የሚያዝበትገንዘብ በደብተሩ ሳይኖር ቼክ መፈረም ያለው ጉዳት

Thursday, 13 July 2017 14:32

 

ክብረት ካህሳይ
ከፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

 

የሚያዝበት ገንዘብ በደብተሩ ሳይኖር ቼክ መፈረም ያለው ጉዳት ምን እንደሚመስል የችሎት መረጃ አጣቅሰን እንዲሁም የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ህግ ጥናት ማርቀቅና ማስረጽ ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ ባለሙያ አነጋግረን በሚከተለው መንገድ አቅርበነዋል፣ መልካም ንባብ።


የሚያዝበት ገንዘብ በደብተሩ ሳይኖር (አምስት መቶ ሰማንያ ስድስት ሺ ሶስት መቶ) ብር ቼክ ፈርሞ ለሌላ ግለሰብ የሰጠው ተከሳሽ በእስራት መቀጣቱ የችሎቱ ውሎ የያዘው መዝገብ ያትታል። ወንጀሉ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 693/1/ ስር የተመለከተውን በመተላለፍ ኑሪ ተማም ሱሩር የተባለ ግለሰብ መከሰሱ የልደታ ፍትህ ጽ/ቤት የዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ ዝርዝር ያትታል።


የወንጀሉ ዝርዝሩ እንደሚያብራራው ተከሳሹ ቼኩ በሚያወጣበት ቀን ወይም ለክፍያ ለባንክ በሚቀርብበት ጊዜ የሚያዝበት በቂ ገንዘብ አለመኖሩን እያወቀ በሐምሌ 15 ቀን 2006 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 6፡00 ሰዓት ሲሆን በልደታ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 09/10 ክልል ልዩ ቦታው ጭድ ተራ ተብሎ ከሚጣራው አካባቢ ከግል ተበዳይ አቶ ሳልህ ርስቀይ ብረት ገዝቶ ክፍያውን ከአዋሽ ኢንተርናሸናል ባንክ ሞጆ ቅርንጫፍ ከአካውንት ቁጥር 002 ከ15/12/2006 ዓ.ም ጀምሮ የሚመነዘር የ586300 (አምስት መቶ ሰማንያ ስድስት ሺ ሶስት መቶ) ብር በቼክ ቁጥር ABY (ኤቢዋይ) 4200714 ጽፎ እና ፈርሞ የግል ተበዳይ በቼኩ ጀርባ ላይ ስማቸውን ጽፎ እና ፈርሞ ለአቶ መሀመድ ሱልጣን ገንዘቡን እንዲያወጡ ሰጥቷቸው ይሄዳል።


አቶ መሀመድ አገር ሰላም ብለው ገንዘቡን ለማውጣት ከአዋሽ ኢንተርናሸናል ባንክ ሞጆ ቅርንጫፍ ሲሄዱ ባንኩ በቂ ገንዘብ የለውም ብሎ ማረጋገጫ ሰጥቶ የመለሳቸው በመሆኑ የሚያዝበት በቂ ገንዘብ ሳይኖር ቼክ ማውጣት ወንጀል አቶ ኑሪ ተማም ከስሻቸዋለሁ ይላል የፌዴራል ዐቃቤ ህግ።


የዐ/ህግ ማስረጃ መርምሮ የቀረበለትን ሰነድ መዝኖ እንዲሁም የተከሳሽ ቃል ያዳመጠው የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 8ኛ ወንጀል ችሎት ተከሳሽ ጥፋተኛ ነው በማለት በ3 ዓመት ከ3 ወር ፅኑ እስራት እና 3100 (ሶስት ሺህ አንድ መቶ ብር) እንዲቀጣ ውሳኔውን አስተላልፏል።
ይህንን በተያያዘ በሌላ ችሎት ላይ የታየ የወንጀል ተግባር ደግሞ እንመልከት።


ተከሣሽ አሸብር አድማሱ ይባላል። ዕለቱ ሚያዝያ 12 ቀን 2ዐዐ7 ዓ.ም. ከቀኑ 8፡ዐዐ ሰዓት ነበር። ተከሣሽ በቂና የሚያዝበት ገንዘብ በባንክ አለመኖሩን እያወቀ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዐ7 ልዩ ቦታው ጉርድ ሾላ ቀበሌ መዝናኛ ፊት ለፊት ለግል ተበዳይ ለገሰ ከበደ በቼክ ቁጥር ኦ.ዋይዐዐዐ625245 በሆነ የቼክ ቅጠል ላይ ብር 2ዐዐ,ዐዐዐ/ ሁለት መቶ ሺህ ብር ከኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ሆራ ቅርንጫፍ በ12/1ዐ/ዐ7 ዓ.ም እንዲከፈል ፅፎና ፈርሞ ሰጠው። የግል ተበዳይም በ13/11/ዐ7 ዓ.ም ቼኩን ለባንኩ ሲያቀርብ በቂ ገንዘብ የሌለ መሆኑን ከባንኩ ተገለጸለት።


በዚህም ምክንያት በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 693/1/ ሥር የተመለከተውን በመተላለፍ የሚያዝበት ገንዘብ ሳይኖር ቼክ መስጠት ወንጀል የቦሌ ፍትህ ጽ/ቤት ዐቃቢ ሕግ ጉዳይን አጣርቶና መርምሮ ክስ መሠሰረተበት።


ዐቃቢ ሕግ ነሐሴ 15 ቀን 2ዐዐ7 ዓ.ም ክሱን ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ ወንጀል ችሎት አቀረበ። ክሱ የቀረበለት ፍርድ ቤትም ከግራ ቀኙ የቀረቡለትን የሰነድና የሰው ማስረጃዎች ከመረመረ በኋላ ተከሳሽ ጥፋተኛ ነው በማለት ጥቅምት ዐ3 ቀን 2ዐዐ8 ዓ.ም በዋለው ችሎት በ3ዓመት ከ3ወር ጽኑ እስራት እና በብር 3ዐዐዐ /ሶስት ሺህ ብር/ እንዲቀጣ ወስኖበታል። በአካውንት በባንክ ደብተር ውስጥ ገንዘብ ሳይኖር ቼክ መፈረም የወንጀል ተግባር መሆኑን ከላይ በተጠቀሱ የችሎት ውሎዎች መረዳት ይቻላል።ከዚህም በተጨማሪ በተጻፈ ቼክ ላይ ሀሰተኛ ቁጥር መጨመርም ከህግ ፊት እንደሚያስቆም ተከታዩ የችሎት ጉዳይ መመልከት ለዛሬው ርእሳችን የሚያጠናክር አስተማሪ ሀሳብ አለው።


የጌታወርቅ ታደሰ ትባላለች። በ1996 ዓ/ም የወጣውን የኢፌድሪ የወንጀል ህግ አንቀፅ 696(ለ) የወንጀል ህግ አንቀፅ 27/2/ 696(ለ) የወንጀል ህግ አንቀጽ 382(1) እንዲሁም አንቀጽ 382(1)) ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ ወንጀል መከሰሷ የልደታ ፍትህ ጽ/ቤት ዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ ያትታል።


የወንጀሉ ዝርዝር እንደሚያስረዳው ተከሳሿ የማይገባ ብልጽግና ለራሷ በማሰብ ሰኔ 30/2006 ዓ.ም ከቀኑ በግምት 8፡00 ሰዓት ሲሆን በልደታ ክ/ከተማ ወረዳ 1 ክልል ልዩ ቦታው ምድር ሀይል ግቢ ውስጥ አንድ ሺ ሁለት መቶ ሃምሳ አራት /1,254/ ብር ከባንክ እንድታወጣ ቁጥሩ 2899686 የሆነ ቼክ ተቀብላ በዚሁ ቼክ ላይ በፊደል ከተጻፈው ፊት ለፊት ላይ ሰባ/70/ እና በቁጥር ከተፃፈው ፊት ለፊት ላይ ሰባት/7/ ጨምራ በመጻፍ ሰባ አንድ ሺ ሁለት መቶ ሃምሳ አራት /71,254/ ብር በ02/11/2006 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቂርቆስ ቀበሌ ቅርንጫፍ ያወጣች በመሆኑ በፈፀመችው ከባድ የማታለል ወንጀል ተከሳለች።


ይህ በተያያዘም የወንጀል ህግ አንቀጽ 382(1) ስር የተመለከተውን በመተላለፍ የማይገባ ብልጽግና ለራሷ በማሰብ በፈፀመችው ቼክን ወደ ሀሰት መለወጥ ወይም ወደ ሀሰት የተለወጠውን ቼክ መገልገል ወንጀል መከሰሷ የፌዴራል ዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ ያስረዳል።


በፌዴራል ከፍተኛ ደረጃ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 20ኛ ወንጀል ችሎት ጥር 16 ቀን 2008 ዓ.ም በዋለው ችሎት ፍ/ቤቱ የዐ/ህግ ማስረጃ መርምሮ ተከሳሿ ጥፋተኛ ነች በማለት 7 ዓመት ፅኑ እስራት እና በ7000.00 /ሰባት ሺ ብር/ እንድትቀጣ ውሳኔውን አስተላልፏል።


ውድ አንባቢዎች ከላይ ለመነሻ የጠቀስናቸው ከቼክ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በበርካታ ችሎቶች ላይ አንዳንድ የህብረተሰብ ክፍሎች ተከሰው ሲቀጡ ይስተዋላል ይህንን አስመልክተን በዚህ ዙርያ የህግ ግንዛቤ እንዲኖር በማሰብ የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ህግ ማርቀቅና ማስረጽ ዳይሬክቶሬት የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ አመለወርቅ አጎናፍር በቼክ ዙርያ ተከታዩን ሙያዊ ትንተና ሰጥተውናል።


ቼክ አንድ ሰው በባንክ ውስጥ ካስቀመጠው ገንዘብ ለሌላ ሰው እንዲከፈልለት ትዕዛዝ የሚያስተላልፍበት ሰነድ ነው። ይህ ሰነድ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ቼክ ነው ብሎ ቼክነቱ ለማረጋገጥ የሚያስፈልጉ በውስጡ የያዙ መስፈርቶች አሉት። ቼኩን የሚያወጣው ሰው ፊርማ፣ ቀን፣ ምን ያህል ገንዘብ መከፈል እንዳለበት እና ሌሎችም የመሳሰሉትን ተሟልተው መጻፍ ይኖርባቸዋል። ቼክ ለመባል እነዚህ መስፈርቶች ሳያሟላ ቼክ ልንለው አንችልም።
የቼክ ባህሪ ለማየት ብንሞክር ለምሳሌ በባህሪው ክፍያን የመፈጸሚያ ሰነድ ከሚባሉት ውስጥ አንዱ ነው። ይህም ምንድን ነው ሰዎች ግብይት በሚፈጽሙበት ጊዜ ብዙ ገንዘብ ይዘው ከቦታ ወደ ቦታ እንዳይሄዱ እንዳይቸገሩ፣ ለስርቆትም እንዳይዳረጉ የሚፈጽሙት ግብይት ብዙ ገንዘብ የሚያስፈልግበት ሊሆን ስለሚችል ያንን ብር ተክቶ የሚከፈል ክፍያውን ሙሉ በሙሉ ተክቶ የሚፈጽም ሰነድ ነው።


የቼክ አላማ ከመነሻው ለክፍያ ብቻ ነው የሚውለው። ቼክ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ሲታይ በሀገራችን ህግ በሁለት መልኩ ማየት ይቻላል። የመጀመርያው በወንጀል ህግ አንቀጽ 693 ላይ የተቀመጠው በቂ ገንዘብ ሳይኖር ቼክ ፈርሞ ማውጣት ነው። ይህ ህጉ ላይ በተቀመጠው አገላለጽ መሰረት እንደሚለው ማንኛውም ሰው በሂሳብ ደብተሩ አካውንቱ ላይ በቂ ገንዘብ ሳይኖረው ቼኩን በሚያወጣበት ጊዜ ፈርሞ በሚሰጥበት ጊዜ ቼኩን የተሰጠው ሰው ቼኩን ለባንክ በሚያቀርብበት ጊዜ በቂ ገንዘብ የሌለው መሆኑን እያወቀ አንድ ሰው ቼኩን ፈርሞ የሚሰጥ ከሆነ ወንጀል ፈጽሟል ማለት ነው።


በወንጀል ህጉ መሰረት ይህ መሰሉ ወንጀል እስከ 10 ዓመትና የገንዘብ መቀጮም ጭምር ያስቀጣል። ሰዎች በግብይት ወቅት ቼኩን እንደ ክፍያ ሲጠቀሙ በአካውንት ደብተራቸው ውስጥ በቂ ገንዘብ መኖሩ አስቀድመው ማረጋገጥ ማወቅ አለባቸው። ያንን ሳያረጋግጡ አለያም እንደሌላቸው እያወቁ ቼኩን ፈርመው የሚያወጡ ከሆነ በባንኩ ውስጥ አለያም በአካውንቱ ውስጥ ገንዘብ ከሌለ ያ ሰው በወንጀል ተጠያቂ ይሆናል።


ይህ በቂ የሆነ ገንዘብ መኖር አለበት ብሎ ህጉ የሚያስቀምጠው በሁለት ሁኔታዎችን ነው። የመጀመሪያው ቼኩን የሚያወጣው ሰው ወይም ፊርማ የሚሰጥ ሰው ቼኩን የፈረመበት ጊዜ ለሚከፍለው ሰው ለሚፈርመው ሰው የሚሰጥበት ቀን አለ። በዛ ሰዓት ባባንኩ ውስጥ በቂ ገንዘብ እንደሌለው የሚያውቅ ከሆነ ያስቀጣዋል። ወይም ደግሞ በዛን ሰዓት ኖሮት እንኳን ቼኩን የተቀበለው ሰው ሄዶ ባንክ ቼኩን በሚያቀርብበት ጊዜ እንዲከፈለው ሲጠየቅ በቂ ገንዘብ እንደሌለው ካወቀ አሁንም ተጠያቂ ይሆናል። በ2 ጊዜዎች ነው ተጠያቂ የሚሆነው። ምናልባትም ቼኩ የተሰጠው ሰው በንግዱ ህጉ ባለው ድንጋጌ መሰረት እስከ 6 ወር ያንን ቼክ ባንክ አቅርቦ ክፍያ መጠየቅ ይቻላል። በ6ወሩ ውስጥ ቼኩን ተፈርሞ እስከ 6 ወር ድረስ ለባንክ የማቅረብ መብት አለው። ቼክ የተቀበለው ሰው በዚህ ጊዜ ውስጥ በፈለገው ጊዜ ውስጥ የመሄድ መብት ስላለው ቼኩ የተቀበለው ሰው በነዚህ 6 ወራት ውስጥ ሂሳብ ውስጥ ገንዘብ ከሌለ ቼኩን ያወጣው ሰው ተጠያቂ ይሆናል ማለት ነው።


ከዚህም ባለፈ በቸልተኝነት ወንጀልም ያስቀጣል። ምናልባት ሰውየው/ሴቷ/ ሲፈርም/ስትፈርም/ ቼኩን የተቀበለ ሰው ባንክ ቤት ሆዶ ገንዘቡን በሚጠይቅበት ጊዜ ገንዘብ እንደሚኖር ማወቅ አለበት። ከሚለው ድንጋጌ በተጨማሪ የዛን ጊዜ ብር አለኝ ወይስ የለኝም ብሎ በጥርጣሬ ማጣራት እየተገባው አለኝ የለኝም ብሎ ሳያጣራ በአካውንቱ ላይ ገንዘብ ሳይኖር በቸልተኝነት የሚፈርም ከሆነ ተጠያቂ ነው። በቂ ገንዘብ ሳይኖር ቼክን ማውጣት አንዱ የወንጀል ተጠያቂነት ነው።


ሌላው በቼክ ሰነድ ላይ የሚመጣው ወንጀል የማታለል ወንጀል ድርጊት ነው። አንቀጽ 692 ይወድቃል። ብዙ ጊዜ ሰዎች ቼክ ፈርመው ሲሰጡ በግብይት ወቅት ሲጠቀሙ በቂ ገንዘብ ሊኖራቸው አለያም ላይኖራቸው ይችላል። ቼኩን ላይ የሚያስቀምጧቸው አንዳንድ ነገሮች ለምሳሌ ፊርማ ቼኩን የሚያወጣው ሰው ፊርማ አንድ አይነት ካልሆነ ክፍያ አይፈጸምለትም። አንድ አይነት አይደለም ይባላል። ስለዚህ በዚህ ሁኔታ የቼክ ፈራሚው ወንጀል ፈጽሟል ማለት ነው። ምክንያቱም ቼኩን የሰጠው ሰው እምነት አጉድሎበታል የተሳሳተ እምነት እንዲኖረው አድርጓል። ትክክለኛ የሆነ ቼክ ነው በዚህ በሚል ያንን ቼክ የተሳሳተ እንደሰጠው በሱ እምነት ተጠቅሞበታል፣ አሳስቶታል በዛ ላይ ደግሞ የተሳሳቱ ነገሮች ተጠቅሟል በሚል በማታለል ወንጀል የሚያስጠይቅ ይሆናል።


ቼክ የሚያወጣ ሰው ብዙ ጊዜ በፖሊስ ጣብያ እና በፍርድ ቤት የሚታዩ የክስ መዝገቦች ላይ ተከሳሾች /በባንክ ሂሳብ ቁጥራቸው በቂ የሆነ ገንዘብ ሳይኖር ቼክ የሚፈርሙ ተከሳሾች የሚሰጡት ምላሽ “አለኝ ብየ ነው የፈረምኩት፣ መቼ እንዳወጣሁት አላውቅም፣ መቼ እንዳለቀብኝ አላውቅም፣ በባንክ አካውንቴ ገንዘብ አለመኖሩ አውቃለሁ። ነገር ግን ለዋስትና፣ ለመያዣ ስል ነው እንጂ ገንዘብ እንደሌለኝ አውቃለሁ ”የሚሉ ሀሳቦች ያቀርባሉ። ያም ሆነ ይህ ከተጠያቂነት አያድናቸውም።


በሀገራችን ህግ የቼክ ዋና አላማ ክፍያ መፈጸም ብቻ እንጂ ዋስትና ማስያዣ ሊያገለግል አይችልም። ህጉም ለዋስትና ይውላል ብሎ አልደነገገም።
ሰበር የሰጠው ውሳኔም ቢታይ ቼክ አገልግሎቱ ክፍያን መፈጸም ብቻ እንጂ ዋስትና መሆን አይችልም ሲል ወስኗል። ስለዚህ ሰዎች ይህንን አውቀው ቼክ ፈርመው በሚያወጡበት ጊዜ መጀመርያ በባንክ አካውንታቸው ላይ በቂ ገንዘብ መኖሩና አለመኖሩን በትክክል ማረጋገጥ አለባቸው። ካልሆነ ግን ተጎጅ የሚሆኑበት አጋጣሚ አለ።


በተበዳዮች በኩል ሲታይ ደግሞ በቼክ ክፍያ የሚቀበል ሰው ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት። ቼክ መቀበል ያለበት ሰው በጣም እምነት በሚጥልበት ሰው ላይ፣ በደምብ የሚግባባው ብዙ ግብይቶች ይፈጽምና ከዚህ በፊት መልካም ግንኙነት ያለው ጥሩ ስነምግባር ካለው ሰው አለያም እምነት ከሚጣልበት ሰው ላይ ቢሆን ይመረጣል።


ቼኩን መቀበል ያለባቸው ብዙ ጊዜ የሚያውቀው ሰው ቢሆን እንኳን ቼኩ ላይ የሚጻፉ ነገሮች ተሳስተው ሊጻፉ ስለሚችሉ ቼኩን አላወጣሁም ጠፍቶኝ ነው የሚሉ ምክንያቶች ሊመጡ ስለሚችሉ ሰዎች በዚህን ወቅት ምስክር እማኝ የሚሆኑ ሰዎች ባሉበት ማድረግ ቢችሉ እነዚህን ቅድመ ሁኔታዎችን ማድረግ የቼክ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች መከላከል ይቻላል።


በመጨረሻ አንድ ሰው የሚያዝበት ገንዘብ በደብተሩ ሳይኖር ቼክ ላይ ከመፈረሙ በፊት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባው እንዲሁም የሚያዝበት ገንዘብ በደብተሩ ሳይኖር ቼክ ላይ መፈረም ከህግ ተጠያቂነት የማያድን መሆኑን ሁሉም ሰው ማወቅ ይገባዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
308 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 941 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us