የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ሕግ እና የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ተሞክሮ

Wednesday, 27 December 2017 12:44

በኮርፓሬት የውስጥ/የውጭ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነው በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ሕግ ረቂቅ ላይ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት እየሠጡ ካሉት አስተያየቶች አኳያ በሕግ አረቃቀቅም ይሁን ጉዳዮችን በመተግበር ረገድ የውጭ አገር ተሞክሮን አንደግብዓት መውሰድ ጠቃሚ ነው ሊባል ቢችልም ሁልጊዜ ከባህር ማዶ ተሞክሮን ማምጣት ብቻ ሳይሆን ሀገር በቀል ተሞክሮችንም በተጠቃሽነት ማቅረብና እንዲለመድም ማበረታታት አስፈላጊነቱን በማመን ከአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ሕግ አፈጻጸም አኳያ የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፑን ተሞክሮ ማሳየት ተገቢ ነው ብሎ በማሰብ ነው፡፡

 

ባለፈው ሰሞን በተለያዩ የዜና ማሠራጫዎች እንደተገለጸው በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካኝነት የተረቀቀው የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ሕግ በያዛቸው አንድ አንድ ጉዳዮች ላይ ተቃውሞ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ረቂቅ ሕጉ ሊደገፍ እንደሚገባው የሚገልጹ አስተያየቶች  እየተሠጡ መሆኑ ተገንዝበናል፡፡ በረቂቅ ሕጉ የተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ተቃውሞ የቀረበው በኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ሲሆን ረቂቅ ሕጉ በአንዳንድ አንቀጾች ምክንያት የሠራተኛውን መብት እንደማያስከብር፣ የኢንዱስትሪ ሰላምን እንደማያሰፍን፣ ምርትና ምርታማነትን እንደማያሳድግ፣ አሠሪዎችን እንደሚደግፍና፣ ከአንዳንድ ጉዳዮች አኳያም ረቂቁ የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታን ያላገናዘቡ ጉዳዮችን እንዳካተተ፣ ከአንዳንድ ዓለም አቀፍ ሕጐች ጋር የማይጣጣም ጉዳዮችም እንደሚታይበት በመጥቀስ ቅሬታውን ስለመግለጹ፣ በኢትዮጵያ  አሠሪዎች ፌዴሬሽን በኩል ደግሞ፣ ያቀረባቸው ማሻሻያ ሀሳቦች ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት ባያገኙም ሰጥቶ መቀበል የሚለውን መርህ በመከተል ለሁሉም የሚጠቅም ሕግ እንዲወጣ መሠራቱን፣ ረቂቅ ሕጉ በሠራተኛው የሥራ ዋስትና ላይ ሥጋት የማይፈጥር መሆኑንና የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታም ከግምት ያስገባ ረቂቅ ስለመሆኑ አስተያየት መሥጠቱን በተለያዩ ዘገባዎች ሲገለጹ ተገንዝበናል፡፡

 

ሕጉን ባረቀቀው የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ደግሞ፣ አሁን በሥራ ላይ ያለው አዋጅ ቁጥር 377/96 ሲወጣ ብዙም ምርታማነት ባልነበረበት ወቅት እንደነበርና የአሁኑ ረቂቅ ሕግ ግን በአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ለውጥ ባለበት ሁኔታ የተረቀቀ እና ረቂቁ በሦስቱም አካላት ማለትም በሚኒስትሪው፣ በኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን እና በኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) በጋራ የተዘጋጀና ውይይት የተደረገበት ስለመሆኑ ተደጋግሞ ሲገለጽ አይተናል፡፡

 

ኢሠማኮ በረቂቅ ሕጉ ቅሬታ ካነሳባቸው አንቀጾች መካከል ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፣

·      የሠራተኛው ቅጥር የሙከራ ጊዜ እስከ 90 የሥራ ቀናት ሊራዘም እንደሚችል የሚገልጸው አንቀጽ፣

·      በሥራ ገበያው ውስጥ ከፍተኛ እጥረት የሚታይበት ሙያ ያለው ሠራተኛ በራሱ ፈቃድ ሥራ ማቋረጥ ሲፈልግ መሥጠት የሚገባው የቅድመ ማስጠንቀቂያ ጊዜ እስከ 90 የሥራ ቀናት ሊራዘም እንደሚችል የሚገልጸው አንቀጽ፣

·      ለህብረት ድርድር አስፈላጊ የሆነ መረጃ ባለማቅረብ የድርድር ጊዜ እንዲራዘም ማድረግ ወይም ሌሎች ከቅን ልቡና ውጪ የሆኑ ተግባራት መፈጸም ሕገወጥ ስለመሆኑ የሚገልጸው አንቀጽ፣

·      ሠራተኛው በ1 ወር ጊዜ ውስጥ ለሁለት ጊዜ ያህል ከሥራ ቢያረፍድ አሠሪው ያለማስጠንቀቂያ በሠራተኛው ላይ የስንብት እርምጃ መወሰድ እንደሚያስችለው የሚገልጸው አንቀጽ፣

·      የሠራተኛ የዓመት ፈቃድ ጊዜ መጠኑ የአገልግሎት ዘመንን መሠረት ባደረገ ገደብ በመከፋፈል ማለትም ከ1-5, ከ6-10, ከ11-15, ከ16-20 እና ከ20 ዓመት በላይ ላገለገለ በሚል ተከፋፍሎ መነሻው 14፣ ከፍተኛው 30 የሥራ ቀናት የዓመት ዕረፍት እንደሚሰጥ የሚያመለክተው አንቀጽ፣

·      ድርጅቶች በኤጀንሲነት በሠራተኛውና በሦስተኛው ሰው መካከል ውል በሌለበት ሁኔታ ሰው ማቅረብ እንዲችሉ የሚፈቅደው አንቀጽ፣

 

በቅድሚያ መንግሥት የሌበር ሕግ እንዲወጣ የሚያደረግበት ዋናው ምክንያት በሥራ ቦታ የሠራተኛ እና የአሠሪው መብት ጥበቃ እንዲኖረው፣ የሥራ ቦታ ሰላማዊ ሆኖ ምርታማነት ከፍ እንዲል እንዲሁም የሥራ ቦታ ለሠራተኛው ጤናማ እንዲሆን ለማስቻል መሆኑ  ይታወቃል፡፡ በዚህ ረገድ ከአምስት ካምፓኒዎች ተነስቶ በአሥራ ሰባት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ወደ ሃያ አምስት ካምፓኒዎችን ያቀፈው በዶ/ር አረጋ ይርዳው ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰር/ ፕሬዚዳንት የበላይነት በሚተዳደረው የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ እያንዳንዱ ኩባንያ ለሌበር ማናጅመንት ግንኙነት መሠረቱ በሥራ ላይ ያለው የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁ.377/96 ነው፡፡ ከዚህም አኳያ ቴክኖሎጂ ግሩፑ ‹‹ሰው ተኮር›› የሚል ዘመናዊ የአመራር መርህን የሚከተል በመሆኑ በቴክኖሎጂ ግሩፑ ያሉ ሠራተኞች በአዋጁ መንፈስ መሠረት በነጻ በማህበር የመደራጀትና የህብረት ድርድር የማድረግ መብታቸውን እንዲጠቀሙ ይበረታታሉ፣ ድጋፍ፣ ይደረግላቸዋል፡፡ ስለሆነም  በቴክኖሎጂ ግሩፑ ባሉ ኩባንያዎች ያሉ ሠራተኞች በፍላጎታቸው የሠራተኛ ማህበር ያቋቋሙ አሉ፡፡ እስካሁንም 11 ያህል የሠራተኛ ማህበራት በቴክኖሎጂ ግሩፑ ውስጥ አሉ፡፡ ይህ ሃቅ በተለምዶ ድርጅቶች የሠራተኛ ማህበርን መቋቋም አይፈቅዱም፣ አይደግፉም የሚለውን ትችት የማይጋራ እንደሆነ መገንዘቡ ግድ ይላል፡፡ እያንዳንዱ በቴክኖሎጂ ግሩፕ የተቋቋመ ማህበርም ከየኩባንያው ማኔጅመንት ጋር በዓይነትና በይዘቱ ፍጹም ልዩና ዘመናዊ የሆነ የህብረት ስምምነት ድርድር ያለአንዳች ችግር በማድረግ ስምምነቶቹ ተግባራዊ በመሆናቸው ለአስራ ሰባት ዓመታት አንዳችም ችግር ሳይፈጠር በሰላም ሥራቸውን እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡

 

በቴክኖሎጂ ግሩፑ ከሰባት ሺህ በላይ ቋሚ ሠራተኞች ያሉ ሲሆን በእያንዳንዱ ኩባንያ የሠራተኛ ማህበር ቢኖርም ባይኖርም የሠራተኞች ሥራ ነክ የሆኑ መሠረታዊ መብቶችና ጥቅማ ጥቅሞች በሰው ኃይልፖሊሲ ማንዋል (Human Resource Policy Manual)፣ በደንቦችና መመሪያዎች መሠረት ይከበሩላቸዋል፡፡

የሠራተኛ ማህበር በተቋቋሙባቸው ኩባንያዎች የሚገኙ የሠራተኛ ማህበራት ሊቃነመናብርት  በየተወሰነ ጊዜ በአንድ ላይ እየተገናኙ በጋራ ጉዳዮች ላይ የሚወያዩበትና እርስ በርስ ልምድ የሚለዋወጡበት የምክክር ፎረም ሁልጊዜም የሠራተኛ ማህበራት የካፓኒዎቻችን አጋሮች ናቸው በሚሉት በቺፍ ኢግዚኪዩቲቭ ኦፊሰራችን ዶ/ር አረጋ ይርዳው አነሳሽነት መሥርተዋል፡፡ ስለሆነም የሠራተኛ ማህበር አመራሮች በየተወሰነ ጊዜ እየተገናኙ የልምድ ልውውጥና ገንቢ ሀሳቦችን ያንሸራሽራሉ፡፡ ለአሠሪው አካልም ምክረ ሃሳብ ያቀርባሉ፡፡ ይህም እውነታ የማህበራዊ ውይይት (Social dialogue) አሠራር በቴክኖሎጂ ግሩፑ ዘንድ እንዳለ አመላካች ነው፡፡

 

በሌላም በኩል ሠራተኛው ዋነኛው የኩባንያ ከፍተኛ ሀብት መሆኑን ከልብ በማመን፣ የኩባንያ አመራሩ ብዙ ድጋፎችን ለሠራተኛው በተለያዩ ዘርፎች ያደርጋል፡፡ በዚህም ረገድ የሠራተኛውና የቤተሰቡ ደህንነት (Well-being) የተጠበቀ እንዲሆን ለሠራተኛው የተለያዩ ጥቅማጥቅሞች ይሰጣሉ፡፡ ይህም የኩባንያውን ዓመታዊ ፔርፎርማንስ (Performance appraisal) ውጤትና የሠራተኛውን የሥራ አፈጻጸም መሠረት ያደረገ ዓመታዊ የደመወዝ ጭማሪ መስጠትን፣ በየዓመቱ ለዘመን መለወጫ ለሁሉም ሠራተኛ የአንድ ወር ደመወዝ በማበረታቻ መልክ መስጠትን፣ የጡረታ ስኪም የሌላቸው ሠራተኞች ከደመወዛቸው 5% እንዲያወጡ በማበረታታት ኩባንያው 10% በመጨመር የ15% የፕሮቪደንት ፈንድ (Provident fund)  እንዲኖር በማድረግ እና ሠራተኛው ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት እስከ ሁለተኛ ዲግሪ መመረቅ ድረስ የትምህርት ድጋፍ እንዲያገኝ በማድረግ የሠራተኛን ለዕውቀት የማለምለም ተግባርን ያካተተ አሠራርን ግሩፑ በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

በሚገባ ግንዛቤን የጨበጠና ኢንፎርሜሽን ያለው ሠራተኛ ምርታማ ነው በሚል መርሆ የኩባንያውን የሥራ እንቅስቃሴ ለሠራተኛው በቀጣይነት በማሳወቅ የጋራ መተማመን ከፍ እንዲል ተደርጓል፡፡ በዚህ የማኔጅመንት የአሠራር ፍልስፍና መሠረትም ሠራተኛው በቴክኖሎጂ ግሩፑ ፓሊሲዎች፣ መመሪያዎችና መረጃዎች ላይ እንዲሁም በመንግሥት በኩል በሚወጡ ሠራተኛን በሚመለከቱ ፓሊሲዎችና ሕጐች ላይ ግንዛቤ ማግኘት እንዲችል አንድ ሰዓት ተኩል የሚፈጅ የውይይት ጊዜ በየወሩ አንድ ጊዜ እንዲኖረው ተደርጓል፡፡ በመድረኩም ሠራተኛው ከፖለቲካና ሃይማኖት ጉዳዮች በስተቀር ሀሳቡን በፈለገው ርዕስ በነጻ ያንሸራሽራል፣ ይወያያል፣ ግብአትን ያቀርባል፣ ቅሬታን ያስወግዳል፣ በአጠቃላይ የኩባንያ ወገንታዊነትን ያጠነክራል፡፡

 

አሠሪው የሠራተኛው ሞራልና የሕብረት ሥራውም (Teamwork) ከፍ እንዲል፣ በሠራተኞች መካከል የአንድነትን ስሜት ለማሳደግ እንዲረዳ በዋና ሥራ ፈጻሚው (CEO) ቢሮ አማካኝነት የተለያዩ ሠራተኞችን የሚመለከት ልዩ ልዩ ዝግጅቶች (events) እንዲዘጋጁ ይደረጋል፡፡ ይህም ‹‹የቤተሰብ ቀን›› ሠራተኛውንና ቤተሰቦችን የሚያገናኝ ፕሮግራም፣ የኩባንያዎች የስፖርት ክለቦች ተቋቁመው ዓመታዊ የስፖርት ውድድር በኩባንያዎቹ መካከል እንዲካሄድ ማድረግን ያካትታል፡፡

መቻሬ በሚገኘው በቴክኖሎጂ ግሩፑ ዋና መሥሪያ ቤት ግቢ የሚሠሩ እናት ሠራተኞች በወለዷቸው ሕጻናት ምክንያት በሥራቸው ላይ ሳይጨነቁና ሳይሰጉ የሥራ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት እንዲችሉ የሕጻናት ማቆያ ማዕከል (Daycare) ተቋቁሞላቸዋል፡፡ በቀጣይም ህጻናቱ በዩኒቲ ዩንቨርሲቲ ሥር በተቋቋመው የKG እና የመደበኛ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በልዩ እገዛ እንዲማሩ ይደረጋል፡፡ ማንኛውም ወንድ ሠራተኛ የወለደችውን ባለቤቱንና የተወለደውን ሕጻን ለመንከባከብ እንዲችል ሕብረት ስምምነትን መሠረት ያደረገ የአምስት ቀን የእረፍት ቀን ከደመወዝ ጋር እንዲሠጠው የሚያደርግ አሠራር በቴክኖሎጂ ግሩፑ ዘንድ ከተቋቋመ 17 ዓመትን አስቆጥሯል፡፡ ይህም ሌላው ሊጠቀስና በሌሎች ድርጅቶች በሥራ ላይ ሊውል የሚገባው የቴክኖሎጂ ግሩፑ ልምድ ነው፡፡

የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ሕግ የያዛቸውን መሠረታዊ የሆኑ የሠራተኛ መብቶችን ከመፈጸም ባለፈም በቴክኖሎጂ ግሩፑ ዘንድ በመተግበር ላይ ያሉ አሠራሮችና ልምዶች በተለይ ለግል ሴክተር በምሳሌነት ተጠቃሽ ሊሆኑ የሚችሉ በሥራ ቦታም ለኢንዱስትሪ ሠላም መኖር የሚረዱ ሀገር በቀል ተሞክሮዎች መሆናቸውን ከግንዛቤ ማስገባት ለድርጊቱ ሀገራዊ መስፋፋት ጥቅም ይኖረዋል፡፡

 

በአጠቃላይ በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ማለትም በማዕድን፣ በእርሻ፣ በሪል እስቴት፣ በኮንስትራክሽን፣በማኒፋክቸሪንግ በትምህርት እና በሌሎችም አገልግሎት ሰጪነት የተሠማራው የቴክኖሎጂ ግሩፑ የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነቱ ሠላማዊ ሆኖ ለ18 ዓመታት ያህል የዘለቀ ነው፡፡ በሥራ ግጭት ወይም ክርክር ምክንያትም የቴክኖሎጂ ግሩፑ ኩባንያዎች ሆኑ ሠራተኞቻቸው ወደ ሦስተኛ ወገን የሄዱበት ጊዜ የለም፡፡ በሠራተኛና ማኔጅመንት መካከል አለመግባባት ሲፈጠር በየደረጃው ባለ አመራር በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚፈታ ነው፡፡ በተለይም የቴክኖሎጂ ግሩፑ ዋና ሥራ ፈጻሚ ወይም ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰር  በሕግ፣ ፖሊሲና ሕብረት ስምምነት ወዘተ አፈጻጸሞች ላይ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ የሚደረግ በመሆኑ በቴክኖሎጂ ግሩፑ ዘንድ የአሠሪውና ሠራተኛው ግንኙነት ሠላማዊ እና በሀገር በቀል ምሳሌነቱ ሊጠቀስ የሚገባው አሠራር ነው፡፡

 

 

ከላይ የተጠቀሰው አጠቃላይ ይዞታ እንዳለ ሆኖ በአሁኑ ጊዜ አዲስ የተዘጋጀውን የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ሕግ ረቂቅን ከማዳበር አኳያ የቴክኖሎጂ ግሩፑ ተሞክሮን መግለጹ ሊጠቅም ስለሚችል እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

 

የሙከራ ጊዜን በተመለከተ (45 ወይም 90 ቀናት)

በቴክኖሎጂ ግሩፑ ለተፈጠረ ክፍት የሥራ መደብ ትክክለኛውን ሠራተኛ ለመቅጠር ሲፈለግ የሥራ መደቡ የሚጠይቀው መስፈርት በማስታወቂያ እንዲወጣ ይደረጋል፡፡ መስፈርቱንም አሟላለሁ የሚሉ ሥራ ፈላጊዎች የመቀጠር ፍላጐታቸውን በመግለጽ ደጋፊ ማስረጃዎችን በማያያዝ ደብዳቤያቸውን ለቅጥር ፈጻሚው ኩባንያ ያቀርባሉ፡፡ የቅጥር መስፈርቱን የሚያሟሉትም የጽሑፍ ፈተና ተሠጥቶአቸው ቀጥሎም ቃለ መጠይቅ ይደረግላቸዋል፡፡ በዚህ ሂደት የበለጠ ውጤት ያገኘው ተወዳዳሪ ተመርጦ ለ45 ቀናት የሙከራ ጊዜ ስለመቀጠሩ በደብዳቤ ይገለጽለታል፡፡ ተቀባይነት ያገኘው ተቀጣሪ ከኩባንያ ሠራተኞች ጋር ትውውቅ ያደርጋል፡፡ ወዲያውም ሌሎች አዳዲስ ተቀጣሪዎችን ጨምሮ ስለቴክኖሎጂ ግሩፑ ግንዛቤ እንዲኖር ሥልጠና (Induction program) ይሰጣል፡፡ በዚህ ሁኔታም አዲስ ተቀጣሪ ሠራተኛ የሙከራ ጊዜ ሥራውን የሚጀምር ሲሆን፣ በሂደትም ስለሥራው ብቃት በቅርብ አለቃው ክትትል ይደረጋል፡፡ የ45 ቀናቱ የሙከራ ጊዜም እንዳበቃ የምዘናው ውጤት ለሠራተኛው በደብዳቤ ይገለጽለታል፡፡

በቴክኖሎጂ ግሩፑ ዘንድ ባለው ተሞክሮ መሠረት ለሙከራ የተቀጠረ ሠራተኛ የሙከራ ጊዜው እንዳበቃ ቅጥሩ ወደ ቋሚነት ይለወጣል፡፡ የቴክኖሎጂ ግሩፑ ፍልስፍና የሰውን ልጅ ማዕከል ያደረገ (Human centered) በመሆኑ በዚህ ሁኔታ የካምፖኒ አባል የሆነ ተቀጣሪ የሥልጠናና የትምህርት ድጋፍ በማግኘት በሥራው እያደገ የሚመጣበት ዕድልም ያለው በመሆኑ ለሙከራ  የሚቀጠር ሠራተኛ በተቀጠረበት ሥራ ላይ ለመቆየት ዋስትና ያለው ነው፡፡ ባለው አሠራር መሠረትም አዲስ ተቀጣሪ ሠራተኛን ለመመዘን የ45 ቀናት ጊዜ በቂ ሆኖ በቴክኖሎጂ ግሩፑ ዘንድ ያለችግር እየተሠራበት ነው፡፡ በተጠቀሰው የ45 ቀናት ጊዜ ውስጥ ሠራተኛው በሥራ የመዝለቅ ዕጣ ፈንታውን ማወቅ ይኖርበታል፡፡ ጊዜውን ወይም ቀናት ማራዘም በሠራተኛው ላይ ውሳኔ በአጭር ጊዜ ባለማግኘቱ የሚያስከትልበት ያለመረጋጋት ችግርን ማባባስን ያስከትላል፡፡ ለሥራው የማይመጥን ሠራተኛ በአጭር ጊዜ (45 ቀናት) በቅልጥፍና በመሥራት ሠራተኛው ቀጣዩን እድሉን በአፋጣኝ እንዲያውቅ ማድረጉ የተሻለ ነው፡፡ አሠሪውም ከ90 ቀናት በኋላ ሌላ እጩ ከመፈለግ በ45 ቀናት ውሳኔን መውሰድና ሥራ እንዳይበደል ማድረጉ የተሻለ አማራጭ እንደሚሆን ከቴክኖሎጂ ግሩፑ የአሠራር ልምድ መገንዘብ ይቻላል፡፡

 

 

ቅድመ ማስጠንቀቂያ መስጠትን በተመለከተ

የቴክኖሎጂ ግሩፑ ኩባንያዎች የሙከራ ጊዜውን የጨረሰ ማንኛውም ሠራተኛ በራሱ ፈቃድ ሥራው መልቀቅ ሲፈልግ የአንድ ወር ቅድመ ማስጠንቀቂያ ለኩባንያው በመሥጠት ሥራውን ማቋረጥ ይችላል፡፡ ይህ ሁኔታ በኩባንያዎች ህብረት ስምምነቶች የተመለከተው በሥራ ላይ ያለውን ሕግ መሠረት በማድረግ ነው፡፡ ይሁንና የቴክኖሎጂ ግሩፑ ሠራተኛ፣ የሥራው አካባቢ ማራኪ፣ ምቹ  የሥራ ሁኔታ ያለውና የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችን የሚያገኝ በመሆኑ ሥራውን ከመልቀቅ ይልቅ በሥራው ላይ የሚቆይበት ሁኔታ እንዳይሰናከል የሚመኝ እንዲሆን የተሻለ አካሄድ ባለበት ሁኔታ የሚሠራ ነው፡፡ ሆኖም በተለያየ ምክንያት ሠራተኛው ሥራውን መልቀቅ ከፈለገ ለአሠሪው በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የባለሙያ፣ የኃላፊነት፣ ወዘተ ጉዳዮችን ክፍተት በማይኖርበት ሁኔታ ለማሟላት በቂ ጊዜ ሊሆነው እንደሚችል ካለን የ30 ቀን አሠራር ተሞክሮ መውሰድ ይቻላል፡፡

 

የህብረት ድርድር ሂደቱን በሚመለከት

ህብረት ስምምነት ለሌበር ማኔጅመንት መልካም ግንኙነት ጠቃሚ የሆነ ጉዳይ መሆኑ እና ተደራዳሪ ወገኖች የሚያካሄዱት የህብረት ድርድር በአግባቡ ካልተመራ ጊዜ ሊፈጅ የሚችልና ውስብስብ ሊሆንም እንደሚችል የታወቀ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር በቴክኖሎጂ ግሩፑ ውስጥ የሠራተኛው ተወካዮችና የማኔጅመንት ወገኖች የህብረት ድርድር ለማድረግ ሊከተሉት የሚገባቸው  ሥርዓት የተዘረጋ በመሆኑ በዚህ ረገድ በቴክኖሎጂ ግሩፑ ዘንድ የአሠራር ችግር አይታይም፡፡ ድርድር አድራጊዎቹ ሥራ ላይ ያለ ህብረት ስምምነት ካላቸው ይህንኑ ለማደስ፣ አዲስ ስምምነት ለማድረግም የሚፈልጉ ካሉም ድርድሩን ለመጀመር ቀደም ብለው ተወካዮቻቸውን በደብዳቤ ለሚድሮክ ሲኢኦ ያሳውቃሉ፡፡ ከዚያም ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰራችን ዶ/ር አረጋ ይርዳው በሚገኙበት የኩባንያዎቹ የሥራ ኃላፊዎችና የሠራተኛ ማህበራት አመራር አባላት ተጠርተው የድርድሩን ሥነ-ሥርዓቱን ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰር በይፋ ይከፍታሉ፡፡ ድርድሩንም ተደራዳሪ ወገኖች በቅንነትና በተገቢው አኳኋን ማካሄድ እንዳለባቸው ያስገነዝባሉ፣ ለድርድሩም መሳካት አስፈላጊው ድጋፍ ለተደራዳሪዎች እንዲደረግ መመሪያ ይሰጣሉ፡፡ ከዚያም በተያዘው የጊዜ ገደብ ውስጥ ድርድሩን ለማጠናቀቅ ተደራዳሪዎቹ የድርድሩን ሂደት ይጀምራሉ፡፡

 

በድርድሩም ሂደት ስምምነት ላይ ሳይደርስ የቀረ ጉዳይ (Dead lock) ከተፈጠረም ጉዳዩ ለዶ/ር አረጋ ለውሳኔ ይቀርባል፡፡ እርሳቸውም ጉዳዩን ካመዛዘኑት በኋላ እና ሁለቱንም ወገኖች ካነጋገሩ በኋላ ተገቢ ነው የሚሉትን ሀሳብ የሚያጸድቁት ይሆናል፡፡ በዚህ መልኩ ውሳኔ ባገኘው ጉዳይ ላይም የሠራተኞው ወገን ቅሬታ አለኝ ካለ ጉዳዩን ለሌላ አካል የማቅረብ መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡ ይህንንም እንዲያውቅ ይደረጋል፡፡ በዚህ መልኩ የድርድር ሂደት ሲጠናቀቅ የህብረት ስምምነት ፊርማ ሥነ-ሥርዓት ፕሮግራም ተዘጋጅቶ፣ የፌዴራል የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካይ፣ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን አመራር አባላት በተገኙበት የፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ይከናወናል፡፡ የተጠናቀቀው የህብረት ስምምነት ዶክሜንትም ለሚመለከተው የመንግሥት አካል ቀርቦ ዕውቅና እንዲያገኝ ይደረጋል፡፡ ሠራተኞች ማህበር እንዲያቋቁሙ ብሎም በድርድር ጊዜ ውጤታማነት እንዳይኖር የሚያደርግ አሠራር ካለ ውጤታማና ምርታማነትን ማስመዝገብ አይቻለውም፡፡

በዚህ መሠረት የህብረት ድርድር በቴክኖሎጂ ግሩፑ ውስጥ ማኔጅመንቱ እና ሠራተኛው ወገን በመካከላቸው ቅን ልቡና በተላበሰ አኳኋን ያለአንዳች ችግርና መጓተት ከተቋጨ በኋላ በሥራ ላይ የሚውል ይሆናል፡፡ ይህን መሳይ ሰላማዊ ሂደት በማድረግ አሠሪና ሠራተኛ በህብረት ሥራቸውን ማከናወን እንደሚችሉ ቴክኖሎጂ ግሩፑ ማረጋገጥ ችላል፡፡ ይህ ሀገር በቀል አሠራር ለሌሎች በልምድ ሊወሰድ ይችላል፡፡

ከሥራ ማርፈድን በተመለከተ

የሠራተኛ ያለፈቃድ ወይም ያለበቂ ምክንያት ከሥራው ላይ መዘግየትም ሆነ መቅረት እርከን ባለው ሁኔታ የማኔጅመንት እርምጃ ማስወሰድ የሚችል የዲሲፕሊን ጥፋት ስለመሆኑ በቴክኖሎጂ ግሩፑ ሕብረት ስምምነቶች የተመለከተ ጉዳይ ቢሆንም፣ አሠሪው ምቹ የሥራ አካባቢን የመፍጠር ኃላፊነት አለበት ከሚለው አስተሳሰብ በመነሳት የቴክኖሎጂ ግሩፑ ሠራተኞች በሥራ መግቢያ ሰዓት እንዳያረፍዱ ወይም እንዳይቀሩ ሁለት ጉዳዮች ተመቻችቶላቸዋል፡፡ አንደኛው ሠራተኛው በአብዛኛው የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲኖረው በመደረጉ በየአቅጣጫው የመጓጓዣ መኪናዎች ተመደበው ሠራተኞች ወደ ሥራ ሲመጡና ወደቤታቸው ሲመለሱ በትራንስፖርቱ ተጠቃሚ እየሆኑ ናቸው፡፡ ሌላው የቴክኖሎጂ ግሩፑ አሠሪ ያመቻቸው የሥራ ሁኔታ የሠራተኞች የሥራ መገቢያና መውጪያ ሰዓት ከሌሎች መ/ቤቶች የተለየ እንዲሆን ማድረጉ ነው፡፡ ጠዋት የሠራተኛው ወደ ሥራ መግቢያው ሰዓት 2 ሰዓት፣ ወደ ቤቱ መመለሻው ደግሞ ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ እንዲሆን በመደረጉ ያለመጨናነቅ ማርፈድም ሆነ መቅረት በማይኖርበት ሁኔታ ሠራተኛው የሥራ ሰዓቱን እንዲያከበር ሁኔታዎች ተመቻችቶለታል፡፡ በመሆኑም ሠራተኛው ከአቅም በላይ የሆነ የራሱ ችግር ካልገጠመው በስተቀር በማርፈድም ሆነ በመቅረት የዕለት ተዕለት ተግባሩን ለማስተጓጐል ምክንያት የሚሆን ከሥራ ሰዓት ጋር የተያያዘ ችግር እንዳይኖር ተደርጓል፡፡ ከሥራ በማርፈድ ወይም በመቅረት እቀጣለሁ በሚል ሠራተኛውን ለሥጋት የሚዳርግ ሁኔታ በቴክኖሎጂ ግሩፑ ዘንድ አይታይም፡፡ ትራንስፖርት በሌለበት፣ እያለም የትራፊክ መጨናነቅ በሚታይበት ሁኔታ  የሠራተኛን የመዘግየትና ያለ መዘግየት ቁጥጥር ሥራ ላይ አሠሪው ተጠምዶ ማስተዳዳር ከፈለገ ውጤታማ መሆን አይችልም፡፡ እንዲያውም ሃላፊነትን እንዲያከብር በማድረግ እያበረታቱ በሥራ ላይ ባለበት ወቅት የተሰጠውን ሥራ በሚገባ እንዲያከናውን መርዳት አወንታዊ ስለሆነ ሊመረጥ ይገባል፡፡

 

 

የዓመት ዕረፍት ፈቃድ በተመለከተ

ሠራተኛ ረዘም ያለ የዓመት ዕረፍት ፈቃድ ቢኖረው ለራሱም ሆነ ለኩባንያው ጠቃሚ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ሠራተኛው ረዘም ላለ ጊዜ የዓመት ዕረፍት አግኝቶ ወደ ሥራው ሲመለስ ይበልጥ በአእምሮም ሆነ በአካሉ ጠንካራ፣ በሥራ ረገድም ምርታማ እንዲሆን እንደሚረዳው የታወቀ ነው፡፡ ከዚህም አንጻር በቴክኖሎጂ ግሩፑ የዓመት ዕረፍት ፈቃድ አሠጣጥ ከሌሎች ድርጅቶች ለየት ባለመልኩ ለአንድ ዓመት አገልግሎት መነሻ 18 የሥራ ቀናት የዕረፍት ፈቃድ ይሰጣል፡፡ ከአንድ ዓመት በላይ ለሆነ አገልግሎትም ከ18 ቀናት በተጨማሪ ለእያንዳንዱ ተጨማሪ የአገልግሎት ዓመት 1 የሥራ ቀን እየተጨመረ ፈቃድ ይሰጠዋል፡፡ በመንግሥት የተወሰነው የ14 ቀን መነሻ አነስተኛው (minimum) ስለሆነ 4 ቀን በመጨመር ሠራተኛው እንዲጠቀም ተደርጓል፡፡ በሌላ መልኩ አንድ ሠራተኛ ለእረፍት ረዘም ላለ ጊዜ ሲወጣ የሱን ሥራ በተጠባባቂነት የሚሠራው ሠራተኛ የአለቃውን ሥራ በመሥራት ልምድ ስለሚያገኝ ይህ ለኩባንያው ከፍተኛ ጥቅም አለው፡፡

ሠራተኛን ቀጥሮ ለሌላ ማቅረብን በተመለከተ

ቴክኖሎጂ ግሩፑ ለዚህች አገር ዕድገት አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል በሚላቸው ቢዝነሶች ሁሉ መሳተፍ እንደሚችል ከአመራሩ ወገን የሚነገር ጉዳይ ነው፡፡ በዚህም ረገድ በቴክኖሎጂ ግሩፑ ውስጥ ሠራተኛን ቀጥሮ ለጥበቃ ሥራ የማሠማራት ተግባር የሚካሄድ ሲሆን በዚህም ቢዝነስ ለመግባት ዋነኛ ምክንያት የሆነው ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ሲባል ነው፡፡ የቴክኖሎጂ ግሩፑ አባል በሆነው ‹‹ትረስት›› (TRUST) የጥበቃና የሰው ኃይል አገልግሎት ኩባንያ አማካኝነት ሥራ ፈላጊዎችን በሠራተኛነት በመቅጠር ለሦስተኛ ወገን አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋል፡፡ በዚህም ሁኔታ የተቀጠሩ ሠራተኞቹን ኩባንያው ተገቢውን ደመወዝ ይከፍላቸዋል፡፡ ዓመታዊ የደመወዝ ጭማሪ እና በቴክኖሎጂ ግሩፑ እህት ኩባንያዎች ላሉ ሠራተኞች የሚሰጡ ጥቅማ ጥቅሞች፣ የሕክምና አገልግሎቶች፣ የተለያዩ ፈቃዶችና ዕረፍቶች ጊዜዎች ሁሉ ይፈጸምላቸዋል፡፡ ሠራተኞቹም የራሳቸው የሆነ የሠራተኛ ማህበር ያላቸውና ከኩባንያ ማኔጅመንት ጋርም ያደረጉት የህብረት ስምምነት አላቸው፡፡

እዚህ ላይ ቴክኖሎጂ ግሩፑ አነስተኛ በሆኑ ቢዝነሶችም ይገባል የሚሉ አንዳንድ አስተያየቶች ቢሰጡም ከላይ በተጠቀሰው የሰው ኃይል አገልግሎት ሥራ ውስጥ ቴክኖሎጂ ግሩፑ የገባው በዋናነት ለዜጐች የሥራ ዕድል ለማስገኘት የበኩሉን ማህበራዊ ድጋፍ ለማድረግ ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃም የቴክኖሎጂ ግሩፑ ኩባንያዎች የጥበቃ ሥራቸውን በየራሳቸው እንዲሠሩት ከማድረግ ይልቅ በሌላ አካል እንዲጠበቅ ቢያደርጉ ጥበቃውን ይበልጥ አስተማማኝ እንደሚያደርገው ስለታመነ ይህም ሁኔታ ለትረስት የጥበቃና የሰው ኃይል አገልግሎት ኩባንያ መቋቋም ሌላው ምክንያት ነበር፡፡ ይህም የጥበቃ አሠራር ውጤታማ የሆነ ሌላው የቴክኖሎጂ ግሩፑ ተሞክሮ ነው፡፡ 

 

 

በዚህም መሠረት በአንዳንድ ኤጀንሲዎች የሚፈጸም የሥራ ስምሪት የሠራተኛ መብት ጥያቄን እያስነሳ ነው የሚባለው ችግር በቴክኖሎጂ ግሩፑ ዘንድ የለም፡፡ 

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
306 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 883 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us