ከስድስቱ የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ

Wednesday, 13 September 2017 12:40

 

1.  የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ /ኦብኮ/

2.  የኦሮሞ አንድነት ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ /ኦአዲፓ/

3.  ኦሮሞ አቦ ነፃነት ግንባር /ኦአነግ/

4.  የገዳ ሥርዓት አራማጅ ፓርቲ /ገሥአፓ/

5.  የኦሮሞ ነፃነት አንድነት ግንባር /ኦነአግ/

6.  የኦሮሞ ነፃነት ብሔራዊ ፓርቲ /አነብፓ/

እኛ እላይ ስማችን የተመለከተው ስድስቱ በአገሪቱ ውስጥ በሰላማዊ የትግል መስመር እየተንቀሳቀስን ያለን ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የወቅቱ ትኩሳት በመሆን በሁለቱ አጎራባች ክልሎች ማለትም በኦሮሚያና በሶማሌ አዋሳኝ አካባቢ በወንድማማች ሕዝቦች መካከል ከረጅም ጊዜ ጀምሮና እስከ አሁንም ድረስ መፍትሔ ከማግኘት ይልቅ እየተባባሰ የመጣውን ግጭት በሚመለከት ከዚህ በፊትም ይህ ግጭት የኦሮሞን ሕዝብ ሰበብ አስባብ በመፈለግ ከማጥቃት ባለፈ ምንም መነሻ ምክንያት እንደሌለውና ችግሩ ተባብሶ ሌላ አቅጣጫ ከመያዙ በፊት ተገቢው መፍትሔ ተደርጎለት ወንድማማች በሆነው በሁለቱም ሕዝቦች መካከል ዘላቂ የሆነ ሰላም እንዲፈጠር በማለት ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ወገኖች አመቺ በሆኑ መንገዶች ሁሉ ስናሳስብ ቆይተናል። በተለይም የኦሮሚያ ክልል ገዥ ፓርቲ ከሆነው ከኦ.ህ.ዴ.ድ ጋር የጋራ ምክር ቤት ስለአለን ከግጭቱ አጀማመር ጀምሮ ሊመጣ የሚችለውን ውጤት ጭምር ስንገልጽ የቆየን ቢሆንም የክልሉ ገዢው ፓርቲ ግን እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ ግጭቱን የተራ ሽፍታ እንቅስቃሴና ከሁለቱም ክልል መንግስታት እውቅና ውጪ እየተደረገ ያለና ሁኔታውን ግን በቅርበት እየተከታተልን ነው በማለት ሲያጣጥልና ሲያስተባብል ቆይቷል።

ይሁን እንጂ በወታደራዊ ፓትሮል ተሽከርካሪ ላይ በተጠመዱ መትረየሶች የሚታገዝ ወራሪ ኃይል ከዚህም በተጨማሪ ልዩ ድጋፍ እየተደረገለት በባህላዊ የጦር መሳሪያ በሚከላከል የኦሮሞ አርሶ አደርና ባዶ እጁን በሚንቀሳቀስ የኦሮሞ ሚሊሻዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳትና እልቂት እየደረሰ በመሆኑ ሰሚ ጆሮ ከተገኘ ብለን ይህን የስድስቱ ፓርቲዎች የጋራ አቋም የሆነውን መግለጫ ለመስጠት ተገደናል።

 

 

ዝርዝር ሁኔታዎች

1.  አሁን ግጭቱ እየተካሄደበት ያለው አካባቢ ማለትም ከጉርሱም እስከ ሞያሌ ባለውና ከ1200 ኪሎ ሜትር በላይ ወሰን የሚጋሩ የኦሮሞና የሶማሌ ሕዝቦች የጋራ ባህል፣ የጋራ እምነት፣ ሁለቱንም ቋንቋዎችን በጋራ የሚነገሩ በሚያገናኙ የልማት ውጤቶችም የሚገናኙና ከሁሉም በላይ በጋብቻ የተሳሰሩና ምንም ዓይነት ለግጭት የሚያበቃቸው ጉዳይ እንደሌለና አሁንም የተፈጠረው ግጭት የሕዝብ ለሕዝብ ግጭት አለመሆኑ የጋራ እምነታችን መሆኑ፤

2.  እላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው ግጭቱ የሸፈነው የወሰን አካባቢዎች ከ 1200 ኪሎ ሜትር በላይ በመሆኑና በተለይም አጥቂ ወገን ለጥቃቱ የሚጠቀምበት እጅግ ዘመናዊ መሳሪያ በመሆኑ ግጭቱ በግጭት መልክ የሚገለጥ ሳይሆን በአከባቢው በአለው የኦሮሞ ሕዝብ ላይ የተደረገ ያልታወጀ ጦርነት መባል እንደሚችል የጋራ አቋማችን መሆኑን በተጨማሪም ይህ ያልታወጀ ጦርነት ያልነው ድርጊት በህዝባችን ላይ ሲካሄድ የነበረው እንኳንስ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጠቀ ቀርቶ ውሃ እንኳን ከኮማንድ ፖስቱ እይታ ውጪ መንቀሳቀስ በማይችልበት በአገሪቱ ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀበት ወቅት በመሆኑ እልቂቱን እየፈፀመ ያለው የሶማሊያ ልዩ ኃይል ከኋላው አይዞህ ባይ አስተማማኝ ኃይል ያለው መሆኑ የጋራ እምነታችን በመሆኑ፣

3.  በአሁኑ ወቅት ከአካባቢ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙ ከሆነ ወራሪው ኃይል የወረራውን ቀጠና እያሰፋ ከጉርሱም እስከ ሞያሌ እያዳረሰ ሲሆን በሌላ በኩል የኦሮሞ ተጠቂ ሕዝብና ሚሊሽያው የያዘውን ኋላ ቀር የጦር መሳሪያ እንኳን በመከላከያ ሠራዊት አማካይነት እየፈታ እንደሚገኝ ነው።

ስለሆነም በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ወገኖ ስለግጭቱ ምክንያት ልዩ ልዩ ሃሳቦች ቢሰነዝሩም ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን በየእለቱ በወራሪ ኃይል ጥይት እየረገፈ ያለው የኦሮሞ ሕዝብ ነው። በመሆኑም፡-

ሀ. የአገር መከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል መንግስት ወደ አንድ ወገን ያጋደለውን ጣልቃ ገብነት በመተው ፍትሃዊና ሕገመንግስታዊ መሠረት ያለው ጣልቃ ገብነት በመፍጠር ወይም በቀጥታ በመግባት እልቂቱ በአስቸኳይ እንዲቆም፣ በወራሪ ኃይሎች ላይ ተገቢ ፖለቲካዊ፣ ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ፣ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ወገኖች ወደመኖሪያቸው ተመልሰው በተገቢ መንገድ እንዲቋቋሙ፤ የንብረትና የአካል ጉዳት የደረሰባቸውንና ለሞቱት ወገኖቻችን አጥፊ ወገን ተገቢ ካሳ እንዲከፍልና በሕዝቦች መካከል ዘላቂነት ያለው ሰላም እንዲወርድ እንዲደረግ ወገናዊ ጥሪአችንን በድጋሚ እናቀርባለን።

ለ. የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የኦሮሞ ህዝብ በጦርነትና በግድ በስደት በለቀቀው ቀበሌዎችና ወረዳዎች ሕዝብ በሌለበት ሁኔታ ሕዝበ ውሳኔ ለማካሔድ እያደረገ ያለውን መፍትሄ አልባ እንቅስቃሴ በመተው በ1998 ሕዝበ ውሳኔ የተካሄደባቸው አካባቢዎች የሕዝብ ድምፅ እንዲከበር በዚህ ወቅት ህዝበ ውሳኔ ያልተካሄደባቸውን አካባቢዎች አሁን ከመኖሪያ ሰፈራቸው የተፈናቀሉ ነዋሪዎችን ወደ መኖሪያ ሰፈራቸው በመመለስ ከተቋቋሙና ከተረጋጉ በኋላ በሕዝቡ ነፃ ፍላጎት እንዲሁም በሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ወገኖች ጋር በመሆን በሕዝቡ እምነት ብቻ በተጣደፈ ሁኔታ ሳይሆን በተረጋጋ ሁኔታ ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ በተጨማሪም የኦሮሚያ ብሔዊ ክልላዊ መንግስት ቆም ብሎ በማሰብ ለኦሮሞ ሕዝብ ከኛ በላይ ለአሳር ማለቱን ትቶ የኛንም ሃሰብ እንዲያዳምጥ በድጋሚ ወገናዊ ጥሪአችንን እናቀርባለን።

ሐ. ኦሮሞና የሶማሌ ሕዝቦችን የሁለቱን የጋራ ትስስርና አብሮነት በምንም መልኩ አሳጥሮ መግለጽ አይቻልም። በአጭሩ የረጅም ጊዜ የጋራ ታሪክ ያለው በመከራም ሆነ በደስታ በጋራ የምትኖር አሁንም እየኖርክ ያለህ ወደፊትም የምትኖር ማንም ጣልቃ ገብቶ ሊያለያይህ የማይችል፣ የአሁኑም ችግር ያንተ ችግር ወይም የህዝብ ለህዝብ ችግር ሳይሆን የፀረ ሰላም ኃይሎች ችግር ስለሆነ በጥቂት የፀረ ሰላም ኃይሎች እንቅስቃሴ ተጠልፈህ ወደ ግጭት እንዳትገባና የረጅም ጊዜ የጋራ ክብር ዓላማህን ይዘን የጋራ ሰላምህን በጋራ እንድትጠብቅ ወገናዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

ድል የሕዝብ ነው!!!

የስድስቱ የኦሮሞ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች

መስከረም 2010

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
327 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 758 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us