ከ“የሆድ በዓል”ነት ባሻገር

Wednesday, 19 April 2017 12:37

 

በእስክንድር መርሐጽድቅ

 

የሸገሯ መዓዛ ብሩ በ‹‹የጨዋታ እንግዳ›› ፕሮግራሟ ከቀድሞው የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ጋር ቆይታ ባደረገችበት አንድ ቅዳሜ፤ ስለ ዓመት በዓላት የእረፍት ቀናት የነገሯት ዓውድ ዓመት በመጣ ቁጥር ይታወሰኛል።


በኢትዮጵያ በሃይማኖት በዓልነታቸው ሥራ የሚዘጋባቸው፤ የእስልምና እና የክርስትና ሃይማኖቶች በዓላት ናቸው። እነዚህ በዓላት በሚዛናዊነት ሥራ ተዘግቶባቸው መከበር የጀመሩት በደርግ ዘመን ነው። ከዚያ በፊት ግን ለእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች በዓላት፤ ሥራም፣ ትምህርትም ሳይዘጋ ተከታዮቹ እንዲቀሩ ይደረግ እንደነበር መናገራቸው ትዝ ይለኛል፤ በዘመኑ የነበሩ የሃይማኖቱ ተከታይ ወዳጆቼም ይህንኑ ነግረውኛል።


ደርግ ይህን ለመጀመር ኮሚቴ አቋቁሞ ቀኖቹን በአዋጅ እንዲዘጉ ከማድረጉ በፊት እረፍትነታቸው ሊቀነስ ወይም ሊቀር ጥናት ከተደረገባቸው መካከል በክርስትና በዓላት ሥራ ከሚዘጋባቸው ቀናት ‹‹አላስፈላጊ›› ተብለው የታዩትን ለማስቀረት ነው። ከነዚህ አንዱ ከትንሳዔ (ከፋሲካ) ቀጥሎ ያለው ቀን (ሰኞ) ‹‹ማዕዶት›› በመባል የሚታወቀው ነው። እናም ቀኑ ለምን ሥራ እንደሚዘጋበት እንዲጠይቅ የነመቶ አለቃ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ኮሚቴ ወደ ጠቅላይ ቤተክህነት ሊቃውንት ተላከ። ሊቃውንቱ ለኮሚቴው ከሰጡት ሃይማኖታዊ ትንታኔ ባሻገር ‹‹ዕለቱ ሊዘጋበት የቻለው ‹ሁለት ወራት የፆመ ሆድ ዕሁድ ገድፎ ለሰኞ እንቅስቃሴ ስለሚከብደው ነው› አሉ›› ነው የተባለው።


ሳንወሻሽ ወይም አስመሳይ ሆነን፣ ‹‹ይኼ ሥራ ከማይወዱ ሰዎች የመነጨ አስተሳሰብ ነው›› ሳንል በነጻ ህሊና ካሰብነው እንዲሁም ከምናየው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር አይደለም በትንሳዔ፤ ሁሉም በሚያከብረው ዘመን መለወጫን ጨምሮ በየትኞቹም የሃይማኖት በዓላት ማግስት ሥራ የሚገባው ወይም ገብቶ በመረጋጋት የሚሰራው ምን ያህሉ ነው?
በኛ ሀገር ዘመድ ከዘመዱ ርቆም ሆነ በቅርብ የሚጠያየቀው በአብዛኛው በበዓላት ቀን ነው። በነዚህ ቀናት ደግሞ የመጓጓዣ እጥረት በከፍተኛ ሁኔታ ስለሚከሰት ሰው ረጅም መንገድ በእግሩ ተጉዞ ወይም ለሰዓታት ቆሞ ነው በግፊያ የሚሳፈረው። ከዚያም ቤቱ የሚገባው ወላልቆ (ደካክሞ)ና ለእኩለ-ሌሊት ተቃርቦ ነው። እንዲህ የደከመውን ሰውና ሰውነት ነው እንግዲህ ማለዳ ተነስቶ ሥራው እንዲገባ የምንፈርድበት።


ከቤት ውጪ በመከበር ከሚታወቁት በዓላት ጥምቀት ዋነኛው ነው። ታቦታት ከመንበራቸው ወጥተው ካደሩበት ጥምቀተ-ባህር እስኪመለሱ 10 እና 11 ሰዓት ይሆናል። በርግጥ ደመራም ቢኖርም በነጋታው በመስቀል በዓል ምክንያት ሥራ ስለማይኖር መነጋገሪያችን አይደለም። በእስልምና ደግሞ ኢድ አል አድሀ (ዓረፋ) እና ኢድ አል ፈጢር (ረመዳን) ስቴዲየም ወይም መስጊድ ተከብረው ወደ ቤት መልስ ሲሆን በከፍተኛ ድምቀት በየጎዳናዎች ልዩ ልዩ የሃይማኖቱ ስርዓቶች ይካሄዳሉ። በነዚህ ሥርዓቶች የተዳከመ ሰውነት ቤቱ ሲገባ ደግሞ የሚጠብቁት ሰውነትን የባሰ የሚያደክሙ ቅባት የበዛባቸው ምግቦች ናቸው። ከዚህ ቀጥሎ ባለው ቀን ነው እንግዲህ ሰዉ ‹‹ሥራ ግባ›› የሚባለው።


ይህን ለመጻፍ ስዘጋጅ የኛን እና ሌላ አንድ ቢሮ ተመለከትሁ። እኛ ክፍል 34 ሠራተኞች የምንገን ሲሆን ሥራ ላይ የተገኙት 13ቱ ብቻ ናቸው። ከ13ቱ በሥራ መግቢያ ሰዓት የገቡት ከአምስት አይበልጡም። ከዚችው ውስጥ ትንሽ ቆይተው ወይም ከሰዓት በኋላ በማስፈቀድ የተመለሱም አሉ። በሌላኛው ቢሮ ከሚገኙት ከ50 በላይ ሠራተኞች ደግሞ ሥራ ገበታቸው ላይ የተገኙት 10 አይሞሉም። ከነዚህ ውስጥ ደግሞ በዓሉ የማይመለከታቸው እንዳሉ በመረዳት የሚመለከታቸው ደግሞ ምን እየሰሩ እንደሚውሉ መገንዘብ አያዳግትም። ቀልብን ቤት ከመላክ አንስቶ ስልክ ላይ ተጠምዶ የበዓሉ ዕለት የመልካም ምኞት ያልተደረገላቸው እየተፈለጉ፣ ‹‹እንኳን አደረሳችሁ!›› በማለትም ጊዜው ያልፋል።


ምናልባት ‹‹አስፈቅዶ መቅረት ይቻላል›› የሚል ካለ ከአጠቃላይ ሠራተኞች ከሁለት ሦስተኛ በላዩ ሲቀር ደንበኛ መስተንግዶ ላይ ችግር አለው። ለነገሩ ደንበኛውስ በነዚህ ቀናት መች ከቤቱ ይወጣና? ከእኔ ባሻገር እናንተም ምስክር ልትሆኑ የምትችሉት በሌሎች የሥራ ቀናት ሠራተኛው እንደዚያ ከተማዋን በታክሲና በአውቶቡስ ጥበቃ ሰልፍ እንዳላጨናነቃት ጭልጥ ብሎ በየቤቱ ስለተከተተ ትራንስፖርት ሰጪዎቹ አፋቸውን ከፍተው መዋላቸውን ነው። ሌላው ቢቀር ለመንግሥት ሠራተኞች ተመድበው እንደ ከተማ አውቶቡስ ጢም አድርገው በመጫን የሚታወቁት የፐብሊክ ሰርቪስ አውቶቡሶች ወንበሮቻቸው ለመኝታም እስኪበቁ ባዶ ሆነው ቀፏቸውን ሲከንፉ ተመልክተናል። ስለዚህ እነኚህን ቀናት አለመዝጋቱ የነዳጅ ብክነትን ጨምሮ በሌሎችም ውጤት የለሽ ወጪዎች ምክንያት ለመ/ቤቱ ራሱ ኪሳራ ነው።


‹‹እነዚህን ቀናት ከሥራ በማቀብ እረፍት መስጠት የሀገር ኢኮኖሚን ይጎዳል›› የሚል ብቻ ጭፍን አመለካከት የለኝም። መፍትሔው በአንዳንድ መ/ቤቶች በተለይም በልማት ድርጅቶች ውስጥ እየተሠራ ባለው መንገድ መሆን ይችላል። ድርጅቶቹ በበዓላት ማግስት ይዘጉና ማካካሻውን ቅዳሜ አስገብተው ያሰራሉ። ይህ በግዳጅ ሳይሆን በስምምነት የተደረገ ነው። ነገር ግን በዓላቱ ዐርብ ወይም ቅዳሜ ከዋሉ ወይም ከዚያ ቀጥሎ ያለው ቀን ሜይዴይ ወይም የድል በዓል ከሆነ ቅዳሜ፣ ዕሁድና በዓላቱ የዕረፍት ቀናት ናቸውና እረፍቱ ማካካሻ ሳያስፈልገው በዚያ ይታያል። ቅዳሜ ግማሽ ቀን በሚሰራባቸው መ/ቤቶች ጨምሮ ችግር ያለው ከዕሁድ እስከ ሐሙስ በሚከበሩ በዓላት ላይ ነው።


እነዚህ ቀናት ለሥራ ከሚከብዳቸው ሰራተኞች ባሻገር ሠርግና ምላሻቸው የሚሆንላቸው ተበቃይ ሰዎች ደግሞ አሉ። ድሮ ተማሪ ሳለን ለሃይማኖት ግድ የለሽ የሆኑ ወይም ጥላቻ ያላቸው መምህራን ፈተና የሚፈትኑት በበዓላቱ ማግስት እንደነበር እናስታውሳለን። ለነገሩ ዛሬም ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ሳይቀር ይህ ክፋት (አባዜ) የተጣባቸው አሉ። የእንዲህ አይነቶቹ ምክንያት ፈላጊዎች በየመ/ቤቶችም ቀናቱን ለቂማቸው መበቀያም ይጠቀሙባቸዋል። ስለዚህ በበዓላት ማግስት ደክሞት ብቻ ሳይሆን አደጋ ደርሶበት የቀረን ሳይቀር ከቀበሌ ጭምር ማስረጃ እንዲያመጣ የሚያደርጉ ናቸው።


ከእንደነዚህ አይነቶቹ አንዱን ደብዳቤ ለአብነት ከዚህ ጽሑፍ ጋር አያይዣለሁ። ደብዳቤው የተጻፈለት ሰው በግቢው ውስጥ የሚያልፈውና የርሱን ጨምሮ የሰፈሩ ቤቶች ኤሌክትሪክ የሚያገኙበት መስመር የትንሳኤ ሌሊት ነዶ በተለይ እሱና ቤተሰቡ የተረፉበትን አደጋ በመንተራስ በነጋታው ስብሰባና መስመር ቁጥጥር ላይ በመቆየቱ ነው። ይህን ክስተት ግራና ቀኙን ከማመዛዘን ይልቅ እንደ መምህራኑ አጋጣሚዎችን ለመበቀያነት ለመጠቀም ለሚተጋው ኃላፊው ("አለቃው") ደውሎ ለማሳወቅ ቢጥርም ሊያነሳለት አልፈለገም። በሌላ ሰው በኩል ሲነገረው ግን፣ "በማህተም የተደገፈ ማስረጃ አምጣ በሉት" ነበር መልሱ። ማስረጃም ሳይጠየቅበት በመተማመንና በመግባባት የፈቃድ ቅጽ ተሞልቶ መታለፍ የነበረበት ክስተት ነው እንግዲህ ማስረጃ ተጠያቂው ባያመጣ ኖሮ የበቀል በትር ሊያርፍበት የነበረው።


ስለዚህ መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ከነዚህ ቀናት ማግስት በብዛት ሳይገባ ወይም በድኑ ብቻ ገብቶ ልቡ ቤቱ ባለ ሠራተኛ ምክንያት የሚደርሰውን ቀውስ ለማስቀረት በቅንነት በማካካሻ ቢያስኬዱት መልካም ነው። ይህን ማድረግ ከሥራው በአንድ ልብ መሠራት ባሻገር ሠው ሥራውን እየወደደው እንዲሠራው ያስችላል። በርግጥ እንዲህ ቢደረግ ደግሞ ተከታዩን ቀን ለመሥራት የሚያንገራግር ቢኖርም ቁጥሩ ግን በጣም የወረደ ነው ሊሆን የሚችለው።


የማጠቃልለው አደራን በማከል ነው። ይህን አቋም ሳንጸባርቅ ሥራን በመጥላት አይደለም። በዚህ በኩል ከሥራ ላይ በየሰበቡ እንደማልቀር ከራሴ ባሻገር የሚያውቁኝ ምስክሮቼ ናቸውና!
* ይህን ሐሳብ ከደብዳቤ ጋር ለኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እና ለሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር በአድራሻቸው አስገብቻለሁ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
322 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 185 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us