የ“አዙሪት” ረጅም ጉዞ

Wednesday, 10 May 2017 13:31

 

የመፅሐፉ ርዕስ          አዙሪት

ደራሲው          ነገሪ ዘበርቲ

አርታኢ           ባዩልኝ አያሌው

የገጽ ብዛት        430

የሕትመት ዘመን    ሐምሌ፣ 2008 ዓ.ም

አሳታሚ           ያልተገለፀ

አስተያየት         ማዕረጉ በዛብህ

በዕውቀት በዳበሩ አገሮች ባዳዲስ መፃሕፍት ላይ አስተያየት ሂስ መጻፍ የተለመደ ነው። ሃያሲያኑ ያፃፃፍን ጥበብ በዩኒቨርስቲዎች ይማሩታል። በኛ አገር ያቅድመ ዝግጅት ትምህርቱም ሆነ የሂሱም ፅሁፍ በሰፊው የተለመደ ባይሆንም አልፎ- አልፎ አንዳንዶቻችን በልምድ እንሞጫጭራለን። አንዳንድ መፅሐፍ አንብበው ሲጨርሱት  ምንም ስለማይል በሰላም ተዘግቶ ባትራኖስ ይቀመጣል። አንዳንዱ ግን “ካነበብከኝ በኋላ ምን ተሰማህ” ብሎ ራሱ የሚያፋጥጥ ይመስላል። ከኔ ያገኘኸውን ቁም ነገር ለምን ለውይይት አታቀርበውም የሚል አይነት ነው። “አዙሪት” የዚህ የኋለኛው ዓይነት መጽሐፍ ሆና አግኝቻታለሁ። መጽሐፍዋ አያሌ ቁምነገሮችን ስለያዘች አስተያየት ለሚሰነዝር ሰው ከየት እንደሚጀምር ሳይቸገር አይቀርም። ደራሲ ነገሪ ዘበርቲ በመጽሐፉ እንደሚታየው ለኢትዮጵያ ያለው አገራዊ ፍቅር እጅግ የሚደነቅና የሚያስገርም በመሆኑ እኔንም በብርቱ ስለኮረኮረኝ ከዚያ ብጀምር እወዳለሁ። ደራሲ ነገሪ ስለ ኢትዮጵያ እንዲህ ይላል።

“ለኔ ኢትዮጵያ ማለት ፅጌረዳ አበባ ነች። ውበትዋ ይማርከኛል። መዐዛዋ ያውደኛል። ልስላሴዋ ይመቸኛል። ሁሉም ለሀገሩ ያለው ስሜት ይህ ይመስለኛል። ኒውዮርኩም ለኒውዮርክ በደዊውም ለአረብ በረሃ ያለው ስሜት እንደዚሁ ነው” ይህንን ይበልጥ ሲያብራራው፤

“ፅጌረዳ የሚያምረው ከነሾሁ ነው። ምናለ እሾሁ ባይኖር ብሎ መመኘት የዋህነት ይመስለኛል። ዛሬም ለኢትዮጵያዊው ኢትዮጵያ ከነችግሯ ልትመቸው ይገባል። ምናለበት ጦና ላይ ባይዘመት፣ ከሐረሪው አሚር ጋር ባንዋጋ እያሉ መነታረክ አይበጅም። በዚህ መንገድ ካልሆነ የዛሬዋን ኢትዮጵያ ማየት አይቻልም። ከዚህ መንገድ ውጭ በዓለም ላይ የተመሠረተ ሀገር ብዙ አላውቅም” ይላል ነገሪ። ይህ ብዙ ሊያስተምረን የሚችል ከፍተኛ ቁምነገር የያዘ አነጋገር ነው። ደራሲው እንዳለው ሁሉም አገሮች ከመንደራዊ ሕልውና ወደ አንድነታዊ ብሔራዊ መንግሥትነት ያደጉበት ብቸኛው የሽግግር መንገድ ይህ ነው። ብሪታኒያ፣ ፈረንሳይ፣ ኢጣሊያ፣ ጀርመን፣ ኢትዮጵያ ሁሉም በብሔረተኝነት መሠረት፣ ከቅንቅን፣ ከውድድርና ከጦርነት ተነስተው ወደ ኀብረብሔርነት መንግስት ያደጉት በዚሁ መንገድ ነው። ዛሬም ስለ አገራችን ፌዴራላዊ አንድነት የማይጥማቸው ካሉ ከደራሲ ነገሪ ዘበርቲ ብዙ ሊማሩ ይችላሉ። እንዲያውም ስለፌዴራሉ ዝምም እጅግ ጠቃሚና ብልህ ትምህርት ለመስጠት ደራሲው የሚከተለውን ይላል።

“ፌዴራሊዝም ለዘመናት የተጻፈነውን የሕዝቦች ጥያቄ ለመመለስ ጥሩ መሣሪያ ነው። ሕዝቦች ለዘመናት በጦርነት፣ በስደት፣ በንግድ ያካበቱትን ያክብሮት ባህል፣ ማህበራዊ ትስስርና ሌሎችንም ሰብዓዊ እሴቶች ለመጠበቅ ካሰማና ማገር ሆኖ ከማገልገሉም በላይ መጪውን አሻግሮ ማየት የሚያስችል አቅም ይሰጠናል። ከዚህ ውጭ “ቋንቋህ አላማረኝም፣ መልክህ ከኔ አይገጥምም” እያሉ ፌዴራሊዝምን ማንገዋለያና ማበጠሪያ ወንፊት ካደረጉት አበሳው ብዙ ነው” ይለናል ደራሲ ነገሪ። ደግሞ ችግሩን ሲተነትነው “ካልተበጠረና ካልተንገዋለለ በቀር እየተቀየጡ ፌዴራሊዝም የለም” የሚሉ ካሉም እነሱ ብሔራዊ ጭቆናን ከፌዴራሊዝም ጋር በስውር ስፌት እየተዘመዘሙ ናቸውና ኧረ በሕግ ማለት አለብን፤ የመጣበትን እንዳንደግመው በንቃት መከራከር ያስፈልጋል” ሲሉ ከምክር አልፎ ያስጠነቅቀናል።

ደራሲው የኢትዮጵያን ያለፈውን ዥንጉርዙር ታሪክና ዛሬም የምትገኝበትን ውጥንቅጥ ሁኔታ በሰፊው ከጠቃቀሱ በኋላ የኢትዮጵያ ምሁራን ባገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሁልጊዜ የሚያነሱትን የአገርአቀፋዊ ውይይትና የእርቅ አስፈላጊነት አጠንክሮ በመጠየቅ እንደዚህ ያስቀምጠዋል። “እነዚህንና ሌሎች እነዚህን የመሰሉ አመለካከቶችን ለማፅዳት የሪፎርም ስራ ይጠይቃል። ግልጽ ክርክር መካሄድ አለበት። የማያባራ ውይይት ያስፈልጋል። ያኔ ጭቆናን የሚጠየፍ ከመንጋው የተነጠለ፣ በሰፈር-ልጅነት ፍቅር ያልነደደ፣ ሆዱ የማያሸንፈው. . . ኢትዮጵያዊ ብቅ ይላል። ያኔ ደምኖ አይቀርም ይዘንባል። ማሳውም ይርሳል፣ ፍሬም ያፈራል። የሰው ልጅም በልማት ሰረገላ ወደ ዕድገት የከፍታ ጫፍ በረራውን ይያያዘዋል” ይላል ረጅም ሕልም አላሚው ደራሲ።

ወደዚህ ድምዳሜ ለመድረስ ደራሲው ረጅም መንገድ ተጉዘዋል። የፋሽስት ኢጣልያ ወራሪዎች የመሰሉት የኢትዮጵያ ጠላቶች በየጊዜው በአገራችን ላይ ያደረሱትን በደልና የፈፀሙትን የእልቂት ግፍ ያወሳል። በረጅሙ የህልውና ታሪካችን ይህ ነው ተብሎ የማያልቀውን መከራና ግፍ እየተቀበሉና ከብረት በጠነከረ አልበገሬነት ዕልቂትንና ሰቆቃውን እየተጋፈጡ ይህቺን ጥንታዊት ውብ ሀገር በነፃነት ያኖርዋትን የአያት የቅድመ አያት፣ አያቶቻችንን ቅድመ አያቶች ውለታ ያነሳል። ወደሃያኛው ክፍለ ዘመን ታሪካችን ሲዘልቅም ኢትዮጵያን አዘምናታለሁ ብለው የተነሱት አፄ ኃይለስላሴም እንዳልተሳካላቸው በወጣት ሂስ አቅራቢ ሳይሆን በንጉሡ ዘመን የልጅ ኢያሱ ደጋፊ በነበሩ ሽማግሌ አንደበት ንጉሡን ያስወቅሳቸዋል።

“ንጉሡ መውረድ ነበረባቸው። ዕድሜያቸው ገፍቷል። ፍትህ ተጓድሏል. . . በመኳንንቱና በዘመናዊ አስተዳደር ስርዓት ናፋቂዎች መካከል ከፍተኛ ቅራኔ አለ. . . ይህን ደግሞ ንጉሡ ሊያስተካክሉት አይችሉም። ለዚህ ነው የወረዱት” ይላሉ አቶ በያን። አቶ በያን የመፅሐፉ አውራ ገፀ-ባህሪ የሆነው የአካሉ አባት ናቸው።

የደራሲ ነገሪ ዘበርቲ የስነፅሁፍ ችሎታ ጎልቶ ከሚታይባቸው ኩነቶች አንዱ የንጉሡ የስደት ጉዞ ገለፃው ነው። በንጉሡ ዙርያ የነበሩት መሳፍንት ሚኒስትሮችና መኳንንት የንጉሠ ነገስቱን የስደት ጉዞ በተመለከተ በሁለት ተከፍለው እንደነበር ብዙ ጊዜ ሲነሳ የኖረ አከራካሪ ነጥብ ነው። አንዱ ወገን ንጉሠ ነገሥቱ ወደዓለም መንግሥት ማህበር ሄደው በመከራከር ያገራችንን ነፃነት ሊያስመልሱልን ይችላሉ የሚል አቋም ሲይዝ፤ ሌላው ወገን ደግሞ ንጉሥ ከሕዝቡ ጋር ሆኖ እስከመጨረሻ ደም ጠብታው ይዋጋል እንጂ እንዴት አገሩን ጥሎ ይሸሻል የሚል ጽኑ አቋም የነበራቸው ወገኖች እንደነበሩ ደራሲው የወቅቱን ድራማ በረቀቀ የስነፅሁፋዊ ጥበብ የገለፀው። ማንም አንባቢ ከሚጠብቀው በተለየ መልኩ ነበር ብዙ ቃላት ሳያባክን፣ ግልፅ ወገናዊ አቋም ሳያሳይ ድራማው እንደዚህ ነበር። ንጉሡ ኢቴጌይቱ ወደውጭ ስለምትሄድ “ተቀብላችሁ ሸኙ” የሚል ትዕዛዝ እንዳስተላለፉ ስለተሰማ ሕዝቡ በተለይ መኳንንቱ ንግሥቲትዋን ሊሸኝ በባቡሩ ጣቢያ ተገኝቶ ንግስቲቱን ይጠባበቅ ነበር። ያልተጠበቀ ነገር ደረሰ። ያንን አስደናቂ ድራማ ደራሲው ያስቀመጠው እንደሚከተለው ነበር።

አቶ በያን በልጅነታቸው አርበኛ የነበሩትን አባታቸውን ተከትለው መኢሶን ባቡር ጣቢያ ተገኝተው ነበር። የእቴጌይቱን መምጣት ሲጠባበቅ የነበረው አርበኛ ንግሥቲቱ ሳይሆኑ ንጉሠ ነገሥቱ ከባቡሩ ፉርጎ ብቅ ሲሉ” ባየ ጊዜ ስሜቱን በጣም እንደተጎዳ ያስተውላሉ። በተለይ አንድ ስማቸው ያልተጠቀሰ “ስመጥር አርበኛ- በቁጭት” ንጉሡን እየተመለከቱ “ይህ እስስት” ብለው ሲናገሩ አቶ በያን ከዚያ አርበኛ አጠገብ ቆመው እንደነበር ነው የተተረከው። ደራሲው በሚኤሶን ባቡር ጣቢያ ከ38 ዓመት በፊት የተከናወነውን ድራማ እንደዚህ አድርጎ የትዝታ ሕይወት ሰጥቶ ነው በአዙሪት ያቀረበው። ይህ የሚደነቅ ስነፅሁፋዊ ጥበብ ነው መፅሐፉን ምነው ፊልም ቢሠራ? የሚያስብለው። ሌላው መፅሐፉን ቁምነገር ሙሉና ለንባብ አስደሳች ያደረገው ስለ ሰው ልጆች ጉራማይሌ ተፈጥሮ የሚያቀርበው ስነ-አእምሯዊ /ህሊናዊ (ሳይኮሎጅካል) ጥልቅ አስተያየት ነው። በመፅሐፉ ስማቸው የተጠቀሰ ብዙ ተዋንያን ቢኖሩም በዋናነት ጽሀፉ የሚያጠነጥነውን በሁለት ከፍሎ ያሳየናል። ባንድ በኩል በሚመሰገነው የቁም ነገሮች ቡድን ውስጥ ሊመደቡ የሚችሉት በሙያቸው የሚከበሩ አገራቸውንና ሥራቸውን የሚወዱ እንደዋናው መሐንዲስ (ቺፍ ኢንጅነር) አንዱ ተሻለ አካሉ መሠረትና ሰላማዊት ያሉ ስለኢትዮጵያ እድገትና ሕልውና ብዙ የሚቆረቆሩ ሲሆኑ፤ በራስ ወዳድነትና በቀልድ እንጂ ብዙም የአገር ፍቅር የማይታይባቸው እንደ በልሁ ፣ ደብሬና ኪው-ጦር ደግሞ በሁለተኛው ቡድን የሚመደቡ ናቸው።

ዋናው መሐንዲስ ኢትዮጵያ በጣም አስጊ በሆነ ውጥረት ላይ በመገኘትዋ ፕሮጀክቶች በሙሉ እንደሚታጠፉና በጀታቸው ለትጥቅ ትግል ድጋፍ እንዲውል የመደረጉን መርዶ ለመስሪያ ቤቱ ሠራተኞች በስብሰባ ሲገልፅ፤ አብዛኛው ሠራተኛ በአገሪቱ ላይ የደራሲውን መከራና ፈተና አስጨንቆት በሀዘን አዳራሹን እየለቀቀ ወደቢሮው ሲሄድና ቅሬታውን በሁኔታው ሲገልፅ በልሁ ግን እንደተለመደው እየቀለደ እቢሮው ገብቶ “አይዞን አንቆዝም፣ ራስን ማመሳሰል ማስተካከል፣ ካስፈለገም መርካቶ ገብቶ መነገድ፣ አየር ባየር ውስጥ ለውስጥ ከመሐንዲስነት ወደ ቸርቻሪነት በሰላም መሸጋገር እያለ ሲስቅ ነው የሚታየው። ነገሪ ከላይ የተገለፁት የሁለቱም አይነት ሰዎች በልሁም ጭምር ምን ጊዜም በህብረተሰብ ውስጥ እንዳለና እንደሚኖሩ ነው የሚያሳየው።

ውበትንና የፍቅር ጭውውትን ማቅረብ ሲፈልግም ደራሲ ነገሪ ስነፅሁፋዊ ችሎታው ይበልጥ ይፈካል። አካሉ ስለመሠረት ውበት ሲገልፅ “የባቄላ አበባ የመሰለ ዓይን፣ የቆዳዋ ፀዳል፣ የጸጉርዋ ልስላሴ የአካሏ ቅጥነት ምንይሁን ብሎ ነው እንዲህ ያሳመራት? ሲል ይስላታል። (ገጽ 19) በሌላ በኩል ደግሞ የህብረተሰብ ጨቋኝ ልማድና ባህል እምብዛም የማያስጨንቃቸውና ነፃነታቸውን የሚወዱ ሴቶች ሊገኙ እንደሚችሉ ሙናን በምሳሌነት ያቀርባል። ቀደም ብሎ የሚያውቃት ሙናን ተሻለ ከአካሉ ጋር ካስተዋወቃት በኋላ “አንቺ ልጅ በፈጠረሽ ረጋ በይ” ሲላት በአካሉ የፈጠራቸው መልስ “አቦ በፈጠረህ እነዚህን አትስማቸው። በግድ በኛ አዕምሮ አስቢ ነው የሚሉኝ” ነበር የሙና ነገር በዚህ አያበቃም። ነጻነቷን መውደዷና ግልፅነቷ እንደኛ ባለ ኅብረተሰብ ብዙ ሊያነጋግር ቢችልም የተማሩ ሴቶችን መወከልዋ ይሆን “ከወደድኩት ከፈለኩት ወንድ ጋራ በፈለኩት ቦታ መውጣት አለብኝ። . . . ዛሬ እኔ ከአንድ ወንድ የምፈልገው ወንድነቱን ብቻ ነው” ትላለች ሙና።

መደምደሚያ

መቸም አንድ ሥራ ምንም በጥንቃቄ ቢሰራ አልፎ አልፎ አንዳንድ ጥቃቅን ህፀፆች አይጠፉምና አዙሪትም ውስጥ ጥቂት ህፀፆች ብቅ ማለታቸው አልቀረም። አንደኛው ህፀፅ እየተለመደ የሄደው በሁ ፈንታ ውን የማስገባቱ ስህተት ነው። በላሁ ለማለት በላው እየተባለ መፃፍ ስለተጀመረ አዙሪት ላይም በገጽ 380 “ማስረዳት እችላለሁ” ለማለት እችላለው፣ በገጽ 381ላይም “የቻልኩትን ያህል አነባለሁ” ለማለት አነባለው ነው የሚለው መዝጊያው ቃል። የሚያሳዝነው መደጋገሙ ነው። በዚያው ገፅ፤ “እዚህ ምን እሰራለሁ” ለማለት “እሰራለው” ነው የሚለው። ችግሩ የእርማት ሥራ (Proof reading) ይመስለኛል። ማንኛውም ለሕዝብ የሚሠራጭ ጽሁፍ ታትሞ እስኪወጣ ድረስ ደጋግሞ መታረም አለበት። “ሁ” የሚለው ካዕል ፊደል ለምን “ው” በሚለው እንደሚለወጥ ጨርሶ ሊገባኝ አይችልም። ሌላው ስህተት ደግሞ የሚያስቅም ነው። ነገሪ ጣሊያንኛ እንደማያውቅ ግልጽ ነው ምክንያቱም ሴት ስትደነቅ “ብራቫ” ነው እንጂ የምትባለው “ብራቮ” አይደለም። ብራቮ ለወንድ ነው። አንድን ነገር እርግጠኛ ሳይሆኑ ከሌሎች ተቀብሎ ዝም ብሎ ከመፃፍ የሚያውቁ ሰዎችን ፈልጎ መጠየቅ ይጠቅማል።

የብራቮ ችግር ልክ እንደ ሰፕፒዮ (spocio) ነው። በመኪና ላይ የኋላውን ለማሳየት ከግራና ከቀኝ የተተከሉት መስታወቶች ስፔኪዮ (specio) ነው የሚባሉት በጣሊያንኛ። አንዱ በስህተት ስፖኪዮ ሲል ስለተሰማ አገሩ በሙሉ ዛሬ የተሳሳተውን አጠራር ይዞ ስፖኪዮ ሲል ይሰማል።

ወደሌላ ነገር ወስድከኝ ባልባል “ፋዘር፣ ማዘርም” ወደቋንቋችን የገቡት በመደበኛ የዕውቀት ሽግግር ሳይሆን በጥራዝ ነጠቆች ነው። ቋንቋ ያወቁ መስሏቸው አባት፣ እናት የሚሉትን ውብ የአማርኛ ቃላት ያለአንድ ምክንያት ወደፋዘር፣ ማዘር ለውጠው ሲጠቀሙ ተሰሙ። ሕዝቡ “ታላቅ ዕወቀት” ያገኘ መስሎት አሮጊቶችና ሽማግሌዎች ሳይቀሩ ዛሬ አባትና እናት ለማለት ፋዘር ማዘር የሚል ጅል ዘይቤ ምርኮ ሆነው ይሰማሉ፣ ያሳፍራል።

በጋዜጠኝነት ሙያ አንድ አነጋገር አለ። እርግጠኛ ካልሆንክ ተወው፣ አታንሳው (If in doubt leave it out) ይባላል። ከዚያም በላይ በዚያ ውብ የአማርኛ ቋንቋ የተስተናገደበት መፅሐፍ የፈረንጅ ቃላት መጨመሩ መፅሐፉን ያቀጭጨዋል እንጂ አላዳበረውም።

ይህም ሁሉ ሆኖ የመፅሐፉ ጠንካራ ጎኖች እጅግ የላቁና ከጥቃቅኖቹ ህጸጾቹ ጋር የሚወዳደሩ አይደሉም። የደራሲው ሙያዊና ጠቅላላ ዕውቀት፣ አገራዊ ተቆርቋሪነቱ፣ የኢትዮጵያን አሳሳቢ ጉዳዮች በሚደንቅ የቋንቋ ችሎታ መግለፁ፣ ፍልስፍናዊውና የስብዕና አመለካከት ጥራት መፅሐፉን ለሚያነቡ ሁሉ ደስታና መልካም ትዝታ የሚሰጡ ናቸው።    

     

v  አቶ ማዕረጉ በዛብህ አንጋፋ ጋዜጠኛ ሲሆኑ በአሁኑ ወቅት በዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ጥናትና ምርምር ክፍል ማኔጂንግ ኤዲተር ናቸው፤

      

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
405 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 183 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us