ይድረስ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማሪያም ደሣለኝ በነካ እጃችሁ የምታፈርሱልንና የምትገነቡልን ነገር አለ

Friday, 12 January 2018 17:02

ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል

                                                                       This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

 

ክቡር ሆይ!
በቅድሚያ የናፍቆቴን ያህል እንደምን አሉ? እኔ እንዳለሁ አለሁ። ክቡርነትዎም እንደሚገነዘቡት እኔ አንድ ተራ ሀገር ወዳድ ዜጋ ነኝ። ለሀገሬ ያለኝ ፍቅር ወሰን የለውም። አሁን አሁን ይሄ አለቅጥ አገሬን መውደዴ “አጥፊዬ ይሆን እንዴ?” የሚል ጥያቄ እያጫረብኝ መጥቷል። ምክንያቱም አንዳንድ ጊዜ “አሁን አርፌ መቀመጥ አለብኝ” ብየ ወስኜ ተቀምጨ ሳለ ባልጠበቅኩት ሁኔታ ስሜቴ ይነካና እንዲህ እንደ አሁኑ እመር ብዬ ብዕሬን አነሳለሁ።

 

ክቡር ሆይ!
ይህቺን ጦማር በሰንደቅ ጋዜጣ በኩል እንድጽፍልዎ ያነሳሳኝ፤ ሰሞኑን የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ 17 ቀናት የፈጀ ግምገማ ካካሄደ በኋላ ያወጣው መግለጫ እና ከዚያም በማስከተል እርስዎና ሌሎች አመራር አባላት የሰጣችሁት ጋዜጣዊ መግለጫና ማብራሪያ ነው።


“ወደቀ፣ ተበተነ፣ አለቀለት፣ አንድ ሀሙስ ቀረው፣”… ሲባል አፈር ልሶ በመነሳት የሚታወቀው ኢህአዴግ ዛሬም እንደተለመደው ተፍገምግሞ መነሳቱን ሰማን። ችግሮቹን ፈትሾ በመመለስ ህዝቡ ሌላ እድል እንዲሰጠው ጠይቋል። አንድ የፖለቲካ ኃይል ይህን ማድረጉ የሚገርም አይደለም። ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ለኢህአዴግ ዕድል የሚሰጠው ስንት ጊዜ ነው?
አበው “አንድ ጥርስ አላት በዘነዘና ትነቀሰው አማራት” እንዲሉ የሆነበት የኢትዮጵያ ሕዝብ ከኢህአዴግ የተሻለ አማራጭ በሌለው ሁኔታ የሚተካውን ሳያዘጋጅ ከኢህአዴግ ጋር “መፋታት” የሚችል መስሎ ስለማይታየኝ ኢህአዴግ “የመጨረሻ እድል” የማግኘቱ ነገር የተዘጋ ሆኖ አይታየኝም። ለማንኛውም ውጤቱን በመጪዎቹ ምርጫዎች የምናየው ይሆናል። ለአሁኑ ኢህአዴግ ይህንን እድል ለመጠየቅ “አደርጋለሁ” ብሎ ባነሳቸው ነጥቦች ላይ በማተኮር አስተያየቴን ላቅርብ።

 

ክቡር ሆይ!
እርስዎና የሦስቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መሪዎች በሰጣችሁት መግለጫ ማብራሪያ ካነሳችኋቸው ነጥቦች አንዱ “የላቀ መግባባትን ለመፍጠር…” ሲባል አንዳንድ የፖለቲካ ውሳኔ መወሰናችሁንና በዚህም መሠረት “የፖለቲካ እስረኞችን” እንደምትፈቱ፣ ከአፄ ኃ/ስላሴ ዘመነ መንግስት ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የኢትዮጵያውያን የግርፋት (ቶርቸር) እና የስቃይ ማዕከል ሆኖ ሲያገለግል የነበረውን በተለምዶ “ማእከላዊ” የተሰኘ አስር ቤት ወደ ሙዚየምነት እንደሚቀየር ገልጻችኋል።


ይህ ውሳኔ በኢህአዴግ የ26 ዓመታት የስልጣን ዘመን ታይቶም ተሰምቶም የማያውቅ መልካም እርምጃ ነው። ኢህአዴግ “በሀገሪቱ የፖለቲካ እስረኛ የሚባል ነገር የለም፣ የዜጎችን ሰብአዊ መብት እንደ እኔ የሚጠብቅ የለም፣ የሰዎች ስቃይ (ቶርቸር) አይፈጸምም…” ከሚል ተጨፈኑና ላሙኛችሁ ከሚል ድርቅና ወጥቶ ለጥፋቶቹ እውቅና መስጠቱ ሊያስመሰግነው ይገባል። ነባሩን አመራር የተካው አሁን ያለው የኢህአዴግ አመራር ለወቅቱ የሚመጥ የፖለቲካ ብልጠት መጀመሩን የሚያመለክትም ነው። “አፍ እንጂ ጆሮ የለውም” ሲባል የነበረው ኢህአዴግ መላ አካሉን ለማሰራት መነሳሳቱ መልካም ነው።

 

ክቡር ሆይ!
ይህ የኢህአዴግ አዲስ አመራር ቁርጠኛነት ካለውና የበለጠ ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠርና የሀገሪቱን የፖለቲካ ምህዳር እንዲሰፋ ለማድረግ ከፈለገ በነካ እጁ ሊያከናውናቸው ይገባል ብዬ ያሰብኳቸውን በህብረተሰቡ ዘንድ በስፋት የሚነሱ ጉዳዮች እንደሚከተለው ለማቅረብ እሞክራለሁ።


“አግኣዚ” የተባለውን ኮማንዶ ጦር ስም መቀየርን በተመለከተ፤
አግኣዚ ክፍለ ሠራዊት በትጥቅ ትግሉ ወቅት በተሰዋ ታጋይ የተሰየመ የጦር ክፍል መሆኑን ሰምቻለሁ። በአሁኑ ወቅት “አግኣዚ” የተሰኘው የሠራዊት አካል በብቃት የሰለጠኑ የፓራ ኮማንዶ አባላት ስብስብ ነው ይባላል። ጦሩ በውሃ ዋና፣ በዝላይ፣ በእጅ ለእጅ ፍልሚያና በመሳሰሉት የሰለጠነ የኢትዮጵያ ልዩ ኃይል መሆኑም ይነገራል። በኔ ግምት ይህንን ጦር ለማሰልጠንና ለማብቃት ሀገሪቱ ወጪ አውጥታለች፣ ጊዜና ጉልበትም ባክኗል።


ይህ የጦር ክፍል “የውስጥም ሆነ የውጭ ጠላቶቻችንን ሃሳብ እና ምኞት ለማምከን ባለፉት 26 ዓመታት ያበረከተው አስተውጽዖ ወደር አይገኝለትም” የሚሉ ወገኖችም አሉ። በርግጥ የአግኣዚ ጦር የሀገሪቱን ዳር ድንበር፣ የህዝቡን ሠላምና ፀጥታ በማስጠበቅ ረገድ የሰራውን ስራ እኔም እገነዘባለሁ።


ይሁን እንጂ ይህ የጦር ሠራዊት አካል ልክ እንደ ማዕከላዊ እስር ቤት በህብረተሰቡ ዘንድ ጥሩ ስም የለውም። ይህ አሉታዊ ገጽታ የተሰጠው ደግሞ በተለይም ከምርጫ 1997 በኋላ በአዲስ አበባና በአንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠሩትን ሁከቶች በማብረድ ሂደት በወሰዳቸው “ያልተመጣጠኑ እርምጃዎች” ምክንያት እንደሆነ አስባለሁ።

 

ክቡር ሆይ!
በዚህ ረገድ በህብረተሰቡ ውስጥ ስለ አግኣዚ ያለውን አመለካከት ለማሳየት ያህል አንድ የፌስ ቡክ ወዳጄ የላከልኝን አስተያየት እንዳለ ላቅርበው፡-
“አብዱ እኔን ጨምሮ ብዙ ሲቪል ሰው አእምሮ ውስጥ አግኣዚ ሲባል የምናቀውና በተግባርም በተደጋጋሚ ያየነው ጉድጓድ ውስጥ እንዳደገ አውሬ ማንንም ከማንም ሳይለይ ህፃናትና ሴቶችን ሳይቀር ያለ ምንም ጥያቄ ለመጨፍጨፍ ብቻ የተዘጋጀ ክፉ ኃይል [እንደሆነ] ነው። ድንጋይ የያዘን ታዳጊ አነጣጥሮ ጭንቅላቱን ለመበተን የማያመነቱ ግዑዛን ናቸው። ለህዝቡም የወገናዊነት ስሜት የሚታይባቸው አይደሉም። ማንም እንደተከላካይ ሠራዊት አይቆጥራቸውም… ማዕከላዊ ተዘግቶ ሙዚየም ይደረግ የተባለው እኮ ያ ግቢ እና ያ ሥም የብዙ ሰዎችን ቁስል ስለሚያመረቅዝ ነው። አግአዚም እንዲሁ ነው… በ97 እና በ98 መርካቶና አካባቢው ላይ በአውሬአዊ ድርጊታቸው የሆነብንን አይተን ሻዕቢያ ወይም ግብፅ ቢወረን ከዚህ በላይ ምን ያረገናል ብለናል። ጨለምተኛ ካላልከኝ… የዛ ጦር አባላት ከእንግዲህ ህዝባዊ ታማኝነት ይኖራቸዋል ብትለኝ ለኔ እጅግ ከባድ ነው” ብሎኛል።

 

ክቡር ሆይ!
አግኣዚን እንዲጠላ ያደረገ ሌላኛው ምክንያት አንዳንድ ከቡድናዊ አስተሳሰብ ያልወጡ ጠባቦች “አግኣዚ የኛ ነው” የሚል ያልተገባ ባለቤትነት መስጠታቸው እንደሆነም የሚናገሩ ወገኖች አሉ።
ከዚህ ሌላ በአግኣዚ ጦር ላይ ስም የማጥፋት ዘመቻ የከፈቱትና እንዲጠላ ያደረጉት “ጥቅማቸው የተነካባቸውና የስልጣን ሕልመኛ የሆኑ ቡድኖችና ተከታዮቻቸው” ጭምር መሆናቸውን የሚናገሩም ወገኖች አሉ። ከዚህ አስተያየት በመነሳት መላ ሕዝቡ “አግኣዚን ይጠላዋል” ብሎ መደምደም ያስቸግራል።


ይሁን እንጂ፤ በርግጥም “አግኣዚ” የተባለው የኮማንዶ ሠራዊት ልክ እንደ ማዕከላዊ እስር ቤት በህብረተሰቡ ዘንድ ጥሩ ስም የሌለው መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም።
በዋናነት ማእከላዊን ይጠሉት የነበሩት ግፍ የደረሰባቸውና ሁኔታውን በቅርበት ያዩ ሰዎች ነበሩ። አግኣዚንም የሚጠሉት በ“አግኣዚ ግፍ ተፈጸመብን” የሚሉ ወገኖች ናቸው።
በበኩሌ የ“አግኣዚ” ኮማንዶ ግዳጁን በመፈጸም ሂደት ያጠፋው ጥፋት እንዳለ አስባለሁ። በአንዳንድ ስፍራዎች ያልተመጣጠነ ኃይል ተጠቅሞ ሊሆን እንደሚችልም እገምታለሁ። በዚህም ምክንያት ልጆቻቸው የሞቱባቸው ወላጆች፣ ወላጆቻቸው የሞቱባቸው ልጆች፣… ወንድሞቻቸው፣ እህቶቻቸው፣ አጎቶቻቸው፣ አክስቶቻቸው፣ ጓደኞቻቸው፣… የሞቱባቸው ሰዎች እንዳሉ ይታወቃል።


በሌላ በኩል በ“አግኣዚ” ኮማንዶ ላይ ለዓመታት የዘለቀ የአሉባልታ ዘመቻ ተካሂዶበታል የሚል እምነትም አለኝ። በዚህም ምክንያት ሌሎች ከመከላከያ ሠራዊቱ ዩኒፎርም ተመሳሳይ ልብስ የለበሱ የፖሊስና የመከላከያ አካላት የፈጸሙትን ጥፋት ሁሉ የ“አግኣዚ” ጥፋት ተደርጎ እንዲወሰድ በመደረጉ የ“አግኣዚ”ን ስም አጠልሽተውታል።


በዚህ ሳቢያ የዚህ ጦር ስም ሲነሳ ከጥቃት ይጠብቀኛል ወይም ይንከባከበኛል ሳይሆን ይጨፈጭፈኛል ብሎ የሚያስብ ህብረተሰብ ጥቂት የሚባል አይደለም። “አግኣዚ” ሲባል አለኝታነቱ፣ መከታነቱ፣… የማይታያቸው ሰዎች አሉ። “አግኣዚ” ሲባል ሽብር፣ ሞት፣ እልቂት፣… የሚታየው ብዙ ሰው ነው።


ስለሆነም፤ እኔ በበኩሌ ይህ ጦር መበተን ሳይሆን ስሙን ቀይሮ ውስጡን ማጥራት፣ ወንጀለኞች ካሉ በህግ መሰረት እንዲጠየቁ ማድረግ አስፈላጊ ነው የሚል እምነት አለኝ። ይህ ቢደረግ የተከፉ ሰዎች የሞራል ካሳ ያገኛሉ ብየ አስባለሁ። የበለጠ መግባባትን ይፈጥራል የሚል እምነትም አለኝ።


በሌላ በኩል፤ ለህዝቦች ነፃነነት የተጋደለውንና የተሰዋውን አግኣዚ ገሠሠን ህዝቦች ላይ ያልተመጣጠነ እርምጃ በመውሰድ በዜጎች ለሚጠላ ተቋም ስያሜ ማድረግ የዚህን ጀግና ታጋይ መልካም ስም፣ ክብርና ዝና መና ማስቀረት መሆኑም ግንዛቤ ሊሰጠው ይገባል የሚል እምነት አለኝ።


የአግኣዚ ስም መቀየር ያለጥፋቱ ስሙ በከንቱ እየጠፋ ያለውን የሀገሪቱን የመከላከያ ሠራዊት ህዝብ የሚመካበት፤ መልካም ስም ክብርና ዝና ያለው ጦር እንዲሆን ለማድረግም ይረዳል ብየ አስባለሁ።

ሌሎች መደረግ የሚገባቸው ጉዳዮች፤


ክቡር ሆይ! በጥልቅ ተሃድሶ አለፍኩ ያለውና አሁን በቅርቡ ተጨማሪ ግምገማ አድርጌአለሁና ህዝብ ተጨማሪ እድል ይስጠኝ እያለ ያለው ኢህአዴግ የበለጠ ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር በርካታ ሊያከናውናቸው የሚገባቸው ጉዳዮች አሉ ብዬ አስባለሁ። ከበርካታዎቹ ጉዳዮች ውስጥ በእኔ በኩል ግምት ሊሰጣቸው ይገባል ያልኳቸውን እንደሚከተለው ጠቅለል አድርጌ አቀርባለሁ።


(1ኛ) በእስር ላይ ለሚገኙ እስረኞች ምህረት ማድረጉ በቂ ስላልሆነ የላቀ መግባባትን ለመፍጠር ይቻል ዘንድ በተለያዩ ምክንያቶች ከአፄ ኃ/ስላሴ ዘመነ መንግስት ጀምሮ ወደ ውጪ ሀገር ለተሰደዱ ምሁራን፣ ባለሀብቶች፣ ጋዜጠኞች፣… ወደ ሀገራቸው ተመልሰው በሀገር ግንባታ ሂደት የየበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ ሀገራዊ ጥሪ ማድረግ፣


(2ኛ) ነፍጥ አንስተው ለሚታገሉ፣ ሠራዊት ሳይኖራቸው በደረቁ ለሚፎክሩ የአሜሪካና አውሮጳ የከተማ ፋኖዎች “ጠመንጃቸውን እና የጠመንጃ አስተሳሰባቸውን አስቀምጠው” ወደ ሀገራቸው በመግባት ሠላማዊ የፖለቲካ ትግል እንዲያደርጉ ሠላማዊ ጥሪ ማድረግ፣


(3ኛ) ባለፉት 26 ዓመታት ኢህአዴግ የወሰዳቸው የሀገሪቱን አንድነት ያናጉና የባህር በር ጭምር ያሳጡ ውሳኔዎችን በጥናት ላይ በመመስረት እንደገና በመፈተሽና በመመርመር የማሻሻያ ውሳኔ መወሰን፣


(4ኛ) የሀገሪቱን አንድነት የሚሸረሽሩ፣ የህዝቦችን አንድነትና ወንድማማችነት የሚያደፈርሱ፣ ዜጎችን ለፍጥጫ ለቂምና ቁርሾ የሚያነሳሱ በመታሰቢያነት የተሰሩ ሀውልቶችን፣ ስያሜዎችን፣ ወዘተ. በተመለከተ ህዝቡን፣ የሃይማኖት አባቶችን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን፣ ምሁራንንና የፖለቲካ አካላትን፣… በማማከርና በማወያየት የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ፣


በመጨረሻም፤ አሁን ያለው ህገ መንግስታዊ ስርዓት እንዳለ ሆኖ፣ ብሔራዊ የእርቅና የመግባባት መድረክ በመፍጠር ለሀገሪቱ ህልውና ወሳኝ በሆኑ ዋና ዋና ሀገራዊ ችግሮች ዙሪያ ለመምከር የሚያስችል ሰፊ ሀገራዊ የእርቅና የመግባባት መድረክ በመፍጠር የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት፣ ሠላማዊ ዴሞክራሲያዊና ህገ መንገስታዊ የስልጣን ሽግግሩ ሂደት እንዲጠናከር ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን በአክብሮት እገልጻለሁ።
የምጊዜም አክባሪዎ!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
109 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1038 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us