ኮሎራዶ፣ ኤፍራጠስና የአባይ ወንዞች ምንና ምን ናቸው?

Wednesday, 15 March 2017 12:27

 

ግዝሽ

አቤት መመሳሰል!!››

ኮሎራዶ፣ ኤፍራተስ፣ እና አባይ

 

 

ይህ ፅሁፍ ‹‹አቤት መመሳሰል!›› በሚል መገረም የጀመረበት የራሱ ምክንያት አለው፡ እነዚህን ሶስት ወንዞች በሚመለከት በተለይ ደግሞ ሁለቱ (ኮሎራዶና ኤፍራተስ)  ሲገደቡ (ሲገነቡ) በርካታ አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንደነበሩና ሁሉንም አስቸጋሪ ሁኔታዎች በማለፍ ለውጤት የተበቃበት ሂደት ቀላል እንዳልነበር ለማመላከት እና ለማነፃፀር በማሰብ ሲሆን እኛም ብንሆን የአባይን ወንዝ ለመገደብ በነበረን ተስፋ ሁሌም እንዳጓጓን ዘልቀን በርካታ ውጣ ውረዶችና ችግሮች ታልፈው መገደብ መጀመራችንና በግንባታው ሂደትም ቢሆን የተከሰቱት ጉዳዮች ከሁለቱ ጋር የሚያመሳስላቸው በመሆኑ በዝርዝር ማቅረብ ዋናው የርእሰ ጉዳያችን ትኩረት ነው። በዚህ ረገድ የሶስቱም ወንዞች የግድብ ግንባታ ሂደት በዝርዝር ሲታይ ባለው መመሳሰል አንዳቸውን ከአንዳቸው መለየት እንደሚያስቸግርና ሲነፃፀርም የጊዜ ልዩነት ካልሆነ በስተቀር በእርግጥም ‹‹አቤት መመሳሰል!›› የሚያስብል በመሆኑ ትምህርት የምናገኝበት እንደሚሆን ነው። እነዚህን ሶስት ወንዞች በሚመለከት የተለያዩ መረጃዎች፣ ጥናታዊ ፊልሞችና የምርምር ጽሑፎች የገለፁትና ያስነበቡት ቁም ነገር በራሱ ለዚህ ጽሁፍ መነሻና ግብዓት በመሆኑ ለማካተት ተሞክሯል። ሶስቱን ወንዞች የሚያመሳስላቸው ዋናው ጉዳይ በብዙ መልኩ በተፈጥሮ  ገፀ-በረከትነታቸው ያላቸው ሕዝባዊ ጥቅም የላቀ መሆኑ ነው።

በአሜሪካ የኮሎራዶ ወንዝን፣ በቱርክ የኤፍራተስ ወንዝን ለመገንባት ገና ከመጀመሪያው ሲታሰብ የነበረው መነሳሳትና የየመንግሥታቱ መሪዎችናሕዝቦች ያደረጉት ጥረት፣ የወሰዱት ኃላፊነት እና ለፍፃሜ በማድረስ ረገድ የተደረገው ርብርብ ለተገኘው ውጤት የላቀ ድርሻ ነበረው። እኛም የአነዚህን አገራት ጥረትና ውጤት ተንተርሰን ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እንደጅምሩ ከፍፃሜ በማድረስ በኩል ከፍተኛ ኃይልና ጉልበት የሚፈጥርልን በመሆኑ በዚህ ርእስ ጉዳይ በሃሳብ ወደ አሜሪካና ቱርክ እንጓዛለን። በቆይታችን ኮሎራዶንና ኤፍራተስን ከአባይ ወንዝ የግድብ ግንባታ  ሂደት ጋር እያነፃፀርን በርካታ ጉዳዮችን እንዳስሳለን። በዚህ የጉዞ ቅኝት በቅድሚያ ወደ አሜሪካ ተጉዘን በኔቫዳ በረሃ ዘልቀን በሽቅርቅሯ ከተማ ላስቬጋስ ተዝናንተን በአሪዞና እና በኔቫዳ ግዛቶች ውስጥ የሚገኘውንና በኮሎራዳ ወንዝ ላይ የተገነባውን የኹቨር ግድብ  እንቃኛለን። የዚህ ግድብ ፍጻሜን በተመለከተም ያኔ በዘመኑ ከነበረው እድገት አንፃር አሜሪካውያኑ የነበራቸውን ቁርጠኝነትና ጥረት እያደነቅን ግድቡ ፍፃሜ እንዲያገኝ የነበራቸውን ጉጉት በዝርዝር እንናሳለን። በወቅቱ የነበሩት ፕሬዚዳንትና የየግዛቱ ነዋሪዎች የኮሎራዶ ወንዝ ያደርስ የነበረውን ጉዳትና ጥፋት በመታደግ ጥቅም ላይ እንዲውል የወሰዱት እርምጃና አማራጭ፣ የተጓዙበት መንገድና የግንባታው ሂደት ብዙ ውጣ ውረድ እንደነበረው በዚህ ጽሁፍ ተካትቷል። ወዲህ ደግሞ በቱርክ በኤፍራተስ ወንዝ ላይ በከማል አታቱርክ ስም የተሰየመውን የአታቱርክን ግድብ ለመገንባት ሲነሱ ከአካባቢው ጎረቤት አገራት ጋር  የተፈጠረው ውዝግብና ለኢራቅ ተፅዕኖና እና ጫና ሳይንበረከኩ ለውጤት እንዴት እንደበቁ እናያለን።

የእነዚሀን አገራት ጥረትና ውጤታማነት ከእኛ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት ጋር እያነፃፃርን እስከአሁን የተጓዝንበትን መንገድና ያጋጠመንን ተግዳሮት እያነሳን ከማስገረም ባለፈ በእውነታው ዙሪያ ይህ ጽሁፍ በርካታ ጉዳዮችን ያነሳል። በዚህ ጉዳይ በተለይም የአሜሪካንን የሁቨር ግድብ እና የቱርክ አታቱርክ ግድብ በሚመለከት በተለያየ ጊዜ በርካታ ምሁራን የገለፁትንና በፊልም የተደገፈ መረጃም ለዚህ ፅሁፍ በግብአትነት በመጠቀም እውነታውን ለማቅረብ ጥረት ተደርጓል። በዚሁ ወደ ዝርዝር ጉዳይ እናምራ።

የአሜሪካ ታላቅነትና ትልቅነት በተለያየ መንገድ መግለጽ ይቻላል የዚህ ጽሑፍ ትኩረት ግን ስለኮሎራዶ ወንዝና ስለሁቨር ግድብ ብቻ ነው። የቱርክ የስልጣኔና የዕድገት ደረጃም ብዙ የተባለለት ቢሆንም በዚህ ጽሁፍ ግን ለኤፍራተስ ወንዝና ስለአታቱርክ ግድብ ብቻ እናነሳለን። ይህን ከእኛ የእድገት ደረጃ ጋር ስናነጻፅረው ደግሞ ዋናው መነሻችን  አገራችን ባላት የቀደመ ታሪክና የሥልጣኔ ደረጃ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። ‹‹ትልቅ ነበርን ትልቅ እንሆናለን!›› እንዲሉ!! እኛ በዓለም የቀደመ ታሪክ በመጀመሪያው ተርታ እንደነበርንና  ከስልጣኔ ማማ ላይ በመድረስ ታላቅ ሆነን የኖርንበት ዘመን ታሪክ ሆኖ  ሲገለጽ ለዛሬው መነሻ ሆኖን በመታደስ ጉዞ የብልፅግና ዘመንን ለማብሰር አስችሎናል።  የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጀመርና ሂደቱሳይቋረጥ ቀጥሎ በመገንባት ላይ መሆኑን የነበረንን ታላቅነት በማጉላት በግድቡ ፍጻሜ የሚኖረው ትርጉም የላቀ ነው። በተለይም በሕዝባዊ መነሳሳት የግድቡን ታላቅነትና ግዙፍነት በሚያረጋግጥ ውጤታማነት‹‹ እንደጀመርን እንጨርሰዋለን!›› በሚል መርህ የተነሳንበትን ዛሬ ደግሞ ግንባታው ከመጋመስ በማለፉ‹‹እንዳጋመስነው እንጨርሰው!›› በማለት በጋራ ልንቀሳቀስ ይገባል እንደ አሜሪካውያኑ የሁቨር ግድብ  እና የቱርክ ኤፍራተስ ወንዝ አታቱርክ ግድብ ፍፃሜ ማግኘት ጋር እኛም ለውጤት የምንበቃበትን ጊዜ ከመናፈቅ ባለፈ እውን እንዲሆን መረባረብ ያስፈልጋል።

እኛ በዓባይ ወንዝ ላይ ከፍተኛ የውሃ ድርሻ እያለን ለዘመናት ሳንጠቀምበት በመፍሰሱና ለጎረቤት አገራት ሲሳይ መሆኑን እያነሳን በግጥም፣ በዜማ፣ በቅኔ ጭምር  የነበረንን ቁጭት በመግለፅ ለዘመናት መኖራችን ብዙ የተባለለት ነው። እኛ በዓባይ ወንዝ የነበረንን ቁጭት ያህል አሜሪካውያኑም ሆኑ ቱርኮቹ በየራሳቸው ወንዞች ተጠቃሚነት ዙሪያ ከተለያዩ መሰናክሎች  ጋር ቁጭት ነበረባቸውበአሜሪካ የኮሎራዶ ወንዝ፣በቱርክ ደግሞ የኤፍራተስወንዝ ለዓመታት ያላንዳች ጥቅም በመፍሰስ ከተማና ገጠሩን በጎርፍ ማጠባቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። እኛ በዓባይ ወንዝ ስንቆጭ እንደኖርን ሁሉ አሜሪካውያንም በኮሎራዶ ወንዝ  ቁጭት ነበረባቸው።  እኛ በአባይ ወንዝ ተጠቃሚ ያለመሆናችን እንዳለ ሆኖ  ወንዙን ለመገደብ ከመነሳታችን በፊት እና ለመገደብ  በመጀመራችን የተለያዩ ውጣ ውረዶችና ተፅዕኖዎች እንዳጋጠመን ይታወቃል። ከእኛ ቀደም ብሎ ደግሞ ቱርካውያን በኤፍራተስ ወንዝ አጠቃቀም ዙሪያ የጎረቤት አገራት በተለይም የኢራቅ ተፅዕኖ ተፈታትኖአቸዋል። አሜሪካውያንም የኮሎራዶን ወንዝ ለመገደብ  ሲነሱ በውሃ የክፍፍል ድርሻ ዙሪያ ክርክሮችና ውዝግቦች አጋጥመዋቸዋል። እነዚህ ውጣ ውረዶችና ተፅዕኖዎች ሁሉም ታልፈው አሜሪካውያን በመሀንዲሶቻቸው ብቃትና አቅም እንደገናም በወቅቱ ፕሬዚዳንት ፕሬዝዳንት ሁቨር የማግባባት ችሎታና ጥረት የኮሎራዶን ወንዝ በመገደብ ለውጤት በቅተዋል። ዛሬ በኮሎራዶ ወንዝ ላይ የሁቨር ግድብ በመገንባቱ  የታየው ለውጥና የአካባቢው ገፅታ ማራኪነት የዚህ ሁሉ ጥረት ውጤት ነው። ቱርክም የኤፍራተስን ወንዝ ገና ለመገንባት ስትነሳ ያጋጠማትን ተፅዕኖዎችና ተግዳሮቶች የተወጣችው በራሷ ጥረት በተለይም በገነባችው ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ የበላይነትና በፈረጠመ አቅሟ ነው። እኛም ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግደብ ለመገንባት ስንነሳ በሚደርሱብን ተፅዕኖዎች እንደማንበረከክ በማረጋገጥ ሲሆን ባለን ቁርጠኝነትና ህዝባዊ ተሳትፎ ወደ ውጤት የማምራታችን ሂደት ከሁለቱ አገራት አንፃር ተመሳሳይነቱ ይጎላል።

በዓለማችን ረጅም በተባለው የዓባይ ወንዝ ላይ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለመገንባት ከመወሰናችንና ግንባታው ከመጀመሩ በፊት ከፍተኛ ቁጭት እንደነበረን ቀደም ሲል ተገልፆል። እኛ በዓባይ ወንዝ ለዘመናት የነበረን ቁጭት ተወግዶ ግንባታውን በመጀመር የግንባታው ሂደት መፋጠኑ ኢትዮጵያውያን እንደ አገር በአንድ ላይ ለአንድ ዓላማ የመቆማችንን ለወደፊትም ይህን መንገድ የመከተላችን ዓቢይ ማሳያ እንደሆነ ይታመናል። ሂደቱ ግን ብዙ ውጣ ውረድ ነበረበት። በተለይም የዓባይን ወንዝ ለመገደብ ለግንባታ የሚሆን ገንዘብ በብድርም ሆነ በእርዳታ እንዳናገኝ በርካታ ተጽዕኖዎች እንዳጋጠመን አይካድም። ለእነዚህ ተጽዕኖዎች ሳንበረከክ አባይን ለመገድብ ስንነሳ እና ከግድቡ መጀመር ቀጥሎም ቢሆን ከተፋሰሱ አገራት ጋር በትብብርና በመግባባት መንፈስ ለመስራት ከፍተኛ ጥረት መደረጉ በበጎ ጎኑና በአርአያነቱ ይጠቀሳል። ያጋጠሙንን አንዳንድ መሰናክሎችና ተግዳሮቶች ለመበጣጠስ ከተካሄዱት ፖለቲካዊና፣ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ጋር የሕዝባችን ቁርጠኝነት ለውጤታማነታችን የላቀ ድርሻ ነበረው። በተለይም የግብፅ አለመረጋጋትን ተከትሎ የፕሬዚዳንት የሙርሲ ወደ ስልጣን መምጣት እና ከሙርሲ መንግሥት ምስረታ በኋላ በግንባታው መጀመር የተለያዩ ተቃውሞዎች እንደነበሩ ይታወቃል። አንዳንዶቹ በአገራችን ላይ ስጋት በማሳደር ጫና ለመፍጠርም የታለሙ ነበሩ ። በተለይም ‹‹ከግብፅ ውሃ ድርሻ አንድ ጠብታ እንኳን ቢቀር አማራጩ ደም ነው›› በሚለው የሙርሲ ዛቻ በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት ለመክፈት የታለመ ውይይት መካሄዱ ይታወሳል። ይህ ወቅት በአካባቢው ውጥረት ቀስቅሶ እንደነበር አይካድም። ከዚህ በተጨማሪ የቱርክ ባለሥልጣናት በአንድ ወቅት ኢትዮጵያን ሲጎበኙ ተመሳሳይ ነገር ተንፀባርቋል። ይህም በቱርክ፣ በሶርያና ኢራቅ መካከል በኤፍራተስ ወንዝ መገንባት ዙሪያ የነበረውን ውዝግባና የአካባቢውን አገሮች የውሃ ፖለቲካ በመንተራስ  ይህንንም  ወደ ምስራቅ አፍሪካ በመሳብ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት ላይ ጫና እና ተፅዕኖ ለመፍጠር  የተሞከረበት ነው። በዚህ ረገድ እ.ኤ.አ. ፌብሪዋሪ 2014 ዓ.ም.  የግብፅ የውሃና የመስኖ ሚኒስቴር የነበሩት መሐመድ አብዱል ሙታሊብ የኢትዮጵያን ታላቁ ህዳሴ ግድብ መገንባት በመቃወም ከቱርክ የኤፍራጠስ ወንዝ መገንባት ጋር በማያያዝ የገለጡት ጉዳይ እንዲህ ይጠቀሳል፡ ‹‹ቱርክ የአታቱርክ ኃይል ማመንጫ ግድብን በገነባችበት ወቅት የሶርያን የኢራቅን ሕዝቦች በውሃ ጥም አሰቃይታለች፣ ዓለም ዓቀፉን ስምምነት ጥሳለች›› ካሉ በኋላ ‹‹አሁን አጠንክሬ ማለት የምፈልገው ግብፅ፡- ሶርያንና ኢራቅን አይደለችም። ኢትዮጵያም ቱርክ አይደለችም›› በማለት ፀብ አጫሪ ንግግር አድርገዋል። ይህ ከመሆኑ በፊት ግን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የተጀመረበት ወቅት በግብፅ ከተቀጣጠለው የአረብ አብዮት ጋር የተገጣጠመ በመሆኑ በወቅቱ በግብፅ በኩል በግንባታው መጀመር ዙሪያ የተሰነዘረ ተቃውሞና ተጽዕኖ እንዳልነበር ይታወሳል። በግብፅ የሙርሲ ሥልጣን መያዝ ጋር የነበሩ አለመግባባቶችም የሙርሲ ከሥልጣን መወገድ ተከትሎ የተሻለ መግባባት ላይ ተደርሷል። በዚህም የነበሩት በርካታ መሰናክሎችና ተግዳሮቶች ታልፈው በመንግሥት ዲፕሎማሲያዊ ጥረትና በሕዝቡ የላቀ ተሳትፎ እንደገናም በታችኞቹ አገራት የትብብር መንፈስ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ለሰከንድ ሳይቋረጥ በመገንባት ላይ ይገኛል። የአሜሪካው የኮሎራዶ ወንዝ ግንባታ እና የቱርክ አታቱርክ ወንዝ መገንባት በበጎ መልኩ ተሞክሮና ትምህርት የሚገኝበት በመሆኑ ከዚህ ተነስተን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፍፃሜ በሚያገኝበትናለአገልግሎት በቅቶ ለማየት እኛ ከእነሱ ምን እንማራለን? በሚል መነሻ የሁለቱን አገራት ተሞክሮ በዝርዝር መመልከት ያስፈልጋል በቅድሚያ ከቱርክ እንነሳ።

ቱርክ የተፈጥሮ በረከት የሆናትን  የኤፍራጠስ ወንዝ ለመጠቀም ስትነሳ በሁለቱ የግርጌ አገራት ሶርያ እና ኢራቅ ተፅዕኖ እንዳጋጠማት መረጃዎች ይገልጻሉ። በተለይም የወንዙን አጠቃቀም በተመለከተ ስምምነት ባለመኖሩ ስምምነት እንዲኖር በዘመኑ ልዕለ ኃያል አገር ኢራቅ ከፍተኛ ግፊት ደርሶባታል። በዚህም የኤፍራተስ ወንዝ ምንጭና መነሻ የሆነችው ቱርክ  የቀድሞዋን ኃያል ሀገር ኢራቅ ሳታማክር የወንዙን አቅጣጫ እንዳትቀይር ተገዳ ነበር። በዚህም ተፅዕኖ ደርሶባታል። እ.ኤ.አ. በ1946 ዓ.ም. በዘመኑ ኃያል አገር ኢራቅ ግፊት በወንዙ አጠቃቀም ዙሪያ ስምምነት ሲደረግ ቱርክ በበኩሏ የተፈጥሮ በረከት የሆነውን የኤፍራተስ ወንዝ ወደ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለመቀየር ወደ ኋላ አላለችም። በዚህም የአታቱርክ ግድብ በመገንባት ለመጠቀም የኤፍራተስን ፍስት ማቆም ስለነበረባት የወንዙን ፍሰት ከማቆሟ አንድ ዓመት ቀድማ እቅዷን ለሶርያ እና ለኢራቅ ዘርዝራ አሳውቃለች። ይህ ሁሉ ሆኖ ግን ድርጊቷ በሁለቱ የግርጌ አገራት እንደ ድፍረት ተቆጠረ።

በዚህ መሰረት የኢራቅ ተፅዕኖ በወቅቱ በነበራት ወታደራዊ የበላይነት ሳብያ ተፅኖዋ  ለዓመታት ቢዘልቅም ቱርክ ግን ግደቡን ትኩረት ሰጥታ ከመገንባት ወደ ኋላ አላለችም። እቅዷም እንደማይቀለበስ ከማሳወቅ ባሻገር የኢኮኖሚና የፖለቲካ አቅሟ እየተቀየር እና እየተጠናከረ በመምጣቱ የአካባቢው የኃይል ሚዛንና የፖለቲካ ተፅዕኖ መለወጥ ቱርክን አፈረጠማት። ግድቡንም መገንባት በመጀመር ገፋችበት። በዚህም ሂደቱን ከመቃወም እና ከማውገዝ ባለፈ የደረሰባት አስገዳጅ እርምጃና ተፅዕኖ አልታየም። የግድቡ ፕሮጅክት ተጀምሮ በመጠናከሩም ቱርክ የበለጠ አቋሟ እየበረታ መጣና ከፍፃሜ በማድረስ ለውጤት በቃች። የዚህ የግድብ ፕሮጀክት ፍፃሜ ማግኘትም የቱርክን የኢንጅነሪንግ አቅም ያንፀባረቀ እንደሆነ ተነግሮለታል። ገና ፕሮጀክቱ ሲጀመር 13 የመስኖ ልማቶች እንደሚኖረው ተወጥኖ ነበር። በመጨረሻ ግን ይህ ሁሉ ተቀይሮ 22 ግድቦችንና 19 የኃይል ማመንጫዎችን በማካተት እንደተጠናቀቀ መረጃዎች ይገልፃሉ። በዚህ መሰረት ከተገነቡት የኃይል ማመንጫዎች መካከል አታቱርክ የተሰኘው የኃይል ማመንጫ  ግድብ ግንባታ የተጠናቀቀው እ.ኤ.አ. በ1990 ነው። የአታቱርክ ኃይል ማመንጫሥራ ለመጀመር ግደቡ በውሃ መሙላት በመጠየቁ ምክንያት የኤፍራተስ ወንዝ ለአንድ ወር ያህል እንዳይፈስ ተገድቧል። ይህ የቱርክ ውሳኔና እርምጃ በተለይም ወንዙን ማገዷ ግድቡን በመገንባት ለውጤት ከመብቃቷ በፊት በመሆኑ በሁለቱ አገሮች ዘንድ ቅሬታ በማሳደሩ ተቃውሞና ተፅዕኖ አጋጥሟታል። በተለይም የአካባቢው የውሃ ፖለቲካና ተፅዕኖ ቢኖርም እንኳ ቱርክን አላንበረከካትም። እሷም በቆራጥነት ግድቡን ለማጠናቀቅም በቅታለች።

የኤፍራተስ ወንዝ ዓመታዊ የውሃ መጠን 32 ቢሊዮን ሜትር ኪዩቢክ ሲሆን የዚህ ወንዝ የውሃ መጠን ዘጠና በመቶ ድርሻ የሚገኘው ደግሞ ከቱርክ ነው። ወንዙ ከቱርክ ተነስቶ የያዘውን ይዞ ወደ ሶርያ ግዛት ይዘልቃል፡ ይህ የኤፍራተስ ወንዝ ታሪካዊና እንደ እትብት ቱርክን ከሶርያ እና ከኢራቅ ጋር ያገናኘ የተፈጥሮ ገፀ በረከት እንደሆነም ይነገርለታል። የኤፍራተስ ወንዝ የውሃ ድርሻ በአብዛኛው ከቱርክ መሆኑ እና የዚህ ወንዝ ፍሰት በማቆም ወደ ግንባታ የገባችበት ሂደት ማንም ምንም ሳይበግራት ለውጤት የመብቃቷ እውነት ከአገራችን ጋር ተመሳሳይነት አለው። በተለይም ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ያላት የውሃ መጠን እና ድርሻ ከ 86 በመቶ በላይ መሆኑ እና ግድቡን ለመገንባት ስትነሳ የነበረው ተፅዕኖ እና ጫና በአብዛኛው ከቱርክ ጋር ያመሳስላታል።

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ታላቁን የህዳሴ ግድብ በመገንባት ሂደት እና ግንባታው ከተጀመረ አንድ ዓመት በኋላ ለግንባታው ስኬት ሲባል የአባይ ወንዝ ተፈጥሮዊ የፍሰት መስመር አቅጣጫ እንዲቀየር መደረጉ  በግብፅ የሙርሲ አስተዳደርና በግብፅ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዘንድ ቁጣን ከመቀስቀሱም በላይ በኢትዮጵያ ላይ ተዕዕኖ ለመፍጠርም ተሞክሯል። ቱርክ በወቅቱ ለኢራቅ ተፅዕኖ ሳትበገር ለውጤት እንደበቃች ሁሉ እኛም በዓባይ ተፋሰስ ውስጥ የግብፅ የበላይነት ለዘመናት ፀንቶ የቆየበትን ሂደት በመበጠስ በዓባይ ወንዝ ግድብ መገንባት መጀመራችንን የመተባበር መንፈስ በመምጣቱ ብቻ ሳይሆን  እኛም እንደ ሀገር የራሳችንን አቅም በመገንባት የተሻለ የእድገት ደረጃ የመድረሳችን ውጤት መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። ከዚህ አንፃር ግድቡን ለፍፃሜ የማድረሱን ጥረት በማጠናከር ረገድ ከቱርክ መማር ያስፈልጋል። ገና ግድቡን መገንባት ስንጀምር ‹‹እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን››የማለታችንም ቁርጠኝነትም በተግባር እንደሚረጋገጥ ማንም አይክደውም። አሁን ደግሞ የግድቡ ግንባታ ተጋምሷል። ‹‹እንዳጋመስነው እንጨርሰዋለን!››በሚለው መርህ ወደ ፍፃሜው ማምራት ግድ ይላል።

‹‹ምንና ምን ናቸው?›› ያስባለን ሌላው ጉዳይ ደግሞ የአሜሪካውያኑ የኮሎራዶ ወንዝ ነው። የኮሎራዶ ወንዝ በርካታ የአሜሪካን ግዛቶች የሚያካልል ትልቅ ወንዝ  ነው። ይህ ወንዝ እንዲገደብ ሲወሰን የፍሰቱን መስመርና አቅጣጫ መቀየር ግድ ነበር። በዚህም የተነሳ በውሃ ክፍፍሉ ድርሻ ዙሪያ ከየግዛቶቹ ክርክሮችና ውዝግቦች ተፈጥረዋል። በእነዚህ አለመግባባቶች እና ክርክሮች የተነሳ ውዝግቡ በመካረሩ የግድቡ ግንባታ ‹‹ሕልም ሆኖ ይቀራል›› እስከ መባል ደርሶ ነበር። እኛ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለመገንባት ቁርጠኛ አቋም ከመውሰዳችን በፊት የነበርንበት ሁኔታ በተለይም በአባይ ወንዝ አጠቃቀም ዙሪያ የገባንበትን ያህል ችግርና ፈተና ያህል አሜሪካውያን ባያጋጥማቸውም በኮሎራዶ ወንዝ በመገንባት ጉዳይ የተነሳ እ.ኤ.አ. 1923 ዓ.ም ከባድ ቀውስና ጭንቀት ውስጥ እንደነበሩመረጃዎች ያስረዳሉ፡፤ የኮሎራዶ ወንዝ ለአሜሪካውያን ከአፍንጫቸው ስር እየተገማሸረና እየተንፏለለ መፍሰሱ ሳያንስ በየዓመቱ ከተማን ከገጠር ሳይለይ በጎርፍ በማጥለቅለቅ ጉዳት ያደርስባቸው እንደነበር ይታወቃል። እኛ ለዘመናት በአባይ ወንዝ ስንቆጭ እንደኖርን ሁሉ አሜሪካውያን በኮሎራዶ ወንዝ ባለመጠቀማቸው መቆጨታቸው ለዘመናት ዘልቋል።

የአባይ ወንዝ ከጎጃም አካባቢ ተነስቶ በጣና ሀይቅ ላይ በመንፈላሰስ ሀይቁን መሀል ለመሀል ሰንጥቆ በረሃማውን የአባይ ተፋሰስ ተከትሎ በተራሮች ግራና ቀኝ የራሱን ሸለቆ በመፍጠር በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በኩል የባምቡዴን ተራራ ግራና ቀኝ በመክፈል በረሀማውን አካባቢ አልፎ አፈራችንን ተሸክሞ ወደ ሱዳን ያመራል።  በተመሳሳይ መልኩ የቱርክ ኤፍራጠስ ወንዝ ከቱርክ ተነስቶ ወደ ሶርያና ኢራቅ እንደሚያመራና የአሜሪካው ኮሎራዶ ወንዝም አሪዞናን ከወዲህ ማዶ የኔቫን በረሃን ወዲያ ማዶ ሰንጥቆ በሸለቆማ ቦታዎች በማለፍ በርካታ ግዛቶችን እያቆራረጠ ያለ አንዳች ጥቅም ለዓመታት ሲፈስ ነበር። አሜሪካውያን ይህንን ወንዝ ለመገደብ ሲነሱ በግንባታው ሂደት የነበረው ውጣ ውረድና ፈተና ይታወሳል። ግንባታው በአሜሪካውያኑ መሀንዲሶች ብቃትና ችሎታ ለውጤት ቢበቃም በግንባታው ሂደት ግንባታው በሚካሄድበት የኔቫዳ በረሃ አካባቢ እነዚህ መሀንዲሶችና ሠራተኞቻቸው ሥራው አሳርና ፍዳ እንዳስቆጠረባቸው በተለይም በዘመኑ ከነበረው ቴክኖሎጂና ከበረሀማው አካባቢ አለመመቸት ጋር መሀንዲሶቹና ሠራተኞቹ ብዙ ውጣ ውረድ እንዳጋጠማቸው መረጃዎች ያስረዳሉ። ይህንን እውነታ አሁን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከሚገነባበት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ  ክልል  ጉባ አካባቢ ጋር በማነፃፀር ማየት ይቻላል። የኔቫዳ በረሃ የሙቀት መጠን የእኛ ህዳሴ ግድብ ከሚገነባበት አካባቢ ጋር ተመሳሳይ የሙቀት መጠን እንዳለው ልብ በሉ። የኮሎራዶ ወንዝ ሲገነባ የነበረው ሙቀት ለግዙፉ የኮንክሪት ሥራ ፍፁም የማይመች እንደነበረና ይህም ሆኖ የአሜሪካ መሀንዲሶች ይህን ችግር ለመወጣት ጥረት አድርገው ለውጤት መብቃት የቻሉት እንዲሁ በቀላሉ አይደለም። በወቅቱ ከነበረው ስልጣኔና ቴክኖሎጂ አንፃር አሜሪካውያን በሰው ልጆች ታሪክ ታላቁን የሁቨር ግድብ በመገንባት እውቀትና ችሎታቸውን በመጠቀም ያደረጉት ጥረት ያጋጠማቸውን ችግርና ፈተና በሚገባ መውጣት አስችሏቸዋል። ይህም የዓላማ ቁርጠኝነት ካለ የማይቻል ነገር እንደማይኖር የአሜሪካውያን ተሞክሮ ጥሩ ማሳያ ነው። እኛ ደግሞ ዘመኑ ባፈራው ቴክኖሎጂ ተጠቅመን በሕዝባችን ጥረትና ተሳትፎ ለውጤት እንደምንበቃ በግንባታው ሂደት ከታየው ቁርጠኝነት ማረጋገጥ ይቻላል።

በመገንባት ላይ የሚገኘው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ  የኮንክሪት ሥራ ያኔ አሜሪካውያን በኮሎራዶ ወንዝ ላይ ከነበረው የኮንክሪት ሥራ ጋር ሲነጻፀር የነበረው አስቸጋሪነትና ውጣ ውረድ እንደአሁኑ ቀላል የሚባል  አልነበረም። የኮሎራዶ ወንዝ ሲገነባ በግድቡ ግራናቀኝ ፊትና ኃላ፣ ላይና ታች በመድፈን የሚገነባው የኮንክሪት ተራራን ያኔ ለማቀዝቀዝ ምንም እድል አልነበረም። አስቸጋሪነቱ ያን ያህል ሲሆን ኮንከሪቱ እስከሚቀዘቅዝ እንጠብቅ ሲባል ኖሮ ግንባታው ዓመታትን እንደሚፈጅ ተገምቶ ነበር። ለዚህ ችግር የመሀንዲሶቹ ብቃትና ችሎታ አፋጣኝ መፍትሔ በማስገኘት ችግሩን መፍታት ተችሏል። አሁን የእኛ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሲገነባ  የኮንክሪት ሥራው በፍጥነት እንዲቀዘቅዝ ቴክኖሎጂው ምቹ ሁኔታ በመፍጠሩ በረዶ በማፍሰስ የግንባታውን ሂደት ማፋጠን ተችሏል። በኮሎራዶ ወንዝ ላይ የተገነባው የሁቨር ግድብ ሲገነባ ግን እንደዛሬው በረዶ ማምረቻ ማሽን በቀላሉ አልነበረም። በመሆኑም መሀንዲሶቹ ውሃ በመጠቀም ኮንክሪቱን የሚያቀዘቅዙበት መላ ዘይደዋል። በዚህ ዘዴ ስራው ሳይጓተት ቀጥሎ ሰባት ዓመት ይፈጃል የተባለው ግንባታ ከታቀደለት ጊዜ ቀደም ብሎ በአምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት ማብቃት ተችሏል። በዚህ ረገድ የኮሎራዶ ወንዝ የግንባታ ሂደት ለእኛ ትምህርት በመሆኑ መነሳሳት እንደሚፈጥርልን አይካድም። የግንባታው አጀማመርና ሂደትም ለውጤቱ መገኘት ዋናው ጉዳይ በመሆኑ ይህንን በዝርዝር ማየት ያስፈልጋል።

አሜሪካውያን  የኮሎራዶን ወንዝ ለመገደብ መጀመሪያ ሲነሱ በውሃው ክፍፍል ድርሻ ዙሪያ ክርክርና ውዝግብ ቢያጋጥማቸውም ይህን ችግር በሰለጠነ መንገድ ለመፍታት ውይይትና ድርድር አካሂደዋል። ለዚህም በወቅቱ የነበሩት የአሜሪካ 31ኛው ፕሬዚዳንት ሁቨር የነበራቸው ድርሻ የላቀ መሆኑ በታሪክ ተጠቅሷል። ፕሬዚዳንቱ ከየግዛቱ አስተዳዳሪዎችና ባለሥልጣናት ጋር በመገናኘት ባካሄዱት ውይይት ሚዛናዊ የውሃ ክፍፍል እንዲኖርና ከስምምነት ላይ እንዲደርስ ያለሳለሰ ጥረት አድርገው ተሳክቶላቸዋል። ፕሬዚዳንት ሁቨር ከፖለቲከኝነታቸው በተጨማሪ መሀንዲስም ነበሩ። ወግ አጥባቂ ቢሆኑም ደግ ሰው መሆናቸውምይነገራላቸዋል። የታታሪነታቸውን ያህል አሳ በማጥመድ መዝናናትን ይወዳሉ። ከሁሉም በላይ ደግሞ ‹‹የሰው ልጅ በአካባቢው የሚገኝ ተፈጥሮአዊ ነገሮችን ወደ መልካምና ጠቃሚ ነገር የመለወጥ ችሎታአለው›› የሚል ጠንካራ እምነትና ራዕይ የያዙ ሰው በመሆናቸው ግድቡ ተገንብቶ ለውጤት እንዲደርስ ብዙ ሰርተዋል።

በኮሎራዶ ወንዝ ላይ ግድብ ለመገንባት በወንዙ አካባቢ የሚገኙ ተራሮችን በድማሚት በመናድ የወንዙን አቅጣጫ ለማስቀየር የተደረገው ጥረትና ትግል ከፍተኛ ውጣ ውረድ የነበረበት ሲሆን የተራራቁትን ተራሮች በሸለቆ በማገናኘት በትኩረት መስራት ግድ ነበር። ሁሉም ችግሮችና ውጣ ውረዶች ታልፈው ግንባታው ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ በማድረግ ረገድ የፕሬዚዳንቱ ሚና የላቀ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ። አሜሪካ በ1930ዎቹ ሁቨር ግድብን (Hoover Dam) ሳትገነባ ሕዝቦቿና መንግስት ወጭውን በወቅቱ መሸፈን ስላቃታቸው የኩባንያዎችን ገንዘብ ለመጠቀም ተገዳለች። ምክንያቱም አሜሪካ በታላቅ የኤኮኖሚ ቀውስ ውስጥ በነበረችበት በ1930ዎቹ የሁቨር ግድብን ስትሰራ ወጭውን መሸፈን ስላልቻለች የስድስት ኩባንያዎች አክስዮን የነበረውንና የግንባታውን ጨረታ ያሸነፈውን ተቋም ገንዘብ መጠቀም ነበረባት። በአሜሪካ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በመንግስትና በሕዝብ ትብብር በተገነባውና በወቅቱ በታላቅነቱ በዓለም ቁጥር አንድ በነበረው በዚህ ግድብ 21 ሺህ ሠራተኞች የተሳተፉ ሲሆን፣ በግንባታው ሥራ ላይ እያሉ ከአንድ መቶ በላይ ሠራተኞች ህይወት አልፏል።

የአሪዞና እና የኔቫዳ ግዛት ነዋሪዎች የኮሎራዶ ወንዝ ተገንብቶ እስከሚበቃ ተስፋ ሰንቀው ፍፃሜውን ለማየት እጅግ በጣም ጉጉት ነበራቸው። ልክ እኛ አሁን ለታላቁ የአትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፍፃሜ እንዲያገኙ በጉጉት እንደምንጠብቅ ሁሉ ያኔ የአሪዞና እና የኔቫዳ ግዛት ነዋሪዎች የነበራቸው ተስፋ ለውጤት መብቃቱን በማየታቸው ደስታቸው ወሰን አልነበረውም።

ግድቡ ሲጠናቀቅ በወቅቱ በነበረው ስሌት ግድቡን ለመስራት የፈሰሰው ሲሚንቶና ኮንክሪት 4674 ኪ.ሜትር የሚደርስ ደረጃውን የጠበቀ ሰፊ የአስፋልት መንገድ ሊሰራ እንደሚችል ይገመታል። ይህም እስከ ደቡብ አፍሪካ የሚዘልቅ የአስፋልት መንገድ ማለት ነው። ለዚህ ግድብ ያኔ የወጣው ገንዘብ 49 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን በግንባታው ሥራ ወደ 21,000 አሜሪካውያን ሰራተኞች ተሳትፈዋል። ያ በጎርፍ እያጥለቀለቀ መከራ ሲያደርስ የነበረው የኮሎራዶ ወንዝ ዛሬ ለሚሊዮኖች የመጠጥና የመስኖ ውሃ አስተማማኝ ምንጭ ከመሆኑም በተጨማሪም የኤሌክትሪክና የብርሃን መፍለቂያ በመሆን የላቀ አገልግሎት በማበርከት ላይ ይገኛል። በግድቡ ምክንያት የተፈጠረውንና እንደ አገር የሚሰፋው ሰው ሰራሽ ሀይቅ በዓለም የመጀመሪያ ትልቅ ሰው ሰራሽ ሀይቅ በመባል በዝነኛነቱ ለመታወቅ በቅቷል። የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎቹ የሚገኙት ከግድቡ ስር መሬት ውስጥ በጥልቅ ቦታ ስለሆነ በሊፍት ወደታች ቁልቁል ብዙ ርቀት መግባት ግድ ይላል። አሁን በኔቫዳ በረሃ ላይ ጉብ ካለችው ሽቅርቅሯ የላስቬጋስ ከተማ ወደ አሪዞና በሚወስደው ምቹ መንገድ እንደተጓዝን ከፊት ለፊት ከዓይናችን ጋር የሚጋጨው ተራራና ገደል የሚመስለው ነገር ድንጋይም፣ ተራራም፣ ገደልም ሳይሆን የሁቨር ግድብና ድልድይ መሆኑን ልብ እንላለን። ይህ የኮሎራዶ ወንዝ ግድብ (ሁቨርዳም) በአሪዞና ግዛት የፊኒክስ ከተማንና የኔቫዳ ግዛት ላስቬጋስን የሚያገናኝ ሰማይ ጠቀስ ድልድይ በመሆኑ በየዕለቱ በርካቶች ይጎበኙታል። ያ የኔቫዳ በረሀማነት ተለውጦ ዛሬ አዲስ ሕይወት እየታየበት ነዋሪዎቹ በተሻለ አኗኗር ህይወታቸውን እየመሩ ይገኛሉ። አሜሪካውያን የኮሎራዶ ወንዝ ግድብ በመገንባት እንደጀመሩት በመጨረስ የላቀ ተጠቃሚ ሆነዋል። አካባቢውም ተመራጭ ሆኗል። የሁቨር ግድብ በተፈጥሮ የታደለ አካባቢ በመሆኑ ዛሬ በቱሪስት መዳረሻነቱና በመዝናኛነቱ በሁሉም ዘንድ ተመራጭ ሆኗል። ከዚህ ስንነሳ  እኛም በራሳችን  አቅምና ያላሰለሰ ጥረት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፍፃሜ እንዲያገኝ ተስፋችን ይበረታል። የኮሎራዶ ወንዝ አሜሪካውያንን የታደገውን ያህል የእኛ አባይ ወንዝም በተሻለ ውጤታማነት እንደሚታደገንና እንደ አሜሪካውያኑ የምንደሰትበት ጊዜ እሩቅ እንደማይሆን እንገምታለን። የህዳሴው ግድብ ሲጠናቀቅ ውሃው ወደ ኋላ የሚተኛበት ቦታም ሰው ሰራሽ ሀይቅ በመፍጠር ከሚኖረው ኤኮኖሚያዊ  ጠቀሜታ ባሻገር በቱሪስት መስህብነቱ የበርካቶች መስህብ እንደሚሆን አያጠራጥረም። በኮሎራዶ ወንዝ ግድብ እንዲገነባ ዋናውን ሚና የተጫወቱትና የመሠረተ ድንጋይ በማስቀመጥ ግንባታውን ያስጀመሩት ፕሬዚዳንት ኸርበርት ሁቨር ግድቡ ሲጠናቀቅ የስልጣን ዘመናቸው በምርጫ በመጠናቀቁ ግድቡን መርቀው የከፈቱት 32ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ፍራንክሊን ፉዝቬልት  ናቸው።

ታላቁ የሁቨርት ግድብ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ የውሃ ምንጭ ከመሆን አልፎ ለበርሃማው አካባቢ አዲስ ህይወት የሚሰጥ ሰው ሰራሽ ሀይቅ ለመፍጠር የበቃውን ግድብ ፕሬዚዳንት ፍራንክሊን ሩዝቬልት መርቀው የከፈቱት እ.ኤ.አ.መስከረም 30 ቀን 1935 ዓ.ም.ነበር። መርቀው ሲከፍቱት ‹‹ቦልደር ዳም›› የሚል ስያሜ ነበረው።  ይህን ስያሜ ‹‹ሁቨርዳም›› በሚል እንዲጠራ የአሜሪካን ኮንግረስ እ.ኤ.አ. በ1947 ዓ.ም.  ወሰነ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ስያሜው ‹‹ሁቨር ዳም›› በሚል መጠራት ጀመረ።  የሁቨርት ግድብ ካለው ፋይዳ እና የአሁኑ ገፅታ አንፃር ለእኛ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያበረክተው ከፍተኛ ተሞክሮ አለው። ይህን የአሜሪካውያን ጠንካራ ቁርጠኝነት ከዛሬ ዘጠና ዓመት በፊት ከነበሩበት የዕድገትና የኑሮ ደረጃ አንፃር በማገናዘብ በጎ ተሞክሮውን መውሰድ ያስፈልጋል።

በአሁኑ ሰዓት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚገኝበት ደረጃ አበረታች ከመሆኑ በተጨማሪ የግንባታው ሂደት በመፋጠን ላይ ይገኛል። ሁሉም የአገራችን ሕዝቦች ዓይንና ጆሮ ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ጉባወረዳ ባምቡዴ ተራራ አካባቢ ከዘለቀ ቆይቷል። መላ ሕዝባችንን በተሳትፎው እንደጀመረው ለመጨረስ በተለያዩ መንገዶች ድጋፉን በማጠናከር ሕዝቡ የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል። ይህ የባንዲራ ፕሮጀክት ፍፃሜው ሩቅ እንደማይሆን ሁሉ ያንን ለማየት የማይጓጓ የለም። ግድቡ ሲጠናቀቅም አካባቢው የሚኖረው ገፅታና ማራኪነት ከወዲሁ ተስፋ ሰጭ ከመሆኑ በተጨማሪ በተለያዩ ዘርፎችም ለበርካታ ዜጎች የሰራ እድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል። በአካባቢው በግድቡ ምክንያት በሚፈጠረው ኃይቅ ለአሳ እርባታና ለከፍተኛ የምርምር ስራ አመቺ መሆኑና በተፈጥሮ ለበርካታ ተመራማሪዎች የምርምር ማዕከል እንደሚሆን መታሰቡ የግድቡ ጠቀሜታ የላቀ እንደሚሆን ነው። እኛም እንደ ላስቬጋስና እንደኔቫዳው ሁቨር ግድብ ተስፋችን እውን ሆኖ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፍጻሜ የተሻለች ኢትዮጵያን የምናይበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም። በእርግጥም ገና ከመነሻው ‹‹እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን››። የማለታችን ያህል አሁን ደግሞ ‹‹እንዳጋመስነው እንጨርሰዋለን›› የሚለው እውነታ ቅርባችን ነው።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ ከፍታው 145 ሜትር፣ የጎኑ ርዝመት 1.8 ከ.ሜ. ሲደርስ የሚከማቸው የውሃ መጠን የጣና ሀይቅን ሁለት እጥፍ ይሆናል። ግድቡ ሲጠናቀቅ 1ሺ 680 ስኩየር ኪ.ሜ.የሚሸፍን ወደ 74 ቢሊዮን ኪዮቢክ ሜትር የውሃ መጠን ይኖረዋል። ከግድቡ ወደ ኋላ ሜዳማ ስፍራውን አልፎ በርቀት የሚታዩት አነስተኛ ተራራማ ስፍራዎች ጭምር ወደ 246 ኪ.ሜ.ወደ ኋላ በሚሞላ የውሃ ሀይቅ ተሞልተው ደሴት ይሆናሉ በግድቡ ምክንያት የሚፈጠረው ሰው ሰራሽ ሀይቅ ከፍተኛ የዓሳ ሀብት የሚመረትበት ከመሆኑ በተጨማሪ ለአካባቢው ስነምሀዳር ጠቀሜታ ያላቸው ሌሎች በየብስና ውሃ ነዋሪ የሆኑ እንስሳት እፅዋትና አእዋፍ መኖሪያም ይሆናል። እንዲሁም በመዝናኛነቱና ለሳይንሳዊ የምርምር ሥራ ከፍተኛ አገልግሎት እንደሚኖረው ይጠበቃል። በዚህም አካባቢው የቱሪስት መዳረሻ ሊሆን እንደሚችል ተረጋግጧል። ግድቡ ሲጠናቀቅ ከ6450 ሜጋዋት ከፍተኛ ኃይድሮ ኤሌክትሪክ ለማመንጨት የሚያስችለው ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም ደግሞ በተመሳሳይ መልኩ ከተገነቡት ፕሮጀክቶች መካከል ሰባተኛ እንደሚሆን ይገመታል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
493 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 262 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us