በሁኔታ ፍቺ እና የፌደራል ፍ/ቤቶች አቋም

Wednesday, 11 October 2017 13:13

 

በነብዩ ምክሩ ወ/አረጋይ
(በማናቸውም ፍ/ቤቶች ጠበቃና የህግ አማካሪ)

ለዚህ ጹህፍ መነሻ የሆነው የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁ.20938 በቅጽ 4 በሰጠው ውሳኔ መሰረት በተዋረድ የፌደራል ፍ/ቤቶች የበታች የቤተሰብ ችሎቶች "በሁኔታ ፍቺ" ተፈጽሟል በሚል በሚሰጧቸው ውሳኔዎች ላይ የግሌን አስተያየት ለማቅረብ እና ለውይይት መነሻ ይሆን ዘንድ ለተጓዥ አንባቢ እንዲሆን በአጭሩ የተሰናዳ ነው።


ስለ ጋብቻ በቤተሰብ ህጎቻችን ለውይይት የሚበቃ ትርጓሜ የለም። ጋብቻ የተለያዩ ፀሐፋት የሰጡት ትርጓሜ ሀገራዊና ውጤት በሚያወጣ መልኩ ስንተረጉመው በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል መንፈሳዊና ቁሳዊ ጥምረት በመፍጠር ዘላቂ ቤተሰብ ለመመስረት የሚደረግ ጥምረት ነው። ይህ ጥምረት በተሸሻለው የቤተሰብ ህግ ቁጥር 213/1992 አንቀጽ 1 መሰረት ጋብቻው በክብር መዝገብ ሹም (በተለምዶ ማዘጋጃ ቤታዊ ጋብቻ)፤ ከተጋቢዎቹ በሁለቱም አልያም በአንዳቸው ሃይማኖት ወይም በሚኖሩበት አካባቢ ባህል መሰረት የሚፀና ጋብቻ ሊቋቋም እንደሚቻል የተደነገገ ሲሆን ከሶስቱ በአንዱ የጋብቻ አፈፃፀም ሥርዓት የተፈፀመ ጋብቻ በእኩል ደረጃ ህጋዊ ዕውቅና ያለው፤ ህጋዊ ውጤቱም ጋብቻ ከተፈፀመ ቀን የሚጀምር ሆኖ በሶስቱም የጋብቻ አፈፃፀም ሥርዓቶች የተፈፀሙ ጋብቻዎች በክብር መዝገብ ላይ መመዝገብ ያለባቸው መሆኑ የህጉ ተጨማሪ ድንጋጌዎች ናቸው።


ጋብቻ በሶስት አይነት የአፈፃፀም ሥርዓቶች ቢፈፀሙም ፍቺ ግን ሊፈፀም የሚገባው በፍርድ ቤት ብቻ መሆኑን የቤተሰብ ህጉ አንቀጽ 76፤ 82 እና 75 የጋራ ንባብ ያሳያል። በዚሁም በማናቸውም አይነት የጋብቻ አፈፃፀም ሥርዓቶች የተቋቋሙ ጋብቻዎች በማፍረስና በውጤቱ ረገድ አንድ ዓይነት መሆናቸውን ልብ ይሏል።


ጋብቻ በሶስት አይነት የአፈፃፀም ሥርአቶች ቢቋቋምም ፍቺ ሊፈፀም የሚገባው በፍ/ቤት የፍቺ ውሳኔ ሲሰጥ ብቻ መሆኑ ተደንግጎ ሳለ "በሁኔታ ፍቺ" ከየት መጣ? ፍርድ ቤቶቻችንስ እንዴት እየተረጎሙት ነው?


የፌደራል ፍርድ ቤቶችን ማቋቋሚያ አዋጅን ለማሻሻል በወጣው አዋጅ ቁጥር 454/97 አንቀጽ 2/1/የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከአምስት ያላነሱ ዳኞች በተሰየሙበት የሰበር ችሎት የሚሰጠው የሕግ ትርጉም በየትኛውም ደረጃ ላይ በሚገኝ የፌደራል ወይም የክልል ፍርድ ቤቶች ላይ አስገዳጅነት ያለው የሕግ ትርጉም በመሆኑ፤ እነዚህ ትርጉሞቹን በተለያዩ ቅጾች ሲያወጣ ቆይቷል። ከነዚህ ውሳኔዎች ውስጥ በቅጽ 4 ላይ ታትሞ የወጣው በሰ/መ/ቁ20938 በወ/ሮ ሸዋዬ ተሰማ እና ወ/ሮ ሳራ ልነጋነ ሙግት የተሰጠው የህግ ትርጉም ውሳኔው በጥቅሉ ሲታይ ጋብቻ በፍ/ቤት ፍቺ ሳይፈፀም መፍረስን ያስተዋወቀ ሲሆን ይኽውም ጋብቻው በፍ/ቤት ባይፈርስም ጋብቻው (ግንኙነቱ) ማንም ሌላ ማስረጃ ሊያስረዳው ከሚችለው በላይ የጋብቻ ግንኙነቱ መፍረሱን ማስረዳት ከተቻለ ጋብቻው በፍ/ቤት ባይፈርስም ጋብቻው "በሁኔታ እንደፈረሰ" ይቆጠራል የሚል ይዘት ያለው ውሳኔ ሰጥቷል። በዚሁ ውሳኔ አስገዳጅ የህግ ትርጓሜ መሰረት የስር ፍ/ቤቶች ውሳኔዎችን በመስጠት ላይ ይገኛሉ።


ከዚህ በላይ በተጠቀሰው ውሳኔ መሰረት በሁኔታ የጋብቻ ግንኙነት መፍጠር የህጉን ዓላማ ያሳካ የህግ ትርጓሜ ነው ወይ? ይህ ትርጓሜ በምን ደረጃ ተግባራዊ ሊሆን ይገባል? የሚሉ ጥያቄዎችን ለማየት ስንሞክር፡-


የፌደራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጠው ውሳኔ ሌላ (ሁለተኛ) የፍቺ መንገድ (ከፍርድ ቤት ውጪ) በማስተዋወቅ ዓላማ ሳይሆን ተጋቢዎቹ በሚያሳዩት ሁኔታ በሁለቱ ተጋቢዎች መካከል ያለው የጋብቻ ሁኔታ በሁለቱም መካከል ጋብቻ መኖርን ዕሳቤ ያላቸው መሆኑን የማያሳይና ይህንኑ ዕሳቤ መሰረት አድርገው የሚፈፅሟቸው ተግባራትም በትዳር አብሮ የመቆየትን ሳይሆን በተቃራኒው ትዳሩ እንደሌለ የሚያሳይ በመሆኑና በዚሁ መነሻ ቀድሞም የሚፈርስ ትዳር የለም (በተጋቢዎቹ ሁኔታ ትዳሩ ፈርሷል) የሚል የህግ ግምት የተያዘበት ሁኔታን የተተረጎመበት እንጂ እንደ ሁለተኛ የትዳር ማፍረሻ መንገድ (ከፍርድ ቤት ውጪ) እንደተዋወቀበት መቁጠር የህብረተሰብ መሰረት፤ የቤተሰብ ምሶሶ ለሆነው ጋብቻ ህጉ የሰጠውን ጉልህ ደረጃ እና ጥበቃ በማውረድ ህጉ በማናቸውም የጋብቻ አፈፃፀም ስርዓተ ጋብቻ ይፈፀም ፍቺው እና ውጤቱ በፍርድ ቤት እንዲመራ ያስቀመጠውን አቅጣጫ የሚያፋልስና ፍ/ቤቶች ከተሰጣቸው የህግ ተርጓሚነት ሚና ወደ ህግ አሻሻይ/አውጪ የሚቀይር የመንግስት ስልጣን ክፍፍል መርህን ጭምር የሚጋጭ በመሆኑ የህግ ተርጓሚው ከህግ አውጪው ሐሳብ አንፃር የሰጠው ትርጓሜ በዚህ ደረጃ የሚገልጽ ነው የሚል አስተያየት አለኝ።


በጋብቻ ውስጥ ያሉ ተጋቢዎች በትዳር ውስጥ ያሉ ተጋቢዎች መፈፀም የሚገባቸውን ግዴታዎች በመወጣት በጋብቻው የመቀጠል ሐሳብ እያላቸው እና ይህንኑ በመፈፀም ላይ ሳሉ ፍቺ ከፍ/ቤት በመለስ ሊደረግ እንደሚችል ተራ ግንኙነት በመቁጠር የጋብቻን ክቡርነትና ጥበቃ በሚቃረን መልኩ በበርካታ የፍርድ ቤት ጉዳዮች "ጋብቻው በሁኔታ ፈርሷል" የሚሉ ውሳኔዎች እየተስተዋሉ ይገኛሉ። ይህም በተለያዩ ፍርድ ቤቶች በተለያዩ መዝገቦች የጋብቻ ፍቺ ጥያቄ ሊቀርብ በተለይም የኢኮኖሚ ችግሮችን ለመቅረፍ በስምምነት በተለያዩ ሀገሮች የሚኖሩ ዜጎችን የጋራ ንብረትና ክፍፍልን መሰል የፍቺ ውጤቶችን የተጋቢዎቹን መብት በሚጎዳ መልኩ በዘፈቀደ "ጋብቻው ቀድሞም በተጋቢዎች ሁኔታ ፈርሷል፤ፍ/ቤቱ የሚያፈርሰው ጋብቻ የለም" በሚል የሚሰጡ ውሳኔዎች የህጉንና የሰበሩን ፍ/ቤት ውሳኔ ዓላማ ያላገናዘበ ነው።


የሰበሩ ውሳኔ ጋብቻው "በተጋቢዎቹ ሁኔታ" ለመፍረሱ በርካታ ግብዓቶችን የተጠቀመ ሲሆን እንደዚሁም የተጋቢዎቹ ግንኙነት (ጋብቻ) ለረዥም ጊዜ የተቋረጠ፣ በዚሁ ግንኙነት መቋረጥ ምክኒያት ሌላ ጋብቻ መፈፀሙንና የዚሁ ግንኙነት መቋረጥ በተጋቢዎቹ መካከል በእርግጥ የሚታወቅ ‹‹ሌላ ማስረጃ ሊያስረዳው ከሚችለው በላይ ነጥቦችን የያዘ ሲሆን በተለይም የሰበር ሰሚ ችሎቱ በሶስተኛነት ያስቀመጠው የማስረዳት ደረጃ የተጋቢዎቹ ትዳራቸው የፈረሰና ይህንኑ ትዳር ለማቆየት በማሰብ ህጋዊ ተግባራትን ያልፈፀሙ፣ ትዳሩ መፍረሱን የሚያውቁ መሆኑን፣ የጋብቻ ኃላፊነቶችን መተጋገዝ፤ ቤተሰብን በጋራ መምራት፣ መተማመን፣ አብሮ መኖር ወዘተ በተቻላቸው ያልፈፀሙ መሆኑን በእጅጉ ጥብቅና ለፍፁማዊነት በቀረበ ደረጃ የማስረዳትን ኃላፊነት/ግዴታ ጋብቻው በሁኔታ ፈርሷል ብሎ ለሚከራከር ተከራካሪ ላይ የጣለ በመሆኑ ይህንን መሰል ጭብጥ በዚህ ደረጃ በጥብቅ የማስረጃ ምዘና መርህ ሊመዘን ይገባዋል።


በጥቅሉ ጋብቻ በዘፈቀደ ከፍ/ቤት በመለስ በታዩ ጥቃቅን የትዳር ጉድለቶች መነሻነት "በሁኔታ ፈርሷል" ሊባል የማይገባ በመሆኑ ይህንኑ መሰረት አድርጎ የሰበር ችሎቱ የሰጠው አስገዳጅ ትርጓሜ በጥንቃቄ ሊጤን የሚገባው ነው እንጂ በተለያዩ መዝገቦች እንደተስተዋለው በቀላሉ ተጋቢዎቹ ትዳራቸውን በሁኔታቸው ከፍርድ ቤት ውጪ አፍርሰውታል የሚል አቋም የጋብቻን ክብርና ጥበቃ የሚያወርድ፤የህግ ትርጓሚውን ሚናም ከህግ አውጪው ጋር የሚያቃርን መስመሩንም የሚያጣብብ ነው እላለሁ። እስኪ እንወያይበት። ፈጣሪን ኢትዮጵያን ይባርክ!!

 

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
345 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1019 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us