የፕሬስ እና መገናኛ ብዙሃን ነፃነት - በኢትዮጵያ የህግ ማዕቀፍ

Wednesday, 06 December 2017 13:30

 

የፕሬስ ነፃነት ማለት ሃሳብን በተለያየ የመገናኛ ብዙሃን ማለትም በኤለሌክትሮኒክስ እና የህትመት ሚዲያዎች የመግለፅ መብት ማለት ሲሆን ይህ መብት መረጃን ጠይቆ የማግኘት እና ይህን መረጃ በተፈለገው መንገድ የማሰራጨት መብትንም ያጠቃልላል። በአብዛኛው ይህን መብት ከመንግስት ጣልቃ ገብነት ውጪ የመተግበር ፍላጎት ቢኖርም ለተለያዩ ዓላማዎች ሲባል ይህ ነፃነት ህገ መንግስታዊ እና ህጋዊ ጥበቃዎች እየተበጁለት የሚተገበር ነው።


የፕሬስ እና ሃሳብን በነፃ የመግለፅ መብትን በተመለከተ በኢትዮጵያ ያለውን ታሪክ ስንመለከት በሃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ተሻሽሎ የወጣው የ1948ቱ ህገ መንግስት ይህን መብት ከማረጋገጥ አኳያ ፈር ቀዳጅ የነበረ ሲሆን በዚህ ህገ መንግስት አንቀፅ 41 ስር «በመላው የንጉሰ ነገስት ግዛት ውስጥ በህግ መሰረት የንግግር እና የጋዜጣ ነፃነት የተፈቀደ ነው።» በሚል ተደንግጓል። በተመሳሳይ የኤርትራ ህገ መንግስት በአንቀፅ 12/d/ ስር ሃሳብን በነፃ የመግለጽ መብት በህገ መንግስቱ የተረጋገጠ መሆኑን እና የፌዴራል መንግስት ይህን መብት የማረጋገጥ ግዴታ እንዳለበት ይደነግጋል።


የንጉሱ ሥርዓት ካበቃ በኋላ ወደ ስልጣን የመጣው የደርግ መንግስት በአብዛኛው የስልጣን ዘመኑን የፕሬስ ነፃነትን የሚያስከብር የህግ ሥርዓት ያልዘረጋ ሲሆን ሆኖም መስከረም 1/1980ዓ.ም የወጣው የኢትዮጵያ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ መንግስት አዋጅ በአንቀፅ 47/1/ ስር ኢትዮጵያውያን የንግግር፣ የፅሁፍ፣ የመሰብሰብ መብት እንዳላቸው ይደነግጋል።


ከላይ የተገለፀው ለፕሬስ ነፃነት የተሰጡ ህጋዊ ከለላዎች ባለፉት ሥርዓቶች ምን ይመስሉ እንደነበር ሲሆን በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃንን በተመለከተ የነበረውን ተጨባጭ ታሪካዊ ዳራን ስንመለከት አጀማመሩ ከህትመት ሚዲያው ጋር የሚገናኝ ሲሆን ከቀዳሚዎቹ የህትመት ውጤቶች መሀከል በአፄ ምኒልክ ዘመን ይሰራጭ የነበረው አእምሮ እና ጎህ ጋዜጣዎች ተጠቃሽ ናቸው። በተለይ በአፄ ሃይለስላሴ ዘመን በቁጥር በርከት ያሉ ጋዜጣዎች ይታተሙ የነበረ ሲሆን ከነዚህም መካከል የዛሬይቱ ኢትዮጵያ፣ ሰንደቅ ዓላማችን፣ ህብረት፣ አዲስ ዘመን እና ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ የሚጠቀሱ ናቸው። በነዚህ ሁለት ነገስታት ወቅት ይታተሙ የነበሩ ጋዜጦችን የሚያመሳስላቸው ነገር የህትመቶቹ ይዘት ሲሆን ይህም በአብዛኛው የዘውዱን ሥርዓት የሚያሞካሹ መሆናቸው ነበር።


የንጉሳዊ ሥርዓት በሀገሪቱ ካበቃ በኋላ ወደ ስልጣን የወጣው የደርግ መንግስት ቀደም ብለው ሲታተሙ የነበሩ የህትመት ውጤቶችን በመዝጋት እና በመውረስ በምትካቸው የዛሬይቱ ኢትዮጵያ እና ሰርቶ አደር የተባሉ ጋዜጦች ታትመው ለስርጭት እንዲቀርቡ አደረገ። በዚህ ሥርዓት ምንም አይነት የግል ፕሬስ ያልነበረ ሲሆን በመንግስት ታትመው የሚወጡ የህትመት ውጤቶች በሙሉ የቅድመ ምርመራ ማለፍ ይጠበቅባቸዋል።
የብሮድካስት አገልግሎትን በተመለከተ የመጀመሪያው ሬዲዮ ጣቢያ የተቋቋመው በ1941 ዓ.ም አካባቢ ከጣሊያን ካምፓኒ ጋር በተደረገ ስምምነት ሲሆን ይህ የሬዲዮ ጣቢያ በጣሊያን ወረራ ወቅት ተቋርጦ በ1949 ዓ.ም አካባቢ በድጋሚ የኢትዮጵያ ሬዲዮ በሶስት ጣቢያዎች እና በስድስት ቋንቋዎች ስራውን ጀምሯል።በኢትዮጵያ የቴሌቭዥን አገልግሎት በ1960ዎቹ መጀመሪያ ተጀምሯል።


የደርግ ሥርዓት ካበቃ በኋላ ወደ ስልጣን የመጣው የሽግግር መንግስቱ ያወጣው የኢትዮጵያ የሽግግር ወቅት ቻርተር በክፍል 1 አንቀፅ (1) (ሀ) ስር የእምነት እና ሃሳብን የመግልፅ መብቶች የተረጋገጡ ሲሆን ከዚህ በኋላ በ1987 ዓ.ም የፀደቀው የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ለፕሬስ ነፃነት የተሻለ ሰፋ ያለ ሽፋን በመስጠቱ በርካታ የግል የህትመት ውጤቶች ወደ ኢንዱስትሪው ሊገቡ ችለዋል።


በዚህ ጽሁፍ በአሁኑ ወቅት የህጎች ሁሉ የበላይ የሆነው የኢፌዴሪ ህገ መንግስት፣ የሀገሪቱ የህግ አካል የሆኑት ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እና እነዚህን መሰረት አድርገው የወጡ አዋጆች ፕሬስ ነፃነትን በተመለከተ የሚያትቱትን እንመለከታለን።

 

የኢፌዴሪ ህገ መንግስት


በህገ መንግስቱ አንቀፅ 29 ስር ሃሳብን የመግለፅ እና የፕሬስ ነፃነት የተረጋጠ ሲሆን ይህ አንቀፅ በዝርዝር ማንኛውም ሰው ሃሳብን በነጻነት የመያዝ እና የመግለፅ መብት እንዳለው፣ የፕሬስና ሌሎች መገናኛ ብዙሃን በነጻነት እንዲሁም የስነ ጥበብ ፈጠራ ነፃነት የተረጋገጠ መሆኑ፣ የቅድሚያ ምርመራ በማንኛውም መልኩ የተከለከለ መሆኑ፣ ሁሉም ሰው የህዝብ ጥቅምን የሚመለከት መረጃ የማግኘት እድል የተሰጠው መሆኑ እና የመሳሰሉት በህገ መንግስቱ ውስጥ ተካተው የሚገኙ መብቶች የፕሬስ እና ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብቶችን በተሻለ ያረጋገጡ ናቸው። በተጨማሪም ማንም ሰው በማናቸውም ዘዴ ሃሳብን በነፃነት የመሰብሰብ እና የማሰራጨት መብት ተረጋግጦለታል።


ሌላው ከፕሬስ ነፃነት ጋር በተያያዘ የተሰጠው ህገ መንግስታዊ መብት የህዝብ ጥቅምን የሚመለከት መረጃ የማግኘት መብት ሲሆን በተጨማሪም ለነፃው ፕሬስ መረጋገጥ የቅድሚያ ምርመራ በማንኛውም መልኩ ተከልክሏል። ከእነዚህ መብቶች ጋር በተያያዘ ህገ መንግስቱ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች፣ ሃሳቦች እና አመለካከቶች በነጻ መንሸራሸራቸውን ለማረጋገጥ ሲባል ፕሬስ በተቋምነቱ የአሰራር ነፃነትና የተለያዩ አስያየቶችን የማስተናገድ ችሎታ እንዲኖረው የህግ ጥበቃ እንደሚደረግለት በመደንገግ በሀገሪቱ የተሻለ የፕሬስ ነፃነት ይሰፍን ዘንድ የህግ ከለላ ለፕሬስ አካሉ መስጠት እንደሚገባ አስቀምጧል።


ሆኖም እነዚህ መብቶች ያለገደብ የሚተገበሩ አይደሉም። ህገ መንግስቱ በአንቀፅ 29/6/ ስር የፕሬስ ነፃነት እና ሃሳብን መግለፅ በመብትነትም ሆነ በነፃነት በማረጋገጥ በኩል ገደብ ሊጣልባቸው የሚችልባቸውን ሁኔታዎች አስቀምጧል። ሃሳብን በነፃነት በመግለፅ በኩል የሚኖር ህገ መንግስታዊ ገደብ በዋናነት የወጣቶችን ደህንነት፣ የሰውን ክብርና መልካም ስም ለመጠበቅ ሲባል በሚወጡ ህጎች መሰረት ሊፈፀሙ የሚችሉ ናቸው።


በተጨማሪም በዚሁ አንቀፅ ስር የጦርነት ቅስቀሳዎችን እንዲሁም ሰብዓዊ ክብርን የሚነኩ የአደባባይ መግለጫዎች በህግ ሊከለከሉ እንደሚችሉ ተደንግጓል። ይህን በማጠናከር ህገ መንግስቱ የፕሬስ አካሉም ሆነ ማንኛውም ዜጋ ከላይ በተረዘሩት መብቶች አጠቃቀም ረገድ የሚጣሉ ህጋዊ ገደቦችን ጥሶ ከተገኘ በህግ ተጠያቂ እንደሚሆን በአንቀፅ 29/7/ ስር ይገልፃል።


በአጠቃላይ ከላይ የተዘረዘሩት ነጥቦች የኢፌዴሪ ህገ መንግስት የፕሬስ እና ሃሳብን የመግለፅ ነፃነትን በተመለከተ እንዲሁም በእነዚህ መብቶች ላይ ሊጣሉ የሚችሉ ገደቦችን በተመለከተ በአንቀፅ 29 ስር በዝርዝር ያስቀመጠ ሲሆን በዚህም መሰረት ማንኛውም ሰው ከፕሬስ ነፃነት እና መገናኛ ብዙሃን ጋር በተያያዘ የተሰጡ መብቶችን ሲተገብር እነዚህን ህገ መንግስታዊ ገደቦች ታሳቢ ማድረግ እንደሚገባ እና በሀገሪቱ መብቶቹን ለማስፈፀም የሚወጡ ህጎችም ሆነ መመሪያዎች የህገ መንግስቱን መሰረታዊ መርሆዎች የተከተሉ መሆን እንዳለባቸው መረዳት ይቻላል።

ዓለም አቀፍ ስምምነቶች


ኢትዮጵያ ዋንኞቹን ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ላይ ያተኮሩ ዓለም አቀፍ ሰነዶችን ያፀደቀች ከመሆኑም በላይ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 9/4/ ስር እነዚህን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሀገሪቱ የህግ አካል መሆናቸው ተደንግጓል። በተጨማሪም በአንቀፅ 13/2/ ስር በህገ መንግስቱ የተዘረዘሩት መሰረታዊ መብቶች እና ነፃነቶች ከእነዚህ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ጋር በተጣጣመ መንገድ መተርጎም እንዳለበት በመደንገግ እውቅና ሰጥታለች። እነዚህ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ስለ ፕሬስ ነፃነት የሚያትቱትን እንደሚከተለው እንመለከታለን።

የሰብአዊ መብቶች ሁሉ አቀፍ መግለጫ


ይህ መግለጫ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሀገሮች ላይ ተፈፃሚነት ያለው የሰብአዊ መብት መግለጫ ሲሆን በአንቀፅ 19 ስር «ማንም ሰው አስተያየት የመስጠት ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት እና መብት አለው። ይህ መብት እንያንዳንዱ ሰው ያለምንም ተፅህኖ አስተያየት እንዲኖረውና እና ጠረፍ ሳይወሰነው በማናቸውም ዓይነት መሳሪያ መረጃዎችን ወይም አሳቦችን የመፈለግ የመቀበልና የማስተላለፍ ነፃነትን ይጨምራል» በማለት ሰዎች ነፃ የሆነ ሃሳብን የመግለፅ እና የማስተላለፍ መብት እንዳላቸው ይደነግጋል።

የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃልኪዳን


ኢትዮጵያ ካፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች መሀከል አንዱ ሲሆን የፕሬስ ነፃነትን በተመለከተ አንቀፅ 19 የሚከተለውን ይደነግጋል፣ ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት የራሱን አስተያየት ሊኖረው መብት አለው፣ ማንኛውም ሰው ሃሳቡን የመግለፅ ነፃነት አለው፣ በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ 2 ስር የተደነገጉ መብቶች ያጠቃቀም ሁኔታ ልዩ ግዴታዎችን እና ሃላፊነቶችን አብሮ ይዟል። በዚህም ምክንያት የተወሰኑ ገደቦች ሊደረጉበት ይችላል። ይሁን እንጂ ገደቦቹ በህግ በተደነገጉ እና የሌሎች መብቶችንና ክብርን ለማስጠበቅ፣ የብሔራዊ ፀጥታን፣ የህዝብን ደህንነት ወይም ጤናን ወይም ሥነምግባርን ለማስከበር መሆን አለባቸው። ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው ከፕሬስ እና መገናኛ ብዙሃን ነፃነት ጋር ተያያዥነት ያላቸው መብቶች ማለት ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ፣ መረጃን ያለምንም የድንበር ገደብ የመፈለግ፣ የማግኘትና የማስተላለፍ መብቶች ለሁሉም ስው የተሰጡ ቢሆንም እነዚህ መብቶች ግን ፍፁማዊ እና ያለምንም ገደብ ሊተገበሩ የሚችሉ አለመሆናቸውን ይልቁንም በህግ በተደነነገ ጊዜ የሌሎችን መብት ለማስጠበቅ እና ብሔራዊ ፀጥታን፣ የህዝብ ደህንነት፣ ጤናን ወይም ስነ ምግባርን ለማስከበር መንግስታት በህግ ይህን መብት ሊገድቡ እንደሚችሉ በዚህ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌ ላይ የተቀመጠ ነው።

 

የአፍሪካ የሰዎችና የህዝቦች መብቶች ቻርተር


የሰዎች ሃሳብን በነፃ የመግለፅ እና የፕሬስ ነፃነትን በተመለከተ ይህ ቻርተር በአንቀፅ 9 ስር የሚከተለውን አስፍሯል። ማንኛውም ሰው መረጃ የማግኘት መብት አለው፤ ማንኛውም ሰው ህግን ተከትሎ ሃሳቡን የመግለፅና የማሰራጨት መብት አለው ይላል። በዚህም መሰረት ሁሉም ሰው መረጃ የማግኘት፣ ሃሳቡን የመግለፅ እና የማሰራጨት መብት እንዳለው ሲደነግግ ነገር ግን ይህን መብት ለማስፈፀም የሚወጡ ህጎችን መሰረት በማድረግ ሊተገበር የሚገባ መሆኑን ይገልፃል። በአጠቃላይ ከላይ እንደተመለከተው ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው እና የሀገሪቱ የህግ አካል የሆኑ በእነዚህ ዓለምአቀፍ ስምምነቶች ውስጥ የፕሬስ ነፃነትን በተመለከተ የተደነገጉ መብት እና ግዴታዎች በሀገሪቱም ተፈፃሚነት አላቸው። በመሆኑም የፕሬስ ነፃነትን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት እነዚህ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ከፍተኛ ሚና ስለሚኖራቸው ታሳቢ ሊደረጉ ይገባል።


የመገናኛ ብዙሃን እና የመረጃ ነጻነትን ለመደንገግ የወጣ አዋጅ ቁጥር 590/2000


ይህ አዋጅ መነሻ ካደረጋቸው በርካታ መሰረታዊ ዓላማዎች መካከል በዜጎች መካከል የሚደረገውን ነጻ የሃሳብ እና የመረጃ ልውውጥ እንዲሁም በመገናኛ ብዙሃን የአሰራር ነጻነት ላይ መሰናክል የነበሩ መዋቅራዊ ችግሮችን ማስወገድ በሀገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ ታላቅ ሚና መጫወት የሚችል ራሱን በከፍተኛ ስነምግባር እና የሙያ ብቃት ያነጸ ዘርፈ ብዙ የመገናኛ ብዙሃን መፍጠር አስፈላጊ መሆኑ መታመኑ በዋናነት ይገኝበታል። በተጨማሪም በአዋጁ መግቢያ ላይ ይህ አዋጅ የወጣው የወጣቶችን ደህንነት የሰውን ክብርና መልካም ስም፣ ብሄራዊ ደህንነትን፣ የህዝብን ሰላምና ጸጥታን እንዲሁም ሌሎች ተነጻጻሪ መብቶችና ጥቅሞችን ለማስጠበቅ ሲባል በግልጽ በሚደነገጉ ህጎች ብቻ ሃሳብን በነጻ የመግለጽና በመገናኛ ብዙሃን ነጻነት ላይ ገደቦች እንዲጣሉ የሚያዘውን ህገመንግስታዊ መርህ በማረጋገጥ መሆኑን ተገልጿል።


በዚህ አዋጅ የመገናኛ ብዙሃን ማለት በየጊዜው የሚወጡ የህትመትና ብሮድካስቶችን የሚያካትት የህትመት ስራ እንደሆነ ትርጉም ተሰጥቶታል። ይህ አዋጅ በአብዛኛው ፕሬሱ መረጃን ጠይቆ የማግኘትና ይህ መረጃ ወይም ሃሳብን የመግለጽ መብት እንዴት እንደሚተገበር የሚያተት ነው።


በቅድሚያ አንቀጽ 4 የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት የሚያብራራ ሲሆን በዚህም የቅድሚያ ምርመራ በማንኛውም መልኩ የተከለከለ መሆኑ፤ በመገናኛ ብዙሃን ነጻነት ላይ ገደቦች የሚጣሉት ህገመንግስቱን መሰረት በማድረግ በሚወጡ ህጎች ብቻ መሆኑን እና ማንኛውም የመንግስት አካል የመገናኛ ብዙሃን ማህበራዊ ተግባራቸውን ለመወጣት፤ ዜና ወይም መረጃን የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሰራጨት ፤ በልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ አስተያየት ወይም ትችት የማቅረብ፤ የተለያዩ ሌሎች ዘዴዎችን በመጠቀም የህዝብን አስተያየት በመቅረጽ ሂደት የመሳተፍ መብታቸውን ማክበር እንዳለበት ይደነግጋል።


                                                                                                                            (በሰላማዊት ተሰማ ከፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ)

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
271 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 937 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us