ግብፅ ዛሬም ድረስ በቅኝ ግዛት ውስጥ ናት

Wednesday, 06 December 2017 13:21

 

አርአያ ጌታቸው


«የግብፅ የውሃ ድርሻ የማይሻር ነው። እንደ ግብፅ ፕሬዚዳንት የማረጋግጥላችሁም ግብፅ የናይል ስጦታ፤ ናይልም የግብፅ ስጦታ መሆኑንና ይሄንን ለማስከበርም ሁሉም ዓይነት አማራጭ እንዳለን ነው» ፕሬዚዳንት ሙርሲ እ.ኤ.አ. ጁን 2013 የተናገሩት፡፡


«ለእኛ ውሃ የልማት ጥያቄ ብቻ ሳይሆን የህይወት እና የሞት ጉዳይ ነው፡፡ ሀገራዊ ደህንነታችንን የማስጠበቅ አቅሙ አለን፡፡ ለእኛ ውሃ የብሔራዊ ደህንነት ጥያቄ ነው፡፡ አራት ነጥብ። የግብፅን የዓባይ የውኃ ድርሻ ማንም እንደማይነካው ለግብፃዊያን ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ›› ፕሬዚዳንት አልሲሲ እአአ በ2017 የተናገሩት፡፡


«ማንም ተናገረ ወይም አስፈራራን ብለን የምናቋርጠው ፕሮጀክትና የምንጀምረው ጦርነት የለም» ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ፡፡


«ለድርድር የሚቀርብ ግንባታ ስላልጀመርን የህዳሴን ግድብ ለድርድር አናቀርበውም» ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፡፡


«ፍትሐዊ ያልሆኑ ውሎችን ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ ተከታታይ መንግሥታት አልተቀበሏቸውም። ይኸም መንግሥት አይቀበልም።» የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እነዚህን ሁለት ተቃራኒ ሃሳቦች ልብ ብለን ስንመዝናቸው ብዙ የሚነግሩን ሃቅ አላቸው።


ግብፃዊያን የናይል ወንዝን የራሳቸውና የራሳቸው ብቸኛ ሀብት አድርገው ይቆጥራሉ። ይሄንን የተሳሳተ ስግብግብ አቋማቸውን ለማስከበር ደግሞ ዛሬም ድረስ በተሳሳተ መንገድ እየሄዱ መሆናቸውን ንግግሮቹ ያሳብቃሉ። በተቃራኒው ኢትዮጵያ ምንም እንኳን እስከ 85 በመቶ የሚሆነው የወንዙ ውሃ ከግዛቷ የሚመነጭ ቢሆንም የጋራ ሀብት ነው በሚል መርህ እየተጓዘች የግብፅን ዛቻ ወደ ጎን ትታ በጋራ ለመልማት እንደምትሥራ ነው።


የናይልን ወንዝ በተመለከተ እንደ ግብፅ በተዛነፈ አቋም ላይ እንቁም ከተባለ የወንዙ ብቸኛ ባለቤት ወንዙ የሚመነጭባቸው አገራት ናቸው። ይህ ማለት ናይልን ናይል ያሰኙት ወንዞች የሚመነጩባቸው አገራት ሁሉ የወንዛቸው ብቸኛ ባለቤቶች ናቸው። በዚህ ስሌት ከሄድን ግብፅ ብቸኛ ሀብቷ የሚሆነው ከአገራቱ ተርፎ የሚፈሰው ውሃ ብቻ ይሆናል። የሚተርፍ ካለ ማለት ነው። ስለሆነም ስለ ብቸኛ የሀብቱ ባለቤትነት ማውራትና ይገባኛል ማለት በተገላቢጦሹ የዚህ ዓይነት እውነት እንዳለው ግብፅና ግብፃዊያን ሊያውቁት ይገባ ነበር። እንደ አለመታደል ግን ግብፃዊያን ከቅኝ ግዛት አስተሳሰብና ውል ለመውጣት ዝግጁ አይደሉም።


እኛ ግን ኢትዮጵያዊያን ነን፤ ነፃና ኩሩ አገር። ነፃ አገር መሆናችን ለቅኝ ግዛት ውልና አስተሳሰብ ቦታ እንዳይኖረን አድርጎናል። እንድንጠየፈውም ጭምር። ለዚህ ነው ግብፅ ዛሬም ድረስ እንደ ሞኝ ዘፈን እየደጋገመች የምታዜመውን የ1959ኙን የቅኝ ግዛት ዘመን ውል አናውቀውም፤ አንቀበለውም ማለታችን። ይሄ ደግሞ አገራችን ቀደም ብለው ያስተዳደሩት መንግሥታት ያልተቀበሉት፤ አሁን አገራችንን እያስተዳደረ ያለው መንግሥትም ያልተቀበለው ወደፊትም የሚመጣው መንግሥት የማይቀበለው ነው። ምክንያቱም ይሄንን ውል መቀበል ኢትዮጵያዊነትን መክዳት ነው። ይሄንን ውል መቀበል ቅኝ መገዛትም ነው። ስለሆነም የግብፅን የቅኝ ግዛት ውል እዚያው ለራሷ ስንል እንሞግታለን። ምክንያቱም እኛ ኢትዮጵያ ነን፤ ነፃና ኩሩ ህዝብ። የቅኝ ግዛት ውል ይተግበርልኝ የሚል አገርና መንግሥት ካለ በቅኝ ግዛት ስር መተዳደር መብቱ ስለሆነ እዚያው በጸበሉ ከማለት ውጪ አማራጭ የለንም።


እንደ እኛ ግን ግብፃዊያን ማወቅ ያለባቸው መሬት ላይ ያለውን እውነታ ነው። መሬት ላይ ያለው እውነታ የናይል ወንዝ የእነሱ ብቸኛ ሀብት አለመሆኑ ነው። የናይል ወንዝ የ10 አገራት ሀብት ድምር ውጤት ነው። እውነታው ይሄ ሆኖ ሳለ እናንተ ተራቡ፤ እኛ ብቻ እንብላ ማለት የህግም የሞራልም ተቀባይነት አይኖረውም። እንደ አለመታደል ሆኖ ግን ግብፃዊያን አሁን እያሉ ያሉት ይሄንን ነው። እናንተ ረሀብንና ድህነትን ለምዳችሁታልና እዚያው ቆዩ፤ እኛ ወደፊት ሊርበን ስለሚችል ወንዙን ተውልን። ይሄ ራስን ማሞኘት ነው። አፍሪካዊያን ከመቼውም ጊዜ በላይ ድህነትን አምርረው መታገልና ማሸነፍ ጀምረዋል። ለዚያም ነው የተስፋዪቱ ምድር፤ አፍሪካ እየነቃች ነው እየተባለ የሚጻፈውና የሚነገረው። መንቃቱ አጠገብ ያለን ሀብት ከመጠቀም ይጀምራል። ይሄ ደግሞ ውሃንም ይጨምራ። የወንዝ ውሃን።


ግብፃዊያን የቅኝ ግዛት ውል ከግምት ውስጥ ይግባልን ከሚለው መከራከሪያቸው ጀርባ ያለው መከራከሪያቸው «እናንተ ሌላ የውሃ አማራጭ አላችሁ፤ እኛ ብቸኛ ሀብታችን እሱ ነው፤ ኢኮኖሚያችንም የግብርና ጥገኛ ነው፤ ግብፅ የናይል ስጦታ ናትና ተውሉን» የሚል ነው። እውነታው ግን ይሄ አይደለም። ይሄ የእነሱ የኖረና ያረጀ አስተሳሰብ ነው። በነገራችን ላይ ለዘመናት እንደዚህ በሚል ቅኝት ውስጥ ስላሉ ብዙዎችን የተፋሰሱን አገራት አሞኝተውና አሳምነው ኖረዋል። እውነታው ግን የግብፅ ኢኮኖሚ እንደሚባለው በግብርና ላይ ጥገኛ አለመሆኑ ነው።


መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከግብፅ ኢኮኖሚ እስከ 49 በመቶ የሚሆን ድርሻ ያለው የአገልግሎቱ ዘርፍ ነው። ኢንዱስትሪ የ13 በመቶ፣ ኮንስትራክሽን የ8 በመቶ ድርሻ አላቸው። የፋኦ መረጃ የሚገልጸው እ.ኤ.አ. በ2010 የግብፅ ግብርና ለዓመታዊ የአገሪቷ ምርት የነበረው ድርሻ 13 ነጥብ 7 በመቶ ብቻ ነው። ከዚህ ዓመት በኋላ ያለውን የተደራጀ መረጃ ማግኘት ስላልቻልኩ መጠቀም አልተቻለኝም። ከተገኘው መረጃ መገንዘብ የሚቻለው ግን የአገሪቷ ኢኮኖሚ ከግብርና እየተላቀቀ መምጣቱን ነው። ስለሆነም ግብፅ የናይል ስጦታ ናት የሚለው አስተሳሰብ ፉርሽ ነው።


እንዲያውም አንድ አንድ መረጃዎች የሚገልጹት የአገሪቷ ኢኮኖሚ ዋነኛ ዋልታዎች ሬሚታንስ፣ ቱሪዝምና ስዊዝ ካናል መሆናቸውን ነው። ይህ የሚነግረን ግብፅ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እያገኘች ያለውና ኢኮኖሚዋን እየደጎመች የምትገኘው እርሷ እንደምትለው በናይል ወንዝ ላይ በተመሰረተው የግብርናው ዘርፍ አለመሆኑን ነው። ይልቁንም ከቱሪዝም እና ከስዊዝ ካናል መተላለፊያ የምትሰበስበው ገንዘብ ላቅ ያለ ሆኖ ይታያል። እ.ኤ.አ. በ2016 ያለው መረጃ የሚያሳየው ግብፅ ከስዊዝ ካናል ብቻ አምስት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ስታገኝ፤ ከቱሪዝም ደግሞ አራት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ወደካዝናዋ ጨምራለች። በተቃራኒው ግብርናዋ የቸራት ገንዘብ ይሄን አያክልም።


የጠቃቀስኳቸው እውነታዎች ሁሉ እውነት መሆናቸው ይቅርና በግብፅ በኖረ ፕሮፖጋንዳ ብናምን እንኳን፤ ግብፅ «ወንዙ የደህንነቴ ጉዳይ ነው፤ ውሃው ከቀነሰ እጠፋለሁ» የምትለው እውነት እንደምትለው የውሃ ችግር ኖሮባት አይደለም። ያማ ቢሆን ኖሮ ውሃውን በአግባቡ በተጠቀመችበት ነበር። በአሁኑ ወቅት ግብፅ በግዛቷ ውስጥ የምታካሂደው የውኃ አጠቃቀም ከህግ እና ከሥርዓት ውጪ የሚፈፀም ነው። ከዚህም በላይ የናይል ወንዝን ተፈጥሯዊ የጉዞ መስመር በማስቀየር(out of basin transfer) በረሃ ሳይቀር እያለማችና እየተጠቀመች እንደሆነ ሁሉም የሚያውቀው ሀቅ ነው።


ከዚህም ባሻገር ግብርናዋ ውሃ አባካኝ እንጂ ቆጣቢ አለመሆኑም ይታወቃል። ስለሆነም እንደምትለው የውሃ ችግር ያለባት አገር ብትሆን ኖሮ አትንኩብኝ ከማለት ይልቅ እጇ ላይ ያለውን ውሃ በአግባቡ መጠቀም በተገባት ነበር።


መረጃዎች የሚነግሩን ግብፅ በአስዋን ግድብ አማካኝነት በያዘችው ውሃ በትነትና በስርገት እስከ 10 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ እያባከነች ስለመሆኗ በጥናት የተረጋገጠ ጉዳይ ነው። የምታመርታቸው አብዛኛዎቹ የግብርና ምርቶችም ውሃን በብዛት የሚጠቀሙና አጠቃቀሙም እንደ ጠብታ ውሃ መስኖ ላሉ ቴክኖሎጂዎችን ባዳ የሆነ ነው። የግብፅ የውሃ አጠቃቀም ይሄ ሁሉ ገበና ባለበት ሁኔታ በፕሮፖጋንዳ ብቻ ውሃ ከቀነሰ አበቃልኝ ማለት ትዝብት ላይ ይጥላል። ተቀባይነትም የለውም።


ስለፍትሐዊነት ማውራት ካለብን ግብፅ ስለሚገባት የውሃ ድርሻ ብቻ ሳይሆን የናይልን ወንዝ ጥቅም ላይ የምታውልበት መንገድም ምን ያህል ከብክነት የፀዳና ፍትሐዊ ነው የሚለው መታየት አለበት። የአገራቱን የውኃ አጠቃቀም ሥርዓት በውል ተፈትሾ ባልታየበት ሁኔታ የህዳሴውን ግድብ ብቻ በተናጠል ወስዶ ስለፍትሐዊነት ማውራት ዓይናችሁን ጨፍኑ ላሞኛችሁ ማለት ነው። እኛ ግን እንደ አገር የምንከተለው መርህ ፍትሐዊነትን ያገናዘበ ነው። የውሃው ባለቤት እኛ ነን፤ ብቻችንን እንጠቀምበት አላልንም። አባይ የደህንነታችን፣ የሞት ሸረት ጉዳያችን ነውም አላልንም፤ አንልምም። ምክንያቱም እኛ ተካፍሎ በመብላት የምናምን፤ ባርነት አምርረን የምንጠላ፣ በወዳጅነት የምናምን ህዝብና አገር ነንና።


ለመሆኑ የአባይ ወንዝ በተገላቢጦሽ ከግብፅ የሚመነጭ ቢሆን ኖሮ ግብፆች ውሃውን አሁን እኛ በጋራ እንጠቀምበት እያልን በፈቀድነው ልክ እንድንጠቀምበት ይፈቅዱልን ነበር? በጭራሽ። ለድርድርም እንደማይቀመጡ አሳምረን እናውቃለን። ምክንያቱም ግብፆች ሁሉም ይገባኛል የሚሉ፣ አፈር የገባውን ቅኝ ግዛት ቆፍረው አውጥተው የዚያ ዘመን ውል ይተግበርልን የሚሉ ራስ ወዳድ ናቸውና። ሀብታችን በእጃችን ላይ ሆኖ እንኳን እያሉን ያለውን የምናውቀው እኛው ነን።


በግሌ የምለው ግብፅ ዛሬም ድረስ በቅኝ ግዛት ውስጥ መሆኗን ነው። ምክንያቱም የቅኝ ግዛት ዘመን ውል ተግባራዊ ይደረግልኝ ማለት ከዚህ ሌላ ስያሜ ሊያሰጠው አይችልምና ነው። ግብፅን በተለያዩ ጊዜያት ያስተዳደሩት መሪዎቿም ይሄ እንደማያስኬድ እያወቁ እውነታውን ለህዝባቸው ነግረው ማስረዳት ሲገባቸው ዛሬም ድረስ ውሃው የደህንነታችን ጉዳይ ነው፤ ማንም አይነካውም እመኑኝ እያሉ በየአደባባዩ ይምላሉ። ለመሆኑ ግብፃዊያን እንዳይራቡ ኢትዮጵያዊያን ስንት ዓመት ይራቡ? ስንት አመትስ በድህነት ይማቅቁ? ይሄ ተቀባይነት የሌላው ንጽጽር ነው። ማንም መራብ የለበትም። ግብፅም፤ ኢትዮጵያም፤ የተፋሰሱ ሁሉም አገራት። ማንም። አራት ነጥብ።


ወንዛችን የተፈጥሮ ሀብታችን ነው። ነጩ ነዳጃችን፤ ከድህነት መውጫ አንዱ መንገዳችን። ስለሆነም ባሻን ጊዜ የምንጠቀምበት ባሻን ጊዜ ደግሞ የምንተወው እኛ ራሳችን እንጂ ማንም ሊሆን አይችልም። ማንም ስላስፈራራን ፕሮጀክቶቻችንን አንተውም፤ ማንም ስለማይረዳንም ገንዘብ አጥሮን ሥራውን አናቆምም። ምክንያቱም ተከዜንና ጣና በለስን ገንብተን የጨረስነው በግብፅ እየተመረቅን፤ በዓለም አገራትም እየተረዳን አይደለም። እየተዛተብን በራሳችን አንጡራ ሀብት ነው። አሁንም ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያለማንም ዕርዳታና በማንም ዛቻ ሳንዘናጋ ከዳር እናደርሰዋለን።


ግድቡ የእኛ ቀይ መስመራችን ነው። መንግሥትና ህዝብ ዳግም በምርጫ ውል ያሠሩት መንግሥት ግድቡን ከዳር እንደሚያደርስ ቃል ስለገባ ነው። ይሄንን ቃል አለመጠበቅ ዋጋው ምን እንደሆነ መንግሥት አሳምሮ ያውቃል ብዬ አምናለሁ። ይህ ግድብ የምንወዳት አገራችን ብሄራዊ ምልክቷ ነው፤ ሰንደቅ ዓላማዋም ጭምር። የዕድሜ ልክ እስራት የተፈረደባቸው የህግ ታራሚዎች ሳይቀር እያዋጡ የሚገነቡትን ይሄንን ምልክትና ሰንደቅ የሆነ ፕሮጀክት ማስተጓጎል አገራችንን እንደ መውረር ይቆጠራል። ለወረራ የምንሰጠው ምላሽ ደግሞ ምን እንደሆነ ታሪካችን ይናገራል። ስለሆነም ላንጨርስ የጀመርነው ግድብ የለም፤ አይኖርምም። ወዳጅ አገር ግብፅና ግብፃዊያን ፈቅደው ከገቡበት ቅኝ ግዛት ፈጥነው ይውጡ። ምርጫው ግን የእነሱ ነው። በዚህ አቋማቸው ከቀጠሉ ግን የተፋሰሱ አገራት በተናጠል ወንዛቸውን ማልማታቸው አይቀርም። ያኔ ግብፃዊያን የማይወጡበት ችግር ውስጥ መግባታቸው የግድ ይሆናል ማለት ነው። አሁንም ግን ምርጫው በእጃቸው ነው!

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
142 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 934 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us