.ም ወደ ሥራ ተገባ።

ጥናቱ አስፈላጊውን የጥናት ደረጃዎችን በሙሉ አልፎ ለዲዛይን የበቃና ወደ ስራ የተገባ ቢሆንም ችግሮች መስተዋል የጀመሩት ገና በሁለተኛው ዓመት ነበር ይላሉ የአማካሪው ድርጅት የኦሮሚያ ውሃ ስራዎችና ዲዛይን ቁጥጥር ኢንተርፕራይዝ  ባለሞያ ኢንጂነር መላኩ አለሙ።

ዋናው የሚባለው የዲዛይን ችግር  በፊት ሳይታዩ የቀሩና ወደ ስራው ተገብቶ የተስተዋሉ ከዳይቨርሽን ኮንዲዩት/diversion conduit እና ከማስተንፈሻ ግድብ (Spill way) ጋር የተያያዙ ናቸው። የክረምት ውሃን ሙሉ በሙሉ በማሳለፍ የውስጣዊ ስርገት መከላከያ (coffer dam) የሚባለውን ኦቨርቶፕ እንዳያደርግ ተብሎ ዲዛይን የተደረገው ከአቅም በታች ሆኖ በመገኘቱ የዲዛይን ለውጥ አሰፈለገ የሚሉት ባለሞያው የተወሰደው የመፍትሄ እርምጃም የዲዛይን ክለሳና በማስተንፈሻ ግድብ በሚገነባበት ስፍራ ላይ ተጨማሪ የማስተንፈሻ ስራ መስራት ነው ብለዋል።

የዲዛይን ክለሳው ራሱ ለመጓተቱ አንድ ምክንያት ይሁን እንጂ ተጨማሪ ምክንያቶችም መኖራቸውን የሚጠቅሱት ኢንጂነር መላኩ እነዚህም የኮንትራክተር አቅም ማነስ፣ ከካሳ ክፍያ ጋር ያሉ ጉዳዮች በወቅቱ ያለመፈታትና የአካባቢው ስነ ምህዳር ለ6 ወራት የዝናብ ወቅት መሆናቸው ናቸው ይላሉ። እነዚህን ችግሮችን በዝርዝር ለመረዳት ይበልጥ የሰው ጉዳይ ያሳስበኛልና ልማትም ሰው ተኮር መሆን ይኖርበታልና በተለየ ሁኔታ ትከረቴን ስለሣበው ከካሳ ክፍያ ጋር ያሉ ችግሮችን እንዲያጫውቱኝ ጠየቅኳቸው። 

“በግድቡ ዙርያ ሰዎች ከሀረር አካባቢ የመጡ ሰፋሪዎች ናቸው። በ 1995 ዓ.ም ሀረር አካባቢ ድርቅ በመከሰቱ እዚህ መጥተው እንዲሰፍሩ ነው የተደረገው። አሁን በዚህ ፕሮጀክት ምክንያት እዚህ እንዲሰፍሩ የተደረጉትን ሰዎች ወደ ሌላ አካባቢ እንዲሰፍሩ/relocate ወደ ማድረግ ግዴታ ውስጥ ተገብቷል። በዚህ ምክንያት ብዙ ችግር ተፈጥሯል። በእርግጥ ምንም አይነት የግንባታ ስራ ሳይጀመር እነዚህን ሰዎች መነሳትም ካለባቸው በአግባቡ ተነጋግሮ የማስነሳት ስራ መጀመር መኖር ነበረበት ወይም የግድቡ ግንባታ እዚህ አካባቢ መሆኑ ከታወቀ ወደ ሌላ አካባቢ እንዲሰፍሩ ማድረግ ቢቻል ጥሩ ነበር። ለችግር ከመጋለጣቸው በፊት የማህበረሰብ ግንባታ ስራ ሊመቻች ይገባ ነበር። ይህ ባለመሆኑ አንደኛ ለግንባታው መዘግየት የራሱ ድርሻ አበርክቷል፣ የመጓተት ሁኔታዎችን ፈጥሯል። ከምንም በላይ ህብረተሰቡ የሚንገላታበት ሁኔታ በስነ ልቦና ላይ የሚፈጥረው የራሱ ጫና ደግሞ ሌላው ትልቅ ችግር ነው” ሲሉ ይገልፃሉ።

ውሃ የሚተኛበት /reservoir ክልል ወደ 11,000 ሺህ ሄክታር በላይ ይሸፍናል። በግንባታው ምክንያት ይፈናቀላሉ ተብለው የሚገመቱት የህብረተሰብ ክፍሎች በዚሁ አካባቢ የሚገኙ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ለግደቡ ግንባታ ጥቅም ላይ የሚውሉ ማቴርያል የሚመረትባቸው አካባቢዎቸ ናቸው። ይህን የመፈናቀል አደጋ ተጋርጦባቸዋል፣ የካሳ ክፍያ ያልተከፈላቸውና የይገባኛል ጥያቄ ያነሳሉ ስለተባሉ አርሶአደሮች ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተወከሉትን በግድቡ ስፍራ የማህበረሰብ ልማት አስተባበሪ የሆኑትን አቶ ምህረት አዲሱ አነጋግሬ እንደተረዳሁት በሁለት ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ በኢሉባቦራና በጅማ ዞን ውስጥ የሚገኙ በጅማ ዞን በኩል ሊሙ ሰቃ በኢሉአባቦራ ዞን ደግሞ የቦሬቻ ወረዳ ውሃው የሚተኛበት በመሆኑ ውሃው ወደ ኋላ ሲመለስ 2296 የሚደርሱ የህብረተሰብ ክፍሎች/አርሶአደሮች አባወራዎችና እማወራዎች እንደሚፈናቀሉና ይሁንና የካሳ ክፍያ እየተፈፀመላቸውና የተለያዩ የመሠረተ ልማት አገልግሎቶችን በማሟላት የማስፈር ስራም ጎን ለጎን እየተከናወነ መሆኑን ይናገራሉ።

ከ2296 አባወራዎች ውስጥ በመጀመርያ ዙር ይነሳሉ ተብለው ከታሰቡት 693 አባወራዎች ካሳቸው ተሰርቶ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ደርሶ ገንዘብም ለወረዳዎች ተልኮላቸው ክፍያው መፈፀሙን የሚናገሩት ባለሞያው ፕሮጀክቱ ለግንባታው ጥቅም ላይ የሚያውለውን የሸክላ አፈር ለማውጣት በሚያደርገው ጥረት በግንባታ ምክንያት የሚፈናቀሉ ደግሞ 275 አባወራዎች መሆናቸውን ምትክ መሬትና ካሳም የተከፈላቸው መሆኑን ገልፀዋል።

በአጠቃላይ በሁለቱም ዞን ባሉ ሁለት ወረዳዎች በሪዘርቫዬሩ አካባቢና በግድቡ የግንባታ ማቴርያል ምክንያት ይፈናቀላሉ ተብሎ የሚገመተው 4446 አባወራዎች ናቸው ያሉን አቶ ምህረት አዲሱ በኢሉአባቦራ በኩል ያለው የቦሬቻ ወረዳ ምንም አይነት መሬት ባለመዘጋጀቱ ምክንያት በ2007 ዓ.ም የውሃ መጥለቅለቅ ተከስቶ የተፈናቀሉና  አሁንም ድረስ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ስለሚገኙ ከ121 እሰከ 200 የሚደርሱ አባወራዎች ሁኔታም አብራርተዋል።  ሸራ ዘርግተው ተጠልለው ስለሚገኙት እነዚሁ ተፈናቃዮች ሲገልፁ በኦሮሚያና በፌዴራል መንግስት የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አማካኝነት እርዳታ እየተሰጣቸው እንደሚገኝና የዞኑ አስተዳደርም 9 ሺህ ሄክታር ነፃ መሬት እንዳለውና ለእነዚሁ ሰዎች ከግድቡ ወደ 160 ኪሎ ሜትር በሚጠጋ መኮ በሚባል አካባቢ ለማስፈር ዝግጅት መጠናቀቁን  አብራርተዋል።

ለፕሮጀክቱ መጓተት ምክንያት ተብለው ከሚገለፁት ሌላው የኮንትራክተር አቅም ማነስን አስመልክቶም ስለ ኮንትራክተሩ የኋላ ታሪክ ለመረዳት ጥቂት እንዲነግሩኝ ኢንጂነር ጌታቸው እሸቱ የተባሉ የተቋራጩ ድርጅት ባለሞያን አነጋገርኩ።

የኦሮሚያ ውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት በ1997 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ የተመሠረተ ድርጅትና ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በርካታ ትላልቅና መካከለኛ ፕሮጀክቶችን ሲሰራ መቆየቱን አጫወቱኝ። የተለያዩ የንፁህ የመጠጥ ውሃና የመስኖ ፕሮጀክቶችን እንደ ሀገርም እንደ ክልልም ሲሰራ መቆየቱን ለማሳያም በክልል ደረጃ በቤቶች ግንባታ፣ የአዳማ የሰማዕታት ሀውልትን፣ የአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ግንባታ፣ የነቀምት ስቴዲየምን በመጠጥ ውሃ የሶማሌ ክልል የጅጅጋ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክትን፣ የሀረርና የጊንቢ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት፣ እንዲሁም በቆላማ የውሃ እጥረት ባለባቸው እንደ ቦረና ጉጂ ያሉ አካባቢዎች  የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን በመስኖ በኩል የወለንጪቲ የመስኖ ልማት የስኳር ፕሮጀክትን ጭምር በመገንባት ታላላቅ ሀገራዊና ክልላዊ ፋይዳ ያላቸውን ተግባራት በስኬት ማጠናቀቁን ይገልፃሉ።

አቶ ጌታቸው ስለ አርጆ ዴዴሳ ግድብና የመስኖ ልማት ፕሮጀክት መጓተት ያሉባቸውን የአቅም ችግርም አይክዱም። ድርጅታቸው ትልቅ ግድብ ግንባታ ላይ ሲሳተፍ ይህ የአርጆ ዴዴሳው የመጀመርያው መሆኑን የሚናገሩት ባለሞያው  ከኮንትራክተሩ አቅም ውስንነት አንሰቶ እስከ ዲዛይን ማሻሻያ ያሉ ችግሮች እንደነበሩና ልምድ መወሰዱንና የነበሩትን ችግሮች በመለየት የተንዛዛ አሰራሮችንና ወደ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚሄዱትንም ችግሮች ከባለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ግን እዛው ግድቡ በሚገኝበት ስፍራ መፍታት ጀምረናል ይላሉ። ይህንንም በምሳሌ ሲያነሱ “ከዞን ወደ ዞን ከወረዳ ወደ ወረዳ፣ ከወረዳ ወደ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በመዞር ችግሮችን ለመፍታት የሄድንበት አሰራርን አሁን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እዚሁ ባለሞያ መድቦልን እየሰራን ከካሳ ክፍያና ከመልሶ ማስፈር ጋር ያሉ ጉዳዮችን መፍታት ጀምረናል” ብለዋል። አክለውም ከአሁን በፊት በነበረው አሰራር  ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የካሳ ክፍያ ለወረዳዎችና ከዚያም ለተነሺዎች ከፈፀመ በኋላ ኮንትራክተሩ quarry ማቴርያል አውጥቶ ለግንባታው ጥቅም ላይ እንደሚያውል አውስተው አሁን ግን የካሳ ክፍያን በኮንትራክተሩ በኩል ለወረዳዎች በአፋጣኝ ገቢ ማድረግ መጀመራቸውንና በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በኩል የተመደበው ባለሞያ ፕሮሰሱን ጨርሶ ወደ ወረዳው እንዲልክ ወረዳውም ለኮንትራክተሩ በአካውንቱ ገቢ እንደሚያደርግና ይህንንም በደብዳቤ በመፃፍና በማሳወቅ እንደሚፈፀም አብራርተዋል።

ስለሆነም ይላሉ ከካሳ ክፍያና ከዲዛይን ጋር የተያያዙ ችግሮችን ሙሉ በሙሉ የተፈቱና ወይም ለመፍታት የተቃረቡ ስለሆነ የኮንትራክተሩ ሌላኛውን የአቅም ማነስ ችግር በተለይ ከማሽንና ከባለሞያዎች ልምድ ማነስ ጋር ያለውንም በመፍታት ድርጅታቸው 24 ሰዓት ሙሉ በመጠቀም ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ በዘንድሮ ዓመት ስራውን እንደሚያጠናቅቅ ገልፀዋል።

ማጠቃለያ

ማንኛውም ልማት በህብረተሰብ ላይ የራሱ አዎንታዊና አሉታዊ ተጽእኖ ሊኖረው ይችላል። የህብረተሰብ የልማት ፕሮጀክቶች የአካባቢና የማህበረሰብ ተፅእኖ ግምገማዎችን ለማለፍ የሚገደዱትም ከዚሁ አኳያ ነው። የአርጆ ዴዴሳ ግድብና መስኖ ልማት ፕሮጀክትም ይህንኑ አግባብ ሂደት አልፎ እንደመጣና አስፈላጊውን የዲዛይን መመዘኛዎች ማሟላቱን የተለያዩ ሰነዶች ያሣያሉ። ስለሆነም የፕሮጀክቱ መጓተት ያሉ መልካም የሚባሉ ነገሮችን እንዳናነሳ የሚያደርጉ አይሆንም። ከዚህ አንፃር ካየነው የመስኖ ልማት ፕሮጀክቱ ከፍተኛ የሆነ የስራ እድል ለአካባቢው ነዋሪ መፍጠሩ፣ ለግንባታው ግብዓት የሚውል ሼል በሚመረትበት አካባቢ ከፍተኛ የድማሚት ፍንዳታ በህብረተሰቡ ላይ አደጋ በመደቀኑ ቅድሚያ ለሰዎች ደህንነት በሚለው መርህ ለተወሰነ ጊዜ ስራ እንዲቋረጥ መደረጉና፣ በአካባቢው ህብረተሰብ ዘንድ ያለው የተፋሳስ እንክብካቤ ግንዛቤ ከፍተኛ መሆኑ የፕሮጀክቱ አዎንታዊ የሚባሉ ገጽታዎች ናቸው። በፕሮጀክቱ ግንባታ አጠቃላይ ወደ 3380 ሠራተኞች ይገኛሉ። ከዚህ ቁጥር ውስጥ 341 የሚደርሱት ብቻ የተቋራጩ የኦሮሚያ ውሃ ስራዎችና ኮንስትራክሽን እንዲሁም የአማካሪው የኦሮሚያ ውሃ ዲዛይንና ቁጥጥር ድርጅት ሠራተኞች ሲሆኑ የተቀሩት ሙሉ በሙሉ በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎች ናቸው። በጾታ ስብጥርና በሴቶች ተሳትፎም ረገድ ከሆነ ፕሮጀክቱ የራሱ በጎ ገፅታዎቸ እንዳሉት እንረዳለን። ወደ 229 የሚጠጉ ሴቶች በፕሮጀክቱ ግንባታ ላይ አሻራቸውን እያሳረፉ ሲሆን ከዚህ 5 ብቻ የሚሆኑት በተቋራጩና በአማካሪው ድርጅት በኩል ከዋናው መስሪያ ቤት መምጣታቸውንና የኢንጂነሪንግና የፅህፈት ባለሞያዎች መሆናቸውን ተረድተናል። ሌሎች የተቀሩት ግን በአካባቢው የሚኖሩ የስራ እድል የተፈጠረላቸው ዜጎች ናቸው።  

የአርጆ ዴዴሳ ግድብ 1.9 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ የመያዝ አቅም አለው ። ለመስኖ ጥቅም ላይ ሊውል የተዘጋጀው (LIVE STORAGE) ወደ አንድ ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ ሲሆን 900 ሚሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃ (DEAD STORAGE) ጥቅም ላይ የማይውል ይሆናል።የግድቡ አካባቢ የሚባለው ወይም ግድቡ ተሰርቶ ከተጠናቀቀ በኋላ የሚሸፍነው መሬት ወደ 11,55 ወይም 11,505 ሄክታር ነው። የግድቡ የቀድሞው ዲዛይን 47 ሜትር ከፍታ የነበረው ሲሆን በኋላ ግን በዲዛይን ክለሳ ወደ 50 ሜትር ከፍ እንዲል ተደርጓል። የጎን ርዝማኔውም በላይኛው በኩል 502.47 ሜትር በታችኛው በኩል 561.69 ሜትር ይረዝማል።

የመስኖ ልማት ፕሮጀከቱ አጠቃላይ የግንባታ ወጪ በፊት በነበረው ዲዛይን 700 ሚሊዮን ብር እንደሚፈጅ የተገለፀ ቢሆንም የዲዛይን ክለሳና የተለያዩ ማሻሻያዎች በመደረጋቸው ወጪው ወደ 2.8 ቢሊዮን አሻቅቧል። ሌላው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኮንትራክተሩን አቅም ባለገናዘበ መልኩ እነዚህን ሁሉ ስራዎች ለአንድ ኮንትራክተር መስጠቱ  ለፕሮጀክቱ መጓተት ትልቁን አስተዋፅኦ አበርክቷል። ከማህበራዊ ጉዳዮች ጋር መሰራት የነበረባቸው ያልተሰሩ ስራዎች ነበሩ። እነሱም ፕሮጀክቱ ሲጠና የአካባቢው የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ይዞታ በበቂ ያለማጥናተ ሁኔታም ታይቷል የሚል ግምት አለኝ። ይህ ብቻ ሳይሆን የህብረተሰቡን ጥያቄ ማዕከል ያደረጉ ስራዎች እስከ 2007 ዓ.ም ድረስ ትኩረት አልተሰጠውም ወይም ትኩረት ተሰጥቶት አልተሰራም። በዚህ ምክንያት ጊዚያዊ ግድብ ተብሎ የተገነባው (cooferr dam) ግድብ ውሃው ሞልቶ የጎርፍ መጥለቅለቅ የፈጠረበትና ሰዎች እንዲፈናቀሉ ምክንያት የሆነበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ከዚህ ሁሉ የምንማረው ቁምነገር ፕሮጀክቶች ሲጠኑ የአካባቢውን የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ይዞታ በበቂ ሁኔታ ማጥናት ግድ እንደሚል፣ የህዘብ ጥያቄዎች ግንባታ ከመገባቱ በፊት ምላሽ ማግኘታቻውን ማረጋገጥ እንደሚገባና በመረጃ ላይ የተመሰረተ በልማቱ ተጠቃሚ ሊሆኑ መቻላቸውን በሚያረጋግጥ መልኩ የማሰመን ስራ መሰራት እንዳለበት ነው። ስለሆነም የፕሮጀክቱን ግንባታ ለማፈጠን እንዲሁም የሚፈለገውን 80 ሺ ሄክታር መሬት (በነገራችን ላይ በአቅራቢያው ያለው የአርጆ ስኳር ፋብሪካ በአሁኑ ሰዓት 4 ሺህ ሄክታር ብቻ ነው የሚያለማው የወንዙን ውሃ በፓምፕ በመሳብና ዝናብን በመጠበቅ) በማልማት ህዝብንና ሀገርን መጥቀም እንዲቻል የግድቡ ግንባታ መፋጠን እንዳለበት በመጠቆም የሚመለከታቸው ወገኖችም ያላሰለሰ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባቸው ማሳሰብ ያስፈልጋል።  

ሀገሪቱ ብዙ ቢሊዮን ብሮችን ብዙ የስኳር ፕሮጀክቶች ላይ እያዋለች ነው። የአርጆ ዴዴሳን ፕሮጀክት ጨምሮ በርካታ ፕሮጀክቶች በዋል ፈሰስ ሆነዋል። የታለመላቸውን ግብ የመቱም አይመስልም። በተመሳሳይ ሁኔታ ከሰም ተንዳሆን መጥቀስ ይቻላል። እነዚሁ ፕሮጀክቶች 10 አስር ዓመት አስቆጥረዋል። ይሁንና ምርት እየሰጠ ያለው የትኛው ነው ብለን ብንጠይቅ በቁጥር ውስን የሆኑ ናቸው። ይሁንና ብዛታቸውን ካየን በጣም በርከት ያሉ ናቸው። አርጆ ዴዴሳ በቀላሉ ሊጠናቀቅ የሚችል ፕሮጀክት ነው። ፕሮጀክቱ ክትትል ተደርጎበትና ቢጠናቀቅ ኖሮ ራሱ የወጣበትን የፋይናንስ ወጪ መመለስ (financial investment return) የሚችልና ሌሎቹንም ፕሮጀክቶች መስራት የሚያስችል  ነበር። የስኳር ፕሮጀክቶችም ሆኑ ሌሎች ፕሮጀክቶች በ10 ዓመት ጊዜ ውስጥ ምን ያህል የወጣባቸውን ወጪ መልሰው የሀገሪቷን ኢኮኖሚ እየደገፉ ነው የሚለውን ነገር ማየት አስፈላጊ ይመስለኛል። ስለዚህ አሁን ካለንበት ልንማር ይገባናል ነው መልዕክቴ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
512 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 187 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us