ጥቂት ነጥቦች ስለወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ

Wednesday, 07 June 2017 13:57

-    ልደት በ90 ቀናት፤ ጋብቻ፤ ፍቺና ሞት በ30 ቀናት ዉስጥ መመዝገብ አለበት

የሰዉ ልጅ ወደ አለም በህይወት ከተቀላቀለበት ሰአት ጀምሮ ብዙ የሚያልፍባቸዉ ተፈጥሯዊ እና ማህበራዊ ለዉጦች አሉ:: ከነዚህም መካከል ልደትን ጨምሮ ጋብቻ ፍቺ እና ሞት በዋነኝነት ተጠቃሾች ናቸዉ። እኝህ ኩነቶች ዋና እና ወሳኝ የተባሉበት ምክንያት ኩነቶቹ የሚያመጡት ለዉጥ ከግለሰብ አልፎ ሀገራዊ ፋይዳም ስላለዉ ነዉ።

በአለማችን የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ታሪካዊ አመጣጥ ስንመለከት ለወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ መፈጠር እና ማደግ መሰረት የሀይማኖት ተቋማት መሆናቸዉ ይታወቃል። ሆኖም ተቋማቱ ይመዘግቡ የነበረዉ ኩነቱን ሳይሆን ኩነቱን ተከትሎ የሚመጣዉን ስርአት ነበር። ለምሳሌ ልደቱን ሳይሆን ክርስትናዉን፣ ሞቱን ሳይሆን ቀብሩን እንዲሁም ጋብቻዉን ሳይሆን ሰርጉን ነበር።

የተለያዩ የታሪክ መዛግብት እንደሚያሳዩት ከክርስቶስ ልደት በፊት በግሪክ እና በሮም በግልጽ በመንግስት ደረጃ ምዝገባዎች ይደረጉ የነበረ ሲሆን የምዝገባዉ አላማ ግን ለዉትድርና የሚመለመለዉን ሰብአዊ ሀብት ለማወቅ እና የመንግስቱን ሀይል ለማጎልበት ነበር። የታሪክ መዛግብቱ እንደሚገልፁት የኩነቶች ምዝገባ ከክርስቶስ ልደት በኋላም የቀጠለ ሲሆን እ.አ.አ በ720 በጃፓን የተወሰኑ ቦታዎች የልደት፣ የሞት እና የጋብቻ ምዝገባ ይካሄድ የነበረ ሲሆን በኋላም ከ15ተኛዉ ክ/ዘመን ጀምሮ በስፔን፣ በእንግሊዝ፣ በፈረንሳይ እንዲሁም በ17 ክ/ዘመን በስዊድን፣ በካናዳ፣ በፊንላንድ እና በዴንማርክ በየአድባራቱ እና ቤተክርስቲያናቱ የጥምቀት፣ የሰርግ እና የቀብር ስርአቶች እንዲመዘገቡ ይደረግ ነበር። በአፍሪካ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ አመሰራረትና እድገት ታሪክ ከቀኝ ግዛት ጋር የሚያያዝ ነዉ። ቀኝ ገዥዎች አፍሪካን በቀኝ ግዛት ሲይዙ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ አሰራርንም ይዘዉ ገብተዋል:: በዚህም ምክንያት አንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት በዘመናት የሚቆጠር የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ታሪክ አላቸዉ። ለምሳሌ ሞሪሺየስ እና ጋናን መጥቀስ ይቻላል። ሆኖም የአፍሪካ ሀገራት በቅኝ ግዛት ስር በነበሩበት ጊዜ የነበረዉ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አሰራር አግባባዊዉን መንገድ ያልተከተለና የቅኝ ገዥ ሀገራቱን ዜጎች ብቻ የሚመለከት የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ስርአት ሆኖ ነበር። አፍሪካ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባን ለራስዋ አህጉራዊ ችግር አድርጋና በከፍተኛ የመንግስትና የፖለቲካ አካላት መነጋገር የተጀመረዉ እ.አ.አ ከ2009 ጀምሮ ነዉ። በዚህም ጥረት የመጀመሪያዉ የአፍሪካ ሚንስትሮች ጉባኤ እ.አ.አ በ2010 በአዲስ አበባ አስተናጋጅነት ተካሂዷል። ስለሆነም ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት ሁሉን አቀፍ በሆነ መንገድ ጥናት እንዲያደርጉ በተስማሙበት መሰረት እያከናወኑ ይገኛሉ።

በኢትዮጵያ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ስርአት ለማቋቋም የተሞከረዉ በአፄ ሚኒሊክ ዘመነ መንግስት ሲሆን ሀገሪቱ የወሳኝ ኩነቶችን የምዝገባ ህግ ድንጋጌዎች ለመቀበል የሞከረችዉ በ1952 በወጣዉ የፍትሐብሄር ህግ መሰረት ሆኖ በሀገሪቱ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባን ለመዘርጋት ተብለዉ ከ100 በላይ አንቀፆች እንካዲተቱ ተደርጓል። ሆኖም በዚህ ህግ የህዝብ ክብር መዝገብ የሚመለከቱ አንቀፆች በቁጥር 336 /1/ ስለ አፈፃፀማቸዉ የተለየ ደንብ እስከሚወጣ እንዳይተገበሩ በመታገዳቸዉ ላለፈዉ ግማሽ ምእተ-አመት አንቀፆቹ ሳይተገበሩ እና ሀገሪቱም ከወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ማግኘት የነበረባትን ህጋዊ፣ አስተዳደራዊና ስታትስቲካዊ ጠቀሜታ ሳታገኝ ቆይታለች። ሆኖም የኩነቶች ምዝገባ የፍትሐብሄር አካል  ከመሆኑ በፊት አዲስ አበባን ጨምሮ በአንዳንድ ከተሞች መዘጋጃ ቤቶች ከ1930 ዓ.ም ጀምሮ በአገልግሎት ፈላጊዉ ጠያቂነት የኩነቶችማለትም ልደት፣ጋብቻ እና ሞት ማስረጃ  የመስጠት ተግባራት ሲከናወን ቆይቷል። በመሆኑም መንግስት የወሳኝ ኩነት ምዝገባ የሚኖረዉን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ በመረዳት አለም አቀፍ ደረጃዉ የጠበቀ የምዝገባ ስርአት እንዲገነባ በአዋጅ እና በደንብ እንዲቋቋም አድርጓል። በአዋጁ ላይ እንደተጠቀሰዉ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ስርአትን በሀገር አቀፍ ደረጃ መገንባት ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን ለማቀድ፣ አገልግሎቶችን ዜጎች ማግኘት እንዲችሉ ለማድረግ፤ በፍትህ አሰራር ቀልጣፋና ዉጤታማ አሰራር እንዲኖር ለማስቻል እና ሁሉን አቀፍና አስገዳጅ ምዝገባ ስርአት ለመገንባት ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል።

የወሳኝ ኩነት ምዝገባ እና ብሄራዊ መታወቂያ አዋጅ ቁጥር 760/2004 ለወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ስርአት መሰረቱን የጣለ ሲሆን አዋጁን ተከትሎ በወጣዉ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 278/2005 መሰረት የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጀንሲ ተቋቁሟል። የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጀንሲ ማቋቋሚያ የሚንስትሮች ምክር ቤት ደንብ አግባብ ካላቸዉ የፌደራል መንግስት መስሪያ ቤቶችና የክልል አካላት የተዉጣጡ ምክር ቤት አባላት እንዲሚሰየሙ ይደነግጋል። ይህን መሰረት በማድረግ ጥቅምት 11 ቀን 2006 ዓ.ም ከሁሉም ክልሎች፣ ከተማ መስተዳድሮችና ከስራዉ ጋር ተያያዥነት ካላቸዉ የፌደራል ተቋማት የተዉጣጣ በጠቅላላዉ 35 አባላት ያሉት አገር አቀፍ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ምክር ቤት ተቋቁሟል።

በደንብ ቁጥር 278/2005 በአንቀጽ 8 እና 9 መሰረት የፌዴራል ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጀንሲን ስራዎች በበላይነት የሚመራ ቦርድ እንደሚቋቋም ያስቀምጣል። የቦርዱ አባላት እና ሰብሳቢው በመንግስት የሚሰየሙ እንደመሆናቸው ስብጥሩ ከምክር ቤቱ ጋር ተመሳሳይ እንደሚሆን ይጠበቃል። ፍትህ ሚኒስቴር (የአሁኑ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ)፣ ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ፣ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ከተማ ልማት እናየኮንስትራክሽንሚኒስቴር፣ብሄራዊ መታወቂያ ኤጀንሲ፣የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ልማት ሚኒስትር እንዲሁም የሴቶችህፃናትእናወጣቶችጉዳይሚኒስቴር ከወሳኝኩነትምዝገባኢጀንሲጋርቀጥተኛየስራግንኙነት ያላቸው ተቋማት ናቸው። በመሆኑም የቦርዱ አባላት ከነዚህ ተቋማት የተዉጣጡ በመሆኑ የኤጀንሲውን ስራ ለማቀላጠፍ ያግዛል።

የፌዴራል ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጀንሲ እራሱን የቻለ በሃገር አቀፍ ደረጃ የወሳኝ ኩነቶችን ምዝገባ የሚመራ፣ የሚያስተባብር እንዲሁም በማዕከል የምዝገባ ሰነዶችን የሚያከማች ተቋም ሆኖ ተቋቁሟል። የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ስራን በክልል ደረጃ የሚመራ፣ የሚያስተባብር እና ድጋፍ የሚሰጥ እንዲሁም የምዝገባ ሰነዶችን ወደ ፌዴራሉ ኤጀንሲ የሚያስተላልፍ በክልል ደረጃ የሚቋቋም ተቋም አስፈላጊ በመሆኑ ክልሎች እና የከተማ መስተዳድሮች ተመሳሳይ ህጎችን በማውጣት ተቋሙን አደራጅተዋል።

በኢትዮጵያ የህዝብ አስተዳደር እርከን ተዋረድ መሰረት ለህዝብ ቅርብና ተደራሽ የሆኑት ዞን፣ ወረዳ እና ቀበሌ በመሆናቸዉ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ፅ/ቤቶችን በዞን፣ በወረዳ እንዲሁም በቀበሌ ደረጃ ማቋቋም አስፈላጊነቱ የማያጠራጥር ነዉ። ስለሆነም ሁሉም ክልሎች እና የከተማ መስተዳደሮች እስከመጨረሻዉ የአስተዳደር እረከኖች ድረስ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ፅ/ቤቶችን በመዘርጋት ለስራዉ ዝግጁ ሆነዉ ይገኛሉ። በአሁኑ ሰአት የቀበሌ ስራ አስኪያጆች የክብር መዝገብ ሹም ሆነዉ የሚሰሩ ሲሆን ከ 94 በመቶ በላይ የቀበሌ ስራ አስኪያጆች በወሳኝ ኩነት መሰረታዊ ፅንሰ ሃሳብ፣ አዋጅ ህጎች እና መመሪያዎች ዙሪያ ስልጠና ወስደዋል።

የምዝገባዉን ስርአት በአስተማማኝ ሁኔታ ለማስኬድ የተለያዩ መንግስት አካላት፣ ባለድርሻ እና ተባባሪ አካላት የበኩላቸዉን ሚና እንዲወጡ የሚያስፈልግ ሲሆን በዋነኝነት ህብረተሰቡ ኩነቶች እንደተከሰቱ በተቀመጠላቸዉ ጊዜ ማለትም ልደት በ90 ቀናት፤ ጋብቻ፤ ፍቺና ሞት በ30 ቀናት ዉስጥ በማስመዝገብ ኃላፊነቱን መወጣት እና የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ስርአት ከሚያስገኘዉ ከፍተኛ ጠቀሜታ ተካፋይ መሆን አለበት። 

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
1203 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 791 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us