“ሚላኖ እንደራሲ ሎጅ እና ሪዞርት” የመቐሌ ሌላኛው ድምቀት

Wednesday, 30 August 2017 13:12

ይህ ወር ለሰሜኑ የአገራችን አካባቢ በእጅጉ የተለየና የድምቀት ጊዜ ነው ማለት ይቻላል። . . . ሻደይ - በሰቆጣ፤ አሸንዳ- በትግራይ፤ ሶለል - በራያ ቆቦ እንዲሁም አሸንድዬ በላስታ አካባቢዎች የልጃገረዶችን ዜማና ጭፈራ አስታኮ ወቅቱን አንዳች ትውስታ ፈጣሪ ያደርገዋል። ቅዳሜ (ነሐሴ 13 ቀን 2009 ዓ.ም) በማለዳ ከአዲስ አበባ ወደ መቐሌ ጉዞ ጀመርን። ሃያ ሁለት የሚሆኑና ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የተውጣጡ አባላት የያዘችው “ነጯ ኮስትር” አዲስ አበባን ተሰናብታ ወደፊት መወንጨፍ ስትጀምር ፀሐይ የብርሃን ጣቶቿን ማሳየት ጀምራ ነበር።

 

በወጣት እና አንጋፋ ጋዜጠኞች (ጓደኛሞች ማለት ይቻላል) የተሞላው ጉዞ በሳቅና በጨዋታ የደመቀ ነበር። ተረቡ፣ ቀልድና ቁምነገሩ እየተፈራረቁ፤ አልፎ አልፎም ዕይታን በሚሰርቁ ውብ በመልክዓ-ምድር ትዕይንቶች እየተቋረጡ ብዙ ተጓዝን። ፀሐይ ሞቅ ስትል የፆም ብቻ የሆነ ቁርሳችንን በቡድን ተከፋፍለን ተመገብን (ባትሪ ቻርጅ አደረግን ይላታል አንድ ጓደኛችን)። ከደብረሲና በኋላ በቁም ነገር የታጀበ ውይይትና ጨዋታ ስር ከዚህም ከዚያም የወሬ መልኩ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወራ (ቡጨቃም ተካሄደ). .  የምሳ ሰዓት አልፎም ቢሆን ኮምቦልቻ ላይ ለምሳ አረፍን። ይሄኔ ፆመኛውና ኢ-ጿሚው ተለየ። ገሚሱ ሽሮ - ገሚሱ ደግሞ ጥብሱን አነከተ። ከሻይ ቡና በኋላ ጉዞው ለአዳር ወደመረጥናት ወልዲያ ከተማ ሆነ። በከፊል ተኝታ በከፊል የነቃች የምትመስለው ወልዲያ በወጣት ወንዶች የቡሄ ጭፈራ ደምቃ ጠበቀችን። መሽቶ ስለነበር በመብረቅ የታጀበውን ዝናባማ ምሽት የደከመ አካላችንን በማሳረፍ አሳለፍነው።

 

እለተ- ሰንበትን በጠዋት ተነስተን የመቐሌ ፀሐይ ለመሞቅ ተጣደፍን። አሸንዳን እያሰብን፣ አከባበሩን እያሰብን፣ የሚገጥመንን የከተማዋን ድባብ እያሰብን፣ የምንጎበኘውን ስፍራ እያቀድን መቐሌ ገባን። ማረፊያችንን ያደረግነው ሚላኖ ሆቴል እንደሆነ ቢነገርም የመቐሌን ምድር የረገጥነው ግን በአሸንዳ ዕለት ተከፍቶ አገልግሎት መስጠት በጀመረው “ሚላኖ እንደራሲ ሎጅ እና ሪዞርት” ነበር።

 

የአፄ ዮሐንስ ልጅ ማለትም ራስ አርአያ ስላሴ እና የእርሳቸው ልጅ የሆኑት የራስ ጉግሳ መኖሪያ ቤት እንደነበር የተነገረን ይህ ግዙፍ ቅጥር ግቢ፤ ወርስ ሆኖ በከተማዋ አስተዳደር በቅርስነት የተመዘገበው ይህ ስፍራ 40 ሺህ ካሬ ሜትር ይሸፍናል። በውስጡም የአይን ማረፊያ የሆኑ ቅርፃ ቅርፆች፤ ቤተሰቦችም ሆኑ ጓደኛሞች ተሰብስበው የሚጨዋወቱባት የጎጆ ቤቶች ባህላዊና ዘመናዊ የሙዚቃ ስራዎች የሚቀርቡበት ግዙፍ አዳራሽና በባህላዊ መንገድ የተዋቀሩ ጥበባዊ ውብ እጅ ስራዎች የሚታዩበት 55 የሚሆኑ ቤቶች ከኢትዮጵያ አልፎ አፍሪካዊንን በሚያንጸባርቅ መልኩም የተገነቡ  መዝናኛዎችን አካቷል።

 

የዚህ ታሪካዊ ስፍራ ባለቤት ደግሞ አቶ ሙሉጌታ ገ/መድህን ይባላሉ። መንግስት ለዲያስፖራዎች ባመቻቸው ልዩ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ መሠረት ከከተማዋ አስተዳደር በጨረታ ያገኙት መሬት መሆኑንም ተናግረዋል። ለግንባታው ከመነሻው የታቀደው ወጪ 245 ሚሊዮን ብር ቢሆንም በሂደት ግን ወጪው ማሻቀቡን ሲነገር ሰምተናል።

 

ይህንን ታሪካዊ ስፍራ ለማግኘት የመጀመሪያው የሆኑት አቶ ሙሉጌታ ለበርካታ ዓመታት በጣሊያን ሀገር በስደት ቆይተዋል። ቀደም ሲል በትግርኛ ፕሮግራም የዳይሬክተርነት ደረጃ ደርሰው እንደነበር የሚያስታውሱት ባለሃብቱ፤ ጣሊያንም ገብተው ለመጀመሪያ ጊዜ በሚላኖ ከተማ ኢትዮጵያዊ መልክ ያላቸውን ሆቴልና ባር በመክፈት የሚቀድማቸው እንዳልነበረ ይጠቁማሉ። ለመቐሌ ከተማ ቀዳሚ ነው የተባለውን ይህንን ሚላኖ እንደራሲ “ሎጅና ሪዞርት” የግንባታና የሥነ-ውበት ግብዓቱ በሙሉ ኢትዮጵያዊ እንደሆነም ተዘዋውረን በጎበኘንበት ወቅት ለመመልከት ችለናል።

 

በባህላዊ እደ-ጥበባት ተዋዝቶ ሀገረኛ ግብዓቶችን ይዞ የተገነባው ይህ “ሎጅ እና ሪዞርት” ለከተማዋም ሆነ ለክልሉ የቱሪስት መዳረሻ ከመሆኑ አንፃር የሚጨምረው አቅም ይኖራል የሚሉት አቶ ሙሉጌታ፤ “ከውጪ ለሚመጡ ፈረንጆች ፎቅ ብቻ ገንብተን ብናሳያቸው በፍጹም አይማረኩም” ይላሉ። ይህ ጉዳይ ገና ጣሊያን ሀገር በነበሩ ወቅትም ያስጨንቃቸው እንደነበር አስታውሰው “በጣሊያን ውስጥ ኢትዮጵያዊ መልኮችን የማሳይባቸው አራት ባሮች፣ አራት ባሮች፣ አንድ ሬስቶራንት እና ሁለት የምሽት ክለቦች ነበሩኝ” ሲሉ ይዘረዝራሉ። ግንባታው ከተጀመረ ቆየት ያለው “ሚላኖ እንደራሲ ሎጅ እና ሪዞርት” በመጠኑም ቢሆን የአሸንዳ ባህልን አስመልክቶ በአዳራሽ በተገኙ እንግዶና በሙዚቃ ድግስ ተከፍቷል። ከወራት በኋላም ሙሉ በሙሉ ግንባታው ተጠናቆ በሙሉ አቅሙ ስራ እንደሚጀምር አቶ ሙሉጌታ ገ/መድህን ነግረውናል።

 

ከከተማዋ ነዋሪዎች ባለፈ ወደ ከተማዋ ለጉብኝትም ሆነ ለዕረፍት ለሚመጡ እንግዶች እንደትልቅ የመዝናኛ ስፍራ ተደርጎ ይወሰዳል በሚል ሃሳብ እየተገነባ ያለውና ለመጠናቀቅም ጥቂት የቀረው ይህ ሎጅና ሪዞርት “መዝናኛነቱ አያጠራጥርም” ተብሎለታል። “ስሰራውም ዘና ብዬ ስለሆነ ሰዎችም ወደዚህ ሲመጡ እንደሚዝናኑበት ባለሙሉ ተስፋ ነኝ” የሚሉት አቶ ሙሉጌታ፤ በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል በየዓመቱ የሚከበረውን አሸንዳን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ እንደመዳረሻ የበኩላችንን እየጣርን ነው ብለዋል።

 

በጣሊያን ቆይታቸው የሚላን ቡድን ደጋፊ እንደነበሩ የሚናገሩት አቶ ሙሉጌታ፤ የማራዶናና የቫንቫስተር ቀንደኛ አድናቂ እንደነበሩም በፈገግታ ተውጠው ያስታውሳሉ። እግር ኳስ በእጅጉ የሚዝናኑበት ስፖርት እንዲሆነም ገልፀዋል። ለዛም ይመስላል ከሮም ይልቅ ሚላንን መርጠው ኑሯቸውን በዚያ ያደረጉት። በዚህ ሂደት ውስጥ አንድ የምትጠቀስ ታሪክም አለቻቸው። ሚላን ውስጥ የከፈቷትን “ብላክ ስታር” የተሰኘች ምሽት ቤት ለመሸጥ ከአንድ ጣሊያናዊ ጋር ይስማማሉ። ለዚህም በምሽት ክለቡ ፈንታ ገዢው ሰውዬ ቤት እና ተጨማሪ ገንዘብ ለመስጠት ይስማማል።

 

ቃል በተገባለት መሠረት ቤት የተሰጠው አቶ ሙሉጌታ ቀሪውን ገንዘብ ለማግኘት ግን ቀላል እንዳልሆነለት ያስታውሳል። በስተመጨረሻም ቀሪውን ገንዘብ በሚመለከት ለመነጋገር በጣሊያናዊው መኖሪያ ቤት ይገኛሉ። በዚህ ውቅት በቤቱ ውስጥ አንድ ግዙፍ ዋንጫ ተቀምጦ ይመለከታሉ። በጣሊያን ሀገር ከተከሳሽ ይልቅ ከሳሽ እንደሚንከራተት የገባቸው አቶ ሙሉጌታም “ይህ የምን ዋንጫ ነው?” ሲሉ ይጠይቁታል። ጣሊያናዊውም የኤሲ ሚላን ዋንጫ መሆኑ ይነገራቸዋል። ለኳስ ካላቸው ፍቅር የተነሳ የሚላንን ዋንጫ ማግኘት ቀላል አልነበርምና በቀሪው ገንዘብ ፋንታ ይሄን ግዙፍ ዋንጫ እንዲሰጣቸው ጠይቀው ተስማሙ። በወቅቱ 50ሺህ ዮሮ የተገመተውን ዋንጫ ይዞ በመምጣት አሁን ድረስ መቐሌ በሚገኘው ሚላኖ ሆቴል- እንግዳ መቀበያ ላይ በክብር ተቀምጦ ይታያል። እውነተኛዋ ዋንጫ ትሁን አትሁን ግድ አይሰጠኝም የሚሉት አቶ ሙሉጌታ፤ ነገር ግን ብሬ ቀልጦ ከሚቀር ቢያንስ ማስታወሻ የሚሆን ነገር ይዤ ተመልሻለሁ ባይ ናቸው።

 

በሶስት ቀናት ቆይታችን በመቐሌ ብዙ ነገሮን ተመልክተናል። መቐሌን ብሎ፣ አሸንዳን ብሎ ሰሜናዊ አካባቢን ለመጎብኘት ወደዚያው ለሚያቀና ሰው ከተማዋ በጣም ሰፊ ናት። የግንባታ አይነት የመብዛቱን ያህል በየመንደሩ እየተሸለኮለኩ የፈለጉበት የሚያደርሱ ባጃጆችም ቀን ከሌት ይሯሯጣሉ። እናም የአሸንዳን በዓል ተንተርሳ መቐሌ ለእንግዶቹ ሽር ጉድ ስትል ከርማለች ማለት ይቻላል።

አሸንዳ በመቐሌ

አሸንዳን ንጋት በዕልልታና በጭፈራ ድምፅ ተውጠን ተጋፈጥነው። ከተማዋ አንዳች ልዩ የባህልና የፌስቲቫል መንፈስ እንደከበባት ያስታውቃል። ልጃገረዶች በቀይ፣ በአረንጓዴ፣ በቢጫና በነጭ የሀገር አልባሳት ተውበው በቡድን- በቡድን ሲጨፍሩ ማየት መንፈስን ያድሳል። ዕለቱ ከፍልሰታ ፆም ፍቺ ጋር የገጠመ በመሆኑም ምግቡና መጠጡ ሁሉ - ሙሉ ሁሉ ዝግጁ የሆነም ይመስላል።

ከዋዜማው ጀምሮ ሮማናት በሚባለው አደባባይ ላይ በርካታ ቁጥር ያለው ህዝብ ተሰብስቦ የልጃገረዶቹን ጭፈራ በማጀብና በመመልከት ይዝናና ነበር። ይህ ቀን ሲመሽ የከተማዋ የጭፈራ መደራሻዎች ማለትም ቀበሌ 14፣16 እና 22 ተብለው የሚጠሩት አካባቢዎች ካለፉት ቀናት በተለየ በወጣት ሴቶችና ወንዶች የዳንኪራ መድረክ ሆነው ሲያመሹ ተመልክተናል። በመላ አገሪቷ የሚደመጡ “ሙዚቃዎች” በየምሽት ክለቦቹ በጉልህ ተሰምተዋል። እግሮች እስኪብረከረኩ፣ ትከሻዎች እስኪናጡ፣ ላቦት እስኪንጠፈጠፉ በደስታ መንፈስ ዳንኪራ ተረግጧል። ወጣቶች ተሰብስበው፤ መጠጥ ጠጥተው፣ በሴቶች ሲከበቡ “ድብድብም” አንዱ መለያ እስኪመስል ድረስ የአሸንዳ ምሽትን በመቐሌ  ምሽት ክበቦች ያሳለፈ ሰው “መቧቀስን” አላየሁም ማለት አይችልም። በቀደሙት ምሽቶች ያልታዩ የግጭት አይነቶች በየቦታው ተመልክተናል። ያም ሆኖ ልጃገረዶች ቀናቸው ነውና በዕድሜ ሳይለያዩ ከእኩለ ሌሊት በላይ በከተማዋ መንገዶችና ጭፈራ ቤቶች በጉልህ ይታዩ ነበር። እናም አሸንዳ የፈጠረላቸውን የነፃነት ምሽት ከሚወዷቸው ጋር ተካፍለውታል ማለት ይቻላል።

 

ሌላው የመቐሌ ትዕይንት ሊባል የሚችለው በቁሳቁስ፣ በፊልም፣ በፎቶና በሃውልት የተሞላው የከተማዋ ከፍታ ማሳያ “ሐውልቲ -ሰማዕታት” ነው። ይህን ግቢ ለመጎብኘት ካረፍንበት ሆቴል በባጃጅ ተሳፍረን በገበያው አቋርጠን ስንደርስ ብዙም ግርግር አልነበረም። መታወቂያ አስይዘን የመግቢያ ትኬት ቆርጠን ስንዘልቅ የግቢው ስፋት ከምንገምተው በላይ መሆኑን ተረድተናል። ይህ ስፍራ ለከተማዋ አንዱ የጎብኚዎች መስህብ እንደሆናትም በምልክታችን ልንታዘብ ችለናል። የሰማዕታት ሀውልቱ ጋር ከመድረሳችን በፊት ቀድመን የምናገኘው በትግል ወቅት ሁሉም በሚባል ደረጃ ታጋዮች ያደረጉት የነበረውን የጎማ ሸበጥ የጫማ ምስል ነው። ይህ የሸበጥ ምስል በሚገርም ግዝፈት በቆርቆሮ ተሰርቶ ለዕይታ ቀርቧል። ከፍ እያልን ደረጃዎችን በወጣን ጊዜ ደግሞ የመቐሌ ከተማ ማማና መለያ የሆነውን ግዙፍ ሃውልት ተከትሎ ግራና ቀኝ የትግሉን ወቅት የሚያስታውሱ ሃውልቶች ቆመዋል።

 

በዚያው ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገኘው የቁሳቁስ፣ የፎቶና የፊልም ምስሎን አካቶ የያዘው አውደ-ርዕይ ቤተ መዛግብት የትግሉን ሂደትና ታጋዮቹ ይጠቀሙባቸው የነበሩትን የጦር መሣሪያ እንድንመለከት አስችሎናል። ይህም የከተማዋ አንዱ የቱሪስት መስህብ ከመሆኑ አንፃር አሸንዳን ብሎ ወደ ከተማዋ የሚመጣ ሰው ይበልጥ ይመለከተው ዘንድ ማስታወሱ አይከፋም። 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
201 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1035 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us