“ቅብጥብጧ”

Wednesday, 26 July 2017 13:33

 

በማዕረጉ በዛብህ

ሩስያ እንደነ ሌብ (ሊዮ) ቶልስቶይ፣ ፍዮዶር ደስተየቭስኪ፣ ኢቫን ተርገነቭ፣ ኒኮላይ ጎጎል፣ አንቶን ቼኮቭርና እንዲሁም የኛው አልግዛንደር ፑሽኪን ያሉና ሌሎችም እጅግ የተደነቁ ጥንታውያን ደራሲዎች በየዘመናቸው እጅግ ተናፋቂ የስነጽሁፍ ችቦ ያበሩባት ሥራቸው በመላው ዓለም የተደነቀ የስነ ጥበብ ሰዎች የፈለቁባት አገር ነች። በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ልዑካን ቡድን የዚያን ጊዜዋን ሶቪየት ኅብረት ሲጎበኝ የቡድኑ አባል በመሆን፣ የስነጽሁፍ ፍቅር እንደመስቀል ዳመና እሳት የሚንቀለቀልባትና ውቢትዋን ሞስኮን ጎብኝቻለሁ። ከሩስያ ደራስያን ማኅበር መሪዎችና አባሎች ጋር በነበረን የጥቂት ቀናት ግንኙነት የተገነዘብኩት ትልቅ ቁም ነገር ሥነጽሁፍ በሕብረተሰቡ ሕይወት ውስጥ የሕልውና ፍልስፍና በር ከፋችና አስደሳች የኑሮ አንቀሳቃሽ ሞተር መሆኑን ነው። ወደ አምልኮ በተጠጋ አድናቆት የሚወራው ከላይ ስለ ጠቀስኳቸውና ስለሌሎችም የጽሁፍ ሰዎች ነው። ከለጋስ መስተንግዷቸው በላይ ስለ ስነጽሁፍና ስለስነጽሁፍ ሰዎች የሚደረገው ውይይትና ጭውውት ውስጣዊ ስሜትን የሚኮረኩር የናፍቆት አባዜ የሚያሳድር ነገር ነው። ምነው ስነጽሁፍ በኛም አገር ይህንን የልዕልና ሕዝባዊ ፍቅር ደረጃ ልትደርስ በቻለች ያስብላል።

በአገራችን ለታላቁ ባለ ቅኔና ደራሲ ተውኔት ሎሪየት ፀጋዬ ገብረመድህን ቀዌሳ ምስጋና ይግባውና በሱ አነሳሽነት የምዕራቡ ዓለም ስመጥር ደራሲ ተውኔት የዊልያም ሸክስፒየርን ሥራዎች ለመተርጎም ከተደረገ መጠነኛ ጥረት ሌላ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደነቁ የሌሎች አገሮች ደራስያንን ሥራ በአማርኛም ሆነ በሌሎቹ ቋንቋዎቻችን ባለመተርጎማቸው የዓለም አቀፍ ስነጽሁፍ ባህልን በሰፊው ማጣጣም የቻልን አይመስለኝም።

ሰሞኑን ለስነጽሁፍ ወዳጆች ከተበረከቱት አዳዲስ ያገር ውስጥ መጻሕፍት መካከል በአጭር ልቦለድ ድርሰቶቹና በጸሐፊ ተውኔትነቱ በዓለም የተደነቀው የሩስያው የአንቶን ፓቪሌቪች ቼኮቭ “ቅብጥብጧ” የተባለችው 256 ገጽ መጽሐፍ በአማርኛ ተተርጉማ ለንባብ በቅታለች። ተርጓሚዋ ጽኑ የስነ ጽሁፍ ፍቅር ያላትና የሩስያኛ ቋንቋን በከፍተኛ ደረጃ በመተርጎም የምትታወቀው አንጋፋ ጋዜጠኛ ትዕግሥት ፀዳለ-ኀሩይ ነች። በመሆኑም የታላላቁ የሩስያ ደራስያን ዘመን አይሽሬ ሥራዎች ወደ አማርኛና ሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የሚተተረጎሙበት ጊዜ እንዲደርስ የስነጽሁፍ አማልክት ፈቅደው ይሆን የሚያሰኝ ነው። ወ/ሮ ትዕግሥት “ወርቃማው ዘመን” ስለምትለው የሩስያ ደራስያን ሥራዎች በናፍቆት ትዝታ ካነሳች በኋላ በተለይ ስለ አንቶን ቼኮቭ ድርሰቶችና የሕይወት ታሪክ በጣፈጠ አማርኛ እያስነበበችን ነው። ለአንዳንዶቻችን ለዓለማቀፋዊ ስነጽሁፍ ንባብ ያለንን አምሮት ለመቀስቀስ ጥረት እያደረገች ይመስላል። ቅብጥብጧ የቼኮብን 22 አጫጭር ልቦለድ ወጎች የያዘች የመጀመሪያዋ የአማርኛ ትርጉም መጽሐፍ ስትሆን የመጽሐፉዋን የአንዷ አጭርልቦለድ ታሪክም የጋራ ርዕስ ነች።

በዝች አጭር ጽሁፍ የምሞክረው ስለ ትርጉሙ ደረጃ ወይም ጥራት አስተያየት ለመስጠት አይደለም፣ ምክንያቱም ሩስያውኛውን ቋንቋ ልክ እንዱ ቪየትናሚዝኛውና እንደቻይኒዝኛው አላውቀውም። ስለመጽሐፉ ይዘት ደራሲው ቼኮቭ ነውና አያሌ የሚደነቁ ነገሮች ቢኖርም እኔን ይበልጥ ያስገረመኝ ትርጉሙ የቀረበበት የአማርኛው ቋንቋ ዕድገት፣ ውበትና ጣዕም ነው። አንዳንድ ምሳሌዎች ለማቅረብ እንዲያመቸኝ ቅብጥብጧ ስለ ተባለችው አጭር ልቦለድ አንዳንድ ነገሮችን አነሳሳለሁ። በዝች አጭር ልቦለድ ወግ ጎልተው የሚታዩ ገጸባህርያት የህክምና ባለሙያ የሆነው ዶ/ር ስቲፓኖቪች ዲሞብ (ዲማ) እና ባለቤቱ አልጋ ኢቫኖቭና ናቸው። ሁለቱ የወደፊት ፍቅረኞች የተዋወቁት ዶ/ር ዲሞቭ የኢቫኖቭናን አባት ህክምና በሚከታተልበት ጊዜ ሲሆን ሰውየው ከሞቱ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ነው የተጋቡት። ዲሞቭ በኋላ እንደምንረዳው እጅግ ተደናቂ የሆነ የሳይንስ ሰውና፣ የተከበረ ሃኪም ሲሆን በተፈጥሮው ዕወቁኝ፣ አድንቁኝ የሚል ጠባይ የሌለው ትሁት ሰው ነው። ባለቤቱ ኦልጋ በተቃራኒው ከታወቁ የስነጥበብ ሰዎች ጋር መተዋወቅ የምትወድና፣ እነሱን እቤቷ ለመጋበዝ እንደ መሯሯጥ የምትወደው ሌላ ነገር የሌላት ሴት ነች።

“ኦለጋ ኢቫኖቭና ትዘፍናለች፣ ፒያኖ ትጫወታለች. . .

. . . ከአማተር አርቲስቶች ጋር ትተውናለች። ይህ ሁሉ ደግሞ እንዲሁ የተገኘ አይደለም ተሰጥኦ ቢኖራት ነው”. . . ታዋቂ ሰዎችን ታመልካቸዋለች። በየሌሊቱ በሕልሟ ሳይቀር ታልማቸዋለች፣ እንደውሃ ይጠሟታል፣ ሆኖም ግን ምንም አድርጋ ከጥሟ ለመርካት አልቻለችም” ይላል ቼኮቭ አድናቆት ይሁን ሂስ ባልለየለት አረፍተ ነገር (ገጽ33)። እነዚህ ባልና ሚስት፣ ሴትየዋ ያላትን የለት ተለት ኑሮና ደስታ በስነጥበብ የታወቁ አርቲስቶችን ለመተዋወቅና ለማስተናገድ ጧት ማታ ስትዳክር ትሁቱ ባለቤቷ ዶ/ር ዲሞቭ ደግሞ የባለቤቱን እንግዶች በመጡ ቁጥር ሳይሰለች “እባካችሁ ጌቶቼ እህል ቅመሱ” ሲል በመቀበል ይታወቃሉ።

ዶ/ር ዲሞቭ ከሞተ በኋላ ጓደኛው ዶ/ር ኮሮስቴሌቭ እንደገለፀው እጅግ በጣም የሚደነቅ ባለሙያና ልዩ ሰው ነበር። “ሞተ! የሞተውም ራሱን መስዋዕት በማድረጉ ነው፣ አቤት ለሳይንስ ምን ዓይነት ጉዳት ነው!” አለ ኮሮስቴሌቭ። በመቀጠል “ሁላችንም ተሰብስበን ከእሱ ጋር ብንወዳደር አንዳችንም ከአጠገቡ አንደርስም. . . በጠራራ ፀሐይ ብርሃን ፋኖስ ተይዞ ቢፈለግ እንኳ የማይገኝ ሊቅ ነበር!. . . “ምን ዓይነት ግብረገብነት ነበረው!. . . ደግ፣ ንጹሕ፣ ሁሉን የሚወድ ልብ ያለው፣ ሰው አይደለም - መስትዋት እንጂ! ሳይንስን አገልግሎ ለሳይንስ ሲልም ሞተ” ሲል ነበር ኮሮስቴሌቭ ስለ ዴሞቭ ጨምሮ የመሰከረው።

ዲሞቭ፣ ኮሮስቴሌቭ እንደሚለው ትልቅ ባለሙያ፣ ሁሉ ነገር የተሳካለት ምርጥ ሰው ሲሆን ባለቤቱ ኦልጋ ኢቫኖቭና ግን ብዙ ችግር አለባት። ሕይወቷ በታወቁ የስነጥበብ ሰዎች ታዋቂነት አምልኮ በሽታ ተመዝብሯል። ስለሆነም የኔ ነው የምትለው የራስዋ ሕይወት የላትም። አንዳንድ ጊዜ የምትወደውና የምታስብለት የሚመስላት ባለቤቷ ዲሞቭ ከርሷ ጋር ይኖራል እንጂ እርሷ ከርሱ ጋር አትኖርም። ለማልቀስ ብዙ ሰብዓዊ ችግር ማግኘት የለባትም፣ ዝም ብላ በያአጋጣሚው ታለቅሳለች። ቅብጥብጥ ነች። የ25 ዓመት ወጣት፣ ቆንጆ ሰዓሊ፣ ከሆነው ከርያቦቭስኪይ ጋር የመሠረተችው ጸያፍ የፍቅር ግንኙነት ከደስታና ከሰላም ይልቅ ለጭንቀትና በየደቂቃው ለመከፋት ዳርጓታል። ባዲሱ ሰዓሊ ፍቅር እየተቃጠለች “ለእሱ (ለባለቤትዋ) ለተራውና ለተለመደው ዓይነት ሰው እስከዛሬ ድረስ ያገኘው ደስታ በቂ ነው። በቃ ያሉትን ይበሉ፣ ቢያሻቸው ያውግዙኝ፣ ይርገሙኝ፣ እኔ ደግሞ ለእልሁ ሁሉንም አደርገዋለሁ. . . አደርገውና እሞታለሁ. . . በሕይወት ውስጥ ሁሉንም መሞከር አስፈላጊ ነው!” የምትል “ጀግና” ሆናለች።

ምስኪኑ ዲማም እየተታለለ መሆኑ እየገባው ከመሄዱ የተነሣ “የህሊና ቁስል ያለበት ይመስል የባለቤቱን ዓይን በቀጥታ ፊት ለፊት ማየት አቃተው” ብዙ ሳይኖርም ከአንድ በሽተኛ “ሕፃን የጉሮሮ ተላላፊ በሽታን ሕዋስ በቱቦ መጥጦ” በሽታው ስተላለፈበት በጠና ታሞ ሞተ። ባለቤቱ ቅብጥብጧ ኢሻናቫና በባልዋ ላይ የምታካሄደው አመንዝራና ማጋጣነት በድብብቆሽ መጋረጃ ሊሸፈን ቢሞከርም ቅሉ በብዙ ባልና ሚስቶች የጋብቻ ሕይወት ውስጥ ያለ የሰው ተፈጥሯዊ እውነታ መሆኑን ነው ቼኮቭ ያሳየን።

ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት ይህች አስተያየት ጽሁፍ የመጽሐፏን ጥራትና ደረጃ ከትርጉሙ አንጻር ለመገምገም ባይሆንም ስለትርጉም ስራው ጥያቄ  ማንሳት አስፈላጊ ሆኖ ይታየኛል። ወይዘሮ ትዕግሥት ትርጉሙን በተመለከተ “ለአንቶን ቼኮቭ ታማኝ በመሆን ከፃፈው ሳልቀንስም ሆነ ሳልጨምር ቃል በቃል ትርጉም የሚቻለኝን ሁሉ አድርጊያለሁ” ብላለች በመግቢያዋ ላይ። በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ ነጥብ ላነሳ እወዳለሁ። እንደሚታወቀው በትርጉም ሥራ ሁለት ዓይነት የታወቁ ዘዴዎች አሉ። አንደኛው ወ/ሮ ትዕግስት እንዳለችው የቃል በቃል ትርጉም ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የሚተረጉመውን ጽሁፍ ወይም ንግግር ወስዶ ቁም ነገሩን በጥልቀት ከመረመሩት ከተረዱ በኋላ Adaptation በተባለው ጥበብ በራስ ባህላዊ የስነ ጽሁፍ ወይም የንግግር ስልትና ቋንቋ መተርጎም ነው። በተለይ ለልቦለዳዊ ስነጽሑፎች የሚመረጠው ይኸው የትርጉም ዘዴ ይመስለኛል። እኔ የሩስያኛን ቋንቋ ባለማወቄ በዚህ ጉዳይ ላይ ለመከራከር የሚያበቃኝ አቋም ባይኖረኝም ትርጉሙ ይበልጥ Adaptation ነው ብዬ እንዳስብ ያደረጉኝን አንዳንድ ምሳሌዎች አነሳለሁ።

በገጽ 36 ዶ/ር ጂሞቭ (ዲማ) . .. “ሁለቱን ጣቶችን ቆርጫቸው ኖሯል። ልብ ያልኩት ቤት ከገባሁ በኋላ ነበር” ይላል። “ልብ ያልኩት” የሚለው አነጋገር ልብ አለ ከሚለው የመጣ ሲሆን ትርጉሙም አስተዋለ፣ አተኩሮ ተመለከተ ማለት ነው። ልብ አለ የሚለውን አነጋገር አስተዋለ ወይም አተኩሮ ተመለከተ ሲል የሚተረጎመው አማርኛ መዝገበ ቃላት፣ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል፣ (1993) ነው። የአካሎቻችን ዋና አዛዥ አዕምሮ ሲሆን የአዕምሮን ሥራ ብዙውን ጊዜ ለልባችን የምንሰጥ እኛ ኢትዮጵያውያን ነን።  ለምሳሌ ሳይኮሎጂ የተባለውን ሳይንሳዊ ቃል ስነ-አዕምሮ ወይም ስነ-ሕሊና ብለን በመተርጎም ፈንታ ስነ-ልቦና በማለት በሰፊው ሲነገር፣ ሲጻፍና ሲነበብ ይሰማል። እንግዲህ ጥያቄው “ልብ አለ” የሚለው አነጋገር በመጽሐፉዋ ውስጥ በተቀመጠው ትርጉም መሠረት በሩስያዊኛ ቋንቋ ቃል-በቃል አለ ወይስ በዘወርዋራ እሳቤ በአዳኘቴሽን ዘዴ ተተርጉሞ ነው የሚል ነው።

ዲማ አሁንም በዚያው ገጽ “የኔ ሆድ አሁንስ አልቀናህ አለኝ” ይላል “የኔ ሆድ” ና “አልቀናህ አለኝ” የሚሉት አነጋግሮችስ የቃል በቃል ትርጉሞች ናቸው ወይስ ለሩስያዊኛ አነጋገር ይቀርባሉ ተብለው የተወሰዱ ናቸው? ትርጉማቸው ይቀራረባል ተብለው የተወሰዱ ከሆኑ የአዳኘቴሽን ትርጉም ውጤት ነው የሚሆኑት። አንድ ሌላ ምሳሌ ልጥቀስ። በገጽ 113 አሊኺን የተባለው የዩኒቨርሲቲ ምሩቅ አባቱ ለትምህርት ያወጣለትን ገንዘብ ለመክፈል ወደ ግብርና እንደገባ ሲናገር “አንድ ቁራሽ መሬት ጦም አላሳደርኩም” ይላል። ይህ አነጋገር ለኔ ፍፁም ኢትዮጵያዊ ምናልባትም ፍፁም አማርኛዊ ሆኖ ነው የሚሰማኝ። አሁንም የሚነሳው ጥያቄው ከላይ እንደተነሳው ስለሆነ ክርክሩን አልደግመውም። ይህን ነጥብ ያነሳሁት ስለ ትርጉም ሥራ እግረ መንገዳችንን ትንሽ እንድንነጋገር ነው እንጂ የመጽሐፉ ትርጉም የተዋጣለት መሆኑን ማስተባበል የሚቻል አይመስለኝም። ውብ ከመሆኑ የተነሳም “ቼኮቭ በአማርኛ ጽፎት ይሆን እንዴ?” የሚል አስተያየት ቢነሳም አያስገርምም።

ሌላው ስለመፅሐፉ ቅርጽ የማነሳው ነጥብ አለ። የመጽሐፉ ዲዛይን (ቅርጽ) ከፊት ሽፋኑ ይዘት ጀምሮ ከተለመደው ያገራችን መጻሕፍት ሕትመት ገጽታ ለየት ያለ ይመስላል። የሴት ወይዘሮዋ (የቅብጥብጧ) የተሽቀረቀረው ውብና ባህላዊ አለባበስ ፎቶግራፍና በገጹ ላይ የሰፈሩት የተለያዩ ቀለሞች አንድነትና ኅብረት የመጽሐፉን ውጫዊ ዕይታ ልዩ ውበት የሰጠውና አንባቢን እንዲስብ የሚያደርግ ይመስላል። ወደ ውስጥ ሲገባ ከወጎቹ የሕይወት እውነታን አንፀባራቂነትና ከቋንቋው ውበትና ጣፋጭነት ሌላ “በግርጌ ማስታወሻዎቹ፣” “በቼኮቭ አባባሎችና” “ማብራሪያ” በተባሉት ክፍሎች የተሰጡት ተጨማሪ መረጃዎች መጽሐፏን ትምህርታዊ አድርገዋታል ማለት ይቻላል። መጽሐፏን ያነበብነውንም ስለሩስያ እንዳገር፣ ስለሕዝቧ ታሪክ፣ ባህል፣ ወግና አኗኗር መጠነኛ ዕውቀት ሳናገኝ አልቀረንም።

በመፅሐፏ ጥሩነት ሳልዘናጋ አንድ ያልተቀበልኩትን ነጥብ በማንሳት አስተያየቱን እደመድማለሁ። በየገጹ ራስጌ ላይ ከደራሲው አንቶን ፓቪሎቪቶ ቼኮብ ስም ቀጥሎ “በትዕግሥት ፀዳለ-ኀሩይ” ይላል። ይህም ራሱ ጥሩ ትሩፋት ቢሆንም ከፊቱ “ትርጉም” በትዕግሥት ፀዳለ-ኅሩይ ባለማለቱ የደራሲውን የፈጠራ ችሎታና ተደናቂነት የሚሻማ ይመስላል። በተረፈ ቅብጥብጧ የተሳካ የረጅም ሥራ መቅድም ሆና ስለምትታየኝ የቼኮቭም ሆኑ የሌሎች ተደናቂ የሩስያ ድርሰቶች ትርጉም እንዲቀጥል ያለኝን ምኞት እገልጻለሁ።

   

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
472 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1112 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us