ሚዲያ - ብሩህና ደፋር መሪዎችን ለመፍጠር

Wednesday, 01 March 2017 12:36

 

 

በስሜነህ

የተከበረው፣ አለም አቀፉ አባይ ወንዝ፤ ባለቤት (ባለአንበሳ ድርሻዎቹ) የሆንነው ኢትዮጵያዊያን ከከፋ ድህነት እንላቀቅ ዘንድ ከሚያስችሉን የተፈጥሮ (ፀጋ) ሀብቶች መካከል አንዱና እጅግም ግዝፉ ሃብታችን ነው። ይህንን ግዙፍ (ከጂኦ/ሀይድሮ ፖለቲክስ እና እኮኖሚ አንፃር ያለውን ሁለንተናዊ ፋይዳ/ንጥርቂያ ትተን) እና ድንበር ተሻጋሪ ተፈጥሯዊ ሃብት ይዘን (ይገርማል!!!)፤ ግን ደግሞ፣ ለዘመናት ከከፋ ድህነት ጋር ተቆራኝተን፤ ሀብታችንን አሳልፈን ስንሰጥ ኖረናል። ይህ (የራስን ሀብት ለባዳ አሳልፎ የመስጠቱና “አባይ . . . “ በማለት በዜማ/ዘፈን የመፀፀቱ ጉዳይ) ደግሞ - የእስከዛሬውን (ስንክሳር) እርግፍ አድርገን ትተን፣ ከድህነት በላይ የከፋ ጠላት የለንም (በአሁኑ የህዳሴ/Renaissance ዘመን ማለት ነው) እያልን ላለለውና ችግሩንም ከእነአካቴው ለማሰወገድ ሌት-ተቀን ለምንማስነው የአሁኑ ዘመን ኢትዮጵያውያን የአብን ፀጋ (ከዚህ፣ ከእስከዛሬው በላይ) አሳልፎ መስጠት፣ ከነውርም በላይ ነውር ብቻ ሳይሆን ለሚቀጥለው ትውልድ የተሻለ መደላድልን ከመፍጠር አንፃር ሲመዘን ሀላፊነቱ ከባድና ለነገ የማይባል ጉዳይ ነው። ድህነትን ድል/ተረት ለማድረግ አባይን ከመሰለ የተፈጥሮ ሃብት በላይ ምንም ሊመጣልን አይችልምና ውሳኔያችን (የኛ የኢትዮጵያዊያን) ፍፁም ትክክል ነው።


የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በነበሩበት የስልጣን ዘመን “የግብጽና የኢትዮጵያ ግንኙነት ለፍቺ የማይመች ጠንካራ ጋብቻ (የደም) ነው” ማለታቸው ሁለታችንም የማንጠማበት እና እኩል ያልተጠቀምንበት የአድልኦ ዘመን ስለነበረ ነው። የአሁኑ የግብጽ ፕሬዚዳንት አል ሲሲም “ፈጣሪ አንድ ውኃ እንድንጠጣ ስላደረገን ያለን አማራጭ ተሳስቦ መኖር ነው።” ሲሉ በስልጣን ማሟሻቸው ወቅት የተናገሩትም (ከልባቸው ከሆነ) ከላይ ስለተመለከተው እውነታ ነው። እነዚህን አባባሎች ወደ መሬት ማውረድ ደግሞ የሁለቱም ሃገራት የጋራ ኃላፊነት ይሆናል፤ በተለይም፣ የሁለቱ ሃገራት ሚዲያ ጋዜጠኞችና ኮሚዩኒኬሽን ባለሞያዎች።


ከቀደሙት የግብጽ አመራሮች እና የሚዲያ ልሂቃን የተገነዘብነው ነገር ቢኖር ለፍትሃዊ የውሃ ሀብት ክፍፍል ጆሮ አለመስጠትን ነው። ኢትዮጵያ አባይን ገድባ የግብጽን ህዝብ ለረሃብና ለስደት ልትዳርግ እየጣረች ነው በማለት ሕዝቡን ሲያደናግሩት ለዘመናት መክረማቸው የናይል ታሪክን ለሚያውቅ ሁሉ ሀ ሁ ነው። ኢትዮጵያ የአባይን ውኃ መጠቀም እንዳትችል ለማድረግም ሲከተሏቸው ከነበሩት የተለያዩ ዘዴዎች መካከል ኢትዮጵያን ሰላም ማሳጣት የሚለው ዋነኛው ስለመሆኑም የናይል ተመራማሪዎች ድርሳናት በስፋት ያወጋሉ።


ከተለያዩ አገራት እነሱ ዘንድ ለሚሄዱ ጎብኚዎች እና ጋዜጠኞች ልሂቃኖቻቸውም ሆኑ ባለስልጣናቶቻቸው የሚሰጡት አታካች ገለፃ በእጅጉ የተዛባ ነው። በአንድ ወቅት በአስዋን ግድብ ጉብኝት ላደረጉ የጋዜጠኞች ቡድን አስጎብኚ የነበሩት የአስዋን መስተዳድር ቃል አቀባይ “ይህ የምታዩት የአስዋን ግድብ ይባላል። ይህ ግድብ በተሰራ በዓመቱ የተገነባበትን ወጪ መሸፈን የቻለ ግድብ ነው፤ አሁን በኢትዮጵያ እየተገነባ ያለው የህዳሴው ግድብ የዚህን አራት እጥፍ ይሆናል። ይህ ግድብ ሲጠናቀቅ ደግሞ ሃገረ-ግብጽ ሙሉ በሙሉ ድርቅ ትሆናለች።” ማለታቸው ከላይ ለተመለከተው አመክንዮ በማሳያነት ሊጠቀስ የሚችል ነው። በወቅቱ በጉብኝት ላይ የነበሩት ከአፍሪካ አገራት የተውጣጡ ጋዜጠኞች የተሳሳተ ሃሳብ ይዘው እንዳይሄዱ ለማድረግ፤ ከኢትዮጵያ በሄዱ ጋዜጠኞች አማካኝነት፣ የተገለፀው ነገር ስህተት መሆኑንና በኢትዮጵያ እየተገነባ ያለው ግድብ የግብጽን ህዝብ የሚጠቅም እንጂ የሚጎዳ አለመሆኑን፤ መጠኑንም አስመልክቶ የቀረበው የተዛባ መሆኑን ማስረዳት የቻሉበት እድል የነበረ ቢሆንም፤ በተለያዩ ጊዜያት ወደስፍራው ለሚሄድ ጎብኚ አካል እንደዚህ ዓይነት የተዛባ ሃሳብ ሊቀርብለት እንደሚችል መገመት አይከብድም።


የኢትዮጵያ መንግሥትና ህዝብ ይህ እምነት የተሳሰተ እንደሆነ ያውቃሉ። ጠንካራ ኢኮኖሚ በተፈጠረ ቁጥር በአገራት መካከል የሚኖረው ትብብር፣ መተሳሰብና መደጋገፍ እያደገ እንደሚሄድ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ እራሳቸው ግብፆችም አሳምረው ያውቃሉ። ችግሩ ያለው ግን ይህን እውቀት የሚያሰርጽ እና የተዛቡ ገለጻቸዎችን በእውቀት እና በመረጃ አስደግፎ የሚገልጥ ሚዲያና የሚዲያ ባለሙያ ባለመኖሩ ነው የሚለው ሚዛን እየደፋ የሚገኝ መከራከሪያ እየሆነ መጥቷል።


በዓባይ ተፋሰስ አገሮች መካከል ውይይት መፍጠርና ይህም የሐሳብ ልውውጥ እንደ የግሉ የንግድ ዘርፍ፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ሲቪል ማኅበራት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ሚዲያ እና የመሳሰሉት ባለድርሻ አካላትን እንዲያካትት ማድረግ የ(ኤን ቤ አይ) የናይል ቤዚን ኢንሺየቲቭ የስራ ድርሻ ነው።


ግብፅ እ.ኤ.አ. ከሰኔ ወር 2010 ጀምሮ በኤን ቢ አይ (ኢንሳፕ) ያላትን ተሳትፎ ያቋረጠች ቢሆንም ኢንሳፕ የተመሰረተው ግብፅ፣ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳንና ሱዳንን ይዞ ነው። ግብጽ ከፕሮግራሙ በይፋ ማቋረጧ ቢታወቅም ኤን ቢ አይ በሚያዘጋጃቸው የተለያዩ እንቅስቃሴዎች መሳተፏን ግን አለማቋረጧ ይታወቃል፤ በየመድረኮቹም ታይቷል። ለአብነትም የናይል የሚኒስትሮች ስብሰባና በዓመት ሁለት ጊዜ በሚካሄደው የናይል ዴቨሎፕመንት ፎረም ያላትን ተሳትፎ መጥቀስ ይቻላል።


የእነዚህ አራት ሃገሮች የሕዝብ ብዛት በአጠቃላይ ከተፋሰሱ 11 አገሮች የሕዝብ ብዛት ጋር ሲነፃፀር 50 በመቶን የሚይዝ በመሆኑ የሚያንሰራራ አካባቢያዊ ገበያ መፍጠር ይችላሉ። እነዚህ ሃገሮች በታሪክ፣ በባህልና በኃይድሮሎጂም የተቆራኙ ናቸው። በአካባቢው ከውኃ ሀብት ኃይል የማመንጨት ከፍተኛ አቅም ያለ በመሆኑም በኃይል (ሀይድ-ሮፓወር) ንግድ መተሳሰር የሚችሉባቸው እድሎችን ማስፋት ይችላሉ። የግብርና ምርትን የማሳደግ አቅምም እንዲሁ። ውኃን በተሻለ ሁኔታ በመጠቀምም ምርታማነትን ማሳደግ ይቻላል።


ያም ሆኖ ግን ከላይ በተመለከተው አግባብ አካባቢው የሰፉ ተስፋዎች እንዳሉት ሁሉ የራሱ ተግዳሮቶችም አሉት። የውኃ አቅርቦት ከቦታ ቦታና ከጊዜ ጊዜ የተለያየ መሆኑ የመጀመሪያው ነው። 86 በመቶ የሚሆነው የናይል ውኃ ከኢትዮጵያ ከፍታማ ቦታዎች የሚመነጨው በዓመት ውስጥ በአራት ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ ነው። ይህ ንዑስ ተፋሰስ ከተራዘመ በድርቅና ከፍተኛ ጎርፍ ትልቅ ጉዳት ይደርስበታል። ይህ ሁኔታ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ይበልጥ ተወሳስቧል። በአካባቢው በትነት ሳቢያ ከፍተኛ የሆነ የውኃ እጦት ይከሰታል። በዚህ ንዑስ ተፋሰስ ነው የናይል ውኃ የሰሃራ በረሃን የሚቀላቀለው። ኢንሳፕ ደግሞ ይህ እንዳይሆን የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን ፖሊሲ ቀረፃ ይደግፋል። የባለድርሻዎችን ተሳትፎ ለማጠናከር የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን ከመስጠት ጀምሮ ወደ ጋራ ትብብርና ተጠቃሚኒት የሚወስዱ መድረኮችን ያመቻቻል።


ከነዚህ መድረኮች ባሻገር ግን የናይል ትብብርን ለማጠናከር እና የጋራ ፍላጎቶችን ለማሳደግ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ሚና የሚኖረው የመገናኛ ብዙሀኑ ዘርፍ ነው። ናይል የፖለቲካ ድንበሮችን አያውቅም። የፖለቲካ ድንበሮችን የማያውቀው ናይልን ታዲያ እንዴት መጠቀም ይቻላል? የሚለውን ሳይንሳዊ ጥያቄና ትንታኔውን መስራትና የየሃገራቱን ህዝቦች ግንዛቤ ማሳደግ የሚዲያው አቢይና የእለት ተለት ስራ ነው። አንድ ቦታ ላይ የሚፈጸም ነገር የላይኛውን ወይም የታችኛውን ተፋሰስ አገሮችን እንዴት ይነካል? የሚሉትን ጥያቄዎች መመለስ ከፖለቲከኞቹም በላይ ሚዲያው ያገባዋል። በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የሚደረግ ምክክር፣ ዕቅድና ድርድር በጠንካራ፣ ብቃት ያለውና ታማኝ የመገናኛ ዘዴ መታገዝ ሲኖርበት ለፖለቲከኞቹ ከተተወ የተጣመሙት መረጃዎች በየሃገራቱ ህዝቦች መካከል አለመተማመን እንዲነግስ እድሉን ይፈጥራል። ስለጋራ ልማትና ተጠቃሚነት የሕዝብን አስተያየትና አመለካከት በመቅረፅ፣ እንዲሁም ሕዝቡ ለአንድ ለተወሰነ አጀንዳ ድጋፍ እንዲሰጥ ወይም እንዲቃወም ለማንቀሳቀስ ቁልፍ ሚና መጫወት ያለበት እና የሚችለው ሚዲያው (ፖለቲከኞችንና ሌሎችንም ይዞ) እንጂ ሌላ ማንም እንዳልሆነ በብዙ አግባቦች ተረጋግጧል። ለዚህ ደግሞ ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ በኋላ የሆነውን እና እየሆነ ያለውን መመልከቱ ብቻ በቂ አስረጅ ነው ።


የሚዲያው የአሰራር ባህል ገና በማደግና በመውጣት ላይ ያለ መሆኑ ፖለቲከኞቹ እንዳሻቸው እንዲዘላብዱ እና ከህዝብ ጠቀሜታ ባሻገር ናይልን እንዲቆምሩበት ካስቻሉ ምክንያቶች አንዱ እንደሆነ በዘርፉ ላይ ምርምር ያደረጉ ተቋማት አየገለጹ ነው። ጋዜጠኛው ናይልን የተመለከቱ ሳይንሳዊና እውነታን የተመለከቱ ዘገባዎችን ሲሠራ በአብዛኛው ቅድመ-ታሪክና ምርምር አያደርግም። ስለዚህ ብዙ ጊዜ በርካታ የእውነታ መፋለሶች ይታያሉ። የማረም አጋጣሚ ቢኖርም የተሳሳቱ ምልከታዎች ግን አይታረሙም። ስለሆነም ሚዲያው የማስተማር ሚናውን በአግባቡ እየተወጣ ነው ማለትም አይቻልም።


ስለናይል ወንዝ የሚጻፉ እና አየር ላይ የሚውሉ ዘገባዎችን ስንመለከት በአብዛኛው በአንድ አዝማሚያ ላይ ተጣብቀው እናገኛቸዋለን። ዓለም አቀፍ ሚዲያው ወደ ናይል ፊቱን የሚያዞረው የግጭት ጽሑፍ ለማቅረብ ብቻ ነው። እኒህ ደግሞ እጅግ ትልቅ የሆነ አውዳሚ አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው። ለ11 አገሮች የሕይወት መሠረት የሆነን ታላቅ ወንዝ ስሜት ቀስቃሽ አድርጎ ብቻ በማቅረብ የሃገራቱን ህዝብ የአባይን ልጅ ውሃ ደእንጠማው እድሜውን እንዲገፋ እየፈረዱበት ነው። ሚዲያ የአንድን ጉዳይ አሉታዊ ገጽታ ብቻ በመጻፍና ጠባብ አቅጣጫ በመከተል፣ ልዩነት ላይ ብቻ አተኩሮ፣ ስለማይቻለውና ቅሬታ ስለቀረበበት ጉዳይ ብቻ ሁሌም በመጻፍ ጎጂ ጎንን ማባባስ እንደሚችል ከግብጹ አልአሃራም በላይ አስረጅ መጥቀስ አስፈላጊ አይሆንም። በዚህ ጊዜ የኛዎቹ ይልቁንም ስለጋራ ልማትና ጥቅም የማያወላውል አቋም ያላቸው ሃገራት ሚዲያዎች ለእነዚህ አይነቶቹ ሚዲያዎች መልስ በመስጠት ስራ ከመፍታት እና ከመዘናጋት የተለያዩ አካላት ያላቸውን የጋራ ስሜት በማውጣት የማቀራረብ ሚና መጫወት ግድ የሚላቸውና ጊዜው ያላለፈ ግን ደግሞ ባመለጣቸውም ለቆጩበት የሚገባ የቤት ስራቸው ነው ።


የኤን ቤ ኢን ቀጠና ጽህፈት ቤትም ይህንኑ ጉዳይ በምሳሌ ሲያስረዳ፦
ሚዲያው አንድ አማካይ ግብፃዊ ዜጋ ራሱን በአንድ አማካይ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በመተካት ዝናብ ላይ ጥገኛ የሆነ ግብርና እንዴት እንደሚከናወን ማሳየት ይችላል። በዚህም በኢትዮጵያ ከፍታማ ቦታዎች የሚኖረው ገበሬ ሕይወት ምን እንደሚመስልና ለሕይወቱ የሚያሠጉ በርካታ አደጋዎችን እንዴት በየቀኑ እንደሚጋፈጥ ግንዛቤ መፍጠር ይችላል። በርካታ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የኢትዮጵያ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አገሪቱ በምታገኘው ዝናብ ጥሩነት ላይ የተመረኮዘ ነው። ስለዚህ የግብፅ የሚዲያ ባለሙያዎች ኢትዮጵያዊ ገበሬ ወይም አማካይ ዜጋ ምን እንደሚመስል፣ ምን ዓይነት የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት አቅርቦት እንደሚያገኝ፣ የሚያገኘው ንፁህ የመጠጥ ውኃ ምን ያህል እንደሆነ ለአንባቢዎቻቸው ማሳየት አለባቸው። በማለት ነው። የጉዳዩን ልዩ ልዩ ገጽታዎች ሚዛናዊና ፍትሐዊ በሆነ አስተማማኝ እውነት፣ ቁጥሮችና ማስረጃዎች በማቅረብ ማሳየት ኃላፊነት የሚሰማው የሚዲያ ተቋምና ባለሙያ ግዴታ ነው።


የአባይ ልጅ ሆነው ውሃ የተጠሙ ሃገራት በሙሉ ጥረቶቻቸውን ማቀናጀትና ዕቅዶቻቸውን በአመክንዮ መምራት እንዲችሉ ከየሃገራቱ ሚዲያዎች በላይ ምእራባውያኑ በባለቤትነት ይሰሩታል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ይሆናል።


የኤን ቤ ኢን የምስራቅ ቀጠና ጽ/ቤት ይህንንም በምሳሌ እንዲህ በማስረዳት የየሃገራቱ ሚዲያዎች የቤት ስራ ጠንካራ መሆኑን እንደሚከተለው ይገልጣል።


በላይኛው ተፋሰስ አገሮች ከፍታማና ቀዝቃዛ ቦታዎች የውኃ ማከማቻ መሠረተ ልማት በመገንባት የውኃ ትነትን በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነስ ውኃ ማትረፍ ይቻላል። ነገር ግን የታችኛው ተፋሰስ አገሮች ውኃቸው ከግዛታቸው ውጪ በመቀመጡ ከሥነ ልቦና አንፃር ላይረጋጉ ይችላሉ። ይህን ለመፈጸም ፍጹም የሆነ መተማመንና እምነት መፍጠር አለብህ። ሚዲያው ኩነቶችንና ክስተቶችን በመዘገብ ራሱን ሳያጥር እንዲህ ዓይነት መረጃዎችንና ሳይንሳዊ ግኝቶችን ፈልቅቆ በማውጣት ለኅብረተሰቡ እንዲደርስ በማድረግ አገልግሎት ሊሰጥ ይገባል። ምን እንደሚቻል ፖሊሲ አውጪዎችን ጨምሮ ለሕዝቡ በማስተማር ላይ ትኩረት የሚያደርግ ልማታዊ ኮሙዩኒኬሽን የተባለ ራሱን የቻለ ዘርፍ አለ። ኅብረተሰቡ ውኃን እንዴት በአግባቡ መጠቀም እንደሚቻልና በግብርና ንግድ ውኃን እንዴት ማትረፍ እንደሚችል ሚዲያው በአግባቡ ቢያስተምረው፣ መሪዎችም ድፍረት የተሞላበትና አዳዲስ ውሳኔዎችን ለመውሰድ ይበረታቱ ነበር። ትክክለኛ መረጃ በመስጠት፣ የሕዝቡን አመለካከት በመቅረፅና በማንቀሳቀስ ብሩህና ደፋር መሪዎችን ለመፍጠርም ቁልፍ ሚና ሊጫወት ይችላል። በየትኛው የኢኮኖሚ ዘርፍ የተፋሰሱ አገሮች ከሌላኛው የተሻለ ተፈጥሯዊ የሆነ አንፃራዊ ተጠቃሚነት እንዳላቸው በማሳየት የጋራ ተጠቃሚነታቸውን ማጉላትም ይችላል። ሚዲያ በናይል ባለድርሻ አካላት መካከል ግንኙነት እንዲኖር ድልድይ ሆኖም ሊያገለግል ይችላል።


የናይል ጉዳይ ከመጠን ያለፈ የፖለቲካ አጀንዳ እንዲሆን አንዱ አስተዋጽኦ ያደረገው ራሱ ሚዲያው ነው። ለምሳሌ ሚዲያው ‘የውኃ ደኅንነት’ የሚል አባባል ይጠቀማል። ይህንን ማንም አይረዳውም። የውኃ ደኅንነቱ የተጠበቀ አገር ሲባል ምን ማለት ነው? ምን ያህል ውኃ ነው የአንድን አገር የውኃ ደኅንነት የሚያረጋግጠው? ከናይል አገሮች የየትኛው የውኃ ደኅንነት ነው የተሻለ የተረጋገጠው? ይኼ ጽንሰ ሐሳብ ሕጋዊ፣ ፖለቲካዊ ወይስ ኢኮኖሚያዊ ነው? ከየት ነው የመነጨው? ሚዲያው እነዚህንና እነዚህን የመሳሰሉ መሰረታዊ ሀሳቦች ከመጠቀሙ በፊት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አንድምታቸውን ጠንቅቆ ሊረዳው ይገባል። በዚህ አግባብ የሚተጋ ሚዲያ በተፋሰስ ሃገራቱ ግድብ መገንባት ከተቻለ በተፋሰስ ሃገራቱ መካከል ሲንከባለሉና እየሰፉ በመሄድ ከዚህ ለደረሱ ልዩነቶች መቋጫ መስጠት የሚችሉ ብሩህ እና ደፋር መሪዎችም አብረው ሊፈጠሩ የሚችሉ እንደሆነ አያጠራጥርም።


ባጠቃላይ፣ ሚዲያው ለአጠቃላይ ህብረተሰቡ፣ ተበደልን ለሚሉ እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ስለአባይና ታላቁ የህዳሴ ግድባችን ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃዎችን በመስጠት፤ እግረ-መንገዱንም የተሻሉ መሪዎችን በመፍጠር ጉልህ ድርሻውን ሊወጣ ይገባል።¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
507 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 260 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us