ስለ አገር ፍቅር ትንሽ ለመወያየት

Wednesday, 17 May 2017 12:30

 

(በማዕረጉ በዛብህ)

ነገሪ ዘበርቲ “አዙሪት” በተባለችው ተወዳጅ ልቦለድ መጽሐፉ ስለ አገር ፍቅር እንዲህ ይላል።”

“እኔ ኢትዮጵያ ማለት ፅጌረዳ አበበ ነች። ውበትዋ ይማርከኛል። መዐዛዋ ያውደኛል። ልስላሴዋ ይመቸኛል። ሁሉም ለሀገሩ ያለው ስሜት ይህ ይመስለኛል። ኒውዮርኩሩም ለኒውዮርክ፣ በደዊውም ለአረብ በረሃ ያለው ስሜት እንደዚሁ ነው።

ኢትዮጵያ አያሌ የሀገር ፍቅር የተጻፉባት የተነገሩባትና የታዩባት አገር ነች። በረጅሙ የሕልውና ታሪካችን የተባሉት የሀገር ፍቅር አነጋገር ቅርሶቻችን በሙሉም ሆነ በከፊል በታሪክ ድርሳናት ወደኛ ሊደርሱ ባይችሉም (ወይም አንዳንዶቻችን ባናውቃቸውም) የኢትዮጵያ አንድነት ሕብረብሔርና መንግሥት መስራች ከሆኑት ከአጼ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት ወዲህ ግን ብዙ እንደተባለ የማወቅ ዕድል አለን። ለምሳሌ ዶ/ር አምባቸው ከበደ፤ “መጽሐፈ ጥቅስ የታወቁ ኢትዮጵያውያን ከተናገሩትና ከጻፉት” ሲል የተዘጋጀው (2007) መጽሐፍ ስላገራችን ከነገስታት እስከ ደራሲያን በተለያዩ አጋጣሚዎች የተነገሩትን ቁም ነገሮች ምንጮቻቸውንም በመጥቀስ ጭምር አቅርቦልናል። በኔ እይታ ይህ መጽሐፍ በጠቃሚነቱ ልዩ ዕውቅና ሊሰጠው የሚገባ ሥራ ነው። አገራቸውን ከሕይወታቸው አብልጠው ይወዱ የነበሩት አጼ ቴዎድሮስ “ሃይማኖት የሚፈልሱ ቀሳውስት አይምጡብኝ” (በሚያዝያ 1847 ለሳሙኤል ኤልጎባት ከጻፉት) ካሉ በኋላ “አሁንም እኔ የምፈልገው እውር ነኝና ዓይኔ እንዲበራ ጥበብ ነው” ነበር ያሉት አምባቸው እንደሚያስታውሰን።

ከሳቸው ቀጥሎ ንጉሠ ነገሥት የሆኑትና እሳቸውም ሕይወታቸውን ለውድ አገራቸው የሰውነት አጼ ዮሐንስ ፬ኛም ለአገራቸው ለኢትዮጵያ የነበራቸውን ጽኑ ፍቅር የገለጹባቸው ቃላት ታላቅ የታሪክ ጥቅሶች ሆነው የሚኖሩ ናቸው። ዮሐንስ እንዲህ ነበር ያሉት፤

“የኢትዮጵያ ልጅ ሆይ ልብ አድርገህ ተመልከት፣ ኢትዮጵያ የተባለችው አንደኛ እናትህ ናት፣ ሁለተኛ ዘውድህ ናት፣ ሦስተኛ ሚስትህ ናት፣ አራተኛም ልጅህ ናት፣ አምስተኛም መቃብርህ ናት፣ እንግዲህ የእናት ፍቅር፣ የዘውድ ክብር፣ የሚስት ደግነት፣ የልጅ ደስታ፣ የመቃብር ከባድነት እንደዚህ መሆኑን አውቀህ ተነሣ።

አጼ ዮሐንስ አራተኛ (ለሰሐጢ ዘመቻ ከተነገረ አዋጅ)

ዶክተር አምባቸው ስላገራቸው ፍቅር ከጻፉትና ከተናገሩት ኢትዮጵያውያን የ40 ሰዎችን ንግግር ወይም ጽሁፍ በ“መጽሐፈ ጥቅስ” ውስጥ ጠቅሷቸዋል። እኔ ላደርግ የሞከርኩት ደግሞ የዘመኑ ኢትዮጵያውያን ስላገራቸው ፍቅር ሰዎች ምን እንዳሉ መጠነኛ ግንዛቤ እንዲያገኙ ለማስታወስ ሲሆን በተለይ መልዕክቱ ለወጣቱ ትውልድ እንዲደርሰው ያለኝ ምኞት ከፍ ያለ ነው። የአንደኛ ደረጃ መምሕራን ይህችን ጽሁፍ ወይም ባጠቃላይ መጽሐፈ ጥቅስን ለተማሪዎቻቸው ቢያነቡላቸው ትልቅ አገራዊ ተግባር እንደፈጸሙ ሊያውቁ ይገባል። በዝች ጋዜጣዊ ጽሁፍ እኔ የመረጥኳቸው ንግግሮች ወይም ግጥሞች የራሴን ምርጫ የሚያሳዩ ናቸው እንጅ ሌላ ምክንያት የላቸውም።

አገሬ ኢትዮጵያን ጥፋት እንዳይነካት

አንተ በጥበብህ በኀይልህ ጠብቃት

ይሄ የኔ ልመና ደካማው ጸሎቴ

ለኢትዮጵያ ነው ላገሬ ለናቴ

ታላቁ ደራሲ ከበደ ሚካኤል (የክብር ዶክተር፤ ካሌብ ገጽ 68)

ታላቁ ባለቅኔና ጸሐፊ ተውኔት ጸጋዬ ገብረመድህን ቀዌሳ በልዩ ልዩ ታሪካዊ ግጥሞቹ /ቅኔዎቹና ከማይጠገቡት የተውኔት ጽሁፎቹ ዶ/ር አምባቸው የጠቀሰው የሚከተለውን (ጴጥሮስ ያችን ሰዓት) ሰቆቃው ጴጥሮስ 1963ን) ነው።

“ባክሽ እመብርሃን - ባክሽ ምስለ ፍቁር ወልዳ፣

ጽናት ስጪኝ እንድካፈል - የናቴን የኢትዮጵያን ፍዳ

ከነከሳት መርዝ እንድቀምስ - ከነደደችበት እቶን

የሷን ሞት እኔ እንድሞት - ገላዬ ገላዋ እንዲሆን።

ቀጥሎ “እኔ ሴት ነኝ፣ ጦርነት አልወድም ሆኖም ይህንን ኢትዮጵያን የኢጣሊያ ጥገኛ የሚያደርግ ውል ከመቀበል ጦርነትን እመርጣሁ” የሚለውን የእቴጌ ጣይቱ ብጡል ከታደሰ ዘወልዲ (የእቴጌ ጣይቱ ብጡል አጭር የሕይወት ታሪክ 1974) ነው አምባቸው የጠቀሰልን። ማሳሰቢያ፡- በዚች ጋዜጣዊ ጽሑፍ ንግግሮቹን ያስቀመጥኩበት ቅድመ -ተከተል ምርጫ የራሴ ነው።

“ሕይወቱን ሰውቶ የሞተ ላገሩ

ዘላለም ይኖራል ነፃነቱ ክብሩ” ሲሉ ታላቁ ገጣሚና ጸሐፈ ተውኔት ዮፍታሔ ንጉሤ በ1928 በጻፉት ግጥማቸው መርሰኤ ኃዘን ወ/ቂርቆስም በተደናቂው ታሪካዊ “አማርኛ ሰዋሰው” መጽሐፋቸው የሚከተለውን ጥልቅ ምስጢር የያዘውን

“አገሬ ተባብራ ካልረገጠች እርካብ

ነገራችን ሁሉ የእምቧይ ካብ፣ የእምቧይ ካብ” ይላሉ።

ወደ ዘመነ ኃይለሥላሴ ምሁራን ስንመጣ ደግሞ፣ ከዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ጀምሮ እስከ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአማርኛ ቋንቋ አስተማሪ የነበሩት አቶ ዓለማየሁ ሞገስ “ሀገር ምንድናት” በተባለችው (1958) መጽሐፋቸው

“ሀገሩን ከሸጠ ለራሱ ጥቅም

እንስሳ ነው እንጅ ሰው አይባልም”

“ከሃይማኖት በልጦ ዓለምን የሚገዛ እንደ ሀገር ፍቅር ያለ ትልቅ ፍልስፍና የለም” ይሉናል።

ኢትዮጵያውያን የሀገርን ፍቅር የሚያዩበት ዓይነ ሕሊና ብዙ ነው። ሁሉም ግን አንድ የሚያደርጋቸው የሀገርን ፍቅር ሁሉም እጅግ የተከበረ ዕንቋዊ የታሪክ ንብረት አድርገው ማየታቸው ነው።

የ“ቴዎድሮስ ታሪካዊ ድራማ (1942)” ጸሐፊ ተውኔትና ደራሲ የነበሩት ደጃዝማች ግርማቸው ተክለሐዋርያት ምሁራዊ ምክር የሚከተለው ሲሆን፤

“አወይ ያገሬ ሰው ስማኝ ልንገርህ

መለያየት ትተህ ባንድ ካልሠራህ

ተንቀህ ተዋርደህ በገዛ አገርህ

ይመጣል ጨካኙ ባዕድ ሊገዛህ” በማለት ሕዝቡን ሲያስጠነቅቁ፤

“አውቀን እንታረም” (1967) የተባለው መጽሐፍ ደራሲ ሌፍተናንት ጀኔራል አቢይ አበበ፤ “የአንድ ሀገር ነፃነትም መብትም የሚጠበቀው በሕዝብ ሕብረት ነው” በሚለው ንግግራቸው በሥራ ባልደረቦቻቸው ይታወቃሉ።

በቀዶ - ጥገና የሕክምና ሙያ በዓለም አንቱ ከተባሉት ሰዎች አንዱ የነበሩት ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ለአገራቸው የነበራቸው ፍቅር ለሙያቸው ከነበራቸው ዕውቀት ስፋትና ጥልቀት ያላነሰ ነበር። ስለኢትዮጵያ ከተናገሩዋቸው አበይት ንግግሮች አንድ ሁለቱን ለመጥቀስ የሚከተሉትን ይመለከትዋል፤

“ትውልድ ያልፋል፣ ሀገር ግን የታሪክና የትውልድ መድረክ በመሆን ታሪክን እያስተናገደች ትኖራለች” ሲሉ መስከረም 7 ቀን 1985 ለኢትዮጵያ ጀግኖች ማኀበር የሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ ከጻፉት ደብዳቤ የሚጠቀስ ሲሆን፤ በባሕርዳር ከተማ የመኢአድ መስራች ጉባኤ ላይ ሰኔ 13 ቀን 1984 ባስተላለፉት መልዕክት ደግሞ፤ “ከሁሉ በፊት የአንድ ሕዝብ ሉዓላዊነት በአንድ አገር ሕጋዊ ክልል ውስጥ የሚረጋገጥ ነው” ብለው እንደነበር ኢትዮጵያ በአክብሮት ስታስታውሳቸው ትኖራለች።

ፕሮፌሰር አስራት ታህሣሥ 11 ቀን 1985 በደብረ ብርሃን ከተማ ካደረጉት ንግግር የሚጠቀስ አቢይ አነጋገር የትናንትና ትዝታችን ያስታውሰናል።

“የኢትዮጵያ ጠላቶች ኢትዮጵያን ለማጥፋት ሲያቅዱና ሲዘምቱ ለረጅም ጊዜ የኖሩ ቢሆንም እንደዛሬው ባዶዋን ያገኙበት ጊዜ አልነበረም” ብለዋል።

የዝችን የሀገር ፍቅር ማስታወሻ ትዝታ በሌላ ጊዜ እስከማቀርብ ለዛሬው አንባቢዎችን በታላቁ ገጣሚና የስነ ስዕል ጠቢብ በገብረክርስቶስ ደስታ ግጥም ልሰናበታችሁ።

“አገሬ አርማ ነው የነፃነት ዋንጫ

በቀይ የተጌጠ ባረንጓዴ ቢጫ

እሾህ ነው አገሬ

በጀግናው ልጅ አጥንት የተከሰከሰ

ጠላት ያሳፈረ አጥቂን የመለሰ። (ሀገሬ ገጽ 130)

           

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
389 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 829 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us