“ሳተናው እና ሌሎች”

Wednesday, 22 November 2017 12:33

 

ደራሲ፤ ደረጀ ትዕዛዙ

አስተያየት - በማዕረጉ በዛብህ

ይህ አሁን እየኖርንበት የሚገኘው ዘመን ለኛ ለኢትዮጵያውያን በብዙ መልኩ ካለፉት ዘመናት የተለየ ነው። ከዘመኑ ጋር ለመጓዝ የምናደርገው ጉዞ እስከ ዛሬ ካየነው ጊዜ ሁሉ ይበልጥ ፈጣንና ለየት ያለ ይመስላል። መቀሌ ወይም አምቦ ዛሬ ጥዋት የተደረገውን የተቃውሞ ሰልፍ ማታ በቪኦኤ እንሰማዋለን ወይም በኢሳት እናየዋለን ወይም ደግሞ በፌስቡክ እናነበዋለን። መረጃን ከማግኘት አንፃር ደህና ነን። እያደግን ነው ማለት የሚቻል ይመስለኛል። በፖለቲካው፤ በኤኮኖሚውና በማህበራዊ ኑሮ ዕድገት ጉዟችንም እጅግ የፈጠነ ግስጋሴ ባይሆንም መጠነኛ እንቅስቃሴ መኖሩ አይካድም፡፤ ዘመኑ ራሱ አስጋሪ ነው ያሰግራል። የሰው ልጅ ሁሉ ያንዲት ዓለማቀፋዊ ጎጆ ነዋሪ ሆኗል እየተባለ ከሌላው ዓለም ተነጥዬ ወደኋላ ልቅር ቢባልስ መቼ ይቻላል!

የዕድገት መለኪያ ጥራትና ጥልቀት ነው ብለን ካላከረርን/ካላከበድን በስተቀር አንዳንድ ጠቃሚ የዕድገት እንቅስቃሴ በአገራችን መታየታቸውን ጨርሶ መካድ ያስቸግራል። በዝች ጽሁፍ ስለጥቂት የዕድገት እንቅስቃሴዎች ጥቂት ለማለት ያህል ከፍተኛ ትምህርትን (tertial education) እና ስነፅሁፍን እንውሰድ፤

ከፍተኛ ትምህርትን በተመለከተ አነጋጋሪ የሆነውን የጥራትን ጉዳይ ለጊዜው ወደ ጎን ትተን፣ ከመጠን አንጻር መስፋፋትን ስናይ በመንግሥትም ሆነ በግሉ ዘርፍ የሚታየው የከፍተኛ ትምህርት ዕድገት የሚደነቅ ነው። ኢትዮጵያ ዛሬ ከ40 ያላነሱ የመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች አሏት ይባላል። እንዲሁም በስነጽሁፍ በኩል የሚታየው የመፃሕፍት ሕትመት ምርት ዕድገት ይሁን ምን በብዛት ይፃፋል፣ ይታተማል፣ ይሰራጫል፣ ይሸጣል።

እነኚህን ቁም ነገሮች እንደመነሻ ያህል አነሳሁ እንጂ የዝች አጭር ጽሁፍ ትኩረት “ሳተናው እና ሌሎች” ስለተባለችው ትንሽ መጽሐፍ ጥቂት ለማውጋት ነው። የመፅሐፍዋ ዋና አርዕስት/ ስም የሆነው ሳተናው የተባለው ወጣት የጋዜጠኝነትን ሙያ የሚወክል ገጸ ባህሪ ነው። ሳተናው የገጽ ባህሪው ዕውነተኛ ስሙ አይደለም። አለቃው ያወጣለትና የሥራ ጓደኞቹም ሳተናው ፈጣኑ፣ ጎበዙ፣ እንደማለት አስበው የተቀበሉት የአድናቆት መጠሪያው ሆነ እንጅ እውነተኛ ስሙ አይደለም። ደራሲው የሳተናውን እውተኛ ስም አልነገረንም። ዝርዝር መረጃን ከመስጠት አንጻር ደራሲው ንፉግ ቢጤ ይመስላል። የአንባቢን ቀልብ በማንጠልጠል ነው አጫጭር ልቦለዶቹን የሚጨርሳቸው።

ለምሳሌ ሳተናው አንድ የቀድሞ ጋዜጠኛ ኋላ ግን በሌላ ሥራ ባለሥልጣን ከሆኑ ሰው ጋር ቃለምልልስ ያካሄዳል። ያንን መረጃ በሬድዮ ለማቅረብ በከፍተኛ ጉጉት ሲጠብቅ መቅረጸ-ድምጹ ንግግሩን ሳይቀርጽ በመቅረቱ ከፍተኛ ድንጋጤ ላይ ይወድቃል። ቃለ-መጠይቅ ሰጪውን ሲደውልላቸው ወደ ውጭ አገር በመሄድ ዝግጅት ላይ እንዳሉ ገልጸው. . . “ከሳምንት በኋላ እመለሳለሁ፤ ያኔ የዜና ቋንጣ ካልሆነብህ እንጂ ደግሜ” ይሉታል። የሳተናው አጭር ልቦለድ እዚያ ላይ ነው የሚያልቀው። ይህ በጋዜጠኞች ላይ ከሚደርሱ አስቸጋሪ ፈተናዎች አንዱ ነው።

ደራሲው በአጫጭር ልቦለድ ጽሁፎቹ የሚፈጥራቸውን ገጸ ባህሪያትን ሲገልጻቸው ለአንባቢ እንደፎቶግራፍ ጎልተው ነው የሚታዩት። ለምሳሌ የድሮ የትምህርት ጓደኛውንና ኋላ አሜሪካ በዲቪ ሄዶ ወደ ቀድሞ መንደሩ ተመልሶ ሊጠይቀው የመጣውን የቅጽል ስሙ ታታ የተባለውን ጓደኛውን ሲገልጸው በፎቶግራፋዊ ዕይታ የሚያቀርበው ነው የሚመስለው። ካገር ቤት ወጥቶ ትምህርት ቤት ሲገባ የነበረውን ገጽታ እንደሚከተለው ነበር የሳለው፤

“ታታ” ወንዳፍራ ነበር ስሙ፤ አጎቱ ዘመናዊ የቀለም ትምህርት ይቅሰም ብለው ከገጠር ያስመጡት ሰሞን የነበረው ሁኔታ መቸም የሚረሳኝ አይደለም። በሰፊ ቁምጣው ቢል ቢል የሚሉ ሰላላ እግሮቹ የሰንበሌጥ ያህል አቅም ያላቸው አይመስሉም። የመጫሚያ አልባው ተረከዙ ንቃቃት ሳንቲም ይደብቃል የሚባል አይነት ነው። እንቅፋት ሲነድላቸው የኖሩት አውራጣቶቹ ደድረዋል። በጠራራ ፀሐይ እስከ አፍንጫው የሚጀቦንበት ጋቢው ከራሱ ይከብዳል። በግራ ጎኑ ደገፍ የሚልበት በትሩ ለቄንጠኛ አቋቋሙ ተገን ሆናው ሳቅን ይፈጥርበት ነበር።”

ያ ታታ ወንዳፍራ ነው፣ ሕይወቱ በማይታመን መልክ በጣም ተለዋውጦ፣ ከአሜሪካ ድረስ መጥቶ ወደ ቀድሞ ሰፈሩ ድሃ ወዳጆቹን ስለመጠየቁ፣ ስለ አለባበሱ፣ ስለ አነጋገሩ ማማርና እቤት ድረስ ይዟት ስለመጣው አውቶሞቢል ነው ደራሲው ያቀረበው ንጽጽራዊ ገለጻ። ከአንድ የኢትዮጵያ ገጠር ታዳጊ ሰው አሜሪካ ሄዶ አድጎና በልጽጎ እስኪመለስ ያለው ልዩነት የተገለጸበት ቋንቋና ስነጽሁፋዊ ለዛው ወጣቱ ደራሲና ጋዜጠኛ ያለውን ሥነጽሁፋዊ አቅም የሚጠቁም ይመስለኛል።

ሌላ ማሳያ ደግሞ ልጥቀስ። “ጉማጅ ፀጉር” በሚል ርዕስ በጻፉት አጭር ልቦለድ ሦስት የአንድ ቤተሰብ አባሎችን ያቀርባል-ግርማ የከባድ መኪና ሹፌር፣ ከቤቱ አልፎ የጎረቤቶቹን ኑሮ የሚደግፍ ደግ ሰው፣ ባለቤቱ እልፍነሽና ታናሽ እህቷ ታሪኳ ናቸው። የግርማ ባለቤት የሆነችው የእልፍነሽ መልክ እንደነገሩ ሲሆን በተለይ የእህቷ የታሪኳን መልክና ውበት አስደናቂነት ደረጃ እንደሚከተለው ነው የገለጸው።

“ሦስትዮሽ የተጎነጎነው ፀጉሯ በጀርባዋ ቁልቁል ወርዷል። በጠይም ገጿ ላይ ስርጉድ የሚለው የጉንጯ መሀል ባትስቅም ያምርባታል። በደረቷ ግራ ቀኝ ያሞጠሞጡት ጡቶቿ ሴትነቷን አልቆታል። አልባሌ ቀሚስዋም ውበቷን መጋረድ አልተቻለውም።”

እልፍነሽን ሲገልፅ ደግሞ “እልፍነሽ ሁሌም እሷነቷን ከእህቷ ጋር ስታነፃፅር በብዙ እጥፍ ውበቷ ስለሚጣጣልባት ውስጧ ይቆስላል። ቅላቷ መስህብ ሆኖ ግርማን ጣለላት እንጂ፤ ቅርጽ አልባ ውፍረቷ፣ ሰፋፊ አፍንጫዋና ባህሪዋ ማንንም ባላቀረበ ነበር። ከመልክ አንጻር የእናት ሆድ ዥንጉርጉር የሚባለው በአግባቡ ገቢራዊ የሆነው በእርሷ ላይ መሆኑ ያበግናታል፣” ይላል።

አቶ ግርማ የባለቤቱን እህት የታሪኳን የትምህርት ጥረት መከታተልና ማበረታታት፣ ይወዳል። “ከማትሪክ ውጤትሽ አንፃር የኮሌጅ ትምህርትሽ ይከብድሻል ብዬ አልሰጋም። … ግን በርትተሸ ማጥናት ነው። ከ… የሚያስፈልግሽን መጽሐፍቶች ንገሪኝ እገዛልሻለሁ። እሺ፣” ነበር ያላት። አንድ ሌሊት ላይ፣ የታሪኳ ዕድገትና ውበት መጨመርና ትኩረት መሳብ በቤተሰቡ ላይ እጅግ አስደንጋጭና አሳዛኝ ድራማ እንዲፈጠር አደረገ። ይህንን ጉድ በራሱ በደራሲው ቃላት ላውጋችሁ።

እኩለ ሌሊት ላይ ሚስቱን ከተኙበት ካጠገቡ ያጣት ግርማ በሰማው ጩኸት ተደናግጦ “መብራቱን ሲያበራው ባለቤቱ ሦስትዮሽ የተጎነጎነ ሁለት ጉማጅ ዘለላ ፀጉር በግራ እጇ፣ በቀኟ ደግሞ እንደ ተወለወለ የሳንጃ ጫፉ የሚያብለጨልጭ መቀስ ይዛ መሀል ወለሉ ላይ እርቃኗን ቆማለች-እልፍ ነሽ። ድንጋጤ ያደነዘዛት ታሪኳ ግን “ወይኔ አምላኬ” ስትል የሞት ሞቷን ተነፈሰች። እልፍነሽ የከሰል ፍም የመሰሉ አይኖቿ እንደፈጠጡ አልጋቸው ጠርዝ ላይ ስትቀመጥ “ታሪኳ ባዶ የሆነ መሀል አናቷን እየደባበሰች በድንጋጤና በፍርሃት ደንዝዛ እዛው እመኝታዋ ላይ ቁጢጥ አለች።” ሲል ነው ደራሲው “ጉማጅ ፀጉር” የሚለውን በ7 ገጽ ያቀረበውን አጭር ልብወለድ የጨረሰው። ቅልብጭ ያለች ታሪክና ቅልብጭ ብላ የተቋጨች የአጭር ልቦለድ ትረካ፤

ደረጀ ትዕዛዙ ገጣሚም ነው፣ “ፅኑ ፍቅር” በሚለው ግጥሙ በከፊል እንዲህ ይላል፤

“ፍጡራን ተረቱ

ወዥንቢጦችም ጨመቱ

ንፋስ ድንፋቱን አደበ፤

ሰላም በምድረ ገጽ ረበበ

“ጭርርር” አለ ሌሊቱ፣

በትንሳኤ ሞት ሰዓቱ።

ስለ ግላዊ የሕይወት ፍልስፍናው ሲነግረን ደግሞ “የማይታጠፍ ዕውነታ” በሚል ርዕስ እንዲህ ይለናል፤

“ውበት እድሜን ተግኖ ላይኖር

      -ጊዜ ጉዘቱን ላይገታ

ሰማይ ከምድር ላይገጥም

      -ፅልመት ወጋግታን ላይረታ

ትንኝ ዝሆንን ላታክል

      -እግዜር ሰይጣንን ላይፈታ

ዓለም ዘልዓለም ላትኖር

      -ሕይወትም ሞትን ላይረታ

ለምን ነው መጨነቅ? የሚሆነው ሊሆን

      የማይሆነው ላይሆን።”

መልካም ሥራ ሁሉ አልፎ-አልፎ እንከን አያጣውም እንዲሉ “ሳተናው እና ሌሎችም” ከበድ ያለ የሕትመት ችግር ገጥሟታል። ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለሕትመት ሥራ ዕድገት የሚያደርገው አስተዋፅኦ የሚደነቅ እንደመሆኑ፣ ለስነፅሁፍ ሥራም እድገትና ጥራት የራሱ አበርክቶ ሊኖረው ሲገባ፣ ዛሬ በሀገራችን በሕትመት በሚቀርቡት ሥራዎች ላይ የሚታዩት ስህተቶች እያደግን ሳይሆን ቁልቁል እየወረድን መሆናችንን እያመለከቱ ያሉ ይመስላል። “ሳተናውና ሌሎች”ም ከዚህ የዘመኑ ችግር ያመለጡ አልሆኑም። አንድ መጽሐፍ አታሚ ድርጅት እያተመ ባለው መጽሐፍ ውስጥ የሰፈሩትን ርዕሰ-ጉዳዮች ተሳስቶ ሁለት ጊዜ ካተመ ለኔ አንድ ልረዳው የማልችል ችግር አለ። ጃጃው አታሚዎችና ዲቨሎፐርስ የተባለው የሕትመት ድርጅት ይህንኑ ነው ያደረጉት። “ምን ይወጠኝ” እና “እድናለሁ” በሚሉ ርዕሶች የተጻፉት ሁለት አጫጭር ልቦለዶች እያንዳንዳቸው ሁለት ጊዜ በመታተማቸው የመጽሕፍዋ ገጽ ብዛት ከ112 ወደ 128 ደርሰዋል። አሳታሚውም አታሚዎችም እንዴት ይህንን ትልቅ ስህተት ሊያዩ እንዳልቻሉና መጽሐፉ እንዲሁ እንዲሰራጭ እንዳደረጉ የተሰጠ መግለጫ ወይም የተጠየቀ ይቅርታ የለም። ይህ ተስፋ የሚጣልበትን የደራሲውን ጉዞ አጠያያቂ እንዳያደርገው እሰጋለሁ።

መጽሐፍዋ ጥሩ ተስፋም ትጠቁማለች። ከብዙ አገሮችና ከኛም እንደምንገነዘበው ጋዜጠኞች ከሙያቸው ጎን-ለጎን የስነጽሁፍ ፍቅርም የሚያዛቸውና በሁለቱም ተቀራራቢ ሙያዎች የሚደነቁ ሥራዎች የሰሩ ሰዎች እንዳሉ የታወቀ ነው። የሚኖራቸውን ርዕዮተዓለማዊ አቋም ትተን፣ እንደፋሽስቱ ቤኒቶ ሙሶሊኒ፣ ቀንደኛው የደቡብ አፍሪካ ዘረኛ መሪ ቬርውርት፣ እንደ ታዋቂው የምዕራብ አውሮፓ ግዙፍ ሰው፣ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዊንስተን ቸርችል፣ የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጃዋህላል ሄህሩ፣ አሜሪካዊው ደራሲ ሄሚንግወይ ያሉት የታወቁ የዓለማችን ሰዎች የተደነቁ ደራስያን ከመሆናቸው በፊት ጋዜጠኞች የነበሩ ናቸው። ባገራችንም ይኸው ዝንባሌ ታይቷል። በደራሲነታቸው የሚደነቁት በዓሉ ግርማ፣ ብርሃኑ ዘርይሁን፣ ዘውዴ ረታ፣ ጳውሎስ ኞኞ፣ አሐዱ ሳቡሬ፣ ማሞ ውድነህ፣ ሽፈራው መንገሻ፣ አጥናፍሰገድ ይልማ ከጋዜጠኝነት ወደ ሥነ ጽሁፉ የተሸጋገሩ ናቸው።

ባሁኑ ወቅት ደግሞ ይህ ዝንባሌ ከሚታይባቸው ወጣቶች እኔ እስከማውቀው ድረስ ደረጀ ትዕዛዙ አንዱ ነው ማለት የሚቻል ይመስለኛል። የደራሲ ጳውሎስ ኞኞንና የደጃዝማች ክንፉ ኪዳኔን… የሕይወት ታሪክ በመጻፍ ደረጃ ከላይ የጠቃቀስኳቸውን ጋዜጠኞችና ደራስያን የሙያ ቅርስ ለመቀላቀል እየሰራ ያለ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።

     

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
200 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 919 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us