የፌደራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን የ15 ዓመታት ጉዞ

Wednesday, 09 August 2017 13:01

 

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግስት ሙስናን ተቋማዊ በሆነ መልኩ ለመከላከልና ለመዋጋት ግንቦት 16 ቀን 1993 ዓ.ም የፌደራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽንን ማቋቋሙ ይታወቃል፡፡ ኮሚሽኑ በ1993 ዓ.ም ሲቋቋም የነበረው የሰው ኃይል 12 ነበር፡፡ ለኮሚሽኑ የተፈቀደው ጠቅላላ የሰው ኃይል 487 ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በሥራ ላይ የሚገኙት ሠራተኞች 410 ናቸው፡፡ ከነዚህ ውጥ ሴቶች 141 ወንዶች ደግሞ 269 ናቸው፡፡ በሙያ ስብጥራቸውም የህግ፣ የምህንድስና፣ የቋንቋ፣ የትምህርት፣ የማህበራዊ ሳይንስ፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ወዘተ. ባለሙያዎች ናቸው፡፡


ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ ሙስናን በሦስት ዋና ዋና መንገዶች (Three-pronged approaches) በመከላከልና በመዋጋት ላይ ይገኛል፡፡ ሦስቱ ዋና ዋና መንገዶችም፡-

 

      • የሥነምግባርና የፀረሙስና ትምህርቶችን በማስፋፋትና በማስረጽ ሙስናን የማይሸከም ህብረተሰብ መፍጠር፣
      • የሙስና ወንጀልንና ብልሹ አሰራርን አስቀድሞ መከላከል፣
      • የሙስና ወንጀልን መመርመር፣ ሙስና ተፈፅሞ ሲገኝም ወንጀለኞችን ለፍርድ በማቅረብ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ማድረግና በሙስና የተገኘ ሐብት ለትክክለኛ ባለመብቱ ማለትም ለህዝብ (ለመንግሥት) እንዲመለስ ማድረግ ናቸው፡፡

 

ኮሚሽኑ እነዚህን ስትራቴጂዎች መሠረት በማድረግ ባለፉት 15 ዓመታት ባደረገው ያላሰለሰ ጥረት ቀላል የማይባሉ ተግባራትን አከናውኗል፤ መልካም የሚባሉ ውጤቶችንም አስመዝግቧል፡፡ በዚህ ጥረቱም ለአገራችን የልማት፣ የመልካም አስተዳደር እና የዴሞክራሲያዊ ሥርአቶች ግንባታ ሰኬቶች የበኩሉን አስተዎጽኦ አድርጓል፡፡


1.1 የኮሚሽኑ ራዕይ

 • በ2015 ሙስና ለልማትና መልካም አስተዳደር እንቅፋት ከማይሆንበት ደረጃ በማድረስ በዓለም ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ከሆኑ የፀረ ሙስና ተቋማት አንዱ ሆኖ መገኘት፤

 

   1.2 የኮሚሽኑ ተልዕኮ

 • አግባብነት ካላቸው አካላት ጋር በመተባበር የሥነምግባርና የፀረ-ሙስና ትምህርትን በማስፋፋት፣ ሙስናና ብልሹ አሰራርን በመከላከል እና የሙስና ወንጀል ተጠርጣሪዎችን በመመርመር፣ በመክሰስና በማስቀጣት ለተመዘበረው ሀብት ተመጣጣኙን በማስመለስ በመንግሥትና በህዝባዊ ድርጅቶች አሠራር ላይ ግልፅነትንና ተጠያቂነትን እንዲሰፍን ማድረግ፤

 

   1.3 የኮሚሽኑ ዓላማዎች:-

 

  • አግባብነት ካላቸው አካላት ጋር በመተባበር የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ትምህርቶች፣ በማስፋፋት የነቃ እና ሙስናን ሊሸከም የማይችል ሕብረተሰብ እንዲፈጠር ጥረት ማድረግ፣
  • አግባብነት ካላቸው አካላት ጋር በመተባበር የሙስና ወንጀልን እና ብልሹ አሠራርን መከላከል፣
  • የሙስና ወንጀልን እና ብልሹ አሠራርን መከታተል፣ መመርመር እና መክሰስ፣

 

 

    1.4 የኮሚሽኑ እሴቶች

 

 • የመልካም ሥነምግባር ተምሳሌት ነን፣
 • ሙስናን ለመታገልና ለማታገል በጽናት ቆመናል፣
 • በተሟላ ስብእና እናገለግላለን፣
 • በጋራ እንሰራለን፣
 • ለለውጥ ዝግጁ ነን፣

 

1.5 የኮሚሽኑ አደረጃጀት፣

ኮሚሽኑ 11 ዳይሬክቶሬቶችና ሁለት አገልግሎቶች አሉት፡፡ ዳይሬክቶሬቶቹ የሥነምግባር ትምህርትና የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች፣ የሙስና መከላከል፣ የሥነምግባር አውታሮች ማስተባበሪያ፣ የሀብት ማሳወቅና ማስመዝገብ፣ የምርመራና አቃቤ ህግ፣ የጥናትና ለውጥ ስራ አመራር፣ የእቅድ፣ ግዥና ፋይናንስ፣ የኦዲት፣ የሰው ሀብት ስራ አመራር እና የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬቶች ሲሆኑ በቅርቡ ደግሞ የኮሚሽኑ የሥልጠና ማዕከል በዳይሬክቶሬት ደረጃ ተዋቅሮ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በአገልግሎት ደረጃ የተደራጁት ደግሞ የህግ እና የጠቅላላ አገልግሎት ናቸው፡፡ የኮሚሽኑ የሥነምግባር መከታተያ ክፍል ደግሞ በጽ/ቤት ደረጃ የተዋቀረ ነው፡፡

 

ከመጋቢት ወር 2002 ዓ.ም ጀምሮ ኮሚሽኑ በድሬዳዋ ከተማ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ከፍቶ ሥራውን በማከናወን ላይ የሚገኝ ሲሆን ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ተከፍቶ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡ ይህም ተጠሪነታቸው ለፌደራል መንግሥት በሆኑት በሁለቱ ከተሞች ሙስናና ብልሹ አሠራርን በቅርበት ለመከላከልና ለመዋጋት እንዲቻል የተቋቋሙ ናቸው፡፡

1. ኮሚሽኑ ባለፉት 15 ዓመታት ያከናወናቸው ዋና ዋና ተግባራት

2.1 የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ትምህርትን ከማስፋፋት አንጻር፡-


በፀረ-ሙስና ትግል ውጤታማ ለመሆን ሙስናን ለመሸከም የማይፈቅድ ሕብረተሰብ መፍጠርን ይጠይቃል፡፡ ይህ እውን የሚሆነው ደግሞ በዋነኛነት በሕብረተሰቡ ውስጥ የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ትምህርቶችትን በማስፋፋት፣ በማስረጽና አስተሳሰብ በመቀየር ነው፡፡


ከዚህ አኳያ የፌደራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ትምህርቶችን በሕብረተሰቡ ውስጥ በማስፋፋት እና በማስረጽ ሙስናን ለመሸከም የማይፈቅድ ሕብረተሰብ ለመፍጠር ሰፊ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡


ኮሚሽኑ ይህን ዓላማውን ለማሳካትም የተለያዩ መንገዶችንና የግንኙነት አውታሮችን ይጠቀማል፡፡ በዚህ መሠረት በዋነኛት በፊት ለፊት ትምሕርት፣ በተለያዩ የሕትመት ውጤቶች እና በኤሌክትሮኒክ ሚዲያ አማካኝነት ሙስናን ለመከላከል የሚያስችል ትምህርት በማስፋፋት እና ልዩ ልዩ መረጃዎችን በማሰራጨት ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ከግንቦት 16 ቀን 1993 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ ሥራዎች አከናውኗል፡፡


በዚህ መሠረት ባለፉት 15 ዓመታት ለመንግሥት መ/ቤቶች፣ ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች፣ በየደረጃው ለሚገኙ የትምህርት ተቋማት የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች፣ ለሥነምግባር መኮንኖች እንዲሁም በራሳቸው ተነሳሽነት የሥነምግባር ትምሕርት ለሚያስፋፉ አካላት በተደረገ ድጋፍ በግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እና በአሰልጣኞች ስልጠና አማካኝነት ለበርካታ የሕብረተሰብ ክፍሎች የፊት ለፊት የስነምግባር እና የፀረ-ሙስና ትምሕርት ተሰጥቷል፡፡ ኮሚሽኑ በ2001 ዓ.ም በጀመረው የአሠልጣኞች ስልጠና ፕሮግራም መሠረት ለ10,910 ተሳታፊዎች የአሰልጣኞች ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ ከመንግሥት ተቋማትና ከህዝብ ክንፍ የተውጣጡ ሰልጣኞች ናቸው፡፡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርትንም በተመለከተ ኮሚሽኑ በራሱ አቅም ባደረገው እንቅስቃሴ ለ350,243 ተሳታፊዎች ትምህርቱ ተሰጥቷል፡፡ በዚህም የመንግሥት ተቋማት ሠራተኞችና ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡


ኮሚሽኑ በሥነምግባርና በሙስና ጽንሰ-ሐሳብ በአጠቃላይም በሙስና መከላከል ዙሪያ ስልጠና የወሰዱ ሰዎች ለሌሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት የሚሰጡበትን ሁኔታ በማመቻቸትም የትምህርቱን ተደራሽነት የማስፋትን ስልት እንደ አቅጣጫ ይዞ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ በዚህ መሰረት በአሠልጣኞች ሥልጠና የትምሕርት መርሐ-ግብር አማካኝነት የሚሳተፉ የሥልጠና ተሳታፊዎች ተመልሰው ለሌሎች ሠልጣኞች በሙስናና በሥነምግባር ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እንዲያስተምሩ የሚያስችል ስልት ተቀይሶ እንቅስቃሴ ሲደረግ ቆይቷል፡፡ ኮሚሽኑ በእራሱ ባለሙያዎች አማካኝነት በቀጥታ ከሚሰጠው የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ትምህርት ባሻገር የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ ትምህርቱን ለማስፋፋት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በዚሁ መሠረት በየተቋማቱ ከተደራጁት የሥነምግባር መኮንኖች እና የየትምህርት ቤቱ የሥነዜጋና ሥነምግባር ትምህርት መምህራን፣ የሀይማኖት ተቋማት፣ የሙያ ማህበራት፣ የወጣት ማህበራት፣ የሴቶች ማህበራት፣ የሚዲያ ተቋማትና ማህበራትን በትምህርቱ ሥራ እንዲሳተፉ በማድረግ ድግግሞሽን ጨምሮ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ትምሕርት ለማዳረስ ተችሏል፡፡


ሥነምግባርን የተላበሰና ሙስናን የማይሸከም ዜጋ ከመፍጠር አኳያ የነገ ሀገር ተረካቢ በሆኑት ወጣቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ እሙን ነው፡፡ ከዚሁ አንጻር የሥነዜጋና ሥነምግባር ትምህርት በሀገሪቱ በሁሉም ደረጃ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች በሥርዓት ትምህርት ውስጥ ተካቶ እንዲሰጥ ለማድረግ የተቻለ ሲሆን ይህም ወጣቱን ትውልድ በሥነምግባር፣ በጠንካራ የሥራ ባህል፣ በዜግነት፣ በመልካም አስተዳደርና በመሳሰሉት እሴቶች ኮትኩቶ መገንባት በሀገሪቱ የልማትና ዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አዎንታዊ ሚና እንዲጫዎት ያስችለዋል ተብሎ ይታመናል፡፡


ኮሚሽኑ የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ትምህርቶችን በማስፋፋት ጥረቱ ሚዲያን በስፋት ለመጠቀምና ከነዚህ ወገኖች ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ በዚህ መሠረት ባለፉት 15 ዓመታት ድግግሞሽን ጨምሮ ከ1,176 በላይ የቴሌቪዥንና የሬድዮ አጫጭር መልዕክቶች፣ 48 ያህል የቴሌቪዥንና የሬድዮ ድራማዎች፣ 37 ያህል ቶክ ሾው፣ ፓናል ውይይት፣ የጥያቄና መልስ ውድድር እና ቴሌ ኮንፍረንስ እንዲሁም 3 የኮሚሽኑን እንቅስቃሴ የሚያሳይ ዘጋቢ ፊልሞች የኤሌክትሮኒክ ሚዲያን በመጠቀም በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ለህብረተሰቡ ክፍሎች እንዲደርሱ አድርጓል፡፡


ከላይ ከተጠቀሱት እንቅስቃሴዎች በተጨማሪ 3,920,800 ያህል ቅጅ ያላቸውን መጽሔቶች፣ ብሮሸሮች፣ የኮሚሽኑ የምርመራና የመከላከል ምርጥ ሥራዎችን ያካተቱ ጥራዞች፣ የማስተማሪያ ሞጁሎች፣ በራሪ ወረቀቶች፣ ስቲከሮች፣ ፖስተሮችና የመሳሰሉትን በማሳተም ለመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ ለመንግስት የልማት ድርጅቶችና ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በማሰራጨት የሥነምግባርና የፀረ-ሙስና ትምህርቱ እንዲስፋፋ አድርጓል፡፡


ሀገሪቱ በምትከተለው የፀረ-ሙስና ትግል አቅጣጫ መሠረት በሀገራችን ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል የሥነምግባርና የፀረ-ሙስና ትምህርት ብቸኛው መሳሪያ ባይሆንም በዚህ እንቅስቃሴ ሙስናን የመዋጋት አስፈላጊነትን በህብረተሰቡ ውስጥ የመነጋገሪያ አጀንዳ እንዲሆን ማድረግ ከመቻሉም በላይ ህብረተሰቡ የሙስና ወንጀልን በማጋለጥ፣ በመጠቆምና በመመስከር በአጠቃላይም በፀረ-ሙስና ትግሉ የሚያደርገው ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና በኮሚሽኑ ላይ ያለው አመኔታም በአንፃራዊ መልኩም እየጨመረ እንዲመጣ አስችሏል፡፡


በሁለተኛው የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ኮሚሽኑ የሕጻናት እና የወጣቶች ሥነምግባር ግንባታ ከዋና ዋናዎቹ የትኩረት መስኮች አንዱ ሆኖ እንዲሰራበት በያዘው አቅጣጫ መሠረት የትምሕርት ተቋማትን፣ መገናኛ ብዙኃንን፣ የኃይማኖት ተቋማትን፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎችን እና ሌሎችንም በማሳተፍ ውጤታማ ሥራ ለማከናወን ዕቅድ ተይዞ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡

 

1.2 የሙስና መከላከል ሥራ


የፌደራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ከተሰጡት ተልዕኮዎች አንዱ አግባብነት ካላቸው አካላት ጋር በመተባበር ሙስናና ብልሹ አሠራርን በመከላከል በመንግስት አሠራር ውስጥ ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ማድረግ ነው፡፡ ይህን ለማድረግም ኮሚሽኑ አግባብነት ካላቸው አካላት ጋር በመሆን የመንግሥት መ/ቤቶች እና የመንግስት የልማት ድርጅቶች የአሰራር ሥርዓቶችን በማጥናት ለሙስና የሚያጋልጡ ክፍተቶች እና ብልሹ አሰራሮች ስለሚታረሙበት ሁኔታ ሀሳቦችን ያቀርባል፡፡ በቀረቡ ሀሳቦች መሠረትም ማስተካከያ ሊደረግባቸው በሚገቡ አሠራሮች ላይ ማስተካከያዎች መደረጋቸውን ይከታተላል፤ ለተጠኝ ተቋማት የምክር አገልግሎትም ይሰጣል፡፡


በተለይም በመንግስት መስሪያ ቤቶች እና የልማት ድርጅቶች ውስጥ ስትራቴጅያዊ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ባላቸው ተቋማት ላይ በቋሚነት ክትትል በማድረግ ብልሹ አሰራር እና ሙስና እንዳይከሰት የእርምት እርምጃ እንዲወሰድባቸው በሚያስፈልጉ አሠራሮች ላይ ሐሳብ በማቅረብ አፈጻጸሙን ይከታተላል፡፡


ኮሚሽኑ ለሙስና የተጋለጡ የመንግሥት መ/ቤቶችና የልማት ድርጅቶች አሠራሮችን በተመለከተ ከሕብረተሰቡ ጥቆማ ሲደርሰው አስቸኳይ የሙስና መከላከል ተግባራትን ያከናውናል፡፡ ለአብነትም ከመንግሥት የግዥ ህግ ውጭ ሊካሄድ የነበሩ ግዥዎችን በማስቆምና ግዥዎቹ ህጋዊ ሥርዓቱን ተከትለው እንደገና እንዲከናወኑ በማድረግ የመንግሥት ገንዘብ ያለአግባብ እንዳይባክን ያደረገባቸው ጊዜያት ነበሩ፡፡ ከዚህ አንፃር ባለፉት 15 ዓመታት በመቶ ሚሊዮኖች ብር የሚጠቀስ የመንግሥት ገንዘብ ሊድን ችሏል፡፡

 

በሌላ በኩል ኮሚሽኑ አዳዲስ ህጎች ሲወጡ ለሙስናና ለብልሹ አሰራር ዝግ መሆናቸውን የማረጋገጥ፣ በዚህም ዙሪያ ምክር የመለገስ ተግባር ያከናውናል፡፡ የተለያዩ አካላት የሥነምግባር ደንብ ሲያዘጋጁ ምክር መስጠትም ሌላው ተግባሩ ነው፡፡ ይህን አገልግሎት ከሚያገኙ ድርጅቶች መካከል የመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ የክልል የፀረ-ሙስና ተቋማት፣ የሥነምግባር መኮንኖች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የግሉ ዘርፍና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ይገኙበታል፡፡


ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ጀምሮ በእስካሁን እንቅስቃሴው በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና የልማት ድርጅቶች ከ648 በላይ የሚሆኑ የአሰራር ስርዓቶችን ተጠኚ ተቋማትን ባሳተፈ መልኩ በአስቸኳይ እና በመደበኛ የሙስና መከላከል ሥራዎች በማጥናትና በመፈተሽ ለሙስና በር የሚከፍቱ አሰራሮችን የመድፈን ስራ አከናውኗል፡፡ ጥናቶቹ ከተጠናቀቁ በኋላ በኮሚሽኑና በተጠኚ ተቋማት በሚደረግ የጋራ ውይይት መግባባት ላይ ለተደረሰባቸው የአሰራር ክፍተቶች የተቀመጡ የመፍትሔ ሀሳቦች እንዲተገበሩ በጋራ በሚቀረፅ የትግበራ ድርጊት መርሀግብር መሠረት የእገዛና የድጋፍ ሥራዎችንም ያከናውናል፡፡
ኮሚሽኑ 30 የሚሆኑ ትላልቅ የመንግሥት ፕሮጀክቶችን በመምረጥ የአፈፃፀም እና የፋይናንስ አጠቃቀም ደረጃን ለህዝብ ይፋ በማድረግ ህብረተሰቡ እነዚህ ፕሮጀክቶች ከሙስናና ብልሹ አሠራር በሚጠበቁበት አግባብ ተሳትፎውን እንዲያጎለብት ጥረት አድርጓል፡፡

2.3 የሙስና ወንጀል ምርመራና ክስ


ሀገራችን በምትከተለው የፀረ-ሙስና ትግል አቅጣጫ መሠረት የሙስና ወንጀል ከመፈጸሙ በፊት የሚደረግ ሙስናን የመከላከል ተግባር በተለይ ጊዜን እና ሀብትን ከብክነትና ከጥፋት ለመታደግ አዋጭነቱ የጎላ ነው፡፡ ይሁንና የሙስና ወንጀል ተፈፅሞ ከተገኘ ሕጋዊ እርምጃ መውሰዱ የሙስና ወንጀል እንዳይስፋፋ ብሎም ትግሉን ለማጠናከር የሚኖረው ፋይዳ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ በመሆኑም የፌደራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ሙስናን አስቀድሞ ለመከላከል ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን የሙስና ወንጀልን የመመርመርና የመክሰስ ተግባራትንም ያከናውናል፡፡


የፌደራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ባለፉት ዓመታት የሙስና ወንጀሎችን በመመርመርና በመክሰስ ረገድ በርካታ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ እስካሁን በርካታ የሙስና ወንጀሎች ተመርምረው በተወሰኑት ላይ ክስ የተመሰረተ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ ከ3 እስከ 23 አመታት በሚደርስ ጽኑ እስራት ተቀጥተዋል፡፡ የኮሚሽኑ ባለፉት ዓመታት ጥፋተኛ የማሰኘት አቅም በመዝገብ ሲታይ በአማካይ 87 በመቶ ነው፡፡ ይህም በሀገሪቱ ደረጃ ካለ ጥፋተኛ የማሰኘት ምጣኔ (conviction rate) የኮሚሽኑ የተሻለ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ የኮሚሽኑ ሙሰኞችን ከሶ የማስቀጣቱ እንቅስቃሴ እያደገ መምጣቱንም አመላካች ነው፡፡


የፌደራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን በሙሰኞች ላይ የእስራት ቅጣት ከማስወሰን ጎን ለጎን በሙስና የተገኘን ሀብት የማሳገድ እና የማስወረስ ሥራዎችን ከማከናወን አኳያም ባለፉት ዓመታት በርካታ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ በፀረ-ሙስና ልዩ የሥነ ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ አዋጅ መሠረት በሙስና የተገኘ ሀብት እና በተፈፀመ ሙስና ምክንያት ለደረሰ ጉዳት ማካካሽያ የሚሆን ተመጣጣኝ ንብረት እንዲወረስ የሚደረግ ሲሆን ይህን ለማድረግም በቅድሚያ በሙስና ወንጀል የተገኘ ነው ተብሎ በሚገመት ንብረት ላይ የእግድ ትእዛዝ ይሰጣል፡፡ በዚሁ መሠረት በሙስና የተገኘ የተጠርጣሪዎች ሀብት እና በተፈፀመ ሙስና ምክንያት ለደረሰ ጉዳት ማካካሽያ ተመጣጣኝ ሀብት እንዲታገድና ጥፋተኝነታቸው ሲረጋገጥም በመውረስ በርካታ መጠን ያለው ጥሬ ገንዘብ፣ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረት ለመንግስት ገቢ ተደርጓል፡፡


ኮሚሽኑ ባለፉት ዓመታት በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ወረራ ወንጀሎችን በመመርመር ከ1.8 ሚሊዮን ካሬ ሜትር በላይ ስፋት ያለው መሬት እንዲታገድ ተደርጓል፡፡ ከዚህ ከታገደ መሬት ውስጥም ከ776,639 ካሬ ሜትር በላይ ቦታ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንዲረከብ ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ያለ ተከሳሾች የአክሲዮን ድርሻና እና ጥሬ ገንዘብ ከ1ዐዐ ሚሊዮን ብር በላይ እንዲታገዱ ተደርጓል፡፡ ከታገደ ጥሬ ገንዘብና የተለያዩ የተወረሱ ንብረቶች ሽያጭ ጨምሮ 35.5 ሚሊዮን ብር በላይ የማስመለስ ሥራ ተሠርቷል፡፡


ከብሔራዊ ባንክ ወርቅ ማጭበርበር ወንጀል እና በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ዱባይ ሲሄድ የተያዘ በድምሩ 96 ኪ.ግ ወርቅ ግምቱ 81,777,777 ብር ለመንግሥት ገቢ እንዲሆን በፍ/ቤት ተወስኗል፡፡ ከዚህ ሌላ የሼባ የብረታብረት ማቅለጫ ፋብሪካና የቀረጥ ማጭበርበር የፈፀሙ ተከሣሾችን ጨምሮ ላደረሱት ጉዳት መካካሻ 11ዐ ሚሊዮን ብር የታገዱ ንብረታቸው እንዲወረስ ክርክር ተጀምሮ በሂደት ላይ ይገኛል፡፡


ባለፉት አመታት ከተደረጉ ምርመራና ክስ ጋር በተያያዘ ልዩ ልዩ ተሽከርካሪዎች የታገዱ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ የፍ/ቤት ክርክር ተጠናቆ የተወሰኑ ተሽከርካሪዎች ለመንግሥትና ለሚመለከተው መ/ቤት እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መኖሪያ ቤቶች እና መለስተኛ ህንፃዎች ታግደው ከነዚህ ውስጥ የተወሰኑት ገቢ እንዲሆኑ ተወስኖ ለመንግሥት ገቢ ሆነዋል፡፡


የፌደራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሀገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትሉ በሚችሉ በግብር እና ታክስ፣ በመሬት አስተዳደር፣ በትላልቅ የመንግሥት ግዥዎች እና በፍትህ አስተዳደር ዘርፍ በሚፈፀሙ ትልልቅ የሙስና ወንጀሎች ላይ ይበልጥ ትኩረቱን በማሳረፍ የሚያደርገው እንቅስቃሴ እየተጠናከረ የመጣ ሲሆን ለአብነትም ከመሬት አስተዳደር፣ ከብሔራዊ ባንክ ወርቅ ማጭበርበር እና ከቴሌኮሙኒኬሽን የ1.5 ቢሊዮን ብር ግዥ ጋር በተያያዘ ባለፉት ዓመታት ያደረጋቸው የምርመራ፣ የክስ መመስረትና በፍርድቤት ውሳኔ የማሰጠት እንቅስቃሴዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ኮሚሽኑ ቀደም ሲል በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ከፍተኛ አመራሮች እና ነጋዴዎች አማካኝነት ከታክስ ስወራ እና ማጭበርበር ጋር በተያያዘ ተፈጽሟል ተብሎ የተጠረጠረን የሙስና ወንጀል የተመለከተ ክስ በፍርድ ቤት መስርቶ ጉዳዩ በሒደት ላይ ይገኛል፡፡


የፌዴራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን የሙስና ወንጀል የመመርመር እና የመክሰስ ስልጣን በመንግስት መስሪያ ቤቶችና የልማት ድርጅቶች ተገድቦ የቆየ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በግሉ ዘርፍ ባንኮችን እና ኢንሹራንሶችን ጨምሮ በሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ጉልህ ድርሻ አላቸው ተብለው በሚገመቱ ዘርፎች የሚፈጸሙ የሙስና ወንጀሎችን የመመመርመርና የመክሰስ ስልጣን በፀረ-ሙስና ህጉ ተካትቶ የኮሚሽኑ የሥልጣን አካል እንዲሆን ተደርጓል፡፡

 

2.4 ሀብትን የመመዝገብና የማሳወቅ ሥራ


በአገራችን የሃብትን የማሳወቅና የማስመዝገብ ሥርዓት ተግባራዊ መሆኑ በአንድ በኩል ሀብታቸውን በማስመዝገብ እና በማሳወቅ ረገድ በህግ ግዴታ የተጣለባቸው የመንግሥት ተመራጮችና ተሿሚዎች እንዲሁም የመንግሥት ሠራተኞች የመንግሥት የሥራ ሀላፊነትንና የግል ጥቅምን ሳይቀላቅሉ በየእራሳቸው መንገድ የሚመሩበትን ግልፅ ስርዓት ከመፍጠር በተጨማሪ ምንጩ የታወቀ ሀብት የያዙ ባለሥልጣናት በሕግ ጥበቃ እንዲደረግላቸው እውቅና ለመስጠት ያስችላል፡፡


ሃብትን ለማሳወቅና ለማስመዝገብ የወጣው አዋጅ ቁጥር 668/2002 ሕዝብ መንግሥትን ይበልጥ እንዲያምን በማድረግ ሕብረተሰቡ ለመንግሥት ፖሊሲዎች፣ ሕጎች፣ መርሐ-ግብሮችና ዕቅዶች ተፈፃሚነት ምቹ ሁኔታና መነሳሳትን እንደሚፈጥር ይታመናል፡፡


አዋጁ ከወጣ በኋላ ከሕዳር ወር 2003 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል፡፡ ይህንኑ አዋጅ ተግባራዊ ለማድረግ ለስነምግባር መኮንኖችና ሌሎች ሃብት አስመዝጋቢዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ለመስጠት በተደረገው እንቅስቃሴ ለ30,087 ሰዎች በሀብት ማሳወቅና ምዝገባ አዋጁና በምዝገባ ማከናወኛ ቅጾች ላይ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ ከሕዳር ወር 2003 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2007 በጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ በተካሄደው የምዝገባ ፕሮግራም ደግሞ 629 የሕዝብ ተመራጮች፣ 2,934 የመንግሥት ተሿሚዎችና 85,250 የመንግስት ሠራተኞች ሀብታቸውን አስመዝግበዋል፡፡ ከእነዚህን የሕብረተሰብ ክፍሎች የምዝገባ መረጃን በማጣራትም ለሁሉም አስመዝጋቢዎች ማለትም ለ93,880 ሀብት አስመዝጋቢዎች የምዝገባ ማረጋገጫ ሰርተፍኬት ተሰጥቷል፡፡ የተመዘገበውን ሀብት መረጃን በተመለከተ 998 ያህል መረጃ ለፍትህ አካላት፣ ለጥናት እና ምርምር እንዲሁም ለሌሎች ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች መረጃ የመስጠት ሥራ ተከናውኗል፡፡


የሀብት ማሳወቅ ምዝገባ ስራውን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (IT) በተደገፈ ሁኔታ ለሕብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እንዲሁም የመረጃውን ትክክለኛነት (verification) ለማረጋገጥ እንዲረዳ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (IT) ዝርጋታ ሥራው (CSM) በተባለ የሕንድ ኩባንያ በመከናወን ላይ የሚገኝ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ኩባንያው የዝርጋታ ሥራውን በማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ ይገኛል፡፡

2.5 ሥነምግባር አውታሮችን የማስተባበር እና የመደገፍ ሥራ


በአንድ አገር የፀረ-ሙስና ትግል የሕብረተሰቡ ሚና የማይተካ መሆኑ ይታወቃል፡፡ይህንንም ታሳቢ በማድረግ የሕብረተሰቡን ተሳትፎ ለማጎልበት ኮሚሽኑ የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ በዚህ መሠረት ሕብረተሰቡ በፀረ-ሙስና ትግሉ የሚያደርገው ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ ይገኛል፡፡ ኮሚሽኑ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በፀረ-ሙስና ትግሉ ዙሪያ የሚያደርገውን ትብብር የሚመራው እና የሚያስተባብረው በሥነምግባር አውታሮች ዳይሬክቶሬቱ አማካኝነት ነው፡፡ በዚህም መሰረት ኮሚሽኑ ባለፉት ዓመታት ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ ከሚዲያ ተቋማትና ማህበራት፣ ከሐይማኖት ድርጅቶች፣ ብዙሐን ማህበራት፣ ንግድና ዘርፍ ማህበራት፣ በህግ ልዕልና ዙሪያ ከሚሰሩ የፌደራል መስሪያ ቤቶች፣ ሙስናን መዋጋትን እንደ አንድ አላማቸው አድርገው ከያዙ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም የሙያ ማህበራት ጋር የጋራ መድረክ እንዲመሰርት አስፈላጊውን ሁሉ አድርጓል፡፡


በተጨማሪም ኮሚሽኑ የክልል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽኖች፣ በመንግስት መ/ቤቶችና የልማት ድርጅቶች ውስጥ የተቋቋሙ የሥነምግባር መከታተያ ክፍሎች፣ ከኮሚሽኑ ጋር የጋራ መድረክ ያቋቋሙ ባለድርሻ አካላት፣ አገር አቀፉ የፀረ-ሙስና ጥምረት፣ ወንጀሎችን በፌደራልም ሆነ በክልል ደረጃ የሚመረምሩና የሚከሱ መንግስታዊ ተቋማት፣ የስነምግባር እና ስነዜጋ ክበባት፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ የሙያ ማህበራት፣ የሚዲያና የሐይማኖት ተቋማት እና ሌሎችም አካላት ሙስናን በመዋጋት ረገድ የሚያድርጓቸውን እንቅስቃሴዎች ከኮሚሽኑ እንቅስቃሴዎች ጋር በማቀናጀትና ትግላቸው ተቋማዊ ቅርጽ እንዲይዝ በማድረግ፣ ስልጠናዎችን በመስጠትና ልምዶችን በማካፈል፣ ከኮሚሽኑ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማጠናከር፣ የምክርና የቴክኒክ ድጋፎችን በመስጠት፣ የሚያጋጥሙ ችግሮችንም ለመፍታት ከእነዚህ ክፍሎችና ከሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ድጋፍ ያደርግላቸዋል፡፡

 

ኮሚሽኑ በበኩሉ በባለድርሻ አካላቱ እንዲከናወኑ ከሚጠብቃቸው ተግባራት መካከል፡- 

 • በእያንዳንዳቸው ውስጥ የሥነምግባርና የፀረ-ሙስና ትምህርቶችን ስርጭት፣
 • የተጠናከረ የፀረ-ሙስና እንቅስቃሴ፣
 • ለሙስና ተጋላጭ ናቸው የሚባሉ ዘርፎችን በተመለከተ አስፈላጊ መረጃዎችን የማቅረብ፣
 • በየተቋሞቻቸው የሙስና ወንጀሎችን በማጋለጥ፣ በመመርመርና በመከላከል ዙሪያ ኮሚሽኑ ለሚያደርጋቸው ጥረቶች ድጋፍ የማድረግ፣
 • ኮሚሽኑ በውክልና የሚሰጣቸውን ኃላፊነቶች በብቃት መወጣት፣ በአጠቃላይ በፀረ-ሙስና ትግሉ በንቃት መሳተፍ ናቸው፡፡

 

3. በዓለም አቀፍ የፀረ-ሙስና እንቅስቃሴ የተደረጉ ተሳትፎዎች


ሙስና የአንድ አካባቢ ወይም የአንድ አገር ችግር ተደርጎ የሚቆጠርበት ጊዜ አልፏል፡፡ አሁን አሁን ሙስና የብዙ አገራትን ህዝቦች እያሰቃየ ያለ ድምበር ተሻጋሪ ችግር ስለመሆኑ አከራካሪ አይደለም፡፡ ይህም ሙስና በትብብር የሚዋጉት እንጅ በተናጠልና ዘለቄታዊነት በሌለው መንገድ ሊያሸንፉት የሚሞክሩት ጠላትም አይደለም፡፡ ይህን ትብብር ለማጠናከር አለም አቀፉ ማህበረሰብ የፀረ-ሙስና ስምምነቶችን በመፈራረምና እነዚህን ስምምነቶች በትብብር ተግባራዊ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ አገራችንም ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ የፀረ-ሙስና ኮንቬንሽኖችን የፈረመች ሲሆን በእነዚህ መድረኮች በንቃት እየተሳተፈች ትገኛለች፡፡ እነዚህ መድረኮችም ከሌሎች ልምድ ለመቅሰም፣ የራሷንም ተሞክሮ ለማካፈል አስችሏታል፡፡


አገራችን ለፈረመቻቸው የእዚህ አይነት ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ተገዥ ከመሆኗም በላይ ለአፈፃፀማቸውም ከተለያዩ አገራትና ድርጅቶች ጋር ተባብራ ለመስራት ዝግጁ ናት፡፡ በዚህ ረገድ አገራችን የተባበሩት መንግስታትና የአፍሪካ ህብረት የፀረ-ሙስና ኮንቬንሽኖች ፈራሚና አጽዳቂ አገር መሆኗ ይጠቀሳል፡፡ በእርግጥ አገራችን በእነዚህ ስምምነቶች ውስጥ ያሉ መርሆዎችንና ድንጋጌዎችን ስምምነቶቹን ከማፅደቋ በፊትም ቢሆን እየተገበረች የቆየች ቢሆንም ስምምነቶቹን ከፈረመች በኋላ ደግሞ በስምምነቱ የተቀመጡ መርሆዎችን መሰረት በማድረግ የፀረ-ሙስና ትግሉን ለማጠናከር እየሠራች ነው፡፡

 

4. የሪፎርም ሥራዎች


የኮሚሽኑን አሠራር የሚያሻሽሉ እና ውጤታማ የሚያደርጉ የሪፎርም ሥራዎች በማከናወን የሕብረተሰቡን እርካታ ለማሳደግ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ በዚህ ረገድ በኮሚሽኑ ከተከናወኑ ሥራዎች መካከል BPR, BSC እና የዜጎች ቻርተር ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ይህንኑ መሠረት በማድረግም የለውጥ ሠራዊት ለመገንባት በተደረገው ጥረት መልካም የሚባሉ ውጤቶች እየተመዘገቡ የሚገኙ ሲሆን ከዚህ የላቀ ውጤት ለማስመዝገብም ብዙ መሠራት እንዳለበት በማመን ተከታታይ ጥረቶች በመደረግ ላይ ይገኛሉ፡፡


ምንጭ፡- የፌደራል የሥነምግባርና የጸረ ሙስና ኮምሽን

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
374 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

 • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

 • Aaddvrrt5.jpg
 • adverts4.jpg
 • Advertt1.jpg
 • Advertt2.jpg
 • Advrrtt.jpg
 • Advverttt.jpg
 • Advvrt1.jpg
 • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1079 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us