ይድረስ ለሰንደቅ ጋዜጣ

Friday, 12 January 2018 17:07

 


ይህችን ጹሑፌን በአምድዎ ላይ እንድያሰፍሩልኝ በትህትና ጠይቃለሁ
ረቡዕ ታህሣሥስ 18 ቀን 2010 ዓ.ም የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም ለመወሰን የወጣ አዋጅ (ረቂቅ) በሚል የተዘገበውን አንብቤ በመገረም ይህንን ማስታወሻ ለመጻፍ ተነሳሳሁ።


መጀመሪያ አዲስ አበባ የማንነች? በሚል ጥያቄ ልነሳና ሃሳቤን ለአንባቢያን ላክፍል ወደድሁኝ።
በመሰረቱ አዲስ አበባ የኢትዮጵያዊያን እንጂ የአንድ ክልል ወይንም የአንድ ብሔረሰብ ንብረት አይደለችም! ልትሆንም አትችልም። ይህንን ለመወሰን የዓለምን ሁኔታ ማየትና ማገናዘብን ይጠይቃል። ይህንን ስል በስሜት ወይንም በማንአለብኝነት ሳይሆን የሰለጠኑትን ዓለማት ሁኔታዎችና ታሪክንም በተገነዘበ በጠራና በፀዳ በሙሁራዊ አስተያየት ነው። ማንም አገር ችግርን ራሱ ጋብዞ በመጨረሻ ለመፍትሄ አይሯሯጥም፤ ግን አስቦና ተዘጋጅቶ ውሳኔዎችን ማሳለፍ ታላቅ ችሎታ ነው።


ኢትዮጵያችን ከጌታ ክርስቶስ ልደት በፊት የነበረች፤ ብዙ ታሪክን መስክራ በትዝብት ያሳለፈች፤ ብዙ መከራንና ችግርን ያየች ታላቅ አገር መሆኗን መዘንጋት የለብንምን፡፡ የዛሬይቱ ታላቋ አሜሪካ ኒውዮርክን እንደዋና ከተማ አድርጋ የመጀመሪያውን ፕሬዚዴንት ጅርጅ ዋሽንግተንን የሰየመችው እዚች ከተማ ነበር፤ ነገር ግን ከተማዋ ሁሉን ልታማክል የምትችል መሆኗ ታይቶ ወደፊላዶልፊያ እንዲሆን ታሰበ ይህም አመቺ ሳይሆን ቀርቶ አሁን ወዳለበት ቦታ እንዲሆን ሲታሰብ ይህ ቦታ የሁለት ግዛቶች በመሆኑ ከቬርጂኒያና ከሜሪላንድ ግማሽ ግማሽ ተቆርሶ ዋና ከተማ እንዲሆን ሲመረጥ በዋሽንግተን ነዋሪ የሆነ ሰው በሴኔትም ሆነ በኮንግረስ ተሳትፎ ድምፅ እንዳይሰጥ ስምምነት ተደረሰ፡፡


ከጁላይ 9 ቀን 1790 ዓ.ም ጀምሮ ዋሽንግተን ነፃ (ወይንም ኒውትራል) እንድትሆን ተብሎ በማንኛውም በፌዴራል ጉዳይ ድምፅ እንድትሰጥ ተደረገ፤ በዚህም ምክንያት የዛሬዎቹ ወጣቶች ያለ ድምፅ ታክስ ከፋይ (TAXATION WITHOUT PRESENTATION) በሚል ሮሮ ሲያሰሙ ኑረው ወደ 20 ዓመታት ገደማ ያለድምፅ በታዛቢነት ብቻ አንድ ሰው እንዲቀመጥ ተደርጎ ታዛቢ መቀመጥ ጀመረ። ይሁን እንጂ ሜሪላንድም ሆነች ቨርጂኒያ ከሌላ አሜሪካን የተለየ ጥቅም ይሰጠን ብለው አያውቁም፤ ቢሉም ከትዝብት ሌላ የሚያገኙት የለም። ታላቋ ብሪታኒያ ሎንዶን የሚባለውን ስም ይዛ የተናሳችው ከጌታ ልደት በኋላ በ43ዓ.ም በሮማኖች በጁሌ ሲዛር (Julius Caesar) ዘመነ መንግሥት እንደነበረ ታሪክ በዋቢነት ያስረዳናል።


ካሊፎርኒያ፤ ቴክሳስ፤ ፊኒክስና ሌሎችም የሜክሲኮ አካል መሆናቸው የታወቀ ሲሆን በኋላ ወደ ሰሜን አሜሪካ መቀላቀላቸው የታወቀ ነው። ሉዚያና በዘመነ ናፖሊዮን በግዢ ወደ አሜሪካ መቀላቀሏ የማይካድ ሐቅ ነው። ታዲያ በዘመኑ ባለቤት የነበሩ ሁሉ ዛሬ ዘመን ተለውጧልና የጋራ ንብረታችን ስለሆነ ከጥቅሙ እንካፈል አላሉም። አገር የጋራ በሚለው ፍልስፍና ያገሬው ሰዎች ባለቤት በመሆን የሰሜን፤ የደቡብ፣ የምስራቅና የምዕራብ ሳይባባሉ ባንድ ብሔርተኝነት ጥቅምን የጋራ በማድረግ ለጋራ አገራቸው እኩል ያስባሉ፤ እኩል ይተጋሉ፤ ይሠራሉም።


ታዲያ ከክርስቶስ ልደት በፊት የነበረችን ኢትዮጵያ ማስብና መገንዘብ ያቃተው ትውልድ ይሆን? ይህንን ሃሳብ አምጥቶ የጋራ ቤትን ሊሰነጥቅ ያሰበው? ወይን የከተማ ባለቤትነት የሁሉ መሆኑ ቀርቶ የዋናው መንግሥትና የክልል ድርሻ የሚባል ታይቶ ተሰምቶ በዓለም ያልታወቀ እንግዳ ነገር ከየት የመጣ? የመለያየትና የመራራቅ ዜይቤ ነው? ለማንኛውም ታላቅ ያገር ጉዳይ በመንግሥት ባለሥልጣናት ከመወሰኑ በፊት በይፋ ለጠቅላላው ሕብረተሰብ ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል እንጂ ያንድ አገር ዜጋ የበይ ተመልካች መሆን እንደሌለብት ታውቆ ይህ የመንግሥት ባለሥልጣናት ብቻ የሚያደርጉት ጉዳይ ሳይሆን የሁሉም ተሳትፎ መኖር ያለበት እንዲሆንና ታላቅ ሕዝባዊ ምክክርና ውይይት ሊደረግበት ተገቢ መሆኑ ታውቆ ሁሉም ትንሽ፤ ትልቅ፤ ደሃ ወይንም ጌታ ሳይባል ተሳትፎ እንዲኖረው ይደረግ ስል፤ ይህም የይስሙላ ሳይሆን ትክክለኛ ሁሉን አቀፍ እንዲሆን አሳስባለሁ።


ማን ነው የኢትዮጵያዊያንን ባለቤትነት ለክልል የተነሳሳው? የደቡቡ፤ የሰሜኑ፤ የምዕራቧና የምስራቁ ኢትዮጵያውዊ ከአዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ባለቤትነት ተሰርዟል ማለት ነው? ወይንስ ይህ እንደፍልስጤሞችና እስራኤሎች የተለያየ ሕዝብ መሆኑ ነው? ይህ ግልጽ ስላልሆነልኝ የሚመለከተው አካል በዚህች ጋዜጣ እንዲያስረዳኝ በአክብሮት እጠይቃለሁ
አሰፋ አደፍርስ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
111 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 946 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us