‘የማንነት ዜማ ቁጥር -፩’ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅትን በጨረፍታ

Wednesday, 12 April 2017 12:13


‘በተረፈ ወርቁ

 

እንደ መንደርደሪያ፡-


ባሳለፍነው ሳምንት ዕለተ ማክሰኞ ምሽት የምስክር ጌታነው ሚዲያና ፕሮሞሽን ድርጅት ከአሻም ሬዲዮ ዝግጅት ክፍል ጋር በመተባበር የማንነት ዜማ ቁጥር - ፩ የሚል በርካታ ታዳሚዎች የተገኙበት፣ የኢትዮጵያዊነት የረጅም ዘመን ታሪክ፣ ገናና ሥልጣኔ፣ አኩሪ ባህልና ታላቅ ማንነት የገነነበት ውብ ዝግጅት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ-ተውኔት/ትያትር ኣዳራሽ አቅርቦ ነበር።


ይህ የኢትዮጵያዊ ባህላዊ መሣሪያዎችና አጨዋወት (በእርግጥ እዚህ ላይ በመድረኩ የቀረቡት ባህላዊ ሙዚቃ መሳሪያዎች ለአብነትም፡- እነ በገና፣ ማሲንቆ፣ ዋሽንት፣ መለከትና ክራር ውሱንና ምናልባትም ደግሞ ከፊል ኢትዮጵያን በአብዛኛው ደግሞ ሰሜናዊውንና መካከለኛውን ኢትዮጵያን የሚወክሉ ናቸው ማለት ይቻላል የሚቻል ቢሆንም ቅሉ)፤ ጥሩና ሊበረታታ የሚገባው መልካም ጅማሬ መሆኑን ግን በደማቁ ላሰምርበት እወዳለኹ።


‹የማንነት ዜማ› ዝግጅት ባልደረቦች በዚህ የመጀመሪያ የተሳካ ዝግጅታቸው ያደረጉትን ጥረታቸውንና እንዲሁም ይህ ዝግጅት የተሳካ እንዲሆን አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ በማድረግ ሀገራዊ ግዴታውን እየተወጣ ያለውን ‹የአቢሲኒያ ባንክን› እጅጉን እያደነቅኩ ለወደፊቱም ይህ ‹የማንነት ዜማ› ዝግጅት - ወደ ደቡብ፣ ምዕራብና ምሥራቅ ኢትዮጵያ ተጉዞ፣ ዘልቆ ለሕዝብ/ለአደባባይ ያልበቁ፣ እምብዛም የማናውቃቸውንና የማንነታችን አሻራ መገለጫ የኾኑ የባህል መሣሪያዎቻችን የሚተዋወቁበትን መድረክ እንዲያስቡበት እግር መንገዴን አስተያየቴን ለመለገስ እወዳለኹ።


በዚህ ‹የማንነት ዜማ› ዝግጅት ላይ ወጣቱ የሙዚቃ ተመራማሪ ሠርፀ ፍሬ ስብሐት ባቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ ላይም እንደጠቀሰው፤ ‹‹የደራሼ ሕዝቦች የትንፋሽ መሳሪያ ዓለም በ፳ኛው መቶ ክ/ዘመን የደረሱበትን፣ ያጠኑትንና ለዓለም ያስተዋወቁትን የሙዚቃ ስልት ደራሼዎች ከረጅም፣ በርካታ ዓመታት በፊት ይጠቀሙበት እንደነበር አንስቷል።›› ይህ በሙዚቃው ሳይንስ ዓለም ኢትዮጵያውያንን የሙዚቃ ስልት በሚገባ እንዲጠና፣ ተገቢው እውቅና እና ክብር እንዲያገኝ በማድረግ ረገድ የራሱ የሆነ ድርሻና ጠቀሜታ ሊኖረው እንደሚችል አያጠራጥርም።


ለአብነትም ከሺሕ ዘመናት በፊት ዓለም ስለ ሙዚቃ ሳይንስ ገና ማውራት ባልጀመረበት የጥንት ዘመን ኢትዮጵያዊው ማሕሌታይ ቅዱስ ያሬድ የተለያዩ የዜማ ስልቶችን በመድረስ፣ ለዜማዎቹ ምልክት/ኖታ በማዘጋጀት ግንባር ቀደም ቢሆንም በዓለማችን በሚታወቁ ስማቸው በገነነ በሙዚቃው ደራሲዎችና አቀንባሪዎች ስም ዝርዝር ውስጥ ስሙ እንደሌለ በቁጭት አንስቷል ሠርፀ።


በእርግጥም ለራሳችን ታሪክ ባዕድ፣ ለባህላችንና ለቅርሳችን እምብዛም ዋጋ የማንሰጠና የውጩን/የምዕራቡን ዓለም አብዝተን ለምናማትር ለእኛ - እንደ ቅዱስ ያሬድና በሌላውም መስክ ያሉ ባለታሪኮቻችንን፣ ጀግኖቻችንን ሌላው ዓለም በክብር ተቀብሎ ዋጋ ይሰጠዋል ብሎ ማሰብ የዋህንት ነው የሚኾነው። ለምን ሲባል ‹‹ባለቤቱ የናቀውን አሞሌ ባለእዳ አይቀበለውም!›› ነውና። ሰርፀ የአዲስ አበባው ዩኒቨርሲቲ ቅዱስ ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ተገንብቶ በተመረቀበት ጊዜ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ያደረጉትን ታሪካዊ ንግግራቸውን በመጥቀስ፡-


‹‹… ይህ ትምህርት ቤት የራሳችንን የባህል የሙዚቃ መሳሪያዎችና ዜማ ስልቶች በሚገባ የሚጠናበት ተቋም እንዲሆነን ነው ያስገነባነው …።›› የሚለውን ንግግራቸውን በማስታወስ ይህ በቅዱስ ያሬድ ስም የተቋቋመው አንድ ለእናቱ የኾነው የሙዚቃ ትምህርት ቤት ስለ ቅዱስ ያሬድ ታሪክና ዜማዎች የሚሰጠው ኮርስ ለአንድ ሴሚስተር ብቻ የተወሰነ መኾኑንና ለሀገራዊ ዜማ መሳሪያዎች ይልቅ ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ለምዕራባዊው የሙዚቃ መሳሪያዎችና ስልት መኾኑን በቁጭት አንስቷል።


የባህል/ሀገሪኛ የሙዚቃ መሳሪያዎችን ለብሔራዊ ማንነት ግንባታ ያላቸው ፋይዳ:-


በሀገረ ጀርመን ማርቲን ሉተር ዩኒቨርሲቲ የሙዚቃ አጥኚና ተመራማሪዋ ዶ/ር ትምክህት ተፈራ፣ ‹‹The Role of Traditional Music among East African Societies: The Case of Selected Aerophones›› በሚል አርዕስት ባስነበቡት የጥናት ጽሑፋቸው፤ ‹‹ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያዎች በማንኛውም ኅብረተሰብ መካከል የእርስ በርስ ትስስርን፣ አንድነትን በማጠናከር፣ እንዲሁም በዕለት ተዕለት ማኅበራዊ ግንኙነቶችና መስተጋብሮች- በኀዘንና በደስታ፣ በሠርግና በሞት፣ በባህላዊና በሃይማኖታዊ ክዋኔዎች፣ ግዛትን ሀገርን ከወረራሪ ለመከላከል በሚደረጉ በዘመቻና በጦርነት ወቅት ያላቸውን ፋይዳ ከፍተኛ መኾኑን …›› በበርካታ ምሳሌዎች አስደግፈው አብራርተው ይገልጹታል።


እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የበርካታ ሕዝቦች፣ ብሔር ብሔረሰቦች የሚኖሩባት ሀገር ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያዎቻችንና ጨዋታዎች - ለኢትዮጵያዊ ማንነት ኅብረ ቀለማትን ያጎናጸፉ፣ ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለነጻነት ተጋድሎአችንና ለጀግንነት ታሪካችን ልዩ ውበትን ያላበሱ፣ ድርና ማግ ኾነው በጥበብ ያስዋቡን፣ የእኛነታችን አሻራ መገለጫዎቻችን፣ ሕያው ቅርሶቻችን ናቸው። በእርግጥም የኢትዮጵያ ባህላዊ መሳሪያዎች የሙዚቃ አጨዋወት ስልት በጨረፍታና በጨለፍታ የታየበት የብሔራዊ ትያትር ‹የማንነት ዜማ ቁጥር- ፩› ዝግጅት ባህላዊ መሣሪያዎቻችንና የሙዚቃ ስልቶቻችን ከማንነታችን፣ ከታሪካችን፣ ከባህላችን ጋር ያላቸውን ተዛምዶና ጥብቅ ቁርኝት ለማሳየት የሞከረ ነው።


በዚህ ደማቅ ዝግጅት ላይ የኢትዮጵያ ቤ/ክ ታሪክና ቅርስ ተመራማሪ፣ ደራሲና ጦማሪ (Blogger) ዲ/ን ዳንኤል ክብረት ባቀረበው ንግግር፣ የማንነታችንና የአንድነታችን ኅብረ ቀለማት መገለጫ የኾኑት ቋንቋዎቻችን፣ የሙዚቃ መሳሪያዎቻችንና ስልቶቻችን፣ ታሪኮቻችን፣ ቅርሶቻችን ዛሬ ዛሬ ‹‹የእኛና የእናንተ›› የሚል የልዩነት ግምብን የገነባንባቸው፣ የልዩነት መስመር ያሰመርንባቸውና የፍርሃትና የጥላቻ ዘር የዘራንባቸው አደገኛ ማሳዎች ኾነውብናል በማለት ነበር የገለጸው። በእርግጥም ልዩነታችን የውበታችን መገለጫ፣ የአንድነታችን ውብ ኅብረ-ቀለማት አድርገን ከመውሰድ ይልቅ ማለቂያ የሌለው በሚመስል ሙግት ... ያለፈው ታሪካችን ላይ ተቸክለን ወደፊት የመራመዱ ነገር ለብዙዎቻችን ጭንቅ ሆኖብናል።


‹‹ታሪክ የኅብረተሰብ የዕድገት መሠረት ቁልፍ ነው።›› ‹‹ታሪክ የትውልድ መሸጋገሪያ ድልድይ ነው።›› የሚለው አባባል ለአብዛኞቻችን የሚሠራ እውነታ አይመስልም፤ እናም ውርክቡ፣ ንትርኩ ቀጥሏል። የትናንትና ታሪካችን ወዲያና ወዲህ እንዳንል እግረ ሙቅ የገባንበት፣ ራሳችንን የቆለፍንበት ያሰርንበት ወኅኒ እየሆነብን ነው። ይህን በበርካታ ምሳሌዎች ማስረዳት ይቻላል። ለአብነትም ባሳለፍነው ሰሞን ያከበረነው የዓድዋ ድል በተመለከተ በተለያዩ ድረ ገጾች፣ በማህበራዊ/በሶሻል ሚዲያው ‹‹ጦር አወርድ›› ያሉ የሚመስሉ ታሪካችንን ማዕከል ያደረጉ ውርክቦች፣ ንትርኮች፣ እሰጥ አገባዎችን ... እያዘንን፣ እየተሳቀቅንና እረ ለመሆኑ ወዴት እየሔድን ነው በሚል ፍርሃትና ሥጋት ዐይተናል፣ ሰምተናል።


እንዲህ ዓይነቶቹን በመካከላችን ጥላቻን፣ በቀልን፣ ሥጋትን የሚዘሩ እኩይ የክፋት ዘሮችን ለማምከን ከመንግሥት፣ ከሃይማኖት አባቶችና መሪዎች፣ ከምሁራን ባሻገርም የጥበብ ዝግጅቶች፣ የጥበብ ሰዎች ትልቅ አቅም እንዳላቸው አያጠራጥርም። ባሳለፍነው ማክሰኞ ምሽት በብሔራዊ ቤተ ተውኔት አዳራሽ ‹የማንነት ዜማ ቁጥር- ፩› በሚል የቀረበው የባህላዊ ሙዚቃ መሳሪያዎችን የአጨዋወት ስልቶች ትዕይንትና የጥናት መድረክም እርስ በርሳችን በሚገባ እንድንተዋወቅ፣ በፍቅርና በቅንነት መንፈስ፣ በአድናቆት እንድንተያይ መንገድን የሚያመቻችና ልዩነቶቻችን የውበታችን መገለጫ አሻራ መኾናቸውን የምናይበት መልካም አጋጣሚን የፈጠረ ዝግጅት ነው ማለት ይቻላል።

 

እንደ መውጫ- ማጠቃለያ፡-
ኪነ ጥበብ በአንድ አገር ሕዝቦች ታሪክ፣ ቅርስና ማንነት እንዲሁም በፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችና በሰው ልጆች የዕለት ተዕለት ማኅበራዊ ግንኙነቶች ላይ ያለው ጉልህ አስተዋፅኦና ድርሻ ከፍተኛ እንደሆነ ግልፅ ነው። የኦክስፎርዱ የኢኮኖሚክስ ምሁር፣ ሐያሲና የሥነ ጽሑፍ ሰው ጋሽ አስፋው ዳምጤ ‹‹ፎረም ፎር ሶሻል ስቴዲስ›› ለሁለት ዓመታት በተከታታይ ባደረገው ‹‹ልማትና ባህል በኢትዮጵያ›› በሚለው የውይይት መድረክ ላይ ‹‹ሥነ ጥበብና ልማት›› በሚል ባቀረቡት የጥናት ጽሑፋቸው፡-


‹‹… ሰው በተፈጥሮው ከአራዊት ወይም ከእንሰሳት የሚዛመድባቸውን ባሕርያት መሞረድ፣ ማለዘብ፣ እና የሰብአዊነት ባሕርያቱን ማጎልበት፣ ብሎም የማኅበራዊ ሕይወት ንቃቱን ከፍ በማድረግ፣ በጎና ሁለተናዊ ለሆኑ የልማት የጋራ ግቦች ለመነሳሳት ምቹ የሚያደርገው የአስተሳሰብ ዝንባሌ እና አመለካከት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የጥበብ ዘርፎች ሁሉ ዓላማና ግብ ነው።›› በማለት ኪነ ጥበብ በሰው ልጆች ማኅበራዊ መስተጋብር ውስጥ ያለውን ሁለተናዊ ፋይዳ እንዲህ ገልጸውታል።


በኪነ ጥበብ ዘርፍ ውስጥ ከሚካተቱትና ከፍጥረት ወይም ከሰው ልጆች ታሪክ ጅማሬ ዘመን ጋር አቻ ሊባል በሚችል በጥንታዊነቱ የሚነሳው ሙዚቃ በሰው ልጆች ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሕይወት ውስጥ ትልቅ አሻራ እንዳለው ብዙዎች የዘርፉ ምሁራን ይስማሙበታል። እናም ከዚህ እውነታ ጋር በተያያዘም ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያዎቻችንና ዜማዎቻችን ለብሔራዊ ማንነታችን፣ አንድነታችን፣ ኩራታችን ያላቸው ድርሻ ጉልህ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።


በአሜሪካ የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ምሁር የኾነው ሴሲሊ ሞሪሰን፣ the Role of Folk Song in Identity Process በሚል ርዕስ ባስነበበው ጥናታዊ ጽሑፉ፡-
‹‹Folk music, from the birth of the idea of the nation state, has been one means of expressive culture used to generate, define, and reinforce national identity ...›› ለብሔራዊ ማንንትና አንድንት ግንባታ ባህላዊ ሙዚቃ ያላቸው ፋይዳ ከፍ ያለ ነው። ስለሆነም ‹የማንነት ዜማ› አዘጋጆች የኢትዮጵያዊነት የረጅም ዘመናት ታሪካችን፣ ማንነታችን፣ የነጻነታችን አኩሪ ተጋድሎ፣ ሕያው ቅርሶቻችን፣ ባህላችን፣ ብሔራዊ አንድነታችንና ውበታችን … ወዘተ ጎልተው የሚታይባቸውን እንዲህ ዓይነቶቹን የኪነ ጥበብ ዝግጅቶችን በስፋት እንዲቀጥሉበትና እንዲሁም መንግሥት፣ የባህል ተቋማቶቻችን፣ የመገናኛ ብዙኃኖቻችን የጀመሩትን ሥራ አጠናክረው በመቀጠል፣ በማበረታታት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ እግረ መንገዴን በማስታወስ ልሰናበት።
ሰላም!!¾

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
447 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 261 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us