ወቅቱ ከመናገር ያለፈ ተግባራዊ እርምጃን ይጠይቃል!

Wednesday, 04 October 2017 13:10

 

ኢዛና ዘ መንፈስ

 

ሀገራችን የምትመራበት ፌደራላዊ ስርዓት ዋነኛ ዓላማ ካለፈው ታሪካችን በወረስናቸው የተዛቡ የዕርስ በርስ ግንኙነቶች ምክንያት ተፈጥሮ የቆየ የህዝቦቻችንን አሉታዊ ዝምድናን በጤናማ ወንድማማችነት እንዲተካ ማድረግ ነው ማለት ይቻላል። የሀገራችን ሕገ መንግስታዊ ስርዓት ምሰሶዎች ተደርግው ከሚወሰዱት መሰረታዊ በህሪያት መካከል ቀዳሚ ስፍራ የሚሰጠው የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ዕርስ በርስ ተፈቃቅደው፤ ተፈቃቅረውና ተከባብረው እንዲኖሩ ማድረግ የሚለው ነጥብ እንደሆነ የሚያከራክር ጉዳይ አይደለም። ይሁን እንጂ ይህን ቁልፍ ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌ እንደተራ ነገር ቆጥረው ሲጥሱት የሚስተዋሉ የአካባቢ መስተዳደር አካላትም ጭምር መኖራቸው አሳሳቢ ጉዳይ እየሆነ ይገኛል።


ለዚህ ደግሞ በቅርቡ የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ ብሔራዊ ክልሎችን በሚያዋስኗቸው አንዳንድ ተጎራባች አካባቢዎች የተስተዋለው ግጭት እንዲከሰት አድርገዋል ተብለው የሚጠረጠሩ የመስተዳድር አካላት መኖራቸውን ብቻ ማስታወስ ይበቃል። ይህ ዓይነቱ ከሕገ መንግስታችን መሰረታዊ ዓላማ ጋር ፈጽሞ በሚቃረን መልኩ ወንድማማች ህዝቦችን አቃቅሮ ደም እንዲቃቡ የማድረግ የአንዳንድ ኪራይ ሰብሳቢ የመስተዳደር አካላት አስነዋሪነት ተግባር ዛሬ የተጀመረ ጉዳይ እንዳልሆነም ይታወቃል። ስለዚህም የችግሩ በተመሳሳይ መንገድ ሲደጋገም መስተዋል፤ ስለጉዳዩ የሚያውቀው ነገር የሌለውን ሰላም ወዳድ ህዝብ ላላአስፈላጊ የህይወትና የንብረት ኪሳራ ከመዳረግም ባሻገር፤ የፌደራል ስርዓቱን ጠቀሜታ የጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚያስገባ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩ እንደማይቀር መገመት አይከብድም። በሰላማዊ መንገድ ተወያይቶ መተማመንና የጋራ ችግሮችን የሚፈታ ሕገ መንግስታዊ አግባብ መከተል እየተቻለ፤ ክቡሩን የሰው ልጅ ህይወት ወደሚቀጥፍ መሰል ግጭት ማምራትን እንደፈሊጥ የያዙት የመስተዳደር አካላቱ ራሳቸው እንደሆኑ ሲነገር ከመስማት በላይ አስደንጋጭ ዜና ሊኖር አይችልምና ነው እኔ በበኩሌ ስለጉዳዩ የሚሰማኝን ስጋት ለመግለጽ መገደዴ።


ስለሆነም ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን የማክበርና የማስከበር ኃላፊነት በተጣለባቸው አንዳንድ ምግባረ ብልሹ የመስተዳደር አካላት ምክንያት ህብረተሰባችን ለፈርጀ ብዙ ጉዳት ሲዳረግ የሚስተዋልበትን መሰል ግጭትና ቅራኔ በመቀስቀስ ረገድ እጃቸው አለበት የሚባሉ ፖለቲከኞች ላይ ለፈፀሙት ወንጀል የሚመጥን የእርምት እርምጃ መውሰድ ለነገ የማይባል አንገብጋቢ ጥያቄ ነው የሚል ጽኑ እምነት አለኝ። እናም ከዚህ አኳያ፤ የኢፌድሪ መንግስት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስቴሩ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ሰኞች መስከረም 15 ቀን 2010 ዓ.ም ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት ወቅታዊ መግለጫ ላይ፤ የኦሮሚያ ክልልን ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ጋር በሚያዋስኑት ዞኖችና ወረዳዎች የተከሰተውን ሰሞነኛ ግጭት ቀስቅሰዋል በተባሉ የመስተዳደሮቹ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ስለመወሰኑ ሲናገሩ መደመጣቸውን እንደ ተስፋ ሰጭ ዜና ወስጀዋለሁ።


ይህን ስል ግን እንደሀገር እንቅልፍ የሚነሳ አሳሳቢ የፀጥታ ችግር እያስከተለብን ያለውን መሰል የመብት ጥሰት ማስቀረት የሚቻለው ከመናገር ያለፈ ተግባራዊ የእርምት እርምጃ በመውሰድና ትርጉም ካለው የፖለቲካ ቁርጠኝነት የሚመነጭ ተጠያቂነትን ማስፈን ሲቻል ብቻ መሆኑን አጥቸው አይደለም። ይልቅስ የሁለቱን ተጎራባች ክልሎች ወንድማማች ህዝብ ፈርጀ ብዙ ጉዳት ወዳስከተለ ትርጉም የለሽ ግጭት እንዲገባ አድርገዋል የተባሉት የመስተዳደር አካላት ሕግ ፊት ቀርበው እንዲጠየቁ የፌደራሉ መንግስት ውሳኔ ላይ ስለመድረሱ መስማታችንም በራሱ እንደ አንድ ጠቃሚ እርምጃ ሊወሰድ የሚችል ሆኖ ስላገኘሁት ነው እንደበጎ ጅምር ማድነቄ።


እንጂማ ይህ አሁን አገራችን ኢትዮጵያ የምትገኝበት ወቅት ከመቸውን ጊዜ በላይ ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን አክብሮ የማስከበር ተግባራዊ እርምጃ መውሰድን ግድ የሚል ስለመሆኑ በጽሑፌ ርዕስ ጭምር ጠቁሜ የለ እንዴ? እንዲያውም እውነቱን እንነጋገር ከተባለማ፤ ለዚህ ዓይነቱ ቅጥ ያጣ የሕገ መንግስታዊ መብት ጥሰት የሚያወላዳ መፍትሔ አለመፈለግና እንደተለመደው በቸልታ ለማለፍ መሞከር፤ አጠቃላይ ሀገራዊ ደህንነታችንን ለማናጋት ያለመ ስትራቴጂ ነድፈው በግልጽና ግልጽ ባለሆነ መልኩ እየተንቀሳቀሱ ያሉት የሻዕቢያው መንግስት ጉዳይ አስፈፃሚዎች የልብ ልብ እንዲሰማቸው ዕድል እንደመስጠት ሊቆጠርም ይችላል። ይህን ያህል ሰላማዊ ህዝብ ከመኖሪያ ቀየው እስኪፈናቀል ድረስ ትርምስ ሲፈጠር አላየሁም አልሰማሁም ሊል የሚችል የክልላዊ መንግስት አካል ሊኖር ይገባልን ወገኖቼ!? እንደኔ እንደኔ ግን አይገባም ባይ ነኝ።
ስለዚህ የፌደራል ስርዓታችን የማዕዘን ድንጋይ ተደርጎ የሚወሰደውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ አንድነት አደጋ ላይ የመጣል ዕኩይ ፍላጎት ያላቸውን ኪራይ ሰብሳቢ የፖለቲካ ቡድኖች ከጥፋት ተግባራቸው እንዲታቀቡ ሊያደርግ የሚችል ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ ረገድ ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ አመራር የተለየ ቁርጠኝነትን እንጠብቃለን። ደግሞስ በአስመራው የማፊያዎች መንግስት ጸረ ኢትዮጵያ አጀንዳ ዙሪያ ተሰባስበው የሚንቀሳቀሱት ሽብርተኛው ኦ.ነ.ግ እና የጥፋት አጋሮቹ ምን እስከሚያደርጉን ነው የምንጠብቀው!? እንደኔም እምነት ግን ፌደራላዊ ስርዓታችን ፈጽሞ ሊቀለበስ በማይችል የሕግ የበላይነት የሚመራና የሚዳኝ እንጂ በጥቂት አኩራፊ ፖለቲከኞች ፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ እንዳልሆነ ልናረጋግጥላቸው የሚገባ ይመስለኛል።


ስለዚህም ከሕገ መንግስታችን መሰረታዊ ዓላማዎች ጋር ፈጽሞ በሚቃረን መልኩ ህዝቦችን ወደለየለት የዕርስ በርስ እልቂት እንዲገቡ የሚጋብዝ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድር ይዘት ያለውን ጠባብ ብሔርተኛ ክልል አቀፍ እንቅስቃሴ በማባባስ ረገድ የመሪ ተዋናይነቱን ሚና ተጫውተዋል በሚባሉ የየአካባቢው መስተዳደር አካላት ላይ ለጥፋታቸው የሚመጥን ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ ግድ ይላል። ምናልባትም ከዚህ ቀደም የተከሰቱትንና ይህንኑ የፈረደበት የመከራው ገፈት ቀማሽ እየሆነ ያለውን ህዝባችንን ለተመሳሳይ የሕይወትና የንብረት ኪሳራ ዳርገውት ያለፉትን ተደጋጋሚ አካባቢያዊ ግጭቶች የቀሰቀሱ የመስተዳደር አካላት ላይ ትርጉም ያለው የተጠያቂነት እርምጃ መውሰድ ቢቻል ኖሮ፤ ቢያንስ የአሁኑን ፈርጀ ብዙ ጉዳት ማስቀረት ይቻል ነበር የሚል እምነት ነው ያለኝ እኔ በግሌ። ስለሆነም የእርምት እርምጃ መውሰድ የሚጠበቅበት ሕጋዊ አካል የመልፈስፈስ አዝማሚያን ባሳየ ቁጥር እቺን ሀገር ለማተራመስ ያለመ የጥፋት ተግባር በመፈፀም የሚታወቁት ኃይሎች ያሻቸውን ቢያደርጉ እንብዛም የሚያሰጋ ተጠያቂነት ሊያስከትልባቸው እንደማይችል ስለሚሰማቸው የበለጠ ሊፈነጩብን መነሳሳታቸው የሚያከራክር ጉዳይ አይሆንም የሚለውን ቁልፍ ነጥብ ልናሰምርበት ይገባል እያልኩኝ እነሆ እዚህ ላይ አበቃሁ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
196 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1079 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us