አንዳንድ ነጥቦች ስለ አየር ንብረት ለውጥ

Wednesday, 09 August 2017 12:54

 

ካለፈው የቀጠለ

ተቋማዊ አቅምና አደረጃጀት

ሀገራችን ለአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ምላሽ ለመስጠት ቁርጠኝነቱን ማሳየት የጀመረችው ገና ከህገመንግስቱ ዝግጅት ወቅት አንስቶ ሲሆን ሕገ መንግስቱ አንቀጽ 44 እና 43 እንዲሁም አንቀጽ 92 የአካባቢ ጉዳዮችን እንዲሁም ዘላቂነት ያለው ልማት ከማረጋገጥ አንፃር በግልፅ ተደንግጓል።

ከዚህ በመነሳትም መንግስት የአካባቢ ጥበቃ አካላትን ከ1987 እስከ 2008 ባሉት ጊዜያት ከወቅቱ ጋር የሚሄዱ አደረጃጀቶችን ከአራት ጊዜ በላይ በአዋጅ አቋቁሟል። የአካባቢ ጥበቃ አካላትም የአካባቢ ፖሊሲን በመቅረፅና አዋጅ በማውጣት ለህጎቹ ተፈፃሚነት ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። ለፖሊሲው ማስፈፀሚያ የሚረዱ ልዩ ልዩ አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ተከታትለው የወጡ ሲሆን የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ አዋጅ፣ የአካባቢ ብክለት ቁጥጥር አዋጅ እና የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ አዋጅ ለአብነት ተጠቃሾች ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም ሀገራዊ የአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣሚያ እቅድ በማውጣት ትግበራው ቀደም ተብሎ የተጀመረ ሲሆን በሀገራዊ አቅም የተለካ የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት ቅነሳ አስተዋፅዖ” (Intended Nationally Determined Contribution)፤ እንዲሁም የተለያዩ ፕሮጀክቶችና ፕሮግራሞች ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ቀርበዋል። ከዚህ ባለፈም ሚ/መ/ቤታችን በአዲስ መልክ ከተደራጀ ወዲህ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ የአየር ንብረት ለውጥ ድርድር ጉዳዮች ከፌዴራል እስከ ክልል የሚገኙ አካላትን በማሳተፍ ሀገራዊ ድርድሩ የሀገራችንን ተጠቃሚነት በይበልጥ የምናጎለብት፣ ከሌሎች ሀገራት ልምዶችን የምንጋራበትና ከተለያዩ ሀገራትና ድርጅቶች የሁለትዮሽ መድረኮችን በማካሔድ ለአየር ንብረት የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ የተለያዩ ድጋፎችን የምናገኝበት እንዲሆን ብርቱ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል።

ሀገራችን የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት የስርየት እርምጃዎች በሌላ አገላለጽ አረንጓዴ ኢኮኖሚ የሚገነባባቸው 75 እርምጃዎችን ያካተተ ሰነድ በኮፐንሀገን ስምምነት መሰረት የተጎዱና ምርታማነታቸው የቀነሱ ተራራማ ቦታዎች እንዲያገግሙና ሙቀት አማቂ ጋዞች ወደ ከባቢ አየር እንዳይለቀቁ አምቆ ለማስቀረት፣ የከተሞች መስፋፋትን ተከትሎ እየጨመረ ካለው ከደረቅ ቆሻሻ የሚመነጨውን የሚቴን ጋዝ ልቀት ለመቀነስ የሚያስችሉ የስርየት እርምጃዎች ተዘጋጅተው በተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ኮንቬንሽን እንዲመዘገቡ ተደርጓል። እነዚህ እቅዶች የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርግ ሀገር/ ድርጅት ሲገኝ የሚተገበር ሲሆን የሚመጣው ገንዘብ የሚውለው ለታለመለት የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት ቅነሳ ዘርፍ ይሆናል።

በሌላ በኩል ሚኒስቴር መ/ቤታችን መሰረታዊ የሥራ ሂደት ለውጥ በማጥናት ወቅቱ የሚፈለገውን ምላሽ ለመስጠት በሚያስችለው መልኩ በማደራጀት በአዋጅ የተሰጡትን ተግባራት አቀናጅቶ ለመምራት ጥረት እያደረገ ይገኛል። በተመሳሳይ መልኩ በሁሉም ክልሎችና የተከማ አስተዳደሮች እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ አደረጃጀታቸውን እንዲስተካከል ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል። እስካሁን በተደረገው ጥረት ከዘጠኙ ክልሎች ውስጥ በሰባቱ ማስተካከያ አድርገዋል።

ለአየር ንብረት የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ የተለየ እቅድ ሳይሆን የልቀትና የተጋላጭነት ቅነሳ ተግባራት በሀገራዊ የልማት ግቦች ውስጥ ተካተው መተግበር ይኖርባቸዋል። ሁለተኛው ሀገራዊ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የአየር ንብረት ለውጡን ተከትለው የሚመጡ አደጋዎችን ለመመከት የሚያስችሉ ጉዳዮችን አካቶ የተዘጋጀ በመሆኑ በትግበራ ወቅት በልዩ ትኩረት ሊመራ ይገባል።

በመሆኑም ይህንኑ ሥራ ለማከናወን የተለዩ የዘርፍ መስሪያ ቤቶች ማለትም እርሻና ተፈጥሮ ሀብት፣ የኢንዱስትሪ፣ የእንስሳትና አሳ ሀብት፣ ውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ፣ ማዕድን፣ ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ፣ ከተማ ልማትና ቤቶች፣ ኮንስትራክሽን፣ ትራንስፖርት፣ የባህልና ቱሪዝም ናቸው። በ2ኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን ውስጥ በእቅዳቸው ውስጥ አካተው ትግበራ የጀመሩ ሲሆን በሚኒስቴር መ/ቤታችን በኩል አስፈላጊው የአቅም ግንባታና የተለያዩ ድጋፎች እየተሰጡ ይገኛሉ። በእቅድ ዘመኑ ስትራቴጂውን ተግባራዊ ለማድረግ ከተለምዷዊ የእድገት አቅጣጫ የሚመጣውን ተጋላጭነትና የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት ለመቀነስ የዘርፋዊ ቅነሳ ሥርዓት ተዘጋጅቶ ስራ ላይ ውሏል። በየዘርፉ የሚዘጋጁ ለአየር ንብረት የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ መገንቢያ እቅዶች ከዚህ አንጻር እየተቃኙ እንዲታቀዱ ተደርጓል።

ለዚሁ ተግባር መ/ቤታችን ከብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን በጋራ በመሆን የፌዴራል የዘርፍ መስሪያ ቤቶች ለአየር ንብረት የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ስታራቴጂንን በእትዕ-2 እቅዳቸው ውስጥ ለማካተት እገዛ የሚያደርግ መመሪያና ቼክሊስት ቀርፆ በተለያዩ መድረኮች ካዳበረ በኋላ በሚኒስትሮች የጋራ መድረክ አስገምግሞና አጽድቆ በብሔዊ ፕላን ኮሚሽን በኩል ለሁሉም የዘርፍ መ/ቤቶች እንዲደርሳቸው ተደርጓል። ከዚህ በኋላም ለአየር ንብረት የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ተግባሪ ዘርፍ መስሪያ ቤቶችና ለክልል ፈፃሚ ባለሙያዎች በመመሪያውና በቼክሊስቱ ላይ የአቅም ግንባታ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል።

ይህም ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የማጣጣሚያ ስራዎችን ሁሉም የዘርፍ መስሪያ ቤቶችና ክልሎች በሚያካሂዷቸው የልማት ሥራዎች ውስጥ አካተው እንዲተገብሩ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች ተከናውነዋል። ስለሆነም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ከሀገራዊው ሁለተኛው የእድገት ትራንስፎርሜሽን እቅድ ጋር አብሮ እንዲካተት ተደርጓል። በዚህም መሠረት በ2012 የሚኖረን የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት መጠንም ከ136 ሚሊዮን  ሜትሪክ ቶን አቻ ካርቦን በላይ እንዳይሆን ነው የታቀደው። ይህም በአምስት ዓመታት ውስጥ 149 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የሚደርስ አቻ ካርቦን ለመቀነስ ያስችላል። ይህም ሆኖ በአፈፃፀም ከትትል ወቅት ለመገንዘብ እንደተቻለው የዘርፍ መስሪያ ቢቶች የሙቀት አማቂ ጋዞች የቅነሳ እርምጃዎችን በመተግበርና ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚጠበቅባቸውን እርምጃዎች በተሟላ መልኩ ወደታች በማውረድ ረገድ እንዲሁም የሙቀት አማቂ ጋዞችን ልቀት የልኬት፣ የዘገባና የማረጋገጫ ስራውን ውጤታማ አድርጎ በመምራት ረገድ ያለው አቅም አነስተኛ ሆኖ ይገኛል።

በሌላ በኩል መንግስት ለአየር ንብረት የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ የገንዘብ ቋት (CRGE Facility) በማቋቋም ከዓለም አቀፍ፣ ከሀገራዊና ከግሉ የባለድርሻ አካላት የፋይናንሱን ፍሰት ወደ ታለመለት ቦታ እንዲደርስ ለማድረግ ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል። በዚህም ምክንያት ከአረንጓዴ የአየር ንብረት የገንዘብ ምንጭ (Global Climate Fund) እስከ 50 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለማግኘት የሚያስችል እውቅና ተሰጥቶናል። እውቅናው የተሰጠው ሀገራችን ያቋቋመችው ለአየር ንብረት የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ፋሲሊቲ መኖሩ እና እስካሁን በነበረው ሂደት በፕሮጀክቶች ትግበራ ውጤታማ ስራዎችን በማከናወኑ ነው። ለዚህ ተቋም ፕሮፖዛል ተቀርፆ በአሁኑ ወቅት በአረንጓዴ የአየር ንብረት የገንዘብ ምንጭ (Global Climate Fund) ባለሙያዎች እየተገመገመ የሚገኝ ሲሆን የሌሎች ፕሮጀክቶች ዝግጅትም በመፋጠን ላይ ይገኛል። ለአየር ንብረት የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ሥራን ለመሞከር በተዘጋጀው የፈጣን ፕሮጀክቶች የተለያዩ ፕሮጀክቶች በዘርፍ መስሪያ ቤቶች በመከናወን ላይ ይገኛሉ። የአብዛኛዎቹ ፕሮጀክቶች ትግበራቸው ውጤታማ ሆነው የተጠናቀቁ ሲሆን ዘግይተው የተጀመሩትም በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

 

ለሀገራዊ ትግበራው የአለም አቀፍ ምላሽና ድጋፍ በሚመለከት

  እ.ኤ.አ. በ2011 በደርባን ከተማ በተካሄደው 17ኛው የአባል ሀገራት የአየር ንብረት ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያ በአገር አቀፍ ደረጃ ለመተግበር ያቀደችውን ለአየር ንብረት ለውጥ ድርድር ሀገራችን ለአየር ንብረት የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ (Climate Resilient Green Economy strategy (CRGE)) በማዘጋጀት ይፋ አድርጋለች። በዚህም መድረክ በኖርዌይ እና እንግሊዝ መንግስታት የሀገራችንን የዘላቂ ልማት አቅጣጫዋን ለመደገፍ በደርባን የአየር ንብረትና እድገት ስምምነት “Durban partnership for climate change and Development” የሚል ተፈርሟል። ከዚህም ቀጥሎ በተካሄዱት የ18ኛው እና የ19ኛው እንዲሁም በ21ኛው የአባል ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ ስብሰባ ላይ የኢፌዲሪ ጠ/ሚኒስቴር ክቡር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በመድረኮቹ ተገኝተው ሀገራችን በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ እየወሰደች ያለችውን ጠንካራ እርምጃ ከማሳወቃቸውም በላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወኑ ያሉ ጥረቶችን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማስገንዘብ በተለያዩ መስኮች ይኸው ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በደርባን የአየር ንብረት ለውጥና ከልማት አጋሮቿ የተደረገውን ስምምነት በማደስ በ2014 በፔሩ ሀገር ሊማ ከተማ በተደረገው 20ኛው የአባል ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ ስብሰባ ላይ በተካሄደው የሁለትዮሽ ድርድር በሊማ የኢትዮጵያና የስድስት የአጋር ሀገራት የአየር ንብረት የጋራ መግለጫ ሰነድ (Ethiopian and Climate Partners Joint Communiqué - Lima Declaration) በዩናይትድ ኪንግደም፣ ጀርመን፣ ዴንማርክ፣ ስዊድን፣ ፈረንሳይ እና ኖርዌይ መንግስታት ተወካዮች ስምምነት ተፈርሟል።

በ2007 ዓ.ም በተደረጉ የተለያዩ የጎንዮሽ ድርድሮች አማካይነት የአሜሪካ መንግስት እና የአውሮፓ ህብረት ይህንኑ አላማ በመደገፍ የድክላሬሽኑ አካል ሆነዋል። ይኸው ትብብር ለፓሪስ ስምምነት መድረስ ትልቅ ድርሻ እንደነበረው ለመገንዘብ ተችሏል። ባለፉት ዓመታት ሀገራችን የአየር ንብረት ለውጥ ሊያደርስ የሚችለውን ቀውስ ለመመከት የምታከናውናቸውን የአረንጓዴ ልማት ተሞክሮዎችን በተለያዩ መድረኮች ላይ ስታቀርብ ቆይታለች። በዘንድሮ ዓመት በሞሮኮ ሀገር በማራክሽ ከተማ በተካሄደው 22ኛው የአባል ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ ስብሰባ ላይ ከጣሊያን መንግስት ጋር በመስኩ በትብብር ለመስራት ስምምነት ተፈራርመናል። እነዚህ ድጋፎች እንዳሉ ሆነው በሃገራችን ያሉት ስራዎች አጠናክረን መስራት እንዲሁም የሰፊውን ህዝባችንን ተሳትፎ በማረጋገጥ ባለቤት እንዲሆን ማድረግ ይገባናል። ከዚህ በተጨማሪ ከተለያዩ ሀገራትና የአለም አቀፍ ተቋማት ጋር የተደረጉ ስምምነቶችን ውጤታማ በማድረግ ከመስኩ የሚገኙ ድጋፎችን አሟጠን ልንጠቀም ይገባናል።

 

የፓሪስ ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ እየተከናወኑ የሚገኙ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች

22ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ባለፈው ህዳር ወር በሞሮኮ ማራካሽ ተካሂዷል። ጉባዔው በዋነኝነት ባለፈው ዓመት በፓሪስ የተደረሰውን አለም አቀፍ ስምምነት ወደተግባር ለማስገባት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር። የፓሪስ ስምምነት ከ170 በላይ ሀገራት በአንድ ጊዜ የፈረሙትና አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አስገዳጅ ሕግ የሆነ ብቸኛው የአለም አቀፍ ስምምነት ነው።

የፓሪስ ስምምነት እ.ኤ.አ. ከ2020 ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ ስምምነት ነው። በዚህም መሠረት በ22ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ላይ የፓሪስ ስምምነትን ወደተግባር ለማስገባት የሚያስችል የቅድም ዝግጅት ስራ እ.ኤ.አ. 2018 መጠናቀቅ እንዳለበት ተወስኗል። በ2017ዓ.ም የየሐገራት የአፈፃፀም ደረጃ የደረሰበት ሁኔታ ላይ ዳሰሳ ጥናት ይደረጋል። ይህ ድርድር የፓሪሱን ስምምነት በፍጥነት ወደ ተግባር ለመቀየር የሚያስችል በመሆኑ የውጤቱ ተጠቃሚ የሚሆኑት ደግሞ ሀገራችንና መሰሎቿ ናቸው። ምክንያቱም የፓሪስ ስምምነት ለአየር ንብረት ለውጥ ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑና በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራትን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ በመሆኑ ነው።

የፓሪስ ስምምነት ዋነኛ ዓላማው በክፍለ ዘመኑ አጋማሽ የአለማችን የሙቀት መጠን እ.ኤ.አ. በ1990 ከነበረው ከ2 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በታች፣ በተቻለ መጠን ደግሞ ከ1 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በታች ለማድረግ ነው። ይህ ደግሞ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ በማደግ ላይ ላሉና የምድራችን የሙቀት መጠን መጨመር ይበልጥ ተጎጂ የሚያደርጋቸው ሀገራት ፍላጎትና በድርድሩ ሂደትም ሲታገሉለት የነበረ አቋም ነው። የፓሪስ ስምምነቱ በተለይም በፋይናንስ፣ በአቅም ግንባታ፣ በቴክኖሎጂ ልማትና ስርፀት ለታዳጊ ሀገራት ቅድሚያ እንዲሰጥ የሚያደርግ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ለአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣሚያ የሚሰጡ የፋይናንስ ድጋፎች እንደ ባለፉት ጊዜያት አብዛኛውን በጀት ለልቀት ቅነሳ የሚያውል ሳይሆን ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖና ለልቀት ቅነሳ የሚመደቡ ገንዘቦች እኩል እንዲሆኑ የሚያስገድድ ነው።

·         በስምምነቱ ላይ የአለም አማካይ ሙቀት ጭማሪ ከኢንዱስትሪ አብዮት ዘመን ከነበረው 2 ድግሪ ሴንትግሬድ በታች ለማድረግ፣ እንዲሁም በሂደት ወደ 1 ነጥብ 5 ሴንትግሬድ ዝቅ ማድረግ፤

·         ይህን ለማሳካት የተለጠጠ የሙቀት አማቂ ጋዞችን ልቀት ለመቀነስ የሚረዱ እርምጃዎችን መውሰድን እንዲሁም ለአየር ንብረት ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚያግዙ የሥሪየት እርምጃዎች መውሰድን፣

·         ለሙቀት አማቂ ጋዞች ቅነሳና ለአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣሚያ በእኩል ደረጃ ትኩረት የሚሰጥ መሆኑ፤

·         ከኢንዱስትሪያል ዘመን ጀምሮ በካባቢ አየር ውስጥ የተከማቸው የሙቀት አማቂ ጋዞች የሚያደርሱትን ጉዳት ለመቋቋም በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ላሉት ሀገሮች አማቂ ጋዞች መቀነስ በተጨማሪ የአየር ንብረት ተጋላጭነትን ለመቋቋም እርምጃዎችን መውሰድ ወሳኝ ነው፤

·         ስምምነቱ የሙቀት አማቂ ጋዞችን ለመቀነስም ሆነ ተጋላጭነት ለመቋቋም ለሚወሰዱ እርምጃዎች ማስፈፀሚያ ግብአቶችን በኢኮኖሚ የበለፀጉ ሀገሮች በማደግ ላይ ላሉ ሀገሮች ወይም እድገታቸው በአነስተኛ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ሀገሮች በልዩ ሁኔታ ድጋፍ እንዲሰጡ ይጠይቃል፤ በፈጣን ሁኔታ በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራትም በራሳቸው ፈቃደኝነት የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ እንደሚችሉና የድጋፍ ምንጮችን መሰረትም እንዲሰፋ አድርጓል፤

·         በተለይም የፋይናንስን ተደራሽነት በሚመለከት የነበረው የተወሳሰበና የፋይናንስ ፍሰት እንቅፋት የሆኑ አሰራሮች እንዲቀረፉ በሚል ተቀምጧል፤ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ለሚወሰዱ እርምጃዎች ቀጥተኛና ተደራሽነት ፋይናንስ ምንጭ እንዲሆን በስምምነት ሰነዱ ተመልክቷል፤

·         እ.ኤ.አ. ከ2020 ጀምሮ የበለፀጉ ሀገራት ለታዳጊ ሀገራት በየዓመቱ 100 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደሚያዋጡ በስምምነቱ ተካትቷል፤

·         የፓሪሱ ስምምነት የካርቦን ንግድን የሚያበረታታ ከመሆኑም በላይ ስምምነቱ ሀገራችን በደን ልማት (REDD + Initiatives) እያደረገች ያለውን ጥረት በሚደግፍ መልኩ ስምምነት ላይ መደረሱ ትልቅ ስኬት ነው፤

እንደሚታወቀው ሀገራችን ለአየር ንብረት ለውጥ መከሰት ያደረገችው አንፃራዊ አስተዋፅኦ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። በሀገራችን እ.ኤ.አ. በ2010 በተደረገው ጥናት መሠረት ዓመታዊ ልቀታችን ከዓለም ዓመታዊ ልቀት ጋር ሲነፃፀር 0.03 ከመቶ ነው። ለዚህ ምክንያቱ የኢኮኖሚያችን እድገት አነስተኛ ደረጃ ላይ መገኘቱ ብቻ ሳይሆን የኃይል ምንጫችንም ንጹህና ታዳሽ በመሆኑ ነው። ነገር ግን የችግሩ ተጋላጭነትና ተጠቂነታችን እጅጉን የጎላ ነው። ይህንንም በማጉላት ሀገራችን በዓለም አቀፍ በሚካሄዱ የአየር ንብረት ለውጥ ድርድሮችና ውይቶች በአመራርና በባለሙያ ደረጃ በንቃት ስትሳተፍ ቆይታለች። ለዚህም ምክንያቱ በችግሩ ግንባር ቀደም ተጠቂ በመሆናችን ተግዳሮቱ እልባት እንዲያገኝም መሟገትና መተባበር ስለሚያስፈልግ ነው። እንዲሁም ለአየር ንብረት የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት ከፍተኛ የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ ስለሚያስፈልግ ለዚህም ደግሞ ውጤታማ አለም አቀፍ የህግና ፖሊሲ ማዕቀፍ እንዲኖር መስረትን ይጠይቃል።

ከነዚህም ውስጥ አንዱ በሰኔ 2007 ዓ.ም ኢትዮጵያ የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት ቅነሳ አስተዋፅኦዋን (Intended nationally determined contributions) ለአለም አቀፉ ለአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፋዊ ኮንቬንሽን አሳውቃለች። ሀገራችን ለአለም ያሳወቀችው “INDC” በተለያዩ የአለም አቀፍ የመገናኛ አውታሮችና ተቋማት በአርአያነት ሲጠቀስ ቆይቷል። ሀገራችን ለአየር ንብረት ለውጥ መከሰት ያላት አስተዋፅኦ እጅግ አነስተኛ ቢሆንም መፍትሄ በማፈላለግና እራሷንም ለተግባር ዝግጁ በማድረግ በአለም አቀፍ ደረጃ ለአብነት የምትጠቀስ ሀገር ናት። ከዚህ በተጨማሪም በአየር ንብረት ለውጥ የድርድር መድረኮች በተለይም በማደግ ላይ ያሉና ለአየር ንብረት ለውጥ ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ ሀገራት ትኩረት እንዲደረግ በምታራምዳቸው ጠንካራና ውጤታማ አቋሞቿ ሀገራችን ለአየር ንብረት ተጋላጭ ሃገራት ፎረምን በፕሬዚዳንትነት እንድትመራ ተመርጣለች። የሊቀመንበርነት ኃላፊነቱንም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ነሐሴ 15/2016 ሊቀመንበርነቱን ከፊሊፒንስ ተረክባለች። በማራካሽ በሀገራችን መሪነት በተካሄደው የሚኒስትሮች ስብሰባም የማራካሽ ዲክላሬሽን የፀደቀ ሲሆን በመድረክም ፎረሙን አምስት አዳዲስ ሀገራት ተቀላቅለውታል። በዚህም የፎረሙ አባል ሀገራት ቁጥር 48 የደረሰ ሲሆን ከጉባዔው በኋላም ሌሎች ሀገራት የአባልነት ጥያቄ በማቅረብ ላይ ናቸው። የፎረሙ አባል ሀገራት እ.ኤ.አ. እስከ 2050 የኃይል ፍላጎታቸውን ከታዳሽ ኃይል ለማድረግ ውሳኔ ማስተላለፋቸው ሀገራቱ ለከባቢ ሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት ያላቸው አስተዋፅኦ እጅግ አነስተኛ ቢሆንም ሌሎች ሀገራት ልቀታቸውን እንዲቀንሱ ከመጠየቅ ባለፈ እራስን ለለውጥ ዝግጁ በማድረግ ቁርጠኝነታቸውን ያሳዩበት መድረክ ነበር። ሀገራችንም ለዚህ መድረክ መሳካት ከፍተኛ ዝግጅትና አስተዋፅዖ አድርጋለች።

ሀገራችን በአለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ መድረኮች የምታደርጋቸው ጠንካራ ድርድሮችና ተሳትፎዎች፣ እንዲሁም በተግባር የአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖን ለመቋቋምና ልቀትን ለመቀነስ በምታደርጋቸው ጥረቶች 48 አባል ሀገራት ያሉትን የታዳጊ ሀገራት ተደራዳሪ ቡድን እንድትመራ የተመረጠችው በዚሁ በ22ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ የድርድር መድረክ ላይ ነው። ይህም በቀጣይ ለሚካሄዱት ድርድሮች ሀገራችን ከመቸውም ጊዜ በላይ በጠንካራ ተሳትፎና ሌሎች የታዳጊ ሀገራትን በመወከል በርካታ ጥረት ማደረግ እንደሚኖርባት ያሳያል። ይህ እንደሚያመለክተው ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲሆን በሀገር ቤት ከምናደርገው እንቅስቃሴ በተጨማሪ በአለም አቀፍ መድረኮች ላይም የነበረንን ሚና አጠናክረን የመቀጠላችን ማረጋገጫ  ነው።

በተደጋጋሚ እንደተወሳው ሀገራችን ለአየር ንብረት ለውጥ ይበልጥ ተጋላጭ ከሆኑ ሀገራት መካከል አንዷ ናት። ለተጋላጭነታችን የምንገኝበት መልከዓምድርና የኢኮኖሚያችን መሰረቱ ግብርና መሆኑ ዋነኛ ምክንያቶች ሲሆኑ የእድገት ደረጃችንም ገና በሂደት ላይ የሚገኝ በመሆኑ ተፅእኖውን አስቀድሞ በመተንበይን ችግሩን ለመቋቋም የሚያስችል ጠንካራ አቅም መገንባት ይኖርብናል። ይሁንና በእነዚህ ነባራዊ ሁኔታዎች ውስጥ ብንሆንም ተፅዕኖውን ለመቋቋምና ለአየር ንብረት የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችል ስትራቴጂ ነድፈን በመተግበራችን ባለፉት 50 ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ ድርቅ በሀገራችን ቢከሰትም የከፋ ጉዳት ሳያጋጥመን ለመቋቋም ችለናል። ለዚህም ዋንኛ ምክንያቶቹ ሀገራችን ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን በተሟላ መልኩ ተግባራዊ በማድረጋችን ሲሆን በተለይም በአንዳንድ አካባቢዎች በበጋ ወራት በሰፊ የህዝብ ንቅናቄ የሚከናወኑ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራዎችና በክረምት ወቅት የምንተክላቸው ችግኞች የከርሰ ምርና የገፀ ምድር ውሃን በመያዝ የክረምቱ ዝናብ ሲዘገይና መጠኑ ሲያንስ በተወሰነ አግባብ መቋቋም ተችሏል።

ከዚህ በተጨማሪ መንግስታችን ለእንደዚህ አይነት ችግሮች ምላሽ ለመስጠት የተደረገው ፈጣን ቅድመ ዝግጅትና ምላሽ የተጠናከረ ስለነበር ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው የከፋ ጉዳት ሳይደርስ በዋናነት በራሳችን አቅም ለመቋቋም ችለናል።

ይሁንና የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ በቀጣይም የሚፈታተነን ጉዳይ መሆኑ ታውቆ ከዚህ በላይ መስራት ይኖርበታል። በተለይም በይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ ዘርፎች የግብርና፣ የውሃ፣ የጤና፣ የደንና የኃይል ዘርፎች ላይ እስከ ህብረተሰቡ የሚዘልቅ የአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣሚያ ስራን በአግባቡ ማውረድና መተግበር ከተቻለ የመቋቋም አቅማችንም ይበልጥ ይጎለብታል። ከዚህ በተጨማሪም አርሶ አደሩ የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት ኢንሹራንስ አባል የሚሆንበትን ስርዓት በመዘርጋት ተግባራዊ ማድረግ ይገባናል። ሥራውን ከፕሮጀክት ባለፈ ማስፋት ይገባል።

ለአየር ንብረት የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታን አላማ አድርጎ ከተነሳባቸው ጉዳዮች አንዱ የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነትን መቀነስና የመቋቋም አቅምን ለማጎልበት ነው። ይኸው አላማም ሆነ ሌሎች ሀገራዊ አላማዎችን ሊሳኩ የሚችሉት ከልማት አቅዶች ጋረ ሜንስትሪም ተደርጎ መተግበር ሲቻል ነው። ይሁንና በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ይኸው ጉዳይ ትኩረት ተሰጦት የተከናወነ ቢሆንም ወደተግባር የዘርፍ መስሪያ ቤቶችና ወደ ክልሎች በሚፈለገው ደረጃ እየተተገበረ ነው ለማለት አያስደፍርም። በተለያዩ ጊዜያት የተካሄዱ የድጋፍ የክትትል ስራዎች እንደሚያሳዩት የዘርፍ መስሪያ ቤቶች በተለይም በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ለመቀነስ የታቀደውን የሙቀት አማቂ ጋዝም ሆነ ተፅዕኖን የመቋቋሚያ ተግባራት በተዋረድ ወደ ክልሎች በተሟላ መልኩ አላወረዱም። ከዚህ ተነስቶ በክልሎች የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ውስጥም ለአየር ንብረት የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ በበቂ መጠን ሚኒስትሪም አልተደረገም። ከዚህ በተጨማሪም ለአየር ንብረት የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታን ሊከታተል የሚችል የሥራ ክፍል በማቋቋም ረገድ በፌዴራል የዘርፍ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በአብዛኛው በአደረጃጀቱ የተፈጠረ ቢሆንም የሚታይ ቢሆንም አስፈላጊውን የሰው ኃይል በመመደብና በግብዓት በማሟላት በኩል እጥረቶች ይታያሉ። በክልል ደረጃ የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ቢሮ ያደራጁ ክልሎችም ቢሆኑ በአንዳንዶቹ ክልሎች መዋቅሩ ወደ ዞንና ወረዳ ብሎም ቀበሌ ድረስ ያላወረዱባቸው ሁኔታዎች መኖራቸውን ያሳያል። ይህንኑ ሥራ ውጤታማ በማድረግ በየደረጃው ለአየር ንብረት የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታን የሚከታተል ስሪንግ ኮሚቴ በማጠናከር ረገድ የተሰራው ተግባር ደካማ ነው ማለት ይቻላል።

የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖዎች ከሀገራዊ ጥረቶች በተጨማሪ አለም ዓቀፋዊ ድጋፍና ትብብርን የሚጠይቁ ናቸው። ለዚህም ነው፤ በየዓመቱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ድርድርን በአባል ሀገራት ተሳትፎ የሚያከናውነው። ሀገራችንም የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖና ለመቋቋም በውስጥ አቅም ከምታከናውናቸው ተግባራት በተጨማሪ በአለም አቀፍ ደረጃ ጠንካራ ተሳትፎና ድርድር በማድረግ ሀገራዊ ፍላጎታችንን ሊያሳኩ የሚችሉ የፋይናንስ፣ የቴክኖሎጂና የአቅም ግንባታ ድጋፎች እንዲገኙ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተግቶ መስራትን ይጠይቃል።

እስካሁን በነበረው ሂደት እነዚህን ድጋፎች ወደ ሀገር ለማስመጣት ከፍተኛ ጥረቶች እየተደረጉ የሚገኙ ቢሆንም የተገኙ ውጤቶች ከጥረታችን ተመጣጣኝ ሆነው አልተገኙም። ለዚህም ዋናው ምክንያት የበለፀጉ ሀገራት ቃል የገቡት ፋይናንስ በጊዜና አስተማማኝ በሆነ ሁኔታ ካለማቅረባቸው ባሻገር ላሉ የሀብት ምንጮች የሚቀርቡ ፕሮፖዛሎች ላይ የሚሰጠው ምላሽ እጅግ የተጓተተና አሰልቺ መሆኑን ነው። በመሆኑም የአየር ንብረት ለውጥ ሳይንሳዊ ክህሎትና እውቀትን የሚጠይቅ በመሆኑ የድርድር፣ የዲፕሎማሲና የአየር ንብረት ለውጥ አመራር አቅምን በማጎልበት መስራት ያስፈልጋል። እነዚህ ተግባራትን ለማከናወን በአለም አቀፍ ደረጃ የሚደረጉ የፋይናንስ ድጋፎች በተጨማሪ በሀገር ውስጥም በቂ የሆነ ፋይናንስ በልዩ ትኩረት ሊመደብላቸው ይገባል።

 

ለአየር ንብረት የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ የምክር ቤት አባላት ሚና

የእያንዳንዱ ተቋም እቅድ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽና በተሟላ መልኩ አካቶ ማዘጋጀቱን፣ እንዲሁም የእቅድ አፈፃፀሙ ከልቀት ቅነሳና ተጋላጭነትን ከመቋቋም አንጻር እንደየተቋሙ ነባራዊ ሁኔታ ተቃንቶ መታቀዱን መገምገምና ድጋፍ ማድረግ።

በየደረጃው ባሉ ምክር ቤቶች የሚፀድቁ ህጎች፣ እቅዶችና መርሀግብሮች ለአየር ንብረት የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ስራ ትኩረት የሚሰጡ መሆናቸውን ማረጋገጥ።

በሁሉም ደረጃዎች በየዘርፍ መ/ቤቶች የአካባቢና የአየር ንብረት ለውጥ ስራን የሚከታተል አደረጃጀት መፈጠሩን እንዲሁም በተገቢው የሰው ኃይልና ግብዓት መሟላቱን ማረጋገጥ ይገባል።

ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታችን እውን የሚሆነው በ2ኛው የእትአ በተቀመጠው አግባብ ከፌዴራል እስከ እያንዳንዱ ቤተሰብ ድረስ ተቀናጅቶ ሲተገበር በመሆኑ በምክር ቤቱ ውስጥም ሆነ፣ በመስክ ምልከታ እንዲሁም ከመረጠን የህብረተሰብ ክፍል ጋር በሚኖረን ግንኙነት አማካኝነት የተለመደው ድጋፍና ክትትል ማድረግ ይገባል።  

ምንጭ፡- የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
297 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1133 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us