“እመጓ”ን ከማጠልሸት እራስን መሻት

Wednesday, 19 April 2017 12:57

 

ከአሰበ ገ/ማርያም

 

“እመጓ” የሚለው የቦታ ስም ለብዙዎች ያልተለመደ እንደሚሆን እገምታለሁ። እኔ ግን በልጅነት ስሰማው እንደነበር በማስታወስ ቀልቤን ስቦት “እመጓ”ን ገዝቼ ገልበጥበጥ አድርጌ መጽሐፉን ሳነበው ተአምር በሚያሰኝ ለዛና ዘዬ እያዋዛና እያጓጓ “መንዝ”ን እንደ አጉሊ መነፅር ቁልጭ አድርጐ በማሳየት በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተ ታሪካዊ ልቦለድ ድንቅ የምርምር ስራ ውጤት ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

 

ለዚህም ለዶ/ር ዓለማየሁ ዋሴ እሸቴ የ“እመጓ” መጽሐፍ ደራሲ ያለኝን ታላቅ አክብሮትና ምስጋና አቀርባለሁ። ተወዳጁ የ“እመጓ መጽሐፍ መታተም ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በተደጋጋሚ በመታተም በመጽሐፍ ሽያጭ በመጀመሪያው ረድፍ እየመራ ይገኛል።

 

በዚህ የምርምር ስራው የተለየ የአፃፃፍ ስልት ይዞ በመምጣት ደራሲውን እፁብ ድንቅ እንዲሆን አድርጐታል። “የታላቁን መምህር አባ አክሊሉን ታሪክና የዘብር ቅዱስ ገብርኤልን ተአምር” ፀሐፊ ነኝ ባዩ አቶ ማሙሽ ባደግ በ2008 ዓ.ም አሳተምኩት ባለው መጽሐፉ መነሻና መድረሻው ያደረገው በ“እመጓ” መጽሐፍ ደራሲ በዶ/ር ዓለማየሁ ዋሴ እሸቴ ላይ በድፍረት የሰነዘረው ፀያፍ ስድብና ዘለፋ ነው። ከስንዴ መካከል እንክርዳድ እንደሚበቅል ሁሉ፤ የኔታ አክሊሉን ታሪክና የዘብር ቅ/ገብርኤልን ተአምር ፃፍኩ የሚል ሰው ከግምት በታች የሆነ ሃሳብ ይዞ መነሳቱ እጅግ የሚያሳዝንና የሚያሳፍር ነው።

 

የ“እመጓ” መጽሐፍ ሽያጭ ለ7 የመንዝ አብያተክርስቲያናት በማኅበረ ቅዱሳን እየታተመ ገንዘቡ እንዲሰጥ በማድረግ ታላቅ የገቢ ምንጭ ስጦታ አበርክቷል። ዶ/ር ዓለማየሁ ሃይማኖታዊ መለኮታዊ ኃይልና - ሳይንሳዊ ምርምር የሥነ-ምህዳር ውጤት ድንቅ ሥራ አክብሮትና ምስጋና ቢቸረው እንጂ ሊያሰድበውና ሊያዘልፈው የሚገባ ባለመሆኑ የታሪክና ተአምር ፀሐፊውን ጽሑፍ አንብቤ ከዝምታ ይልቅ አስተያየቴን ልሰነዝር ተገድጃለሁ። ታሪክና ተአምር ፀሐፊው አሳተምኩት ባለው መጽሐፉ ስሙን እንጂ አድራሻውን ባለመግለፁ፣ የምለውን እንዳልል አድርጐኛል።

 

ይሁንና የሱ ዘለፋና ስድብ የ“እመጓ”ን መጽሐፍ ደራሲ ዶ/ር ዓለማየሁ ዋሴ እሸቴን ክብርና ዝና ዝቅ ያደርገዋል ወይም ያጠለሸዋል የሚል ግምት ኖሮኝ ሳይሆን፤ ሃይማኖታዊ እንደምታ ስላለው ብዙዎችን ሊያሳስት የሚችል ሆኖ ስለተሰማኝ ነው።

 

ይህ ታሪክና ተአምር ፃፍኩ የሚለው ተበለጥኩና ተቀደምኩ በሚል ሰይጣናዊ ቅናት ብዙ እንዲሳደብ እንዳደረገው መገመት ይቻላል። ለዚህ ማረጋገጫው “ዶ/ር ነኝ ባዩ መንፈሳዊ መስሎ ሰዎችን በማሳመን ገንዘብ ለመሰብሰብ ተሳክቶለታል” የሚለው አባባሉ ነው። በመቀጠልም በቁጭት መልክ “የእውነተኛ አባቶች ታሪክ እንደዚህ ባሉ አስመሳዮች ሊበረዝ አይገባም” ይልና፤ “… በይሆናል አፃፃፍ የቃላትን አገባብን አሳምሮ በመፃፍ እንዲሁም ሳምን ዶክተር ነኝ ብሎ ለመታመን መሞከርና…. እውነተኛውን ታሪክ አለመግለጽ ስማቸውን ከነጭራሹ ማጥፋት ከሐዲነት ነው በማለት የ“እመጓ” ፀሐፊ እራሱን ይመርምር ሲል ዘለፋውን ገልጿል።

 

ይህ ነው እንግዲህ ባልተሟሸ ብዕሩ የእመጓን መጽሐፍ ደራሲ - ዶ/ር ዓለማየሁ ዋሴ እሸቴን ድንቅ የምርምር ሥነ-ጽሑፍ ያለሀፍረት በድፍረት ለመንቀፍና ለመዝለፍ የቃጣው። ይህ ብቻም አይደለም የታሪክና ተአምር ፀሐፊው የመንዝን ታላቅ ሕዝብና ካህናት ያለ ሐፍረት እንዲህ ሲል ዘልፏል። “መንዝ አባ አክሊሉ ከመምጣታቸው በፊት ሰባክያነ ወንጌል በጭራሽ አልነበረም። ካህናቶቹም ቢሆኑ ከአያት አባቶቻቸው አካሄድ የሰሙትን ማስተላለፍ እንጂ ጠለቅ ብሎ የተማረ ኃይል አልነበረም። የአያት አባቶችን አካሄድ/ባህል ለመቀየር የፈለገው መምህር ነኝ ባይ ቢመጣ በቀላሉ የሚሰጠውን ትምህርት ለመቀበል ፈቃደኛ አይደለም። ስለሆነም የመንዝ ሕዝብና ካህናት የዘልማድ አሰራር ያጠቃቸዋል። ወይም ያጠቃቸው ነበር” ሲል ታላቁን የመንዝን ሕዝበ-ክርስቲያንና ካህናት በድፍረት ዘልፏል። በታላቅ ተጋድሎ የመንዝ ሕዝብና ካህናት ኦርቶዶክሳዊ ሃይማኖታቸውን ትውፊታቸውን ጠብቀው የኖሩትን እንደ-ኢ-አማኒ በመቁጠር የዘልማድ በማለት አጣጥሏል።

 

የኔታ አክሊሉን ለመግለፅ የመንዝን ሕዝበ ክርስቲያንና ካህናት መዝለፍ ተገቢ ነው አልልም። የኔታ አክሊሉን /ዕፁብ/ ከ300-400 የሚደርሱ ተማሪዎቻቸውን “ምንተስማለማርያም” ሲሉ ሰንቆ ሰጥቶ ያስተማረን ሕዝብ -ኢ-አማኒ ነው ማለት መናፍቅነት ነው። ታላቁን - የአክሱምን - ሥርወ መንግሥት ጥላ - አክሱምና አካባቢዋን ታቦተ ጽዮንን ያቃጠለችውን ዮዲት ጉዲትን ሠራዊት እራሱንም ጭምር አሳፍሮ በመመለስ ቅርሱንና ንጉሱን ጠብቆ ያቆየ ባለውለታ ሕዝብ በአንድ ተራ ፀሐፊ ነኝ ባይ ቢዘለፍ ሊያስገርም አይችልም።

 

ወራሪ ጠላትን በተደጋጋሚ አሳፍሮ በመመለስ ለሀገሩና ለሃይማኖቱ ቀናኢ ታቦታቱንና መፃሕፍቱን፣ ቅርሱን በገደልና ዋሻ ሸሽጐ፣ ቅዱስ ፅዋውን በሚስጥር ጠብቆ ያኖረን ሕዝብ ከትውልድ ወደ ትውልድ ያስተላለፈን ታላቅ ሕዝብ መዝለፍ ኢ-አማኒነት ወይም በሌላ ተልዕኮ መገለፅ ነው።

 

የመንዝን ታላቅ ሕዝብና ካህናት የ“እመጓ”ን መጽሐፍ ደራሲ ዶ/ር ዓለማየሁ ዋሴ እሸቴን ያለ ሀፍረት በድፍረት የሰደበና የዘለፈ ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለውና በሕግ ሊጠየቅ ይገባል።

 

የ“እመጓ” ፀሐፊ ዶ/ር ዓለማየሁ ዋሴ እሸቴ በእውነተኛ ታሪካዊ ልቦለድ አፃፃፍ መብቱን ተጠቅሞ በመጽሐፉ ገጽ 90 የኔታ አክሊሉን ዕፁብ በማለት ስራቸውን /ግብራቸውን/ በማድነቅ “አካላቸው የኮሰሰ፣ አእምሮአቸው በዕውቀት የበለፀገ የእርሳቸው አስተምህሮ መማር ታላቅ ዩኒቨርስቲ በማለት ከገለፃቸው በኋላ - የኋሊት የመንዝ ትዝታውን ሲቃኝ የኔታ ዕፁብን እንዴት እረሳቸዋለሁ? ከ300-400 የቆሎ ተማሪዎች ጐጆአቸውን ቀይሰው ተምረው የሚያስተምሩ ለሀገራችን ትልቅ ተሞክሮ ያላቸው” ሲል ይገልፃቸዋል።

 

የ“እመጓ” መጽሐፍ ደራሲ ዶ/ር ዓለማየሁ እውነትን እንደዋዛ እያዋዛ በመድረክ የዘመናችን የክቡር ዶ/ር ሐዲስ ዓለማየሁ “የፍቅር እስከ መቃብርን” ያህል ጉልበት የፈጠረ ከንባብ የራቀውን ትውልድ በ“እመጓ” መጽሐፉ ትርክት ጠርንፎ የንባብ ፍቅር በማስያዝ ትልቅ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆኖ አግኝቸዋለሁ።

 

በታህሳስ 30 ቀን 2009 ዓ.ም በብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመፅሐፍት (ወመዘክር) በዲ/ን ዳንኤል ክብረት በ“እመጓ” መጽሐፍ ላይ ባደረገው ሰፊ ገለፃና ውይይት ከተሳተፊ ምስጋናና አክብሮት ተችሮታል። ዲ/ን ዳንኤልም “እመጓ”ን በዳሰሰበት ምናባዊ እይታው “መንፈሳዊውን መለኮታዊ ኃይልና በዕውቀት ያዳበረውን የሳይንስ የሥነ-ምህዳራዊ ሳይንስ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮችን እንድናይ ያደረገ ድንቅ ሥራ ነው” ሲል ገልጾታል።

 

“የጓሳ ፓርክን ሥነ ምህዳር የእንስሳቱንና የዕፅዋቱን የሕዝቡን መስተጋብር ከትውልድ ወደትውልድ እንዴት ተጠብቆ እንደኖረ፣ ለአካባቢው የውሃ ማማ ምንጭ መሆኑን ሙያዊ ክህሎቱን ተጠቅሞ ተንትኖ አሳይቶናል።”

 

ስለዚህ “እመጓን ከማጠልሸት እራስን መሻት” ተገቢ ነው። እያልኩ የ“እመጓ”ን ደራሲ ዶ/ር ዓለማየሁን በድጋሚ እያመሰገንኩ አስተያዬቴን እገታለሁ።¾

ይምረጡ
(4 ሰዎች መርጠዋል)
960 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 257 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us