የበጎ ሰው ሽልማት በጎ ያልሆኑ ጉዞዎች፤ ከማመስገን በላይ መተራረም የት ያደርሰን ነበር

Wednesday, 13 September 2017 12:29

ከስናፍቅሽ አዲስ

በመጀመሪያ በጎ ሰውን የማመስገን መንፈስ በኢትዮጵያ ብዙም አይታይም ነበር። ስለ በጎ ሰዎች የማሰብ ስሜቱ በጎንደር ከተማም ነበር። ንስር የተባለ የሽልማት ድርጅትም በ2001 ዓ.ም. በጎ ሰዎችን ላመሰግን እሸልማለሁ ሲል በህግ የሽልማት ድርጅት ሆኖ ተቋቋመ። ከዚያ በኋላ ንሥር የሽልማት ድርጅት በተከታታይ በጎንደር ባህልና ወግ ለሀገር የሰሩ ታላላቆችን ሸለመ፤ በዚህ አግባብም ባለ ሀብቱ አቶ ታዬ በላይ፣ አፍሮ አሜሪካዊው ዶክተር በርናንድ፣ የልብ ህሙማን መርጃው ባለ ራዕይ ዶክተር በላይ አበጋዝ፣ የቱሪዝም አባቱ አቶ ሀብተ ስላሴ ታፈሰ፣ ተመራማሪው አቶ ታለጌታ እንደ ቅደም ተከተላቸው ለመሸለም በቁ።

ከዚህ ሽልማት ከዓመታት በኋላ በአዲስ አበባ በዲያቆን ዳንኤል ክብረት አሳሳቢነት እና ጀማሪነት የበጎ ሰው ሽልማት የሚል ሀሳብ ተጀመረ። በሀሳቡ መነሻ እንዲህ ያለ ነገር በሀገራችን ስላልተሰራ ጀመርነው በሚል ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጥ ግን በጎንደር በጎ ሰው ሽልማት ላይ የታደሙ ጋዜጠኞች ሳይቀር የመጀመሪያው ሀሳብ ብለው ሳይሞግቱት አጮሁት፤ ተጀመረ ቀጠለ።

መቼም በጎ ሰውን እናመሰግናለን ለማለት ለምን እከሌን ተከትሎ እከሌ ቀጠለ አሊያም ጀመረ የሚለው ሙግት መልካም የሚመስልን ሀሳብ የሚያደናቅፍ ስለሚመስለኝ ያን ማንሳቱ ተገቢ አይደለም። በጎ ሰው አደረጃጀት እንዳለው ሰምቻለሁ። ዳኞችም አሉት የሚል ነገር ይደመጣል። ዳኞች ናቸው ተብለው ከቀረቡት ሰዎች መካከል እሱ እያለ እንዴት እንዲህ ያለ ነገር ሆነ የምንለው አንድ ሰው አለ። ሰርጸ ፍሬ ስብሐት ነው። የሙዚቃ ባለሙያው ሰርጸ መልካም እና ብሩህ አእምሮ ያለው ነገሮችን በስል እና በሰከነ መንፈስ የሚያይ ሰው ነው። ይሄን አካሄድ ዝም ብሎ ለማየት ያልፈለግኩትም ለዚሁ ነው።

በኢትዮጵያ ምድር የኖህ ልጅ ምድሪቷን ከሚረግጥበት ቀን እስከ ዛሬ እንዲህ ያለ ቅጥ ያጣ እውቅና አሰጣጥ ሰምቼም፣ አንብቤም፣ በተረት አድምጬም አላውቅም። ስህተቱ የማይነካ ሰው ሀሳብ ሆኖ ሲብስ ቆመን ማየት ቀጥለናል።

በጎ ሰው አንድ በጎ ሰው ለመሸለም አስር በጎ ሰዎችን ቅስም የሚሰብር ከሆነ ይሄ እንደ ሙስናው፣ እንደ አፈናው፣ እንደ መብት ጥሰቱ ሁሉ በህዝቡ ላይ የመጣ መዐት ነው ብዬ አምናለሁ። መስራቹ ለቤተክርስቲያን ቅርብ ነው፤ ቤተክርስቲያን ለዘመናት የማታፍርበት አንድ የአበው ትውፊት አላት። በደቀ መዝሙር በአቻ እና በመምህር መካከል ያለውን ድንበር በአግባቡ የምታስጠብቅ ናት። ይሄንን የሚያፈርሰው የበጎ ሰው ሽልማት ተስፋዬ ገሰሰን ያክል ሰው ከተማሪው ከአለማየሁ ታደሰ ጋር አወዳድሮ አሸንፈሃል ብሎ ሲሸልመው እንደማየት ልብ የሚሰብር ነገር የለም።

ለዚህ ነው በቅኔ ጉባኤ እንኳን መምህር ተማሪው ተማሪ መምህሩ ላይ ቅኔ የማይሞላው። አለም የአቻዎች ናት። አሁን ጋዜጠኛ ንጉሤ አክሊሉ አሸነፈ፤ ተሸለመ። ንጉሤ የሚገባው ሰው ነው። የማይገባው የተወዳደረበት መድረክ ነው። የሸገሩ ጋዜጠኛ እሸቴ አሰፋ እና ሸገር ራዲዮን ተወዳድሮ ንጉሤ አሸነፈ ማለት መልዕክቱ እሸቴና ሸገር አንድ ላይ ሆነው የንጉሤን ያክል አልሰሩም ማለት ነው። እሸቴ በግሉ ቢወዳደርም የሸገርም ዋና አዘጋጅ ነውና።

ተቋም እና ሰውን አንድ ላይ ማን ይበልጣል ብሎ ለውድድር መቀመጥ ሀገሬ እንዴት ያሉ ምጡቅ ባለ አእምሮዎችን አፈራች የሚያሰኝ ስላቅ ውስጥ ይከተናል። ሰው ግለሰብ ነው። ተቋም ተቋም ነው። ለምሳሌ የዘንድሮውን ሽልማት አስቡት ሆስፒታል የመራ እና የኦዲት መስሪያ ቤት የመራ በአንድ ዘርፍ የላቀ ተቋማዊ መሪ ተብሎ ቀርቧል። ያ ጤና ያ ሂሳብ ይሄን ፊደል ማወቅ ሳያስፈልግ የማይሰራ ስህተት በስህተት ሆነ ብዬ ላልፈው ያልፈለኩትም ለዚሁ ነው። አምስት አመታት ሙሉ እንዲህ ያለው አሰራር የቀጠለው በርቱ ባይ አሽሙረኛ በዝቶ ከሆነ ለምን አንድ እድል የራሴን አልሞክርም አስብሎ ሰንደቅ ላይ ያመጣኝም ይሔው ነው።

ለምሳሌ አንድን የታሪክ ምሁር ከአንድ የጤና ምሁር ጋር አወዳድራችሁ ታሪክ አሸንፏል ማለት አንድ ሰው ለመሸለም ሌላ ሰው በሰራው እና ለሀገሩ በኖረው ስሜቱን መግደል እና ክብሩን መንካት ነው። አንድን ታላቅ ተቋም አስር ዳኞች ስለመረጡት ከአንድ ግለሰብ ጋር አወዳድሮ ግለሰቡን መሸለም ሽልማቱን ዋጋ እንዲያጣ ማድረግ ይመስለኛል። ከዚህ ቀደም እንደ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ያሉ ተቋማት ከግለሰብ ጋር ሲወዳደሩ አይተን ስህተት መስሎን ነበር ዘንድሮም ተደግሞ አየነው።

ይህ የበጎ ሰው ሽልማት በጎ ያልሆኑ ጉዞዎች ማሳያ ነው። ማንም መስራት የሚችለው ነገር ለምን እንዳቃታቸው ሊገባኝ አልቻለም። የቻሉት ማንም መስራት ያልቻለውን ጥቂቶች የሚደፍሩትን በጎ ሰው መሸለም ነው። ታዲያ ይሄን የመሰለ ታላቅ ሀሳብ ችሎ እንዴት ተራ ነገር በየዓመቱ ስህተት ሆኖ ይቀጥላል?¾ 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
209 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 972 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us