ዝዋይ ሐይቅን ለመታደግ እነ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ምን መከሩ?

Wednesday, 03 May 2017 12:22

 

·        ሐይቁን ለመታደግ ለባለድርሻ አካላት ጥሪ ቀርቧል

 

የዝዋይ ሐይቅ በመሀል ስምጥ ሸለቆ ከሚገኙና ንፁህ ውሃ ካላቸው ትልልቅ ሐይቆች አንዱና ቀዳሚው ነው፤ 31 ኪሎ ሜትር (19 ማይልስ) ርዝመት ያለው ይሄው ሐይቅ 44 ኪሎ ሜትር ስኩየር (170 ስኩየር ማይልስ) ስፋትና 8 ነጥብ 9 ሜትር (29 ጫማ) ጥልቀት ያለው ሲሆን፤ እንደነዘቢዳር ካሉ የጉራጌ ከፍተኛ ቦታዎች እየፈሰሰ በሚመጣው የመቂ ወንዝና ከጭላሎ ተራራዎች እየተጓዘ በሚሄደው ከታር ወንዝ ይገብራል። ሐይቁ ለመስኖ፣ ለዓሣ ማጥመድና ለመዝናኛነት በመዋል ለበርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች የገቢ ምንጭ ከመሆኑም በላይ ለቱሪስት መስህብ በመሆን የውጭ ምንዛሬን በማስገኘትም የአገር አለኝታ የሆነ ትልቅና ታሪካዊ ሐይቅ ነው።

 

በዚህ ሐይቅ ላይ መኖሪያቸውን ያደረጉ የተለያዩ አይነት ያላቸው አዕዋፋትና በውስጡ ያሉ ብዝሃ ህይወቶች የሐይቁ መለያዎች መሆናቸውም የሚታወቅ ነው። እነዚህን ዘርፈ ብዙ ገፀ-በረከቶች በውስጡ የያዘው ሐይቁ በተለያዩ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ህልውናውን ሊያጣ ጫፍ ላይ መድረሱንና አፋጣኝ እርምጃ ተወስዶ መፍትሄ ካልመጣ ለከፍተኛ አደጋ እንደሚጋለጥ ባለፈው ሳምንት ወልቂጤና አርሲ ዩኒቨርስቲዎች በጋራ በመተባበር በዝዋይ ኃይሌ ሪዞርት ያዘጋጁት አገር አቀፍ ጉባዔ ላይ የቀረቡ ጥናቶች አመላካች ናቸው።

 

“National workshop participatory water shade management of Lake Ziway” በተሰኘው በዚህ አገር አቀፍ ወርክሾፕ ሐይቁ ምን ምን እክሎች እንደገጠሙት፣ ምን ቢደረግ ሐይቁን ከጥፋት እንታደገዋለን በሚሉት ጉዳዮች ዙሪያ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ፣ አርሲ ዩኒቨርሲቲና የስምጥ ሸለቆ ተፋሰስ ድርጅት የተባለው ተቋም ጥናታዊ ጽሁፎችን አቅርበው በርካታ ሀሳቦች ተንሸራሽረዋል።

 

በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አድማስ ብርሃኑ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የሐይቁ የውሃና የጥልቀት መጠን እየቀነሰ ቢሆንም ከዚህ በፊት ያልነበረ መጤ አረም የሐይቁን ዳርቻ ሙሉ ለሙሉ ወሮታል። ይህ አረም በዓለም አቀፍ ደረጃ ካለ ተሞክሮ በመነሳት ሐይቆችንና በውስጣቸው ያሉትን ብዝሀ ህይወቶች በማጥፋት ጥልቅ ጥፋት ሊያስከትል እንደሚችለም የአቶ አድማስ ብርሃኑ ጥናት ያመለክታል። አረሙ “እምቦጭ” ወይም በእንግሊዝኛው “Water hysin” የሚባል ሲሆን ይህ ክፉ አረም ከአሜሪካ አማዞን ጀምሮ በምስራቅ አፍሪካ በቪክቶሪያ ሐይቅ አቋርጦ ከቆቃ ጀምሮ እስከ ዝዋይ ሐይቅ በመስፋፋትና በቀላሉ በራባት የሐይቁን ውሃ ጨለማ በማልበስና ኦክስጅን እንዲያጥር በማድረግ ዓሣን ጨምሮ በሐይቁ ውስጥ ያሉ ብዝሃ ህየወቶች እንዲጠፉ እንደሚያደርግ ጥናታቸው አመልክቷል።

በአሁኑ ወቅት አረሙ የሐይቁን ዳርቻ ሙሉ ለሙሉ የወረረው መሆኑን በጥናታቸው ያመለከቱት አቶ አድማስ ብርሃኑ በዝምታ የምንቆይ ከሆነ ሐይቁን ሙሉ በሙሉ በመውረርና በምቾት በመንሰራፋት ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያደርስ አሳስበዋል።

 

በአርሲ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍና የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ኤፍሬም ተሰማ በበኩላቸው የህዝብ ቁጥር እየበዛ በመጣ ቁጥር የተፈጥሮ ሀብቶች እየተመናመኑ ደኖች እየተጨፈጨፉና በውስጡ ያሉ እንስሳት እየጠፉ የሚሄዱ መሆናቸውን አስታውሰው የጭላሎ ተራራ ለዚህ ችግር በመጋለጡ ለዝዋይ ሐይቅ ፈተና መሆኑን ያስረዳሉ። በቅርቡ የተመሰረተው አርሲ ዩኒቨርሲቲ በጭላሎ ተራራ ግርጌ እንደመቋቋሙና መስራቾቹም የአካባቢውን ስነ ምህዳር የሚያውቁ በመሆናቸው እየተመናመነ የመጣውን የተፈጥሮ ሀብት በመመልከት ከ2 ዓመት በፊት በዝዋይ ከተማ ባለድርሻ አካላትን በመሰብሰብ ውይይት ተደርጐ እንደነበር አቶ ኤፍሬም ያስታውሳሉ። “በዚህ ውይይት ዝዋይ ሐይቅንና ዙሪያውን ከጥፋት ለመታደግ ጥናት በማስፈለጉ የምርምርና ሕትመት ዳይሬክቶሬት ተቋቁሞ ፕሮጀክት ተቀረፀ” ይላሉ።

 

ጥናቱ ሲጀመር ጉዳዩን አርሲ ዩኒቨርሲቲ ብቻውን ለችግሩ መፍትሄ ማምጣት እንደማይችል በመታመኑ እንደነ ወልቂጤ ዩኒቨሲቲና የስምጥ ሸለቆ ተፋሰስ ድርጅት ካሉ ባለ ድርሻ አካላት ጋር ተባብሮ መፍትሄ ለማምጣት ይህ አገር አቀፍ ወርክሾፕ መዘጋጀቱንም አቶ ኤፍሬም አስታውሰዋል። እስካሁን በተደረጉት ጥናቶች የተገኙት ውጤቶች ሐይቁ ቀድሞ ከሚሸፍነው ቦታ መሸሹ የዓሣ ዝርያዎች መመናመን፣ ከፍተኛ የውሃ ብክለትና የጥልቀት መቀነስ በግልፅ ታይተዋል ያሉት አቶ ኤፍሬም ከውሃው ብክለት የተነሳ ጉማሬዎች ጤናማ ማንነታቸውን በማጣት ወደ ቤት እንስሳነት እየተቀየሩ ነው ካሉ በኋላ በተለይ በሐይቁ ምስራቃዊ ክፍል (በአሰላ) በኩል ያሉ ስድስት ተፋሰሶች የኢንተርቬንሽን ፕሮጀክት የተቀረፀላቸው መሆኑንና ይህንን ለመስራት 391 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ጥናቶች አመልክተዋል ብለዋል።

 

የወልቂጤ ዩኒቨርስቲው የጥናትና ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አድማስ ብርሃኑ በበኩላቸው ዩኒቨርስቲያቸው በስምንት የምርምር ዘርፎች የተዋቀረ 25 የጥናትና ምርምር ቡድን መኖሩን፣ እንደ ዝዋይ ሐይቅ ያሉ የተፈጥሮ ሐብቶችን ለመጠበቅ ስምንት ቅድመጥናቶች መስራታቸውን ገልፀው፤ እነዚህም ጥናቶች በውሃና በአፈር ጥበቃ፣ በእንስሳትና ዓሣ ሀብት፣ በሐይልና በምጣኔ ሀብት፣ ማኅበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት፣ በማኅበረሰብ አመለካከትና ግንዛቤ እንዲሁም በሕግ ማዕቀፍ ላይ ማተኮራቸውን ያብራራሉ። “የዝዋይን ሐይቅ ለመታደግ ከላይ የተዘረዘሩት ስምንት ቅድመ ጥናቶችም የግድ አስፈላጊ ናቸው ይላሉ” የጥናት ቡድኑ ዳይሬክተር።

 

የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ፕሮፌሰር ደጀኔ አየለ የጉባዔው ዋና ዓላማ ወልቂጤና አርሲ ዩኒቨርሲቲዎች እንደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋምነታቸውና የዝዋይ ሐይቅ ገባሮች ከጉራጌ ሰንሰለታማ ተራሮችና ከጭላሎ ፏፏቴዎች እንደመምጣታቸው ጉዳዩ በዋናነት የሚመለከታቸው ስለሆነ ባለ ድርሻ አካላትን በማሰባሰብ ሐይቁን ከጥፋት መታደግ ነው ሲሉ ያብራራሉ። ለሐይቁ ውሃ፣ ለጥልቀቱ መቀነስ፣ ለዓሣና ለሌሎች ብዝሃ ህይወት መጥፋትና መመናመን ምክንያት ናቸው ተብለው በዋናነት በጥናት ስለተጠቀሱት ምክንያቶች ፕ/ር ደጀኔ ሲያብራሩ፤ የውሃው መጠን የቀነሰው ሐይቁ ላይ ለመስኖ አገልግሎት ውሃ ለመሳብ በርካታ የውሃ ፓምፖች መቀመጣቸው ሲጠቀስ ለዓሣና ለሌሎች በሐይቁ ውስጥ ለሚገኙ ብዝሃ ህይወቶች መጥፋትና መመናመን ደግሞ በሐይቁ አካባቢ ከሚገኙ የአበባ እርሻዎች የሚለቀቁ ኬሚካሎች እያደረሱ ያሉት ብክለት በግልፅ ተቀምጧል ይላሉ።

 

ፕ/ር ደጀኔ አክለውም ለጥልቀቱ መቀነስ በሐይቁ ዙሪያ ያለ ደን በመጨፍጨፉና በዝናብ ወቅት የሚሸረሸረው አፈር ወደ ሐይቁ በደለል መልክ መግባቱ አንዱ ሲሆን ቀደም ብለው የገለፁት ውሃውን ለመስኖ ስራ የሚወስዱት የውሃ ፓምፕ ሞተሮች ለጥልቀቱ መቀነስ ግልፅ ምክንያቶች እንደሆኑ ይናገራሉ። “ይህ የሐይቅ ጉዳት ከፍተኛ ስለመሆኑ ቀደም ሲል በእነ ፕሮፌሰር ብሩክ ተጠንቷል” ያሉት ፕሮፌሰር ደጀኔ በእርሳቸው ዩኒቨርሲቲ በኩል የቀረበው ጥናት ለእነዚህ ችግሮች ስለሚሆኑ መፍትሄዎችና አሁን ሐይቁ ስለሚገኝበት ተጨባጭ ሁኔታ አዲስ መጣ ስለተባለው አረም (እምቦጭና) በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ መሆኑን ይጠቅሳሉ።

 

እንደ ፕሮፌሰር ደጀኔ ገለፃ፤ ይህንን ሐይቅ አሁን ከተጋረጠበት አደጋ ለመታደግ በተፋሰሶቹ ላይ መስራትና ብክለቱን እያደረሱ ያሉት የአበባ እርሻዎች የብክለታቸው መጠን ተጠንቶ ከዚህ በኋላ የሚለቁትን ኬሚካል አጣርተው ካልሆነ በስተቀር እንዳለ ወደ ሐይቁ እንዳይለቁ ለማድረግ ይህንንም ተፈፃሚ ለማድረግ ስምምነት ላይ ተደርሷል። በሌላ በኩል ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲና ከአርሲ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ቡድን የተውጣጡና ከዚህም በፊት ሲሰሩ የነበሩ ኮሚቴዎች መዋቀራቸውንና ሐይቁን ለመታደግ በምን መልኩ እንቅስቃሴ ይጀመር እና ዋና ዋና ባለ ድርሻ አካላት እነማን ናቸው፣ የትኛው ባለድርሻ አካላት ምን ይስራ የሚለውን አጥንተው ነሐሴ 15 ቀን 2009 ዓ.ም በሚካሄደው ጉባዔ ላይ እንደሚያቀርቡና ከዚያ በኋላ በሐይቁ ላይ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንደሚጀመር የገለፁት ፕሮፌሰሩ፤ ዋና ዋና ባለድርሻ አካላት የሚባሉት ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ፣ አርሲ ዩኒቨርሲቲ፣ እንስሳትና ዓሣ ሀብት ሚኒስቴር፣ የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ፣ የስምጥ ሸለቆ ተፋሰስ ድርጅትና የአካባቢና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ሐይቁን ለመታደግ በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል።

 

ሚያዚያ 14 ቀን 2009 ዓ.ም በዝዋይ ከተማ ኃይሌ ሪዞርት በተካሄደው በዚህ ዓለም አቀፍ ጉባዔ ዩኒቨርስቲዎች፣ የምርምር ተቋማት፣ አካባቢ ጥበቃ ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስትና የግል ተቋማት እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች ተሳታፊ የነበሩ ሲሆን፤ በቀረቡት ጥናቶችና በመፍትሄዎቻቸው ዙሪያ ከፍተኛ ውይይቶችና ሀሳቦች ተሰንዝረዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
381 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 178 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us