በብላቴና እንቅፋት ተጀምሮ ግዙፍ እንቅፋቶች ያልበገሩት በጎነት

Wednesday, 24 January 2018 14:58

 

በይርጋ አበበ

 

ጊዜው እንደ አውሮፓዊያኑ የዘመን ስሌት 1992 ሲሆን ቦታው ደግሞ ሆሳዕና ከተማ ነው። የስምንት ዓመት ብላቴና ወደ ትምህርት ቤት ስትጓዝ አንድ ነገር ትመለከታለች። በእድሜ እኩያዋ የሚሆን ተባዕት የአንደኛ ደረጃ ተማሪ ወደ ቀለም ቀንዱ ተቋም ሲያቀና እንቅፋት የእግሩን አውራ እጣት ያነግለዋል። እንቅፋቱ የበረታ ኖሮ የብላቴናው ጥፍር ከእጣቱ ተነቅሎ ሲወድቅ ቆማ የምትመለከተው ህጻን ልጅ ቀኑን ሙሉ ሃሳቧ በዚያ ክስተት ላይ ሆነ። የቀለም ትምህርቷን ትታም የህይወት ትምህርት ስትማር ውላ ተመለሰች። ‹‹ኢትዮጵያዊያን ህጻናት ለምን ድሃ ይሆናሉ? ለምን አይኖራቸውም?›› እና የመሳሰሉትን መልስ አልባ ጥያቄዎች ስታወጣና ስታወርድ ውላ ወደ ቤቷ ተመለሰች። እናም እንዲህ ስትል በልቧ ተመኘች ‹‹አንድ ከረጢት ሙሉ ብር ባገኝ ለልጆች ጫማ እገዛላቸዋለሁ፤ እንቅፋት ሲመታቸውም ጉዳት እንዳይደርስባቸው ይመክትላቸዋል›› ስትል አሰበች።


የልጅነት ሚጢጢ ልብ ትልቅ ምኞት እንጂ ትልቅ ብር ያገኛል ተብሎ አይጠበቅምና ብሩን ሳታገኝ ዓመታትን አሳለፈች። ከምትማርበት የካቶሊክ ሚሽን ትምህርት ቤት ወጥታም ወደ ጣሊያን አገር ሄደች። ከ17 ዓመታት የባዕድ አገር ቆይታ በኋላ ወደ አገሯ ተመልሳ በልጅነት ልቧ የተመኘችውን የበጎ አድራጎት ስራ ለመስራት አሰበች። (ከረጢት ሙሉ ብር አግኝታ ይሆን? ያሰኛል) መልካምነትን ለመስራት ስትንቀሳቀስም ጫማ የሌላቸውን ብላቴናዎች ፍለጋ ጀመረች። መቼም ኢትዮጵያ ውስጥ የጫማ መግዣ እንጂ ጫማ የማያደርግ ብላቴና ማግኘት ቀላል ስለሆነ ብዙም ሳትደክም በአዲስ አበባ ውስጥ ልዩ ስሙ ሣሪስ ተብሎ ከሚጠራው ሰፈር 40 ልጆች በአዳም ጫማ እንደሚገዙ ከቀበሌው ጽ/ቤት ተነገራት። ከ40ዎቹ ልጆች መካከልም 16 ልጆችን ብቻ በመያዝ የመልካምነት ሥራዋን ጀመረች ‹‹ጆይፉል ላይፍ ፋውንዴሽን››ን ጀመረች። ከ8 ዓመት በኋላ በይፋ ይህን ያደረገችው የያኔዋ ብላቴና የአሁኗ ወጣት ሰብለወንጌል (ሰብሪና) ኦርጂኖ ትባላለች። ስለ ድርጅቱ እንቅስቃሴ እና የስራ ሂደት የሚዳስሰውን ልዩ ዘገባ ከዚህ በታች አቅርበነዋል።

 

የደስተኛ ህይወት ፋውንዴሽን ምስረታ


ጆይ ፉል ላይፍ ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ የበጎ አድራትና ማህበራት ማደራጃ ኤጄንሲ ‹‹የኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅት ኤጄንሲ ቁጥር 2627›› ስም የተመዘገበ ሲሆን አብዛኛው የገቢ ምንጩ የሚገኘው ከድርጅቱ መስራች ሰብለወንጌል ኦርጂኖ ኪስ ነው። እ.ኤ.አ በ2004 ለእግራቸው ጫማ የሌላቸውና የምግብ እርዳታ የሚፈልጉ 16 ህጻናትን በመርዳት የጀመረው ጆይፉል ፋውንዴሽን በአሁኑ ወቅት 103 ህጻናትን ይደግፋል። ህጻናቱ ከፋውንዴሽኑ ድጋፉን የሚያገኙት በአንድ ቅጥር ግቢ ውስጥ ተሰብስበው ሳይሆን በወላጆቻቸው እቅፍ ውስጥ ሲሆን ሙሉ ትጥቅ እና የሰለጠነ አሰልጣኝ ያለው የእግር ኳስ ክለብም አቋቁሟል።


የጆይፉል ላይፍ ፋውንዴሽን መስራች ሰብለወንጌል ኦርጂኖ በአሁኑ ሰዓት ከ100 በላይ የአገሯን ህጻናት መታደግ የሚችል ፕሮጅክት ከመክፈቷ በፊት አጀማመሯ በ30 ብር ጫማ ነበር። ‹‹ምኞቴም ሆነ የመኖሬ ትርጉም ድህነትን በቻልኩት መጠን ለማጥፋት መስራት ነው። ለዚህም የራሴ የምለው ኑሮ እና ሕይወት ሳይኖረኝ ለአገሬ ችግረኛ ህጻናት ህይወት መስተካከል ስል ዕድሜዬን ሙሉ ኖሬያለሁ፣ እየኖርኩም ነው እኖራለሁም›› ስትል ትናገራለች።


ወደ ትምህርት ቤት ስትሄድ መንገድ ላይ አንድ ብላቴና የአውራ እጣቱ ጥፍር በእንቅፋት ምክንያት ተመንግሎ ሲወድቅ የተመለከተችው ሰብለወንጌል፤ የግለኝነት አስተሳሰብም ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ከውስጧ ተመንግሎ እንደወደቀ ትገልጻለች። ለዚህ እቅዷ መሳካት ስትልም ከቤተሰብ የሚሰጣትን ስብርባሪ ሳንቲም አጠራቅማ 30 ብር ሲደርስላት አንድ ጫማ ገዝታ ለአንዲት እህቷ ማበርከት ጀመረች። በዚህ ስራዋ ግን መግፋት እንደማትችል ከቤተሰብ የገጠማት ፈተና ቀላል አልነበረም። ከቤተሰብ ተቃውሞ የገጠማት ቤተሰቦቿ ድሃን መርዳት ስለሚጠሉ ሳይሆን ልጃቸው በአግባቡ ተምራ እድገቷን ጠብቃ ወደ ፈለገችው የህይወት መንገድ እንድትሄድ በማሰብ ነው። የያኔዋ ብላቴና ግን ይህ የቤተሰቦቿ እቅድ ሊገባት ስላልቻለ ከቤት ተጣልታ ወጥታ ከካቶሊክ በጎ ፈቃደኛ ሴቶች ጋር አብራ መኖር ጀመረች። ለአራት ዓመታት አካባቢም የካቶሊክ ሴቶችን ህይወት (ገዳም ሊባል በሚችል መንገድ ለግል ህይወት መኖር ትተው ለበጎነት መሰጠት ላይ ያተኮሩ ናቸው) መምራት ቻለች። ይህ ድርጊቷ ደግሞ ከቤተሰቦቿ ከባድ ተቃውሞ አስነስቶባት በተለይ አባቷ ፊትሽን እንዳላይሽ እንዳሏት ትናገራለች።


በዚህ መሃል ግን አንድ ዕድል መጣላት። ወደ ጣሊያን አገር ሄዳ የምትማርበትና የምትሰራበት ዕድል ስታገኝ እድሉን ተጠቅማ ጣሊያን ገባች። ‹‹ጣሊያን ገብቼ ለሶስት ዓመታት አንድ ጫማ እና አንድ ልብስ ብቻ እየለበስኩ ገንዘብ አጠራቀምኩ። ያጠራቀምኩትን ገንዘብ ይዤ ወደ አገሬ ገባሁና ሣሪስ አካባቢ አንድ ቤት ገዛሁ። ከሣሪስ አካባቢ አንድ ቀበሌ ሄጄ የችግረኛ ቤተሰብ ልጆችን እንዲሰጠኝ ስጠይቀው 40 ልጆችን ሰጠኝ። ነገር ግን በወቅቱ የነበረኝ አቅም 10 ልጆችን ብቻ መርዳት የሚያስችል ቢሆንም በወቅቱ ከቀበሌው ከተሰጡኝ ልጆች መካከል የባሰ ችግር የነበረባቸውን 16 ልጆች መርጬ መርዳት ጀመርኩ። ከአንድ ዓመት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ስመለስ የልጆቹ ህይወት ተስተካክሎ ስመለከት ድጋፍ ማድረጉን ጨመርኩ። ለዚህም እንደገና ሌላ ቤት ገዛሁና አንዱን ቤት ለጽ/ቤት እንዲሆን ሳደርግ የመጀመሪያውን ቤት ደግሞ ተከራይቶ የኪራዩ ገቢ ለድጋፍ እንዲሆን አደርኩ›› ስትል የፋውንዴሽኑን ጅማሬ ትናገራለች።

ደስተኛ ህይወት ሲባል?


‹‹የሰውን ልጅ ኑሮ ደስተኛ እንዳይሆን ከሚደርጉት በርካታ ምክንያቶች መካከል አንዱ ድህነት ነው። ድህነት ደግሞ ሌሎች ተደራራቢ እና ዘርፈ ብዙ ችግሮችን በሰው ልጆች ላይ ጥሎ የሚያልፍ የሰው ልጆች ፈታኝ የህይወት ክፍል ነው›› ብሎ ለመደምደም ሰፊ ጥናት የሚጠይቅ ቢሆንም የድህነት በጎ ገጽታ ይኖራል ብሎ መናገር ግን ይከብዳል። በድህነት አስከፊነት ዙሪያ የአገራችን አዝማሪዎች ደጋግመው አዚመዋል። ለአብነት ያህልም ዘፋኙ ጥላሁን ገሰሰ ‹‹ከሌለህ የለህም›› እንዳለውም ሆነ ሌላው ዘፋኝ ኤፍሬም ታምሩ ‹‹ኪስህ ነው የቅርብ ወዳጅህ›› እንዳለው ማለት ነው።


እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ድሃ አገራት ውስጥ የሚኖሩ ድሃ ዜጎች ደግሞ የችግራቸው ጥልቀት መጠን የለውም። ለዚህም ሳይሆን አይቀርም በየጎዳናው የወደቁ የአገሪቱን ዜጎች ሰቆቃ የምናየው፤ ወይም ደግሞ ድህነት በፈጠረው ቀውስ የተነሳ ሰቆቃ በርትቶባቸው እጃቸውን ለምጽዋት የሚዘረጉ ዜጎች ቁጥር የበዛው። ለእንጄራ ፍለጋ ውቅያኖስንና ጫካ አቋርጠው ወደ ባዕድ አገር የሚፈልሱ ዜጎች ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት የሚበዛውም በዚህ ምክንያት መሆኑ አያጠያይቅም።


ከዚህ ሁሉ የከፋው ደግሞ የድህነቱ መጠን የበረታባቸው የህጻናት ቁጥር በአገሪቱ በሁሉም አቅጣጫዎች የመኖራቸው ምስጢሩ የድሃ አገር ድሃ ዜጎች መሆናቸው ነው። እነዚህን በችግር የተከበቡ የአገሪቱ ዜጎች ደስተኛ ህይወት እንዲኖራቸው ማድረግ ቀላል ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም። የበጎ አድራጎት መስራቿ ሰብለወንጌል ኦርጂኖ ግን ‹‹እነዚህን ዜጎች ደስተኛ ህይወት እንዲመሩ ማድረግ ቀላል ነው። ለዚህ ደግሞ በመጀመሪያ ከንጹህ ልቦና በመነጨ መንፈስ በጎነትን ማድረግ ከተቻለ የዜጎችን ኑሮ መቀየር ይቻላል፣ ይህ ደግሞ ደስተኛ ይሆናሉ›› በማለት ደስተኛ ሆኖ ሰውን መርዳት ከተቻለ የችግረኛ ቤተሰቦች ህይወት ሊቀረፍ እንደሚችል ትናገራለች።


እንደ ሰብለወንጌል እምነት ችግርን መቅረፍ የሚቻለው ሁሉም የአቅሙን አስተዋጽኦ ሲያደርግ ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ እሷ የግል ህይወቷን ሳይቀር ትታ ሙሉ ዘመኗን ለበጎ አድራጎት ስራ እንዳዋለችው ሁሉ ሌሎችም የአቅማቸውን ማድረግ ከቻሉ በአገራችን ስር የሰደደው ድህነትና የህጻናት ጉስቁልና ሊቀረፍ ይችላል።


በዚህ ላይ አንድ ገጠመኝ ማንሳት ተገቢ ሳይሆን አይቀርም። ከሦስት ዓመታት በላይ አንድ ልብስ እና አንድ ጫማ ብቻ በማድረግ ገንዘብ ስታጠራቅም ቆይታለች። ከሦስት ዓመት በኋላ ልብስ መቀየሯን የተመለከቱ ወዳጆቿ እንደ ዜና ይቀባበሉት ነበር። ስልክ ሲደዋወሉ “ምን አዲስ ነገር አለ?” ሲባባሉ የሁሉም መልስ “ሰብሪና አዲስ ልብስ እና ጫማ ገዛች” ይሉ ነበር። ይህን ሁሉ መስዋዕትነት የከፈለችው ሰዎችን ደስተኛ ለማድረግ ነው። ሰዎች ደግሞ ደስተኛ የሚሆኑት ችግራቸው ሲቀረፍ መሆኑን ቀደም ሲል አይተናል።

ዳግማዊት ማዘር ትሬዛ?


የሰብለወንጌል ኦርጂኖ የደግነት ስራ በአገር ውስጥ የችግረኛ ቤተሰብ ልጆችን በመርዳት ብቻ የተገደበ አይደለም። የበጎነት ተግባሩ ውቅያኖስን ተሻግሮ በጣሊያን አገርም የኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን እና ሶማሊያ ስደተኞችን ጉዳይ በመከታተል ለስደተኞቹ አጋርነቱን አሳይቷል። ይህን በተመለከተ ሰብለወንጌል ስትናገር ‹‹በስደተኞቹ ስም የጣሊያን መንግስት ከአውሮፓ ህብረት ገንዘብ ይቀበላል። ያንን ገንዘብ ተቀብሎ ተገቢውን ድጋፍና አስፈላጊውን እርዳታ እንዲሰጣቸው የማድረጉን ስራ እንሰራለን። ምክንያቱም ብዙ ጊዜ ስደተኞቹ የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ በጊዜውና በተመጣጣኝ መልኩ ስለማይደርሳቸው ተደራራቢ ችግር ያጋጥማቸዋል። ይህን ስመለከት ቆሜ ማየት ስለሌለብኝ በጆይላይፍ ፋውንዴሽን ስም ለስደተኞቹ ድጋፍ እናደርጋለን›› ብላለች።


እ.ኤ.አ በ2012 የተመሰረተው ጆይላይፍ ፋውንዴሽን በቦርድ የሚተዳደር ሲሆን በውስጡም ስድስት የቢሮ ሰራተኞችን የያዘ የበጎ አድራጎት ድርጅት ነው። ይህ የበጎ አድራጎት ድርጅት በጣሊያን ስደተኞችን ሕጋዊ ሰነድ እንዲያገኙ ከመርዳትና በአገር ውስጥም ችግረኛ ህጻናትን ከመደገፍ በዘለለም የተለያዩ ትምህርት ቤቶችን መስራት፣ መጠገን እና ንጹህ የመጠጥ ውሃ እንዲያገኙ መስራት ላይ ያተኮረ ድርጅት ነው። ይህን ሁሉ የምታደርገው ወጣቷ ሰብለወንጌል ኦርጆኖ ስትሆን የድርጅቱን ከ70 በመቶ በላይ የገንዘብ ድጋፍ ከመቀነቷ ፈትታ የምታበረክተውም እሷ ናት። ይህን የተመለከቱት መንፈሳዊ ትምህርት አስተማሪው ዶክተር ዘካሪያስ ዓምደብርሃን ‹‹ኢትዮጵያዊቷ ማዘር ትሬዛ›› ሲሉ ይጠሯታል። እኛም ይህን ሁሉ በጎነት የምታደርገውን ወጣት ኢትዮጵያዊት የበጎነት ስራዋን ስንመለከት በዶክተር ዘካሪያስ ስያሜ መስማማታችን አልቀረም።


ነገር ግን ‹‹ጋን በጠጠር ይደገፋል›› እንዲሉ ይህች እንስት የግል ህይወቷን ሁሉ ትታ እያደረገች ያለውን መልካምነት ዕድሉ እና አቅሙ ያላቸው ሁሉ (መንግስት፣ የዲፕሎማት ተቋማት፣ ግዙፍ በጀት የሚያንቀሳቅሱ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ ታላላቅ የንግድ ድርጅቶች፣ የመገናኛ ብዙሃን እና አቅም ያላቸው ግለሰቦች) ከጎኗ ቢሆኑ የችግራችን መጠን ሊቀንስ እንደሚችል እናምናለን። 

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
196 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 935 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us