የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ በሠላማዊ ተቃውሞ ምክንያት የታሠሩ እንዲፈቱ ጠየቀ

Wednesday, 19 July 2017 13:19

 

 

እኛ የኢሶዴፓ 1ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ተሳታፊዎች የፓርቲያችንን የ5 ዓመት የሥራ እንቅስቃሴ ሪፖርት በማዳመጥ በስኬቶቻችንና በሂደቱ ባጋጠሙን ውስብስብ ችግሮች እንደዚሁም በሀገራችን ወቅታዊና ነባራዊ ተጨባጭ ሁኔታዎች ላይ በስፋት በመወያየት የሚከተለውን የአቋም መግለጫ አውጥተናል።


1ኛ፡- በደቡብ ሕብረትና በቀድሞው ኢሶዴፓ ውሕደት ሕልውናውን ያገኘው ፓርቲያችን (ኢማዴ-ደሕአፓ) የተያያዘውን ሕብረ-ብሔራዊና ሀገር አቀፋዊ አደረጃጀቱን ይበልጥ አጠናክሮ በተሟላ መልኩ ተግባራዊ በማድረጉ ረገድ አሁንም የሚቀሩን በርካታ ሥራዎች እንዳሉ በመገንዘብ ፓርቲያችን በርዕዮተ-ዓለማዊ መሠረቱ ላይ ጠንክሮ የቆመ ሀገራዊና ሕብረ-ብሔራዊ አደረጃጀቱን በመላው ሀገራችን ተግባራዊ እንዲያደርግ እንታገላለን። ስያሜውም ለዚህ ዓላማ የሚመጥን እንዲሆን በመስማማት ከዛሬ ጀምሮ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ተብሎ እንዲጠራ ወስነናል።


2ኛ፡- በተለያዩ አካባቢዎች የተዋቀሩ የፓርቲያችን አካላት ድርጅታዊ አቋማቸውና ርዕዮተ-ዓለማዊ ግንዛቤአቸው ይበልጥ እንዲጠናከርና መዋቅሩ ባልተዘረጋባቸው የሀገራችን አከባቢዎችም ዓላማችንን የሚደግፉ ዜጎችን በማደራጀት አዳዲስ መዋቅሮች እንዲዘረጉ በማድረግ፣ በከተማዎች፣ በወጣቶችና በሴቶች ከሚቴዎች አደረጃጀት ረገድ ያሉ ድክመቶች በአስቸኳይ እንዲታረሙ ለማድረግና የፓርቲያችንን የፋይናንስ አቅምም ለማጠናከር ትኩረት ሰጥተን ለመሥራት ተስማምተናል።


3ኛ፡- ኢህአዴግ በአሁኑ ወቅት በየአካባቢው ባሉት አባሎቻችንና በፓርቲያችን እንቅስቃሴዎች ላይ የሚፈጽማቸውን ሕገ-ወጥ ተጽዕኖዎች በማባባስ በብዙ አካባቢዎች ቅ/ጽ/ቤቶቻችንን ከመዝጋቱም በላይ ጽ/ቤት በሚያከራዩንም ሆነ በነጻ በሚሰጡን ዜጎች ላይ ከፍተኛ የማስፈራራትና የማንገላታት ተግባር እየፈጸመባቸው ሥራችንን የሚናከናወንበት ቢሮዎች እንዳናገኝ ከፍተኛ ተጽዕኖዎችን እያደረሰብን ይገኛል። ስለዚህም በየዞኖቹና ወረዳዎች የተዘጉብን ቢሮዎች በአስቸኳይ እንዲከፈቱና በአባሎቻችን ሕጋዊ የስራ እንቅስቃሴዎች ላይ የሚደረጉ ተጽዕኖዎች በአስቸኳይ እንዲቆሙ አጥብቀን እንጠይቃለን።


4ኛ፡- የኢህአዴግ አገዛዝ በአምባገነናዊ የከፋፍለህ ግዛ ስልቱ በመጠቀም በአካባቢ ካድሬዎቹ አማካይነት ለዘመናት አብረው የኖሩትን ሕዝቦች በየክልሎቹ በብሔር-ብሔረሰብና በእምነት ምክንያት በየጊዜው እያጋጫቸው ሰላማዊ ኑሮአቸውን የሚያናጉ ሁኔታዎችን ሲፈጥር ቀይቷል። ስለዚህም በየአካባቢው ሕዝቡን የማጋጨት ተግባር በሚሳተፉ ካድሬዎቹ ላይ ጥብቅ እርምጃዎችን በመውሰድ የሕዝባችንን አንድነትና አብሮነት እንዲያከብር አጥብቀን እንጠይቃለን።


5ኛ፡- የኢህአዴግ አገዛዝ በአሁኑ ወቅት ከሕዝባችን አቅም በላይ በሆኑ የተለያዩ መዋጮዎች፣ የማዳበሪያ ዕዳና ከአቅማቸው በላይ በሆነ የግብር ጫና አማካይነት የሕዝባችንን የኑሮ ውድነት እጅግ እያባባሰው ይገኛል። ስለዚህም ከእነዚህ በተለይም ከድህነት ያልተላቀቀውን ህዝባችንን ሰቆቃ እያባባሱ እያማረሩት ከሚገኙ ተግባራቱ እንዲቆጠብ አጥብቀን እንጠይቃለን።


6ኛ፡- የሀገራችን የፖለቲካ ምህዳር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠበበና ወደ አስቸጋሪ ሁኔታ እየወረደ መሄዱ እጅግ አሳስቦናል። ይህንኑ የሀገራችንን ችግሮች በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ አግባብ በሚደረግ ድርድር በዘላቂነት ለመፍታት እንዲቻል ፓርቲያችን ከመድረክ አባል ድርጅቶች ጋር በመተባበር ሲያደርግ የቆያቸው ጥረቶች ተገቢና በአርቆ አስተዋይነት የተደረጉ መሆናቸውን በመገንዘብ እስከ አሁን ለተደረገው ጥረት ያለንን ጠንካራ ድጋፍ እናረጋግጣለን።


7ኛ፡- ኢህአዴግ የፓርቲያችንና የመድረክን ትክክለኛ የመፍትሔ ሀሳቦችና ጥረቶችን ወደ ጎን በመግፋት ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ እንዲሆነው ብቻ በማሰብ ከእውነተኛ የድርድር ሂደት ውጭ ቀድሞውንም አብሮአቸው ሲሰባሰብና ልዩ የገንዘብ ድጋፍ ሲሰጣቸው ከቆያቸው የጋራ ም/ቤት አባላት የሆኑ ፓርቲዎች ጋር ድርድር እያካሄደ ለማስመሰል ያህል እየፈጸመ ያለውን የማደናገር ተግባር አጥብቀን እናወግዛለን። መድረክና አባል ድርጅቶቹ በጠየቁት መሠረት በተጨባጭ የሀገራችንን የፖለቲካ ምህዳር ችግሮች ሊፈታ የሚያስችል ድርድር ሙያና ልምድ ባላቸው ኢትዮጵያዊያን አደራዳሪዎች አማካይነትና ገለልተኛ ታዛቢዎች ባሉበት በአስቸኳይ እንዲያካሄድና ለዚህም የሚመጥን የመተማማኛ እርምጃዎችን እንዲወስድ አጥብቀን እንጠይቃለን።


8ኛ፡- ኢህአዴግ የሀገራችንን ውስብስብ ችግሮች በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ አግባብ በሚካሄድ ትግል መፍትሔ ለማስገኘት ሲታገሉ የቆዩ የሰላማዊ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አባላትና የመገናኛ ብዙሃን አባላትን በማሰርና በማንገላታት የሰላማዊ ትግልን አማራጭ በመዝጋት ረገድ እየፈጸማቸው ያሉትን ፀረ-ዴሞክራሲያዊና ፀረ-ሰላም ተግባራትን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ይገኛል። ስለዚህም ኢህአዴግ ሰላማዊ ትግላችንን አጣብቂኝ ውስጥ ለመክተት እየፈጸማቸው ያሉትን ተግባራት አጥብቀን እናወግዛለን። በዚሁም መሠረት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ም/ሊቀመንበር ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩትን ዶ/ር መረራ ጉዲናን ጨምሮ በሰላማዊ ተቃውሞአቸው ምክንያት በአሁኑ ወቅት በእስር እንዲማቅቁ እየተደረጉ ያሉት የመድረክ አባላትና ሌሎችም ሰላማዊ ተቃዋሚዎች፣ የመገናኛ ብዙሃን አባላትና የሙስሊም ሕብረተሰብ ሰላማዊ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት በአስቸኳይ ከእስር እንዲፈቱ አጥብቀን እንጠይቃለን።


9ኛ፡- ኢህአዴግ የሀገራችንን ፖለቲካዊ ችግሮች በኃይል ለመፍታት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከማውጣቱም በላይ ይህንኑ አዋጅ በማራዘም የሕዝባችንን ሕገ-መንግሥታዊ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አፍኖ ይገኛል። በዚህ አይነት አፈና የሀገራችንን ውስብስብ ችግሮች ለመፍታት ስለማይቻል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በአስቸኳይ እንዲያነሳና ከኃይል እርምጃው ታቅቦ የሰላማዊና ዘላቂ መፍትሔ አቅጣጫ እንዲከተል አጥብቀን እንጠይቃለን።
10ኛ፡- በየክልሎቹ የሪፎርም ከተማዎችን ማስፋፋትና ለኢንቨስትመንት በሚል ሰበብ ከመሬታቸው እየተፈናቀሉ ያሉ ዜጎች በገበያ ዋጋ ተመጣጣኝ ዋጋ እንዲከፈላቸውና መልሶ የማቋቋም ተጨባጭ እርምጃዎች በአስቸኳይ እንዲወሰዱ እንጠይቃለን።

 

የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ
ሐምሌ 9 ቀን 2009 ዓ ም
አዲስ አበባ

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
163 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1098 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us