ዶክተር ቴዎድሮስ የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር እንዳይሆኑ መቃወም ማለት ማንን መቃወም ማለት ነው?

Wednesday, 10 May 2017 13:15

(በክብሮም አድሃኖም ገ/እየሱስ)

 

የቀድሞው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተርነት በውድድር ላይ መሆናቸውንና ከሶስቱ እጩዎች መካከልም አንዱ ሆነው ለመጨረሻ ዙር ያለፉ መሆናቸው ይታወሳል። ከሁለት ሳምንት በኋላ የ 189 ሐገራት የጤና ሚኒስትሮች በሚሰጡት ድምፅ ለቀጣዩ አምስት ዓመታት የዓለም ጤና ድርጅትን የሚመራውን ሰው ይመርጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።


ይህንን የምርጫ ቀኑን ተከትሎ አንዳንድ የጭፍንና የጥላቻ ፓለቲካ አራማጆች አክራሪ ዲያስፓራዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በግልፅ አንዴ የተቃውሞ ፊርማ በማሰባሰብ በእርሱ አልሆን ሲላቸውና ሲከሽፍባቸው በሌላ ጊዜ ደግሞ በዓለም ጤና ድርጅት ፅ/ቤት በሚገኝበት በስዊዘርላንድ ሰልፍ ለማድረግ በቅስቀሳ ላይ ይገኛሉ። ይህንን ሳይ አንድ ታሪክ አስታወሰኝና ላካፍላችሁ አሰብኩ የሆነው እንዲህ ነው፦


በቀድሞው መንግስት በደርግ ስርዓተ መንግስት ደርግ ወደ ሥልጣን በወጣ ዓመታት አካባቢ በፓለቲካ ልዩነት የተነሳ ብዙ ወጣቶች ተገድለውና ተሰድደው ነበር። በወቅቱም ደርግን ተቃውመው ከአገር ከተሰደዱት መሐል አንዱ የሕብረት ባንክ መስራችና ፕሬዝዳት የሆኑት አቶ ኢየሱስወርቅ ዛፉ አንዱ ነበሩ እኝህ ሰው በስደት አገር በነበሩበት ለአፍሪካ ልማት ባንክ ለመምራት በወጣው ማስታወቂያ መሰረት መወዳደር ይፈልጋሉ። ነገር ግን በወቅቱ አንድ ነገር ያስፈልጋቸው ነበር ኢትዮጵያዊ እንደመሆናቸው በውድድሩ ለመሳተፍ የኢትዮጵያ መንግሰት ፈቃድ ያስፈልጋቸው ነበር። በወቅቱ አቶ ኢየሱስበርቅ ዛፉ ደርግን የሚቃወሙና የደርግን መንግስት የማይደግፉ እንደመሆናቸው ደርግ ድጋፍ ይሰጠኝ ይሆን የሚለው ጉዳይ አሳሰባቸው። ነገር ግን ለምን አልሞክርም በሚል በወቅቱ በነበሩበት ሐገር የኢትዮጵያ አምባሳደር ለነበረው ሰው ለአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንትነት መወዳደር እንደሚፈልጉና የኢትዮጵያ መንግስት ድጋፍ/ እውቅና ይሰጣቸው እንደሆነ ጠየቁ። አምባሳደሩም ኢትዮጵያ ለሚገኘው የደርግ መንግስት ጥያቄውን ላከ ምላሹም ያልተጠበቀ ሆነ በወቅቱ እንዲህ ነበር ያለው " በዓለም መድረክ ኢትዮጵያውያንን ማየትና የኢትዮጵያውያን መቀመጥ አገራችንን የሚጠቅምና ሊበረታታ የሚገባው ተግባር በመሆኑ የኢትዮጵያ መንግስት እውቅና ብቻ ሳይሆን አስፈላጊ የሆነ ሙሉ ድጋፍም እንደሚሰጣቸው ንገራቸው!" ነበር ያለው አቶ ኢየሱስወርቅ ዛፉም በመልሱ በጣም ነበር የተገረሙት በዚህም በወቅቱ ተወዳድረው የአፍሪካ ልማት ባንክን ለመምራት በቁ እንደ መሪነትም እንደ ኢትዮጵያዊነታቸውም ኢትዮጵያን መጥተው እስከ መጎብኘትና አገራቸውን ኢትዮጵያን የሚጠቅም ብዙ ተግባሮች አከናወኑ።


ዛሬስ ምን እየተደረገ ነው? ቢያንስ በአስተሳሰብ ለምን ተሽለን መገኘት አቃተን? ለምንስ ወርደን ተገኘን?


ለመሆኑ ዶክተር ቴዎድሮስ አድሐኖም የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ሆነው ቢመረጡ የሚጠቀመው ማን ነው?


1. በበሽታ ብዛት ለምትሰቃየውና በየዓመቱ ኢቮላ በመሰሉ ገዳይ በሽታዎች ለምትሰቃየው አህጉራችን አፍሪካ ትልቅ እድልና ተስፋ ነው። ከምንም በላይ እንደ አፍሪካዊነታቸው የወንድሞቻቸውን አፍሪካውያን ስቃይ በቅርበት ያውቁታልና መፍትሔ በማምጣት ረገድ ትልቅ ስራ ይሰራሉ ተብሎ ይጠበቃል። ለዚህ ነው የአፍሪካውያን መንግስታት ሙሉ ድጋፍና እውቅና የተሰጣቸው፤


2. አገራችን ኢትዮጵያ በጤና ፓሊሲው ረገድ የሚሊኒየሙን ጎል ለማሳካት በተቃረበችበትና ደፋ ቀና በምትልበት በአሁኑ ሰዓት የእርሳቸው በመሪነት ስፍራ መመረጥ ግቡን ለማሳካት ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።


3. የዓለም ጤና ድርጅት ራሱ በእርሳቸው መመረጥ ተጠቃሚ ይሆናል። ለምን ቢሉ እርሳቸው ባለፈው ጊዜ Presentation ሲያቀርቡ ወደፊት ሊሰሩና በድርጅቱ ሊቀይሩ ካሰቡት መሐል በዋነኛነት የድርጅቱን የፋይናንስና የበጀት ዓቅም ማሳደግ ነው። በተለይም ከጠቀሱት ምሳሌ መሐልም የአንድ በአሜሪካ የሚገኝ የኒውዮርክ ሆስፒታል ዓመታዊ በጀት አራት ቢሊዮን ዶላር እንደሆነና የአለም ጤና ድርጅት በጀት ግን ከዚህ ያነሰ መሆኑ አንዱ ነው። በዚህም ድርጅቱ ምን ያህል የፋይናንስ ቀውስ ውስጥ እንዳለ እሙን ነው በዚህም የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር በነበሩበት ጊዜ የፋይናንስ ምንጭ በማፈላለግ የሚኒስትሩን መ/ቤት በጀት 90% ከውጭ በሚገኝ ፋይናንስ እንዲሸፈን በማድረግ የሰሩት ስራና ያላቸው ልምድ የድርጅቱ ዳይሬክተር በመሆን ቢመረጡ በፋይናንስ አቅሙና በሚሰጠው የጤና ሽፋን ረገድ ትልቅ ለውጥ ያመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። ለዚህ ነው የእርሳቸው መመረጥ ድርጅቱን ይጠቅማል ያልነው፤


4. አብዛኛውን የአገራችንን ታሪክ ስናይ በዓለም ታሪክ እንደ ቀዳማዊነታችን በዓለም የመሪነት መድረክ ግን ብዙም ኢትዮጵያዊ ማግኘት ሲኖርብን ግን ይህንን ማድረግ አልቻልንም። ከእኛ ይልቅ የረጅም ጊዜ የፓለቲካ ባላንጣችን ግብፅ በቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊ የተባበሩት መንግስታት መሪነት የአረብ ሊግ ዋና ፀሐፊነትን አሕመድ ሙሳ እና በአለም የገንዘብ ድርጅት IMF ቁልፍ ቁልፍ ቦታዎች ዜጎቿን በማስሾም ትበልጠናለች። በእነርሱ ተፅእኖ በመፍጠርም የፋይናንስ ምንጭ አግኝተን የአባይ ግድብ እንዳንገነባ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ተፅእኖ ስትፈጥርብን ነበር። ዛሬ ግን እንደ የሰው ዘርና የታሪክ ቀዳሚነታችን ያጣነውን ስፍራ በዶክተር ቴዎድሮስ አድሐኖም አማካኝነት ለመቀየር ጫፍ ላይ ደርሰናል። ለያውም ተቀናቃኞቻችን ግብጾች እንኳን መርተውት የማያውቁትን የአለም ጤና ድርጅት ለመምራትና የአፍሪካ ቀዳሚ ለመሆን ጫፍ ላይ ደርሰናል። የእርሳቸው በዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተርነት መቀመጥና መመረጥም ለአገራችን ምሁራን የእችላለሁ መንፈስ እንዲሰርፅና ለማነሳሳት ትልቅ እመርታ ይሆናል። እርሳቸውም ኢትዮጵያዊ ሆነው በአለም መድረክ በመቀመጥ ለአገራቸውና ለራሳቸው ታሪክ ይሰራሉ ማለት ነው።


ስለዚህ ዶክተር ቴዎድሮስ አድሐኖም የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር እንዳይሆኑ መቃወም ማለት፦


ሀ. ከበሽታ የፀዳችና ነፃ የሆነች አፍሪካን ላለማየት መቃወም ማለት ነው፤


ለ. በጤናው ረገድ ኢትዮጵያ ልታሳካው ያቀደችውን ፓሊሲ መቃወምና በየገጠሩ አሁንም በበሽታ የሚሞቱ ወገኖቻችን ላይ ሞት ማወጅ ማለት ነው፤


ሐ. ላለፉት ረጅም አመታት በፋይናንስ እጥረት አጣብቂኝ ውስጥ በመሆን RADICAL ስር ነቀል ለውጥ ማምጣት ያቃተው የአለም ጤና ድርጅት በዶክተር ቴዎድሮስ መመምጣት ካለበት ችግር እንዳይወጣና በድህነትና በበሽታ ለሚሰቃዩ የሶስተኛ ሐገር ሕዝቦች ተደራሽ የሆነ የጤና ሽፋን እንይሰጥ መቃወም ማለት ነው።


መ. በታሪክ የሰው ዘር መገኛ የምትባለው አገራችን ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ብቸኛና ቀዳሚ የተባበሩት መንግስታት መስራች አባልነቷና የታሪክ ቀደምትነቷ በዓለም የመሪነት መድረክ እስከ ዛሬ ትልቅ ቦታ የደረሱ ዜጎችን ለማፍራት ያለመቻሏ የሚያስቆጭ ታሪካችንና ያጣነው የነበረ ነገር እንደ መሆኑ ከዚህ በኋላ የዶክተር የዓለም ጤና ድርጅት መሪ መሆን ለኢትዮጵያውያን ምሁራን መነሳሳትን ይፈጥራል ታሪክም ይቀይራሉ ተብሎ ይጠበቃል። ስለዚህ ዶክተር ቴዎድሮስን መቃወም ማለት አገራችን በዓለም መድረክ ሊኖራት የሚገባውን የመሪነት መድረክና በታሪካችን ያጣነውን ነገር እንዳይሳካ ማሰናከል ማለት ነው።


ስለዚህ ሲጠቃለል መልእክታችን የምንቃወመውን እንወቅ ነው። ለመሆኑ በጥላቻ ፓለቲካ ታውረን የምንቃወመው እስከ መቼ ነው? ይህ የመጠላለፍ ፓለቲካ የሚያበቃው መቼ ነው? ጭራሽ የቤታችንን አመል እዛው መፍታት ሲገባን በዓለም መድረክ ራስ በራሳችን በመቀዋወም መሳቂያ መሆናችን አሳፋሪ ተግባር ነው። ሰው እንዴት የራሱ ዜጋ የሆነ ምሁር እንዳይመረጥ ብሎ እንዴት ሰልፍ ለመውጣት ይዘጋጃል። ሌላው ቢቀር ከቀድሞ ተሽለን አለመገኘታችን ያሳፍራል። ኢትዮጵያዊውን ምሁር በዓለም መሪነት ስፍራ እንዳይቀመጡ እየተቃወሙ ለኢትዮጲያዊነት እቆረቆራለሁ ማለት ፌዝ ነው፤ ማላገጥ ነው። ለዚህ ነው ኢትዮጵያዊነት ምን ማለት እንደሆነ አልገባችሁም የምንለው፤


ስለዚህ በዶክተር ቴዎድሮስ የፓለቲካ አቋም ችግር ቢኖራችሁ እንኳ እንዲህ እንበል "በዓለም መድረክ ኢትዮጵያውያንን ማየትና የኢትዮጵያውያን መቀመጥ አገራችንን የሚጠቅምና ሊበረታታ የሚገባው ተግባር በመሆኑ የኢትዮጵያውያን እውቅና ብቻ ሳይሆን አስፈላጊ የሆነ ሙሉ ድጋፍም እንደምንሰጣቸው እንንገራቸው ከዚህ ቀደምም እንዳደረግነው ሁሉ ሙሉ ድጋፋችንን እንቀጥል።


የአገራቸው ምሁር እንዳይመረጥ ለሚተጉና ለተቃውሞ ሰልፍ ለተዘጋጁ ሁሉ ደግሞ የሚያደርጉትን የሚቃወሙትን አያውቁምና እግዚአብሔር ወደ ልቦናቸው ይመልሳቸው!


ትልቅም ነበርን ትልቅ እንሆናለን!
ድል ለዶክተር ቴዎድሮስ አድሐኖም 

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
312 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 179 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us