የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአደረጃጀትና የአወቃቀር ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው

Wednesday, 16 August 2017 12:17

 

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መዋቅራዊ አደረጃጀት፣ የሥራ አስፈጻሚውና የዳኝነቱ ሥራ መቀላቀሉ፥ ለአሠራር ሥርዓት ክፍተት፣ ለመልካም አስተዳደር ዕጦትና ለፍትሕ መዛባት ምክንያት እንደሆነ የሚጠቅስ ጥናት በግንቦት ወር 2009 ዓ.ም መጀመሪያ ለቅዱስ ሲኖዶስ ቀርቦ ከታየ በኋላ ጥናቱ ከሕግ አንጻር ተመርምሮ ለጥቅምት 2010 ዓ.ም ስብሰባ እንዲቀርብ መወሰኑ የሚታወስ ነው።

 

 

የቤተ ክርስቲያኒቱን መሠረታዊ ችግሮች አጥንቶ ከመፍትሔ ሐሳቦች ጋራ እንዲያቀርብ ቅዱስ ሲኖዶሱ ባለፈው ዓመት ጥቅምት ምልአተ ጉባኤ የሠየመው ከፍተኛ ኮሚቴ ባረቀበው ጥናታዊ ሪፖርት፥ በጠቅላይ ቤተ ክህነትና በሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ደረጃ የተቋቋመ መንፈሳዊ ፍርድ ቤት ቢኖርም፣ የአሠራር ደንብ ያልተዘረጋለትና ብቁ ባለሞያዎች ያልተካተቱበት የይስሙላ መዋቅር መሆኑን ተችቷል።

 

ለቅዱስ ሲኖዶሱ ተጠሪ ኾኖ የተቀመጠው መንፈሳዊ ፍርድ ቤቱ፣ የዳኝነትና የፍትሕ ተግባር ከመሥራት ይልቅ፣ በሥራ አስፈጻሚው ጥላ ሥር ኾኖ የአስፈጻሚነት የሚመስል ሥራ መሥራቱ፣ የአስተዳደር በደል ደርሶብኛል የሚለው ካህንና ምእመን፣ ተገቢውን ፍትሕና የዳኝነት አገልግሎት እንዳያገኝ ምክንያት መኾኑን ጥናታዊ ሪፖርቱ ገልጿል።

 

ካህናትና ምእመናን፣ በብዛት እየተሰበሰቡ ውሳኔ ወደሰጣቸው አስፈጻሚና ወደ ዋናው የሕግ አውጭ አካል (ቅዱስ ሲኖዶስ) እንዲሁም ወደ መንግሥት መደበኛ ፍርድ ቤት ለመሔድ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ፣ እንግልትና መንከራተት በሰፊው ተንሰራፍቶ የሚታየው፣ መንፈሳዊ ፍ/ቤቱ፣ ቀድሞ በነበረው ልማድ ያለበቂ ሥራ በመቀመጡ እንደሆነ ጥናቱ አስረድቷል።

 

በየመዋቅሩ የሚገኙት ሥራ አስፈጻሚዎች በሚሰጡት ውሳኔ ቅር የተሰኘ አካል የሚያቀርበውን አቤቱታና የፍትሕ ጥያቄ የሚተረጉምና የሚዳኝ ሥርዓት ባለመኖሩ፣ የአስተዳደር ሓላፊዎች ሥልጣናቸውን ያለገደብ እንዳስፈለገ የሚተገብሩበት አጋጣሚ በስፋት እንደሚታይ በጥናቱ ተጠቅሷል።

 

የመዋቅራዊ አደረጃጀት ችግር በተለይም፣ የሥልጣን በአንድ ቦታ መከማቸትና የሕግ አውጭው፣ የሕግ አስፈጻሚውና የሕግ ተርጓሚው አካላት ተለይተው አለመደራጀታቸው፣ የተጠያቂነት የአሠራር ሥርዓት እንዳይዳብር ያደረገ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ችግሮች ሁሉ ዋነኛ መንሥኤ እንደሆነ ጥናታዊ ሪፖርቱ አመልክቷል።

 

 

መዋቅራዊ አደረጃጀቱ፥ የቤተ ክርስቲያኒቱን ተልእኮ የሚያሳካ፣ ዓላማዎቿንና ግቦቿን ለማስፈጸም በሚያስችል አኳኋን፣ ስትራቴጅያዊና መሠረታዊ በሆነ መልኩ መልሶ ሊደራጅና ሊስተካከል እንደሚገባ የጠቆመው ጥናቱ፤ በዐዲሱ መዋቅራዊ አደረጃጀት ለመሥራትም፣ ቅድሚያ ሊሰጣቸውና በአስቸኳይ ሊወጡ ይገባቸዋል ካላቸው ቃለ ዓዋዲዎች መካከል፥ የዳኝነት አካሉን ከነዝርዝር ተግባሮቹ እንዲሁም የመዋቅሩን ተዋረድ፣ የአሠራር ሥርዓቱን የሚገልጽና የሚደነግግ ሕግ ይገኝበታል።

 

በአጥኚ ኮሚቴው በቀረበው የዐዲስ መዋቅር አማራጭ መሠረት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ መንፈሳዊ ፍርድ ቤት፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ ሥልጣን ባለው በቅዱስ ሲኖዶስ በገለልተኝነት መዋቀር እንዳለበት ነው የተጠየቀው።

 

 

ፍርድ ቤቱ፣ በሕገ ቤተ ክርስቲያን በተሰጠው ሓላፊነትና ሥልጣን፦ የፓትርያርክ፣ የቋሚ ሲኖዶስና የጠቅላይ ቤተ ክህነት ክፍሎች ጣልቃ እንደማይገቡና ሥራውን በገለልተኝነት እንዲሠራ፤ የመጨረሻ የይግባኝ የፍትሕ ዳኝነት ግን የቅዱስ ሲኖዶስ እንደሆነ በጥናቱ ተገልጿል። የፍርድ ቤቱ ችሎትና ዳኝነትም፣ በሚወጣው ደንብና መመሪያ መሠረት እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ያለውን የፍትሕ ሥራ በማቀናጀት እንደሚሠራ ተጠቁሟል።

ግንቦት 1 ቀን 2009 ዓ.ም ምሽት፣ የመክፈቻ ጸሎቱን በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ያካሔደው፣ የቅዱስ ሲኖዶሱ የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ፣ ከግንቦት 2 ቀን ጀምሮ ከተነጋገረባቸው ዐበይት አጀንዳዎች መካከል፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን አወቃቀር ጨምሮ የቤተ ክርስቲያኒቱን መሠረታዊ ችግሮችና የመፍትሔ ሐሳቦች የሚጠቁመው ጥናታዊ ሪፖርት እንደሚገኝበት ታውቋል።

 

በሕገ ቤተ ክርስቲያኒቱ መሠረት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በምታስተዳድራቸው ካህናት ምእመናን ላይ የመንፈሳዊ ዳኝነት ሥልጣን ያላት ሲሆን፤ ወንጀል ነክ ከሆኑ ጉዳዮች ውጭ፦ ካህናት፣ ኤጲስ ቆጶሳትና ሊቃነ ጳጳሳት መንፈሳዊ አገልግሎታቸውን በሚመለከት ቢከሠሡ ወይም ቢከሡ፣ ጉዳያቸው፣ በቤተ ክርስቲያን ሕግና ሥርዓት ይታያል እንጅ በመደበኛ ፍርድ ቤቶች እንደማይዳኙ ተደንግጓል። የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደራዊ ዳኝነት እንደ ክሡ አቀራረብ እየተመዘነ ከሚታይባቸው አካላት መካከልም፣ መንፈሳዊ ፍርድ ቤት አንዱ እንደኾነ በሕጉ ተመልክቷል።

 

ቤተ ክርስቲያኒቱ በ2003 ዓ.ም.፣ “የፌዴራል መንፈሳዊ ፍርድ ቤቶችን እንደገና ለማቋቋም፣ ለማደራጀትና ለማጠናከር የወጣ ዐዋጅ/ቁጥር 2003” በሚል፣ የዳኝነት ሥርዓቷን ለማደራጀትና በኦፊሴል እንዲሠራበት ለማድረግ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ አጽድቃ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብትልክም፣ ውሳኔው በመዘግየቱ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለአስተዳደር ሥራዋ ልታገኝ የሚገባትን የሕግ ድጋፍ እንዳላገኘች በአጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባ የጋራ መግለጫ አማካይነት ቅሬታዋን አሰምታለች። ቅዱስ ሲኖዶሱም፣ ጉዳዩን ተከታትሎ የሚያስፈጽም አካል እንዲሠይም በመግለጫው መጠየቁን በወቅቱ መዘገባችን የሚታወስ ነው።

 

ይህ ጥናት በሶስት ሊቃነጳጳሳት፣ በሁለት ሊቃውንት፣ በሁለት ምሁራን እና በአንድ የመንግስት ተወካይ አባለ፤ የሆኑበት ኮሚቴ ተጠንቶ የቀረበ ሲሆን ከአጠቃላ ይዘቱ መካከል የሚከተለው ይጠቀሳል።

 

መዋቅራዊ አደረጃጀት፣ ሕግ፣ ደንብና

የአሠራር ስርዓትን በሚመለከት

 

አጠቃላይ

በዚህ ምዕራፍ የተካተቱት መዋቅራዊ አደረጃጀትና፣ ሕግንና ደንብን የተከተለ የአሠራር ሥርዓትን በተመለከተ የተደረገውን የነባራዊ ሁኔታ ዳሰሳ፣ ውጤቶችና ግኝቶች እንዲሁም ማጠቃለያና የመፍትሔ ሃሳቦችን የያዙ ጉዳዮች የተካተቱበት ነው።

 

የጥናቱ ነባራዊ ሁኔታ ዳሰሳ

የመዋቅራዊ አደረጃጀት ይዞታ ሲዳሰስ

 የተደረገው ዳሰሳ እንደሚያመለክተው የቤተ ክርስቲያኒቱ የመዋቅርና የአደረጃጀት መሠረት የሆኑት ሕገ ቤተክርስቲያኑና ቃለ ዓዋዲው ናቸው።

በሕገ ቤተ ቤተክርስቲያኑ ምዕራፍ ሁለት አንቀጽ አሥር መሠረት የቤተ ክርስቲያን የሥልጣን መዋቅር ከቅዱስ ሲኖዶስ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ ከላይ ወደታች የተዘረጋ ሲሆን፤ በዚህም መሠረት፡-

1.  ከቅዱስ ሲኖዶስ ውስጥ፡-

-    የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ

-    ቅዱስ ፓትሪያርክ

-    ቋሚ ሲኖዶስ

-    የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት

2.  የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት

3.  የአህጉረ ስብከት ቤተ ክህነት ጽ/ቤት

4.  የወረዳ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት

5.  የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባዓ ጽ/ቤት

 

የቤተ ክርስቲያኒቱ የሥልጣን መዋቅር ሆነው ተደንግገዋል።

 በዚሁ ሕገ ቤተክርስትያን ውስጥ የከፍተኛ መንፈሳዊ ሙያና የቁጥጥር ነክ ሥራዎችን የያዙና በበጐ አድራጐት ነክ ሥራዎች ከውጭ ሀገሮች ድርጅቶች ጋር ግንኙነት ያላቸው ድርጅቶች መዋቅራዊ ተጠሪነት ለቅዱስ ሲኖዶስ ሆኖ ተደንግጓል።

በቃለ ዓዋዲው መሠረት ደግሞ የቤተክርስቲያንን አንድነትና አስተዳደሩን ለማጠናከር ቤተ ክርስቲያን በካህናትና በምዕመናን ህብረት በሰበካ ጉባዔ እንድትደራጅ ሲደነገግ፡- አመራርና አስተዳደርዋ በማህበረ ካህናቱና በምዕመናኑ ጠቅላላ ጉባዔ በተመረጡ ቅዱስ መንፈስ ባደረባቸው ኃላፊዎች ሥራ አስፈፃሚነት እንዲካሄድ ይደነግጋል። የሥራ አለመግባባት ቢፈጠር በፍትህ መንፈሳዊ እንዳታይና እንዲወሰን ተደንግጓል።

·         በቅዱስ ሲኖዶስ በፀደቀው ቃለ ዓዋዲ ምዕራፍ 2 አንቀጽ 4 ላይ በተደነገገው መሠረት የሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ በአራት ደረጃዎች ተዋቅሮ እንዲሰራ ተወስኗል። እነኝህም፡-

-    የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ

-    የመንበረ ጵጵስና ሀገረ ስብከት ጠቅላላ መንፈሳዊ ጉባዔ

-    የወረዳ ሰበካ ጠቅላላ መንፈሳዊ ጉባዔ

-    የአጥቢያ ቤተክርስቲያን ሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ

·         የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ፤ የመንበረ ጵጵስና ሀገረ ስብከትና የወረዳ ሰበካ ጠቅላላ መንፈሳዊ ጉባዔዎች በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚሰበሰቡ በመሆኑ የጉባዔዎቹን ውሳኔዎች እየተከታተሉ የሚያስፈጽሙ የአስተዳደር ጉባዔዎች (ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴዎች) አሏቸው።

·         የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ በዓመት ሁለት ጊዜ የሚሰበሰብ በመሆኑ የአጥቢያ ቤተክርስቲያኑን አስተዳደራዊ ሥራዎች የሚመራ በየ15 ቀኑ የሚሰበሰብ አንድ የሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባዔ አለው።

·         በሥራ ላይ ያሉት አደረጃጀቶች በዝርዝር ሲፈተሹ የሚከተለውን ይመስላሉ፡-

·         የቅዱስ ሲኖዶስ መልዓተ-ጉባዔ የመጨረሻውና ከፍተኛው የቤተ ክርስቲያኑ የሥልጣን አካል ሲሆን፤ በመደበኛ ሁኔታ በዓመት ሁለት ጊዜ (ጥቅምት 12 ቀንና ትንሳዔ በዋለ በ25ኛው ቀን-በርክበ-ካህናት) እየተሰበሰበ በቤተክርስቲያኒቱ ከፍተኛና የፖሊሲ የስትራቲጂያዊ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ይሰጣል። አስቸኳይና ድንገተኛ ጉዳይ ሲያጋጥም በማናቸውም ጊዜ ስብሰባ ያካሂዳል።

·         የቅዱስ ሲኖዶስ መልዓተ ጉባዔውን ውሳኔዎች የሚያስፈጽምና ሥራዎቹን የሚያቀናጅና የሚያደራጅ እንዲሁም አስተዳደራዊና የጽሕፈት አገልግሎት የሚሰጥ የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት አለ።

·         የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ የወጡ ሕግጋትን፣ ደንቦችንና መመሪያዎችን፣ ውሳኔዎችን በሥራ ላይ መተርጐማቸውን የሚከታተልና የሚቆጣጠር በየሦስት ወሩ አባላቱ እየተቀያየሩ የሚሠራ ቋሚ ሲኖዶስ በመባል የሚጠራ አካል አለ፡-

·         የቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት የሚባል በቅዱስ ፓትርያርኩ ቢሮ ውስጥ ይገኛል።

·         የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በዋና ሥራ አስኪያጁና በምክትል ሥራ አስኪያጅ የበላይ አስተባባሪነት በሥሩ የቤተ ክርስቲያኒቱን ዓላማዎች የሚያስፈጽሙና የድጋፍ አገልግሎት የሚሰጡ 17 (አሥራ ሰባት) መምሪያዎችንና አገልግሎቶችን ይዞ ይሠራል። ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የወል ውሳኔ በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ የሚመክር የአስተዳደር ጉባዔ አለው።

·         አህጉረ ስብከቶችና የወረዳ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶችም እንደ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ተቀራራቢ የሆነ መዋቅራዊ አደረጃጀት አላቸው።

·         የቤተ ክርስቲያኒቱ አካል የሆኑ ነገር ግን የየራሳቸው የመቋቋሚያ ደንብና መዋቅር ያላቸው በሥራ አመራር ቦርድና በዋና አስፈፃሚ የሚመሩ ድርጅቶችና ኮሌጆች አሉ።

·         የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መዋቅር እንደ ወረዳና እንደ ሀገረ ስብከት ተመሳሳይ ቢመስልም አመራር የሚያገኘው በሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ ጽ/ቤት አማካይነት ነው።

 

ሕግ፣ ደንብና የአሠራር ሥርዓት ሁኔታ ሲዳሰስ

 የቤተ ክርስቲያኒቱን ያሠራር ስርዓት የሚገልፁ ሕጐች፣ ደንቦችና መመሪያዎች በተሟላ መልኩና ባለቀላቸው ሰነዶች መልክ ያልተዘጋጁና ለሚመለከታቸው ሁሉ በሰፊው ያልተሰራጩ ቢሆኑም የሚከተሉት ይገኙባቸዋል፡-

-    መጽሐፈ ዲድስቅልያና ፍትሀ ነገሥት መጻሕፍት የሕግና የስርዓት መጻሕፍት በመሆን በቤተ ክርስቲያኒቱ ተቀባይነት ያገኙ ናቸው።

-    ሕገ-ቤተ ክርስቲያን የቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ ሕግ ነው። በሁሉም የቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅሮች ላይ ተፈጻሚነት አለው።

-    ቃለ ዓዋዲ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ ደንብ ሲሆን፤ በሁሉም የቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅሮች በስፋት የተሰራጨና ምዕመናን ጭምር በሚገባ የሚያውቁትና እንደዋንኛ ሕግ አድርገው የሚጠቅሱት ነው።

-    የሠራተኞች አስተዳደር ደንብ (በ1988) በቅዱስ ሲኖዶስ ፀድቆ ከጠቅላይ ቤተክህነት እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እንዲሠራበት የወጣ ሲሆን በሥርጭት፣ በዕውቅና በትግበራ በኩል ችግር የሚታይበት ነው።

 ከላይ ከተገለጹት ውጭ በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቀው የወጡና በሥራ ላይ እንዲውሉ የተደረጉ የቋሚነት ባህርይ ያላቸው ሕጐችና ደንቦች ባይኖሩም በየደረጃው ያሉ አስፈጻሚዎች የሚያወጧቸው መመሪያዎች በቀላጤ ደብዳቤ መልክ እየተሰራጩ በሥራ ላይ እንዲውሎ የመደረግ ልምድ አለ።

 ራሳቸውን ችለው በሥራ አመራር ቦርድ የሚመሩት ድርጅቶች በማቋቋሚያ ደንብ የተደራጁ ሲሆን የየራሳቸው መዋቅርና የውስጥ ያሠራር ስርዓት ደንብና መመሪያ አላቸው።

 

መረጃና ትንተና

በቃለ መጠይቅ፣ በጽሑፍ መልስና በሰነድ ዳሰሳ የተገኙትን አንኳር ነጥቦች በግንዛቤ ውስጥ በማስገባት፣ ተያያዥነት ያላቸው መዋቅሮች፣ ጥናቶች ያጋጠሙ ችግሮች ወዘተ በመጠቀም የሚከተለው ትንተና ቀርቧል።

 

መዋቅሩንና አደረጃጀቱን በተመለከተ የቀረበ ትንተና

·         የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ ከፍተኛውና የመጨረሻው የስልጣን አካል ሲሆን፤ በዓመት ሁለት ጊዜ ብቻ የሚገናኝ በመሆኑ ለዕለት ተዕለት ሥራዎች ቋሚ ሲኖዶሱ የተወከለ ቢሆንም፤ ከሰባቱ የቋሚ ሲኖዶስ አባላት ውስጥ አራቱ ተለዋጭ አባላት በመሆናቸውና በየሦስት ወሩ የሚቀያየሩ በመሆኑ ጉዳዮችን በስፋትና በጥልቀት አጥንቶ በመወሰን በኩል አንዲ የጀመረውን ሌላው እንደ አዲስ ጥሬ አድርጐ ስለሚያየው ያሠራር ችግር እንዲከሰት ምክንያት ሆኖዋል።

·         በዚህም የተነሳ ቅዱስ ፓትርያርኩና የሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ለኃላፊነት ደረጃቸው በማይመጥኑ በዝርዝር ጉዳዮች ላይ ሳይቀር እንዲሰማሩና ውሳኔ እንዲሰጡ የሆነበት በርካታ አጋጣሚዎች ታይተዋል። ይህም ለሥራ ድርርቦሽ፣ ለኃለፊነት፣ ለተጠያቂነት ክፍተት፣ በሚገባ ላልታሰበበትና ላልተመከረበት ቅጽበታዊ ውሳኔ፣ ላሠራር ስርዐት መፋለስ፣ ለሀብት ብክነት፣ ለሰዎች ወቅታዊ ውሳኔ ባለማግኘት መንገላታትና መጉላላት ለመሳሰሉት የመልካም አስተዳደር ችግሮች ምክንያት ሊሆን በቅቷል።

·         በቅዱስ ፓትርያርኩ ቢሮ የተቋቋመው የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት የቢሮ አካል ሆኖ ለፓትርያርኩ የአስተዳደር አገልግሎት ድጋፍና ለጽሕፈት ነክ ሥራዎች የታሰበ ቢሆንም ያለ አግባብ ራሱን የቻለ ከፍተኛ የመዋቅርና የሥልጣን አካል አድርጐ የሚሠራ በመሆኑ ለሕግና ስርዓት መዛባት፣ ለመልካም አስተዳደር እጦትና ለመሳሰሉ ችግሮች ቀዳዳ የከፈተ አሠራር ሆኖ ታይቷል።

·         የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ፣ ቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ቋሚ ሲኖዶሱ፣ የሲኖዶሱ ጽ/ቤት በአጠቃላይና ከፍተኛ ስትራቴጂያዊና የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ እየመከሩ የመሥራትና ሕጐችንና ደንቦችን እያወጡና እያፀደቁ ኃለፊነታቸውን መወጣት ሲገባ፣ የሥራ አስፈጻሚውን ተግባርና የዳኝነቱን ሥራ ጭምር (ሦስቱንም የሥልጣን አካላት) ይዞ በመተግበር ቀላቅለው የሚሠሩ መሆኑ ለአሠራር ሥርዓት ክፍተት፣ ለመልካም አስተዳደር እጦት፣ ለፍትህ መዛባት ምክንያት ከመሆኑም በላይ እነኝህ ሦስቱ የሥልጣን መርህዎች በየደረጃው ተለያይተውና ተመጣጥነው በቋሚ ሲኖዶሱ ተቋም በአጥጋቢ ሁኔታ የተዘረጉበት ሁኔታ አይታይም።

·         የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የቤተክርስቲያኒቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አካልና የሥራ መሪ በመሆን ቅዱስ ሲኖዶሱ ያወጣቸውን ሕጐች፣ ደንቦችና መመሪያዎች እየፈፀሙ እያለ እንደገና በቋሚ ሲኖዶስ ውስጥ አባል ሆነው መሥራታቸው ራሳቸው የሚወሰኑትን ሥራ በሌላ ስልጣን ራሳቸው መልሰው እንዲያዩት የሚያደርግ ለቁጥጥር የማያመችና ፍትህ ሊያዛባ የሚችል አሠራር እንዲኖር የሚያደርግ ነው።

·         ለቅዱስ ሲኖዶሱ ተጠሪ የተደረጉት መምሪያዎችና ድርጅቶች ሲገመገሙ፡-

-    የቁጥጥርና ምርመራ (ኦዲትና ኢንስፔክሽን) አገልግሎትና የሥርዓትና ሥነ ምግባር ክሚሽን የተባሉት በተሟላ ሁኔታ ተደራጅተው ካለመቋቋማቸውም በላይ ኃላፊነትና ተግባራቸው በግልጽ ተደንግጐ እንዲሠራ ባለመደረጋቸው አንድ ጊዜ ወደ ሲኖዶሱ ሌላ ጊዜ ደግሞ ወደ አስፈጻሚው ጠቅላይ ቤተ ክህነት እየገቡና እየወጡ የሥራ ድርሻቸውን በአግባቡ መወጣት አልቻሉም።

-    የመንፈሳዊ ፍርድ ቤት በቅዱስ ሲኖዶስ ሥር የተደራጀበትን መዋቅራዊ አደረጃጀት ትቶ በአስፈጻሚው አካል በጠቅላይ ቤተክህነት ውስጥ በመግባት የዳኝነት ሳይሆን የአስፈፃሚነት የሚመስል ሥራ የሚሠራ በመሆኑ ማኅበረ ካህናቱም ሆኑ ምዕመናን ተገቢውን ፍትህና የዳኝነት አገልግሎት በተገቢው ሁኔታ እንዲያኙ እያደረገ አይደለም።

-    የሊቃውንት ጉባዔና የውጭ ጉዳይ መምሪያዎች ተግባራቸው የአስፈጻሚነት ዓይነት እንጂ የፖሊሲ አውጭ አይነት ባለመሆኑ ተጠሪነታቸው ለቅዱስ ሲኖዶስ መሆኑ አሠራሩንና አደረጃጀቱን የተዘበራረቀ አድርጐታል።

-    የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን በበጐ አድራጐት ድርጅቶችና ማህበራት አዋጅ ቁጥር 621/2001 መሠረት በኢትዮጵያ ነዋሪዎች በጐ አድራጐት ድርጅትነት በመዝገብ ቁጥር 1560 ተመዝግቦ የሚንቀሳቀስና አጠቃላይ አመራር የሚሰጥ የራሱ የሆነ ጠቅላላ ጉባኤና ፖሊሲ ነክ ጉዳዮችን የሚከታተልና የሚያስፈጽም የሥራ አመራር ቦርድ ያለው ሲሆን፤ በአዋጁ ላይ በተደነገገው መሠረት ተጠሪነቱ ለጠቅላላ ጉባኤ የሆነ የልማት ድርጅት ነው። ስለሆነም ተጠሪነቱ ለቅዱስ ሲኖዶስ መሆኑ ለአሠራር ምቹ ይሆናል።

-    የመንፈሳዊያን ኮሌጆች መዋቅራዊ አደረጃጀትና ኃላፊነት ተጠሪነት በግልጽ በሕጉ ላይ አልተደነገገም። ባለቤትና ቁጥጥር አልተበጀላቸውም።

·         የጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት የቤተ ክርስቲያንን የሥራ አስፈጻሚነትና አስተዳደር የማከናወን ሥልጣን የተሰጠው ከፍተኛው አካል መሆኑ በሕገ ቤተክርስቲያኑ ላይ በግልጽ የተደነገገ ቢሆንም፤ ይህንኑ ከፍተኛ የማስፈጸም ሚና ለመጫወት የሚያስችል ሁኔታ አልተደራጀም፣ በተግባር ሲታይም ይህን ኃላፊነቱን እየተወጣ አይደለም።

ቅዱስ ሲኖዶሱ አንዳንድ ጊዜ የአስፈጻሚነት ዝርዝር ጉዳዮችን ሁሉ ስለሚሠራ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በዚህ ሰበብ ሥራዎቹን ራሱ እየወሰነ ከመሥራት ይልቅ ሁሉንም ወደ ቅዱስ ሲኖዶስ ይዞ የመሄድ ሁኔታ ላይ ያተኮረ በመሆኑ የሥራ ቅልጥፍና እና ውሳኔ አሰጣጥ ላይ ችግር ይታያል።

·         የጠቅላይ ቤተ ክህነት መምሪያዎችም ተገቢው ስልጣንና ኃላፊነት ተሰጥቷቸው የተደራጁ ካመሆናቸውም በላይ በብቁ ባለሙያተኞች የታገዙ ባለመሆናቸው ሥራቸውን በብቃት እየመሩ ናቸው ማለት አይቻልም። የጠባቂነት አስተሳሰብና ተግባር የተንሰራፋበትና ቢሮክራሲያዊ ውጣ ውረድ የበዛበት፣ በዕቅድና በሥራ ፕሮግራም የመመራት ችግር ያለበት ሆኖ ይታያል።

·         የሀገረ ስብከት ጽ/ቤት አወቃቀር ሲፈተሽ ባለበት ክልል /ዞን/ ለሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት አጠቃላይ አመራርና አስተዳደር የሚሰጥ ከፍተኛ የሥራ አስፈፃሚ አካል ሆኖ መደራጀቱ ተገቢ ነው።

የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ በሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቅራቢነት ለጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ቀርቦ በፓትርያርኩ ስምምነትና ፊርማ ሲጸድቅ የሚሾምና ተጠሪነቱ ለሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ሆኖ ከለቀጳጳሱ ቀጥሎ የመሪነት ኃለፊነትና ስልጣን እንዳለው በሕጉ ሲገለጽ በሌላ በኩል በሀገረ ስብከቱ ውስጥ የተቋቋሙት የሥራ ዘርፎችም ተጠሪነት ለሊቀጳጳሱ እንደሆነ በመደንገጉ ሥራ አስኪያጁ ከስም በስተቀር ተግባሩንና ኃለፊነቱን የሚፈጽምበት ያሰራር ስርዓት የለም ማለት ይቻላል። ሥራ አስኪያጁ በሊቀጳጳሱ መልካም ፈቃድ የሚመደብና የሚነሳ በመሆኑ ሥራውን በሙሉ የኃላፊነት መንፈስ ለመሥራት አቅም ስለሚያንሰው ከፍተኛ የሥራ ክፍተት ተፈጥሯል።

·         በየሀገረ ስብከቶቹ ጽ/ቤቶች ውስጥ ያሉት የሥራ ዘርፎች ስያሜዎች ወጥ አይደሉም። ግማሹ ዋና ክፍል፣ ሌላው ክፍል የሚል የተዘበራረቀ ስያሜ አላቸው። አንዳንዶቹ በመዋቅር ያልተፈቀደ የምክትል ሥራ አስኪያጁ መደብ በመዘርጋት ያለ በቂ ሥራ የበለጠ የተዘበራረቀና ለተለያዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችና አግባብ ላልሆኑ ተግባሮች የሚዳርግ ሥራ ይፈጽማሉ።

·         የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አወቃቀር እንደሌሎቹ አህጉረ ስብከት ተመሳሳይ ሆኖ አልተደራጀም። የቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ሀገረስብከት ነው የሚለው ድንጋጌ ግልጽ ባመሆኑ ለበርካታ ውዝግቦች መነሻ ሆኗል። ይህን በመጠቀም አንዳንድ የሀገረ ስብከቱ የሥራ ክፍሎችና የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት ተጠሪነታችን ለፓትርያርኩ ነው በሚል ከሕግና ከስርዓት ውጭ በመሆን በጠቅላይ ቤተ ክህነት የሚሰጠውን አመራር ያለመቀበል አዝማሚያ ሊያሳዩ በቅተዋል። ይህም ስነ ምግባር ከሃይማኖታዊና ከቤተ ክርስቲያኒቱ ስርዓት ውጭ ለሆነ ተግባር፣ ለመልካም አስተዳደር ችግር፣ ለምዝበራ እና ለሌሎች አግባብ ላልሆኑ ተግባሮች በር የከፈተ ሆኖ ተገኝቷል።

·         የታላላቅ ገዳማትና አድባራት መዋቅራዊ አደረጃጀትም ለበላይ አመራሩ መሆኑና ከመደበኛው የቤተክህነት አስተዳደርና አሰራር አንፃር የሥራ ድርርቦሽና ክፍተት በማይፈጥር ሁኔታ ታስቦና ተለይቶ ላለመቀመጡ ከፍተኛ ችግር ይታያል።

·         የሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ መዋቅርና አደረጃጀት ከመደበኛው የቤተ ክህነት አስተዳደርና አሰራር አንፃር የሥራ ድርርቦሽና ክፍተት በማይፈጥር ሁኔታ ታስቦና ተለይቶ ባለመቀመጡ በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ደረጃ ካልሆነ በስተቀር በሌሎቹ የመዋቅር ዕርከኖች ተግባራዊ ሊሆን አልቻለም።

በአጠቃላይ መዋቅራዊ አደረጃጀቱ የሥራዎችን ተዛማጅነትና ውስብስብነት፣ ተመሳሳይ ሥራዎች በአንድ አካባቢ ተጀምረው እዚያው በሚያልቁበት ሁኔታ፣ የተቀላጠፈና ውጤታማ የሆነ አሰራር እንዲሰፍን ካለማድረጉም በላይ ያደረጃጀቱ ክፍተት ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመልካም አስተዳደር እጦት፣ ለሙስና፣ ለመከፋፈልና አገልጋዮቹም ሆነ ምዕመኑ በቤተክርስቲያኒቱ አሠራር ላይ እምነት እስከማጣት የሚያደርስ ሁኔታና ሥጋት እንዳለ የሚያሳይ ነው።

 

ሕጐችን፣ ደንቦችና የአሠራር ሥርዓቶችን በተመለከተ

ሀ/ ቤተ ክርስቲያኒቱ የተቀበለቻቸው እንደ መጽሐፈ ዲድስቅልያና ፍትሃ-ነገሥት የመሳሰሉት የሕግና የሥርዓት መጻሕፍት በሁሉም የቤተክርስቲያኒቶ መዋቅሮች በይፋ ሊሰራባቸው እንደሚገባ በሕግ በግልጽ አልተቀመጠም። የመጽሐፍቱ ስርጭት በጥቂቶች እጅ ብቻ መገኘቱና በስፋት እንዲታወቅ አለመደረጉ ለአሠራር ከፍተኛ ችግር ፈጥሯል።

ለ/ ሕገ ቤተክርስቲያኑ እንደ ዋንኛና የበላይ ሕግነቱ የኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ እምነትን ጠብቆ ለማቆየትና ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ፣ ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋትና የቤተክርስቲያኒቱን አመራርና አስተዳደር በተገቢው ስርዐት ለማስፈፀም የሚያስችሉ ጠቅላላ ድንጋጌዎችና መሠረታዊ መርሆዎች የሚገልፁበት እጥር ምጥን ያለ፣ የሕገመንግሥት ይዘት ያለው፣ ግልጽና በቀላሉ የሚረዱት ሕግ እንጂ እንደ ማስፈፀሚያ ሕግ ዝርዝር ጉዳዮች የሚገለፁበት ሊሆን አይገባም።

ከድንጋጌዎችና መሠረታዊ የሕገ ቤተ ክርስቲያን መርሆዎች ይልቅ የማስፈፀሚያ ዝርዝር ጉዳዮችንም ደበላልቆ የያዘ በቀላሉ የሚለወጥና የሚከለስ መሆኑ ከፍተኛ ችግር ፈጥሯል።

ሐ/ በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ መሠረታዊ መብቶችና ግዴታዎች፣ ሃይማኖታዊ መርሆዎች፣ ፖሊሲዎችና ዓላማዎች ስትራቴጂያዊ አቅጣጫዎች በግልጽ ራሳቸውን ችለው በተለየ ምዕራፍ አልተፃፉም።

መ/ ከሕገ ቤተክርስቲያኑ ላይ የሚፈልቁ፣ ለአፈፃፀም የሚያግዙ ዝርዝር ሕጐችና ደንቦች (ቃለ ዓዋዲዎች) በየዘርፉ መውጣት ሲገባቸው ከሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ ደንብና ከሠራተኛ ማስተዳደሪያ ደንብ በስተቀር እስካሁን ሌሎች ደንቦች አልወጡም።

ሠ/ ቃለ ዓዋዲ በመባል የሚታወቀው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ ደንብ ሰበካ ነክ የሆኑ ጉዳዮች ብቻ ሊገለፁበትና ሊገለገሉበት ሲገባ ሌሎች ጉዳዮችም ውስጥ በመግባት ዝርዝሮችን መግለጹ ለካህናቱም ሆነ ለመዕመኑ ግራ የሚያጋባና የተደበላለቀ ሁኔታን የሚያሳይ ነው።

ረ/ በሁሉም መዋቅሮችና አደረጃጀቶች ኃላፊዎችን ጨምሮ ሕጐችን፣ ደንቦችንና ያሠራር ስርዓቶችን ጠብቆና አክብሮ የመሥራት እመትና ተነሳሽነት ያለ አይመስለም። እያንዳንዱ የመዋቅር አካል ከሕግና ከደንብ ውጭ የፈለገውንና የመሰለውን መሥራት እንደሚችል አስተሳሰብና ተግባር ይታያል። ሕግና ደንብ ሲጣስ ተጠያቂ ስለማይደረግ ዝም ተብሎ ስለሚታለፍ አንዳንድ ግለሰቦችም የሕጐቹን፣ የደንቦቹንና የአሰራር ሥርዓቶቹን ጥብቅ ያለመሆን አጋጣሚና የሥራ ደረጃቸውን በመጠቀም የቤተ ክርስቲያኒቱን ሀብትና ንብረት ለግል ጥቅም የማዋል ሁኔታ ስለሚታይባቸው የመልካም አስተዳደር ችግርና ሌሎች አግባብ ያልሆኑ የምዝበራና የሥነ ምግባር ችግሮች ሊበራከቱ ችለዋል።

ሰ/ የዳኝነት ሥርዓቱን ልክ እንደ ሕግ አውጭው የሲኖዶስ አካል አመጣጥኖ ማደራጀት ሲገባ ቀድሞ በነበረውና በተለመደው አሠራር የመንፈሳዊ ፍርድ ቤት በሚል በጠቅላይ ቤተ ክህነትና በሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ደረጃ የተቋቋመ ቢሆንም፤ ያሰራር ደንብና መመሪያ ያልተዘረጋለትና ብቁ ባለሙያ ያልተካተተበት የይስሙላ መዋቅር በመሆኑ ሁሉም ይህን ሁኔታ በመጠቀም ፍትህ እንዲያገኝ ማድረግ ባለመቻሉ መንፈሳዊ ፍርድ ቤቱ የዳኝነትና የፍትህ ተግባር ከመሥራት ይልቅ በሥራ አስፈጻሚው ጥላ ሥር ሆኖ ያለ በቂ ሥራ የተቀመጠበት ሁኔታ ይታያል። በዚህም ምክንያት የአስተዳደር በደል ደርሶብኛል የሚለው ካህንና ምዕመን ፍትህ ፍለጋ በብዛት በመሰባሰብ ውሳኔ ወደሚሰጠው አስፈጻሚና ወደ ዋናው ሕግ አውጭ አካል እንዲሁም ወደ መንግሥት መደበኛ ፍርድ ቤት ለመሄድ የሚያደርገው እንቅስቃሴ፣ እንግልትና መንከራተት በሰፊው ተንሰራፍቶ ይታያል።

ሸ/ በየደረጃው የሚገኙት ሥራ አስፈጻሚዎችም በሚሰጡት ውሳኔ ቅር የተሰኘ፣ አካል የሚያቀርበውን አቤቱታና የፍትህ ጥያቄ የሚተረጉምና የሚዳኝ ሥርዓት ባለመኖሩ ሥልጣናቸውን ያለገደብ እንዳስፈለገ የሚተገብሩበት አጋጣሚ በስፋት ይታያል።

ቀ/ የፍትሀብሔር ሕግ አንቀጽ 3 ምዕራፍ 1 ቁጥር 398 ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሕግ በኩል እንደ አንድ ሰው እንደምትቆጠርና በዚሁ መሠረት በመሥሪያ ቤቶቹ አማካይነት በአስተዳደር ሕጐች የተፈቀዱትን መብቶች ሁሉ ልታገኝና ልትሠራባቸው እንደምትችል የተደነገገ ቢሆንም፤ በዚህ ሕግ በመጠቀም ሕጐቹንና የዳኝነት ሥርዓቷን በአግባቡ አደራጅታ በመንግሥትም ዕውቅና አግኝቶ እንዲሠራበት ማድረግ አለመቻሏ ከፍተኛ ችግር ፈጥሯል።

በ/ በእያንዳንዱ መዋቅር ውስጥ ያሉ የሥራ ዘርፎች በየዓመቱ የሚያከናውናቸውን ተግባራትና እነኝህን ተግባራት ለማከናወን የሚያስፈልጋቸውን በጀትና ሌሎች ግብዓቶች የሚገልጽ የሥራ ዕቅድና ፕሮግራም እያወጡ የሚሰሩበት መንገድ ባመዘርጋቱ ሥራዎችን አቅዶ ለመሥራትና አፈጻጸማቸውንም ለመገምገም የሚያስችል ያሠራር ስርዓት የለም። ስለሆነም የኃላፊነትና የተጠያቂነት አሠራር ፍጹም አናሳ የሆነበት ወይም የሌለበት ሁናቴ በሰፊው ይታያል።

ተ/ የሠራተኞች አስተዳደር ደንብ መኖሩ ጥሩ ቢሆንም፡-

-    ደንቡ ከላይ እስከታች በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ኖሮት በሥራ ላይ እንዲውል ባለመደረጉ ደንቡ እያለ ሥራ አስፈጻሚዎች ከደንቡ ውጭ እንደፈለጋቸው የሚሠሩበት ሁኔታ ይታያል። ከደንቡ ውጭ የፈለጉትን የመቅጠር፣ የማሳደግ፣ ማዛወር፣ የማገድና የማሰናበት ተግባራትን ይፈጽማሉ።

-    ደንቡም ቢሆን ከወጣ ሃያ ዓመት ያህል ጊዜ (1988) ያለው ሲሆን ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ ባስገባ እና ዘመኑን በዋጀ ሁኔታ ሊሻሻልና ሊስተካከል ሲገባው እስካሁን እንዳለ መሆኑ በሠራተኞች ላይ ከፍተኛ የአስተዳደር ችግር እየፈጠረ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። በዚህም የተነሳ አገልጋዩ ከዓለማዊው ተግባራት ጋር የተደበላለቀ ስነመግባር የሚያንፀባርቅ በመሆኑ ለትችትና ለሀሜት የተጋለጠ ከመሆኑም ባሻገር የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብርና ዝና የሚፈታተን፣ የሠራተኞችን መብት የማያስከብር ሆኖ ተገኝቷል። 

ቸ/ የክህነት አገልግሎት በጥብቅ ዲሲፕሊን ሊፈፀም የሚገባው ነው። የቤተክርስትያን ሥርዓት አምልኮ በሚል በአንድ ወቅት (2006) የቀረበው ረቂቅ ለዚህ ተግባር ሊረዳ ይችል የነበረ ቢሆንም፤ ሰነዱ ተሟልቶና ፀድቆ በሥራ ላይ እንዲውል አልተደረገም። በዚህም የተነሳ ካህናቱ ከዓለማዊ ተግባራት ጋር የተደበላለቀ ሥነምግባርና ዲሲፕሊን ይታይባቸዋል። ይህም የቤተ ክርስቲያኒቱን ሃዋርያዊ ተልዕኮ ለትችትና ለሀሜት የሚያጋልጥ ከመሆኑም ባሻገር ክብሯንም ጭምር የሚፈታተን፤ የሠራተኞችን መብት የማያስከብር ሆኖ ተገኝቷል።

ዓ/ ቤተ ክርስቲያኒቱ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ሀብትና ገንዘብ የምታንቀሳቅስ ሲሆን ይህንኑ በሥርዓት ለመምራት የሚያስችል የራሷ የሆነ የፋይናንስ አስተዳደር ደንብ፣ የግዥና የንብረት አስተዳደር ደንብ ሊኖራት ሲገባ እነኝህ ደንቦች ይፋዊ በሆነ መልኩ ተሟልተው ባለመገኘታቸው አሠራሩ ለብልሹና ውጤታማ ላልሆነ ሥራ የተጋለጠ ነው።

ነ/ በሁሉም መዋቅሮች ውስጥ የሰው ሀብት ልማቱና አስተዳደሩ የሚመራበት የሠራተኞች አስተዳደር ደንብ መኖሩ ጥሩ ጅምር ቢሆንም፤ ደንቡ ሊያካትታቸው የሚገቡ በርካታ ጉዳዮች ተሟልተው አልቀረቡበትም። በተለይም ወሳኝና ቁልፍ የሆኑ የሥራ መደቦች ላይ ያለው ምደባ ዕውቀትን፣ ችሎታንና ልምድን ያገናዘበ ሊሆን ሲገባ ምደባው የሚፈፀመው በዝምድና፣ በጐጥ፣ በትውውቅና በምልጃ መሆኑ ተጠቁሟል። የደመወዝ ስኬል፣ የሥራ ዝርዝር፣ ዓመታዊ የሥራ ውጤት መመዘኛ፤ ወ.ዘ.ተ. ያልተካተቱበት፣ ዘመኑን ያልዋጀ ደንብ ነው።

በተጨማሪም የሠራተኞቹን ብቃት ለማሳደግ የሚያስችሉ የተለያዩ የአቅም ግንባታና የሥልጠና ሥራዎችን አላካተተም። የመንፈሳዊ ኮሌጆቹ በጅምላ ከሚሰጡት አጠቃላይ ሥልጠና ውጭ የቤተክርስቲያኒቱን ቀጣይነት ለማረጋገጥ የሚረዳ በዕቅድና በፕሮግራም የሚመራ የተተኪ ዝግጅት የለም።

ኘ/ የቤተ ክርስቲያኗ ውጭ ግንኙነት በሚመለከት የምትመራበት ግልጽ የሆነ ፖሊሲና መመሪያ የለም። የሥራ ዘርፉም አንድ ጊዜ ወደ ፓትርያርኩ ጽ/ቤት ሌላ ጊዜ ደግሞ ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነት እያለ የሚዋዥቅ ከመሆኑም በላይ፡-

-    በሀገር ውስጥ ካሉ የሃይማኖት ተቋማት ጋር በትብብር እየተሠራ ያለው ተግባር የሚመራበት ሥርዓትና ከቤተ ክርስቲያኑ ጥቅም አንፃር የሚመራበት መመሪያ የለም።

-    ከሌሎች መንግሥታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶችና ተቋሞች ጋር የሚደረገው ግንኙነት በግልጽ በመመሪያ የተደገፈ አይደለም።

-    ከሀገር ውጭ የሚደረግ ግንኙነትን የሚገልጽ ግልጽ መመሪያ አለመኖሩ ቤተ ክርስቲያኒቷ ማድረግ የሚገባትን ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዳትሠራ አድርጓታል።

በአጠቃላይ የሀገርም ሆነ የውጭ ግንኙነቶች የቤተ ክርስቲያኗን ክብርና ጥቅም በሚያስከብር ሁኔታ በፖሊሲ የተደገፈ አሰራር አለመሆኑ ያሰራር ጉድለት አስከትሏል።

 

የትንተናው ውጤቶችና ግኝቶች

የቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅራዊ አደረጃጀትና ያሠራር ሥርዓት ግምገማ ውጤት የሚያሳየው፡-

ሀ/ መዋቅራዊ አደረጃጀቱ የቤተ ክርስቲያኒቱን ተልዕኮ የሚያሳካ፣ ዓላማዎችንና ግቦችን ለማስፈፀም የሚያስችል እንዳልሆነ፡-

ለ/ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሥልጣን ሁሉ ተጠቃልሎ አንድ ቦታ ላይ በሆኑ በሀገር አቀፍም ሆነ በመላው ዓለም እንደሚሰራበት አሰራር የሥልጣን ክፍፍል የሌለውና የሕግ አውጭው፣ የሕግ አስፈፃሚውና የሕግ ተርጓሚው አካላት ተለይተውና ተመጣጥነው የተደራጁበት ሁኔታ እንደሌለ፡-

ሐ/ በመዋቅሩ መሠረት የተደራጁት የሥራ ዘርፎች ያለባቸውን ኃላፊነቶችና ተግባራት በግልጽ የሚያሳይና በሙሉ ኃይል ወደ ሥራ እንዲገቡ የማያደርግና ተጠያቂነት ባለበት ሁኔታ እንዲሠራ የሚያደርግ የአሠራር ሥርዓት በጣም አስፈላጊ እንደሆነ፡-

መ/ የቤተ ክርስቲያኒቱ ዋንኛና የበላይ የሆነው ሕገ-ቤተክርስቲያን እጥር ምጥን ብሎ በግልጽ አቀራረብ ጠቅላላ ድንጋጌዎችንና መሠረታዊ መርሆዎችን በያዘ መልኩ (በሕገመንግሥት መልክ) እንደገና ተስተካክሎ መፃፈና በየጊዜሙ ሳይቀያየር ቋሚና ዘላቂ እንዲሆነ ማድረግ እንደሚያስፈልግ፡-

 

ሠ/ ከሕገ ቤተ ክርስቲያኑ ላይ በመነሳት ለተለያዩ ሥራዎች ማስፈፀሚያ እንዲያግዙ የተለያዩ ሕጐችና ደንቦች ሊወጡ (ሊጻፉ) እንደሚገባ፣ በተለይም የቤተክርስቲያኒቱ ሥራዎች የሚለኩትና የሚመዘኑት የሥራ አስፈፃሚ አካላቱ በሚያከናውኗቸው ተግባራት በመሆኑና የሥራ አስፈጻሚዎቹም ተግባርና ኃላፊነታቸውን በብቃት ለመወጣት ተጠያቂነትን ለማስረጽ የሚያስችሉ ሕጐችና ደንቦች ወጥተውላቸው በነኝሁ ሕጐችና ደንቦች መሠረት ሥራቸውን ሲያከናውኑና ኃላፊነታቸውን ሲወጡ በመሆኑ ይሄው የሕጐችና የደንቦች አወጣጥ ጉዳይ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ህልውና ወሳኝ እንደሆነና ልዩና ወቅቱን የዋጀ የሆነ ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግ፡-

በአጠቃላይ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የሙስና መስፋፋትና የውሳኔዎች አስፈፃሚ ማጣትና ሌሎች ችግሮችም ሊከሰቱ የቻሉት መዋቅራዊ አደረጃጀቱና ያሠራር ስርዓቱ ዘመኑን በዋጀና የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብርና ዝና በጠበቀ ሁኔታ ተስተካክሎ ባለመገኘቱ መሆኑን የጥናቱ ውጤት ያሳያል።

 

የምዕራፍ ማጠቃለያና መደምደሚያ

በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ እየታየ ያለው ችግር እጅግ አሳሳቢ እንደሆነ ከጥናቱ መገንዘብ ይቻላል። ቅዱስ ሲኖዶስ ችግሩን ለመፍታት ያሳየው ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት ተገቢና ወቅታዊ ነው።

ቤተክርስቲያኒቱ የክርስቶስን ወንጌል መንግሥት በማስተማርና በመስበክ፣ ምዕመኖቿን በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ እምነት በመጠበቅ እያከናወነች ያለችው ተግባር ከፍተኛ ነው። ይህንኑ ውጠት ጠብቆ ለማቆየትና የበለጠ አጠናክሮ ለመቀጠል ችግር ፈቺ የሆኑ ሕግ፣ ደንብ፣ መመሪያ፣ መዋቅራዊ አደረጃጀትና ያሠራር ስርዓቶች እጅግ ያስፈልጋሉ።

ምዕመኑም ከቤተ ክርስቲያኒቱ የሚያገኘውን ሃይማኖት ትምህርት መቀበል የሚችለው ከላይ እስከ ታች ያሉት አገልጋይ ካህናት የቤተ ክርስቲያኒቱን አንድነት ጠብቀው፣ ለችግሮቻቸው መፍትሄ አበጅተው በንፁህ መንገድ አገልግሎቱን ሲሰጡት ብቻ ነው።

 

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዲኖር የሚጠበቀው ፍቅር፣ አንድነት፣ ሰላም፣ መልካም አስተዳደር፣ የወንጌል አገለግሎት እንጂ እንደዓለማዊው አሠራር ሀብትና ንብረት በመዝረፍ፣ የግል ጥቅምን በማሳደድ፣ ሥልጣንን ያለ አግባብ በመጠቀም፣ ምዕመናንን በተለያዩ ቡድናዊ ስሜቶች በመከፋፈልና የቤተ ክርስቲያንን ህልውና በመሸርሸር ሊሆን አይገባም።

 

በጥናቱ የተረጋገጠው የችግሮቹ ሁሉ ዋንኛ መንስዔዎች መዋቅራዊ አደረጃጀቱ በአግባቡ የተዘረጋ አለመሆኑ፣ የዕዝ ሰንሰለቱ የላላ፣ የተንዛዛ፣ ለኃላፊነትና ለተጠያቂነት የማያመች መሆኑና ያሠራር ስርዓቱንም ባግባቡ ለማከናወን የሚያስችሉ ሕግና ደንቦች ያለመኖራቸው በመሆኑ እነኝህ መንስዔዎች ከሥር ከመሰረቱ በማጥራት የቤተክርስቲያኗን ህልውና ማስጠበቅ እንደሚገባ ጥናቱ አረጋግጧል።¾

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
552 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 969 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us