የአጻጻፍ ስሕተቶች

Wednesday, 17 January 2018 13:37

 

ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ

 

የአማርኛ መጻሕፍት ሳነብ አንዳንድ ስሕተቶች ተደጋግመው ያጋጥሙኛል። በአማርኛ ብዙ መጻሕፍት ያላነበቡ ግን የመጻፍ ችሎታ ያላቸው ደራሲዎች አሉን። እነዚህ ደራሲዎች የአማሮችን ባህልና በአማርኛ የሚባለውን የንግግር ፈሊጥ ሁሉ ያውቋቸዋል። ግን ይህን ዕውቀት ያገኙት ከመማር (ማለት መጻሕፍት ከማንበብ) ሳይሆን ሲባል ከመስማት ነው። ያ ዕውቀት የአማርኛ ደራሲ ለመሆን የሚያበቃ ይመስላቸዋል። ያንን ዓይነት ዕውቀት ፊደል ያልቆጠረ መሃይምም ሁሉ ያውቀዋል። በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት አንዱ ፈደል መቍጠሩና የሰማውን መጻፉ ሲሆን ሌላው አለመቍጠሩና የሰማውን ለመጻፍ አለመቻሉ ነው።


ከዚህ በታች በግራ ያሉት ስሕተቶች፥ ከፍላጻው (ከ→) ቀጥሎ በቀኝ ያሉት ትክክለኛ ማብራሪያ ናቸው።


ጸባይ → ጠባይ (“ጸ” እና “ፀ” ወደ “ጠ” ይለወጣሉ። “ጠባይ” ግን “ጠባይ” የሆነው “ጸ” ወይም “ፀ” ወደ “ጠ” ተለውጦ አይደለም። ዱሮውኑ ሲፈጠር “ጠባይ” ሆኖ ነው። 
እዛ → እዚያ።
ለዛ → ለዚያ።
ከዛ → ከዚያ።
ወደዛ → ወደዚያ።
ወደ እዛ → ወደ እዚያ።
የዛው → የዚያው።
እንደዛው → እንደዚያው።
እነዛ → እነዚያ።
በዛው → በዚያው።
እስከዛ → እስከዚያ።
እዛው → እዚያው።
ሚስጥር/ ምስጥር → ምስጢር።
ተመስጌን → ተመስገን (አለዚማ “ተቀሜጥ”፥ “ተኔሣ”፥ “ተዜጋጅ” ማለት ልክ ሊሆን ነው።)
እንደው → እንዲያው።
እግዚአብኤር → እግዚአብሔር።
ነብስ → ነፍስ (ምንጩ “ነፋስ” ስለሆነ፥ “ነብስ” ሊሆን አይችልም።)
አንደበተ ርትሁ → አንደበተ ርቱዕ።
ጋር → ጋ ወይም ዘንድ።
ጊወን → ግዮን።
እቺ → ይቺ።
ተሞክሮ → ተመክሮ።


ግርግዳ → ግድግዳ (አማርኛ እንደ ሌሎቹ ሴማዊ ቋንቋዎች ብዙ የቃል አፈጣጠር ዘዴዎች አሉት። አንዱ ዘዴ በሦስት ፊደል አንድ ቃል መፍጠር ነው። ነቀለ፥ ወደቀ፥ ሰበረ፥ ወረደ፥ ወዘተ። ሌላው ዘዴ ሁለትን ፊደሎች መድገም ነው። ሰበሰበ፥ ቀረቀረ፥ ገመገመ፥ በጠበጠ፥ ገደገደ፥ ገሠገሠ፥ ወዘተ። “ግርግዳ” ስሕተት የሚሆነው፥ የጥንቱን ፊደል በሌላ ፊደል በመተካት ሕጉን ስለጣሰ ነው።)


ምዕተ ዓመት → ምእት ዓመት።
የሚጠቀመው → የሚጠቀምበት።
የሚጠቀመው መርፌ → ሚጠቀምበት መርፌ። 
መርፌውን ተጠቀመው → መርፌውን ተጠቀምበት።
ኩምሳጥን → ቁም ሳጥን (ሁለት ዓይነት ሳጥኖች አሉ።)


ኢትዮጵያኖች → ኢትዮጵያውያን/ያት። (ኢትዮጵያኖች የEthiopian ብዙ ቍጥር ነው። ካስፈለገ “ኢትዮጵያዊዎች/ ኢትዮጵያዊቶች” ማለት ይቻላል። Ethiopianoች /Ethiopiaኖች ግን ጸያፍ፡ ነው። የአገራችን ስም “ኢትዮጵያ” ነው እያልን። ራሳችንን Ethiopianoች አንበል።)


ህብው → ኅቡእ።
በስማአብ → በስመ አብ።
“ማለት ነው” ይኸ ሐረግ አለቦታው ተመላልሶ ይመጣል። (“ይሄዳል ማለት ነው”፥ “ይመጣል ማለት ነው”፥ “እንበላለን ማለት ነው”። የዘመኑ ቋንቋ መሆኑ ነው መሰለኝ።)
-ሁኝ → ሁ (“በላሁኝ፥ ጠጣሁኝ፥ አየሁኝ፥ ጻፍኩኝ” አይባልም፤ ባለቤትንና ተሳቢን መደባለቅ ይሆናል። የሚባለው (“በላሁ፥ ጠጣሁ፥ አየሁ፥ ጻፍኩ” ነው። “-ኝ” ን ከመረጥን “በላኝ፥ ጠጣኝ፥ አየኝ፥ ጻፈኝ” ማለት ነው። “ሁ” አድራጊን (ማድረጌን) ያመለክታል፤ “አየሁ” ፤ “ኝ” ተደራጊን (መደረጌን) ያመለክታል፤ “አየኝ”። ሁለቱ አንድ ግሥ ላይ አብረው አይመጡም። “አየሁኝ” ካልን “አየሁ”ን እና “አየኝ”ን መደባለቅ ይሆናል። 
የ “ሀ፥ ሐ፥ ኀ”፣ የ “ሰ፥ ሠ”፣ የ “አ፥ ዐ” ፣ የ “ጸ፥ ፀ” አገባብ አስቸግሯል። ፈጥኖ ደራሽ መፍትሔ የለኝም። በትምህርት ያደግነው አገባባቸውን ሳንማር ነው። ያልተማረ ሰው ቢሳሳት አይወቀስም። በግዕዝ መጻሕፍት ሳይቀር ተዘበራርቀው እናገኛቸዋለን። ሆኖም፥ አንድ ነገር ማድረግ ይቻላል። አንድን ቃል ከነዚህ ባንዱ መጻፍ የጀመረ በዚያው ይጨርሰው። “ሀይለ ስላሴ” “ሐይለ ሥላሴ” “ኀይለ ስለሤ” እያሉ ማፈራረቅ አስፈላጊ አይደለም።
"መልካም" በዓላት።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
145 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 810 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us