እምቧለሌ በእምቧለሌያዊ ንባብ እኔያዊ አተያይ

Wednesday, 24 January 2018 14:12

 

 


በዮሐንስ አለነ፤


አአዩ ጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ክፍል

ያ' ገር ሰው ከጉበኑ ቁመህ እንግድነትህን ስታውጅ ግንባሩን አያስርም አያዋ….. አንቱ….. ቤት የእግዜር አደል ግባ እንጂ ይላል።
ለድካምህ ማራገፊያ አጎንብሶ እግርህን ያጥብሀል። ከወዴት መጥተህ ነው አያ…… ምንደህና… እያለ በደረቁ አያደርቅህም ከማድጋው ድፍድፉ ጠላ ተዘልሎ በዋርማ አለበለዚያም ከቁንድፍቷ አንተው ይቀርብልሀል። ጨዋታን ጨዋታ ነውና የሚያመጣው በፀሐይ ግባት ወጋገን ከአማጋው ፈረሶች ጭራቸውን እያወናወኑ ይግጣሉ። አማጋውን የሚያሳይህ ጉብል ያያ ብሎህ የያዘውን ኮርቻ ፈረሱ ላይ ዘፉ አድርጎ እርካቡን ረግጠህ እንድትወጣ ያረግሀል። ፈረሱን በአማጋው ትጋልባለህ። ያ ባትህ ነውና ከጦር ውሎ እስከ መፈንደቂያ ፈረስ ሁነኛ ነበር በሰርግም በለቅሶም ላይ አጀቡ ደማቅ ነው ….. ካባ ለባሽ ምንድነው ሞትና ሰርግ አንድ ነው እንዲል ተረቱ። ሰግረህ ከማደሪያህ ባድማ ደርስሀል። ሌላ ጥሪ አገሬው ስም ሲያወጣ ትንቢትና ፍቅር አለውና የሺፋና፣ የሺመቤት፣ የሺ፣ የሺዋስ፣ የሺወርቅ የሺሐረግ ይልሀል ባለስሞችም ከስማቸው አይሸሹም። የሺሐሳብ እንዲህ ብሎ ጠርቶሀል፤ ፈረሱ ሳር እየጋጠ ነው። ኮርቻውም ከቤቴ እልፍኝ ዝለቅና ውሰድ…. ትህትና አለውና ጉሮሮውን ሞርዶ ቤት ለእንቦሳ ምኞቱን አጉርሶ እንቦሳ እሰር ምላሹን ተቀብሎ መደላድል ዳውላውንና ኮርቻውን ያቀብልሀል። ኮርቻ ና ጋሻው ይኸው ይልሃል። የመጋለብ ፋንታውን ለአንተ ሰጥቶ ዟሪዎችን ከዛሬ በር ሳይወጡ ድረስ ብሎሀል። የሺሃሳብ አበራ እኒህ ስምንት ነዲድ ፊደላት ከስያሜ ባለፈ ትርጓሜ አላቸው የጫቅማ ድምር ስደራ ጨለማን ያሸንፋል። የሺሀሳብ ግን እኛ ውስጥ ያለን ጨለምተኛ አስተሳሰብ በጦሩ ይወጋል ሞገዱም ሃያል ነው። ድምጽ ሆኖ ሲወጣ ግንቡን ይንዳል።


በማህበራዊ ሚዲያ አውደ ታሪክን፣ አውደ እለትን አውደ ወቅት የሆኑ ጉዳዮችን አንጉቶ ሲያጎርስ አውቀዋለሁ። ጋዜጠኛ የሺሐሳብ አሁን ይዞ የመጣው እንጎቻ ብቻ አይደለም። ቃተኛ ሸልሞታል። ተሳምንት በፊት ፌስ ቡክ ላይ ተወዝፌ መጣሁ፣ መጣሁ ሲል አይቼ ጓጉቻለሁ። ምን ይዞ ይሆን ሚለውን ሐሳብ ሳጠነጥን መፃፉ ሸዋ ገብቷል እምቧለሌ። መፃፉ ከዛ ሰፈር ሰው ደረሰኝ አሁን በተዘዋዋሪ ዘልቄ አግኝቼዋለሁ አግኝቶኛል። ውሀ ሲጣድ መፍላት ሲዳዳው ሲ ሲ ሲ ጥ ጥ ጥ ሽ ሽ……..እያለ ዜመኛ ይሆናል የፍለተ ዜማው አዝማቾች ግን ከተጣደው ውሀ ላይ ያሉ ነጠብጣቦች (ትኳቱኬ) ናቸው። አለበለዚያ ግን ነጠብጣቦች ከተነሱ ወይም በዘይት ከተሸፈኑ ውሃው አይፈላም፤ ዶ/ር ይሁኔ እንዲል። ማህበረሰቡ ስጋን ሲበርደው ሳት ዳር ሆኖ ሁናቴውን ከአኗኗር እያስተባበረ ያወጋል በእሳት ሙቀት ብርዱን ይከላል። ህብረተሰብ በቆፈን ሲወድቅ በላይ ሆነው የሚያሞቁት የእንፋሎት ድምሮች ከመንደር ከቤት ልጃቸው ተነስተው ወደ እስር ተወርውረዋል ብቻ ብሎ ከደረቅ እውነት ጋር አያፋጥጥህም እንዲህ ሀሳቡን ያንጓልለዋል…... ብርዱን የሚያሞቅበት እና ፅልመቱን የሚገፍበት ፀዳል አጥቷል (ሌላ ሌላውም ፀዳለ… ብሎ እንዳይል ተደርጓል ፀዳለ ማርያም እንዲል) ማገዶውን ቢቆሰቁሰውም አቀጣጣዮች ቀድመው ስለተወረወሩ ይጨሳል እንጂ አይነድም፣ ውሀውም ይሞቃል እንጂ አይፈላም ምግቡ ይጣዳል እንጂ አይበስልም አብሳዮች የሉምና እርሾዎችም ከሊጡ ታጥበዋል። ከእድፋችን ከ3 ሺህ ዘመን በላይ ብንኖርበትም የዕድገት ብስለከታችን ገና ቂጣ ነው።


በእነዚህ መስመሮች ደራሲው በሰላ ብእሩ በእድልህ ብዙ አመታትን መኖርህን ይነግርህና ገና ጭጭጭ የሚል ቂጣ እንደሆንክ ነግሮህ ያርፋል። ምንም ወፍራም ግንድ ተፈልጦ ማገዶ ብትቆሰቁስ ስንጥር ፍልጥላጭ ስለሌለው አይነድም። ከህብረተሰቡ አብራክ የወጡ አሳቢያን በወህኒ ናቸውና ስጋህ ቢጎለምስ አዕምሮህ ቂጣ ነው።


ዝናብ ሲያከረስሰው ገሳ (ዣንጥላ ) አያረግም በቁንጣን እንጂ በዕውቀት መቃተት አይቸግርም ቂጣነት በታዛው አሳርፎ ሲነግርህ ይቆይና የዚህን መፅሐፍ ሐውልትነት ለእርሾዎች ይቆም ዘንድ በአደባባይ ፈቅደናል ብሎ ይኩራራል። በልኮራ ኮራ ዘና ዘና ዜማን ሰምቶ ያደገ የባላገር ልጅ ይመስላል። የእንጀራውን እርሾ ልንገርህማ….. ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ከነጻነት ማግስት የተገኙ የቀዶ ጥገና ህክምና ፕሮፌሰር ናቸው። አንድ ለና'ቱ የሆነውን ጥቁር አንበሳ ሆስፒታልን በማቋቋምና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ትምህርትን ያደራጁ ሀኪም ነበሩ። የኤርትራን መገንጠል የተቃወሙ አንድነትን የሰበኩ ከሀሳብ ይልቅ ነገድ ላይ ትኩረት ሲደረግ ጋዋናቸውን ጥለው ሞግተዋል ባለብእሩ ጀግና እያደር ዘመንን እየቀደመ ይፈጠራል። ልክነቱም በነገ ትከሻ ላይ ይሰፋል። ለኖረበት ዘመን ማህበረሰብ ምልክት ይሆናል በማለት ለእሳቸው ብኩርናውን እንዲታወሱበት ሐውልት አቁሞላቸዋል።


ሌላ እርሾ ጸሐይ ወጣች ብሎ ከአሜሪካ ወደ እናት ሀገሩ ከ1983 በኋላ ለሌላው ለመኖር ተመለሰ፤ በህትመት ጋዜጠኝነት 18 ዓመት ሰርቷል። ሰባት ጊዜ ለእስር ተዳርጓል ከባለቤቱ ሰርካለም ፋሲል ጋር በእስር እያሉ የመጀመሪያ ልጃቸውን አግኝተዋል፤ ናፍቆት ይባላል። መስከረም 3 ቀን 2004 ዓ.ም በሽብር ተጠርጥሮ ከተያዘ በኋላ 18 ዓመት ተፈርዶበት በቃሊቲ ማጎሪያ ይገኛል። ጋዜጠኛ የሺሐሳብ የመንፈስ ልጅ ነውና ይህን አንዲያ ልጁን አበርክቶለታል የተገባም አደል ….. እንዴታ!!


ያለእርሾዎች ሊጦች ሁሉ እንጀራ አይሆኑም-
ደራሲው የ'ራሱን እርሾዎች እንዲህ ቀምሯል።


በመታወሻ ገፁ ግርጌ ….. ለነጠብጣቦች በሙሉ ተበረከተ ይላል። ከታሪኩ ቁድሻ በተጨማሪ ለተደራሲያን አክብሮቱን ያሳቅፋል። የእንቧለሌ ወጋግራዎች እኒህ ናቸው።
ተማር ልጄ፣ አብዮተኛ እግሮች ካንጋሮው፣ የጥያቄው ጥያቄ፣ ስምና ፍቅር አላዛሩ ንጉስ፣ ጭብጨባ የወሲብ ሱናሜ፣ ፍካሬ ዳያስፖራ የመሐል መንገደኞች ለእኒህ አርዕስት ሐሳቡን ቃኝቶ ተጠብቧል። ይሰነስናል እንደ ንጥር ቅቤ በሚጣፍጠው ወጉ አለሳልሶ ያስገባሀል ፖለቲካን ይመነጥራል ትምህርት ላይ ያሽሟጥጣል በገፀባህሪያት ያስተውስሀል ሀሳቡን ያስነግራል፣ በአሽሙር ይወጋጋሀል በሕፀፆች እንድትቆዝም በመሷለኪያዎች ደግሞ ፈገግ እንድትል ያደርጋል .. መፈልቀቂያ… በወፉ በረር የዳሰሳ ጨዋታ እንጀምር።


ተማር ልጄ በሚለው በመጀመሪያ አርዕስቱ ብላቴናው ታላቁ ፈላስፋ ሶቅራጥስ የዓለም ትልቁ ችግር ዓላዋቂነት ነው መድሀኒቱ ደግሞ ዕውቀት ነው ዕውቀት ደሞ አለማወቅን ከማወቅ ይጀምራል በማለት ተረኩን አይወጥነውም ይልቅስ በአሽሙር ይኮረኩምሀል ግድ የለም ባትቀጠር እንኳን ትምህርት ብዙ ጥቅም አለው ይላል (በግዴለሽነት እጁን የሚያወራጭ መሰለኝ ባየሁት) ይህን የአሽሙር ቡጢ ሲያቀምስህ ጉተንበርግ የህትመት መሳሪያን ከመፍጠሩ በፊት ብራና እና ቀለም ፈጥረው ዘመን በአቡሻኸር ቀምረው የኖሩትን ታሪክ…. እንደምድጃ ዳር ተረት አድርገህ ትስለዋለህ አልያም ደብተራ ታሪክ ነው ብለኅ ባዶነትህን ለመሸፈን በእስራኤል ታሪክ እየተፅናናህ ራስህን ታሞቃለህ እቅጩን ይነግርሀል። ሌላ ምፀት መማር ወደ ውስጥህ እንዳትብከነከን ኬሻ ሙሉ ሰላም ሰጥቶሀል እናማ ዩኒቨርሲቲ የውጭ ቲዎሪ መማርህን ወደደው ተጨዋች ሳትሆን በተመልካችነት እየተፅናናህ እንድትኖር ያደርግሀል የምታስበው በአማርኛ የምትማረው ደሞ በመጤ ቋንቋ ነው ታዲያ እንዴት ብሎ ተመራማሪ ትሆናለህ እርፉ ይዞ ወደኋላ የሆነውን ጉዳያችንን እንዲህ አለስልሶ ይደቃሀል ተማር ልጄ!! በቆሎ ትምህርት ተሜው ተኮልኩሎ ጨወታ ያነሳል ከመጠምጠም መማር ይቅደም ትምህርት ሲባል ወደ ሲሚዛ መሀራ ገብቶ ዋንጫ መዘዛ ትምህርትን ማልከስከስ መሃራ ሲሆን መንቶስቶስ ወዘተ ፈርጀ ብዙ ጭውቶች አሉ ከመጠምጠም መማር ይቅደም ሚለውን ይወስድና ሙጋቤ ተናገረው ይልሀል።


በቅንፍ ውስጥ ነገርየውስ የእኛ ነው የውጭ ሰው ሲባል ታምነኛለህ ብዬ ነው ብሎ ይለካሀል። አባይ ከስከላ እንደሚነሳ ጀምስ ብሩስ ከስኮትላንድ መጥቶ መስክሯል ዳሩ ግን የሰከላ ገበሬ ያውቀዋል ልጆች ተንቦራጭቀውበታል ድፋቂያ ተጫውተውበታል ከብቶችን ሲያግዱ ተጎንብሰው ጥማቸውን ቆርጠውበታል በመቃው ቀለም እንዲህ ይላል እኛ ማንኪያ እና ወጥ እንሰራለን ፈረንጅ በማንኪያችን ወጥ ቀማሻችን ይሆናል።


ስሞች በየዘመናቱ ይቀያየራሉ ባለንበት ዘመን አለባበስህ ስምህ የቆዳ ቀለምህ ዘርህ ወዘተ… ግምት ውስጥ ይገባል ለመቀጠር ተፈልገህ ደራሲው ስምህን እንዲህ ብትቀይር የሚል ቅያስ ያሳይሀል ሕዳሴ ልማቱ (ፀረ)፣ ተሐድሶ፣ 1ለ5 ….. የሺሐሳብ ምንኛ ዜደኛ ነው ካልሆነማ ቅርጫት እንደተደፋባቸው ጫጩት ነው ምትሆነው።


ጋዜጠኛ ጌጡ በአንድ ወቅት በሰራው የአባይስሞች በተሰኘው ዶክመንተሪ ሁነኛ የልማት ሰው አስተዋውቆናል (የአዲሲቷ ኢትዮጵያ አካል ይሆን እንዴ) አባት ልጆቻቸውን እንዲህ ሰይመዋል ተፈራ አባይ፣ኢትዮጵያ አባይ የግብፅ ሕይወት አባይ፣ ይገደብ አባይ ፣….. ግድቡ ከተጀመረ በኋላ የወለዷ/ዱትን ልጅ ደግሞ ደሞዜ አባይ ወይም እይየው አባይ ብለው የሰየሙ ይመስለኛል ለጊዜው መረጃ የለኝም ተማር ልጄ በሚለው አርዕስት ውረፋ ከምፀት ተጋብተው ተረኩን ወዛም እና ፈርጣማ አድርገውታል።


‹‹መማር ባታገኝም ግን በተስፋ ብቻ እያኖረ ለአካልህ (ስጋ) እንድትገዛ ያደርጋል››
ብዕረኛው መማር ሞትን አያስደፍርህም እንኳን ሞትን ደሞዝህ እንዳይቆረጥ ያባባሀል ለውጥ ከሌላ ስው እንድትጠብቅ ቀዝቃዛ ስሜት ይሸልምሀል አይ መማር ደጉ!! ለማንኛውም ተማር ልጄ!!
ሌላው ወጋግራ አብዮተኛ እግሮች ይሰኛል። በገፅ ብዛትም በሐሳብም ጠሊቅ ነው። ታሪክ፣ ሁነት፣ እውነት ርዕዮት ተቀነጣጥበው የቀረቡበት ነው የደራሲው አተያይንም ልብ ይሏል። በ2008 ዓ.ም የነበረውን የሕዝብ ደምፍላት የባህርዳርንና የጎንደርን ትላንት ዛሬ ታሪክ አድርጎ ጠብሰቅ ካሉ ትችቶቹ ጋር ውሽንፍሩን አንባቢው ሚዛናዊ እንዲሆን በሚያደርጉ የሀሳብ መስመሮች በመዝጊያ ዓ.ነገሮች ወዳንተ ይዶላቸዋል።


የብሔር ፌደራሊዝም በአግባቡ ካተያዘና አንዴ ከሚዛን ከወጣ ለመመለስ ይከብድና ነገዶች ወደ ሀገርነት ሊፈለፈሉ ይችላሉ በቆሎው ከተፈለፈለ የሚቀረው ቆረቆንዳ ነው ሁሉም እኔ ማለት ከጀመረ ራሱን ይበላል።


ዳሩ የበስተቀሮችን በር መዝጋት የለብንም ሰሚ አድማጭ ይኑር በማለት በአፅንኦት ይናገራል።
በአውስትራሊያ ብርቅዬ እንስሳ ግብር በመነሳት በተሰየመው ካንጋሮው በሀሳብ እንሳፈር በዚህ እርስ የሚፍለቀለቁ ሀሳቦች ኮናኔ ፍትህ ናቸው ማለት ይቻላል በብዕሩ ይጎነትላል .ካንጋሮ ብዙ ትዘላለች ፍርድ ቤቶችም እውነትን ይዘላሉ ካንጋሮ ልጇን በጉያዋ ባለ ኪስ ታሳድጋለች ዳኞችም በጉያቸው ጉቦ ካልገባላቸው እውነትን አቅፈው አያሳድጉም. እኒህ ፍርድ ቤቶች ተገዝነታችው እና አለኝታነታቸው ለእውነት እንዳልሆነ ታሪክን ነቃቅሶ ያስረዳሀል።


የጥያቄው ጥያቄ በዚህ ፈርጅ እውነት ታሪክ ትምህርት በትንታግ ብዕሩ ይመትራቸዋል።
ኢኮነሚክስ የሚባል ጅምላ ቸርቻሪ የትምህርት ዘርፍ ሲበዛ አድሎኛ ነው ብዙሀን በጥቂቶች መጋረጃ ተሸጉጠው ጠግበዋል ብሎ የሚናገር የእንጀራ እናት የሆነ ትምህርት ነው።


እውነት ወይስ ስምምነት ቀመር ወይስ ከርስ ደስታና ለውጥ ወይስ ቁጥር የትኛው ነው ትክክል በማለት ይጠይቃል
(በ11 አሀዝ እያደግን እንዴት ይህን አታውቁትም)
ደራሲው እንዲህ ያሰጋል የጫት ምርትና ተጠቃሚዎች መስፋፋትበዚህ ከቀጠለ ኢትዮጵያ እንደ የመን እና እንደ ሶማሊያ መሆኗ አይቀርም።


ስምና ፍቅር የደረሲው ምናብ ምን ያህል ተምዘግዛጊ እንደሆነ ለመገመት በዚህ ርዕስ የቀረቡት ሀሳቦች መጓዣ ይመስሉኛል። በመሰረት ተለክፎ መሰረተ ድንጋይ ሲባል አቲቱ ይሄዳል ለምለምን አፍቅሮ በለምለሙ መስከረም …. ሲባል ሲሰማ ያስታውሳታል አብዮትን ደሞ ይከጅላል አብዮታዊ ዴሞክራሲ በሚሉ እና ሌሎች ተያያዥ ቃላቶች ተጠፍንጎ አቅሉን ይስታል (አርፎ አይቀመጥም)… ከፎተሊካው እያወዳጀ እንደ መስቀል በአል ጉብል እንጎሮጎባሽ ብሎ በሀሳቦቹ ተረኩሶህ ይፈተለካል ትከተልውምአለህ ተረኩ እንዲያ ነው።


አልአዛሩ ንጉስ ወጋግራ ታሪክን እና ሁናቴን ቃኝቶበታል የአስተሳሰብ ቁስል እዥ ሆኖበት ሲነዘንዘው የከተበው ይመስላል አብዝቶ ይቆረቆራል ቆም ብለን እንድናስብ ይጠቁማል በወሬ በወሬ የምናነሳቸውን ጉዳዮች ጥበብ ዘራርቶ እንዲፈኩ አድረርጓቸዋል። አስተሳሰብን ማከም አካል ከማከም ይበልጣል። በቁዋንቁዋ አለላ ባጌጠው ወጉ እምቧለሌ ተጫውቷል በማህበረሰቡ ኑረት ያሉ እክሎችን ያነሳሳል ቆይ አቴንዳንስ ይይዛል። ምሳ ተበላ ተብሎ አይወጣም ገና መግባባት ላይ ሳንደርስ መላቀቅ የለም። መቼም አንላቀቅም፤ ፈሪ በአንደበቱ ባይናገር በእጁ እያጨበጨበ ዘመኑን ይገፋል። አንተ ጋር ያለን እውነት ያስቆነጥርሀል (ተቀበል እንግዲህ ያለው ማን ነበር) የአገልግሎት ዘርፉ ተለጣፊነት እና የሪፖርት ጥገኝነቱን ፍንትው አድርጎ ሰንዶታል የመንግስት ሰራተኛው የሃገሪቱ የተማረ እና በስራው በአስትሳስቡ ሃገራችንን የሚያስፍነጥር የህብረተሰብ ክፍል ነው ነፃነቱን ከማክበር ይልቅ ገሸሽ መደረጉ ደግም አይደል በማለት ጭብጨባ በሚለው እርስ ስር ቀምሞታል።


በወሲብ ሱናሜ ማዕቀፍ ውስጥ ደራሲው ስጋቱን መሸፈን አልቻለም። የሀሳቡን ብናኝ ከሀይማኖት አስተሳሰብ አይቀዳም በአንድ ሌሊት ብቻ በዓለም ከ 130 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በወሲብ ተጣምደው ያድራሉ። ይህ ቅዠት አይደለም እውነት ነው የወሲብ ማእበል የሮም ስልጣኔን አንሸራቶ ጥሏል።


እንደ ተሞክሮ ደቡብ አፍሪካ፣ ግሪክ፣ ብራዚል፣ ታይላንድ ሀገራትን ጉዳይ ግብአት በማድረግ ያነፅራል። ግብረ ገብነትን የሚያስጠብቅ የሕግ ማእቀፉ ካልወጣ አደጋው የከፋ እንደሆነ ያረዳሀል።
ኢትዮጵያ ከ2 ሚሊዮን በላይ ዲያስፖራ ልጆች አሏት ብዙዎች ታዲያ ስለተቃወሙ ብቻ ወደ እናታቸው ቤት ገብተው የአያት ምርቃትን፣ የአባት ዳረጎትን እንዳይቀምሱ በር ተዘግቷል። በፍካሬ ዳያስፖራ ትልሙ ሰቆቃውን ፍላጎቱን ምኞቱን ከታሪክ ጋር በማጣቀስ ከታትቦታል።


የመፅሀፉ የመጨረሻ ክፍል የመሐል መንገደኞች ይሰኛል። (ለመሐል መንገደኞች ይሆን) በዚህ ወጉ ያፌዛል ከእወነት ጋር ያጋትርሀል ታሪክ ማለት የመኪና ስፖኪ ነው የኋላውን ማየት ወደፊት ለማደርገው ጉዞ ይጠቅመኛል። (በግርድፉ እና ፉራንክ እንዳላችው) ደራሲው በወጎቹ ቅንጣት ታሪክን እያስኮረሰመ ከአሁን ጋር አዋህዶ በተረኩ ውስጥ አብሮ ያጉዝሀል።


በእኛም የመሐል መንገዱ በትራፊክ ዝግ ከሆነ ቆይቷል የጃንሆይ ስርዓት እና ደርግን በአማካኝ መዝኖ ሁለቱም መጥፎም ክፉም ሰርተዋል ብሎ የሚቆም የመሐል መንገደኛ የለም።
አቤት አከሻሸን ማለት የሚያስችል ወጉ ጥዑም ነው። የሰፊው ሕዝብ አገልጋይ የሆኑ ተቋማት ተገዢነታቸው በየዘመኑ ለነበሩት ስርኣቶች እንደሆነ አስቀድሞ ይናገራል። ኢትፈዮጵያ እናት ዛፉ ናት። ከዛፉ ቅርንጫፉ አንዱን ወደ መሬት ለስ ከድርገው እንደትንጨዋለል ያደርጉሃል። በጎሳ በቀለም በሃይማኖት በአስተሳሰብ … ወዘተ የሚዛናዊነት በር እንዲዘጋ ያደረገው የመንግስት ፕሮፖጋንዳ እንደሆነ የወቅቱን ሁኔታ ከኋላ ታሪክ ጋር በማኳኳል ለዛ ባለው ቋንቋ ያጫውትሃል።


“ታሪካችን የፖለቲካ ማሟያ መሆኑ የደረቅ ፕሮፓጋንዳ ተጠቂ አድርጐታል። ረጅም ቁመናው ላይ እከክ ሆኖ ፊቱን አብልዞታል። የትውልዱ ጭንቅላትም ፕሮፖጋንዳውን ተመግቦ ስላደገ ወደመሃሉ ጎዳና ገብቶ ለመጫወት ወኔው ዝሎበታል” በማለት ሰብዞታል። በ208 ገፆች የተቀነበበው መፅሃፋ በአስሩ አርዕስት የታዘሉት ሀሳቦች ያባብላሉ፤ ያባባሉ ፀሃፊው የራሱን ሃሳብ የመጫን አዝማሚያው ስስ ሆኖ እምቧለሌ እንድትሾር ያደርጋል። እምቧለሌ ጉልህ ጥቅም አለው። ልጅ ሆነን የአምሮሯችንን የመንቦዥቦዥ ፍጥነት ለክተንበታል። አንደኛው ልጅ ትንሽ እንደሾረ በአፋጢሙ ሲተከል ወይ በጀርባው ሲንጋለል ተሳስቀን ቦርቀንበታል። እንዝርት እንቧለሌ ካልሾረች ክር እና ማግ አይኖርም ጋቢ እና ነጠላም እንዲሁ አሁን ግን እንደ ልጅነታችን እጆቻችንን ወደ ጐን ዘርግተን አንሾርም የሚጠበቅብን በሃሳብ እምቧለሌ ነፋሳቱን(ነፋሱን) መቅዘፍ መሰንጠቅ ነው። ሐሳብ ሃገር ድንበር ባይኖረውም ወደ አንድ አቅጣጫ የሔደ ይመስላል ደራሲው ለምን ቸኮልበት ባይነኝ ባይቸኩል ኖሮ ድንቅ ታሪክ ቀመስ ወግ እናገኝ ነበር ጋዜጠኛ መሆኑ አተራረኩ የየ ነገራቱን መነሾ ከመረጃ ጋር እንዲያጐዳኘው ረድቶታል።


የህትመቱ አና የወረቀት ጥራቱ ጥያቄ ውስጥ ይከታል። በገበያ የቀረበበት ዋጋም ከጥራቱ ጋር አይጣጣምም። ያም ሆኖ ግን የብላቴናው እምቧለሌ፤ በእምቧለሌ ውስጥም ተሁኖ መነበብ አለባት ባይ ነኝ አካፋይ ናትና። ይህን ድፍረቴን እና ስህተቴን ግን በበጐ እንድታዩት እገልፃለሁ።
ለዘዘወ ዳፉ

 

ይምረጡ
(14 ሰዎች መርጠዋል)
432 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 877 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us