የሰሚ ያለህ?!

Wednesday, 14 June 2017 12:57

 

የዕውቁ ኢትዮጵያዊ አርበኛ፣ ዲፕሎማትና ደራሲ የክቡር ዶ/ር ሀዲስ አለማየሁ መኪና በቅርስነት መጠበቅ ሲገባት የስጥ ማስጫ የሆነችው በምን ምክንያት ይሆን?!


ለታሪኩ ለሥልጣኔው፣ ለባህሉ፣ ለቅርሱ ባዕድና እንግዳ የሆነ ትውልድ ከራሱ ከማንነቱ እየሸሸና እየተንሸራተተ የራሱን ንቆ የሌላውን ናፋቂ የመሆኑ ጉዳይ ብዙ የተባለበት፤ የተጻፈበት ነው። ባለፈው ሳምንት የሸገር ሬዲዮ ባልደረባ የሆነው ጋዜጠኛ ወንድሙ ኃይሉ በልዩ ወሬው ዝግጅቱ ዕረቡ ማለዳ ላይ አንድ አሳዛኝ የሆነ ዜና አሰምቶን ነበር።


ይኸውም ለዕውቁ ኢትዮጵያዊ ለአርበኛውና ለዲፕሎማቱ ለደራሲ ለክቡር ለዶ/ር ሀዲስ አለማየሁ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ በተቋቋመው ትምህርት ቤት ውስጥ ለረጅም ዓመታት ይነዷት የነበረችው መኪናቸው በትምህርት ቤቱ አንድ ጥግ ላይ እንደ አልባሌ ዕቃ ተጥላና ወድቃ፣ ቀንና ሌሊት ፀሐይና ብርድ እየተፈራረቀባት፣ ዝጋና ወላልቃ በአራሙቻ ተውጣ ይባስ ብሎም ደግሞ ዕጣ ፈንታዋ የስጥ ማስጫ የመሆኗን አሳዛኝ ዜና ነበር ሸገር በልዩ የወሬው ጊዜው ያረዳን።


ጋዜጠኛ ወንድሙ ኃይሉ ልዩ ወሬ እንዳተተውም የትምህርት ቤቱ አስተዳደር የእኝህን ታላቅ ደራሲና ዲፕሎማት ታሪካዊ መኪና በተመለከተ ብዙም ትኩረት አለመስጠቱንና በትምህርት ቤታቸውም ያሉ አብዛኛው ተማሪዎቻቸውም ክቡር ዶ/ር ሀዲስ አለማየሁን በተመለከተ ስለ ታሪካቸውና ሥራዎቻቸው እምብዛም እንደማያውቁ  ነበር ከጋዜጠኛ ወንድሙ ጋር በነበራቸው አጭር ቆይታቸው የገለጹት። እስቲ በዚህ ጉዳይ ላይ ጥቂት ጥያቄዎችን እናንሳ።


ለመሆኑ ክቡር ዶ/ር ሀዲስ አለማየሁ ለስማቸው መታሰቢያ ይሆን ዘንድ በተቋቋመው ትምህርት ቤት ሥራቸውና ታሪካቸው ነገ የሀገራቸው ተስፋ ለሆኑ ወጣቶች ባዕድና ባይተዋር መሆኑ ከማንገብገብም ከማስቆጨትም በላይ ለምን ብለን እንድንጠይቅ እንገደዳለን። ለመሆኑ የትምህርት ቤቱ አስተዳደርም ሆነ የትምህርት ቤቱ የአማርኛ ቋንቋ እና የታሪክ መምህራን የእኝህን ታላቅ ኢትዮጵያዊ ታሪካቸውንና ሥራዎቻቸውን ለተማሪዎቻቸው በማስተዋወቅ ረገድ ምን ያህል ሠርተዋል ወይም ምን እየሠሩ ነው?!


ለመሆኑ በትምህርት ቤቱ ስያሜውን በእኝህ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ስም ከማድረግ ባለፈ እንዴት ለአንድ ቀን እንኳን ክቡር ዶ/ር ሀዲስ አለማየሁን በሥራዎቻቸው የሚዘከሩበት የሚታወሱበት ውይይትና የሐሳብ ልውውጥ የሚደረግበት መድረክ አይኖረውም ወይም ለመፍጠር ጥረት አላደረገም ማለት ነው?!


በመሠረቱ መቼም ትምህርት ቤቱ በክቡር ዶ/ር ሀዲስ አለማየሁ ስም በተማሪዎች መካከል የሥነ ጽሑፍ፣ የፈጠራና ሌሎች ስፖርታዊ ውድድሮች በማድረግ በተማሪዎቻቸው ልብ ውስጥ እኝህን ታላቅ ሰው ስማቸውና ታሪካቸው ሕያው እንዲሆን ለማድረግ ቢጥር የትምህርት ቤቱ አስተዳደር፤ "ተማሪዎቻችን ስለ ደራሲ ሀዲስ አለማየሁ ብዙም የሚያውቁት ነገር የለም...!" የሚል እንዲህ ዓይነቱን አሳፋሪ ምላሽ አይሰጥንም ነበር ለማለት እደፍራለሁ። ትምህርት ቤቱ ክቡር ሀዲስ አለማየሁ የነበረችው መኪናቸው ለስማቸው መታሰቢያ ይሆን ዘንድ በተቋቋመው የዕውቀት ገበያ ግቢ ውስጥ ሳር በቅሎባትና የስጥ ማስጫ እስክትሆን ድረስ ምን እየጠበቀ እንደነበር ከማስገረምም አልፎ በእውነት የሚያስቆጭ ነው።


ትምህርት ቤቱ መኪናዋን በቅርስነት መንከባከብና መጠበቅ አቅም ባይኖረው እንኳን ጉዳዩን ለሕዝብና ለሚመለከተው የመንግሥት አካል ለማሳወቅ ምን ጥረት፤ ምን እንቅስቃሴ አድርጓል። በግሌ እንደማውቀውና እንዳለኝ መረጃ የክቡር ዶ/ር ሀዲስ አለማየሁ የድርሰት ሥራዎቻቸው ረቂቅ የእጅ ጽሑፎቻቸውና ሌሎች ጥቂት ንብረቶቻቸው በክብር በአደራነት ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም መሰጠቱን አውቃለሁ። በአንድ ወቅትም ተቋሙ ለሕዝብ ዕይታ ክፍት እንዲሆን ዐውደ ርእይ/ኢግዝቢሽን አዘጋጅቶም ነበር። የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም በተጨማሪም የሀገራችን ታላላቅ ደራሲ የሆኑትን የሎሬት ጸጋዬ ገ/መድኅን፣ የአብዬ መንግሥቱ ለማን እና የጳውሎስ ኞኞን ሥራዎችንና በቅርስነት መጠበቅ የሚገባቸውን ንብረቶቻቸውን በክብር ተረክቦ ማስቀመጡን አውቃለሁ።


ስለሆነም የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም አሊያም ብሔራዊ ቤተ መዘክር/ሙዚየም የኢትዮጵያዊውን አርበኛ፣ የትምህርትና የአስተዳደር ባለሙያ፣ ዕውቅ ዲፕሎማትና ደራሲ የክቡር ዶ/ር ሀዲስ አለማየሁን መኪና ከትምህርት ቤቱ በአደራ ተረክቦ ተገቢውን እደሳ በማድረግ በቅርስነት ሊጠብቀው ይገባል። ሌላው ዓለም ታላላቅ ደራሲዎቻቸው የጻፉበትን ብዕራቸውንና የተቀመጡበትን መቀመጫ ሳይቀር እንኳን በክብር በቅርስነት ጠብቀው ሕዝባቸውን ለማስተማርና ለቱሪዝም ገቢ አድርገው ሲጠቀሙበት እኛ ብዙም የነቃን አይመስልም። ቅርሶቻችን ለሀገራችን ልማትና ለቱሪዝም ዕድገት ያላቸው ፋይዳ ትልቅ ነው እያልን በተቃራኒው ቅርሶቻችን ተረስተውና ወድቀው ሲበላሹ እያየን ዝም ማለት አይገባንም።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
212 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 933 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us