እንቦጭ

Wednesday, 23 August 2017 12:46

 

እንደ መግቢያ

 

በተለምዶ water hyacinth (እንቦጭ) ተብሎ የሚጠራው ነው Eichhornia crassipes የአማዞን ተፋሰስ አካባቢ የውኃ ተክል ሲሆን በአብዛኛው በጣም ተፈጥሯዊ የሆነ ወረርሽኝ ነው ። እንቦጭን በፍጥነት ተስፋፊነቱን ምክንያት በማድረግ "100 of the world's worst invasive alien species" ይሉታል ። እንቦጭ መጤ አረም እንደመሆኑ መጠን በተለያዩ ሀገራት ስያሜውና ስነምህዳራዊ ስርጭቱ ይለያያል። ጥናቶች እንደሚያመለክቱት መነሻው የብራዚሉ አማዞን አካባቢ እንደሆነ ነው። “Holm et al., በ1977 'The world's worest weeds" በሚል ባሳተመው ጥናታዊ ፅሁፍ ውስጥ በወቅቱ አሜሪካን ጨምሮ ከ50 በላይ ሀገሮች በእንቦጭ ወረራ ተካሄዶባቸው እንደነበር ያትታል።


የቤልጂየም ቅኝ ግገዥወች በሩዋንዳ ይዞታቸውን ለማስዋብ እንዳመጡት የሚነገረው እንቦጭ በተፈጥሮ ወደ ታችኛው የቪክቶሪያ ሀይቅ ተፋሰስ አከባቢዎች እንደተዛመተና እኤአ በ1988 ጀምሮ በስፋት መታየት እንደጀመረ መዛግብት ያመለክታሉ። በ’ኛም ሀገር በ1965 ለመጀመሪያ ጊዜ በቆቃ ግድብና እና በአዋሽ ወንዝ ላይ ተገኝቷል። ከዚህ አልፎም በጋንቤላ ክልል ረግረጋማ ቦታወች ላይ ይስተዋላል።


እንቦጭ 10 እስከ 20 ሴሜ ርዝመት ያለው፣ ተንሳፋፊ፣ እስከ 5 ሴሜ ስፋት ያለው አበባ ያለውና ጥቅጥቅ ብሎ የሚንሰራፋ ተክል ነው። እንቦጭ ከ 10 እስከ 15 ሳምንት ውስጥ ሲያብብ፤ ዘሩ ደግሞ 15 እስከ 30 አመት በሴድመንት ውስጥ መቆየት ይችላል። ይሁንና አንዳንድ የእንቦጭ ዝርያወች ከ2 እስከ 5 ሜትር ርዝማኔ ሊኖራቸው ይችላል። እንቦጭ ከትሮፒካል እስከ ሞቃትና ዝናባማ አካባቢወች ውስጥ የመብቀል አቅም ያለው። በተለይም በቂ የፀሐይ ብርሃን (22.5 እስከ 35 ዲሴ.) እስከ 90 በመቶ የእርጥበት መጠን ያለበት አከባቢ በፍጥነት ለመዛመት አመች ነው።


በአንዳንድ ሀገሮች እንቦጭን ለሰው ሰራሽ አፀድ ማስዋቢያነት፣ ለወረቀትና ለጌጣጌጥ ስራ፣ ለሽቶና ኮስሞቲክስ፣ ለማዳበሪያና ለእንስሳት መኖ፣ ለአከባቢያው ጥበቃ (ለምሳሌ በካይ የሜታል ውህዶችን በስሩ አጠራቅሞ የመያዝ አቅም አለው) እንዲሁም ለሀይል አቅርቦት ይጠቀሙበታል። ይሁን እንጅ እንቦጭ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዘነ እንደሆነ እዚሁ ጎረቤት ኬንያን አለፍ ካለም ካንቦድያና ጎረቤቶቿን መመልከት በቂ ነው።

 

እንቦጭ ጣና እንዴት ተከሰተ?


መጤ አረም እንደመሆኑ መጠን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ለጣና ምህዳር እንዲጋለጥ የተደረገ ይመስላል። ለምሳሌ በዙሪያው የተኮለኮሉት ሎጅና ሆቴሎች ለግቢያቸው ማስዋቢያነት ባለማወቅ ተጠቅመው ከሆነ ባንድም በሌላ መንገድ ወደ ጣና ምህዳር ለመግባት ቅርብ ነው። በሌላ በኩል አንድ ተንኮለኛ በተን አድርጎት ሊሆንም ይችላል ወይም ለምርምር የታሰበው እንቦጭ ከምርምር ተቋማቱ እንቦጭ ብሎ ወደ ጣና ገብቶ ሊሆን ይችላል። (ሁሉም ነገር ይቻላል በሚለው ከሎ ያምናል)!


ደረጀና ተባባሪ ተመራማሪዎች እኤአ በ2017 ባሳተሙት ጥናታቸው ላይ እንቦጭ ከ50 ሺህ ሄክታር በላይ የጣናን ሀይቅ እንደወረረውና ይህም አስደንጋጭ እንደሆነ ያትታሉ (Tewabe et al.2017)። በተለይ ለመጀመሪያ ጊዜ ከታየበት እኤአ ከ2011 አንስቶ መጠኑ እጅጉን እንደጨመረና ለቁጥጥርም አዳጋች እንደሆነ ጥናታቸው ይዳስሳል።

 

እንቦጭ እና ስነምህዳራዊ ጉዳቱ


በተለይ ለእንደኛ አይነቱ አብዛኻኛውን በእርሻ ለሚተዳደር ህዝብ እንዲሁም በተደጋጋሚ የድርቅና የዝናብ እጥረት ለሚፈትነን፤ በውኃ አካላት ላይ እንደ እንቦጭ አይነት መጤ አረም መከሰት ችግሩን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ያደርገዋል። እንቦጭ በተፈጥሮያዊ ይዘቱ ብዙ ቦታ እንደመሸፈኑ በጣና ውስጥ ያሉ የኦክስጅን፣ የናይትሬትና የአሞንያ መጠን ይቀንሳል። ይህም አሳን ጨምሮ ነባር የጣና ውስጥ ተክሎችን ያጠፋል። ለምሳሌ ጣና ውስጥ የነበረው ሳር ከጊዜ ወደ ጊዜ በእንቦጭ እየተሸፈነ ሲሆን በተለይ ለከብቶች መኖ ሲጠቀሙ የነበሩ የአክባቢው አርሶ አደሮች ላይ ብክነትን አስከትሏል። ከዚህ በላይ በትነት መልክ የውኃን መጠን እንዲቀንስ ያደርጋል። በተጨማሪም በዙሪያው ያሉ የእርሻ ማሳወችን፣ የመስኖና የሀይድሮ ፓወር ሲስተሞችን ያቃውሳል። በጣና ላይ የሚደረግ ትራንፖርትን ያስተጓጉላል። በዝናባ ወቅትም በቀላሉ መንቀሳቀስ ስለሚችል አከባቤያዊ ምህዳሩ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል።

 

እንቦጭን እንዴት መከላከል ይቻላል?


የእንቦጭ አረምን በሶስት ዋና መንገዶች መከላከል ይቻላል። እርግጥ የሚጠይቁት የመዋዕለ ንዋይና የእንቦጭ የስርጭት መጠን የማስወገድ አቅማቸውን ይወስነዋል።


Physical control: ይሄኛው አየነት በሰው ጉልበትና መካኒካል ማሽነሪወችን በመጠቀም የሚተገበር አይነት ነው። በተለይም አፋጣኝ እርምጃ መወሰድ ባለበት ጊዜ ማሽነሪወችን መጠቀም አዋጭና አስፈላጊ ነው። ነገር ግን የሚጠይቀው ኢንቨስትመንት፣ የተሰበሰበውን እንቦጭ መሰብሰብና ማስወገድ ለተግዳሮቱ ማነቆ ነው። ተግባር ላይ ከዋሉት ማሽነሪወች ውስጥ bucket cranes፣ draglines፣ vegetation shredder ይገኙበታል።


Chemical control: ሁሉተኛው አየነት የኬሚካል ርጭት ሲሆን፣ 2,4-D,glyphosateና diquat የተባሉ ኬሚካሎች ጥቅም ላይ ይውላሉ። በጀልባ ላይ በሚገጠም መርጫ ወይም በ አነስተኛ አውሮፕላን መርጨት ይቻላል። ነገር ግን የተርጩት ኬሚካሎች ድህረ ችግር መጠናትና መታሰብ አለበት።


Biological control: ይህም የተለያዩ ነፍሳትን እንቦጭ ላይ በመበተን ለምግብነት እንዲያውሉት እንዲሁም በተፈጥሮ የሚረጩት ኬሚካል እድገቱን እንዲገታና እንዲያመክነው በማድረግ ነው። ምን እንኳ በወጭ ረገድ ተመራጭ ቢያደርገውም ዘለግ ያለ ጊዜ መውሰዱ በፍጥነት እየተዛመተ ላለ እንቦጭ የማጥፋት አቅሙን ያሳንሰዋል።


ሲጠቃለል ሁሉም ተረባርቦ ጣናን መታደግ አለበት። በተለይ መንግስትና የእርሻና ውሃ ሃብት ሚኒስተር አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ አለባቸው።


(ምንጭ፤ ከማኅበራዊ ድረ ገፅ የተወሰደ)

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
970 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 939 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us